ይሖዋ ፈጽሞ አልተወንም
ናሾ ዶሪ እንደተናገረው
እብሪስታን ከግሪክ ብዙም የማትርቅ በደቡባዊ አልባኒያ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ትንሽ ተራራማ መንደር ናት። በ1907 እዚያ ተወለድኩ። አምስት ዓመት ሲሞላኝ በአንድ የግሪክ ትምህርት ቤት ውስጥ መማር ጀመርኩ፤ ይሁን እንጂ የኢጣሊያ ሠራዊት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አልባኒያን ሲወርር ትምህርቴን አቋረጥኩ። ከጦርነቱ በኋላ ትምህርቴን በአልባኒያ ቋንቋ ቀጠልኩ።
ወላጆቼ ለሃይማኖት የነበራቸው ፍላጎት እምብዛም ቢሆንም የአልባኒያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ወጎች ይጠብቁ ነበር። የአባቴ አጎት በእብሪስታን በቅስና ያገለግል ነበር፤ ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እሠራ ስለ ነበር በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚሠራውን ሥራ እኔ ራሴ በዓይኔ ለማየት ቻልኩ። ሃይማኖታዊ ሥርዓቶቹ በጣም ከንቱ እንደ ሆኑ ተሰማኝ። ግብዝነታቸው ሕሊናዬን ይከነክነው ነበር።
በአካባቢው ልማድ መሠረት ወላጆቼ አንዲት ወጣት እንዳገባ መረጡልኝ። አርጅሮ በአቅራቢያችን በሚገኝ ግራቦቫ በሚባል መንደር ውስጥ ትኖር የነበረች ስትሆን ከእኔ ጋር የተጋባነው በ18 ዓመቷ በ1928 ነበር።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቅ
በዚያ ወቅት ከዩናይትድ ስቴትስ ሊጠይቀን ለመጣው ለአጎቴ ልጅ ስለ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን ያለኝን ቅሬታ ገለጽኩለት። “በአሜሪካ ውስጥ እኔ በምኖርበት አካባቢ ያሉ ቤተ ክርስቲያን የሌላቸው ነገር ግን አንድ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ ሰዎች አሉ” ሲል አጫወተኝ። ቤተ ክርስቲያን ሳይኖር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚለው ሐሳብ ማረከኝ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እንዲልክልኝ ጠየቅሁት።
ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ከሚልዎኪ ዊስከንሲን አንድ በወረቀት የተጠቀለለ ነገር እስኪደርሰኝ ድረስ ያደረግነውን ውይይት ፈጽሞ ዘንግቼው ነበር። በውስጡ የአምላክ በገና የተባለው መጽሐፍ በአልባኒያ ቋንቋና የግሪክኛ መጠበቂያ ግንብ ነበረበት። መጽሐፉን እንዲሁ እየገለጥኩ ገረፍ ገረፍ አድርጌ ስመለከተው ስለ እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን እንደሚጠቅስ ተገነዘብኩ። ነገሩ አበሳጨኝ። በልቤ ‘ቤተ ክርስቲያን የሚባል ነገር አልፈልግም’ አልኩ። ስለዚህ መጽሐፉን ፈጽሞ አላነበብኩትም።
በ1929 ወደ ውትድርናው ዓለም ገባሁና የአልባኒያ ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ወደ ቲራን ተላክሁ። እዚያም ስታቲ ሙኪ አንድ የግሪክኛ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ አገኘሁት። “ቤተ ክርስቲያን ትሄዳለህ?” በማለት ጠየቅሁት። “አልሄድም። ከቤተ ክርስቲያን ወጥቻለሁ። ከዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች አንዱ ነኝ” ሲል መለሰልኝ። እሑድ እኔና አንድ ወታደር ከስታቲ ጋር ወደ ስብሰባ ሄድን። እዚያም እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን አንድ ሕንፃ ወይም አንድ ሃይማኖት ሳይሆን ቅቡዓን የክርስቶስ አገልጋዮች እንደሆኑ ተማርኩ። አሁን የአምላክ በገና የተባለው መጽሐፍ ምን እንደሚል ተረዳሁ።
በ1920ዎቹ አጋማሽ ላይ ናሾ ኢድሪዚና ስፒሮ ቩሮ ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ አልባኒያ ተመልሰው እዚያ የተማሯቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አሰራጩ። ከጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቸ ጋር ቲራን ውስጥ መሰብሰብ ጀመርኩ። ወዲያው የይሖዋን ድርጅት እንዳገኘሁ ግልጽ ሆነልኝ። ስለዚህ ነሐሴ 4, 1930 በአቅራቢያችን በሚገኝ አንድ ወንዝ ውስጥ ተጠመቅሁ።
ከዚያ በኋላ ወደ እብሪስታን ተመለስኩና የጫማ ሰፊነት ሙያዬን ቀጠልኩ። ይሁን እንጂ ከዚህ በተጨማሪ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርኳቸውን እውነቶች ለሌሎች ሰዎች ማካፈል ጀመርኩ። “ኢየሱስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሥዕል እንደምታዩት አይደለም። እሱ ሕያው ነው!” በማለት እነግራቸው ነበር።
ተቃውሞ ቢኖርም መስበክ
በ1925 አህመድ ባ ዞጊ ሥልጣን ጨበጠና በ1928 ራሱን ንጉሥ ዞግ አንደኛ በማለት ሰየመ። እስከ 1939 ድረስ ገዛ። የሰብዓዊ መብቶች ሚኒስትሩ ለክርስቲያናዊ ሥራችን ፈቃድ ሰጠን። ሆኖም ችግሮች ነበሩብን። ይህ የሆነው በወቅቱ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ሙሳ ጁካ ከሮሙ ሊቀ ጳጳስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ስለነበረው ነው። ጁካ እስልምና፣ ኦርቶዶክስና የሮም ካቶሊክ የተባሉት ሦስት ሃይማኖቶች ብቻ ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኙ ትእዛዝ አስተላለፈ። ፖሊሶች መጽሐፎቻችንን ውርስ ለማድረግና የስብከት ሥራችንን ለማስቆም ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም።
በ1930ዎቹ ሚሃል ሲቪሲ የስብከት ሥራችንን ወደሚመራበት ብራት ወደ ተባለ የአልባኒያ ትልቅ ከተማ ብዙ ጊዜ እሄድ ነበር። በጠቅላላው የአገሪቱ ክልል ውስጥ የስብከት ዘመቻዎች ለማድረግ ዝግጅት አደረግን። አንድ ጊዜ ሸኮደር ወደ ተባለ ከተማ ተላኩና ብዙ ጽሑፎችን አበረከትኩ። በ1935 አንድ ቡድን ካቀናጀን በኋላ ኬልሳየር ወደ ተባለ ከተማ ሄደን ለመስበክ አውቶብስ ተኮናተርን። ከዚያም ፕሪሜት፣ ሌስኮቪክ፣ ኢርሴክ፣ ኮርች፣ ፖግሬዲክ እና ኢልብሳን በተባሉት የአልባኒያ ከተሞች ውስጥ ሰፋ ያለ የስብከት ዘመቻ ለማድረግ ታቀደ። የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ የሚከበርበት ጊዜ ሲደርስ በቲራን ውስጥ ያደረግነውን የስብከት ዘመቻ አጠናቀቅን።
የመንፈሳዊ ምግብ አቅርቦት በመንፈሳዊ ጠንካሮች ሆነን እንድንቀጥል ስለረዳን ፈጽሞ እንደ ተተውን ተሰምቶን አያውቅም። ከ1930 እስከ 1939 ዘወትር የግሪክኛ መጠበቂያ ግንብ ይደርሰኝ ነበር። በተጨማሪም በየቀኑ ቢያንስ አንድ ሰዓት መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ግብ የነበረኝ ሲሆን የማየት ችሎታዬ እስከ ደከመ ድረስ ወደ 60 ለሚጠጉ ዓመታት ይህን ግብ ከዳር አድርሻለሁ። ጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ በአልባኒያ ቋንቋ የተተረጎመው በቅርቡ ስለሆነ በልጅነቴ የግሪክኛ ቋንቋ በመማሬ ተደስቻለሁ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት ሌሎች የአልባኒያ ተወላጅ የይሖዋ ምሥክሮችም ጠቅላላውን መጽሐፍ ቅዱስ ለማንበብ ሲሉ የግሪክኛ ቋንቋ ተምረዋል።
አርጅሮ በ1938 ተጠመቀች። በ1939 ከአሥር ልጆቻችን ውስጥ ሰባቱ ተወልደው ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ከመጀመሪያዎቹ ሰባት ልጆቻችን ውስጥ ሦስቱ ገና በልጅነታቸው ሞቱ።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ያጋጠሙን ችግሮች
ሚያዝያ 1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጃመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ የኢጣሊያ ፋሽስት ሠራዊት አልባኒያን ወረረ። ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ታገደ። ይሁን እንጂ ወደ 50 የሚጠጉ አዋጅ ነጋሪዎችን ያቀፈው አነስተኛ ቡድናችን መስበኩን ቀጠለ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወደ 15,000 የሚያህሉ መጽሐፎቻችንና ቡክሌቶቻችን ከተወረሱብን በኋላ ተቃጠሉ።
ጃኒ ኮሚኖ ከቤቱ ጋር ተያይዞ የተሠራ አንድ ትልቅ የጽሑፍ ማከማቻ ክፍል ነበረው። የኢጣሊያ ወታደሮች መጽሐፎቹ የሚታተሙት በዩናይትድ ስቴትስ መሆኑን ሲገነዘቡ በጣም ተናደዱ። “ፕሮፓጋንዳ ነዢዎች ናችሁ! ዩናይትድ ስቴትስ የኢጣሊያ ጠላት ናት!” አሉ። ቶሚና ቫዚሊ ካማ የተባሉት ቀናተኛ ወንድሞች ታሰሩ። በተጨማሪም እነሱ የሚያሰራጯቸው መጽሐፍት የተገኙት ከኮሚኖ እንደሆነ ሲደረስበት እሱም ጭምር ታሰረ። ወዲያውኑ ፖሊሶች እኔን ለጥያቄ ጠሩኝ።
“እነዚህን ሰዎች ታውቃቸዋለህ?” በማለት ጠየቁኝ።
“አዎን” ስል መለስኩላቸው።
“ከእነሱ ጋር ትሠራለህ?”
“አዎን። የይሖዋ ምሥክሮች ነን። መንግሥትን አንቃወምም። ገለልተኛ ነን” አልኋቸው።
“ይህን ጽሑፍ አሰራጭተህ ታውቃለህ?”
አዎን የሚል ምላሽ ስለሰጠሁ እጄን በካቴና ጠፍረው ሐምሌ 6, 1940 እስር ቤት ጨመሩኝ። እዚያም አምስት የሰፈሬን ሰዎች ማለትም ጆሴፍ ካሲ፣ ሉካን ባርኮ፣ ጃኒ ኮሚኖና የካማ ወንድሞችን አገኘሁ። በእስር ቤት ሳለን ጎሪ ናሲ፣ ኒኮዲም ሻይቲና ሊዮኒዳስ ፖፕ የተባሉትን ሌሎች ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች አገኘን። ዘጠኛችንም 1.8 በ3.7 ሜትር በሆነ ክፍል ውስጥ ታጎርን!
ከጥቂት ቀናት በኋላ አንድ ላይ በሰንሰለት ታስረን ፕሪሜት ወደ ተባለችው ከተማ ተወሰድን። ከሦስት ወራት በኋላ በቲራን ወደሚገኘው እስር ቤት ተዛወርንና ጉዳያችን በፍርድ ቤት ሳይታይ ለስምንት ተጨማሪ ወራት ታሰርን።
በመጨረሻም በአንድ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ፊት ቀረብን። እኔና ወንድም ሻይቲ 27 ወራት ሲፈረድብን ወንድም ኮሚኖ 24 ወራት ተፈረደበት። ሌሎች ደግሞ ከ10 ወራት እስራት በኋላ ተፈቱ። እኛ ግን ወደ ጊርካስተር እስር ቤት ተዛወርን። እዚያም በ1943 ወንድም ጎል ፍሎኮ እንድንለቀቅ ረዳን። ከዚያ በኋላ ቤተሰባችን የአንድ ትንሽ ጉባኤ የበላይ ተመልካች በሆንኩበት በፕሪሜት ከተማ ውስጥ መኖር ጀመረ።
ምንም እንኳ ሥራችን የታገደና በዙሪያችን ያሉት አገሮች በተፋፋመው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ገብተው የነበሩ ቢሆንም የመንግሥቱን መልእክት የመስበክ ተልእኳችንን ለመፈጸም የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችንን ቀጠልን። (ማቴዎስ 24:14) በ1944 በጠቅላላው 15 የይሖዋ ምሥክሮች ታስረው ነበር። ሆኖም በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ይሖዋ እንደተወን በፍጽም ተሰምቶን አያውቅም።
በገለልተኛነት ጉዳይ መፈተን
ምንም እንኳ ጦርነቱ ያበቃው በ1945 ቢሆንም ችግሮቻችን አላቆሙም፤ እንዲያውም በይበልጥ እየከፉ መጡ። ታኅሣሥ 2, 1946 በነበረው የምርጫ ወቅት ሰዎች በግዴታ ድምፅ እንዲሰጡ ተደረገ። ድምፅ አልሰጥም የሚል ሁሉ የአገር ጠላት እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። የፕሪሜት ጉባኤ አባላት “ምን እናድርግ?” በማለት መጠየቅ ጀመሩ።
“በይሖዋ ከተማመናችሁ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ እኔን መጠየቅ አያስፈልጋችሁም። የይሖዋ ሕዝቦች ገለልተኞች እንደሆኑ ታውቃላችሁ። የዓለም ክፍል አይደሉም” በማለት መለስኩላቸው።—ዮሐንስ 17:16
የምርጫው ቀን ደረሰና የመንግሥት ተወካዮች ወደ ቤታችን መጡ። ረጋ ብለው “ቡና እየጠጣን እንጫወት። ዛሬ ምን እንደሆነ ታውቃለህ?” በማለት ጉዳዩን ጀመሩ።
“አዎን፣ ዛሬ ምርጫ ይካሄዳል” ስል መለስኩላቸው።
አንድ የፖሊስ አዛዥ “ቶሎ ትመርጣለህ ወይስ ትቆያለህ” በማለት ጠየቀኝ።
“ለመሄድ አላሰብኩም። እኛ የምንመርጠው ይሖዋን ነው” ስል መለስኩለት።
“እሺ፣ መጥተህ የተቃውሞ ድምፅ ስጥ።”
የይሖዋ ምሥክሮች ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ እንደሆኑ ገለጽኩለት። አቋማችን በደምብ ሲታወቅ በእኛ ላይ የሚደርስብን ተጽዕኖ እየጨመረ መጣ። እንዳንሰበሰብ ስለ ተከለከልን በምሥጢር መሰብሰብ ጀመርን።
ወደ ትውልድ መንደራችን መመለስ
በ1947 እኔና ቤተሰቤ ወደ እብሪስታን ተመለስን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በጣም ቀዝቃዛ በሆነው በታኅሣሥ ወር አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ሲገሪሚ (የምሥጢር ፖሊስ) ቢሮ ተጠራሁ። የፖሊስ አዛዡ “ለምን እንደጠራሁህ ታውቃለህ?” አለኝ።
“ስለ እኔ ክስ ደርሶህ ይመስለኛል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ዓለም ይጠላችኋል ስለሚል መከሰሴ አያስደንቀኝም” አልሁት።—ዮሐንስ 15:18, 19
“ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አታውራልኝ። ጭንቅላትህን ነው የምልህ” ሲል በቁጣ ጮኸብኝ።
የፖሊስ አዛዡና ወታደሮቹ ቢሮውን ለቀው ወጡና ውጪ ብርድ ላይ እንድቆም አዘዙኝ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የፖሊስ አዛዡ ወደ ቢሮው ጠራኝና በቤታችን ስብሰባ ማድረጋችንን እንድናቆም አዘዘኝ። “በሰፈራችሁ ውስጥ ስንት ሰዎች ይኖራሉ” ሲል ጠየቀኝ።
“መቶ ሃያ” በማለት መለስኩለት።
“ሃይማኖታቸው ምንድን ነው?”
“የአልባኒያ ኦርቶዶክስ።”
“አንተስ?”
“እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ።”
“መቶ ሃያ ሰዎች በአንድ መንገድ ሲጓዙ አንተ በሌላ መንገድ ትሄዳለህ?” አለኝ። ከዚያም ቤተ ክርስቲያን ሄጄ ሻማ እንዳበራ አዘዘኝ። ይህን እንደማላደርግ ስነግረው በዱላ ይደበድበኝ ጀመር። በመጨረሻ ስለቀቅ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ገደማ ሆኖ ነበር።
የጽሑፍ አቅርቦት ተቋረጠ
የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ መጠበቂያ ግንብ በፖስታ ማግኘት ጀመርን። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ መጽሔቶቹ መምጣታቸውን አቆሙ። ከዚያ በኋላ አንድ ቀን ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ የምሥጢር ፖሊሱ ጠራኝ። “አንድ ግሪክኛ መጽሔት ደረሰን። መጽሔቱ ምን እንደያዘ እንድታብራራልን እንፈልጋለን” ሲል አዘዘኝ።
“ግሪክኛ በደምብ አላውቅም። ጎረቤቴ ከእኔ የተሻለ ያውቃል። ምናልባት እሱ ሊረዳችሁ ይችላል” አልሁ።
የፖሊስ አዛዡ “እኛ የምንፈልገው አንተ ይህን እንድታብራራልን ነው” አለና አንዳንድ የግሪክኛ መጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችን አወጣ።
ደስ ብሎኝ “ይህማ የእኔ ነው። እርግጥ ስለዚህ ማብራሪያ ልሰጥህ እችላለሁ። ታያለህ እነዚህ መጽሔቶች የሚመጡት ከብሩክሊን ኒው ዮርክ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኘው እዚያ ነው። እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ። ሆኖም አድራሻ የተሳሳቱ ይመስለኛል። እነዚህ መጽሔቶች ለእኔ እንጂ ለአንተ መላክ አልነበረባቸውም” አልሁት።
መጽሔቶቹን አልሰጡኝም፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከ 1991 ድረስ ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት አንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ደርሶን አያውቅም። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት በመጽሐፍ ቅዱሳችን ብቻ ተጠቅመን መስበካችንን ቀጥለናል። በ1949 ወደ 20 የሚጠጉ ወንድሞች የታሰሩ ሲሆን አንዳንዶች የአምስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው ነበር።
ችግሮች እየጨመሩ ሄዱ
በ1950ዎቹ ሰዎች ውትድርናን እንደሚደግፉ የሚያሳዩ የጽሑፍ ማስረጃዎች እንዲይዙ ትእዛዝ ወጥቶ ነበር። ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች እንደነዚህ ዓይነቶቹን የጽሑፍ ማስረጃዎች አንይዝም አሉ። በዚህ ምክንያት እኔና ወንድም ኮሚኖ ሁለት ወር ታሰርን።
በወቅቱ መንግሥት አንዳንድ ሃይማኖቶች እንዲንቀሳቀሱ ስለ ፈቀደ መጠነኛ ነፃነት አገኘን። ሆኖም በ1967 ሁሉም ሃይማኖቶች መታገዳቸው አልባኒያን በይፋ አምላክ የለም ባይ አገር እንድትሆን አደረጋት። የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ማድረጋቸውን ለመቀጠል ቢሞክሩም ይህ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ መጣ። አንዳንዶቻችን ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ደብቀን ለመያዝ እንድንችል ከኮታችን ገበር ሥር ስውር ኪስ ሰፋን። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ በዚያ ውስጥ ደብቀን ወደ መስክ እንወጣለን።
በቲራን የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያነቡ ስለ ተያዙ ሦስቱ ራቅ ብለው በሚገኙ የጉልበት ሥራ ቅጣት በሚሰጥባቸው ካምፖች ለአምስት ዓመታት እንዲሠሩ ተፈረደባቸው። በዚህም ምክንያት ቤተሰቦቻቸው ችግር ላይ ወደቁ። ነጠል ብለው በሚገኙ አነስተኛ መንደሮች የምንኖረው ብዙም እንደማናሰጋ ስለታመነበት ወደዚያ አልተላክንም። ይሁን እንጂ ገለልተኛነታችን ምግብ እንዲያገኙ ከሚፈቀድላቸው ሰዎች ስም ዝርዝር ውስጥ እንድንሰረዝ አደረገን። ስለዚህ ኑሮ አስቸጋሪ ሆነ። በተጨማሪም ሌሎች ሁለት ልጆቻችን ሞቱ። ሆኖም ይሖዋ እንደተወን ፈጽሞ ተሰምቶን አያውቅም።
በአልባኒያ ውስጥ ፍርሃት ተስፋፋ። ሁሉም ሰው ላይ ክትትል ይደረግበት ነበር፤ በተጨማሪም የምሥጢር ፖሊሶች የገዢው ፖርቲ ካለው አመለካከት የተለየ ሐሳብ ለመግለጽ በሚዳፈር በማንኛውም ሰው ላይ ሪፖርት ይጽፉበት ነበር። ስለዚህ ስለ ሥራችን የሚገልጹ የጽሑፍ ሪፖርቶች በምናደርግበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርግ ነበር። መንፈሳዊ ማበረታቻ ለማግኘት ከሁለት ወይም ከሦስት በላይ ሆነን መሰብሰብ አንችልም ነበር። ሆኖም መስበካችንን ፈጽሞ አላቆምንም።
በወንድሞች መካከል ግራ መጋባትን ለመፍጠር የምሥጢር ፖሊሶች በቲራን የሚኖር አንድ በጣም ጎበዝ የይሖዋ ምሥክር ሰላይ እንደሆነ የሚገልጽ ወሬ ነዙ። ይህም አንዳንዶች እምነታቸውን እንዲክዱና በጥቂቱም ቢሆን አንድነታችን እንዲናጋ አደረገ። በወቅቱ ምንም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ ስላልነበረና ከይሖዋ የሚታይ ድርጅት ጋር የነበረን ግንኙነት ስለተቋረጠ ጥቂቶች ለፍርሃት ተንበረከኩ።
ከዚህም በተጨማሪ ባለ ሥልጣናት በአልባኒያ ከፍተኛ አክብሮት ያተረፈ ክርስቲያን ሽማግሌ የነበረው ስፓየሮ ቩሮ ራሱን ገደለ የሚል ወሬ አሰራጩ። “ቩሮ እንኳን ተስፋ እንደ ቆረጠ ትመለከታላችሁ” አሉ። ከጊዜ በኋላ ወንድም ቩሮ እንደተገደለ ተረጋገጠ።
በ1975 እኔና አርጅሮ በቲራና ከሚገኘው ልጃችን ጋር ጥቂት ወራት ቆየን። በምርጫው ወቅት በከተማዋ ውስጥ የሚገኙት ባለ ሥልጣናት “ድምፅ ካልሰጣችሁ ልጃችሁ ከሥራ ይባረራል” በማለት ዛቱብን።
“ልጄ 25 ዓመታት በዚህ ሥራው ላይ ቆይቷል። ስለ እሱና ስለ ቤተሰቡ ዝርዝር መረጃዎች አላችሁ። እኔም ከ40 ለሚበልጡ ዓመታት ድምፅ ሰጥቼ አላውቅም። በመሠረቱ ይህ መረጃ በግል መዝገቦቻችሁ ውስጥ ይገኛል። የማይገኝ ከሆነ ደግሞ መረጃዎቻችሁ በሥርዓት አልተያዙም ማለት ነው። ይህ መረጃ በመዝገቦቻችሁ ውስጥ የሚገኝ ከሆነ ይህን ያህል ዓመታት እንዲሠራ ስትፈቅዱለት ለፓርቲያችሁ ታማኝ አልነበራችሁም” ስል መለስኩላቸው። ባለ ሥልጣኖች ይህን ሲሰሙ ወደ እብሪስታን ከተመለስን ጥያቄውን በድጋሜ እንደማያነሡ ተናገሩ።
አስደናቂ ለውጦች
በ1983 ከእብሪስታን ከተማ ወደ ላክ ሄድን። ይህ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አምባገነኑ መሪ በ1985 ሞተ። በ1946 በግዴታ ምርጫ ይደረጉባቸው ከነበሩት የመጀመሪዎቹ ጊዜያት አንሥቶ ሲገዛ ቆይቶ ነበር። ከጊዜ በኋላ በቲራን ዋና አደባባይ ላይ ጎላ ብሎ ይታይ የነበረው ሐውልቱና የስታሊን ሐውልት እንዲፈርስ ተደረገ።
በሥራችን ላይ እገዳ በተጣለባቸው አሥርተ ዓመታት ወቅት ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ ሥቃይ ደርሶባቸዋል፤ አንዳንዶችም ተገድለዋል። አንድ ሰውዬ የይሖዋ ምሥክሮችን መንገድ ላይ አግኝቷቸው እንዲህ አላቸው፦ “በኮሚኒስቶች አገዛዝ ዘመን ሁላችንም አምላክን ክደናል። ብዙ ፈተናዎችና መከራዎች ቢደርስባቸውም ለእሱ ታማኝ ሆነው የቀጠሉት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው።”
የበለጠ ነፃነት ሲገኝ በሰኔ 1991 ዘጠኝ ሰዎች ሪፖርት አድርገዋል። እገዳው ከተነሣ ከአንድ ወር በኋላ ማለትም በሰኔ 1992 በስብከቱ ሥራ ላይ 56 ሰዎች ተሳትፈዋል። በዚያ ዓመት መጀመሪያ 325 ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ በመገኘታቸው ተደስተናል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የሰባኪዎች ቁጥር ከ600 በላይ ሆኗል። በተጨማሪም ሚያዝያ 14, 1995 በተከበረው የመታሰቢያ በዓል ላይ 3,491 ሰዎች ተገኝተዋል! ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጉባኤዎቻችን ውስጥ በጣም ብዙ ወጣቶች መገኘታቸው በቃላት ልገልጸው የማልችለው ደስታ አስገኝቶልኛል።
አርጅሮ ለይሖዋ ታማኝ ሆና ከመኖሯም በተጨማሪ በእነዚህ ሁሉ ብዙ ዓመታት ለእኔ ታማኝ ደጋፊዬ ሆናለች። በእስር ቤት ሳለሁ ወይም በስብከቱ ሥራ በጉዞ ላይ ስሆን ለቤተሰባችን የሚያስፈልጉትን ነገሮች ምንም ሳታማርር በትዕግሥት ታቀርብ ነበር። በ1993 ከልጆቻችን አንዱ ከነባለቤቱ ተጠመቀ። ይህ በጣም አስደስቶናል።
ለአምላክ መንግሥት ብቻ
በአልባኒያ ውስጥ የይሖዋ ድርጅት ከፍተኛ አንድነትና መንፈሳዊ ብልጽግና ሲያገኝ በማየቴ ተደስቻለሁ። ከረጅም ጊዜ በፊት ተስፋ የተሰጠበትን መሲሕ የማየትን ውድ መብት እንዳገኘው በኢየሩሳሌም ውስጥ እንደ ነበረው አረጋዊው ስምዖን የሆንኩ ይመስለኛል። (ሉቃስ 2:30, 31) በአሁኑ ወቅት የትኛውን መንግሥት ትመርጣለህ? የሚል ጥያቄ ሲቀርብልኝ እንዲህ በማለት መልስ እሰጣለሁ፦ “ኮሚኒዝምንም ሆነ ካፒታሊዝምን አልመርጥም። መሬት በሕዝብም ይያዝ በመንግሥት ለውጥ የለውም። መንግሥታት መንገዶችን ይሠራሉ፣ ራቅ ብለው ለሚገኙ መንደሮች መብራት ያስገባሉ እንዲሁም መጠነኛ ሥርዓት ያስከብራሉ። ሆኖም አልባኒያም ሆነች ሌሎች አገሮች ላሉባቸው ችግሮች ብቸኛ መፍትሔ የሚያስገኘው የይሖዋ መስተዳድር የሆነው ሰማያዊ መንግሥቱ ነው።”
የአምላክ አገልጋዮች በመላው ዓለም ስለ አምላክ መንግሥት በመስበክ የሚያከናውኑት ተግባር የማንኛውም ሰው ሥራ አይደለም። የአምላክ ሥራ ነው። እኛ የእሱ አገልጋዮች ነን። በአልባኒያ ውስጥ ብዙ ችግሮች ያጋጠሙንና ከሚታየው የይሖዋ ድርጅት ጋር የነበረን ግንኙነት ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም እሱ ፈጽሞ አልተወንም። መንፈሱ ምን ጊዜም አብሮን ነበር። እያንዳንዱን እርምጃችንን ይመራ ነበር። ባሳለፍኩት ሕይወት ይህን ተመልክቻለሁ።