የመንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የኢየሱስ በጎች ድምፁን ይሰማሉ
የስብከቱ ሥራ በሁሉም የምድር ክፍሎች እየተስፋፋ ሲሄድ ይሖዋ በመላእክቱ አማካኝነት አገልጋዮቹን ወደ በግ መሰል ሰዎች ይመራቸዋል። እነርሱም የኢየሱስን ድምፅ ሰምተው የዘላለም ሕይወት ተስፋ አግኝተው እርሱን ማገልገል ይማራሉ። ኢየሱስ በዮሐንስ 10:27, 28 ላይ “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ እኔም አውቃቸዋለሁ ይከተሉኝማል፤ እኔም የዘላለም ሕይወትን እሰጣቸዋለሁ” ብሎአል። በማዳጋስካር የሚኖሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የኢየሱስን ድምፅ እንዴት እንደሰሙ ተመልከቱ።
አንድ የይሖዋ ምሥክር በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ እና ከወጣትነትህ የተሻለውን ማግኘት የተሰኙትን መጻሕፍት ቅጂዎች የታመመ አባቱን ሊመረምር ለመጣው ሐኪም ሰጠው።
ሐኪሙ ፕሮቴስታንት ነበርና ምሥክሮቹን አጥብቆ ይቃወም ነበር። ሆኖም መጽሐፉን አነበበ፣ ጥቅሶቹንም ከገዛ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ እያወጣ መረመረ። ካቶሊካዊትና እንደ እርሱ ሐኪም የሆነችው ሚስቱ የወጣትነትህ መጽሐፍ በተለይ ለእርሷ የተጻፈ መስሎ ስለተሰማት ደጋግማ አነበበችው። ማኅበሩ 1914 ትልቅ ትርጉም ያለው ዓመት ስለመሆኑ የሰጠው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ማብራሪያ ሁለቱንም አስገረማቸው። ባልየው መጽሐፉን ከሰጠው ምሥክር ጋር ተገናኘ። ምሥክሩም ሕይወት—እንዴት መጣ? በዝግመተ ለውጥ ነውን ወይስ በፍጥረት? የሚለውን መጽሐፍ ሰጠውና ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ እርሱንና ሚስቱን ለመጎብኘት ዝግጅት አደረገ። ሊጠይቃቸው በሄደ ጊዜም ከእነርሱና ከሦስት ልጆቻቸው ጋር የዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀታቸው ያደረጉት መሻሻል በጣም ፈጣን ነበር።
ከመጀመሪያው ጥናት በኋላ መላው ቤተሰብ በመንግሥት አዳራሹ በስብሰባዎች መገኘት ጀመረና ከዚያም በኋላ ወዲያው በቲኦክራቲካዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መካፈል ጀመሩ። የልጆቹ ጠባይ በጣም ተሻሻለ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው የልደት በዓላቸውንና ሌሎችንም ሃይማኖታዊ በዓላት ማክበር ክርስቲያናዊ እንዳልሆነ ስለተማሩ በዓላቱን ማክበር ተዉ። ምንም እንኳን ስለ ደም የሚመለከተውን ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታቸው ላይ ገና ያልተወያዩበት ቢሆንም ባልየው ለአንድ ዘመዱ ደም ለመስጠት እንቢ አለ። ወዲያው የካራቴ ዩኒፎርሙ ከቁም ሣጥኑ ውስጥ ተወገደ፤ ለልጆቹ የሚሆን ልብስ እንዲሰፋበት ወደ ልብስ ሰፊ ላከው። ስለ ጥንቆላና ስለ ኮከብ ቆጠራ የሚገልጹ መጽሔቶቹንና መጽሐፎቹን በሙሉ አቃጠላቸው። ማጥናት በጀመሩ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ እርሱና ሚስቱ ከየቤተ ክርስቲያኖቻቸው በፈቃዳቸው ለቀቁና በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ። አሁን ተጠምቀዋል።
◻ በታይላንድ አንዲት ሴት እውነትን ትፈልግ ነበር። ቡዲሂስት ብትሆንም እንኳን በሃይማኖቱ ውስጥ ብዙ ግብዝነትና ስግብግብነት ስለተመለከተች ለሃይማኖቷ ያደረች ሆና አታውቅም ነበር። በተጨማሪም አስቀያሚ ሆነው ያገኘቻቸው ብዙ ባሕሎች ነበሩ። ሁሉም ሰልችቷት ነበር።
ከዚያም አንዲት ጎረቤቷ ክርስቲያኖችን ደግሞ እንድትሞክራቸው ብላ ወደ ጴንጠቆስጠ ቤት ክርስቲያን ወሰደቻት። ስብሰባው በመካሄድ ላይ እንዳለ ሁሉም የሚጸልዩት እየጮኹ ስለነበር በጫጫታው ምክንያት ከዚያ ወጥታ ወደ ቤቷ ለመሄድ በጣም ፈልጋ ነበር። ያ ቀ በቤተ ክርስቲያኑ የተሰበሰበችበት የመጨረሻውም ቀን ሆነ።
በኋላም የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ሞክራ ነበር። ነገር ግን ብዙ ጊዜ ከተከታተለች በኋላ ግብዝነትና ስግብግብነት መኖሩንና የቀሳውስቱን የቅንጦት ኑሮ ተገነዘበች። ተጸየፈችውና ወደ ቤተ ክርስቲያኑ መሄዷን አቆመች። ቄሱ ለምን እንደተወች ለማወቅ ጉጉት አድሮበት ነበር። ምክንያቱን ሲረዳ በቀልድ አነጋገር “በእርግጥ በጣም ጥብቅ የሆኑ ሰዎችን ለማግኘት ትፈልጊ እንደሆነ ወደ ይሖዋ ምሥክሮች ሂጂ” አላት። “እነርሱ ደግሞ የት ነው የሚገኙት?” ብላ ጠየቀችው። ቄሱ “በውኃ ማከፋፈያው አጠገብ ናቸው” ብሎ መለሰ። በሚቀጥለው ቀን ልትፈልጋቸው ሄደች፤ ግን አላገኘቻቸውም። ተስፋ ብትቆርጥም ሁልጊዜ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ታስብ ነበር።
አንድ ቀን ከጎረቤቶቿ አንዷ በማሾፍ “በቅርቡ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ትሆናለህ!” ብላ ለሌላ ሰው ስትናገር ሰማች። ይህን ስትሰማ ወደ ጎረቤቷ ሮጣ ሄደችና “እዚህ አካባቢ የይሖዋ ምሥክሮች አሉ እንዴ?” ብላ ጠየቀቻት። መልሱ “አዎ” ነበር። “አንዳንዶቹ ከቤት ወደ ቤት እየሰበኩ ወደ ሰፈራችን ይመጣሉ። በንጹሕና ጥዱ አለባበሳቸው ታውቂያቸዋለሽ” አለቻት። በዚህ ጊዜ ልትፈልጋቸው ሮጣ ወጣች። መጀመሪያ አላገኘቻቸውም ነበር፤ ወደ ቤቷ ተመልሳ ስትሄድ ግን ጥዱ ልብስ የለበሱ ሁለት ሴቶች ከአንድ ሰው ጋር ሲነጋገሩ ተመለከተች። ቀረበችና የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ጠየቀቻቸው። እነርሱም የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን በነገሯት ጊዜ “እባካችሁ ወደ ቤቴ ኑ። ላነጋግራችሁ እፈልጋለሁ” አለቻቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላትና ከቤተሰቧ አባሎች ተቃውሞና ስድብ ቢደርስባትም ይህች ሴት በስብሰባዎች መገኘትና ለጎረቤቶቿም መመስከር ጀመረች።
ኢየሱስ በእርግጥም በጎቹን ስለሚያውቅ ከጥፋት ተርፈው ወደ ራሱ ጽድቅ ያለበት አዲስ ዓለም ለመግባት እንዲችሉ ወደ ድርጅቱ እያሰባሰባቸው ነው።