አስደናቂዎቹ የጆሴፈስ የታሪክ ጽሑፎች
የታሪክ ተማሪዎች አስደናቂ በሆኑት የጆሴፈስ ጽሑፎች ላይ ረዘም ላሉ ጊዜያት ጥንቃቄ የተሞላበት ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል። ጆሴፈስ የተወለደው ክርስቶስ ከሞተ ከአራት ዓመት በኋላ ነበር። ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ስለነበረው የአይሁድ ብሔር የተናገረው አስፈሪ ትንቢት ሲፈጸም አይቷል። ጆሴፈስ የጦር አዛዥ፣ ዲፕሎማት፣ ፈሪሳዊና ምሁር ነበር።
የጆሴፈስ ጽሑፎች አእምሮን በሚመስጡ ዝርዝር ትረካዎች የተሞሉ ናቸው። የጳላስጢናን ምድር አቀማመጥና ጂኦግራፊያዊ ሁኔታ ለመረዳት የሚያስችሉ ሥነ ጽሑፎች ከመሆናቸውም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነተኝነት ያብራራሉ። ብዙዎች የጆሴፈስን ጽሑፎች እንደ ውድ ንብረት በመቁጠር በቤተ መጻሕፍቶቻቸው ማስቀመጣቸው አያስደንቅም።
የልጅነት ሕይወቱ
ጆሴፈስ ቤን ማትያስ ወይም ጆሴፈስ የተወለደው በሮማዊው ገዥ በካሊጉላ የመጀመሪያ የግዛት ዘመን በ37 እዘአ ነበር። የጆሴፈስ አባት ከካህናት ወገን ነበር። እናቱ መቃባዊ የነበረው የሊቀ ካህኑ የዮናታን ተወላጅ እንደነበረች ይነገራል።
ጆሴፈስ በልጅነት ዕድሜው የሙሴን ሕግ በትጋት አጥንቷል። ሦስቱን የአይሁድ ሃይማኖት ቡድኖች ማለትም ፈሪሳውያንን፣ ሰዱቃውያንንና የአይሁድ መነኮሳንት ማኅበርን በጥንቃቄ መርምሯል። ለመጨረሻው ቡድን ከፍተኛ ግምት በመስጠት በምድረበዳ ከሚኖር ባነስ ከተባለ ባህታዊ ጋር ለ3 ዓመት ለመኖር ወስኖ ነበር። ጆሴፈስ በ19 ዓመቱ ምንኩስናውን ትቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰና ፈሪሳዊ ሆነ።
ወደ ሮም ሄዶ ተመለሰ
ጆሴፈስ የአይሁድ ገዥ የነበረው ፈሊክስ እንዲፈረድባቸው ወደ ንጉሠ ነገሥት ኔሮ ልኳቸው ስለነበሩት የአይሁድ ካህናት ለማማለድ ሲል በ64 እዘአ ወደ ሮም ተጓዘ። ጆሴፈስ በመንገድ ላይ የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞት ስለነበር ከሞት የዳነው ለጥቂት ነበር። በመርከቡ ውስጥ ከነበሩት 600 መንገደኞች መካከል የተረፉት 80 ብቻ ነበሩ።
ጆሴፈስ ሮምን በሚጎበኝበት ጊዜ አንድ አይሁዳዊ ተዋናይ ከኔሮ ሚስት ከንግሥት ፓፔ ጋር አስተዋወቀው። እርሷም ለተልዕኮው መሳካት ቁልፍ ሚና ተጫውታለች። በሮም ቆይታው ጆሴፈስን በጣም ያስደነቀው ነገር የከተማዋ ውበት ነበር።
ጆሴፈስ ወደ ይሁዳ በተመለሰ ጊዜ አይሁዶች በሮም ላይ ለማመፅ ቆርጠው ተነሥተው አገኛቸው። እርሱም የአገሩን ሰዎች በሮም ላይ ጦርነት መክፈት ከንቱ መሆኑን ለማሳመን ሞክሮ ነበር። ግን ከድርጊታቸው ሊገታቸው ስላልቻለና ከዳተኛ እንዳይባል በመፍራት ይመስላል በገሊላ ላሉት የአይሁድ ወታደሮች አዛዥ እንዲሆን የቀረበለትን ሹመት ተቀበለ። ጆሴፈስ ሰዎቹን ሰብስቦ አሰለጠናቸው። ከሮም ወታደሮች ጋር ለሚደረገው ጦርነት አስፈላጊውን ስንቅና ትጥቅ እንዲያገኙም አደረገ፤ ሆኖም የተደረገው ጥረት ሁሉ መና ሆኖ ቀረ። ገሊላ በቬስፓዚየን ጦር እጅ ወደቀች። 47 ቀናት ከፈጀ ከበባ በኋላ በጆታፕታ የነበረው የጆሴፈስ ታላቅ ምሽግ ድል ተመታ።
ጆሴፈስ እጁን በሰጠበት ጊዜ ቬስፓዚየን በቅርቡ ንጉሠ ነገሥት እንደሚሆን በብልጠት ትንቢት ተናገረ። ለጊዜው ቢታሰርም በተናገረው ትንቢት ምክንያት ከቅጣት ዳነ። ጆሴፈስ የተናገረው ትንቢት በተፈጸመ ጊዜም ከእስር ተለቀቀ። ይህም ለሕይወቱ አዲስ ምዕራፍ ከፈተለት። በቀረው የጦርነቱ ጊዜ በአስተርጓሚነትና በአስታራቂነት ሮማውያንን አገልግሏል። ቬስፓዚየንና የቬስፓስየን ልጆች ቲቶና ዶሚሽያን ያደረጉለትን ውለታ ለማሳየት ሲል ፍላቭየስ የሚለውን የቤተሰቡን መጠሪያ የራሱ መጠሪያ እንዲሆን አደረገ።
የፍላቭየስ ጆሴፈስ ጽሑፎች
ከጆሴፈስ ጽሑፎች ሁሉ ጥንታዊው የአይሁዶች ጦርነት (ዘ ጂውሽ ዎር) የሚባለው ነው። ይህ ባለ ሰባት ጥራዝ የታሪክ መዝገብ የሮምን ጥንካሬ በጉልህ ለአይሁዶች ለማሳየትና ለወደፊቱ ዓመፅ እንዳይነሣ ለመከላከል ያዘጋጀው ነው ተብሎ ይታመናል። እነዚህ ጽሑፎች ኢየሩሳሌም በአንቶኒከስ ኢፒፋንስ (በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ) ከተያዘችበት አንስቶ እስከ 67 እዘአ የተነሣው ኃይለኛ ብጥብጥ ድል እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ ያለውን ታሪክ ይቃኛሉ። ጆሴፈስ የዓይን ምስክር ስለነበረ በ73 እዘአ ስላከተመው ጦርነት አብራርቶ ጽፏል።
ሌላው የጆሴፈስ ጽሑፍ የአይሁዶችን ታሪክ የያዘው የአይሁድ ጥንታዊ ታሪክ (ዘ ጂውሽ አንቲኩቲስ) የሚል ርዕስ ያለው ባለ 20 ጥራዝ መጽሐፍ ነው። ከፍጥረትና ከአይሁድ መጀመሪያ ታሪክ ጀምሮ ከሮም ጋር ጦርነት እስከ ከፈቱበት ጊዜ ድረስ ያለውን ታሪክ ያጠቃልላል። ጆሴፈስ ባህላዊ አተረጓጎሞችንና የውጭ አስተያየቶችን የጨመረ ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪክ ቅደም ተከተል በጥንቃቄ ተከትሏል።
ጆሴፈስ ሕይወት (ላይፍ) በሚል ርዕስ የግል ታሪኩን ጽፏል። በመጽሐፉ ውስጥ በጦርነቱ ወቅት ወስዶት የነበረው አቋም ተገቢ እንደነበረ ለማስረዳትና በጢባርዮሱ ጀስተስ የቀረበበትን ክስ ለማስተባበል ሞክሯል። አራተኛው ጽሑፉ ኤጌንስት አፒየን የተባለ ባለ ሁለት ጥራዝ መጽሐፍ ሲሆን በአይሁዶች ላይ ተገቢ ያልሆነ አመለካከት እንዳይኖር ያቀረበውን የመከላከያ ሐሳብ የያዘ ነው።
ስለ አምላክ ቃል ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡ ነጥቦች
አብዛኛው የጆሴፈስ ታሪክ ትክክለኛ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ኤጌንስት አፒየን በተባለው ጽሑፉ አይሁዶች በአምላክ መንፈስ አነሣሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አዋልድ መጻሕፍትን ያልጨመሩ መሆናቸውን ገልጿል። በመለኮት መሪነት የተጻፉት ጽሑፎች ትክክለኛ ለመሆናቸውና እርስ በእርስ ስላላቸው ስምምነት የምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል። ጆሴፈስ እንዲህ ይላል፦ “እርስ በእርስ የማይስማሙና አንደኛው ከሌላው የሚቃረኑ ቁጥር ስፍር የሌላቸው መጻሕፍት የሉንም። . . . ያሉን መለኮታዊ ምንጭ እንዳላቸው የሚታመንባቸውና ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙትን ታሪኮች የያዙ ሃያ ሁለት መጻሕፍት ብቻ [ዛሬ ካሉን ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከ39ኙ ጋር አንድ የሆኑት] ናቸው።”
ጆሴፈስ ዘ ጂውስ አንቲኩቲስ በተባለው መጽሐፉ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ ዘገባ ላይ አንዳንድ አስፈላጊ ዝርዝር መረጃዎችን ጨምሯል። አብርሃም ይስሐቅን መሥዋዕት ለማድረግ እግሩንና እጁን በሚያስርበት ጊዜ “ይስሐቅ ሃያ አምስት ዓመት ሆኖት ነበር” ይላል። እንደ ጆሴፈስ አባባል ይስሐቅ መሠውያውን በመሥራት አባቱን ከረዳ በኋላ “‘የአምላክንና የአባቴን ውሳኔ አልቀበልም ከምል . . . ቀድሞውኑ ባልወለድ ይሻለኛል’ ብሎ ወዲያውኑ ለመሠዋት ወደ መሠውያው ሄደ።”
የእስራኤል ሕዝብ ከጥንቷ ግብጽ በወጡበት ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ አስመልክቶ ቅዱስ ጽሑፉ በዘገበው ላይ ጆሴፈስ እነዚህን ዝርዝር ሁኔታዎች ጨምሯል፦ “እስራኤላውያንን ተከትለዋቸው የነበሩት ስድስት መቶ ሰረገሎች፣ አምሳ ሺህ ፈረሰኞችና ሁለት መቶ ሺህ እግረኞች ሲሆኑ ሁሉም የታጠቁ ነበሩ።” በተጨማሪም ጆሴፈስ “ሳሙኤል ትንቢት መናገር ሲጀምር አሥራ ሁለት ዓመቱ ነበር። አንድ ቀን ተኝቶ ሳለ አምላክ በስሙ ጠራው” ይላል።—ከ1 ሳሙኤል 3:2–21 ጋር አወዳድር።
ጆሴፈስ በሌሎች ጽሑፎቹ ላይ ስለ ቀረጦች፣ ስለ ሕጎችና ስለ አንዳንድ ክንውኖች ተጨማሪ እውቀት አንድናገኝ የሚያስችሉ መረጃዎች ሰጥቷል። ሄሮድስ ባዘጋጀው ግብዣ ላይ የዘፈነችውና በኋላም የአጥማቂው ዮሐንስ አንገት እንዲሰጣት የጠየቀችውን ሴት ስም ሰሎሜ ነበር ብሏል። (ማርቆስ 6:17–26) ስለ ሄሮድስ ቤተሰቦች የምናውቀው አብዛኛው ታሪክ ከጆሴፈስ ጽሑፎች የተገኘ ነው። ጆሴፈስ “[ሄሮድስ] በዕድሜ የገፋ መሆኑን ለመሸፈን ፀጉሩን ቀለም ይቀባ” እንደነበረ ሳይቀር ጠቅሷል።
ታላቁ ፀረ–ሮማውያን ዓመፅ
ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ቤተ መቅደሷ ተናግሮት የነበረው ትንቢት ከ33 ዓመት በኋላ መፈጸም ጀመረ። በኢየሩሳሌም የነበሩት ለውጥ ፈላጊ የአይሁድ ቡድኖች የሮማውያንን ቀንበር ሰባብረው የመጣል ፍላጎት አደረባቸው። የዚህ እንቅስቃሴ ወሬ ስለተሰማ በ66 እዘአ የሶርያ ገዥ በነበረው በሴስተስ ጋለስ በሚመራ የሮማ ሠራዊት በፍጥነት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲላክ ተደረገ። የጭፍሮቹ ተልዕኮ ዓመፀኞቹን ለመደምሰስና ጥፋተኛ ሆነው የተገኙትን ለመቅጣት ነበር። የሴስተስ ወታደሮች በኢየሩሳሌም ዳርቻ በነበሩት መንደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካደረሱ በኋላ በከተማዋ ዳርቻ ባለው ግንብ ዙርያ ሰፈሩ። ሮማውያኑ ወታደሮች የተጠቀሙበት ተስቱዶ የተባለው ጋሻዎቻቸውን እርስ በእርስ አገጣጥሞ እንደ ዔሊ በመሸፈን ከጠላት የመከላከል ስልት ጥሩ ውጤት አስገኝቶላቸው ነበር። ይህ ዘዴ ውጤታማ ስለመሆኑ ጆሴፈስ እንዲህ ይላል፦ “ይወረወሩ የነበሩት ፍላጻዎች ምንም ጉዳት ሳያደርሱባቸው ተንሸራትተው ይወድቃሉ፤ በዚህ ምክንያት ወታደሮቹ ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ግንቡን ሰርስረው ገብተው በቤተ መቅደሱ በር በኩል እሳት ለመለኮስ የሚያስችሏቸውን ሁኔታዎች ሁሉ አመቻቹ።”
ጆሴፈስ “ይህ ከሆነ በኋላ ሴስተስ . . . ያለምንም በቂ ምክንያት ወታደሮቹ ወደ ኋላቸው እንዲመለሱ ጥሪ አደረገ” ሲል ይናገራል። ጆሴፈስ የአምላክን ልጅ ከፍ ከፍ ለማድረግ ባያስብም በኢየሩሳሌም የነበሩት ክርስቲያኖች ሲጠባበቁት የነበረው ሁኔታ በትክክል መፈጸሙን መዝግቧል። ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙ ነበር! አዎን፣ ከብዙ ዓመታት አስቀድሞ የአምላክ ልጅ እንዲህ ሲል አስጠንቅቆ ነበር፦ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋቷ እንደ ቀረበ እወቁ። በዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ፤ የተጻፈው ሁሉ እንዲፈጸም ይህ የበቀል [የፍርድ አዓት] ጊዜ ነውና።” (ሉቃስ 21:20–22) የኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች ልክ እንዳዘዛቸው በፍጥነት በመሸሽ ከከተማዋ ርቀው ወጡ። ይህን ማድረጋቸው ቆይቶ በከተማዋ ላይ ከደረሰው አሰቃቂ ሁኔታ እንዲድኑ አስችሏቸዋል።
ጆሴፈስ በ70 እዘአ ሮማውያን ወታደሮች ተመልሰው በመጡ ጊዜ የተከሰቱትን ሁኔታዎች ግልጽ በሆነ መንገድ በዝርዝር መዝግቧል። ታላቁ የቬስፓዚየን ልጅ ጄኔራል ቲቶ ኢየሩሳሌምንና ዕጽብ ድንቅ የሆነውን ቤተ መቅደሷን ድል አድርጎ ለመያዝ መጣ። በከተማው ውስጥ የነበሩ የተለያዩ ቡድኖች የበላይነት ለማግኘት እርስ በእርስ ይዋጉ ነበር። ባለ በሌለ ኃይላቸው በመጠቀማቸው ብዙ ደም ፈሰሰ። ጆሴፈስ አንዳንዶች “ብዙ ስቃይ ካስከተለባቸው የእርስ በእርስ ግጭት ለመገላገል ሲሉ ሮማውያን መጥተው እንዲወሯቸው ይመኙ ነበር” ብሏል። በከተማዋ ውስጥ ያለውን ሀብትና ንብረት የሚያወድሙትንና ከሮማውያን ጋር ስምምነት አድርገዋል ብለው የጠረጠሯቸውን ትልልቅ ቦታ የነበራቸው ሰዎች የሚገድሉትን ተዋጊ ኃይሎች “ቀማኞች” ሲል ጠርቷቸዋል።
በተደረገው የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት በኢየሩሳሌም የነበረው የኑሮ ሁኔታ ሊገመት ወደማይችል አዘቅት ወደቀ። ከተማይቱም በሬሳ ቁልል ተሞላች። ሕዝቡን ያነሣሱ የነበሩት ቡድኖች ራሳቸው “በከመሯቸው ሬሳዎች ላይ እየተረማመዱ እርስ በእርስ ይዋጉ ነበር።” ምግብና ሀብት ለመቀማት ብለው ሕዝቡን ይዘርፉና ይገድሉ ነበር። የተገፉት ሰዎች ጩኸት የማያቋርጥ ሆኖ ነበር።
ቲቶ አይሁዶች ከተማውን አሳልፈው እንዲሰጡትና ራሳቸውን እንዲያድኑ ጥረት አድርጎ ነበር። ቲቶ “ከራሳቸው አገር ሰው ጋር ይበልጥ ይግባቡ ይሆናል ብሎ በማሰብ በራሳቸው ቋንቋ እንዲያነጋግራቸው ጆሴፈስን ልኮት ነበር።” እነርሱ ግን ጆሴፈስን ነቀፉት እንጂ አልተቀበሉትም። ከዚያ ቀጥሎ ቲቶ በከተማዋ ዙርያ ረጅም ቅጥር ሠራ። (ሉቃስ 19:43) ሊያመልጡ በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ወደቁ። እንቅስቃሴያቸውም ውስን ሆነ። ረሃብ “በሁሉም ቤተሰቦችና ቤቶች ያሉትን ሰዎች ጨረሰ።” ባልተቋረጠው ጦርነት የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሄደ። ቲቶ የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢት በመፈጸም ላይ እንዳለ ባይታወቀውም ኢየሩሳሌምን ድል አድርጎ ያዘ። ቲቶ የኢየሩሳሌምን ሰማይ ጠቀስ ጠንካራ ግንቦች ካየ በኋላ “አይሁዶችን ከአምላክ ሌላ ማንም ከዚህ ጠንካራ ግንብ ሊያወጣቸው የሚችል ኃይል አይኖርም ነበር” ሲል በመደነቅ ተናግሯል።—ሉቃስ 21:5, 6, 23, 24
ከጦርነቱ በኋላ
ከጦርነቱ በኋላ ጆሴፈስ ወደ ሮም ሄደ። የፍላቭየስ ቤተሰቦች ባደረጉለት ድጋፍ ሮማዊ ዜግነት አግኝቶ የንጉሠ ነገሥቱ ጡረተኛ በመሆን የጡረታ አበል እያገኘና ከቲቶ ዳረጎት እየተቀበለ የቬስፓዚየን የቀድሞ መኖሪያ በነበረው ትልቅ ቤት መኖር ጀመረ። ከዚያ በኋላ ጆሴፈስ በሥነ ጽሑፍ ሥራው ላይ አተኮረ።
ከሁኔታው በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው “ቲኦክራሲ” የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመበት ጆሴፈስ መሆኑን ማስተዋል ይገባል። የአይሁድን መንግሥት በተመለከተ “መንግሥታችን . . . ሥልጣንና ኃይል ያገኘው ከአምላክ በመሆኑ ቲኦክራሲ ተብሎ ሊጠራ ይችላል” በማለት ጽፏል።
ጆሴፈስ ክርስቲያን ነኝ ብሎ አያውቅም። ጽሑፎቹንም የጻፈው በአምላክ መንፈስ ተነሣስቶ አልነበረም። ሆኖም በአስደናቂዎቹ የጆሴፈስ ታሪካዊ ዘገባዎች ውስጥ የሚገኙት ምሁራዊ ማብራሪያዎች ታሪካዊ ጠቀሜታ አላቸው።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጆሴፈስ በኢየሩሳሌም ግንቦች አጠገብ