በቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ሥር የሚያገለግሉ እረኞችና በጎች
“ይሖዋ ፈራጃችን ነው፣ ይሖዋ ሕግ ሰጪያችን ነው፣ ይሖዋ ንጉሣችን ነው፤ እርሱ ያድነናል።”—ኢሳይያስ 33:22 አዓት
1. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖችና በዛሬው ጊዜ የሚኖሩት ክርስቲያኖች ቲኦክራሲያዊ ናቸው ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው?
ቲኦክራሲ ማለት የአምላክ አገዛዝ ማለት ነው። ይህ አገዛዝ የይሖዋን ሥልጣን መቀበልንና በሕይወታችን ውስጥ ማንኛውንም ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ የይሖዋን መመሪያዎችና ትምህርቶች መከተልን ይጨምራል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤ ቲኦክራሲያዊ ነበር። በዚያን ጊዜ የነበሩት ክርስቲያኖች በሐቀኝነት “ይሖዋ ፈራጃችን ነው፣ ይሖዋ ሕግ ሰጪያችን ነው፣ ይሖዋ ንጉሣችን ነው” ለማለት ይችሉ ነበር። (ኢሳይያስ 33:22 አዓት) ቅቡዓን ቀሪዎች ማዕከል የሆኑለት የዛሬው የይሖዋ አምላክ ድርጅትም ቲኦክራሲያዊ ነው።
በአሁኑ ጊዜ ቲኦክራሲያዊ የሆንነው በምን መንገድ ነው?
2. የይሖዋ ምስክሮች ራሳቸውን ለይሖዋ አገዛዝ ከሚያስገዙባቸው መንገዶች አንዱ ምንድን ነው?
2 የይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ቲኦክራሲያዊ ነው ለማለት የምንችለው እንዴት ነው? ምክንያቱም የድርጅቱ አባሎች በሙሉ ራሳቸውን ለይሖዋ አገዛዝ ስለሚያስገዙ ነው። እንዲሁም ይሖዋ ንጉሥ አድርጎ በዙፋን ላይ ያስቀመጠውን የኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ይከተላሉ። ለምሳሌ ያህል የሚከተለው የታላቁ ቲኦክራት ቀጥተኛ ትእዛዝ ለኢየሱስ ተሰጥቷል፦ “የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፣ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና።” (ራእይ 14:15) ኢየሱስ ይህንን ትእዛዝ ተቀብሎ የምድርን መከር እያጨደ ነው። ክርስቲያኖች በቅንዓት የምሥራቹን በመስበክና ደቀ መዛሙርት በማድረግ ንጉሣቸውን በዚህ ከፍተኛ ሥራ ይደግፋሉ። (ማቴዎስ 28:19፤ ማርቆስ 13:10፤ ሥራ 1:8) ይህንን በማድረጋቸውም የታላቁ ቲኦክራት የይሖዋ የሥራ ባልደረቦች ሆነዋል።—1 ቆሮንቶስ 3:9
3. ክርስቲያኖች ሥነ ምግባርን በተመለከቱ ጉዳዮች ራሳቸውን ለቲኦክራሲው የሚያስገዙት እንዴት ነው?
3 ክርስቲያኖች በአኗኗራቸውም ጭምር ራሳቸውን ለአምላክ አገዛዝ ያስገዛሉ። ኢየሱስ “እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል” ብሏል። (ዮሐንስ 3:21) በዛሬው ጊዜ በሥነ ምግባር ደንቦች ረገድ ብዙ ጭቅጭቅ ይደረጋል። ይሁን እንጂ እነዚህ ጭቅጭቆች በክርስቲያኖች መካከል ቦታ የላቸውም። ይሖዋ ከሥነ ምግባር ውጭ ነው ያለውን ድርጊት እነሱም ከሥነ ምግባር ውጭ እንደሆነ በመቁጠር እንደ መቅሰፍት ይሸሹታል። ቤተሰባቸውን ይንከባከባሉ፣ ለወላጆቻቸው ይታዘዛሉ፣ ለበላይ ባለ ሥልጣኖችም ይገዛሉ። (ኤፌሶን 5:3–5, 22–33፤ 6:1–4፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8፤ ቲቶ 3:1) በዚህም ምክንያት ከአምላክ ጋር በመስማማት ቲኦክራሲያዊ የሆነ ኑሮ ይመራሉ።
4. አዳምና ሔዋን እንዲሁም ሳኦል ምን ዓይነት የተሳሳተ ዝንባሌ ነበራቸው? ክርስቲያኖች ግን ከዚህ የተለየ ዝንባሌ የሚያሳዩት እንዴት ነው?
4 አዳምና ሔዋን ገነት የሆነችውን መኖሪያቸውን ያጡት ትክክል ስለሆነውና ስሕተት ስለሆነው ነገር የራሳቸውን ውሳኔ ለማድረግ ስለ ፈለጉ ነበር። ኢየሱስ ግን የፈለገው እነሱ ካደረጉት ተቃራኒ የሆነውን ነገር ነበር። “የላከኝን ፈቃድ እንጂ ፈቃዴን አልሻምና” ብሏል። ክርስቲያኖችም እንዲሁ ለማድረግ ይፈልጋሉ። (ዮሐንስ 5:30፤ ሉቃስ 22:42፤ ሮሜ 12:2፤ ዕብራውያን 10:7) የእስራኤል የመጀመሪያ ንጉሥ የነበረው ሳኦል ይሖዋን የታዘዘው በከፊል ብቻ ነበር። በዚህ ምክንያት አምላክ ሳይቀበለው ቀረ። ሳሙኤል “መታዘዝ ከመሥዋዕት፣ ማዳመጥም የአውራ በግ ስብ ከማቅረብ ይበልጣል” በማለት ነግሮታል። (1 ሳሙኤል 15:22) ምናልባት አዘውትሮ በስብከቱ ሥራ እየተካፈሉ ወይም በስብሰባዎች ላይ እየተገኙ ሥነ ምግባርን በሚመለከት ጉዳይ ወይም በሌላ መንገድ ግን ጠንካራ አቋም ባለመያዝ የይሖዋን ፈቃድ እስከ ተወሰነ ደረጃ ብቻ መከተል ቲኦክራሲያዊ ነውን? ቲኦክራሲያዊ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ‘የአምላክን ፈቃድ በሙሉ ነፍስ ለማድረግ’ እንጥራለን። (ኤፌሶን 6:6፤ 1 ጴጥሮስ 4:1, 2) ሳኦል ከወሰደው እርምጃ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ለአምላክ አገዛዝ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ እናስገዛለን።
የዘመናችን ቲኦክራሲ
5, 6. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ከሰው ልጆች ጋር ግንኙነት የሚያደርገው እንዴት ነው? ከዚህ ዝግጅት ጋር መተባበር ምን ውጤት ያስገኛል?
5 በጥንት ጊዜያት ይሖዋ እንደ ነቢያት፣ ነገሥታት እና ሐዋርያት በመሳሰሉ ግለሰቦች አማካኝነት ሲገዛና እውነትን ሲገልጥ ቆይቷል። ዛሬ ግን ሁኔታው ተለውጧል። በመንፈስ አነሣሽነት የሚናገሩ ነቢያት እና ሐዋርያት የሉም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣን በሚገኝበት ወቅት አንድ የታማኝ ተከታዮች አካል ማለትም “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንዲታወቅ እንደሚያደርግና ይህንንም አካል ባለው ሁሉ ላይ እንደሚሾም ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:45–47፤ ኢሳይያስ 43:10) ይህ ባሪያ የቅቡዓን ክርስቲያን ቀሪዎች ድርጅት መሆኑ በ1919 ታወቀ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህ በይሖዋ ምስክሮች የአስተዳደር አካሉ የተወከለው ድርጅት በምድር ላይ ላለው ቲኦክራሲ እምብርት ሆኖ አገልግሏል። የአስተዳደር አካሉ በመላው ዓለም በሚገኙ የቅርንጫፍ ኮሚቴዎች፣ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች እና የጉባኤ ሽማግሌዎች ይወከላል።
6 ከቲኦክራሲያዊው ድርጅት ጋር መተባበር ራስን ለቲኦክራሲ የማስገዛት ዋነኛ ክፍል ነው። እንደዚህ የመሰለው ትብብር በዓለም ዙሪያ ለሚገኘው “የወንድሞች ማኅበር” አንድነትና ሥርዓት ያስገኛል። (1 ጴጥሮስ 2:17) ይህ ደግሞ “የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” የተባለውን ይሖዋን ደስ ያሰኘዋል።—1 ቆሮንቶስ 14:33
በቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ሥር የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች
7. ክርስቲያን ሽማግሌዎች የተሾሙት ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ ነው ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
7 የተሾሙ ሽማግሌዎች በሙሉ ምንም ዓይነት የሥልጣን ቦታ ቢኖራቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ በላይ ተመልካች ወይም ስለ ሸማግሌ የተዘረዘሩትን ብቃቶች በሙሉ ያሟሉ ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:1–7፤ ቲቶ 1:5–9) ከዚህም በተጨማሪ ጳውሎስ ለኤፌሶን ጉባኤ ሽማግሌዎች የተናገረው ቃል ለሁሉም ሽማግሌዎች ይሠራል። “መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት [የበላይ ተመልካቾች አዓት] አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ብሏል። (ሥራ 20:28) አዎን፣ ሽማግሌዎች የሚሾሙት ከይሖዋ አምላክ በሚመጣው መንፈስ ቅዱስ ነው። (ዮሐንስ 14:26) ሹመታቸው ቲኦክራሲያዊ ነው። ከዚህም በላይ በተጨማሪም የአምላክን መንጋ በእረኝነት ይጠብቃሉ። መንጋው የሽማግሌዎቹ ሳይሆን የይሖዋ ነው። የአምላክ ድርጅት ቲኦክራሲያዊ ነው።
8. በዛሬው ጊዜ የሽማግሌዎች አጠቃላይ ኃላፊነቶች ምንድን ናቸው?
8 ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ሽማግሌዎች ያለባቸውን አጠቃላይ ኃላፊነት ሲዘረዝር እንደዚህ ብሏል፦ “እርሱም አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ ሌሎቹም ነቢያት፣ ሌሎቹም ወንጌልን ሰባኪዎች፣ ሌሎቹም እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሰጠ፤ . . . ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንፃ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።” (ኤፌሶን 4:11, 12) “የክርስቶስ አካል” ሕፃን የነበረበት ጊዜ ሲያልፍ ሐዋርያትና ነቢያት መኖራቸው አብቅቷል። (ከ1 ቆሮንቶስ 13:8 ጋር አወዳድር።) ሽማግሌዎች ግን እስከ አሁን ድረስ ወንጌልን በመስበክ፣ በእረኝነት እና በማስተማር ሥራቸው በጣም ይተጋሉ።—2 ጢሞቴዎስ 4:2፤ ቲቶ 1:9
9. ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ የአምላክን ፈቃድ ለመወከል እንዲችሉ ራሳቸውን እንዴት ማዘጋጀት ይገባቸዋል?
9 ቲኦክራሲ የአምላክ አገዛዝ ስለሆነ ውጤታማ የሆኑ ሽማግሌዎች ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚገባ የተዋወቁ ናቸው። ኢያሱ የሕጉን መጽሐፍ በየቀኑ እንዲያነብ ታዝዞ ነበር። ሽማግሌዎችም አዘውትረው ቅዱሳን ጽሑፎችን ማጥናትና ማመሳከር እንዲሁም በታማኝና ልባም ባሪያ እየተዘጋጁ ከሚወጡት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ጋር በደንብ መተዋወቅ ይኖርባቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) ይህም መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ እንዴት ያለ ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው የሚያሳዩ ሌሎች ጽሑፎችን ማንበብን ይጨምራል።a ይሁን እንጂ አንድ ሽማግሌ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ላይ የወጡትን መመሪያዎች ማወቅና መከተሉ አስፈላጊ ነገር ቢሆንም ከእነዚህ መመሪያዎች በስተጀርባ ካሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ጭምር በሚገባ መተዋወቅ ይኖርበታል። እንደዚህ ካደረገ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን በማስተዋልና በርኅራኄ ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል አቋም ይኖረዋል።—ከሚክያስ 6:8 ጋር አወዳድር።
በክርስቲያናዊ መንፈስ ማገልገል
10. ሽማግሌዎች ከየትኛው መጥፎ ዝንባሌ ራሳቸውን መጠበቅ ይገባቸዋል? እንዴትስ?
10 ሐዋርያው ጳውሎስ በ55 እዘአ ገደማ በቆሮንቶስ ለሚገኘው ጉባኤ የመጀመሪያ ደብዳቤውን ጻፈ። እንዲሻሻል ከጠቀሳቸው ችግሮች መካከል አንዱ በጉባኤው ውስጥ ታዋቂ ለመሆን ይፈልጉ የነበሩትን ሰዎች የሚመለከት ነበር። ጳውሎስ “አሁን ጠግባችኋል፤ አሁንስ ባለ ጠጎች ሆናችኋል፤ ያለ እኛ ነግሣችኋል፤ እኛ ደግሞ ከእናንተ ጋር እንድንነግሥ ብትነግሡ መልካም ይሆን ነበር” በማለት ጽፎላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 4:8) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በሙሉ ከኢየሱስ ጋር ሰማያዊ ነገሥታትና ካህናት ሆኖ የመግዛት ተስፋ ነበራቸው። (ራእይ 20:4, 6) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በቆሮንቶስ ይገኙ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች በምድር ላይ በሚገኘው ክርስቲያናዊ ቲኦክራሲ ውስጥ ነገሥታት የሌሉ መሆናቸውን ረስተው ነበር። ክርስቲያን እረኞች እንደዚህ ዓለም ነገሥታት ከመሆን ይልቅ ይሖዋን ደስ የሚያሰኘውን የትሕትና ባሕርይ ይኮተኩታሉ።—መዝሙር 138:6፤ ሉቃስ 22:25–27
11. (ሀ) ለትሕትና ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑን እነማን ናቸው? (ለ) ሽማግሌዎችና ሌሎች ክርስቲያኖች በጠቅላላ ስለ ራሳቸው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?
11 ትሕትና ድክመት ነውን? በጭራሽ! ይሖዋ ራሱ ትሑት እንደሆነ ተገልጿል። (መዝሙር 18:35) የእስራኤል ነገሥታት መሪ ሆነው ሠራዊቶቻቸውን ወደ ጦርነት ያዘምቱና ከይሖዋ በታች ሆነው ሕዝቡን ይገዙ ነበር። ሆኖም እያንዳንዱ ንጉሥ ‘ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኮራ’ መጠንቀቅ ነበረበት። (ዘዳግም 17:20) ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ሰማያዊ ንጉሥ ነው። በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ግን የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል። ሐዋርያቱ በተመሳሳይ መንገድ ትሑቶች እንዲሆኑ የሚፈልግ መሆኑን ሲያሳያቸው “እንግዲህ እኔ ጌታና መምህር ስሆን እግራችሁን ካጠብሁ፣ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ትተጣጠቡ ዘንድ ይገባችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ (13:14፤ ፊልጵስዩስ 2:5–8) ክብርና ውዳሴ ሁሉ ሊቀርብ የሚገባው ለይሖዋ ነው እንጂ ለማንም ሰው አይደለም። (ራእይ 4:11) ሁሉም ክርስቲያኖች ሽማግሌዎች ሆኑም አልሆኑ አስተሳሰባቸው “የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፣ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል” በሚሉት የኢየሱስ ቃሎች ላይ መመሥረት ይኖርበታል። (ሉቃስ 17:10) ማንኛውም ከዚህ የተለየ አስተሳሰብ ቲኦክራሲያዊ አይደለም።
12. ፍቅር ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሊኮተኩቱት የሚገባ አስፈላጊ ባሕርይ የሆነው ለምንድን ነው?
12 ክርስቲያን ሽማግሌዎች ከትሕትና በተጨማሪ ፍቅርንም ይኮተኩታሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ “ፍቅር የሌለው እግዚአብሔርን አያውቅም፣ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና” በማለት የፍቅርን አስፈላጊነት አስገንዝቧል። (1 ዮሐንስ 4:8) ፍቅር የሌላቸው ግለሰቦች ቲኦክራሲያዊ አይደሉም። ይሖዋን አያውቁትም። መጽሐፍ ቅዱስ “ኢየሱስም . . . በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው” በማለት ስለ አምላክ ልጅ ይነግረናል። (ዮሐንስ 13:1) ኢየሱስ የክርስቲያን ጉባኤ የአስተዳደር አካል አባሎች ለሚሆኑት 11 ሰዎች “እኔ እንደ ወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” ብሏል። (ዮሐንስ 15:12) ፍቅር ክርስቲያኖች ተለይተው የሚታወቁበት ባሕርይ ነው። ልባቸው የተሰበረውን፣ ያዘኑትን እና በመንፈሳዊ እስራት ውስጥ ሆነው ነፃ ለመውጣት የሚናፍቁትን ሰዎች ይስባል። (ኢሳይያስ 61:1, 2፤ ዮሐንስ 13:35) ሽማግሌዎች ፍቅር በማሳየት ረገድ ጥሩ ምሳሌዎች መሆን ይኖርባቸዋል።
13. በዛሬው ጊዜ ያሉት ችግሮች ከበድ ያሉ ቢሆኑም አንድ ሽማግሌ በሁሉም አቅጣጫ ጥሩ እርዳታ ሊያበረክት የሚችለው እንዴት ነው?
13 በዛሬው ጊዜ ሽማግሌዎች የተወሳሰበ ችግር እንዲፈቱ ይጠየቃሉ። የጋብቻ ችግሮች ሥር የሰደዱና የማይሻሻሉ ሊሆኑ ይችላሉ። ወጣቶች ለትልልቅ ሰዎች ለመረዳት አዳጋች የሆኑ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ከስሜት መቃወስ ጋር የተያያዙ በሽታዎች ብዙውን ጊዜ ለመረዳት ያስቸግራሉ። አንድ ሽማግሌ እንደነዚህ ያሉ ችግሮች ሲገጥሙት ምን ማድረግ እንደሚኖርበት እርግጠኛ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ እና በታማኝና ልባም ባሪያ በታተሙት ጽሑፎች ላይ ምርምር ካደረገ፣ በይሖዋ የሚታመንና የሚጸልይ ከሆነ፣ በጎቹን በትሕትናና በፍቅር ከያዘ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመው እንኳ በጣም ጠቃሚ የሆነ እርዳታ ሊያበረክት ይችላል።
14, 15. ይሖዋ ሕዝቦቹን በብዙ ጥሩ ሽማግሌዎች እንደ ባረካቸው የሚያሳዩ ደብዳቤዎች ምን ብለዋል?
14 ይሖዋ ድርጅቱን ‘በሰዎች ስጦታ’ አብዝቶ ባርኳል። (ኤፌሶን 4:8) የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአምላክን ሕዝቦች በርኅራኄ የሚጠብቁ ትሑት ሽማግሌዎች ስላሳዩት ፍቅር የሚናገሩ ልብን በደስታ የሚያሞቁ ደብዳቤዎች በየጊዜው ይደርሱታል። ለምሳሌ ያህል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የዚህን ያህል በጣም የነካኝና እስከ አሁን ድረስ የጉባኤ አባሎች የሚነጋገሩበት የክልል የበላይ ተመልካች ጉብኝት አጋጥሞኝ አያውቅም። የክልል የበላይ ተመልካቹ ከወንድሞች ጋር ባለኝ ግንኙነት ይሆናል የሚል አመለካከት መያዝና ወንድሞችን በማመስገን ላይ ማተኮር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እንድገነዘብ ረድቶኛል።”
15 የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ራቅ ወዳለ ክሊኒክ መሄድ የነበረባት አንዲት እኅት “ከቤቴ በጣም ርቄ በሄድኩበት በዚያ አስጨናቂ ሌሊት ከአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ጋር በሆስፒታሉ ውስጥ ለመገናኘት መቻሌ በጣም አጽናንቶኛል። እርሱም ሆነ ሌሎች ወንድሞች ከእኔ ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፈዋል። የደረሰብኝን ሁኔታ የተመለከቱ ዓለማዊ ሰዎች እንኳ አፍቃሪ የሆኑት የእነዚህ ውድ ወንድሞች ማጽናኛ፣ እንክብካቤ እና ጸሎት ባይጨመር ኖሮ ልተርፍ እንደማልችል ተሰምቷቸዋል” በማለት ጽፋለች። ሌላዋ እኅት ደግሞ “ዛሬ በሕይወት ለመገኘት የቻልኩት የሽማግሌዎች አካል ስዋጋ በነበረው ከባድ የመንፈስ ጭንቀት የሚያስፈልገኝን አመራር በትዕግሥት ስለሰጡኝ ነው። . . . አንድ ወንድምና ሚስቱ የሚነግሩኝ ነገር ጠፋባቸው። ነገር ግን በጣም የነካኝ ስላለሁበት ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ባያውቁም ለእኔ የሚያስቡ መሆናቸውን በሆነ መንገድ መግለጻቸው ነው” በማለት ጽፋለች።
16. ጴጥሮስ ለሽማግሌዎች ምን ምክር ሰጥቷል?
16 አዎን፣ ብዙ ሽማግሌዎች ሐዋርያው ጴጥሮስ “በእናንተ ዘንድ ያለውን የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ፤ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ” በማለት የሰጠውን ምክር ይሠሩበታል። (1 ጴጥሮስ 5:1–3) እንደዚህ ያሉ ቲኦክራሲያዊ ሽማግሌዎች ትልቅ በረከት ናቸው!
በቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ሥር የሚኖሩ በጎች
17. በጉባኤው ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ሊኮተኩቷቸው የሚገቡትን አንዳንድ ባሕርዮች ጥቀስ።
17 ይሁን እንጂ ቲኦክራሲ በሽማግሌዎች ብቻ የተገነባ አይደለም። እረኞቹ ቲኦክራሲያዊ እንዲሆኑ ከተፈለገ በጎቹም ቲኦክራሲያዊ መሆን ይኖርባቸዋል። በምን መንገዶች? እረኞቹ የሚመሩበትን መሠረታዊ ሥርዓት በጎቹም መከተል ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ክርስቲያኖች የይሖዋን በረከቶች ለመቀበል ከፈለጉ ትሑታን መሆን ይኖርባቸዋል። (ያዕቆብ 4:6) ሁሉም ፍቅርን መኮትኮት አለባቸው። ምክንያቱም ያለ ፍቅር የምናቀርባቸው መሥዋዕቶች ይሖዋን ደስ ሊያሰኙ አይችሉም። (1 ቆሮንቶስ 13:1–3) እንዲሁም ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም “[የይሖዋ ፈቃድ] እውቀት መንፈሳዊ ጥበብና አእምሮ ሁሉ” ሊሞላብን ይገባል።—ቆላስይስ 1:9
18. (ሀ) ላይ ላዩን የሆነ የእውነት እውቀት በቂ ያልሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ሁላችንም በትክክለኛ እውቀት ልንሞላ የምንችለው እንዴት ነው?
18 ወጣቶችም ሆኑ ሽማግሌዎች በሰይጣን ዓለም ውስጥ እየኖሩ በታማኝነት ለመኖር በሚሞክሩበት ጊዜ አስቸጋሪ ውሳኔዎች ያጋጥሟቸዋል። ዓለም በአለባባስ፣ በዘፈን፣ በፊልሞች እና በጽሑፎች የሚከተለው አዝማሚያ የአንዳንዶቹን መንፈሳዊነት ይፈታተናል። ላይ ላዩን ብቻ የሆነ የእውነት እውቀት ሚዛናችንን ለመጠበቅ አያስችለንም። በታማኝነት ጸንተን ለመኖር ከፈለግን በትክክለኛ እውቀት መሞላት ያስፈልገናል። ከአምላክ ቃል ብቻ ሊገኝ የሚችለው ማስተዋልና ጥበብ ያስፈልገናል። (ምሳሌ 2:1–5) ጥሩ የጥናት ልማድ ማዳበር፣ የተማርነውን ማሰላሰል እና የተማርነውን ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልገናል ማለት ነው። (መዝሙር 1:1–3፤ ራእይ 1:3) ጳውሎስ ለሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ክርስቲያኖች “ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው” በማለት ጽፎ ነበር።—ዕብራውያን 5:14
እረኞችም ሆኑ በጎች አንድ ላይ ይሠራሉ
19, 20. ሁሉም ክርስቲያኖች ከሽማግሌዎች ጋር እንዲተባበሩ ምን ምክሮች ተሰጥተዋል? ለምንስ?
19 በመጨረሻም ከሽማግሌዎች ጋር የሚተባበሩ ሁሉ እውነተኛ የሆነ ቲኦክራሲያዊ መንፈስ እንደሚያሳዩ መጥቀስ ያስፈልጋል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ “በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፣ ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፣ እጥፍ ክብር ይገባቸዋል” በማለት ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:17፤ 1 ጴጥሮስ 5:5, 6) ሽምግልና አስደናቂ መብት ቢሆንም ብዙዎቹ ሽማግሌዎች የራሳቸው ቤተሰብ ስላላቸው በየቀኑ ወደ ዓለማዊ ሥራቸው የሚሄዱና የሚያስተዳድሯቸው ሚስቶችና ልጆች ያሏቸው ናቸው። በአገልግሎቱ በመካፈላቸው ደስተኞች ቢሆኑም አገልግሎታቸው ቀላልና ይበልጥ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው ጉባኤው ሲደግፋቸው እንጂ ከመጠን በላይ ሲተቻቸውና ብዙ ነገር እንዲያደርጉለት ሲጠይቃቸው አይደለም።—ዕብራውያን 13:17
20 ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ቃል የተናገሩአችሁን ዋኖቻችሁን አስቡ፣ የኑሮአቸውንም ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነታቸው ምሰሉአቸው” ብሏል። (ዕብራውያን 13:7) ጳውሎስ እዚህ ላይ ወንድሞች የሽማግሌዎች ተከታይ እንዲሆኑ መናገሩ አይደለም። (1 ቆሮንቶስ 1:12) የሰው ተከታይ መሆን ቲኦክራሲያዊ አይደለም። ይሁን እንጂ በወንጌላዊነቱ ሥራ ትጉ የሆነ፣ በስብሰባዎች አዘውታሪ የሆነ እና ከጉባኤው ጋር በትሕትናና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ የሚመላለስን የአንድን ቲኦክራሲያዊ ሽማግሌ የተፈተነ እምነት መምሰል ጥበብ እንደሆነ አያጠራጥርም።
የእምነት ማረጋገጫ
21. ክርስቲያኖች የሙሴን የመሰለ ጠንካራ እምነት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
21 በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ከማንኛውም ጊዜ ይበልጥ በተበላሸው በዚህ ዘመን ቲኦክራሲያዊ የሆነ ድርጅት መኖሩ ታላቁ ቲኦክራት ላለው ታላቅ ኃይል ምስክር ነው። (ኢሳይያስ 2:2–5) በተጨማሪም ከዕለት ተዕለት የኑሮ ችግሮች ጋር መታገል ቢኖርባቸውም ይሖዋ ገዥያቸው መሆኑን ያልረሱት ወደ አምስት ሚልዮን የሚጠጉ ክርስቲያን ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ላላቸው እምነት ምስክር ነው። ታማኙ ሙሴ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና” እንደተባለ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ጠንካራ እምነት አላቸው። (ዕብራውያን 11:27) በቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ሥር መኖራቸውን እንደ ታላቅ መብት ስለሚቆጥሩ ይሖዋን በየዕለቱ ያመሰግኑታል። (መዝሙር 100:4, 5) የይሖዋን የማዳን ኃይል እየቀመሱ በታላቅ ደስታ “ይሖዋ ፈራጃችን ነው፣ ይሖዋ ሕግ ሰጪያችን ነው፣ ይሖዋ ንጉሣችን ነው፤ እርሱ ያድነናል” ይላሉ።—ኢሳይያስ 33:22 አዓት
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል “ለራሳችሁና ለመንጋው ሁሉ ተጠንቀቁ” የተባለው ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን የያዘና ለተሾሙ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾች ወይም ሽማግሌዎች የተዘጋጀው መጽሐፍም ይገኛል።
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያመለክታል?
◻ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለቲኦክራሲው የሚያስገዙት በምን መንገድ ነው?
◻ በዛሬው ጊዜ ቲኦክራሲያዊ አገዛዝ የተደራጀው እንዴት ነው?
◻ ሽማግሌዎች ኃላፊነቶቻቸውን ለመወጣት ራሳቸውን በምን መንገዶች ማዘጋጀት ይችላሉ?
◻ ሽማግሌዎች ሊኮተኩቱትና ሊያሳዩት የሚገባ በጣም አስፈላጊ ባሕርይ ምንድን ነው?
◻ በቲኦክራሲያዊው አገዛዝ ሥር በበጎቹና በእረኞቹ መካከል ምን ዓይነት ዝምድና ሊኖር ይገባል?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዳምና ሔዋን ከገነት የተባረሩት ትክክል እና ስሕተት ስለ ሆነው ነገር የራሳቸውን ውሳኔ ለማድረግ ስለፈለጉ ነው
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ሽማግሌ በጎቹን በትሕትናና በፍቅር ከያዘ ሁልጊዜ ለመልካም ድርጊት ጥሩ አጋዥ ይሆናል