ዋጋው እጅግ ውድ የሆነ ሀብት አገኘሁ
በፍሎረንስ ዊዶሰን እንደተነገረው
እየመሸ ስለሄደ በአንድ ባሕር አጠገብ በድንኳን ለማደር ወሰንን። ቦታው ሁለት ሴቶች ብቻቸውን የሚያድሩበት ጥሩ አካባቢ ባይሆንም ለአንድ ሌሊት ምንም አይደለም ብለን አሰብን። እኔ ድንኳኑን ለመወጠር ወዲያ ወዲህ እያልኩ ሳለሁ ማርጆሪ እራታችንን አዘጋጀች።
ልክ ድንኳኑን ዘርግቼ እንደጨረስኩ በአንድ ጥቁር የዛፍ ጉቶ አጠገብ አንድ ነገር ሲንቀሳቀስ አየሁ። “እዚያ ጉቶ አጠገብ አንድ ነገር ሲንቀሳቀስ አየሽ?” ስል ማርጆሪን ጠየቅኳት።
ትንሽ ግራ በመጋባት “አይ አላየሁም” ስትል መለሰችልኝ።
“በእርግጥ ተንቀሳቅሷል” ስል ጮህኩ። “ማንቆርቆሪያውን ስጪኝ!”
በትከሻዬ ላይ መጥረቢያ አድርጌ ማንቆርቆሪያውን ይዤ ወደ ባሕሩ ሄድኩ። ልክ በጉቶው አቅጣጫ ልደርስ ስል አንድ ሰው ከጉቶው ሥር ብድግ ብሎ መጣብኝ!
“የባሕሩ ውኃ ለመጠጥ ይሆናል?” ስል መቀባጠር ጀመርኩኝ።
“አይሆንም፣ ነገር ግን የሚጠጣ ውኃ ከፈለግሽ እኔ አመጣልሻለሁ” ሲል በጎረነነ ድምፅ መለሰልኝ።
ቶሎ ብዬ እንደማልፈልግ ገለጽኩለት። እሱም ወዲያው ጥሎኝ ሄደ። እየተንቀጠቀጥኩ በጥድፊያ ወደ ማርጆሪ ተመለስኩና የሆነውን ነገር ነገርኳት። በፍጥነት ድንኳኑን ነቀልንና እቃችንን ጠቅልለን ከዚያ ቦታ ሄድን። በኋላ ሰውዬው በቅርቡ ከወህኒ ቤት የተለቀቀ መሆኑ ተነገረን።
ምንም እንኳን በእነዚህ የአውስትራሊያ የወርቅ መስኮች ላይ በ1937 አካባቢ የማዕድን ፈላጊዎች ይሰፍሩባቸው የነበረ ቢሆንም እኛ ግን የተለየ ዓይነት ማዕድን ፈላጊዎች ነበርን። እኛ ለአምላክ የከበሩ ሰዎችን እየፈለግን ነበር።
የቤተሰቤ ሁኔታ
አባቴ ከመቶ ዓመት በፊት በቪክቶሪያ ግዛት በምትገኘው ፖረፐንክ በምትባለው ትንሽ መንደር ውስጥ ቀጥቃጭ ነበር። እኔም በ1895 በዚያች መንደር ውስጥ ተወለድኩና በቡፋሎ ተራራ ሥር በኦቨንስ ወንዝ አጠገብ ከአራት ታላላቅ ወንድሞቼ ጋር አደግኩ። ወላጆቼ በዩኒየን ቤተ ክርስቲያን አዘውትረው ይሰበሰቡ ነበር። እኔም ሰንበት ትምህርት ቤት ገባሁ። አባቴ የትምህርት ቤቱ ተቆጣጣሪ ነበር።
በ1909 አንድ ወቅ ት ኃይለኛ የባሕር ማዕበል ተነሳና እናቴ በልብ ድካም በአባቴ ክንዶች ላይ እንዳለች አረፈች። ከዚያ በ1914 መጀመሪያ አካባቢ አንዱ ወንድሜ ከቤት ወጣና ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሬሳው መጣልን። ራሱን ገድሎ ነው። ራስን መግደል ይቅር የማይባል ኃጢአት ነው ተብሎ ስለሚነገር ሲኦል ውስጥ ገብቶ ይቃጠላል የሚለው የቤተ ክርስቲያኑ ትምህርት የባሰ ኀዘናችንን አባባሰው።
ከዚያም በዚያው ዓመት ትንሽ ቆይቶ አንደኛው የዓለም ጦርነት ተነሳ። ሁለቱ ወንድሞቼ ወደ ውጭ አገር ሄደው በውትድርና ለማገልገል ተመዘገቡ። ስለሚደርሰው የደም መፋሰስና ሥቃይ የሚገልጸው አስፈሪ ዜና ስድስት ልጃገረዶች ከአባቴ ጋር ሆነን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የዮሐንስን መጽሐፍ እንድናጠና ገፋፋን።
እውነተኛ ሀብት ማግኘት
ኤለን ሀድሰን በቻርልስ ቴዝ ራስል የተዘጋጀው ጊዜው ቅርብ ነው (ዘ ታይም ኢዝ አት ሀንድ) የተባለው መጽሐፍ አንድ ቅጂ ነበራት። ኤለን ለመጽሐፉ የነበራት የጋለ ስሜት በቡድኑ ውስጥ ያለነውን የቀረነውንም መጽሐፉን እንድናጠና ገፋፋን። ኤለን መጽሐፉ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት (ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ) በሚል ርዕስ በተከታታይ በሚወጡ ስድስት ጥራዞች ከተዘጋጀው ውስጥ አንዱ ብቻ መሆኑን ስታውቅ በሜልቦርን ለሚገኘው ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር ቢሮ ደብዳቤ ጻፈችና የቀሩት በተከታታይ የወጡት መጽሐፎች እንዲላኩላት ጠየቀች። ቡድናችን መለኮታዊ የዘመናት እቅድ (ዘ ዲቫይን ፕላን ኦቭ ዘ ኤጅስ) የተባለውን የመጀመሪያውን ጥራዝ በሳምንታዊ ጥናታችን ለመጠቀም ተስማማ።
እኔና አባቴ የመቃጠያ ሲኦል እንደሌለ ስናውቅ ምን ያህል እንደተደሰትን ገምቱ። ወንድሜ በእሳታማ ሲኦል ውስጥ ገብቷል የሚለው ፍርሃቴ ተወገደልኝ። የተኛ ሰው ምንም እንደማይሰማ ሁሉ ሙታንም ምንም እንደማይሰሙና በሌላ ቦታ በሕይወት እየተሰቃዩ እንዳልሆኑ የሚናገረውን እውነት ተማርን። (መክብብ 9:5, 10፤ ዮሐንስ 11:11–14) በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድናችን ውስጥ ያሉ አንዳንዶች እየተማርነው ያለነውን እውነት ለጎረቤቶቻችን ሄደው ለመስበክ ወሰኑ። በአቅራቢያችን ወደሚገኙት ቤቶች ሄድን፤ ሆኖም ገጠር ወዳሉት ለመሄድ በብስክሌትና በአንድ ፈረስ በሚጎተት ጋሪ ተጠቀምን።
ከቤት ወደ ቤት የሚደረገውን ምስክርነት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀመስኩት ኅዳር 11, 1918 አንደኛውን የዓለም ጦርነት ለማቆም ስምምነት በተደረገበት ቀን ነው። ዘ ፒፕልስ ፐልፒት የተባለውን ትራክት ለማሰራጨት ከጥናት ቡድናችን ውስጥ ሦስታችን ዋንግራታ ወደምትባል ከተማ 80 ኪሎ ሜትር ተጓዝን። በመግቢያው ላይ ያለው ተሞክሮ ያጋጠመኝ ከብዙ ዓመታት በኋላ በአንድ የገጠር አካባቢ ለስብከት ተመድቤ ሳለሁ ነው።
በ1919 በሜልቦርን በተደረገው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትልቅ ስብሰባ ተካፈልኩ። በዚያ ስብሰባ በሚያዝያ 22, 1919 ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። በዚያ የቀረበው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ለሰማያዊቷ መንግሥት መንፈሳዊ ሀብትና ለይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ያለኝን አድናቆት ይበልጥ ጥልቅ አደረገው።—ማቴዎስ 13:44
ከስብሰባው በኋላ ወደ ቤት አልተመለስኩም ከዚህ ይልቅ ለአንድ ወር ምስክርነት የሙሉ ጊዜ ሰባኪ ከሆነችው ከጄን ኒኮልሰን ጋር ለአንድ ወር እንዳገለግል የቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። የተመደብነው በኪንግ ወንዝ አጠገብ በሚገኘው የእርሻና የከብት እርባታ ቦታ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት ይህ ተራራማ አካባቢ ዘ ማን ፍሮም ስኖዊ ሪቨር ለተባለው ፊልም ታሪክ መነሻ ቦታ ተደርጎ ነበር።
በ1921 የአምላክ በገና (ዘ ሀርፕ ኦቭ ጎድ) የተባለ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ ግሩም መጽሐፍ አገኘን። አባቴ ይህን መጽሐፍ ለሰንበት ትምህርት ቤት የመማሪያ መጽሐፍ አድርጎ መጠቀም ሲጀምር ብዙ ወላጆች ይህን በመቃወም ሥራውን እንዲለቅ ጠየቁት። እሱም ወዲያው ሥራውን ለቀቀ። ቀጥሎ በሽፋኑ ላይ “ሲኦል ምንድን ነው? በሲኦል ውስጥ ያሉትስ እነማን ናቸው? ከሲኦል ውስጥ ሊወጡ ይችላሉን?” የሚሉትን የሚከነክኑ ጥያቄዎች የያዘውን ሲኦል (ሄል) የተባለውን ቡክሌት አገኘን። አባቴ በሐሳቡ ላይ በቀረቡት ግልጽ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች በጣም ስለተደሰተ ወዲያው ቡክሌቱን ከቤት ወደ ቤት እየሄደ ማሰራጨት ጀመረ። በመንደራችንና በአቅራቢያችን ባሉት የገጠር አካባቢዎች በብዙ መቶ የሚቆጠር ቡክሌት አበረከተ።
ከአባቴ ጋር ያደረግኩት የስብከት ጉዞ
በመጨረሻም አባቴ በሌላ አካባቢ ለሚገኙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለማድረስ አንድ መኪና ገዛ። ቀጥቃጭ እንደመሆኑ መጠን እሱ የለመደው ፈረሶችን ነው፤ ስለዚህ እኔ ሹፌር ሆንኩ። በመጀመሪያ ማታ ማታ ሆቴል ውስጥ እናድር ነበር። ገንዘቡ ስለከበደን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውጭ በድንኳን ማደር ጀመርን።
አባቴ እኔ መኪናው ውስጥ ለመተኛት እንድችል ብሎ የመኪናውን የፊት መቀመጫ ለጥ ብሎ እንዲዘረጋ አደረገው። አባቴ የሚተኛበት አንድ ትንሽ ድንኳን ዘረጋን። ለበርካታ ሳምንታት በድንኳን ከተቀመጥን በኋላ ወደ ፖረፐንካህ ተመለስን። በዚያም አባቴ በድጋሚ የራሱ የቅጥቀጣ ሱቅ ከፈተ። የሚቀጥለውን የስብከት ጉዞአችንን ወጪዎች የሚሸፍንልንን ገንዘብ የሚሰጡን ብዙ ደንበኞች ዘወትር ማግኘታችን በጣም ያስደንቀን ነበር።
ቀና አመለካከት ያላቸው ብዙ ሰዎች ለምናደርግላቸው ጉብኝት አዎንታዊ ምላሽ ሰጡ። በመጨረሻም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላቸው የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉ። በፖረፐንካህ የሚገኘው አነስተኛ ቡድናችን ባገለገለበት በዚህ አካባቢ አሁን የራሳቸው የመንግሥት አዳራሽ ያላቸው ሰባት ጉባኤዎች አሉ። በእርግጥም “የጥቂቱን ነገር ቀን” ማን ሊንቅ ይችላል?—ዘካርያስ 4:10
በ1931 አባባና እኔ አንድ ልዩ ስብሰባ ለመካፈል አስቸጋሪ በሆኑ መንገዶች 300 ኪሎ ሜትር ያህል በመኪና ተጓዝን። በዚህ ስብሰባ ላይ “የይሖዋ ምስክሮች” የሚለውን አዲሱን ስማችንን አገኘን። በዚህ ልዩ በሆነው ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም ሁለታችንም በጣም ተደሰትን። (ኢሳይያስ 43:10–12) “የይሖዋ ምስክሮች” የሚለው ስም እስከዚያ ጊዜ ድረስ እንጠራበት ከነበረው “ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች” ከሚለው ስም የበለጠ ማንነታችንን በሚገባ ይገልጻል።
አንድ ቀን በቤታንጅ ከተማ ስመሰክር የአካባቢው ደብር አለቃ ከሆነ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቄስ ጋር ተገናኘን። ቄሱ በጣም ተናደደና ሰዎች መጽሐፎቻቸውን እንዲሰጡት በመጠየቅ ያበረከትናቸውን ብዙ መጽሐፎች እየፈለገ መሰብሰብ ጀመረ። ከዚያ በኋላ በከተማዋ አደባባይ መጽሐፎቹን አቃጠለ። ይሁን እንጂ ወራዳ ድርጊቱ መልሶ እርሱን ጎዳው።
የተፈጸመውን ነገር ለማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ከገለጽኩ በኋላ የቄሱን ድርጊት የሚያወግዝ የተቃውሞ ደብዳቤ ታተመ። በተጨማሪም ደብዳቤውን በአውራጃው በሙሉ ለማሰራጨት ብዙ ምስክሮች በመኪና ሆነው እንዲሄዱ ዝግጅት ተደረገ። አባቴና እኔ ከተማውን በሌላ ጊዜ ስንጎበኝ ከበፊቱ የበለጠ ብዙ መጽሐፎችን አበረከትን። የከተማው ሕዝብ እነዚህ “ክልክል” የሆኑ ጽሑፎች ምን እንደያዙ ለማወቅ ጉጉት አድሮበት ነበር!
በሰሜናዊ ምሥራቅ ቪክቶሪያ በእኛ ስብከት ምክንያት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበለው የመጀመሪያው ሰው ሚልተን ጊብ ነው። ተመልሰን እስክንጎበኘው ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የተውንለትን የማኅበሩን ጽሑፎች በሙሉ አንድ በአንድ አነበባቸው። በአንዱ ጉብኝታችን ወቅት “እኔ አሁን ከደቀ መዛሙርቶችሽ አንዱ ነኝ” በማለት አስገረመን።
ምንም እንኳ በውሳኔው ብደሰትም “ሚልተን ከእኔ ደቀ መዛሙርት አንዱ ልትሆንም አትችልም” በማለት ሁኔታውን አብራራሁለት።
“እሺ፣ እንግዲያው ከራዘርፎርድ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነኝ” አለ
“አይደለም፣ ከራዘርፎርድ ደቀ መዛሙርት አንዱም አይደለህም። ከዚህ ይልቅ ከክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱ እንደምትሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ስል ገለጽኩለት።
ሚልተን ጊብ ለብዙ ዓመት ስፈልጋቸው ከነበሩት የከበሩ ማዕድኖች አንዱ ሆነ። እሱና ሁለት ወንዶች ልጆቹ የጉባኤ ሽማግሌዎች ናቸው። እንዲሁም ሌሎቹ የቤተሰቡ አባሎች በጉባኤው ውስጥ ትጉህ አስፋፊዎች ናቸው።
የተለያዩ ፈተናዎችን ማሸነፍ
ምንም እንኳን በጥር 1941 በአውስትራሊያ በሚገኙት በይሖዋ ምስክሮች ሥራ ላይ እገዳ ቢደረግም መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ በመጠቀም መስበካችንን ቀጠልን። ከዚያም በጠና የታመመውን አባቴን ለማስታመም ወደቤት በተጠራሁ ጊዜ አቅኚነቴ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴ ተቋረጠ። በኋላ እኔም ታመምኩና ከባድ የሆነ ቀዶ ሕክምና አስፈለገኝ። ወደተሻለ ጤንነት ለመመለስ ጊዜ ወስዶብኝ ነበር። ይሁን እንጂ አምላክ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” ሲል የገባው ቃል በኔ ላይ ተፈጽሞ ተመልክቻለሁ። (ዕብራውያን 13:5) አንዲት ክርስቲያን እኅት “ፍሎ ምን ጊዜም ብቻሽን አትሆኝም። ይሖዋ ምን ጊዜም ከአንቺ ጋር ነው” ስትል አጽናናችኝ።
ከዚያም የምወደው አባቴ ለ13 ሳምንታት ታመመ። ሐምሌ 26, 1946 በሞት ዓይኖቹን ከደነ። አባቴ ጥሩ ሕይወት አሳልፏል። ሰማያዊ ተስፋም ነበረው። (ፊልጵስዩስ 3:14) ስለዚህ አብዛኛውን የልጅነት ሕይወቴን ከአባቴ ጋር ካሳለፍኩ በኋላ በ51 ዓመቴ ብቻዬን ቀረሁ። ከዚያም ባል የሚሆነኝን አገኘሁ። በ1947 ተጋባንና አብረን አቅኚነት ጀመርን። ይሁን እንጂ ይህ አስደሳች ወቅት ለረጅም ጊዜ አልዘለቀም። በ1953 ባለቤቴ ደሙ በአንጎሉ ውስጥ በመፍሰሱ ሽባ ሆነ።
የባለቤቴ የመነጋገር ችሎታ በጣም ስለተነካ ከእሱ ጋር መነጋገር ምንም የማይቻል ሆነ። እሱን ማስታመሙን በጣም አስቸጋሪ የሚያደርገው ይህ ነበር። እሱ ለመናገር በሚታገልበት ጊዜ ሐሳቡን ለመረዳት መጣር የሚያስከትለው የአእምሮ ጭንቀት በእርግጥ ቀላል አልነበረም። ምንም እንኳን በአቅራቢያው ምንም ጉባኤ በሌለበት ገለልተኛ አካባቢ የምንኖር ቢሆንም በእነዚህ ፈታኝ ዓመታት ወቅት ይሖዋ ብቻችንን አልተወንም። አዳዲስ የሆኑ ድርጅታዊ ትምህርቶችን በንቃት እከታተል ነበር። እንዲሁም በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች አማካኝነት የሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ አልተቋረጠብኝም። ታኅሣሥ 29, 1957 ውድ ባለቤቴ አረፈ።
በአድሌይድ ማገልገል
አሁንም ብቻዬን ቀረሁ። ከእንግዲህ በኋላ ምን ላደርግ ነው? አምስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ ካቋረጥኩ በኋላ በሙሉ ጊዜ ለማገልገል ተቀባይነት አገኝ ይሆን? ተቀባይነት አገኘሁ፤ ስለዚህ ቤቴን ሸጥኩና የደቡብ አውስትራሊያ ዋና ከተማ በሆነችው በአድሌይድ የአቅኚነትን ሥራ እንደ አዲስ ጀመርኩ። በወቅቱ በዚያ ቦታ አቅኚዎች ይፈለጉ ነበር። እኔም ፕሮስፔክት በተባለው ጉባኤ ውስጥ እንዳገለግል ተመደብኩ።
በጣም መኪና በሚበዛበት ከተማ ውስጥ መንዳት እፈራ ስለነበረ መኪናዬን ሸጥኩና በብስክሌት መጠቀም ጀመርኩ። 86 ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ በብስክሌት እጠቀም ነበር። በዚህም ምክንያት በአካባቢው “ሰማያዊ ብስክሌት የምትነዳው ትንሿ ሴት” በመባል ታወቅሁ። ከጊዜ በኋላ መኪና በሚበዛበት አካባቢ ስደርስ መፍራት ጀመርኩ። የብስክሌቴ የፊት ጎማ ያለማቋረጥ ይንቀጠቀጥ ጀመር። ብዙ መጥፎ ሁኔታዎች ካጋጠሙኝ በኋላ ለመጨረሻ ጊዜ ብስክሌት መንዳት ተስፋ ያስቆረጠኝ አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ አንድ የአትክልት አጥር ውስጥ መውደቄ ነው። ‘ከእንግዲህ በቃ’ ስል ለራሴ ተናገርኩ። ስለዚህ በእግሬ መጓዝ ጀመርኩ።
ከጥቂት ዓመታት በፊት የወረዳ ስብሰባ እየተካፈልኩ ሳለሁ እግሮቼ መዛል ጀመሩ፤ ከጊዜ በኋላ ወገቤ ላይ ባሉት መጋጠሚያዎች ሁለት ቀዶ ሕክምና ተደረገልኝ። አንድ ትልቅ ውሻ ገፍትሮ እስከጣለኝ ድረስ ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ተሽሎኝ ነበር። ይህም ሌላ ሕክምና እንዲደረግልኝ አስፈለገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ወዲያ ወዲህ ለመንቀሳቀስ የሚረዳ ድጋፍ አስፈለገኝ። አእምሮዬ አሁንም ንቁ ነው። አንዲት ጓደኛዬ “ያረጀው ሰውነትሽና የወጣትነት አስተሳሰብሽ አብሮ አይሄድም” ስትል እንደተናገረችው ነው።
ከጊዜ በኋላ በአድሌይድ የሚገኙ ጉባኤዎች ሲያድጉ፣ ሲሰፉና ሲከፈሉ ተመልክቻለሁ። ከዚያም በ1983 ይኸውም 88 ዓመት ሲሆነኝ በቪክቶሪያ ግዛት ውስጥ በምትገኘው በኪያብራም ከተማ ከሚገኝ አንድ ቤተሰብ ጋር ለመኖር ከአድሌይድ ሄድኩ። በዚያም አሥር አስደሳች ዓመታት አሳለፍኩ። አሁንም ወደ መስክ አገልግሎት መውጣት እችላለሁ። ዘወትር ከእኔ መጽሔት የሚወስዱትን ሰዎች እንዳነጋግራቸው በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እኅቶች በመኪና ይዘውኝ ይሄዳሉ። ሰዎቹም መኪናው ድረስ መጥተው ያነጋግሩኛል።
ከ98 ዓመት በላይ ያሳለፍኩትን ሕይወት መለስ ብዬ ሳሰላስል ምን ጊዜም በታማኝነት በመቆም ከእኔ ጋር ይሖዋን ያወደሱትን ሁሉ በፍቅር አስባቸዋለሁ። በተለይ በጣም ግሩም የነበረውን አባቴን አስታውሰዋለሁ። በአቅኚነት አገልግሎት አብረውኝ ሲያገለግሉ የነበሩት ታማኝ ወንድሞችና እኅቶች ሁሉ ሲሞቱ እኔ ብቻ ቀረሁ። ይሁን እንጂ በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት የሕይወት ሽልማት ተካፋይ የመሆን ተስፋ ካላቸው ጋር እንደገና የመገናኘት በጣም ትልቅ ደስታ ይጠብቀኛል። ይህም ዋጋው እጅግ የላቀ ሀብት ነው!
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የተጠመቅኩት ሚያዝያ 22, 1919 ነበር
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዕድሜዬ ወደ 100 ዓመት በተጠጋበት ባሁኑ ጊዜ ይሖዋን እያገለገልኩ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ