የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • wp21 ቁጥር 3 ገጽ 12-14
  • ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት ይቻላል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት ይቻላል?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2021
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከሁሉ የተሻለ መመሪያ የምናገኘው ከማን ነው?
  • መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
    ንቁ!—2017
  • አምላክን የሚያስደስቱ እውነተኛ ትምህርቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ትክክል ወይስ ስህተት? መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መመሪያ ይሰጠናል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2024
  • እምነት የሚጣልበት አመራር ከየት ልታገኝ ትችላለህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2021
wp21 ቁጥር 3 ገጽ 12-14
መጽሐፍ ቅዱስን እያነበበ ያለ ሰው

ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት ይቻላል?

ቀደም ባሉት ርዕሶች ላይ እንደተመለከትነው ሰዎች በዕድል በማመን፣ ከፍተኛ ትምህርት በመከታተል፣ ሀብት በማሳደድ፣ ጥሩ ሰው ለመሆን በመጣርና እንዲህ የመሳሰሉ ነገሮችን በማድረግ የወደፊት ሕይወታቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ይሞክራሉ። ሆኖም እነዚህን አማራጮች በመጠቀም የወደፊት ሕይወትን አስተማማኝ ለማድረግ መሞከር የተሳሳተ ካርታ ተጠቅሞ ያሰቡበት ቦታ ለመድረስ እንደመሞከር ነው። ይህ ሲባል ታዲያ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ መመሪያ ማግኘት አይቻልም ማለት ነው? በፍጹም!

ከሁሉ የተሻለ መመሪያ የምናገኘው ከማን ነው?

አብዛኛውን ጊዜ ውሳኔ ስናደርግ በዕድሜም ሆነ በተሞክሮ ከእኛ የሚበልጥን ሰው እናማክራለን። ከወደፊቱ ጊዜ ጋር በተያያዘም አስተማማኝ መመሪያ ሊሰጠን የሚችል አካል አለ፤ ይህ አካል በዕድሜም ሆነ በጥበብ ከእኛ በእጅጉ የላቀ ነው። እሱ የሰጠንን ምክር የምናገኘው ጥንታዊ በሆኑ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ነው። እነዚህ መጻሕፍት መጻፍ የጀመሩት ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ነው፤ የመጻሕፍቱ ስብስብ መጽሐፍ ቅዱስ ተብሎ ይጠራል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል የምትችለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈው በጽንፈ ዓለም ውስጥ በዕድሜም ሆነ በጥበብ ተወዳዳሪ የሌለው አካል ነው። “ከዘመናት በፊት የነበረ” እንዲሁም “ከዘላለም እስከ ዘላለም” የሚኖር እንደሆነ ተገልጿል። (ዳንኤል 7:9፤ መዝሙር 90:2) ‘ሰማያትን የፈጠረው፣ እውነተኛ የሆነው አምላክና ምድርን የሠራት’ እሱ ነው። (ኢሳይያስ 45:18) ስሙ ይሖዋ እንደሆነ ተናግሯል።—መዝሙር 83:18

መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ዘር ሁሉ ፈጣሪ የሆነው አምላክ ያጻፈው መጽሐፍ ስለሆነ አንዱን ባሕል ወይም ዘር ከሌላው አያበላልጥም። በውስጡ የያዘው ምክር ዘመን የማይሽረው ሲሆን በሁሉም የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ሰዎችን ይጠቅማል። ከየትኛውም መጽሐፍ ይበልጥ በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመና በስፋት የተሰራጨ መጽሐፍ ነው።a ይህ ሲባል ደግሞ በየትኛውም የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ መረዳትና በውስጡ ባለው ምክር ሕይወታቸውን መምራት ይችላሉ ማለት ነው። እነዚህ እውነታዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ከሚናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማሉ፦

“አምላክ [አያዳላም]፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35

አንድ አፍቃሪ ወላጅ ለልጆቹ መመሪያ እንደሚሰጥ ሁሉ አፍቃሪ አባታችን ይሖዋም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት መመሪያ ይሰጠናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ይህን መጽሐፍ ያጻፈው እኛን የሠራንና ለእኛ ከሁሉ የተሻለውን ነገር የሚያውቀው አምላክ ስለሆነ በቃሉ ላይ ሙሉ እምነት መጣል እንችላለን።

አስተማማኝ መመሪያ

1. አንድ ሰው በባቡር እየተጓዘ ስልኩ ላይ ሲያነብ 2. በሰውየው ስልክ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ተከፍቶ

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ መመሪያ እንደሚሰጠን እርግጠኛ መሆን እንችላለን፤ ምክንያቱም ዛሬ እየተፈጸሙ ያሉትን ክስተቶች እና የሰዎችን ባሕርይ አስመልክቶ ከ2,000 ዓመታት ገደማ በፊት በትክክል ተንብዮአል።

ክስተቶች

“ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል። ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ፤ በተለያየ ስፍራም የምግብ እጥረትና ቸነፈር ይሆናል።”—ሉቃስ 21:10, 11

የሰዎች ባሕርይ

“በመጨረሻዎቹ ቀናት ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ግትሮች፣ በኩራት የተወጠሩ፣ ከአምላክ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-4

መጽሐፍ ቅዱስ ዛሬ ስለሚከናወኑት ነገሮች ከረጅም ጊዜ በፊት በትክክል እንደተነበየ ስታውቅ ምን ይሰማሃል? በሆንግ ኮንግ የሚኖረው ሎዪንግ በተናገረው ሐሳብ እንደምትስማማ ምንም ጥርጥር የለውም። እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የተጻፉት ከረጅም ጊዜ በፊት ነው። እነዚህን ነገሮች እንዲህ በትክክል ሊተነብይ የሚችል ማንም ሰው የለም። መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈው ከእኛ እጅግ የላቀ አካል መሆን አለበት።”

መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል ፍጻሜያቸውን ያገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ትንቢቶችን ይዟል።b ይህም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ያረጋግጥልናል። ይሖዋ “እኔ አምላክ ነኝ፤ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም” በማለት ተናግሯል። አክሎም ‘ከመጀመሪያ መጨረሻውን እናገራለሁ’ ብሏል። (ኢሳይያስ 46:9, 10) በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በሚናገረው ሐሳብ ላይ ሙሉ እምነት እንድትጥል የሚያደርግህ በቂ ምክንያት አለ።

አሁንም ሆነ ለዘላለም የሚጠቅም መመሪያ

ወላጆች የሁለት ልጆቻቸውን እጅ ይዘው በደስታ መስክ ላይ ሲጓዙ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ መከተልህ ብዙ ጥቅም ያስገኝልሃል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

ለገንዘብ እና ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

“ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል።”—መክብብ 4:6

የቤተሰብ ሕይወት

“ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ታክብር።”—ኤፌሶን 5:33

ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት

“ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው፤ ተበሳጭተህ ክፉ ነገር አትሥራ።”—መዝሙር 37:8

የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግህ በአሁኑ ጊዜ ይጠቅምሃል፤ ለወደፊቱም ብሩህ ተስፋ እንዲኖርህ ያደርጋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት አምላክ የሰጣቸው ተስፋዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

ሰላም እና መረጋጋት

“በብዙ ሰላም . . . እጅግ ደስ ይላቸዋል።”—መዝሙር 37:11

ሁሉም ሰው መኖሪያና ምግብ ያገኛል

“ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።”—ኢሳይያስ 65:21

ሕመም ወይም ሞት አይኖርም

“ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:4

ታዲያ እንዲህ ያለውን ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ ይጠበቅብሃል? እስቲ ቀጣዩን ርዕስ ተመልከት።

a የመጽሐፍ ቅዱስን ትርጉም ሥራና ስርጭት በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት www.jw.org ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች > ታሪክ እና መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው ሥር ተመልከት።

b ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት። መጽሐፉ www.jw.org ላይ ይገኛል። ላይብረሪ > መጻሕፍትና ብሮሹሮች በሚለው ሥር ተመልከት።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ