የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 1/15 ገጽ 10-15
  • ይሖዋ የሚገዛው በቲኦክራሲ ነው

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ የሚገዛው በቲኦክራሲ ነው
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ቲኦክራሲ ተወለደ
  • በቲኦክራሲ ሥር የሚገኝ ሥልጣን
  • ቲኦክራሲያዊ ያልሆኑ ድርጊቶችና አስተሳሰቦች
  • የቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ፍጻሜ
  • አዲስ ቲኦክራሲ
  • ቲኦክራሲውን የሙጥኝ በሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • በቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ሥር የሚያገለግሉ እረኞችና በጎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ከታላቁ ፈጣሪያችን ጋር መንጋው መጠበቅ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛ መሆኑ ተረጋገጠ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 1/15 ገጽ 10-15

ይሖዋ የሚገዛው በቲኦክራሲ ነው

“እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል።”—መዝሙር 146:10

1, 2. (ሀ) የሰው ልጅ በአገዛዝ ረገድ ያደረገው ጥረት ያልተሳካለት ለምንድን ነው? (ለ) በትክክል የተሳካለት ብቸኛው የአገዛዝ ዓይነት የትኛው ነው?

ሰዎች ከናምሩድ ዘመን ጀምሮ የሰው ልጆችን ማኅበረ ሰብ ለመግዛት የተለያዩ የአገዛዝ ዓይነቶችን ሞክረዋል። አምባገነናዊና ዙፋናዊ አስተዳደሮች፣ በጥቂት የገዥ መደብ አባላት የሚመሩ መንግሥታትና የተለያየ ቅርጽ ያላቸው ዲሞክራሲያዊ መስተዳድሮች ተሞክረዋል። ይሖዋ እነዚህ ሁሉ አገዛዞች እንዲሞከሩ ፈቅዷል። አምላክ የመጨረሻው የሥልጣን ምንጭ ስለሆነ የተለያዩ ገዥዎችን በየቦታቸው ያስቀመጠው እርሱ ነው ሊባል ይችላል። (ሮሜ 13:1) ይሁን እንጂ ሰዎች በአገዛዝ ረገድ ያደረጉት ሙከራ ሁሉ ሳይሳካ ቀርቷል። ዘላቂ፣ የተረጋጋና ፍትሕ የሰፈነበት ኅብረተሰብ ማስገኘት የቻለ አንድም ሰብአዊ መሪ አልተገኘም። በተደጋጋሚ እንደታየው ‘ሰው ሰውን የገዛው ለጉዳቱ ነው።’—መክብብ 8:9

2 ይህ ነገር ሊያስደንቀን ይገባልን? ሊያስደንቀን አይገባም። ፍጹም ያልሆነ ሰው ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ሆኖ አልተፈጠረም። “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።” (ኤርምያስ 10:23) በሰው ልጆች ታሪክ በሙሉ የተሳካለት መንግሥት አንድ ብቻ ሆኖ የተገኘው በዚህ ምክንያት ነው። ይህ አገዛዝ የትኛው ነው? በይሖዋ አምላክ የሚመራው ቲኦክራሲ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት የግሪክኛ ቋንቋ “ቲኦክራሲ” ማለት የአምላክ [ቴኦስ] አገዛዝ [ክራቶስ] ማለት ነው። ከይሖዋ አምላክ አገዛዝ የሚሻል ምን ዓይነት አገዛዝ ሊኖር ይችላል?—መዝሙር 146:10

3. በምድር ላይ ለነበሩት ጥንታዊ ቲኦክራሲዎች ምሳሌ የሚሆኑን የትኞቹ ናቸው?

3 ቲኦክራሲ አዳምና ሔዋን በይሖዋ አምላክ ላይ እስካመጹበት ጊዜ ድረስ ለጥቂት ጊዜ በኤደን ሰፍኖ ነበር። (ዘፍጥረት 3:1–6, 23) በአብርሃም ዘመን መልከ ጼዴቅ ንጉሥና ካህን በሆነበት ዘመን ቲኦክራሲያዊ አገዛዝ በሳሌም ከተማ የነበረ ይመስላል። (ዘፍጥረት 14:18–20፤ ዕብራውያን 7:1–3) ይሁን እንጂ በመጀመሪያ በብሔር ደረጃ በይሖዋ አምላክ የሚተዳደር ቲኦክራሲ የተቋቋመው በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በሲና ምድረበዳ ውስጥ ነበር። ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ይህ ቲኦክራሲያዊ መንግሥትስ ሥራውን ያከናውን የነበረው እንዴት ነው?

ቲኦክራሲ ተወለደ

4. ይሖዋ ቲኦክራሲያዊውን የእስራኤል ብሔር ያቋቋመው እንዴት ነበር?

4 በ1513 ከዘአበ ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት አድኖ ያሳድዳቸው የነበረውን የፈርኦን ሠራዊት በቀይ ባሕር ውስጥ አጠፋ። ከዚያም እስራኤላውያንን ወደ ሲና ተራራ መራቸው። በተራራው ግርጌ ከሰፈሩ በኋላ አምላክ በሙሴ በኩል እንዲህ ሲል ነገራቸው፦ “በግብፃውያን ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ እንደ ተሸከምኋችሁ፣ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፣ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ።” እስራኤላውያንም “እግዚአብሔር ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” በማለት የእሺታ መልስ ሰጡ። (ዘጸአት 19:4, 5, 8) ቃል ኪዳን ተጋቡና ቲኦክራሲያዊ የሆነው የእስራኤል ብሔር ተወለደ።—ዘዳግም 26:18, 19

5. ይሖዋ በእስራኤል ላይ ይገዛ ነበር ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው?

5 ታዲያ እስራኤላውያን ለሰዎች ዓይን በማይታየው በይሖዋ የተገዙት እንዴት ነበር? (ዘጸአት 33:20) ሕጎቹና የብሔሩ የክህነት አገልግሎት ከይሖዋ የተገኙ በመሆናቸው ነው። ሕጎቹን የታዘዙና በመለኮታዊ ትእዛዝ በተዘጋጀው ዝግጅት መሠረት ያመለኩ ሁሉ ታላቅ ቲኦክራት የሆነውን ይሖዋን አገልግለዋል። በተጨማሪም አስቸኳይ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ይሖዋ አምላክ መመሪያ የሚሰጠው በሊቀ ካህኑ ኡሪምና ቱሚም ነበር። (ዘጸአት 28:29, 30) ከዚህም በላይ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች በቲኦክራሲያዊው አገዛዝ የይሖዋ ወኪሎች ሆነው ስለነበር የአምላክ ሕግ ሥራ ላይ መዋሉን ይከታተሉ ነበር። ከእነዚህ ሰዎች መካከል የአንዳንዶቹን ታሪክ ብንመረምር ሰዎች እንዴት ለአምላክ አገዛዝ ራሳቸውን ማስገዛት እንደሚገባቸው ማስተዋል እንችላለን።

በቲኦክራሲ ሥር የሚገኝ ሥልጣን

6. በቲኦክራሲ ውስጥ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ብርቱ ጥረትና ትጋት ያስፈልጋቸው የነበረው ለምንድን ነው? ለዚህስ ኃላፊነት የሚፈለጉት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?

6 በእስራኤላውያን መካከል ሥልጣን የነበራቸው ሰዎች ትልቅ መብት የነበራቸው ቢሆንም ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ዘወትር ጥረትና ትጋት ማሳየት ነበረባቸው። የራሳቸው ምኞትና ፍላጐት ከይሖዋ ስም መቀደስ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ አድርገው እንዳይመለከቱ መጠንቀቅ ነበረባቸው። “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” የሚለው በመንፈስ አነሣሽነት የተነገረ ቃል ለሰው ዘር በሙሉ፣ ለእስራኤላውያንም ጭምር ይሠራል። የእስራኤል ሕዝብ ይበለጽግ የነበረው ሽማግሌዎቹ የእስራኤል ብሔር ቲኦክራሲያዊ መሆኑን ሲያስታውሱ እና የራሳቸውን ሳይሆን የይሖዋን ፈቃድ ሲያደርጉ ብቻ ነበር። የእስራኤል ብሔር ከተመሠረተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሙሴ አማች የነበረው ዮቶር እነዚህ ሽማግሌዎች ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንደሚገባቸው በሚገባ ገልጿል። “አዋቂዎችን፣ እግዚአብሔርን የሚፈሩትን፣ የታመኑ፣ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ” ብሎታል።—ዘጸአት 18:21

7. በይሖዋ አምላክ ሥር የተሰጠውን ሥልጣን በአግባቡ በመጠቀም ረገድ ሙሴ ግሩም ምሳሌ የሚሆነን በምን መንገዶች ነው?

7 በእስራኤላውያን መካከል ከፍተኛ ባለ ሥልጣን ለመሆን የመጀመሪያ የሆነው ሙሴ ነበር። እርሱም በቲኦክራሲያዊው አደረጃጀት ውስጥ ሥልጣን ለሚይዙ ሰዎች ግሩም ምሳሌ የተወ ሰው ነበር። እውነት ነው ሰብአዊ ድክመቱ አይሎ የታየበት ወቅት ነበር። ይሁን እንጂ ሙሴ ሁልጊዜ በይሖዋ ይታመን ነበር። ከዚህ በፊት መፍትሔ ያላገኘ አንድ ዓይነት ጥያቄ ሲነሣ የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ይጥር ነበር። (ከዘኁልቁ 15:32–36 ጋር አወዳድር።) ሙሴ የነበረውን ከፍተኛ ሥልጣን ለራሱ ክብር ለማስገኘት እንዲጠቀም የሚገፋፋውን ፈተና የተቋቋመው እንዴት ነበር? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦችን የሚመራ ሰው ቢሆንም “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ።” (ዘኁልቁ 12:3) ዘወትር ያስብ የነበረው ስለ አምላክ ክብር ነበር እንጂ ስለራሱ ፍላጎት አልነበረም። (ዘጸአት 32:7–14) በተጨማሪም ሙሴ ጠንካራ እምነት ነበረው። ሐዋርያው ጳውሎስ የሕዝብ መሪ ሆኖ ከመመረጡ በፊት ስለነበረው ሁኔታ ሲገልጽ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና” ብሏል። (ዕብራውያን 11:27) ሙሴ የሕዝቡ ገዥ ይሖዋ መሆኑን ፈጽሞ እንዳልረሳ ግልጽ ነው። (መዝሙር 90:1, 2) በዛሬው ጊዜ ለምንኖረው እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

8. ይሖዋ ለኢያሱ ምን ትእዛዝ ሰጠው? ይህንንስ ልብ ልንል የሚገባው ለምንድን ነው?

8 የእስራኤልን ሕዝብ በበላይ ተመልካችነት ማስተዳደር ሙሴ ብቻውን የሚሸከመው ኃላፊነት አለመሆኑ ሲረጋገጥ ይሖዋ በሕዝቡ ላይ በመፍረድ ሥራ ሊረዱ ለሚችሉ 70 ሽማግሌዎች መንፈሱን ሰጣቸው። (ዘኁልቁ 11:16–25) በኋለኞቹ ዓመታት እያንዳንዱ ከተማ የየራሱ ሽማግሌዎች እንዲኖሩት ተደርጓል። (ከዘዳግም 19:12፤ ከ22:15–18ና ከ25:7–9 ጋር አወዳድር።) ሙሴ ከሞተ በኋላ ይሖዋ ኢያሱን የሕዝቡ መሪ እንዲሆን ሾመው። ኢያሱ በርካታ ሥራ እንዲያከናውን የሚጠይቅበት መብት እንደሆነ መገመት እንችላለን። ይሁን እንጂ በዚህ ሁሉ ኃላፊነቱ ላይ ቸል ሊለው የማይገባ አንድ ነገር እንዳለ ይሖዋ ነግሮታል። እርሱም “የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፣ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም” አለው። (ኢያሱ 1:8) ኢያሱ ከ40 ዓመት በላይ ይሖዋን ያገለገለ ሰው ቢሆንም ሕጉን ማንበብ አስፈልጎት ነበር። ይሖዋን ያገለገልንበት ዓመት ምንም ያህል ብዙ ቢሆን ወይም ያገኘናቸው መብቶች ምንም ያህል ብዙ ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ስለ ይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለንን እውቀት ማደስ ያስፈልገናል።—መዝሙር 119:111,112

9. በመሳፍንት ዘመን በእስራኤል ምን ነገር ተደረገ?

9 ከኢያሱ በኋላ በተከታታይ የተነሡ መሳፍንት ነበሩ። የሚያሳዝነው ግን በእነዚህ መሳፍንት ዘመን እስራኤላውያን እየደጋገሙ “በእግዚአብሔር ፊት ክፉ የሆነ ነገር አደረጉ።” (መሳፍንት 2:11) ታሪኩ ስለ መሳፍንት ዘመን ሲናገር “በዚያን ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰው ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር” ይላል። (መሳፍንት 21:25) እያንዳንዱ ሰው ስለሚከተለው ምግባርና አምልኮ የየራሱን ውሳኔ ያደርግ ነበር። ታሪክ እንደሚያሳየው አብዛኞቹ እስራኤላውያን ያደረጉት ውሳኔ መጥፎ ነበር። በጣዖት አምልኮ ይጠላለፉና አንዳንድ ጊዜም አሠቃቂ ወንጀል ይፈጽሙ ነበር። (መሳፍንት 19:25–30) ይሁን እንጂ በዚህ መካከል በምሳሌነት የሚጠቀስ እምነት ያሳዩ ጥቂት ሰዎች ነበሩ።—ዕብራውያን 11:32–38

10. በሳሙኤል ዘመን በድንገት የመንግሥት ለውጥ የተደረገው እንዴት ነበር? እዚህ ደረጃ ላይስ ያደረሳቸው ምንድን ነው?

10 የመጨረሻ መስፍን በሆነው በሳሙኤል ዘመን በእስራኤላውያን መካከል አገዛዝን የሚመለከት ችግር ተፈጠረ። እስራኤላውያን በዙሪያቸው ባሉትና በነገሥታት ይገዙ በነበሩት ጠላት ብሔራት ተጽእኖ በመገፋፋት እነሱም ነገሥታት እንደሚያስፈልጋቸው አሰቡ። ንጉሥ እንዳላቸውና መንግሥታቸውም ቲኦክራሲያዊ እንደሆነ ረሱ። ይሖዋ ለሳሙኤል “በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን እንጂ አንተን አልናቁምና በሚሉህ ነገር ሁሉ የሕዝቡን ቃል ስማ” በማለት ነገረው። (1 ሳሙኤል 8:7) የእነርሱ ምሳሌ መንፈሳዊ አመለካከታችንን እንዴት በቀላሉ ልናጣ እንደምንችልና በአካባቢያችን ባለው ዓለም ተጽእኖ እንዴት በቀላሉ ልንወሰድ እንደምንችል ያሳስበናል።—ከ1 ቆሮንቶስ 2:14–16 ጋር አወዳድር።

11. (ሀ) የመንግሥት ለውጥ ቢኖርም እስራኤል በነገሥታት የምትተዳደር ቲኦክራሲያዊ አገር ሆና ቀጥላለች ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለእስራኤል ነገሥታት ምን ትእዛዝ ሰጥቷቸው ነበር? ዓላማው ያደረገውስ ምንን ነበር?

11 ያም ሆነ ይህ ይሖዋ በእስራኤላውያን ጥያቄ ተስማማና የመጀመሪያዎቹን ሁለት ነገሥታት ማለትም ሳኦልንና ዳዊትን መረጠላቸው። እስራኤል አሁንም በይሖዋ የምትገዛ ቲኦክራሲያዊ ብሔር መሆኗን ቀጠለች። ከዚህም የተነሣ እያንዳንዱ ንጉሥ “አምላኩን እግዚአብሔርን መፍራት ይማር ዘንድ፣ የዚህን ሕግ ቃል ሁሉ ይህችንም ሥርዓት ጠብቆ ያደርግ ዘንድ፣ ልቡ በወንድሞቹ ላይ እንዳይኮራ” የሕጉን መጽሐፍ አስገልብጦ እንዲይዝና በየቀኑ እንዲያነበው የተሰጠውን ግዴታ ማስታወስ ነበረበት። (ዘዳግም 17:19, 20) አዎን፣ ይሖዋ በቲኦክራሲው ውስጥ ሥልጣን ያላቸው ሁሉ ራሳቸውን ከፍ ከፍ ማድረግ እንደማይገባቸውና ድርጊታቸው ሁሉ ሕጉን የሚያንጸባረቅ እንዲሆን ይፈልግ ነበር።

12. ንጉሥ ዳዊት ምን የታማኝነት ታሪክ አስመዝግቧል?

12 ንጉሥ ዳዊት በይሖዋ ላይ ከፍተኛ እምነት ስለ ነበረው አምላክ ዘላለማዊ ለሆነ የነገሥታት ሐረግ አባት እንደሚሆን ቃል ኪዳን ገባለት። (2 ሳሙኤል 7:16፤ 1 ነገሥት 9:5፤ መዝሙር 89:29) ዳዊት ለይሖዋ በትሕትና የተገዛበት ሁኔታ ልንከተለው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ነው። እርሱም “አቤቱ፣ በኃይልህ ንጉሥ ደስ ይለዋል፤ በማዳንህ እጅግ ሐሤትን ያደርጋል” ብሏል። (መዝሙር 21:1) ዳዊት በሥጋዊ ድክመት ምክንያት ኃጢአት የሠራበት ጊዜ ቢኖርም ዘወትር ይታመን የነበረው በራሱ ሳይሆን በይሖዋ ብርታት ነበር።

ቲኦክራሲያዊ ያልሆኑ ድርጊቶችና አስተሳሰቦች

13, 14. የዳዊት ወራሾች ከወሰዱአቸው ቲኦክራሲያዊ ያልሆኑ እርምጃዎች መካከል አንዳንዶቹ ምን ነበሩ?

13 ሁሉም እስራኤላውያን መሪዎች እንደ ሙሴና እንደ ዳዊት አልነበሩም። ለቲኦክራሲያዊው ዝግጅት ከፍተኛ ንቀት በማሳየት በእስራኤላውያን መካከል የሐሰት አምልኮ እንዲስፋፋ ፈቅደዋል። ታማኝ ከነበሩት ገዥዎች መካከል እንኳ አንዳንዶቹ ቲኦክራሲያዊ ያልሆነ ድርጊት የፈጸሙበት ጊዜ ነበር። ከፍተኛ ጥበብና ብልጽግና ተሰጥቶት የነበረው የሰሎሞን ሁኔታ በጣም የከፋ ነበር። (1 ነገሥት 4:25, 29) የይሖዋን ሕግ ንቆ ብዙ ሚስቶችን አገባና በእስራኤል የጣዖት አምልኮ እንዲስፋፋ ፈቀደ። ከሁኔታዎቹ መረዳት እንደሚቻለው የኋለኞቹ የሰሎሞን የንግሥና ዓመታት ጭቆና የበዛባቸው ነበሩ።—ዘዳግም 17:14–17፤ 1 ነገሥት 11:1–8፤ 12:4

14 የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም የተገዢዎቹን ሸክም እንዲያቃልል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር። እርሱ ግን የተፈጠረውን ችግር በየዋህነት ከመፍታት ይልቅ ሥልጣኑን አላግባብ በኃይል ሊጠቀምበት በመፈለጉ ከ12ቱ ነገዶች 10ሩን አጣ። (2 ዜና መዋዕል 10:4–17) የተገነጠለው አሥር ነገድ የመጀመሪያ ንጉሥ ኢዮርብዓም ነበር። መንግሥቱ ከተገነጠለበት መንግሥት ጋር እንዳይዋሃድ ለማድረግ የጥጃ አምልኮን አቋቋመ። ይህ ድርጊት በፖለቲካ አንጻር ሲታይ ብልጠት የተሞላበት እርምጃ ሊመስል ቢችልም ለቲኦክራሲው ግን ዓይን ያወጣ ንቀት ማሳየቱ ነበር። (1 ነገሥት 12:26–30) ቆይቶም ንጉሥ አሳ የረጅም ጊዜ የታማኝነት አገልግሎቱን በትዕቢት አጐደፈ። የይሖዋን ወቀሳ ይዞለት በመጣው ነቢይ ላይ ግፍ ፈጸመ። (2 ዜና መዋዕል 16:7–11) አዎን፣ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉም እንኳ ወቀሳ የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ይኖራል።

የቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ፍጻሜ

15. ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አይሁዳውያን መሪዎች ጥሩ የቲኦክራሲ ወኪሎች ሆነው ለማገልገል አለመቻላቸው የታየው እንዴት ነበር?

15 ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ጊዜ እስራኤል የምትተዳደረው በቲኦክራሲያዊ አገዛዝ ነበር። የሚያሳዝነው ግን በኃላፊነት ቦታ ላይ ከነበሩት ሽማግሌዎች አብዛኞቹ መንፈሳዊ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች አልነበሩም። ሙሴ የነበረውን ዓይነት የቅንነት ጠባይ አላዳበሩም። ኢየሱስ “ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል። ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፣ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ” በማለት መንፈሳዊ ድክመታቸውን አመልክቷል።—ማቴዎስ 23:2, 3

16. የመጀመሪያው መቶ ዘመን አይሁዳውያን መሪዎች ለቲኦክራሲ አክብሮት እንደሌላቸው ያሳዩት እንዴት ነበር?

16 የአይሁድ መሪዎች ኢየሱስን ለጴንጤናዊው ጲላጦስ አሳልፈው ከሰጡ በኋላ ለቲኦክራሲው ከመገዛት ምን ያህል ርቀው እንደነበረ አሳይተዋል። ጲላጦስ ኢየሱስን ከመረመረ በኋላ ንጹሕ ሰው መሆኑን አረጋገጠ። ኢየሱስን አውጥቶ በአይሁድ ፊት ካቆመ በኋላ “እነሆ ንጉሣችሁ” አላቸው። አይሁዶች ኢየሱስ እንዲገደል እየጮኹ በጠየቁት ጊዜ ጲላጦስ “ንጉሣችሁን ልስቀለውን?” ብሎ ጠየቃቸው። የካህናት አለቆችም “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው መለሱ። (ዮሐንስ 19:14, 15) ‘በይሖዋ ስም የመጣውን’ ኢየሱስን ሳይሆን ቄሣርን እንደ ንጉሣቸው አድርገው ተቀበሉ።—ማቴዎስ 21:9

17. ሥጋዊ እስራኤል ቲኦክራሲያዊ ብሔር መሆኑን ያቆመው ለምን ነበር?

17 አይሁዶች ኢየሱስን አንፈልግም በማለታቸው ቲኦክራሲያዊውን አገዛዝ ሳይቀበሉ ቀሩ። ምክንያቱም ወደፊት በሚቋቋመው ቲኦክራሲያዊ ዝግጅት ከፍተኛውን ሥልጣን የሚይዘው እርሱ ስለሆነ ነው። ኢየሱስ ለዘላለም የሚነግሥ የዳዊት ንጉሣዊ ልጅ ነበር። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ ሉቃስ 1:33፤ 3:23, 31) በዚህም ምክንያት ሥጋዊ እስራኤል የአምላክ የተመረጠ ሕዝብ መሆኑ ቀረ።—ሮሜ 9:31–33

አዲስ ቲኦክራሲ

18. በመጀመሪያው መቶ ዘመን ምን አዲስ ቲኦክራሲያዊ ብሔር ተወለደ? አብራራ።

18 አምላክ ሥጋዊ እስራኤልን በመተዉ ቲኦክራሲ በምድር ላይ መኖሩ አላከተመም። ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት አዲስ ቲኦክራሲ አቋቋመ። ይህ አዲስ ቲኦክራሲ የአዲሱ ብሔር ማለትም የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ነበር። (1 ጴጥሮስ 2:9) ይህንን ብሔር ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር እስራኤል” በማለት ሲጠራው አባሎቹም ከጊዜ በኋላ “ከነገድ ሁሉ፣ ከቋንቋም ሁሉ፣ ከወገንም ሁሉ፣ ከሕዝብም ሁሉ” የተውጣጡ ይሆናሉ። (ገላትያ 6:16፤ ራእይ 5:9, 10) የአዲሱ ቲኦክራሲ አባሎች በሚኖሩባቸው አገሮች ለሚገኙ ሰብአዊ መንግሥታት የሚገዙ ቢሆንም ገዥያቸው አምላክ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:13, 14, 17) አዲሱ ቲኦክራሲ ከተወለደ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሥጋዊ እስራኤል ገዥዎች አንዳንድ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የሰጣቸውን ትእዛዝ መፈጸማቸውን እንዲያቆሙ ለማስገደድ ሞክረው ነበር። የተሰጣቸው መልስ ምን የሚል ነበር? “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” የሚል ነበር። (ሥራ 5:29) በእውነትም ቲኦክራሲያዊ አመለካከት ነበራቸው!

19. የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ቲኦክራሲያዊ ነበር ሊባል የሚቻለው እንዴት ነው?

19 ታዲያ አዲሱ ቲኦክራሲ ሥራውን ያከናውን የነበረው እንዴት ነበር? ታላቅ ቲኦክራሲያዊ አደራጅ የሆነውን ይሖዋን በመወከል ንጉሥ ሆኖ ይሠራ የነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። (ቆላስይስ 1:13) ምንም እንኳ ንጉሡ የሚኖረው በሰማያት በመሆኑ በዓይን የማይታይ ቢሆንም አገዛዙ ለተገዢዎቹ እውን ነበር። ሕይወታቸውንም የሚቆጣጠረው የንጉሡ ቃል ነበር። በሚታይ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ረገድ መንፈሳዊ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎች ይሾሙ ነበር። በኢየሩሳሌም የነበረው የእነዚህ ሽማግሌዎች ቡድን የአስተዳደር አካል በመሆን ይሠራ ነበር። ይህ አካል እንደ ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስና ቲቶ በመሰሉ ተጓዥ ሽማግሌዎች ይወከል ነበር። በተጨማሪም እያንዳንዱ ጉባኤ በሽማግሌዎች አካል ይጠበቅ ነበር። (ቲቶ 1:5) አንድ ከበድ ያለ ችግር ሲፈጠር ሽማግሌዎቹ የአስተዳደር አካሉን ወይም እንደ ጳውሎስ ያለውን የአስተዳደር አካል ወኪል የሆነ ሽማግሌ ያማክራሉ። (ከሥራ 15:2፤ ከ1 ቆሮንቶስ 7:1፤ ከ8:1ና ከ12:1 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በተጨማሪ እያንዳንዱ የጉባኤ አባል ቲኦክራሲውን በመደገፍ የየራሱን ድርሻ ያከናውናል። እያንዳንዱ አባል በሕይወቱ ውስጥ የቅዱሳን ጽሑፎችን መሠረታዊ ሥርዓቶች ሥራ ላይ የማዋል ኃላፊነት አለበት።—ሮሜ 14:4, 12

20. ከሐዋርያት ሞት በኋላ በነበሩት ዘመናት ስለ ቲኦክራሲ መኖር ምን ሊባል ይቻላል?

20 ጳውሎስ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ክህደት እንደሚነሣ አስጠንቅቆ ነበር። ይህም በትክክል ተፈጽሟል። (2 ተሰሎንቄ 2:3) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሰዎች ቁጥር በሚልዮኖችና በመቶ ሚልዮኖች እስከመቆጠር ደረሰ። እነርሱም እንደ ሃይርአርኪካል፣ ፕሪስቢተሪያን እና ኮንግሪጌሽናል እንደሚባሉት ያሉትን የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን የአገዛዝ ሥርዓቶች አቋቋሙ። ይሁን እንጂ የእነዚህ ቤተ ክርስቲያኖች ምግባርም ይሁን እምነት የይሖዋን አገዛዝ የሚያንጸባርቅ አልሆነም። ቲኦክራሲዎች አልነበሩም።

21, 22. (ሀ) ይሖዋ በፍጻሜው ዘመን ቲኦክራሲውን እንደገና መልሶ ያቋቋመው እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹ ቲኦክራሲን የሚመለከቱ ጥያቄዎች መልስ ያገኛሉ?

21 በዚህ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከሐሰተኛ ክርስቲያኖች የመለየት ሥራ መከናወን ነበረበት። (ማቴዎስ 13:37–43) ይህ የተከናወነው በቲኦክራሲያዊው ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ በተደረገበት በ1919 ነበር። በዚያን ጊዜ ክብራማው የኢሳይያስ 66:8 ትንቢት ፍጻሜውን አገኘ። “ከቶ እንዲህ ያለ ነገር ማን ሰምቶአል? እንዲህስ ያለ ነገር ማን አይቶአል? በውኑ አገር በአንድ ቀን ታምጣለችን? ወይስ በአንድ ጊዜ ሕዝብ ይወለዳልን?” ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ አዎ በማለት ያስተጋባል። የክርስቲያን ጉባኤ በ1919 ከሌሎች የተለየ “ብሔር” ሆኖ ተቋቋመ። ቲኦክራሲያዊ የሆነ “አገር” በአንድ ቀን ተወለደ። የፍጻሜው ዘመን ወደፊት እየገፋ በሄደ መጠን የዚህ አዲስ ብሔር አደረጃጀት በየጊዜው እየተስተካከለ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበረው አደረጃጀት ጋር በጣም እንዲመሳሰል ተደርጓል። (ኢሳይያስ 60:17) ነገር ግን ምንጊዜም ቢሆን ቲኦክራሲያዊ ነበር። በምግባሩና በእምነቱ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትንና በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት የተሰጡትን ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ሲያንጸባርቅ ኖሯል። እንዲሁም ሁልጊዜ ራሱን በዙፋን ላይ ለተቀመጠው ንጉሥ ለኢየሱስ ክርስቶስ አስገዝቷል።—መዝሙር 45:17፤ 72:1, 2

22 አንተስ የዚህ ቲኦክራሲ ተባባሪ ሆነሃልን? በቲኦክራሲውስ ውስጥ የሥልጣን ቦታ አለህን? ከሆነ፣ ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ መመላለስ ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህን? ከየትኞቹ ወጥመዶች መጠበቅ እንደሚገባህ ታውቃለህን? የመጨረሻዎቹ ሁለት ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ ይብራራሉ።

ልታብራራ ትችላለህን?

◻ ቲኦክራሲ ምንድን ነው?

◻ እስራኤል ቲኦክራሲያዊ ብሔር የነበረችው በምን መንገድ ነበር?

◻ እስራኤል ቲኦክራሲያዊ ብሔር መሆኗን ለነገሥታቷ ለማስታወስ ይሖዋ ምን ዝግጅት አደረገላቸው?

◻ የክርስቲያን ጉባኤ ቲኦክራሲያዊ የነበረው በምን መንገድ ነበር? የተደራጀውስ እንዴት ነበር?

◻ በዘመናችን ምን ቲኦክራሲያዊ የሆነ ድርጅት ተቋቁሟል?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት የአይሁድ መሪዎች በቲኦክራሲያዊ መንገድ በይሖዋ የተሾመውን ንጉሥ ትተው የቄሣርን ንግሥና ተቀብለዋል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ