ቲኦክራሲውን የሙጥኝ በሉ
“እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፣ እግዚአብሔር ሕግን ሰጪያችን ነው፣ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው።”—ኢሳይያስ 33:22
1. የአገዛዝ ጉዳይ አብዛኞቹን ሰዎች የሚያሳስብ ጉዳይ የሆነው ለምንድን ነው?
የአገዛዝ ጉዳይ ሁሉንም ሰዎች የሚያሳስብ ነገር ነው። ጥሩ መስተዳድር ሰላምና ብልጽግና ያስገኛል። መጽሐፍ ቅዱስ “ንጉሥ በፍርድ [“በፍትሕ፣” NW] አገሩን ያጸናል” ይላል። (ምሳሌ 29:4) በሌላ በኩል ደግሞ ብልሹ መስተዳድር የፍትሕ መጓደል፣ ምግባረ ብልሹነትና ጭቆና ያስከትላል። “ኀጥአን በሠለጠኑ ጊዜ ግን ሕዝብ ያለቅሳል።” (ምሳሌ 29:2) በታሪክ ዘመናት በሙሉ ሰዎች የተለያዩ መስተዳድሮችን ሞክረዋል፤ የሚያሳዝነው ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ በገዥዎቻቸው ጭቆና ሕዝቦች ‘አልቅሰዋል።’ (መክብብ 8:9) ለተገዢዎቹ ዘላቂ እርካታ በማምጣት ረገድ የሚሳካለት መንግሥት ይኖር ይሆን?
2. “ቲኦክራሲ” በጥንቷ እስራኤል ለነበረው መስተዳድር ተስማሚ መግለጫ የሆነው ለምንድን ነው?
2 ታሪክ ጸሐፊው ጆሴፈስ እንደሚከተለው ብሎ በጻፈ ጊዜ አንድ በዓይነቱ ልዩ የሆነ መስተዳድር ጠቅሷል:- “አንዳንድ ሕዝቦች ከፍተኛውን የፖለቲካ ሥልጣን ለንጉሣዊ አገዛዝ፣ ሌሎቹ ለጥቂቶች ሲያስረክቡ የተቀሩት ደግሞ ሰፊው ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን አድርገዋል። ይሁን እንጂ ሕግ ሰጪያችን [ሙሴ] ከእነዚህ የፖለቲካ ሥርዓቶች በአንዳቸውም አልተማረከም። ይልቁንም ሕገ መንግሥቱ (ይህን ያልተለመደ ቃል እንድጠቀም ከተፈቀደልኝ) ‘ቲኦክራሲ’ ሊባል የሚችል ሉዓላዊነትንና ሥልጣንን ሙሉ በሙሉ በአምላክ እጅ የሚያደርግ ሥርዓት እንዲሆን አድርጓል።” (ኤጌንስት ኤፒዮን፣ 2, 164–5) ከንሳይስ ኦክስፎርድ ዲክሽነሪ ቲኦክራሲ የሚለውን ቃል “በአምላክ የሚመራ መስተዳድር” የሚል ፍቺ ሰጥቶታል። ቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም የጥንቷን እስራኤል መስተዳድር ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ ነው። ምንም እንኳ እስራኤላውያን ከጊዜ በኋላ የሚታይ ንጉሥ የተሾመላቸው ቢሆንም እውነተኛው ገዥያቸው ይሖዋ ነበር። እስራኤላዊው ነቢይ ኢሳይያስ “እግዚአብሔር ፈራጃችን ነው፣ እግዚአብሔር ሕግ ሰጪያችን ነው፣ እግዚአብሔር ንጉሣችን ነው” ብሏል።—ኢሳይያስ 33:22
እውነተኛ ቲኦክራሲ ምንድን ነው?
3, 4. (ሀ) ትክክለኛ ቲኦክራሲ ምንድን ነው? (ለ) በቅርቡ ቲኦክራሲ ለሁሉም የሰው ልጆች ምን በረከት ያመጣል?
3 ጆሴፈስ ቃሉን ከፈለሰፈ ወዲህ ብዙ ብሔራት ቲኦክራሲዎች ተብለው ተጠርተው ነበር። አንዳንዶቹ ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው፣ አክራሪዎችና ጨቋኞች ነበሩ። ትክክለኛ ቲኦክራሲዎች ነበሩን? ጆሴፈስ ቃሉን በተጠቀመበት መንገድ ከሄድን ትክክለኛ አልነበሩም። ችግሩ “ቲኦክራሲ” ለሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም መሰጠቱ ነው። ወርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ “ቀሳውስት ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሥልጣን እንዲኖራቸው የሚያደርግ በአንድ ቄስ ወይም በቀሳውስት የሚመራ የመስተዳድር ዓይነት” ሲል ተርጉሞታል። ሆኖም እውነተኛ ቲኦክራሲ በቀሳውስት የሚመራ መስተዳድር አይደለም። የአምላክ አገዛዝ ማለትም አጽናፈ ዓለምን በፈጠረው በይሖዋ አምላክ የሚመራ መስተዳድር ነው።
4 በቅርቡ መላዋ ምድር በቲኦክራሲ የምትተዳደር ትሆናለች፤ ይህ ደግሞ እንዴት ያለ በረከት ይሆናል! “እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ [ከሰዎች] ጋር . . . ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” (ራእይ 21:3, 4) ፍጹም ባልሆኑ ሰዎች የሚተዳደር ክህነታዊ አገዛዝ እንዲህ ያለውን ደስታ ሊያመጣ አይችልም። ይህን ሊያመጣ የሚችለው የአምላክ አገዛዝ ብቻ ነው። ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ቲኦክራሲን ለማስፈን አይሞክሩም። አምላክ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ በዓለም ዙሪያ ቲኦክራሲያዊ አገዛዙን እስኪያሰፍን ድረስ በትዕግሥት ይጠባበቃሉ።—ዳንኤል 2:44
5. በአሁኑ ጊዜ እውነተኛ ቲኦክራሲ ተግባራዊ እየሆነ ያለው የት ነው? ይህን በተመለከተስ ምን ጥያቄዎች ይነሣሉ?
5 ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን እውነተኛ ቲኦክራሲ ተግባራዊ በመሆን ላይ ነው። የት? ለአምላክ አገዛዝ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ባስገዙና ፈቃዱን ለማድረግ እርስ በርስ በሚተባበሩ ሰዎች መካከል ነው። እነዚህ የታመኑ ሰዎች አንድ ላይ ተሰባስበው በራሳቸው መንፈሳዊ “ምድር” ላይ ምድር አቀፍ መንፈሳዊ “ብሔር” ሆነዋል። እነዚህም ‘የአምላክ እስራኤል’ ቀሪዎችና ከአምስት ሚልዮን ተኩል በላይ የሚሆኑት ክርስቲያን ተባባሪዎቻቸው ናቸው። (ኢሳይያስ 66:8 NW፤ ገላትያ 6:16) እነዚህ ሰዎች ‘የዘመናት ንጉሥ’ የሆነው ይሖዋ አምላክ ሰማያዊ ንጉሥ አድርጎ የሾመው የኢየሱስ ክርስቶስ ተገዥዎች ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 1:17፤ ራእይ 11:15) ይህ ድርጅት ቲኦክራሲያዊ የሆነው በምን መንገድ ነው? አባላቱ የሰብዓዊ መንግሥታትን ሥልጣን የሚመለከቱት እንዴት ነው? በመንፈሳዊ ብሔራቸው ውስጥ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች የቲኦክራሲን መሠረታዊ ሥርዓት የሚጠብቁትስ እንዴት ነው?
ቲኦክራሲያዊ ድርጅት
6. አንድ የሚታይ ሰብዓዊ ድርጅት በአምላክ ሊመራ የሚችለው እንዴት ነው?
6 አንድ ሰብዓዊ ድርጅት በማይታዩት ሰማያት ውስጥ በሚኖረው በይሖዋ ሊመራ የሚችለው እንዴት ነው? (መዝሙር 103:19) ይህ የሚሆነው ተባባሪዎቹ በሙሉ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ” የሚለውን በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈ ምክር ስለሚከተሉ ነው። (ምሳሌ 2:6፤ 3:5) “የክርስቶስን ሕግ” በመጠበቅና በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈውን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ተግባራዊ በማድረግ አምላክ እንዲመራቸው ይፈቅዳሉ። (ገላትያ 6:2፤ 1 ቆሮንቶስ 9:21፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16፤ በተጨማሪም ማቴዎስ 5:22, 28, 39፤ 6:24, 33፤ 7:12, 21 ተመልከት።) ይህን ለማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መሆን አለባቸው። (መዝሙር 1:1–3) “ልበ ሰፊዎች” እንደነበሩት እንደ ጥንቶቹ የቤርያ ሰዎች ሌሎችን አይከተሉም፤ ከዚህ ይልቅ የሚማሯቸው ነገሮች ትክክል መሆናቸውን ለማረጋገጥ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው ይመረምራሉ። (ሥራ 17:10, 11፤ መዝሙር 119:33–36) ልክ እንደ መዝሙራዊው “በትእዛዛትህ ታምኛለሁና መልካምን ምክርና እውቀትን አስተምረኝ” ብለው ይጸልያሉ።—መዝሙር 119:66
7. በቲኦክራሲ ውስጥ ያለው የበላይ ጠባቂነት ተዋረድ እንዴት ነው?
7 በማንኛውም ድርጅት ውስጥ ሥልጣን ያላቸው ወይም መመሪያ የሚሰጡ አንዳንድ ሰዎች መኖር እንዳለባቸው የታወቀ ነው። በይሖዋ ምሥክሮችም ዘንድ ሁኔታው ተመሳሳይ ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ የገለጸውን የሥልጣን መዋቅር ይከተላሉ:- “ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፣ የሴትም ራስ ወንድ፣ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር [ነው]።” (1 ቆሮንቶስ 11:3) ከዚህ ጋር በመስማማት በጉባኤ ውስጥ በሽምግልና የሚያገለግሉት ብቃት ያላቸው ወንዶች ብቻ ናቸው። “የወንድ ሁሉ ራስ” የሆነው ክርስቶስ ያለው በሰማይ ቢሆንም ከእሱ ጋር በሰማይ ገዥዎች የመሆን ተስፋ ካላቸው የተቀቡ ወንድሞቹ መካከል ‘ቀሪዎቹ’ አሁንም በዚህ በምድር ላይ ይገኛሉ። (ራእይ 12:17፤ 20:6) የእነዚህ ሰዎች ጥምረት “ታማኝና ልባም ባሪያ” አስገኝቷል። ክርስቲያኖች ‘የባሪያውን’ የበላይ ጥበቃ በመቀበል ለኢየሱስ ብሎም የኢየሱስ ራስ ለሆነው ለይሖዋ እንደሚገዙ ያሳያሉ። (ማቴዎስ 24:45–47፤ 25:40) በዚህ መንገድ ቲኦክራሲው ሥርዓታማ ይሆናል። “እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና።”—1 ቆሮንቶስ 14:33
8. ክርስቲያን ሽማግሌዎች የቲኦክራሲን መሠረታዊ ሥርዓት የሚደግፉት እንዴት ነው?
8 ክርስቲያን ሽማግሌዎች ገደብ ያለው ሥልጣናቸውን የሚጠቀሙበትን መንገድ በተመለከተ በይሖዋ ፊት በኃላፊነት እንደሚጠየቁ ስለሚገነዘቡ የቲኦክራሲን መሠረታዊ ሥርዓት ይደግፋሉ። (ዕብራውያን 13:17) እንዲሁም ውሳኔ በሚያደርጉበት ጊዜ በራሳቸው ሳይሆን በአምላክ ጥበብ ይታመናሉ። በዚህ መንገድ የኢየሱስን ምሳሌ ይከተላሉ። ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ጥበበኛ ሰው ነበር። (ማቴዎስ 12:42) ያም ሆኖ ግን አይሁዳውያንን “አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 5:19) በተጨማሪም ሽማግሌዎች ንጉሥ ዳዊት የነበረው ዓይነት አመለካከት አላቸው። ዳዊት በቲኦክራሲው ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ነበረው። ሆኖም የራሱን ሳይሆን የይሖዋን መንገድ ለመከተል ፈልጓል። “አቤቱ፣ መንገድህን አስተምረኝ፣ . . . በቀና መንገድ ምራኝ” ሲል ጸልዮአል።—መዝሙር 27:11
9. በቲኦክራሲ ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ተስፋዎችና መብቶች በተመለከተ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች ሚዛኑን የጠበቀ ምን አመለካከት አላቸው?
9 አንዳንዶች በጉባኤ ውስጥ ያለው ሥልጣን ብቃት ባላቸው ወንዶች ብቻ መያዙ ወይም የተወሰኑ ሰዎች ሰማያዊ ተስፋ የተቀሩት ደግሞ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው መሆኑ አድሎ ያለበት ነው ይላሉ። (መዝሙር 37:29፤ ፊልጵስዩስ 3:20) ይሁን እንጂ ራሳቸውን የወሰኑ ክርስቲያኖች እነዚህ ዝግጅቶች በአምላክ ቃል ውስጥ በዝርዝር መገለጻቸውን ይገነዘባሉ። ቲኦክራሲያዊ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ ስለነዚህ ነገሮች ጥያቄ የሚያነሱ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ያልተገነዘቡ ናቸው። ከዚህም በላይ ክርስቲያኖች መዳንን በተመለከተ በይሖዋ ፊት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች እኩል መሆናቸውን ያውቃሉ። (ገላትያ 3:28) ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ጌታን ማምለክ ከሁሉ የሚበልጥ መብት ሲሆን ይሖዋ የሚሰጣቸውን ማንኛውም ቦታ ለመቀበል ፈቃደኞች ናቸው። (መዝሙር 31:23፤ 84:10፤ 1 ቆሮንቶስ 12:12, 13, 18) ከዚህም በላይ በሰማይም ይሁን በምድራዊ ገነት ውስጥ ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘት እጅግ አስደናቂ ተስፋ ነው።
10. (ሀ) ዮናታን ጥሩ አመለካከት እንደነበረው ያሳየው እንዴት ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖች ከዮናታን ጋር ተመሳሳይ የሆነ አመለካከት የሚያሳዩት እንዴት ነው?
10 በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች አምላካዊ ፍርሃት የነበረውን የንጉሥ ሳኦልን ልጅ ዮናታንን ይመስላሉ። ዮናታን የተዋጣለት ንጉሥ ሊሆን ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ሳኦል ታማኝነቱን በማጉደሉ ምክንያት ይሖዋ የእስራኤል ሁለተኛ ንጉሥ እንዲሆን ዳዊትን መረጠ። ዮናታን በዚህ ተማርሮ ነበርን? አልተማረረም። ለዳዊት ጥሩ ጓደኛ ሆነው፤ እንዲያውም ከሳኦል እጅ አድኖታል። (1 ሳሙኤል 18:1፤ 20:1–42) ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ሰማያዊ ተስፋ ባላቸው ሰዎች አይቀኑም። እንዲሁም እውነተኛ ክርስቲያኖች በጉባኤ ውስጥ በሚገኙ ቲኦክራሲያዊ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች አይቀኑም። ከዚህ ይልቅ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ሲሉ ጠንክረው እንደሚሠሩ በመገንዘብ ‘በፍቅር ከመጠን ይልቅ ያከብሯቸዋል።’—1 ተሰሎንቄ 5:12, 13
ለሰብዓዊ አገዛዝ ሊኖረን የሚገባው ቲኦክራሲያዊ አመለካከት
11. ለቲኦክራሲው ራሳቸውን የሚያስገዙ ክርስቲያኖች ሰብዓዊ ባለ ሥልጣናትን የሚመለከቱት እንዴት ነው?
11 የይሖዋ ምሥክሮች በቲኦክራሲ ማለትም በአምላክ አገዛዝ ሥር ቢሆኑም ብሔራዊ ገዥዎችን የሚመለከቱት እንዴት ነው? ኢየሱስ ተከታዮቹ ‘የዓለም ክፍል እንዳልሆኑ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:16) ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች “ለቄሣር” ማለትም ለሰብዓዊ መንግሥታት ባለ ዕዳዎች እንደሆኑ ይገነዘባሉ። ኢየሱስ “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር” ማስረከብ እንዳለባቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 22:21) መጽሐፍ ቅዱስ በሚለው መሠረት ሰብዓዊ መንግሥታት “በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው።” የሥልጣን ሁሉ ምንጭ የሆነው ይሖዋ መንግሥታት እንዲኖሩ የፈቀደ ሲሆን በሥልጣናቸው ሥር ላሉትም መልካም ነገር እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል። እንዲህ በሚያደርጉበት ጊዜ “የእግዚአብሔር አገልጋይ” ይሆናሉ። ክርስቲያኖች በሚኖሩበት አገር ላለው መንግሥት “ስለ ሕሊና[ቸው]” ሲሉ ይገዛሉ። (ሮሜ 13:1–7) እርግጥ ነው፣ መንግሥት የአምላክን ሕግ የሚጻረር ነገር በሚጠይቅበት ጊዜ አንድ ክርስቲያን “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር [ይታዘዛል]።”—ሥራ 5:29
12. ክርስቲያኖች በባለ ሥልጣናት በሚሰደዱበት ጊዜ የማንን ምሳሌ ይከተላሉ?
12 የመንግሥት ባለ ሥልጣናት እውነተኛ ክርስቲያኖችን በሚያሳድዱበት ጊዜስ? በዚህ ጊዜ ከባድ ስደቶችን የተቋቋሙትን የጥንት ክርስቲያኖች ምሳሌ ይከተላሉ። (ሥራ 8:1፤ 13:50) ኢየሱስ እነዚህ የእምነት ፈተናዎች እንደሚመጡ አስቀድሞ የተናገረ በመሆኑ እንግዳ ነገሮች አልነበሩም። (ማቴዎስ 5:10–12፤ ማርቆስ 4:17) ሆኖም እነዚህ የጥንት ክርስቲያኖች ለአሳዳጆቻቸው አልተበገሩም፤ የነበራቸውም እምነት በደረሰበት ተጽእኖ አልተዳከመም። ከዚህ ይልቅ የኢየሱስን ምሳሌ ተከትለዋል:- “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም መከራንም ሲቀበል አልዛተም፣ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” (1 ጴጥሮስ 2:21–23) አዎን፣ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሰይጣንን ትንኮሳዎች አሸንፈዋል።—ሮሜ 12:21
13. የይሖዋ ምሥክሮች ለደረሰባቸው ስደትና ስም የማጥፋት ዘመቻ ምላሽ የሰጡት እንዴት ነው?
13 ዛሬም ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስ አስቀድሞ በተናገረው መሠረት በዚህ መቶ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች በአምባገነን መሪዎች ከፍተኛ መከራ ደርሶባቸዋል። (ማቴዎስ 24:9, 13) በአንዳንድ አገሮች፣ ባለ ሥልጣናት በእነዚህ ቅን ክርስቲያኖች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ለመገፋፋት ሲባል የሐሰት ወሬዎችና የተዛቡ መረጃዎች ይነዛሉ። እንዲህ ያለ ‘ክፉ ወሬ’ እየተነዛ ቢሆንም ምሥክሮቹ ጥሩ ምግባር በማሳየት ራሳቸውን የአምላክ አገልጋዮች አድርገው ያቀርባሉ። (2 ቆሮንቶስ 6:4, 8) የሚቻል ሆኖ ሲያገኙት ምንም ጥፋት የሌለባቸው መሆኑን ለማሳየት ሲሉ ጉዳያቸውን ለባለ ሥልጣናትና ላሉበት አገር ፍርድ ቤት ያቀርባሉ። ለምሥራቹ ጥብቅና ለመቆም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀማሉ። (ፊልጵስዩስ 1:7) ሆኖም ሕግ የሚፈቅድላቸውን ሁሉ ካደረጉ በኋላ ጉዳዩን ለይሖዋ ይተዉታል። (መዝሙር 5:8–12፤ ምሳሌ 20:22) አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ እንደ ጥንቶቹ ክርስቲያኖች ሁሉ እነሱም ለጽድቅ መከራን ለመቀበል ዝግጁ ናቸው።—1 ጴጥሮስ 3:14–17፤ 4:12–14, 16
የአምላክን ክብር አስቀድም
14, 15. (ሀ) የቲኦክራሲን መሠረታዊ ሥርዓት ለሚደግፉ ሰዎች ከሁሉ የላቀው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ሰሎሞን በነበረው የበላይ ጠባቂነት ቦታ ጥሩ የትሕትና ምሳሌ የተወው እንዴት ነው?
14 ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዴት እንደሚጸልዩ ባስተማራቸው ጊዜ በመጀመሪያ የጠቀሰው ነገር የይሖዋ ስም ቅድስና ነው። (ማቴዎስ 6:9) ከዚህ ጋር በመስማማት በቲኦክራሲ አመራር ሥር የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸውን ሳይሆን የአምላክን ክብር ይፈልጋሉ። (መዝሙር 29:1, 2) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ‘የሰውን ክብር በመውደዳቸው’ ማለትም በሰዎች ዘንድ ከፍ ተደርገው ለመታየት በመፈለጋቸው ምክንያት ኢየሱስን ለመከተል አሻፈረን ስላሉ ይህ ጉዳይ የማሰናከያ ድንጋይ እንደሆነባቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ዮሐንስ 12:42, 43) በእርግጥም ከራስ ክብር ይልቅ የይሖዋን ክብር ማስቀደም ትሕትና ይጠይቃል።
15 ሰሎሞን በዚህ ረገድ ጥሩ መንፈስ አሳይቷል። የሠራው ታላቅ ቤተ መቅደስ ለይሖዋ በተወሰነ ጊዜ የተናገራቸውን ቃላት ናቡከደነፆር ስለ ግንባታ ስኬቱ ከተናገራቸው ቃላት ጋር አወዳድሩ። ናቡከደነፆር “ይህች እኔ በጉልበቴ ብርታት ለግርማዬ ክብር የመንግሥት መኖሪያ እንድትሆን ያሠራኋት ታላቂቱ ባቢሎን አይደለችምን?” ሲል በከፍተኛ የኩራት ስሜት ደነፋ። (ዳንኤል 4:30) ከዚህ በተቃራኒ ግን ሰሎሞን ስላከናወነው ነገር ሲናገር በትሕትና ራሱን ዝቅ አድርጓል:- “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፣ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ ይይዝህ ዘንድ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ ይሆን?” (2 ዜና መዋዕል 6:14, 15, 18፤ መዝሙር 127:1) ሰሎሞን ራሱን ከፍ ከፍ አላደረገም። የይሖዋ ወኪል ከመሆን ሌላ ምንም እንዳይደለ ያውቅ ስለነበር እንዲህ ብሎ ጽፏል:- “ትዕቢት ከመጣች ውርደት ትመጣለች፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።”—ምሳሌ 11:2
16. ሽማግሌዎች ራሳቸውን ከፍ ከፍ ባለማድረግ ትልቅ በረከት መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?
16 በተመሳሳይም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ራሳቸውን ሳይሆን ይሖዋን ከፍ ከፍ ያደርጋሉ። “ማንም ሰው . . . የሚያገለግልም ቢሆን፣ እግዚአብሔር በሚሰጠኝ ኃይል ነው ብሎ ያገልግል፤ . . . በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል እግዚአብሔር በነገር ሁሉ ይከብር ዘንድ” የሚለውን የጴጥሮስ ምክር ይከተላሉ። (1 ጴጥሮስ 4:11) ሐዋርያው ጳውሎስ “የበላይ ተመልካችነትን ሥራ” ታዋቂነት የማትረፊያ ቦታ ሳይሆን ‘መልካም ሥራ’ መሆኑን ገልጿል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1 NW) ሽማግሌዎች የተሾሙት ለመግዛት ሳይሆን ለማገልገል ነው። የአምላክ መንጋ አስተማሪዎችና እረኞች ናቸው። (ሥራ 20:28፤ ያዕቆብ 3:1) ትሑቶችና የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ሽማግሌዎች ለአንድ ጉባኤ ትልቅ በረከት ናቸው። (1 ጴጥሮስ 5:2, 3) ‘እንዲህ ዓይነቶቹን ሰዎች አክብሩአቸው፤’ እንዲሁም በእነዚህ ‘የመጨረሻ ቀናት’ ቲኦክራሲውን የሚደግፉ ብቃት ያላቸው ብዙ ሽማግሌዎች በመስጠቱ ይሖዋን አመስግኑ።—ፊልጵስዩስ 2:29፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1
“እግዚአብሔርን የምትመስሉ ሁኑ”
17. በቲኦክራሲው ሥር የሚገኙ ሰዎች አምላክን የሚመስሉት በምን መንገዶች ነው?
17 ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ [“የምትመስሉ፣” NW] ሁኑ” ሲል አሳስቧል። (ኤፌሶን 5:1) ራሳቸውን ለቲኦክራሲው የሚያስገዙ ሁሉ ያለባቸው አለፍጽምና የሚፈቅድላቸውን ያህል አምላክን ለመምሰል ይጥራሉ። ለምሳሌ ያህል መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “ሥራው ፍጹም ነው፣ መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸውና። የታማኝነት አምላክ፣ ፍትሕ የማያጓድል፣ እርሱ ጻድቅና ቅን ነው” ይላል። (ዘዳግም 32:3, 4 NW) ክርስቲያኖች በዚህ ረገድ አምላክን ለመምሰል ታማኝነትን፣ ጽድቅንና ፍትሐዊ አመለካከትን ማዳበር አለባቸው። (ሚክያስ 6:8፤ 1 ተሰሎንቄ 3:6፤ 1 ዮሐንስ 3:7) እንደ ሥነ ምግባር ብልግና፣ መጎምጀትና ስግብግብነት የመሳሰሉ በዓለም ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ በርካታ ነገሮችን ያስወግዳሉ። (ኤፌሶን 5:5) የይሖዋ አገልጋዮች ሰብዓዊ ሳይሆን መለኮታዊ የአቋም ደረጃዎችን ስለሚከተሉ ድርጅቱ ቲኦክራሲያዊ፣ ንጹህና የሚያንጽ ነው።
18. ከሁሉ የላቀው የአምላክ ባሕርይ ምንድን ነው? ክርስቲያኖችስ ይህን ባሕርይ የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?
18 ከሁሉ የላቀው የይሖዋ አምላክ ባሕርይ ፍቅር ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” ብሏል። (1 ዮሐንስ 4:8) ቲኦክራሲ ማለት የአምላክ አገዛዝ ማለት ስለሆነ ቲኦክራሲ የፍቅር አገዛዝን ያመለክታል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) ቲኦክራሲያዊው ድርጅት በእነዚህ አስቸጋሪ የመጨረሻ ቀናት ልዩ ፍቅር አሳይቷል። በአፍሪካ በተካሄደው የዘር ማጥፋት ዘመቻ የይሖዋ ምሥክሮች ጎሣ ሳይለዩ ለሁሉም ፍቅር አሳይተዋል። በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ጦርነት በተካሄደበት ወቅት ሌሎች የሃይማኖት ቡድኖች የዘር ማጽዳት ዘመቻ በተባለው እንቅስቃሴ ሲካፈሉ በሁሉም ቦታዎች የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ግን አንዳቸው ሌላውን ረድተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በግለሰብ ደረጃ የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ይጥራሉ:- “መራርነትና ንዴት ቊጣም ጩኸትም መሳደብም ሁሉ ከክፋት ሁሉ ጋር ከእናንተ ዘንድ ይወገድ። እርስ በርሳችሁም ቸሮችና ርኅሩኆች ሁኑ፣ እግዚአብሔርም ደግሞ በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ ይቅር ተባባሉ።”—ኤፌሶን 4:31, 32
19. ራሳቸውን ለቲኦክራሲ የሚያስገዙ ሰዎች በአሁኑ ጊዜና ወደፊት ምን በረከቶች ያገኛሉ?
19 ራሳቸውን ለቲኦክራሲው የሚያስገዙ ሁሉ ታላላቅ በረከቶችን ያገኛሉ። ከአምላክና ከመሰል ክርስቲያኖች ጋር ሰላም አላቸው። (ዕብራውያን 12:14፤ ያዕቆብ 3:17) ሕይወታቸው ዓላማ አለው። (መክብብ 12:13) መንፈሳዊ ጥበቃና አስተማማኝ ተስፋ አላቸው። (መዝሙር 59:9) በእርግጥ ሁሉም የሰው ዘር በቲኦክራሲ አገዛዝ ሥር በሚሆንበት ጊዜ የሚኖረው ሁኔታ ምን እንደሚመስል አስቀድሞ የመቅመስ አጋጣሚ አግኝተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ከዚያ በኋላ “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” ይላል። (ኢሳይያስ 11:9) ይህ እንዴት ያለ ክብራማ ጊዜ ይሆናል! ሁላችንም በአሁኑ ጊዜ ቲኦክራሲውን የሙጥኝ ብለን በመኖር መጪዋን ገነት ለመውረስ እንጣር።
[ልታብራራ ትችላለህ?]
◻ ትክክለኛ ቲኦክራሲ ምንድን ነው? ዛሬስ የት ይገኛል?
◻ ሰዎች ሕይወታቸውን ለቲኦክራሲ አመራር የሚያስገዙት እንዴት ነው?
◻ በቲኦክራሲ ሥር የሚገኙ ሁሉ ከራሳቸው ይልቅ የአምላክን ክብር የሚፈልጉት በምን መንገዶች ነው?
◻ ቲኦክራሲን የሚደግፉ ሰዎች የሚኮርጁአቸው አንዳንድ አምላካዊ ባሕርያት ምንድን ናቸው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰሎሞን ከራሱ ይልቅ የአምላክን ክብር አስቀድሟል