ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምሩ
“በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ።”—ዘጸአት 15:1
1. ይሖዋን እንድናወድሰው የሚያደርጉን የትኞቹ ጠባዮቹና ችሎታዎቹ ናቸው?
መዝሙር 150 አሥራ ሦስት ጊዜ ይሖዋን ወይም ያህን እንድናመሰግነው ያዘናል። የመጨረሻው ቁጥር እንዲህ ይላል፦ “እስትንፋስ ያለው ሁሉ እግዚአብሔርን ያመስግን። ሃሌ ሉያ።” የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋ የእኛ ውዳሴ የሚገባው መሆኑን እናውቃለን። እርሱ የጽንፈ ዓለም ሁሉ የበላይ ገዥ፣ ከማንም በላይ የሆነና የዘላለም ንጉሥ፣ ፈጣሪያችንና ደጋፊያችን ነው። እርሱ በብዙ መንገዶች ተወዳዳሪ የሌለው፣ ማንም የማይመስለው፣ አቻ ወይም እኩያ የሌለው ነው። እርሱ ሁሉንም ነገር ማወቅና ማድረግ የሚችል፣ ፍጹም ፍትሕ ያለውና ሁለንተናው ፍቅርን የተላበሰ ነው። ከማንም ይበልጥ ጥሩ የሆነና በታማኝነት ከጎን የሚቆም ነው። (ሉቃስ 18:19 አዓት ፤ ራእይ 15:3, 4) ታዲያ ውዳሴያችን ይገባዋልን? ምንም አያጠያይቅም!
2. ለይሖዋ ምስጋና የምናቀርብባቸው ምን ምክንያቶች አሉን?
2 ይሖዋ አምልኮታችንና ውዳሴያችን ብቻ ሳይሆን ላደረገልን ነገር ሁሉ ምስጋናም ልናቀርብለት የሚገባው ነው። እርሱ ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ የፍጹምም በረከት ሁሉ’ ሰጪ ነው። (ያዕቆብ 1:17) እርሱ የሕይወት ምንጭ፣ የሕይወት መፍለቂያ ነው። (መዝሙር 36:9) የሰው ልጆች ያሏቸው አስደሳች ነገሮች ሁሉ ከእርሱ የመጡ ናቸው። ምክንያቱም እርሱ ታላቁ ፈጣሪያችን ነው። (ኢሳይያስ 42:5) በተጨማሪም በመንፈሱ፣ በድርጅቱና በቃሉ በኩል የሚመጡልንን መንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ የሰጠን እርሱ ነው። ልጁን ቤዛችን እንዲሆን በመስጠቱ የኃጢአት ይቅርታ አግኝተናል። (ዮሐንስ 3:16) ‘ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር’ በሚያመጣው መንግሥት ሥር ለመኖር ተስፋ እናደርጋለን። (2 ጴጥሮስ 3:13) ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር ጥሩ ወዳጅነት አለን። (ሮሜ 1:11, 12) የእርሱ ምሥክሮች የመሆን ክብርና በረከት አግኝተናል። (ኢሳይያስ 43:10–12) ውድ የጸሎት መብትም አለን። (ማቴዎስ 6:9–13) በእውነትም ይሖዋን የምናመሰግንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉን!
ይሖዋን ልናመሰግን የምንችልባቸው መንገዶች
3. ይሖዋን በምን ልዩ ልዩ መንገዶች ልናወድሰውና ምስጋናችንን ልንገልጽለት እንችላለን?
3 ለይሖዋ ያደርን አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን እርሱን ልናወድስና ለሚያደርግልን ሁሉ ምስጋናችንን ልንገልጽለት የምንችለው እንዴት ነው? በክርስቲያን አገልግሎት በመካፈል ማለትም ከቤት ወደ ቤት እየሄድን በመመሥከር፣ ሰዎችን ተመላልሰን በመጠየቅ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራትና ከመንገድ ወደ መንገድ እየሄዱ በመመሥከሩ ሥራ በመካፈል ምስጋናችንን ልንገልጽለት እንችላለን። አጋጣሚ ባገኘን ጊዜ ሁሉ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በመመሥከርም ልናወድሰው እንችላለን። እንዲሁም ትክክለኛ ጠባይ በማሳየት፣ ንጹሕና ልከኛ በሆነው አለባበሳችንና አበጣጠራችንም ጭምር ይሖዋን ልናወድስ እንችላለን። የይሖዋ ምሥክሮች ብዙውን ጊዜ በዚህ ረገድ አርዓያ የሚሆኑ ናቸው ተብለው ተመስግነዋል። ከዚህም በላይ በጸሎታችን ይሖዋን ልናወድሰውና ልናመሰግነው እንችላለን።—1 ዜና መዋዕል 29:10–13ን ተመልከቱ።
4. አፍቃሪውን የሰማይ አባታችንን ልናመሰግን ከምንችልባቸው በጣም ጥሩ መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
4 በተጨማሪም አፍቃሪውን የሰማይ አባታችንን ልናወድስ ከምንችልባቸው በጣም ጥሩ መንገዶች አንዱ እርሱንና ባሕርያቱን ጣዕም ባላቸው የመንግሥቱ መዝሙሮች በማሞገስ ነው። ብዙ ሙዚቀኞችና የዘፈን ደራሲዎች ተወዳዳሪ የሌለው የሙዚቃ መሣሪያ የሰው አንደበት የሚያሰማው ድምፅ ነው ይላሉ። ይበልጥ የሚያረካው ሰዎች ሲዘፍኑ መስማት ስለሆነ ከዚህ በፊት ክላሲካል ሙዚቃ የሚደርሱ ሰዎች የኦፔራ ሙዚቃን ለማዘጋጀት ተነሳስተዋል።
5. የመንግሥቱን መዝሙሮች ለመዘመሩ ጉዳይ ክብደት እንድንሰጥ የሚያደርጉን ምን ምክንያቶች ናቸው?
5 ይሖዋ ሰዎች ሲዘምሩ በሚሰማበት ጊዜ፣ በተለይም የውዳሴና የምስጋና መዝሙር ሲዘምሩ እንዴት ደስ ይለው ይሆን! እንግዲያው በተለያዩ ስብሰባዎቻችን ላይ ማለትም በጉባኤ ስብሰባዎች፣ በክልል ስብሰባዎች፣ በልዩ ስብሰባ ቀኖች፣ በወረዳና በብሔራት አቀፍ ስብሰባዎቻችን ላይ የመንግሥቱን መዝሙሮች የመዘመሩን ጉዳይ በቁም ነገር መመልከት ይገባናል። የመዝሙር መጽሐፋችን በጣም ደስ በሚሉ ጣዕመ ዜማዎች የተሞላ ነው። የዜማዎቹን ውበት የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችም በተደጋጋሚ አድንቀውታል። የመንግሥቱን መዝሙሮች በተመስጦ ስንዘምር ሌሎችን ከማስደሰታችንም በላይ ራሳችንም እንጠቀማለን።
በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር መዘመር
6. እስራኤላውያን በቀይ ባሕር ስላገኙት መዳን ምስጋናቸውን የገለጹት እንዴት ነበር?
6 ሙሴና ሌሎች እስራኤላውያን በቀይ ባሕር ከፈርዖን ሠራዊት ከዳኑ በኋላ በድል አድራጊነት እንደዘመሩ የአምላክ ቃል ይነግረናል። መዝሙራቸው እንዲህ በማለት ይጀምራል፦ “በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር እዘምራለሁ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ። ጉልበቴ ዝማሬዬም እግዚአብሔር ነው፣ መድኃኒቴም ሆነልኝ፤ ይህ አምላኬ ነው አመሰግነውማለሁ።” (ዘጸአት 15:1, 2) እስራኤላውያን በተዓምር ከጥፋት ከዳኑ በኋላ እንዴት ባለ ግለትና ደስታ እንደዘመሩ ልንገምተው እንችላለን።
7. በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተመዝግበው የምናገኛቸው እስራኤላውያን ይሖዋን በመዝሙር ያወደሱባቸው ምን ሌሎች የሚታወሱ አጋጣሚዎች አሉ?
7 በ1 ዜና መዋዕል 16:1, 4–36 ላይ ዳዊት ታቦቱን ወደ ኢየሩሳሌም ባመጣበት ጊዜ ይሖዋ በመዝሙርና በሙዚቃ መሣሪያዎች አማካኝነት ተወድሶ እንደነበር እናነባለን። ያ ጊዜ በእርግጥም በጣም ደስ የሚል ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን በኢየሩሳሌም ያሠራውን ቤተ መቅደስ በሚመርቅበት ጊዜም በሙዚቃ መሣሪያዎች በመታጀብ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ተዘምሮ ነበር። በ2 ዜና መዋዕል 5:13, 14 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ካህናቱም ከመቅደሱ በወጡ ጊዜ፣ መለከቱንም የሚነፉ መዘምራኑም በአንድነት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑና እያከበሩ፦ እግዚአብሔር ቸር ነውና ምሕረቱም ለዘላለም ነውና፣ እግዚአብሔርን አመስግኑ እያሉ በአንድ ቃል ድምፃቸውን ወደ ላይ ከፍ አድርገው በመለከትና በጸናጽል በዜማም ዕቃ ሁሉ እግዚአብሔርን ባመሰገኑ ጊዜ፣ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶት ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ መቆምና ማገልገል አልተቻላቸውም።” ይህ ምን ያሳያል? ሕዝቡ በጣዕመ ዜማ ያቀረቡትን ውዳሴ ይሖዋ ይሰማ እንደ ነበረና ተዓምራዊው ደመና እንዳመለከተውም በዚህ ውዳሴ ይሖዋ እንደተደሰተ ያሳያል። በኋላም በነህምያ ዘመን የኢየሩሳሌም ቅጥር ሲመረቅ ሁለት የመዘምራን ቡድን በኅብረት ዘምሮ ነበር።—ነህምያ 12:27–42
8. እስራኤላውያን መዝሙር መዘመርን አክብደው ይመለከቱት እንደነበረ የሚያሳየው ምንድን ነው?
8 እንዲያውም መዝሙር መዘመር በቤተ መቅደሱ በሚከናወነው የአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ስለተሰጠው ለሙዚቃ አገልግሎት የተለዩ 4,000 ሌዋውያን ነበሩ። (1 ዜና መዋዕል 23:4, 5) እነዚህ ሙዚቀኞች መዘምራኑን ያጅቡ ነበር። ለሙዚቃ፣ በተለይም ለመዘምራን በአምልኮ ሥርዓት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቶ ነበር። ይህም የተደረገበት ምክንያት የሕጉን ከባድ ጉዳዮች ለማስገንዘብ ብቻ ሳይሆን የአምልኮቱ ሥርዓት በትክክለኛ መንፈስ እንዲካሄድ ታስቦም ጭምር ነው። መዝሙር እስራኤላውያን በጋለ መንፈስ ለይሖዋ የአምልኮ ሥርዓት እንዲፈጽሙ ረድቷቸዋል። ለዚህኛው የአምልኮ ሥነ ሥርዓት ክፍል የሚደረገውን ዝግጅትና ለዝርዝር ጉዳዮች የተሰጠውን ትኩረት ቀጥሎ ባሉት ቃላት ላይ ተመልከቱ፦ “እነዚህ ሃያ አራቱ ሰዎች ሁሉ ከፍ ያለ ችሎታ ያላቸው ነበሩ፤ ወገኖቻቸው ደግሞ የሠለጠኑ መዘምራን ሲሆኑ ቁጥራቸውም በድምሩ ሁለት መቶ ሰማኒያ ስምንት ነበር።” (1 ዜና መዋዕል 25:7 የ1980 ትርጉም) ለይሖዋ ያቀርቡት የነበረውን የውዳሴ መዝሙር እንዴት አክብደው እንደተመለከቱት አስተውሉ። መዝሙር በመዘመር ሠልጥነው ነበር፤ ከፍ ያለ ችሎታም ነበራቸው!
9. በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ መዝሙር መዘመር ምን ያህል ጠበቅ ተደርጎ ተጠቅሷል?
9 ወደ መጀመሪያው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር ብንመጣስ ሁኔታው እንዴት ነበር? ኢየሱስ አልፎ በተሰጠባት ምሽት በአእምሮው ውስጥ ከበድ ያሉ አያሌ ጉዳዮች የነበሩ ቢሆንም የማለፍን በዓልና በዚህ ጊዜ ያስጀመረውን የሞቱን መታሰቢያ በዓል መዝሙር በመዘመር መደምደሙ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል። (ማቴዎስ 26:30) ጳውሎስና ሲላስም ተደብድበውና ታስረው በነበሩበት ጊዜ “በመንፈቀ ሌሊት . . . እየጸለዩ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰግኑ ነበር፣ እስረኞቹም ያደምጡአቸው ነበር።”—ሥራ 16:25
የውዳሴ መዝሙር መዘመር አስፈላጊ የሆነ የአምልኮታችን ክፍል ነው
10. የአምላክ ቃል እርሱን በመዝሙር ማወደስን በተመለከተ ምን ብሎ ያዝዘናል?
10 ምናልባት የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመር ያን ያህል አስፈላጊ ስላልሆነ ከልቤ ትኩረት ባልሰጠውም ምንም አይደለም የሚል ስሜት ተሰምቷችሁ ይሆን? እንዲህ ተሰምቷችሁ ከሆነ ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ ለመዝሙር ከሚሰጡት ከፍተኛ ቦታ አንፃር ጉዳዩን እንደገና ብታጤኑት ጥሩ አይመስላችሁም? የአምላክ ቃል ይሖዋን እንድናመሰግነውና የውዳሴ መዝሙሮች እንድንዘምርለት ብዙ ጊዜ ያዘናል! ለምሳሌ ያህል በኢሳይያስ 42:10 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “ወደ ባሕር የምትወርዱ በእርስዋም ውስጥ ያላችሁ ሁሉ፣ ደሴቶችና በእርሱም ላይ የምትኖሩ ሆይ፣ ለእግዚአብሔር አዲስ መዝሙር፣ ከምድርም ዳርቻ ምስጋናውን ዘምሩ።”—በተጨማሪም መዝሙር 96:1ንና 98:1ን በ1980 ትርጉም ተመልከቱ።
11. ሐዋርያው ጳውሎስ መዘመርን በተመለከተ ምን ጥብቅ ምክር ሰጥቶ ነበር?
11 ሐዋርያው ጳውሎስ መዝሙር ስሜታችንን ሊያነቃቃው እንደሚችል ያውቅ ነበር። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ጊዜ አጥብቆ መክሮናል። በኤፌሶን 5:18, 19 ላይ እንዲህ እናነባለን፦ “መንፈስ ይሙላባችሁ . . . በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ።” በቆላስይስ 3:16 ላይም እንዲህ እናነባለን፦ “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ፤ በጥበብ ሁሉ እርስ በርሳችሁ አስተምሩና ገሥጹ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ።”
12. አንዳችን ሌላውን እንድናስተምርና እንድንመክር የሚያበረታቱ ለምሳሌ የተጠቀሱልን የትኞቹ መዝሙሮች ናቸው?
12 በሁለቱም ላይ ጳውሎስ ‘በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ’ በማለት መዝሙር ስለ መዘመር ደጋግሞ እንደተናገረ ልብ በሉ። ለቆላስይስ ክርስቲያኖችም በሰጣቸው ምክር መግቢያ ላይ በዚህ መንገድ ‘እርስ በርስ ማስተማርና መገሠጽ’ እንደሚችሉ ነግሯቸዋል። እኛም እንዲሁ እናደርጋለን። ይህንንም ከመዝሙሮቻችን ርዕሶች ማየት ይቻላል። ጥቂት ምሳሌዎች ለመጥቀስ ያህል፦ “ፍጥረታት በሙሉ ይሖዋን አወድሱ!” (ቁጥር 5)፣ “ጸንተህ ቁም፣ አትነቃነቅ!” (ቁጥር 10)፣ “በመንግሥቱ ተስፋ ተደሰት!” (ቁጥር 16)፣ “አትፍሯቸው!” (ቁጥር 27)፣ “ይሖዋ አምላካችንን አመስግኑ!” (ቁጥር 100) የሚሉ ይገኙበታል።
13. “ታማኝና ልባም ባሪያ” መዝሙር መዘመር የአምልኮታችን አንዱ አስፈላጊ ክፍል አድርገን ከፍ አድርገን መያዝ እንደሚገባን ያሳየው እንዴት ነው?
13 በነዚህ ትዕዛዞች መሠረት “ታማኝና ልባም ባሪያ” ስብሰባዎቻችን ማለትም የጉባኤ ስብሰባዎች፣ የክልል ስብሰባዎች፣ የልዩ ስብሰባ ቀኖች፣ የወረዳ ስብሰባዎችና ብሔራት አቀፍ የሆኑ ትልልቅ ስብሰባዎችን የመንግሥቱን መዝሙሮች በመዘመር እንዲከፈቱና እንዲዘጉ የሚያስችል ዝግጅት በፕሮግራሙ ውስጥ ጨምሯል። (ማቴዎስ 24:45) በተጨማሪም በነዚህ ስብሰባዎች ላይ በየጣልቃው የሚዘመሩ መዝሙሮች በፕሮግራሙ ላይ ይወጣሉ። ስብሰባዎቻችንን የምንጀምረው የመንግሥቱን መዝሙር በመዘመር ስለሆነ የአምልኮታችን ክፍል በሆነው መዝሙር ለመካፈል ቀደም ብለን መድረስ እንደሚያስፈልገን እንገነዘባለንን? ስብሰባዎቻችንን የምንዘጋው በመዝሙር እንደመሆኑ መጠን በመደምደሚያው መዝሙርና ከመዝሙሩ ቀጥሎ በሚቀርበው ጸሎት ለመካፈል እስከመጨረሻው መቆየት አይገባንምን?
14. ለፕሮግራሞቻችን ተስማሚ መዝሙሮች እንደሚመረጡ የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎች አሉን?
14 በስብሰባዎቻችን ላይ የምንዘምራቸው መዝሙሮች ከስብሰባው ፕሮግራም ጋር እንዲጣጣሙ ተደርገው በጥንቃቄ የተመረጡ ናቸው። ለምሳሌ በ1993 በተደረገው “መለኮታዊ ትምህርት” የወረዳ ስብሰባ ላይ ሦስቱን ጠላቶቻችንን የሚመለከቱ ሦስት ንግግሮች ከቀረቡ በኋላ ክርስቲያኖች ሰይጣንን፣ ዓለምንና ውዳቂውን ሥጋችንን እንድንዋጋ የሚያበረታታን “እውነትን የራስህ አድርግ” የሚለው መዝሙር ቁጥር 191 ተዘምሮ ነበር። እንዲሁም “ራስን ለአምላክ መወሰን” የሚለው መዝሙር ቁጥር 13 መለኮታዊው ትምህርት ራስን ወደ መወሰንና ወደ ጥምቀት የሚመራ መሆኑን የሚገልጽ ንግግር ከቀረበ በኋላ ተዘምሯል። “የይሖዋ ምሥክሮች ነን” የሚለው መዝሙር ቁጥር 113 የተዘመረው ደግሞ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች የተሰጡትን መልሶች፣ ጤናማውን ትምህርት የሕይወት መንገድ ስለማድረግና የሕይወትን ዓላማ ከሚያብራሩት ሦስት ንግግሮች በኋላ ነበር። በመጠበቂያ ግንብ ጥናት፣ በአገልግሎት ስብሰባ እና በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ የሚዘመሩት መዝሙሮችም የሚመረጡት እንዲሁ በጥንቃቄ ነው። የሕዝብ ንግግር የሚሰጡ ሽማግሌዎችም በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የሚዘመረውን መዝሙር ሲመርጡ ከሚያቀርቡት ንግግር መልእክት ጋር በጣም የሚስማማውን መምረጥ ይኖርባቸዋል።
15. የስብሰባው ሊቀመንበር የሚዘመረውን መዝሙር በሚመለከት አድናቆት ሊገነባ የሚችለው እንዴት ነው?
15 የስብሰባው ሊቀ መንበር የሚዘመረውን መዝሙር በሚያስተዋውቅበት ጊዜ ርዕሱን ወይም ዋና መልእክቱን በመናገር ወንድሞች ለመዝሙሩ አድናቆት እንዲኖራቸው ሊያደርግ ይችላል። የምንዘምረው ቁጥሮችን ሳይሆን ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክቶችን ነው። ከመዝሙሩ ርዕስ ሥር የተጠቀሰውን ጥቅስ ቢናገር ደግሞ ጉባኤው ለመዝሙሩ ይበልጥ አድናቆት እንዲኖረው ሊረዳ ይችላል። በተጨማሪም ሁሉም በመዝሙሩ ተመስጠው እንዲዘምሩ ቢናገር ጥሩ ነው።
መዝሙር በመዘመር ለይሖዋ ጥሩነት አድናቆት አሳዩ
16. በመዝሙሮቻችን ልንመሰጥ የምንችለው እንዴት ነው?
16 በመንግሥት መዝሙሮቻችን ውስጥ ያሉት ግጥሞች ትርጉም አዘል በመሆናቸው መዝሙር ስንዘምር በቃላቱ ላይ ማተኮር ያስፈልገናል። በያንዳንዱ መዝሙር ለመመሰጥ እንፈልጋለን። የመንፈስ ፍሬ ስለሆነው ስለ ፍቅር የሚናገሩ መዝሙሮችና የመሳሰሉት ልብ የሚነኩ ናቸው። (ገላትያ 5:22) እንደነዚህ ዓይነቶቹን መዝሙሮች ሞቅ ባለ ስሜት እንዘምራለን። ሌሎቹ የደስታ መዝሙሮች ናቸው። እነዚህን በደስታ ለመዘመር መሞከር አለብን። የሚያበረታቱና ለዘመቻ የሚያንቀሳቅሱትን ደግሞ በግለትና በልበ ሙሉነት ልንዘምራቸው ይገባል። በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በምናቀርባቸው ክፍሎች ላይ ፍቅራዊ ስሜትና ግለት እንዲኖረን እንመከራለን። በምንዘምርበት ጊዜ ሞቅ ያለ ስሜትና ግለት ማሳየታችን ደግሞ ይበልጥ አስፈላጊ ነው።
17. (ሀ) በአዘማመራችን ረገድ ታማኝ ላልሆኑት እስራኤላውያን የተሰጠው የትኛው ተግሣጽ እንዲደርስብን አንፈልግም? (ለ) በመዝሙሮቻችን ውስጥ ያሉትን ምክሮች በቁም ነገር ብናስብባቸው ምን ውጤት ይገኛል?
17 ሌሎች ነገሮችን እያሰብን የመዝሙሩን ቃላት በደንብ ሳናስተውል የመንግሥት መዝሙሮችን ብንዘምር ልባቸው ከአምላክ ርቆ ሳለ በከንፈራቸው ብቻ በማመስገናቸው እንደተወቀሱት እስራኤላውያን መሆናችን አይደለምን? (ማቴዎስ 15:8) የመንግሥቱን መዝሙሮች መዘመራችንን በተመለከተ እንዲህ ዓይነት ዘለፋ እንዲደርስብን አንፈልግም፤ አይደለም እንዴ? የመንግሥት መዝሙሮቻችንን በተገቢው ሁኔታ የምንዘምር ከሆነ የራሳችንን መንፈስ ከማነቃቃታችንም ሌላ በአጠገባችን የተቀመጡትን ወንድሞች፣ ወጣቶችንም ጭምር ልናበረታታ እንችላለን። አዎን፣ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ መዝሙር የሚዘምሩ ሁሉ መዝሙሮቹ የያዟቸውን ምክሮች በቁም ነገር ቢያስቡባቸው በአገልግሎቱ ቀናተኞች እንዲሆኑና ከኃጢአት ወጥመድ እንዲጠበቁ የሚያደርግ ኃይለኛ ማበረታቻ ያገኛሉ።
18. የመንግሥቱ መዝሙር ሲዘመር መስማቷ በአንዲት ሴት ላይ ምን ለውጥ አመጣ?
18 የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎች በተደጋጋሚ በመንግሥት መዝሙሮቻችን ተደንቀዋል። አንድ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ ላይ እንዲህ የሚል ታሪክ ወጥቶ ነበር፦ “መዝሙራችንም ሰዎች ይሖዋ አምላክን እንዲያውቁ ለማድረግ እንደሚያገለግል በ1973 በያንኪ ስታዲየም በተደረገው ‘መለኮታዊ ድል’ የተባለ ስብሰባ ላይ የተጠመቀች የአንዲት ሴት ተሞክሮ ያሳያል። ሴትየዋ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካባቢዋ ወደሚገኝ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ማንም ሳይጋብዛት ሄዳ ሁለቱንም ስብሰባዎች ስትከታተል ቆየች። በመጨረሻ ላይ ጉባኤው ‘ዓይንህን በሽልማቱ ላይ አድርግ!’ የሚለውን መዝሙር ሲዘምር በመዝሙሩ ቃላትና ጉባኤው እንዴት ባለ ስሜት እንደዘመረው ስትመለከት በጣም ተነክታ አባል መሆን የምፈልገው እዚህ ሃይማኖት ውስጥ ነው ብላ ወሰነች። በኋላም ከምሥክሮቹ አንዷን መጽሐፍ ቅዱስን እንድታስጠናት ጠየቀቻት። ከዚያ እድገት እያሳየች ሄደችና የተጠመቀች ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በቃች።”
19. የመንግሥቱን መዝሙር በሙሉ ልባችን መዘመርን በሚመለከት በመጨረሻ የተሰጠን ማበረታቻ ምንድን ነው?
19 በብዙዎቹ ስብሰባዎቻችን ላይ አድማጮች ስሜታቸውንና አድናቆታቸውን በቃላት ለመግለጽ የመዝሙርን ያህል ብዙ አጋጣሚ አያገኙም። ይሁን እንጂ ሁላችንም የመንግሥቱን መዝሙር ከልባችን በመዘመር ስለ ይሖዋ ጥሩነት የተሰማንን ስሜት ለመግለጽ እንችላለን። በተጨማሪም ለስብሰባ አንድ ላይ በምንገናኝበት ጊዜ ደስ ይለን የለምን? እንግዲያው በዚህ ጊዜ ለመዘመር ልንገፋፋ ይገባል! (ያዕቆብ 5:13) በርግጥም ለይሖዋ ጥሩነትና እርሱ ላሳየን ይገባናል የማንለው ደግነት ያለንን አድናቆት ለማሳየት በሙሉ ነፍሳችን ለእርሱ የውዳሴ መዝሙር ልንዘምርለት እንችላለን።
እንዴት ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ ይሖዋን የምናወድስባቸው ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
◻ ይሖዋን በምን ልዩ ልዩ መንገዶች ልናወድሰው እንችላለን?
◻ ይሖዋን ከምናወድስባቸው በጣም ጥሩ መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
◻ ይሖዋን በመዝሙር በማወደስ ረገድ ምን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎች አሉልን?
◻ የመንግሥት መዝሙሮቻችንን በተገቢው ሁኔታ ለመያዝ የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
መዝሙሮቹን በመዘመር ተደሰቱ!
አንዳንዶች በርካታዎቹን መዝሙሮች ለመልመድ ትንሽ የተቸገሩ ይመስላል። አንዳንድ ጉባኤዎች ግን ከነዚህ መዝሙሮች ውስጥ አብዛኞቹን ለመልመድ የጎላ ችግር አልነበረባቸውም። ምናልባት ግር የሚሉ መዝሙሮችን ለመለማመድ ጥረታችሁን ትንሽ ጨመር ማድረግ ሊበቃ ይችል ይሆናል። ብዙውን ጊዜ ጉባኤው እነዚህን መዝሙሮች ከቻላቸው በኋላ ያለ ብዙ ችግር ከለመዳቸው መዝሙሮች ይልቅ እነዚኞቹን መዝሙሮች የበለጠ ይወዳቸዋል። ከዚያ በኋላ መላው ጉባኤ በልበ ሙሉነት ሊዘምራቸው ይችላል። አዎን፣ በፊት ያስቸገሯቸውን መዝሙሮች በመዘመር ሊደሰቱ ይችላሉ!
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለጨዋታ በርከት ብላችሁ ስትሰበሰቡ የመንግሥቱን መዝሙሮች ዘምሩ
የመንግሥት መዝሙሮቻችንን መዘመር ያለብን በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ብቻ አይደለም። ጳውሎስና ሲላስ እስር ቤት እያሉ ለይሖዋ የውዳሴ መዝሙር ዘምረዋል። (ሥራ 16:25) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ከእናንተ መካከል . . . ደስ ያለው ሰው ቢኖር እግዚአብሔርን በማመስገን ይዘምር” ብሏል። (ያዕቆብ 5:13 የአዓት የግርጌ ማስታወሻ) ሰዎች በርከት ብለው በሚሰበሰቡበት ግብዣ ላይ ሰው ሁሉ ደስ ይለዋል። ታዲያ ለምን የመንግሥት መዝሙሮች አትዘምሩም? በተለይ በፒያኖ ወይም በጊታር ታጅባችሁ ብትዘምሩት በጣም ደስ ይላል። ይህ ካልሆነ ደግሞ በፒያኖ የተቀነባበረ የመንግሥት መዝሙራችን ካሴት አለ። ምሥክሮች የሆኑ ብዙ ቤተሰቦች የዚህ መዝሙር አልበም አላቸው። እነዚህ ካሴቶች መዝሙሩን ለመዘመር የሚረዱ ብቻ ሳይሆኑ ሌላ ሥራ እየሠራን በቀስታ ቢደመጡ ደስ የሚሉ ናቸው።
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እስራኤላውያን በቀይ ባሕር ከጥፋት ከዳኑ በኋላ ደስታቸውን በመዝሙር ገልጸዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዛሬም በደስታ መዘመር የክርስቲያናዊ አምልኮ ክፍል ነው