የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 7/1 ገጽ 23-28
  • ለሥልጣን በደስታ መገዛት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለሥልጣን በደስታ መገዛት
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ለይሖዋ ሉዓላዊነት በፈቃደኝነት መገዛት
  • ለንጉሣችን በደስታ መገዛት
  • የበላይ ተመልካቾች በደስታ ይታዘዛሉ
  • ቲኦክራሲያዊ ተገዥነት
  • በደስታ ማገልገል
  • በደስታ ከመገዛት የሚገኝ ሰላም
  • አፍቃሪ ለሆኑት እረኞች በትሕትና ተገዙ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2007
  • በቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ሥር የሚያገለግሉ እረኞችና በጎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • ክርስቶስ ጉባኤውን ይመራል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2002
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 7/1 ገጽ 23-28

ለሥልጣን በደስታ መገዛት

“ ከልባችሁ . . . ታዘዛችሁ።”—ሮሜ 6:17

1, 2. (ሀ) ዛሬ ባለው ዓለም ውስጥ ምን መንፈስ በግልጽ ይታያል? የዚህ መንፈስ ምንጭና መንፈሱ የሚያስከትለው ውጤትስ ምንድን ነው? (ለ) ራሳቸውን የወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች የተለዩ መሆናቸውን የሚያሳዩት እንዴት ነው?

‘በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን የሚሠራው መንፈስ’ በዛሬው ጊዜ በሚዘገንን ሁኔታ በግልጽ እየታየ ነው። ይህም ‘በአየር ላይ ሥልጣን ካለው አለቃ’ ከሰይጣን የሚመነጭ ገደብ የሌለው በራስ የመመራት መንፈስ ነው። ይህ መንፈስ ማለትም ይህ ‘አየር’ ወይም ሰዎችን የሚያሸንፈው የራስ ወዳድነትና የዓመፀኝነት መንፈስ በአብዛኞቹ የሰው ዘሮች ላይ “ሥልጣን” ወይም ኃይል አለው። ዓለም በሥልጣን ውዝግብ ውስጥ እንድትገባ ያደረጋት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።—ኤፌሶን 2:2

2 ደስ የሚለው ግን፣ ዛሬ ያሉት ራሳቸውን ለይሖዋ የወሰኑ አገልጋዮቹ መንፈሳዊ ሳምባቸውን በዚህ በተበከለ ‘አየር’ ወይም የዓመፅ መንፈስ አይሞሉትም። “በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ” እንደሚመጣ ያውቃሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ “እንግዲህ ከእነርሱ ጋር ተካፋዮች አትሁኑ” ሲል ጨምሮ ጽፏል። (ኤፌሶን 5:6, 7) ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘የይሖዋ መንፈስ እንዲሞላባቸው’ ይጥራሉ። እንዲሁም “ንጹሕ፣ ታራቂ፣ ምክንያታዊና ለመታዘዝ ዝግጁ” የሆነችውን ‘ላይኛይቱን ጥበብ’ እንደ ውኃ ይጠጣሉ።—ኤፌሶን 5:17, 18፤ ያዕቆብ 3:17 አዓት

ለይሖዋ ሉዓላዊነት በፈቃደኝነት መገዛት

3. በፈቃደኝነት ለመገዛት ቁልፉ ምንድን ነው? ታሪክ ምን ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል?

3 በፈቃደኝነት ለመገዛት ቁልፉ ሕጋዊ ሥልጣንን ማወቅ ነው። የይሖዋን ሉዓላዊነት አልቀበልም ማለት ደስታ እንደማያመጣ የሰው ዘር ታሪክ ያሳያል። የይሖዋን ሉዓላዊነት አልቀበልም ማለት ለአዳምና ለሔዋንም ሆነ እነሱን ለዓመፅ ላነሳሳቸው ለሰይጣን ዲያብሎስ ደስታ አላመጣም። (ዘፍጥረት 3:16–19) ሰይጣን አሁን ባለበት የተዋረደ ሁኔታ፣ የቀረው ጊዜ ጥቂት መሆኑን ስለሚያውቅ “በታላቅ ቁጣ” ነዷል። (ራእይ 12:12) የሰው ዘር ሰላምና ደስታ፣ አዎን፣ የጠቅላላው አጽናፈ ዓለም ደስታ የተመካው የይሖዋን ፍትሐዊ የበላይ ገዥነት በመቀበል ላይ ነው።—መዝሙር 103:19–22

4. (ሀ) ይሖዋ አገልጋዮቹ ምን ዓይነት ተገዢነትና ታዛዥነት እዲያሳዩ ይፈልግባቸዋል? (ለ) ምን ነገር አምነን መቀበል ይኖርብናል? መዝሙራዊውስ ይህን የገለጸው እንዴት ነው?

4 ይሁን እንጂ ይሖዋ በአስደናቂ ሚዛናዊነት የሚንፀባረቁ ባሕርያት ስላሉት በቀዝቃዛ ስሜት ብንታዘዘው አይረካም። እጅግ ግዙፍ ኃይል አለው፤ ይሁን እንጂ አምባገነን አይደለም። እሱ የፍቅር አምላክ ነው። ስለሆነም የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረቶቹ በፍቅር ተነሳስተው በፈቃደኝነት እንዲታዘዙት ይፈልጋል። እሱን ለዘላለም ከመታዘዝ የበለጠ ምንም ነገር ሊኖር እንደማይችል አምነው ጻድቅና ሕጋዊ ከሆነው ሥልጣኑ ሥር ራሳቸውን ለማስገዛት በሙሉ ልባቸው መርጠው እንዲገዙለት ይፈልጋል። ይሖዋ ንብረቱ በሆነው አጽናፈ ዓለም ውስጥ እንዲኖር የሚፈልገው ሰው እንደሚከተለው ብሎ ከጻፈው መዝሙራዊ ስሜት ጋር የሚስማማ ነው፦ “የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ነው፤ ነፍስን ይመልሳል፤ የእግዚአብሔር ምስክር [ማሳሰቢያ አዓት] የታመነ ነው፤ ሕፃናትን ጠቢባን ያደርጋል። የእግዚአብሔር ሥርዓት ቅን ነው፣ ልብንም ደስ ያሰኛል፤ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ብሩህ ነው፣ ዓይንምም ያበራል። የእግዚአብሔር ፍርሃት ንጹሕ ነው፤ ለዘላለም ይኖራል፤ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነትና ቅንነት በአንድነት ነው።” (መዝሙር 19:7–9) የይሖዋ ሉዓላዊነት ትክክለኛና ጻድቅ ስለመሆኑ የማያወላውል ትምክህት ሊኖረን ይገባል። በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ ለመኖር ከፈለግን ዝንባሌያችን ይህ መሆን አለበት።

ለንጉሣችን በደስታ መገዛት

5. ኢየሱስ ላሳየው ታዛዥነት ሽልማት ያገኘው እንዴት ነው? እኛስ በፈቃደኝነት ምን መቀበል አለብን?

5 ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለሰማያዊ አባቱ በመገዛት ረገድ ዋነኛው ምሳሌ ነው። “ራሱን አዋረደ፣ ለሞት ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ” የሚል እናነባለን። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል፦ “በዚህም ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፣ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፣ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊልጵስዩስ 2:8–11) አዎን፣ በመሪያችንና በመግዛት ላይ በሚገኘው ንጉሣችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት በደስታ እንንበረከካለን።—ማቴዎስ 23:10

6. ኢየሱስ ለአሕዛብ ምሥክርና መሪ የሆነው እንዴት ነው? ከታላቁ መከራ በኋላ “መስፍናዊ አገዛዙ” የሚቀጥለው እንዴት ነው?

6 መሪያችን የሆነውን ክርስቶስን አስመልክቶ ይሖዋ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “እነሆ፣ ለአሕዛብ ምስክር፣ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ።” (ኢሳይያስ 55:4) በምድራዊ አገልግሎቱ እንዲሁም ሞቶ ከተነሣ በኋላ ከሰማይ ሆኖ የስብከቱን ሥራ በመምራት ለአሕዛብ ወገኖች ሁሉ የአባቱ ‘ታማኝና እውነተኛ ምስክር’ መሆኑን አሳይቷል። (ራእይ 3:14፤ ማቴዎስ 28:18–20) በክርስቶስ መሪነት “ከታላቁ መከራ” የሚተርፉት ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደው “እጅግ ብዙ ሰዎች” ከእነዚህ የአሕዛብ ወገኖች የተውጣጡ ናቸው። (ራእይ 7:9, 14) ይሁን እንጂ የኢየሱስ መሪነት በዚሁ አያበቃም። ‘መስፍናዊ አገዛዙ’ ለአንድ ሺህ ዓመት ይዘልቃል። ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች “ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም አለቃ [መስፍን አዓት]” ይሆንላቸዋል።—ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ራእይ 20:6

7. ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ‘ሕይወት ውኃ ምንጭ’ እንዲመራን ከፈለግን ሳንዘገይ ምን ማድረግ አለብን? በኢየሱስና በይሖዋ ዘንድስ የተወደድን የሚያደርገን ምንድን ነው?

7 በጉ ኢየሱስ ክርስቶስ ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭ ይመራቸዋል። እኛም ከዚህ የሕይወት ውኃ ምንጭ ለመጠቀም ከፈለግን በንጉሣዊ ሥልጣኑ ሥር በደስታ እንደምንገዛ ሳንውል ሳናድር በድርጊታችን ማረጋገጥ አለብን። (ራእይ 7:17፤ 22:1, 2፤ ከመዝሙር 2:12 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። ትእዛዜ በእርሱ ዘንድ ያለችው የሚጠብቃትም የሚወደኝ እርሱ ነው፤ የሚወደኝንም አባቴ ይወደዋል እኔም እወደዋለሁ” ብሏል። (ዮሐንስ 14:15, 21) በኢየሱስ እና በአባቱ የተወደድክ ለመሆን ትፈልጋለህ? እንግዲያው ለሥልጣናቸው ተገዢ ሁን።

የበላይ ተመልካቾች በደስታ ይታዘዛሉ

8, 9. (ሀ) ክርስቶስ ጉባኤዎችን ለመገንባት ምን ዝግጅት አድርጓል? እነዚህ ወንዶች ለመንጋው ምሳሌ መሆን የሚኖርባቸውስ በምን ረገድ ነው? (ለ) የክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ተገዢነት በራእይ መጽሐፍ ውስጥ በምሳሌ የተገለጸው እንዴት ነው? የፍርድ ጉዳዮችን በሚመለከቱበት ጊዜ “ታዛዥ ልብ” እንዲኖራቸው መጣር የሚኖርባቸው እንዴት ነው?

8 ‘ጉባኤ ለክርስቶስ ይገዛል።’ ክርስቶስ የጉባኤው የበላይ ተመልካች እንደመሆኑ መጠን ጉባኤውን ለማነጽ ‘ወንዶችን ሥጦታ’ አድርጎ ሰጥቷል። (ኤፌሶን 4:8, 11, 12፤ 5:24) እነዚህ በመንፈሳዊ የሸመገሉ ወንዶች ‘በእነሱ ጥበቃ ሥር ያለውን መንጋ በኃይል ሳይገዙ ምሳሌ በመሆን እንዲጠብቁት’ ተነግሯቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:1–3) መንጋው የይሖዋ ሲሆን ክርስቶስ ደግሞ የመንጋው ‘መልካም እረኛ’ ነው። (ዮሐንስ 10:14) የበላይ ተመልካቾች ይሖዋና ክርስቶስ አደራ ከሰጧቸው በጎች ተገቢ የፈቃደኝነት ትብብር እንዲደረግላቸው ቢጠብቁ ትክክል እንደሆነ ሁሉ እነሱ ራሳቸው ተገዢ በመሆን ረገድ ጥሩ ምሳሌዎች መሆን አለባቸው።—ሥራ 20:28

9 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተቀቡ የበላይ ተመልካቾች በምሳሌያዊ አገላለጽ በክርስቶስ ቀኝ እጅ “ውስጥ” እና በእጁ “ላይ” እንዳሉ ተገልጾ ነበር። ይህም ክርስቶስን የጉባኤው ራስ አድርገው በመመልከት የሚገዙለት መሆኑን ያሳያል። (ራእይ 1:16, 20፤ 2:1) ዛሬም በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ የበላይ ተመልካቾች ከዚህ ባላነሰ መንገድ ለክርስቶስ አመራር መገዛትና ‘ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳቸውን ማዋረድ’ አለባቸው። (1 ጴጥሮስ 5:6) የፍርድ ጉዳዮችን እንዲመለከቱ በሚጠየቁበት ጊዜ ሰሎሞን ታማኝ በነበረባቸው ዓመታት እንደጠየቀው “በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፣ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው” ብለው ለይሖዋ መጸለይ ይኖርባቸዋል። (1 ነገሥት 3:9) ታዛዥ ልብ አንድ ሽማግሌ ነገሮችን ይሖዋና ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያዩበት መንገድ እንዲያያቸው ይገፋፋዋል። በዚህ መንገድ በምድር የሚደረገው ውሳኔ በሰማይ ከሚደረገው ውሳኔ ጋር የተቻለውን ያህል የሚመሳሰል ይሆናል።—ማቴዎስ 18:18–20

10. ሁሉም የበላይ ተመልካቾች ክርስቶስ በጎቹን የያዘበትን መንገድ መከተል የሚኖርባቸው እንዴት ነው?

10 ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ ሽማግሌዎች በተመሳሳይ ክርስቶስ ለበጎቹ የሚያደርገውን አያያዝ ለመከተል ይጥራሉ። ኢየሱስ በዚያን ጊዜ እንደነበሩት ፈሪሳውያን አስቸጋሪ የሆኑ ብዙ ሕጎችን በበጎቹ ላይ አልጫነባቸውም። (ማቴዎስ 23:2–11) ኢየሱስ በግ መሰል ለሆኑት ሰዎች የሚከተለውን ብሏል፦ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ። ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፣ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀሊል ነውና።” (ማቴዎስ 11:28–30) እያንዳንዱ ክርስቲያን “የራሱን ሸክም መሸከም” ያለበት ቢሆንም የበላይ ተመልካቾች የኢየሱስን ምሳሌ ማስታወስና ወንድሞቻቸው ያለባቸው ክርስቲያናዊ የኃላፊነት ሸክም “ልዝብ፣” ‘ቀላልና’ ለመሸከም የሚያስደስት ሆኖ እንዲሰማቸው መርዳት አለባቸው።—ገላትያ 6:5

ቲኦክራሲያዊ ተገዥነት

11. (ሀ) አንድ ሰው የራስነት ቦታን ቢያከብርም ቲኦክራሲያዊ ላይሆን የሚችለው እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ። (ለ) በእርግጥ ቲኦክራሲያዊ መሆን ምን ማለት ነው?

11 ቲኦክራሲ የአምላክ አገዛዝ ማለት ነው። ይህ አገዛዝ በ1 ቆሮንቶስ 11:3 ላይ የተገለጸውን የራስነት መሠረታዊ ሥርዓት የሚጠይቅ ነው። ይሁን እንጂ ከዚያም በላይ ትርጉም አለው። አንድ ሰው ለራስነት ሥልጣን አክብሮት ያለው መስሎ ሊታይ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ቃሉ ካለው ሙሉ ትርጉም አንፃር ገና አሁንም ቲኦክራሲያዊ ላይሆን ይችላል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት ያክል፣ ዲሞክራሲ ሕዝባዊ አገዛዝ ማለት ሲሆን ዲሞክራት ደግሞ “በዲሞክራሲ ዓላማዎች የሚያምን ሰው” ነው። አንድ ሰው ዲሞክራት ነኝ ሊል፣ በምርጫዎች ሊሳተፍና እንዲያውም የወጣለት የፖለቲካ ሰው ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በጠቅላላ ጠባዩ የዲሞክራሲን መንፈስና መሠረታዊ ሥርዓቶች የሚቃረን ከሆነ ይህ ሰው በእርግጥ ዲሞክራት ነው ሊባል ይችላልን? በተመሳሳይም አንድ ሰው በእርግጥ ቲኦክራሲያዊ ለመሆን ለስሙ ያክል ለራስነት ሥልጣን መገዛት ብቻ አይበቃውም። የይሖዋን መንገዶችና ባሕርያት መምሰል አለበት። በማንኛውም መንገድ በእርግጥ በይሖዋ የሚመራ መሆን አለበት። እንዲሁም ይሖዋ ለልጁ ሙሉ ሥልጣን ስለሰጠው ቲኦክራሲያዊ መሆን ማለት ኢየሱስን መምሰል ማለት ጭምር ነው።

12, 13. (ሀ) ቲኦክራሲያዊ መሆን በተለይ ምን ማድረግን ይጠይቃል? (ለ) ቲኦክራሲያዊ ተገዢነት ብዙ ሕጎችን መታዘዝ የሚጠይቅ ነውን? በምሳሌ አስረዳ።

12 ይሖዋ ሰዎች በፍቅር ተገፋፍተው በፈቃደኝነት እንዲገዙለት እንደሚፈልግ አስታውስ። አጽናፈ ዓለምን የሚያስተዳድረው በዚህ መንገድ ነው። ይሖዋ ሁለንተናው ፍቅርን የተላበሰ አምላክ ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) ኢየሱስ ክርስቶስ “የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ” ነው። (ዕብራውያን 1:3) ኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ ይፈልጋል። (ዮሐንስ 15:17) ስለዚህ ቲኦክራሲያዊ መሆን ማለት ተገዢ መሆን ብቻ ሳይሆን አፍቃሪ መሆንንም ይጨምራል። ነገሩን እንደሚከተለው በማለት ማጠቃለል ይቻላል፦ ቲኦክራሲ የአምላክ አገዛዝ ነው፤ አምላክ ደግሞ ፍቅር ነው፤ ስለዚህ ቲኦክራሲ ፍቅራዊ አገዛዝ ነው።

13 ወንድሞች ቲኦክራሲያዊ ለመሆን ሁሉንም ዓይነት መመሪያዎች መታዘዝ አለባቸው ብሎ አንድ ሽማግሌ ሊያስብ ይችላል። አንዳንድ ሽማግሌዎች “በታማኝና ልባም ባሪያ” አልፎ አልፎ ከሚሰጡት አስተያየቶች ሕጎችን ያወጣሉ። (ማቴዎስ 24:45) ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ካሉት ወንድሞች ጋር ይበልጥ ለመተዋወቅ ሲባል በመንግሥት አዳራሹ ውስጥ ሁልጊዜ አንድ ቦታ ላይ አለመቀመጥ ጥሩ ሊሆን እንደሚችል አስተያየት ተሰጥቶ ነበር። ይህ ጠቃሚ የሆነ አስተያየት እንጂ ግትር ያለ ሕግ አልነበረም። ነገር ግን አንዳንድ ሽማግሌዎች ይህን ወደ ሕግነት ሊለውጡትና ይህን የማይከተሉ ወንድሞች ቲኦክራሲያዊ እንዳልሆኑ ሊሰማቸው ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ ወንድም ወይም አንዲት እኅት አንድ የተወሰነ ቦታ ላይ ለመቀመጥ የፈለጉበት ብዙ ጥሩ ምክንያቶች ሊኖሯቸው ይችላል። አንድ ሽማግሌ በፍቅር እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ ካላስገባ እሱ ራሱ በእርግጥ ቲኦክራሲያዊ መሆኑ ነውን? ቲኦክራሲያዊ ለመሆን “በእናንተ ዘንድ ሁሉ በፍቅር ይሁን።”—1 ቆሮንቶስ 16:14

በደስታ ማገልገል

14, 15. (ሀ) አንድ ሽማግሌ አንዳንድ ወንድሞች ወይም እኅቶች ይሖዋን በማገልገል ማግኘት የሚችሉትን ደስታ ሊያሳጣቸው የሚችለው እንዴት ነው? ይህስ ድርጊት ቲኦክራሲያዊ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ከሰዓት ብዛት ይልቅ በአገልግሎታችን የምናሳየውን ፍቅር እንደሚያደንቅ ያሳየው እንዴት ነው? (ሐ) ሽማግሌዎች ግምት ውስጥ ማስገባት የሚኖርባቸው ምንድን ነው?

14 በተጨማሪም ቲኦክራሲያዊ መሆን ይሖዋን በደስታ ማገልገል ማለት ነው። ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት) አምላኪዎቹ በደስታ እንዲያገለግሉት ይፈልጋል። መመሪያዎች ሁሉ ካልተከበሩ የሚሉ አጥባቂዎች እስራኤላውያን ‘እንዲጠብቋቸው’ ከተሰጧቸው ሕግጋት መካከል የሚከተለው እንደሚገኝበት ማስታወስ ይኖርባቸዋል፦ “እጅህን በምትዘረጋበት ነገር ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይበልህ።” (ዘዳግም 12:1, 18) በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ የምናበረክተው ማንኛውም ድርሻ የሚያስደስት እንጂ ሸክም መሆን የለበትም። ወንድሞች ይሖዋን በማገልገል ረገድ አቅማቸው የሚፈቅደውን ያህል በደስታ እንዲሠሩ የበላይ ተመልካቾች ብዙ ሊረዷቸው ይችላሉ። በሌላም በኩል ሽማግሌዎች ጥንቃቄ ከጎደላቸው የወንድሞችን ደስታ ሊያሳጡ ይችላሉ። ለምሳሌ የጉባኤውን አማካኝ የአገልግሎት ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ያመጡትን በማመስገንና ይህን ለማምጣት ያልቻሉትን ደግሞ በተዘዋዋሪ በመተቸት የሚያወዳድሩ ከሆነ እንደዚህ ዓይነት ዝቅተኛ ሪፖርት እንዲመልሱ ያደረጋቸው በቂ ምክንያት ያላቸው አስፋፊዎች እንዴት ይሰማቸዋል? ይህስ አላስፈላጊ የሆነ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸውና ደስታቸው እንዲጠፋባቸው ሊያደርግ አይችልምን?

15 አንዳንዶች በሕዝባዊ የምሥክርነቱ ሥራ ላይ የዋሏቸው ሰዓታት ጥቂት ይሆኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሌሎች በዕድሜ ለጋ ስለሆኑ፣ ጤንነታቸው ጥሩ ስለሆነና ሌሎች አመቺ ሁኔታዎች ስላሏቸው በስብከቱ ሥራ ላይ ካጠፉት ሰዓት የበለጠ ግምት የሚሰጣቸው እንሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህን በተመለከተ በእነሱ ላይ የሚፈርዱት ሽማግሌዎች አይደሉም። አብ “ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን” የሰጠው ለኢየሱስ ነው። (ዮሐንስ 5:27) ድኻዋ መበለት የሰጠችው ከሌሎች በጣም ያነሰ በመሆኑ ኢየሱስ ተችቷታልን? አልተቻትም፤ እነዚህ ሁለት ሳንቲሞች ምን ማለት እንደሆኑ በደንብ ተረድቶት ነበር። እነዚህ ሁለት ሳንቲሞች “ከጉድለቷ የነበራትን ሁሉ ትዳሯን ሁሉ” ማለት ነበሩ። ለይሖዋ ያላትን በጣም ጥልቅ ፍቅር የሚገልጹ ናቸው። (ማርቆስ 12:41–44) ታዲያ ሽማግሌዎች “አማካኝ” ሰዓታቸው ዝቅተኛ የሆነ አስፋፊዎች ለሚያደርጉት ፍቅራዊ ጥረት ከዚህ ያነሰ ሊሰማቸው ይገባልን? ለይሖዋ ካላቸው ፍቅር አንፃር እነዚህ ጥረቶች ከአማካኙ ሰዓት ሊበልጡ ይችላሉ!

16. (ሀ) የበላይ ተመልካቾች በንግግሮቻቸው ውስጥ የአገልግሎት ሪፖርቶችን አኀዞች የሚጠቅሱ ከሆነ ማስተዋልና ጥሩ ማመዛዘን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) ወንድሞች አገልግሎታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ማበረታታት የሚቻልበት የተሻለ መንገድ ምንድን ነው?

16 ይህ ምክር የአገልግሎት ሪፖርት፣ ሌላው ቀርቶ አማካይ የሰዓት ሪፖርትም እንኳ ቢሆን መጠቀስ የለበትም ወደሚል አዲስ ሕግ መለወጥ ይኖርበታልን? በፍጹም አይኖርበትም። ለማለት የተፈለገው የበላይ ተመልካቾች ወንድሞች አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ በማበረታታና አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል በደስታ እንዲሠሩ በመርዳት ረገድ ሚዛናዊ መሆን አለባቸው ነው። (ገላትያ 6:4) ኢየሱስ ስለ መክሊት በሰጠው ምሳሌ ውስጥ ጌታው ያለውን ገንዘብ ሁሉ ለባሪያዎቹ “ለእያንዳንዱ እንደ ዓቅሙ” ሰጠ ይላል። (ማቴዎስ 25:14, 15) ሽማግሌዎችም በተመሳሳይ የእያንዳንዱን የመንግሥቱን አስፋፊ አቅም ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው። ይህም ማስተዋልን ይጠይቃል። እርግጥ ነው፣ አንዳንዶች የበለጠ እንዲሠሩ ማበረታቻ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ሥራዎቻቸውን ሁሉ በሥርዓት አደራጅተው የተሻለ እንዲሠሩ መረዳት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ የአቅማቸውን ያህል በደስታ እንዲሠሩ እርዳታ ከተሰጣቸው ይህ ደስታ አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያህል ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴያቸውን እንዲያሰፉ ያበረታታቸዋል።—ነህምያ 8:10፤ መዝሙር 59:16፤ ኤርምያስ 20:9

በደስታ ከመገዛት የሚገኝ ሰላም

17, 18. (ሀ) በደስታ መገዛት ሰላምንና ጽድቅን ሊያስገኝልን የሚችለው እንዴት ነው? (ለ) ለአምላክ ትእዛዞች በሚገባ ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ ምን ነገሮችን ልናገኝ እንችላለን?

17 ሕጋዊ ለሆነው የይሖዋ ሉዓላዊነት በደስታ መገዛት ብዙ ሰላም ያመጣልናል። መዝሙራዊው ለይሖዋ ባቀረበው ጸሎት “ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፣ ዕንቅፋትም የለባቸውም” ብሏል። (መዝሙር 119:165) የአምላክን ሕግ በመታዘዛችን ራሳችንን እንጠቅማለን። ይሖዋ ለእስራኤል እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል፦ “ታዳጊህ፣ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ። ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።”—ኢሳይያስ 48:17, 18

18 የክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲኖረን ያደርጋል። (2 ቆሮንቶስ 5:18, 19) ከኃጢአት በሚያድን የክርስቶስ ደም ላይ እምነት ካለንና ድክመቶቻችንን ለመዋጋት በትጋት ከጣርን እንዲሁም የአምላክን ፈቃድ ካደረግን ከጥፋተኝነት ስሜት እፎይታ እናገኛለን። (1 ዮሐንስ 3:19–23) እንዲህ ዓይነቱ በሥራ የሚደገፍ እምነት በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲኖረን ያደርጋል፤ እንዲሁም ‘ከታላቁ መከራ’ ተርፈን በይሖዋ አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አስደናቂ ተስፋ ይሰጠናል። (ራእይ 7:14–17፤ ዮሐንስ 3:36፤ ያዕቆብ 2:22, 23) ለአምላክ ትእዛዛት ልባዊ ትኩረት ከሰጠን እነዚህ ሁሉ የእኛ ይሆናሉ።

19. አሁን ያለን ደስታና የዘላለም ሕይወት ተስፋችን በምን ላይ የተመኩ ናቸው? ዳዊት ልባዊ እምነታችንን የገለጸው እንዴት ነው?

19 አዎን፣ አሁን ያለን ደስታም ሆነ ገነት በሆነች ምድር ውስጥ የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ያለን ተስፋ ይሖዋን አጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታ አድርገን በመመልከት ለእርሱ ሥልጣን በደስታ በመገዛታችን ላይ የተመካ ነው። ምን ጊዜም ቢሆን እንደሚከተለው በማለት ከተናገረው ከዳዊት ጋር የሚስማማ ስሜት ይኑረን፦ “አቤቱ፣ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፣ ክብርም ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፣ መንግሥት የአንተ ነው፣ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። አሁንም እንግዲህ፣ አምላካችን ሆይ፣ እንገዛልሃለን፣ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን።”—1 ዜና መዋዕል 29:11, 13

ልናስታውሳቸው የሚገቡ ነጥቦች

◻ ይሖዋ አገልጋዮቹ ምን ዓይነት ተገዢነትና ታዛዥነት እንዲያሳዩ ይፈልግባቸዋል?

◻ ኢየሱስ ላሳየው ታዛዥነት ሽልማት ያገኘው እንዴት ነው? እኛስ በምናደርገው ነገር ምን ማረጋገጥ አለብን?

◻ ሁሉም የበላይ ተመልካቾች ኢየሱስ በጎቹን የያዘበትን መንገድ መከተል የሚኖርባቸው እንዴት ነው?

◻ ቲኦክራሲያዊ መሆን ምን ነገሮችን ይጨምራል?

◻ በደስታ መገዛት ምን በረከቶችን ያመጣልናል?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች መንጋው የአቅሙን ያህል በደስታ እንዲሠራ ያበረታታሉ

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ከልባቸው በሚታዘዙት ሰዎች ይደሰታል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ