ትክክለኛውን ሃይማኖት ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ
አንዳንድ ሰዎች ከልጅነታቸው ጀምረው ሕይወትን በተመለከተ ለሚነሡባቸው ጥያቄዎች አርኪ መልስ ለማግኘት ሲፈልጉ ኖረዋል። ወጣት በነበርክበት ጊዜ አንዳንድ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ተገኝተህ ይሆናል። ብዙዎቹ ግን እዚያ በመሄዳቸው ለጥያቄዎቻቸው መልስ አላገኙም፤ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያኑ የሚካሄደው ሥነ ሥርዓት በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ታግለው እንዲያሸንፉ አልረዳቸውም።
ምንም እንኳን ወደ ቤተ ክርስቲያን ባትሄድም የወላጆቼን ሃይማኖት ይዣለሁ ትል ይሆናል። አንድ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቄስ እንደተናገሩት ሰዎቹ ያላቸው እምነት ሰንካላ ነው። ሃይማኖትን ሥራዬ ብለው አይከታተሉም። ሌሎቹ ደግሞ በሃይማኖቶች ውስጥ የሚያዩት ግብዝነት አሰልችቷቸው ሃይማኖትን እርግፍ አድርገው ትተውታል። ሕይወትን በሚመለከት ያሏቸው ጥያቄዎች ግን እንዳሉ ናቸው።
አንዳንዶች ከፍተኛ ጥርጣሬ ያደረባቸው ለምንድን ነው?
ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት መኖሪያ ቤት የሌላቸውን የሚረዱ፣ ለችግረኞች ምግብ የሚያድሉና ባሕላዊ በዓሎች ሲኖሩ ወጪውን የሚሸፍኑ ድርጅቶች እንዳሏቸው አብዛኛው ሰው ያውቃል። ይሁን እንጂ ክርስቲያን ባልሆኑ ሕዝቦች መካከል ብቻ ሳይሆን ክርስቲያን ነን በሚሉትም መሃል በሃይማኖት ሳቢያ ስለተቀሰቀሰ አምባጓሮና ደም መፋሰስ የሚያወሩ ዜናዎችን በየቀኑ ይሰማሉ ለማለት ይቻላል። ታዲያ ሰዎች እንዲህ ባለ ሁከት ውስጥ የሚሳተፉ ቡድኖች ትክክለኛውን ሃይማኖት እየተከተሉ ስለመሆናቸው ቢጠራጠሩ ሊያስደንቀን ይገባልን?
ሃይማኖተኛ ሆነው ያደጉ ብዙ ሰዎች አንዳንድ ቤተ ክርስቲያኖች ወላጆች የሌሏቸውን ልጆች ሰብስበው ማሳደጋቸው ጥሩ ነው ብለው ያስቡ ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በየቦታው የሚገኙ ቀሳውስት የሚያሳድጓቸውን ልጆች በግብረ ሥጋ በማስነወራቸው መከሰሳቸውን ሲሰሙ በነገሩ በጣም አፍረዋል። በመጀመሪያ በዚህ ድርጊት የሚወቀሱት ጥቂት ቄሶች ናቸው ብለው ሰዎች ያስቡ ነበር። አሁን ግን ቤተ ክርስቲያኑ ራሱ አንድ መሠረታዊ ችግር ሳይኖርበት አይቀርም ብለው ማሰብ ጀምረዋል።
እንደ ዩጅንያ ያሉ አንዳንድ ሰዎች በሆነ ወቅት ላይ ሃይማኖታቸውን አጥብቀው በመያዝ ከፍተኛ ተሳትፎ ያደርጉ ነበር። ዩጅንያ በአርጀንቲና ስትኖር በወጣትነቷ ወቅት የኤታቴን ድንግል ለመሳለም ከሚሄዱት ሰዎች አንዷ ነበረች። ለ14 ዓመታት መነኩሴ ሆና ገዳም ትኖር ነበር። ከዚያ ገዳሙን ለቀቀችና በአብዮታዊ ትግል በኅብረተሰቡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መዋቅሮች ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ይቻላል ብሎ የሚያምን ሃይማኖትንና ፖለቲካን በአንድነት የሚያራምድ የአንድ ዓለም አቀፋዊ ቡድን አባል ሆነች። እዚያም ባየችውና ባጋጠማት ነገር የተነሣ በአምላክ ላይ የነበራትን እምነትና ትምክህት አጣች። እሷ ትጥር የነበረው የምታምንበት ሃይማኖት ለማግኘት አልነበረም። ትፈልግ የነበረው ለድኾች ፍትሕ ማምጣት የምትችልበትን መንገድና የምታምነው ጓደኛ ለማግኘት ነበር።
ሌሎች ደግሞ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሲደረጉ ባዩአቸው ነገሮች የተነሣ ሃይማኖትን በሩቁ ይሸሹታል። በ1991 ስፑትኒክ በተባለ መጽሔት ላይ አምላክ የለም የሚል አንድ ሰው ያለው አመለካከት ታትሞ ወጥቶ ነበር። ሰውዬው በጻፈው ጽሑፍ ላይ በግልጽ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በአረማዊና በክርስትና ትምህርቶች መካከል ያለው መሠረታዊ ልዩነት አይታየኝም።” ለዚህም ምሳሌ ሲጠቅስ በወርቅ የተዘመዘመ ካባ የለበሱ ቄሶች በመድኃኒት እንዲደርቅ የተደረገ ሬሳ የያዘ ከድንጋይ የተሠራ የሬሳ ሣጥን አጅበው በሞስኮ ዋና ዋና ጎዳናዎች ላይ በቀስታ ይጓዛሉ አለ። ሬሳው ከአንድ ሙዚየም ወጥቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚወሰድ “በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ዘንድ እንደ ቅዱስ ተደርጎ የሚታይ ሰው” ሬሳ ነበር። ይህ ድርጊት ጸሐፊው የጥንቷን ግብፅ ካህናትና ግብፃውያን ሬሳን ለማድረቅ ይጠቀሙበት የነበረውን መሚ የተባለ መድኃኒት እንዲያስታውስ አድርጎት ነበር። እንዲሁም በሞስኮ ሬሳውን አጅበው የተጓዙት ቄሶች “የክርስቲያኖችን ሥላሴ” የሚያምኑ ሲሆኑ ግብፃውያንም ኦሲሪስ፣ አይሲስ እና ሆረስ የተባሉ የሦስት አማልክት ጣምራ ያመልኩ እንደነበረ አስታወሷል።
ይኸው ጸሐፊ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” እንዲሁም ‘ባልንጀራህን ውደድ’ የሚለውን ክርስቲያኖች ስለ ፍቅር ያላቸውን አመለካከት ጠቀሰና አረማዊ በነበረችው ግብፅ ውስጥ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነገር አላገኘሁም አለ። ይሁን እንጂ የታዘበውን ነገር ሲጽፍ፦ “የወንድማማች ፍቅር በዓለም ውስጥ፤ እንዲያውም ክርስቲያን ነኝ በሚለው የዓለም ክፍል እንኳን ድል አድርጎ ለማየት አለመቻሉን” ገልጿል። ከዚያም በማስከተል ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንግሥት ጉዳዮች ጣልቃ መግባት አለብኝ በሚል አቋም በመጽናት ስላፈራችው መጥፎ ፍሬ አስተያየቱን ሰጥቷል። ከተመለከተው ነገር በመነሣት የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እርሱ ለማግኘት እየፈለገ የነበረውን ነገር እንዳልሰጡት ተሰምቶታል።
በአንፃሩ ግን ሌሎች ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው የሚያረኩ መልሶች አግኝተዋል። መልሶቹን ያገኙት ግን በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አይደለም።
ስለ ሙታን እውነቱን አወቀች
የ37 ዓመቷ ማግዳሊና የምትኖረው በቡልጋሪያ ነው። በ1991 አማቷ በመሞታቸው በጣም ተስፋ ቆረጠች። ‘ሙታን የሚሄዱት ወዴት ይሆን? አማቴ የት ናቸው?’ በማለት ደጋግማ ራሷን ጠየቀች። ወደ ቤተ ክርስቲያን ሄደች፤ እቤቷ ደግሞ በአንድ ምስል ፊት ተንበርክካ ጸለየች፤ ነገር ግን ለጥያቄዋ ምንም መልስ አላገኘችም።
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጎረቤቷ ስልክ ደወለላትና ወደ ቤቱ እንድትመጣ ጋበዛት። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ማጥናት የጀመረ አንድ ወጣት ጓረቤቷን እየመጣ ያነጋግረው ነበር። ወጣቱ ስለ አምላክ መንግሥትና አምላክ ምድርን ሰዎች ለዘላለም ተደስተው የሚኖሩባት ገነት ለማድረግ ስላለው ዓላማ ሲናገር አዳመጠችው። በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለው መጽሐፍ ጠረጴዛው ላይ ተቀምጦ ነበር። ወጣቱ በመጽሐፉ በመጠቀም በመክብብ 9: 5 ላይ ያለውን “ሙታን . . . አንዳች አያውቁም” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አነበበላት። የዚያን ዕለት ማታ ብዙ አነበበች። ሙታን ወደ መንግሥተ ሰማያትም ሆነ ወደ ሲኦል ሄደው ሌላ ዓይነት ኑሮ እንደማይኖሩ ከዚህ ይልቅ ልክ በከባድ እንቅልፍ ላይ እንዳሉ ያህል ምንም የማይሰሙ መሆኑን ለማወቅ ቻለች። በአካባቢው ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ በሚያደርገው ስብሰባ ላይ እንድትገኝ የቀረበላትን ግብዣ በደስታ ተቀበለች። ከስብሰባው በኋላ ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ተስማማች። በስብሰባው ላይ ጸሎት የሚቀርበው ለይሖዋ መሆኑን ተመለከተችና እርሷም ያለባትን ሥር የሰደደ ድካም እንድታሸንፍ ይረዳት ዘንድ ወደ ይሖዋ ትጸልይ ጀመር። ጸሎቷ በተመለሰላት ጊዜ ትክክለኛውን ሃይማኖት እንዳገኘች አወቀች።
ትርጉም ያለው ሕይወት አገኙ
አንድሬ ያደገው በቤልጅየም በሚኖር አክራሪ ካቶሊክ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ሲሆን በአካባቢያቸው ለሚኖር አንድ ቄስ ረዳት ሆኖ ይሠራ ነበር። ይሁን እንጂ በዚሁ ጊዜ የተመለከታቸው ነገሮች ለቤተ ክርስቲያኒቱ የነበረውን አክብሮት ዝቅ አደረጉበት። በዚህም ምክንያት የካቶሊክን ሃይማኖት እንዲያው ለስሙ ያህል ይዞ መኖሩን ቀጠለ።
ለ15 ዓመታት ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ ይጫወት ነበር። አንድ ጊዜ እሱ ያለበት ቡድን ለዋንጫ የእግር ኳስ ግጥሚያ ስለነበረው ወደ ጣልያን አገር ሄደ። በዚሁ አጋጣሚ ጳጳሱ ተቀብለው አነጋገሯቸው። ከጳጳሱ ጋር ያሳለፉት ጊዜ በመንፈሳዊ የሚያንጽ ምንም ነገር አልነበረበትም። ጳጳሱ በሀብት የበለጸጉ መሆናቸው አንድሬን በጣም አናደደው። በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የነበረው ጥርጣሬ እየጨመረ ሄደ። ሁለት ጊዜ አግብቶ ስለፈታ ደስተኛ ኑሮ አልነበረውም። የዓለም ሁኔታ ተስፋ አስቆረጠው። በ1989 በማስታወሻ ደብተሩ ላይ ‘በዙሪያችን የሚፈጸሙት የእነዚህ ሁሉ መጥፎ ነገሮች ትርጉም ምንድን ነው?’ በማለት ጽፎ ነበር። ሃይማኖቱ ለዚህ ጥያቄው ምንም መልስ ሊሰጠው አልቻለም።
በ1990 አንድሬ በአይስላንድ ውስጥ የእግር ኳስ አሠልጣኝ ሆኖ እየሠራ ሳለ አይሪስ የምትባል አንዲት የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናዊት አግኝታ አነጋገረችው። ያቀረበችለትን ጽሑፍ ወሰደና ሚስዮናዊቷ ሌላ ጊዜ መጥታ እንድታነጋግረው ፈቃደኛ ሆነ። እሷም ሼል ከሚባለው ባለቤቷ ጋር ተመልሳ ሄደች። ከአንድሬ ጋር ቁጭ ብለው ሲወያዩ አንድሬ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመረዳት ጥልቅ ፍላጎት እንደነበረው በግልጽ ማየት ይቻል ነበር። አስታ የምትባለው ሚስቱም እንደሱ ፍላጎት ነበራት። እኩለ ቀን ላይ ሥልጠና የማይሰጥባቸው ሦስት የዕረፍት ሰዓታት ስላሉት ያንን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲጠቀሙበት ወሰኑ። “ጊዜዬን ቁጭ ብዬ በማረፍ ከማሳልፈው ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ሳጠናበት ይበልጥ እነቃቃለሁ” ይላል። እያደር መጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቻቸውን መለሰላቸው። ቀስ በቀስ በይሖዋና በመንግሥቱ ላይ ያላቸው እምነት እያደገ ሄደ። ሰላም የሰፈነበትና ‘በዙሪያችን የሚፈጸሙት እነዚህ ሁሉ መጥፎ ነገሮች’ የሌሉበት አዲስ ዓለም እንደሚመጣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ግሩም ተስፋ እውን እየሆነላቸው መጣ። በአሁኑ ጊዜ አንድሬና አስታ አዲስ ያገኙትን እምነታቸውን ለሌሎች እያካፈሉ ናቸው።
ማግዳሊና፣ አንድሬ እና አስታ በመጨረሻው ትክክለኛውን ሃይማኖት እንዳገኙ እርግጠኞች ናቸው። ዩጅንያም በፖለቲካ ለዓለም ችግሮች መፍትሔ ለማምጣት ስትሞክር ከቆየች በኋላ በመጨረሻው ለእሷ ትክክለኛ ሆኖ የታያትን ሃይማኖት በይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ አገኘች። ይሁን እንጂ አንድ ሃይማኖት ትክክለኛ መሆን አለመሆኑን በእርግጥ የሚወስነው ነገር ምንድን ነው? እስቲ ቀጥሎ ያለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከአምስት ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ለጥያቄዎቻቸው የሚያረኩ መልሶች ለማግኘት በሚያደርጉት ፍለጋ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የሚያደርጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየረዳቸው ነው