ትክክለኛውን ሃይማኖት ማወቅ ኃላፊነት ያስከትላል
“የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት [ደስተኞች አዓት] ናቸው።”—ሉቃስ 11:28
1. ትክክለኛውን ሃይማኖት ካገኙ በኋላ ሕይወታቸውን በርሱ መሠረት የቀረጹ ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?
ትክክለኛውን ሃይማኖት ለይቶ ማወቁ ብቻ አይበቃም። ትክክለኛና እውነት የሆነውን ነገር የምንወድድ ከሆንን፣ ትክክለኛውን ሃይማኖት ካገኘን በኋላ አኗኗራችንን በእርሱ መሠረት እንቀርጻለን። እውነተኛው ሃይማኖት እንዲያው የአእምሮ ፍልስፍና አይደለም፤ የሕይወት መንገድ ነው።—መዝሙር 119:105፤ ኢሳይያስ 2:3፤ ከሥራ 9:2 ጋር አወዳድር።
2, 3. (ሀ) ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያጎላው እንዴት ነው? (ለ) ትክክለኛውን ሃይማኖት ያወቀ ሁሉ ምን ኃላፊነት አለበት?
2 አምላክ ፈቃዴ ነው ብሎ የገለጸውን ነገር መፈጸም በጣም አስፈላጊ መሆኑን ኢየሱስ ክርስቶስ አጥብቆ ተናግሯል። ኢየሱስ ዛሬ የተራራ ስብከት ተብሎ የሚጠራውን ንግግሩን ሲደመድም ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡት የአባቱን ፈቃድ የሚያደርጉት ብቻ እንጂ ጌታ ሆይ እያሉ የሚጠሩት ሁሉ (ክርስቲያን ነን የሚሉ ሁሉ) አለመሆናቸውን አሳውቋል። የቀሩት “ዓመፀኞች” ተብለው እንዳይገቡ ይከለከላሉ ብሏል። ለምን ዓመፀኞች ተባሉ? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የአምላክን ፈቃድ አለማድረግ ኃጢአት ነው፤ ማንኛውም ኃጢአት ደግሞ ዓመፅ ነው። (ማቴዎስ 7:21–23፤ 1 ዮሐንስ 3:4፤ ከሮሜ 10:2, 3 ጋር አወዳድር።) አንድ ሰው ትክክለኛው ሃይማኖት የትኛው እንደሆነ ያውቅ ይሆናል። እውነተኛውን ሃይማኖት የሚያስተምሩትንም ሰዎችን ያመሰግን፤ ተከታዮቹንም ያደንቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ እርሱም ራሱ ያንን ሃይማኖት በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። (ያዕቆብ 4:17) ያንን ኃላፊነት ቢቀበል ሕይወቱ ግሩም ይሆንለታል፤ በሌላ መንገድ ሊያገኘው የማይችለውን ደስታም ያገኛል።
3 ባለፈው ርዕሰ ትምህርት እውነተኛው ሃይማኖት ተለይቶ የሚታወቅባቸውን ስድስት ነጥቦች ተመልክተን ነበር። እያንዳንዱ ነጥብ እውነተኛውን ሃይማኖት ለመለየት ይረዳናል። ከዚህም ሌላ በግላችን ልንወጣው የሚያስፈልግ ፈተናና ጥሩ አጋጣሚ ከፊታችን ያስቀምጣል። እንዴት?
ለአምላክ ቃል ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
4. (ሀ) አዲሶች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መቀራረብ ሲጀምሩ ስለ ምሥክሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀም ወዲያውኑ ምን ይገነዘባሉ? (ለ) የይሖዋ አገልጋዮች በመንፈሳዊ በደንብ የተመገቡ መሆናቸው ምን ውጤት አምጥቶላቸዋል?
4 የይሖዋ ምሥክሮች ፍላጎት ያላቸውን አዳዲስ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ሲያስጠኗቸው ከነዚህ አዲሶች መካከል ብዙዎቹ የተማሩት ነገር ከመጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ወዲያው ይገነዘቡታል። ለጥያቄዎቻቸው መልስ የሚሰጣቸው በቤተ ክርስቲያን ወጎች፣ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣ የሰዎች ልማድ፣ ወይም ታዋቂ ሰዎች በሰጡት አስተያየት ላይ ተመርኩዞ አይደለም። እንደ ወሳኝ ባለ ሥልጣን ተደርጎ የሚጠቀስላቸው የአምላክ ቃል ራሱ ነው። ወደ መንግሥት አዳራሹ ሲሄዱ፣ እዚያም ዋነኛው ማስተማሪያ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን ይመለከታሉ። በቅንነት እውነትን የሚፈልጉ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች መካከል የሚያዩት ደስታ ምሥክሮቹ በመንፈሳዊ ረገድ ከአምላክ ቃል በሚገባ የተመገቡ በመሆናቸው የመጣ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አይወስድባቸውም።—ኢሳይያስ 65:13, 14
5. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮችን የሚመለከቱ ሰዎች ምን ፈታኝ ሁኔታ ተደቅኖባቸዋል? (ለ) ምሥክሮቹ ካገኙት ደስታ እነርሱም ተካፋይ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?
5 ይህን ከተገነዘብክ ምን ታደርጋለህ? ነገሩ ገብቶህ ከሆነ ዳር ቆመህ ተመልካች አትሆንም፤ እንደዚያ መሆንም የለብህም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ቃል ‘የማያደርጉት’ ነገር ግን ‘ሰሚዎች ብቻ’ የሆኑት ሰዎች ‘የውሸት ምክንያት እያቀረቡ ራሳቸውን እንደሚያታልሉ’ ይገልጻል። (ያዕቆብ 1:22) እነሱ የፈለጉትን ቢሉም አምላክን ሳይታዘዙ መቅረታቸው እርሱን በእውነት እንደማይወዱት ስለሚያሳይ ራሳቸውን እያታለሉ ናቸው። በሥራ ያልተደገፈ እምነት የሞተ ነው። (ያዕቆብ 2:18–26፤ 1 ዮሐንስ 5:3) በተቃራኒው ግን ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተገፋፍቶ ይህን በተግባር የሚያሳይ ሰው ደስተኛ ይሆናል። አዎን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገለጸው “የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት [ደስተኞች አዓት] ናቸው።”—ያዕቆብ 1:25፤ ሉቃስ 11:28፤ ዮሐንስ 13:17
6. የአምላክን ቃል በእውነት የምናደንቅ ከሆንን እያንዳንዳችን በየትኛው አጋጣሚ ለመጠቀም እንጥራለን?
6 ስለ አምላክ ፈቃድ ያለህ እውቀት እያደገ ሲሄድና የተማርካቸውን ተጨማሪ ነገሮች በሥራ ላይ ስታውላቸው ይህ ደስታህ ይበልጥ እየጨመረ ይሄዳል። የአምላክን ቃል ለማጥናት ምን ያህል ጥረት ታደርጋለህ? በፊት መሃይማን የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ማንበብ ለመቻል ብዙ ጥረዋል። ይህንንም ያደረጉት በተለይ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማንበብና ሌሎችን ለማስተማር ሲሉ ነው። ሌሎች ደግሞ በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ከእንቅልፋቸው ቀደም ብለው በመነሣት ለተወሰነ ሰዓት መጽሐፍ ቅዱስን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ እንደ መጠበቂያ ግንብ ያሉ ጽሑፎችን ያነባሉ። አንተ በግልህ መጽሐፍ ቅዱስን ከመጀመሪያው ጀምረህ ስታነብ ወይም በሌሎች የጥናት ጽሑፎች ውስጥ የተጠቀሱ ጥቅሶችን እያወጣህ ስታነብ እዚያ ላይ ያሉትን የይሖዋ ሕግጋትና ትዕዛዛት ልብ በል። እንዲሁም መመሪያ ይሆኑን ዘንድ የተሰጡንን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማስተዋል ጥረት አድርግ። እያንዳንዱ ምንባብ ስለ አምላክ፣ ስለ ዓላማዎቹና እርሱ ከሰዎች ጋር ስላደረጋቸው ግንኙነቶች በሚገልጸው ሐሳብ ላይ አሰላስል። የተማርከው ነገር ልብህን እንዲቀርጸው ጊዜ ስጠው። የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በሕይወትህ ውስጥ ይበልጥ ተግባራዊ የምታደርግባቸው መንገዶች እንዳሉ ፈልግ።—መዝሙር 1:1, 2፤ 19:7–11፤ 1 ተሰሎንቄ 4:1
ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደርክ ነህን?
7. (ሀ) የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ሰዎች አምላክን ለማምለክ ያደረጉትን ጥረት የነካው እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሰው ስለ ይሖዋ እውነቱን ሲማር ምን ሊያደርግ ይችል ይሆናል?
7 በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛው አምላክ ሥላሴ አለመሆኑን መማራቸው እፎይታን አምጥቶላቸዋል። ነገሩ “ምሥጢር ነው” የሚለው አባባል አያረካቸውም ነበር። ማንነቱን ለመረዳት አዳጋች ወደሆነ አምላክ እንዴት ሊቀርቡ ይችላሉ? በዚህ ምክንያት (በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፈጽሞ ስሙን ሰምተውት የማያውቁትን) አብን ተዉና ኢየሱስን እግዚአብሔር ነው በማለት ማምለክ ወይም (‘የእግዚአብሔር እናት’ ናት ተብሎ ስለተነገራቸው) ማርያምን ወደ ማምለክ አዘነበሉ። አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን ገልጦ የአምላክ የግል ስም ይሖዋ መሆኑን ሲነግራቸው ግን ደስ ብሏቸዋል። (መዝሙር 83:18 አዓት) አንዲት ቬንዙዌላዊት መለኮታዊውን ስም ስታይ በደስታ ከመፈንደቋ የተነሣ ይህን ውድ እውነት የነገረቻትን ወጣት እህት አቀፈቻት። የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላትም ተስማማች። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ኢየሱስ ‘አምላኬ አምላካችሁ’ ብሎ ስለ አባቱ እንደተናገረና አባቱን ‘ብቻህን እውነተኛ አምላክ የሆንክ’ እንዳለው ሲማሩ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ የሚያስተምረው ነገር ለመረዳት አዳጋች አለመሆኑን ተገንዝበዋል። (ዮሐንስ 17:3፤ 20:17) የይሖዋን ባሕርያት ሲያውቁ ወደርሱ ለመቅረብ፣ ወደርሱ ለመጸለይና እርሱን ለማስደሰት ፈልገዋል። በውጤቱስ ምን ተገኘ?
8. (ሀ) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለይሖዋ ፍቅር ስላላቸውና እርሱን ሊያስደስቱት ስለሚፈልጉ ምን አድርገዋል? (ለ) የክርስቲያኖች ጥምቀት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
8 ባለፉት አሥር ዓመታት በስድስት አህጉሮችና በበርካታ ደሴቶች የሚኖሩ 2,528,524 ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ይህን ውሳኔያቸውን በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል። አንተ ከነሱ አንዱ ነበርክ? ወይስ ገና ልትጠመቅ እየተዘጋጀህ ነህ? ጥምቀት በእያንዳንዱ እውነተኛ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት እርምጃ ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ ከሁሉም ሕዝቦች ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉና እንዲያጠምቋቸው አዟል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ ከተጠመቀ በኋላ ወዲያውኑ ይሖዋ ከሰማይ “የምወድህ ልጄ አንተ ነህ፣ በአንተ ደስ ይለኛል” ብሎ መናገሩንም ልብ ልንለው ይገባናል።—ሉቃስ 3:21, 22
9. በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ዝምድና ጠብቆ ለመኖር በኛ በኩል ምን ይፈለግብናል?
9 በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና እንደ ውድ ሀብት ልንንከባከበው ይገባናል። ራስህን ለአምላክ በመወሰንና በጥምቀት እንዲህ ዓይነቱን ዝምድና ጀምረህ ከሆነ ይህን ዝምድናህን ሊያበላሽብህ የሚችል ማንኛውንም ነገር አስወግድ። ልዩ ልዩ የኑሮ አሳቦችና ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ ለዚህ ዝምድና ሁለተኛ ደረጃ እንድትሰጠው እንዲያደርጉህ አትፍቀድላቸው። (1 ጢሞቴዎስ 6:8–12) በምሳሌ 3:6 ላይ ከሚገኘው “በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” ከሚለው ምክር ጋር ተስማምተህ ኑር።
የክርስቶስ ፍቅር ምን ያህል በጥልቅ ነክቶሃል?
10. ይሖዋን ማምለካችን ኢየሱስን ችላ እንድንለው የማያደርገን ለምንድን ነው?
10 አንድ ሰው ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን በትክክል መረዳቱ ኢየሱስ ክርስቶስን ችላ እንዲለው እንደማያደርገው የታወቀ ነው። እንዲያውም በተቃራኒው ራእይ 19:10 (አዓት) “ትንቢት እንዲነገር የተደረገው ስለ ኢየሱስ ለመመስከር ሲባል ነው” ይላል። ከዘፍጥረት እስከ ራእይ የሚገኙ በመንፈስ አነሣሽነት የተነገሩ ትንቢቶች ኢየሱስ ክርስቶስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ስላለው ሚና ዝርዝር ማብራሪያ ይዘዋል። አንድ ሰው እነዚህን ነገሮች አንድ በአንድ በሚገባ ካወቃቸው ሕዝበ ክርስትና ስለ ክርስቶስ ከምታስተምረው የተዛባና የተሳሳተ ትምህርት የተለየ አስደናቂ ሥዕል ቁልጭ ብሎ ይታየዋል።
11. በፖላንድ የምትኖር አንዲት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ልጅ የሚያስተምረውን እውነት ማወቋ የነካት እንዴት ነው?
11 አንድ ሰው ስለ አምላክ ልጅ እውነቱን ማወቁ በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣለት ይችላል። በፖላንድ የምትኖረው ዳኑታ ያጋጠማት ይኸው ነበር። ለስምንት ዓመታት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ትገናኝ ነበር። የሚያስተምሩት ትምህርት ደስ ይላታል። ይሁን እንጂ እውነተኛውን አምልኮ የሕይወት መንገዷ አላደረገችውም ነበር። አንድ ቀን ክርስቶስ ያሳለፈውን ሕይወት በቀላሉ መረዳት በሚቻልበት መንገድ የሚተርከው እስከ ዛሬ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው የተባለውን መጽሐፍ ወሰደች።a ማታ እስቲ አንድ ምዕራፍ ላንብብ ብላ መጽሐፉን ጀመረች። መጽሐፉን ያስቀመጠችው ግን ንጋት ላይ ሙሉውን መጽሐፍ አንብባ ስትጨርስ ነበር። አለቀሰች። “ይሖዋ ሆይ፣ ይቅር በለኝ” ስትል ለመነችው። ባነበበችው ነገር የተነሣ ይሖዋና ልጁ ያሳዩት ፍቅር ከበፊቱ ይበልጥ ግልጽ ሆነላት። ለስምንት ዓመታት አምላክ በትዕግሥት ይሰጣት ለነበረው እርዳታ አመስጋኝ በመሆን ፈንታ ችላ ስትለው እንደነበረ ተገነዘበች። በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላትን እምነት መሠረት በማድረግ ሕይወቷን ለአምላክ መወሰኗን ለማሳየት በ1993 ተጠ መቀች።
12. ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት ማግኘታችን ሕይወታችንን የሚነካው እንዴት ነው?
12 ‘ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት’ ማግኘታችን ትጉና ፍሬያማ ክርስቲያኖች ከመሆናችን ጋር የተዛመደ ነው። (2 ጴጥሮስ 1:8) የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች በማካፈሉ ሥራ የቱን ያህል ትካፈላለህ? እያንዳንዱ ሰው ሊሠራ የሚችልበት መጠን በብዙ ሁኔታዎች ሊወሰንበት ይችላል። (ማቴዎስ 13:18–23) አንዳንዶቹን ሁኔታዎች ልንለውጣቸው አንችልም፤ ሌሎቹን ግን እንችላለን። መለወጥ የምንችላቸውን ነገሮች ለይተን ለማወቅ አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ የሚገፋፋን ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል” በማለት ጽፏል። በሌላ አባባል እርሱ ሕይወቱን ለኛ ሲል በመሠዋት ያሳየን ፍቅር በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ ለፍቅሩ ያለን አድናቆት እየጨመረ ሲሄድ እርምጃ ለመውሰድ ልባችን በጥልቅ ይገፋፋናል። ስለዚህ ራስ ወዳድ የሆኑ ግቦችን መከታተላችንን መቀጠላችንና አኗኗራችን በአንደኛ ደረጃ ራሳችንን ብቻ የሚያስደስት እንዲሆን መጣራችን በጭራሽ ተገቢ አለመሆኑን እንገነዘባለን። በዚህ ፈንታ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ እንዲያደርጉት ላስተማራቸው ሥራ ቀዳሚውን ቦታ ለመስጠት እንችል ዘንድ ሥራዎቻችንን እናስተካክላለን።—2 ቆሮንቶስ 5:14, 15
ከዓለም የተለየን መሆን ያለብን እስከ ምን ድረስ ነው?
13. ራሱን የዓለም ክፍል ያደረገ ሃይማኖት አባል ለመሆን የማንፈልገው ለምንድን ነው?
13 ሕዝበ ክርስትናና ሌሎች ሃይማኖቶች የዚህ ዓለም ክፍል ለመሆን በመፈለጋቸው ምን ዓይነት ታሪክ እንዳስመዘገቡ መመልከት አያዳግትም። የቤተ ክርስቲያኑን ገንዘብ ለአብዮታዊ እንቅስቃሴዎች ማራመጃ ተጠቅመውበታል። ቀሳውስት የሽምቅ ተዋጊዎች ሆነዋል። ጋዜጦች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች እየተዋጉ ስላሉ የሃይማኖት ቡድኖች የሚገልጹ ዘገባዎችን በየዕለቱ ያቀርባሉ። በደም የተነከረው እጃቸው ደም ያንጠባጥባል። (ኢሳይያስ 1:15) በዓለም ዙሪያ ቀሳውስት የፖለቲካውን መስክ ለመቀየስ ይጥራሉ። እውነተኛ አምላኪዎች በዚህ ጉዳይ ውስጥ እጃቸውን አያስገቡም።—ያዕቆብ 4:1–4
14. (ሀ) ከዓለም እንደተለየን ለመኖር ከፈለግን በግላችን ከምን መራቅ አለብን? (ለ) ዓለማዊ በሆኑ ጠባዮችና ድርጊቶች እንዳንጠመድ ምን ሊረዳን ይችላል?
14 ነገር ግን ከዓለም መለየት ሲባል በዚህ ብቻ አያበቃም። የዓለም ሰዎች ለገንዘብና ገንዘብ ለሚገዛቸው ነገሮች ባላቸው ፍቅር፣ ዝና ለማትረፍ ባላቸው ፍላጎት፣ ሳያቋርጡ ደስታን የሚያሳድዱ በመሆናቸውና ለሌሎች ምንም ደንታ የሌላቸው በመሆናቸው፣ በአጭበርባሪነታቸውና በተሳዳቢነታቸው፣ ለሥልጣን አልገዛም በማለታቸውና ራሳቸውን መግዛት የማይችሉ በመሆናቸው የታወቁ ናቸው። (2 ጢሞቴዎስ 3:2–5፤ 1 ዮሐንስ 2:15, 16) አንዳንድ ጊዜ በራሳችን አለፍጽምና ምክንያት ከነዚህ ባሕርያት አንዳንዶቹን እናንጸባርቅ ይሆናል። ከእነዚህ ወጥመዶች ለመሸሽ በምናደርገው ትግል ምን ነገር ለማሸነፍ ሊረዳን ይችላል? ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ያለው ማን እንደሆነ ማስታወስ ያስፈልገናል። ‘ዓለምም በሞላው በክፉው ተይዟል።’ (1 ዮሐንስ 5:19) አንድ ድርጊት ምንም ያህል የሚማርክ ቢመስል፣ የቱንም ያህል ሰዎች እንደዚያ የሚያደርጉ ቢሆኑ፣ ከድርጊቱ በስተጀርባ ያለው ዋነኛው የይሖዋ ጠላት ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑን ስናስብ ድርጊቱ ምን ያህል አስቀያሚ እንደሆነ እንገነዘባለን።—መዝሙር 97:10
ፍቅርህ እስከምን ድረስ ይሄዳል?
15. የተመለከትከው ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ትክክለኛውን ሃይማኖት ለይተህ እንድታውቅ የረዳህ እንዴት ነው?
15 ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መቀራረብ በጀመርክ ጊዜ በመካከላቸው የሚታየው ፍቅር ከዓለም መንፈስ የተለየ በመሆኑ ሳይማርክህ እንዳልቀረ አያጠራጥርም። ራስ ወዳድነት ለሌለበት ፍቅር የሚሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ንጹሑን የይሖዋን አምልኮ ከሌሎቹ የአምልኮ ዓይነቶች ሁሉ ልዩ ያደርገዋል። ትክክለኛውን ሃይማኖት የያዙት ያለ ምንም ጥርጥር የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው ብለህ እንድታምን ያደረገህ ይህ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል።—ዮሐንስ 13:35
16. በግለሰብ ደረጃ ፍቅራችንን ልናሰፋ የምንችልባቸው ምን አጋጣሚዎች ሊኖሩን ይችላሉ?
16 ታዲያ አንተም ጭምር ከክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱ መሆንህን ይህ ጠባይ ይመሠክርልሃልን? የምታሳየውን ፍቅር ልታሰፋ የምትችልባቸው መንገዶች ይኖሩ ይሆን? ሁላችንም ፍቅራችንን ልናሰፋው እንደምንችል ምንም አያጠራጥርም። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ እርስ በርስ ወዳጃዊ ስሜት ማሳየታችን ብቻ አይበቃም። የሚወዱንን ብቻ ብንወድስ ከዓለም በምን እንለያለን? መጽሐፍ ቅዱስ “ከሁሉ በፊት እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ተዋደዱ” በማለት አጥብቆ ይመክረናል። (1 ጴጥሮስ 4:8) የበለጠ ፍቅር ማሳየት የሚኖርብን ለማን ነው? አስተዳደጉ ከኛ የተለየ ለሆነና በግል የማንወዳቸውን አንዳንድ ነገሮች ለሚያደርግ ወንድም ነውን? ወይም እንደዚያ ለምታደርግ እህት ነው? በሕመም ወይም በእርጅና ምክንያት አዘውትሮ በስብሰባ ላይ ለማይገኝ ሰው ይሆን? ለትዳር ጓደኛችን ነውን? ወይስ ዕድሜያቸው እየገፋ ለሄደው ወላጆቻችን? ፍቅርንና ሌሎቹንም የመንፈስ ፍሬዎች በሚገባ ሲያሳዩ የኖሩ አንዳንዶች ከቤተሰባቸው አባል አንዱ ከፍተኛ የአካል ጉዳት ሲደርስበትና እርሱን እንዲያስታምሙት የሚያደርግ በጣም ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው እነዚህን ጠባዮች እንደ አዲስ መማር እንደ ጀመሩ ተሰምቷቸዋል። እርግጥ ነው፤ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም እንኳን ፍቅራችን ከቤተሰባችን ክልል ውጭ ያሉትንም ጭምር ማቀፍ ይኖርበታል።
ስለ መንግሥቲቱ መመሥከሩን ምን ያህል አክብደህ ትመለከተዋለህ?
17. የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጥተው እኛን በማነጋገራቸው ከተጠቀምን እኛ ደግሞ አሁን ምን እንድናደርግ ልንገፋፋ ይገባናል?
17 መሰሎቻችን ለሆኑት የሰው ልጆች ፍቅር የምናሳይበት አንዱ ትልቅ መንገድ ስለ አምላክ መንግሥት ለነሱ መመሥከር ነው። ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረውን ይህን ሥራ እየሠራ ያለው አንድ የሰዎች ቡድን ብቻ ነው። (ማርቆስ 13:10) እነሱም የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። እኛ በግላችን ከዚህ ሥራ ጥቅም አግኝተናል። አሁን ደግሞ በተራችን ሌሎችን የመርዳት መብት አለን። አምላክ ስለዚህ ጉዳይ ያለውን ዓይነት አመለካከት ቢኖረን ይህ ሥራ በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ሥፍራ ይይዛል።
18. የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች የተባለውን መጽሐፍ ማንበባችን ስለ መንግሥቲቱ በመመሥከሩ ሥራ ያለንን ተሳትፎ እንዴት ሊነካው ይችላል?
18 የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች በተባለው መጽሐፍ ውስጥ በነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የመንግሥቱ መልእክት ራቅ ወዳሉት የምድር ክፍሎች በሙሉ እንዴት እንደተዳረሰ የሚገልጽ ስሜትን የሚቀሰቅስ ዘገባ ቀርቦልናል። እንግሊዝኛ የምታውቅ ከሆነ ይህን መጽሐፍ አንብበው። በምታነብበት ጊዜ ግለሰቦች ስለ መንግሥቲቱ ምሥክርነቱን በመስጠቱ ሥራ የተካፈሉባቸውን መንገዶች ሁሉ ይበልጥ ልብ ብለህ ተከታተለው። አርዓያቸውን ልትከተል የምትችላቸው ይኖሩ ይሆን? ሁላችንም ብዙ አጋጣሚዎች ተከፍተውልናል። ለይሖዋ ያለን ፍቅር በነዚህ አጋጣሚዎች እንድንጠቀም የሚያንቀሳቅሰን ይሁን።
19. ትክክለኛውን ሃይማኖት ማወቁ የሚያስከትለውን ኃላፊነት በመቀበላችን የተጠቀምነው እንዴት ነው?
19 በዚህ መንገድ የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ ራሳችንን ስናቀርብ ‘የመኖር ትርጉሙ ምንድን ነው?’ ለሚለው ጥያቄ መልስ እናገኛለን። (ራእይ 4:11) መልሱ ጠፍቶን በባዶነት ስሜት ተውጠን ስንቃትት አንኖርም። ራስህን ለይሖዋ አምላክ አገልግሎት በሙሉ ነፍስ ከማቅረብ የበለጠ እርካታ የሚያስገኝልህ ሌላ ሥራ የለም። በዚህ ሥራ ከተካፈልን እንዴት ያለ ታላቅ ተስፋ ይጠብቀናል! ችሎታዎቻችንን ሁሉ አምላክ ሰውን ከፈጠረበት ፍቅራዊ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመጠቀም የምንችልበት በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚያረካ የዘላለም ሕይወት ይጠብቀናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ አንድ ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርጎ መቀበሉና ይሖዋን ደግሞ እንደ እውነተኛ አምላክ አድርጎ ማክበሩ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ እውነተኛው ሃይማኖት ስለ ኢየሱስ የቤዛነት ሚና ምን ያስተምራል?
◻ ክርስቲያኖች ከዓለም መለየትና ራስ ወዳድነት የሌለበት ፍቅር ማሳየት የሚገባቸው ለምንድን ነው?
◻ ስለ መንግሥቲቱ መመሥከር በትክክለኛው ሃይማኖት ውስጥ ምን ቦታ አለው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥምቀት እውነተኛው አምልኮ የሚያስከትላቸውን ኃላፊነቶች ለመቀበል የሚወሰድ በጣም አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ነው። በየወሩ በዓለም ዙሪያ 25,000 የሚያክሉ ሰዎች ይህን እርምጃ ይወስዳሉ
ሩስያ
ሴኔጋል
ፓፑዋ ኒው ጊኒ
ዩናይትድ ስቴትስ
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማካፈል የእውነተኛው አምልኮ ክፍል ነው
ዩናይትድ ስቴትስ
ዩናይትድ ስቴትስ
ብራዚል
ሆንግ ኮንግ