የይሖዋ ምስክሮች በዓለም ዙሪያ ባሃማስ
የባሃማስ የጋራ ብልጽግና በፍሎሪዳና በኩባ መካከል በሚገኘው ወደ ሰማያዊ የሚያደላ አረንጓዴ ቀለም ባለው ባሕር ላይ ከዛጎል የተሠራ የአንገት ሀብል መስለውና በ900 ኪሎ ሜትር ርዝመት ላይ ተደርድረው ያሉ 3,000 ትልልቅና ትንንሽ ደሴቶች የተሰበሰቡባት አገር ናት። በአገሪቱ 267,000 ነዋሪዎች መካከል ቁጥሩ እየጨመረ የሚሄድ አንድ የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የመዘምራን ቡድን አለ። የዚህ ቡድን የውዳሴ መዝሙር ኢሳይያስ 42:10–12ን ያስታውሰናል፦ “ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርስዋም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፣ ደሴቶችና በእነርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፣ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ። . . . በተራሮችም ራስ ላይ ሆነው ይጩኹ። ለእግዚአብሔር ክብርን ይስጡ፣ ምስጋናውንም በደሴቶች ይናገሩ።”
አዲሱ እምነት ፈተና ደረሰበት
በሐምሌ 1992 አንድ የዘወትር አቅኚ (የመንግሥቲቱ የሙሉ ጊዜ ሰባኪ) በሥጋዊ ሥራው በአጋጣሚ ለሚያውቀው ሰው በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዳ መጽሐፍ አበረከተለት። ሰውየው መጽሐፉን ካነበበው በኋላ ‘ይህን ሃይማኖት መመርመር ይገባኛል’ ሲል አሰበ። በሚቀጥሉት ሁለት እሁዶች በሁለት የተለያዩ የይሖዋ ምስክሮች የመንግሥት አዳራሾች በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ ተገኘ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። ሆኖም ጥናት ከጀመረ ገና ወር ከአሥራ አምስት ቀን እንደሆነው አዲሱ እምነቱ ፈተና ደረሰበት። የልደት በዓል የማክበር ፈተና አጋጠመው።
የዚህ ነጋዴ ቤተሰብ እንዲህ ዓይነት በዓላትን የማክበር ልማድ ነበረው። እርሱ ግን ለአምላክ ቃል ፍቅር ስለነበረው በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ገፋበት። ስለ ቅዱስ ጽሑፋዊው እውነት ያለው እውቀት እየጨመረ ሲሄድ ይሖዋ ስለ ልደትና ስለ ሌሎች ዓለማዊ በዓላት ምን አመለካከት እንዳለው የበለጠ ተረዳ።
የሰውየው ሚስት ፋዘርስ ዴይ (የአባት ቀን) ለሚባል በዓል ድግስ ደገሰች። እርሱ ግን በድግሱ ላይ እንደማይገኝ በትሕትና ገለጸላት። ሆኖም እሷን የጠላትና አዲሱን ሃይማኖቱን ከእርሷም ሆነ ከቤተሰቡ የሚያስበልጥ መሰላት። እርሱም ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚማረውን ነገር ሥራ ላይ ማዋሉ የተሻለ ባልና አባት እንዲሆን እየረዳው መሆኑን በደግነት አስረዳት። እያደር በቅዱስ ጽሑፉ ውስጥ ለሚገኘው እውነት ያለውን ፍቅር ተገነዘበችና መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማች። አሁን ለቤተሰቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ይመራል። “መለኮታዊ ትምህርት” በተባለው በአምናው የወረዳ ስብሰባ ላይ በጣም የተደሰተበትን እርምጃ ወሰደ። በዚህ ስብሰባ ላይ ሲጠመቅ ሚስቱና ልጆቹ ተገኝተው ተመልክተውታል።
ከሌሎች አገሮች የመጡ ሰዎች አዲሱን መዝሙር ሰሙ
ከሃይቲ የመጡ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከባሃማ ኅብረተሰብ ጋር መቀላቀል ጀምረዋል። እነሱም ስለ መንግሥቲቱ እውነት የሚገልጸውን አዲስ መዝሙር መስማት ያስፈልጋቸዋል። በባሃማስ ውስጥ የሚኖሩ የይሖዋ ምስክሮች የሃይቲና የአሜሪካ ክልሶች የሆኑ ሁለት ባልና ሚስቶች ወደ ባሃማስ በመምጣታቸው ይሖዋን አመስግነዋል። እነዚህ ባልና ሚስት በግራንድ ባሀማና በአባኮ የተቋቋሙትን የሃይቲ ተወላጆች አዳዲስ ቡድኖች ለማጠናከር እርዳታ እያበረከቱ ናቸው።
ለመጀመሪያ ጊዜ በባሃማስ ውስጥ ከሐምሌ 31 እስከ ነሐሴ 1, 1993 ድረስ ብዙ የሃይቲ ተወላጆች በሚናገሩት በክሬዎል ቋንቋ የወረዳ ስብሰባ መደረጉ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ላሳዩ የሃይቲ ተወላጆች ተጨማሪ እርዳታ አበርክቷል። 214 ተሰብሳቢዎች የተገኙ ሲሆን ራሳቸውን የወሰኑ ሦስት አዳዲስ ሰዎች ተጠምቀዋል። እውነትን በባሃማስ ውስጥ የሰሙ ብዙ የሃይቲ ተወላጆች ከዚያ በኋላ ወደ ትውልድ ደሴታቸው ተመልሰዋል፣ ወይም በአገሩ ውስጥ ካሉ ምስክሮች ጋር ተባብረው ለይሖዋ ውዳሴ ለመዘመር ወደሚችሉባቸው ሌሎች ቦታዎች ተዛውረዋል።
[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሣጥን8]
የ1993 የአገልግሎት ዓመት
የአገሪቱ ሪፖርት መግለጫa
የምስክሮቹ ከፍተኛ ቁጥር፦1,294
የምስክሮቹ ቁጥር ከአገሩ ሕዝብ ብዛት ጋር ሲነፃፀር፦ 1 ምስክር ለ197 ሰዎች
በመታሰቢያው በዓል የተገኙ ተሰብሳቢዎች፦3,794
የአቅኚዎች ብዛት በአማካይ፦186
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብዛት በአማካይ፦1,715
የተጠማቂዎች ብዛት፦79
የጉባኤዎች ብዛት፦22
ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኝበት ቦታ፦ናሳው
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የ1994 የይሖዋ ምስክሮችን የቀን መቁጠሪያ ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የቅርንጫፍ ቢሮና የሚስዮናውያን ቤት የሚገኝበት የመጀመሪያው የመንግሥት አዳራሽ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምስክሮቹ ምሥራቹን በቅንዓት ያውጃሉ
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከ45 ዓመታት በፊት ሚልተን ጂ ሄንሸልና ናታን ኤች ኖር በናሳው ከሚገኙ ሚስዮናውያን ጋር
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የካቲት 8, 1992 የተመረቀው አዲሱ ቅርንጫፍ ቢሮ