እምነት የሚጣልበት አመራር ከየት ልታገኝ ትችላለህ?
“አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም። አቤቱ፣ ቅጣኝ።”—ኤርምያስ 10:23, 24
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ኤርምያስ እነዚህን ቃሎች የጻፈው ከ25 መቶ ዘመናት በፊት ነው። በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሰብአዊ አመራርን በሥራ ላይ ማዋል ያስከተላቸው አስከፊ ሁኔታዎች የዚህን አባባል የማይካድ እውነተኛነት አረጋግጠዋል። ነገር ግን ‘እምነት የሚጣልበት አመራር ከየት ሊገኝ ይችላል?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
ከላይ የተጠቀሰው ጥቅስ እምነት የሚጣልበት አመራርና መመሪያ የሚገኘው ከሰው ልጅ በጣም የላቀ ከሆነው ከሰው ፈጣሪ ከይሖዋ አምላክ መሆኑን ያመለክተናል። ከፈጣሪያችን ይበልጥ ስለ ሰው አሠራርና ስለሚያስፈልጉት ነገሮች የሚያውቅ ማንም የለም። ሆኖም ግን አምላክ እንደዚህ ያለውን አመራርና መመሪያ ለእኛ ለመስጠት ፈቃደኛ ነውን? ይህንንስ የሚያደርገው እንዴት ነው? ለእኛ ዘመን ሊሠራ ይችላልን?
መለኮታዊ አመራርን ለመቀበል የሚያስችል አፈጣጠር
ሰውን ከእንስሳት የሚለየው ዋና ነገር በሰው አእምሮ አፈጣጠር፣ ችሎታና አሠራር ላይ የሚያተኩር መሆኑ የታወቀ ነው። እንስሳት አእምሮአቸው የሚሠራው አስቀድሞ በተወሰነ በተፈጥሮ በተገኘ ጥበብ ነው። የሰው ልጆችን በተመለከተ ግን ነገሩ እንደዚህ አይደለም።—ምሳሌ 30:24–28
ከእንስሳት አእምሮ በተለየ መንገድ የሰው አእምሮ ትልቅ ክፍል አስቀድሞ የተወሰነ ነገር የሌለው በነፃነት የሚሠራ ነው። አምላክ ለሰው ልጆች የነፃ ምርጫ ስጦታ አድሏል። ይህም አስቦ ውሳኔ ማድረግ መቻልንና እንደ ፍቅር፣ ልግስና፣ ከራስ ወዳድነት ነፃ መሆን፣ ፍትሕና ጥበብ ያሉትን ብልጫ ያላቸው ባሕርያት እንዲያሳዩ አድርጓቸል።
አምላክ ሰውን እንደዚህ ያለ የአእምሮ ችሎታ እንዲኖረው አድርጎ ከፈጠረ በኋላ በጥሩ ሁኔታ ሊጠቀምበት እንዲችል አንድ ዓይነት አመራር ሳይሰጠው ይቀራል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነውን? አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ሰዎች ቀጥተኛ የሆነ አመራር ሰጥቷቸዋል። (ዘፍጥረት 2:15–17, 19፤ 3:8, 9) ሰው በኃጢያት ከወደቀ በኋላ እንኳ አምላክ ለታማኝ ወንዶችና ሴቶች መመሪያ መስጠቱን ቀጥሏል። ይህንንም ያደረገው በአብዛኛው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (መዝሙር 119:105) ይህ ዝግጅት ሰዎች በነፃ ምርጫቸው በጥበብ በመጠቀም ዕለታዊ ችግሮቻቸውን በተሳካ ሁኔታ እያሸነፉ እንዲኖሩ አስችሏቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ ደራሲ
መጽሐፍ ቅዱስን እምነት የሚጣልበት አመራር ምንጭ ያደረገው ነገር ምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ፈጣሪ ብቻ ሊያስታውቅ የሚችለውን እውቀት መያዙ ነው። ሰብአዊ ሕይወት ከመፈጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት የተከናወኑትን ነገሮች ይተርካል። ለምሳሌ ያህል ምድር ለሰብአዊ ሕይወት ተስማሚ እስክትሆን ድረስ በተከታታይ ወቅቶች እንዴት እንደተዘጋጀች የሚናገር ታሪክ ይዟል። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2) ምንም እንኳ ይህ ጉዳይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፈው ከ3,000 ዓመታት በፊት ቢሆንም ከዘመናዊ የሳይንሳዊ ጽንሰ ሐሳብ ጋር ይስማማል።
የሰው ዘር ምድር ክብ መሆኗን ከመቀበሉ ከብዙ ጊዜ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ “ሰሜንን በባዶ ስፍራ ላይ ይዘረጋል፣ ምድሪቱንም በታችዋ አንዳች አልባ ያንጠለጥላል” በማለት ይናገራል። (ኢዮብ 26:7) ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ “እርሱ በምድር ክበብ ላይ ይቀመጣል፣ በእርስዋም የሚኖሩት እንደ አንበጣ ናቸው” በማለት ይገልጻል። (ኢሳይያስ 40:22) ይህን ዝርዝር ሐሳብ ሊያስረዳ የሚችለው አምላክ ማለትም ፈጣሪ ብቻ ነው።
ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ችሎታ ለሰው የተሰጠ ስጦታ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ፈጣሪ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ትንቢት ይናገራል። አምላክ ነቢዩ ኢሳይያስን “እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔ ያለ ማንም የለም። ከመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ” ብሎ እንዲጽፍ በመንፈስ አነሣስቶታል።—ኢሳይያስ 46:9, 10
መጽሐፍ ቅዱስ በአስደናቂ ትክክለኛነት ከመጀመሪያ መጨረሻውን መናገር የሚችል መሆኑን አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል በሺዎች በሚቆጠሩት ዓመታት የሰዎች ታሪክ ወቅት የተፈራረቁትን ዋና ዋና የዓለም ኃያል መንግሥታት አነሣስ፣ አወዳደቅና ባሕርይ አስቀድሞ ተናግሯል። እነዚህ አስደናቂ ትንቢቶች የተጻፉት ፍጻሜያቸውን ከማግኘታቸው ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የተጻፉ ናቸው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን የሚከናወኑትን ነገሮችና የመጨረሻ ውጤታቸውን በትክክል ይተነብያል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ የሆነበት ሌላው መንገድ ፍጽምና የጎደላቸው ሰው ሠራሽ መንግሥታት ‘በታላቁ ሁሉን በሚገዛ በአምላክ ቀን በሚሆነው ጦርነት’ ማለትም በአርማጌዶን ሲጠፉ እንዴት መዳን እንደሚቻል ስለሚያመለክት ነው። በአምላክ ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራው የአምላክ መንግሥት ይህንን ታላቅ ሥራ ይፈጽማል።—ራእይ 16:14, 16፤ 17:9–18፤ ዳንኤል ምዕራፍ 2 እና 8
ሁልጊዜ ጠቃሚ ነው፤ ፈጽሞ ጐጂ አይደለም
ሰብአዊ ጥበብ ፍጽምና የለውም። ስለዚህ ምንም እንኳ በቅን ልቦና ተነሣስተው ቢያደርጉትም ሰዎች የሚሰጡት ምክር ጠቃሚ የማይሆኑባቸው ጊዜያት አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ግን እንደዚህ ዓይነት ጉድለት የለበትም። አምላክ ራሱ “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” በማለት ይናገራል።—ኢሳይያስ 48:17, 18
መለኮታዊ አመራር ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች ለይተን እንድናውቅና በሕይወታችንም ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች አጥብቀን እንድንከተል ይረዳናል። ዘመናዊው ኅብረተሰብ ቁሳዊ ነገሮች በማግኘት ላይ ግብ ማድረግን የተሳካ የኑሮ መንገድ አድርጎ ቢከተልም መጽሐፍ ቅዱስ ‘የማይታየውን እንጂ የሚታየውን አንመልከት። የሚታየው የጊዜው ነውና፣ የማይታየው ግን የዘላለም ነው’ በማለት ዋጋ ያለውን ነገር ጎላ አድርጎ ይገልጽልናል። (2 ቆሮንቶስ 4:18) በዚህ መንገድ ከሁሉ የሚበልጠውን የሕይወት ግብ ማለትም መጨረሻው በጻድቅ አዲስ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሆነውን የአምላክን ፈቃድ ከማድረግ ጋር የተያያዘ መንፈሳዊ ግብ እንድንከተል ማበረታቻ ተሰጥቶናል።
አንድ ክርስቲያን እነዚህን ከፍ ያሉ ግቦች ለመከተል ጥረት ሲያደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ከሁሉ የተሻለ ሕይወት እንዲኖር ይረዳዋል። ዘመናዊው ሰብአዊ ጥበብ ትንሽ ሠርተህ ብዙ አግኝ የሚለውን ፍልስፍና ወደ መከተል ያዘነበለ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ “የታካች እጅ ችግረኛ ታደርጋለች፤ የትጉ እጅ ግን ባለጠጋ ታደርጋለች” በማለት ይነግረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች “በነገር ሁሉ በመልካም እንድንኖር ወደን፣ መልካም ሕሊና እንዳለን ተረድተናልና” በማለት ጽፎላቸዋል።—ምሳሌ 10:4፤ ዕብራውያን 13:18
መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰብ ዝግጅት የሚረዳ ተግባራዊ ምክር ይሰጣል። ባልና ሚስት በጋብቻ ዝግጅት ውስጥ የሚጫወቱትን ሚናና ልጆችን ማሳደግ የሚቻልበትን ትክክለኛ መንገድ በግልጽ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ “ባሎች ደግሞ እንደ ገዛ ሥጋቸው አድርገው የገዛ ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። . . . [ሚስትም ለባልዋ ጥልቅ አክብሮት ሊኖራት ይገባል አዓት] ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ . . . እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን [በይሖዋ አዓት] ምክርና በተግሣጽ አሳድጓቸው እንጂ አታስቆጡአቸው” ይላል። የፈጣሪን ከሁሉ የላቀ ምክር መከተል ቤተሰቡ ተረጋግቶና ተደስቶ እንዲኖር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።—ኤፌሶን 5:21 እስከ 6:4
የአምላክን መመሪያ ለሚከተሉ የተዘጋጀላቸው አስተማማኝ የወደፊት ጊዜ
ተጽፎ የሚገኘው የአምላክ ቃል አምላክ ለሁሉም የሰው ዘር ችግሮች ያዘጋጀውን መፍትሔ በግልጽ ይነግረናል። ይሖዋ አምላክ በቅርቡ አሁን ያለውን የነገሮች ሥርዓት ከሥቃዮቹ፣ ከፍትሕ አልባነቱና ከመከራዎቹ ጋር አጥፍቶ በራሱ ጻድቅ አዲስ ሥርዓት ይተካዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን በ2 ጴጥሮስ 3:7–10 ላይ ከገለጸ በኋላ በቁጥር 13 ላይ “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” በማለት ጨምሮ ይናገራል። ይህ ምሥራች ለሰብአዊው ቤተሰብ ሊሰጥ ከሚችለው ምሥራች ሁሉ እጅግ በጣም የላቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የያዘው መልዕክትም ሆነ የይሖዋ ምስክሮች ከ200 በሚበልጡ አገሮችና ደሴቶች ውስጥ የሚሰብኩት ምሥራች ይኸው ነው።
በመላዋ ምድር ላይ የአምላክ ፈቃድ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ መላው ሰብአዊ ቤተሰብ የፈጣሪውን የይሖዋን ግሩም መመሪያ በመከተል ጥቅም ያገኛል። ድህነት፣ ወንጀልና ዕፅ የሚያስከትሏቸው ችግሮች አይኖሩም። የሰው ዘር በበሽታ፣ በእርጅናና በሞት አይሠቃይም። ሰብአዊው ቤተሰብ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በአምላክ መመሪያ ላይ ከማመፃቸው በፊት ወደነበራቸው የፍጽምና ደረጃ ይደርሳል።
በመለኮታዊ መመሪያ ላይ እምነታቸውን የጣሉ ሰዎች የሚኖራቸውን አስደሳች ሁኔታ የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ እንዴት ጥሩ አድርጎ አጠቃልሎ ገልጾታል! ራእይ 21:4, 5 “[አምላክ] እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ” ይላል። ፈጣሪያችን ይህ የሚፈጸም ለመሆኑ ዋስትና ሲሰጥ “እነሆ፣ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ” ካለ በኋላ “እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸው” በማለት ጨምሮ ተናግሯል።
እነዚህን በረከቶች ለማግኘት አምላክ ከእኛ ምን ይፈልግብናል? ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ” እንዲደርሱ መሆኑን ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) የይሖዋ ምስክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ በማጥናት ትክክለኛ የእውነት እውቀት እንድታገኝ በአክብሮት ይጋብዙሃል። ስለ መለኮታዊው ፈቃድ ተግተህ በመማር በዚህ አደገኛ ዘመን አስተማማኝ መመሪያ ሊሆን የሚችለው መለኮታዊ ጥበብ ብቻ መሆኑን በራስህ ኑሮ ለማየት ትችላለህ። የጊዜው አጣዳፊነት ከምንጊዜውም የበለጠ ይህንን ምክር መከተሉን አስፈላጊ ያደርገዋል።