የአምላክን ፈቃድ እያደረግህ ነውን?
ሁለት የይሖዋ ምስክሮች ከቤት ወደ ቤት በሚያገለግሉበት ጊዜ የኤጲስቆጶሳውያን ቤተ ክርስቲያን ቄስ ከሆነ አንድ ሰው ጋር ተገናኙ። ይህ ሰው በ60 ዓመት ዕድሜ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ደስ የሚል ቁመና ያለውና ጺሙን ያሳደገ ሰው ነበር። የቤተ ክርስቲያኑ ስም የተጻፈበት ካናቴራ ለብሷል። በአንድ ትንፋሽ “የቤተ ክርስቲያናችን አባሎች ቃሉን በማዳረስ በኩል እንደ እናንተ ያለ ቅንዓት ያላቸው ቢሆኑ እመኝ ነበር፤ ቢሆንም ሁለተኛ ቤቴ እንዳትመጡ እጠይቃችኋለሁ” አለ።
አዎን፣ የይሖዋ ምስክሮችን ሥራ የሚያደንቁና ስለ ቅንዓታቸውና ስለ ግለታቸው የሚያመሰግኗቸው ብዙ ሰዎች አሉ። ሆኖም ምስክሮቹ በሚሠሩት ሥራ ምንም ዓይነት ፍላጎት የላቸውም። በሥራውም ለመካፈል አይፈልጉም። ይሁን እንጂ ይህን የመሰለው እርስ በርሱ የሚጋጭ አቋም አዲስ አይደለም። ኢየሱስ በዘመኑ በነበሩት ሰዎች ዘንድ ይህን የመሰለ አቋም እንደነበረ ተገንዝቦ ነበር። ይህንንም ነጥብ ለማስገንዘብ ሲል አእምሮ በሚቀሰቅስ ምሳሌ ተጠቅሟል።
“ነገር ግን ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት፤ ወደ አንደኛው ቀርቦ፦ ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ሂድና በወይኔ አትክልት ሥራ አለው። እርሱም መልሶ፦ አልወድም አለ፤ ኋላ ግን ተጸጸተና ሄደ። ወደ ሁለተኛውም ቀርቦ እንዲሁ አለው እርሱም መልሶ፦ እሺ ጌታዬ አለ፤ ነገር ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ ያደረገ ማን ነው?”—ማቴዎስ 21:28–31
መልሱ ግልጽ ነው። ኢየሱስን ያዳምጡ እንደ ነበሩት ሰዎች “ፊተኛው” ብለን እንመልሳለን። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ግልጽ ከሆነው የምሳሌው ትርጉም በስተጀርባ ሊያስገነዝበን የፈለገው በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር የአባቱን ፈቃድ ማድረግ መሆኑን ነው። ሁለተኛው ልጅ ለመሄድ አልፈልግም ቢልም በኋላ ግን ሄዶ ስለ ሠራ ተመስግኗል። ትክክለኛውን ዓይነት ሥራ መሥራትም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። ሁለተኛው ልጅ በአባቱ የወይን አትክልት ቦታ ሠራ እንጂ ወደ ራሱ የወይን አትክልት ሄዶ አልሠራም።
ይህ ሁሉ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? አምላክ ከዛሬዎቹ አምላኪዎቹ ምን ይፈልግባቸዋል? ከኢየሱስ ሕይወት የአባቱን ፈቃድ እንድናደርግ የሚረዳ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን? እነዚህ በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች ናቸው። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለም” ስለሚኖር የእነዚህን ጥያቄዎች ትክክለኛ መልስ ማወቅ የዘላለም ደህንነት ያስገኝልናል።—1 ዮሐንስ 2:17፤ ኤፌሶን 5:17
“የአምላክ ፈቃድ” ምንድን ነው?
“ፈቃድ” የሚለው ስም በአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ኮምፕርሄንሲቭ ኮንኮርዳንስ ውስጥ ከ80 ጊዜ በላይ ተዘርዝሯል። ከእነዚህ ውስጥ 60 በሚያክሉት ቦታዎች ላይ (ወይም 75 በመቶ በሚያክሉት) ቃሉ የሚያመለክተው የአምላክን ፈቃድ ነው። “የአምላክ ፈቃድ” እና “የአባቴ ፈቃድ” እንደሚሉት ያሉ ሐረጎች ከ20 ጊዜ በላይ ተጠቅሰዋል። ከዚህ መረዳት እንደምንችለው መለኮታዊው ፈቃድ በሕይወታችን የመጀመሪያ ቦታ ሊሰጠው ይገባል። በሕይወታችን ውስጥ በዋነኛነት ሊያሳስበን የሚገባው የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችን መሆን አለበት።
በእንግሊዝኛ ቋንቋ “ፈቃድ” [“ዊል”] የሚለው ስም ‘ምኞት፣ ቁርጥ ውሳኔ፣ ፍላጎት፣ የሚፈለግ ነገር፣ በተለይም ሥልጣን ወይም ኃይል ባለው ግለሰብ የሚደረግ ምርጫ ወይም ቁርጥ ውሳኔ ነው። ስለዚህ የሥልጣን ሁሉ ምንጭ የሆነው ይሖዋ አንድ ፈቃድ፣ ምኞት ወይም ቁርጥ ውሳኔ አለው። ይህ ፈቃድ ምንድን ነው? ‘ከአምላክ ፈቃድ አንዱ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና ትክክለኛ የእውነት እውቀት እንዲያገኙ’ እንደሆነ ቅዱሳን ጽሑፎች ይገልጻሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ኢየሱስ ክርስቶስና የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ይህን ትክክለኛ እውቀት ለሌሎች ለማድረስ በሙሉ ነፍሳቸው ጥረዋል።—ማቴዎስ 9:35፤ ሥራ 5:42፤ ፊልጵስዩስ 2:19, 22
በዛሬው ጊዜ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው? የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን ከሚሉት ወደ 2 ቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል በኢየሱስ ምሳሌ ውስጥ የአባቱን ፈቃድ እንዳደረገው ታናሽ ልጅ ያደረጉት ስንቶቹ ናቸው? መልሱን ማግኘት አያስቸግርም። እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ፈለግ ተከታዮች ይሠሩታል ብሎ የተናገረለትን ሥራ የሚሠሩ፣ ማለትም “አስቀድሞም ወንጌል ለአሕዛብ ሁሉ ይሰበክ ዘንድ ይገባል” የሚለውን ትእዛዙን የሚፈጽሙ መሆን አለባቸው። (ማርቆስ 13:10) በዓለም ዙሪያ ከአራት ሚልዮን ተኩል የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምስክሮች ሰላምና አስተማማኝ ኑሮ የሚመጣው የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ በሆነችው መንግሥት አማካኝነት እንደሆነ በማመልከት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በትጋት በመስበክና በማስተማር ላይ ይገኛሉ። የአምላክን ፈቃድ በማድረጉ ረገድ ሙሉ ተሳትፎ አለህን? ኢየሱስ እንዳደረገው የመንግሥቱን ምሥራች ትሰብካለህን?—ሥራ 10:42፤ ዕብራውያን 10:7
የአምላክን ፈቃድ በማድረግ መደሰት
የአምላክን ፈቃድ ማወቅ ደስታ የሚያስገኝ ቢሆንም ሌሎች ሰዎች ስለ አምላክ ፈቃድ እንዲያውቁ ማስተማር ከዚያ የሚበልጥ ደስታ ያስገኛል። ኢየሱስ ሰዎችን ስለ አባቱ ፈቃድ ማስተማሩ ደስታ አስገኝቶለታል። እንደ ምግብም ሆኖለት ነበር። (ዮሐንስ 4:34) እኛም ኢየሱስ እንዳደረገው ብናደርግ ማለትም ኢየሱስ ከአባቱ ተቀብሎ ያስተማራቸውን ነገሮች ብንሰብክና ብናስተምር እውነተኛ ደስታ እናገኛለን። (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ “ይህን ብታውቁ ብታደርጉትም ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] ናችሁ” በማለት የተናገረው ተስፋ ይፈጸምልናል።—ዮሐንስ 13:17
ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ በቅርቡ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት የተመለሰች አንዲት እናት እንዲህ ብላለች፦ “አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ልቡን ሲነኩትና ከዚህም የተነሣ ፊቱ ሲፈካ ማየት በጣም ያስደስታል። በተለይ አንድ ጥናቴ ከጥናታችን በፊት ጥቅሶቹን ሁሉ ጽፋ ስትመጣና በክለሳ ጥያቄዎቹ ወቅት ደግሞ መልስ ለመስጠት እንዲረዳት በጥናቱ ወቅት ማስታወሻ ስትጽፍ ማየቴ በጣም ያስደስተኛል።” ሌላዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዋ በልጅነቷ ማለትም ከ13 እስከ 16 ዓመት ዕድሜ በነበረችበት ጊዜ እውነትን ታጠና የነበረች ናት። አሁን አግብታ አንዳንድ የግል ችግሮች ስለገጠሟት ምስክሮቹን ለማግኘት በጣም ትናፍቅ ነበር። ይህች አቅኚ እኅት ስታገኛት እንዴት ተደሰተች! ሴትየዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን እንደገና ለመጀመር በመቻሏ እጅግ ተደሰተች።
የአምላክን ፈቃድ ከማድረግ የሚገኘውን ደስታ ጠብቆ ማቆየት
በጥንቷ እስራኤል ይኖር የነበረው ንጉሥ ዳዊት በሕይወቱ ሁሉ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ የጣረ ሰው ነበር። በእርሱ ላይ ብዙ አስቸጋሪ ሁኔታዎችና ተጽዕኖዎች የደረሱበት ቢሆንም “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፣ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” ብሎ እንዲናገር በመንፈስ አነሣሽነት ተገፋፍቶ ነበር። (መዝሙር 40:8) የይሖዋን ፈቃድ የማድረግ ጉዳይ በዳዊት ሁለንተና ማለትም በነፍሱ ሁሉ ውስጥ ነበር። ይሖዋን ከማገልገል ያገኝ የነበረው ደስታ አንድም ጊዜ ያልተቀነሰበት ምሥጢር ይህ ነበር። የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ለዳዊት አስቸጋሪ ነገር አልነበረም። ከዚህ ይልቅ፣ ዘወትር የሚያስደስተውና ከልቡ የሚመነጭ ነገር ነበር። ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ኃጢአት ቢሠራና ድክመት ቢያሳይም በሕይወቱ ሁሉ አምላኩን ይሖዋን ለማገልገል የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ታግሏል።
አንዳንድ ጊዜ ደስታችን ሊቀንስብን ይችላል። ልንደክም ወይም ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ምናልባትም ከዚህ በፊት ያደረግናቸው ስሕተቶች ድቅን እያሉ ያስቸግሩን ይሆናል። ባለፉት ጊዜያት የፈጸምናቸው የስሕተት ድርጊቶች የሕሊና መረበሽ ያስከትሉብን ይሆናል። ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ያሉትን ስሜቶች የአምላክን ቃል ይበልጥ በማጥናት ማሸነፍ ይቻላል። ዳዊት እንዳደረገው የአምላክን ሕግ በእኛ “ውስጥ” ለመቅረጽ መጣር ይኖርብናል። የአምላክን ፈቃድ ባለን ችሎታ ሁሉ በሙሉ ነፍስ ለማድረግ የምንሞክር ከሆነ እርሱ ታማኝ ስለሆነ የሚገባንን ዋጋ ይሰጠናል።—ኤፌሶን 6:6፤ ዕብራውያን 6:10–12፤ 1 ጴጥሮስ 4:19
ሐዋርያው ጳውሎስ በመዝሙር 40:6–8 ላይ የሚገኙት የዳዊት ቃሎች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ እንደ ተፈጸሙ በዕብራውያን 10:5–7 ላይ መጥቀሱን ማስተዋል ይገባል። በዚህም ኢየሱስ ከአባቱ ጋር ምን ያህል ቅርበት እንደነበረው አመልክቷል። “ፈቃድ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ‘ደስታ፣ ምኞት፣ ሞገስ ወይም ፍስሐ’ የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ስለዚህ ስለ ክርስቶስ የሚናገረው መዝሙር 40:8 “አምላኬ ሆይ፣ ደስ የሚያሰኝህን ነገር ለማድረግ ወደድሁ” ተብሎ ሊነበብ ይችላል።a ኢየሱስ አባቱ የሚደሰትበትን ነገር ለማድረግ ፈልጎ ነበር። ኢየሱስ ያደረገው ከእሱ የሚጠበቀውን ብቻ አልነበረም። የአባቱን ልብ ደስ የሚያሰኘውን ሁሉ አድርጓል። ይህን በማድረጉም ተደስቷል።
የኢየሱስ ሕይወት ሌሎች ሰዎች የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ እንዲያውቁና የአምላክን በረከቶች ለማግኘት ምን ማድረግ እንደሚኖርባቸው በማስተማር ላይ ያተኮረ ነበር። የሙሉ ጊዜ ሰባኪና አስተማሪ በመሆንና ይህንንም ሥራ በመሥራት ታላቅ ደስታ አግኝቷል። ስለዚህ የይሖዋን ሥራ በብዛት በሠራን መጠን ብዙ ደስታ እንደምናገኝ የታወቀ ነው። አንተስ፣ ደስታህ እንዲበዛልህ በስብከቱ ሥራ ሙሉ ጊዜ ልታገለግል ትችላለህን?
የአምላክን ፈቃድ በማድረግ የምናገኘውን ደስታ ጠብቀን ለማቆየት የሚረዳን ሌላው ነገር የወደፊቱን ጊዜ በትኩረት መመልከት ነው። ኢየሱስ ያደረገው ይህንን ነበር። ‘እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱ ስላለው ደስታ በመከራ እንጨት ታገሠ።’ እርሱ እንደ ታላቅ ደስታ ይቆጥረው የነበረው እስከ መጨረሻው ለአምላክ በታማኝነት መቆምንና ንጉሥ ሆኖ በአባቱ ቀኝ የመቀመጥ ሽልማቱን ማግኘት ነበር።—ዕብራውያን 12:2
የአምላክን ፈቃድ ማድረጋቸውን የሚቀጥሉ ሰዎች ሁሉ ወደፊት የሚያገኙትን ደስታ እስቲ አስብ! የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ጥረት በሚያደርጉት ላይ መከራ የሚያመጣባቸው ቢሆንም የራሳቸውን ፈቃድ ብቻ በማድረግ የሚቀጥሉ ሰዎች ሲጠፉ ይመለከታሉ። (2 ተሰሎንቄ 1:7, 8) የምናፈቅራቸው ሰዎች ከሞት ተነሥተው የአምላክን ፈቃድ የመማርና የማድረግ አጋጣሚ ሲያገኙ የሚኖረውን ደስታ አስብ። ወይም ምድርን ወደ ገነትነት የሚለውጠውን የአምላክን ዓላማ መመልከት ይቻላል። በመጨረሻም የይሖዋ ፈቃድ ተቃዋሚ የሆነው ሰይጣን ሙሉ በሙሉ ሲጠፋ የሚገኘውን ነፃነት በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት።
አዎን፣ በዛሬው ጊዜ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ አሁንም ሆነ ወደፊት ፍጻሜ የሌለው ደስታ ሊያመጣ ይችላል። ሰዎች በስብከቱ ሥራችን ምንም ዓይነት አቀባበል ቢያሳዩ የአባቱን ፈቃድ በማድረግ ይደሰት የነበረውን ኢየሱስን እንምሰል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በመዝሙር 40:8 ላይ ያለውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።