ዘወትር በሚያደርገው እድገት ተወዳዳሪ ከሌለው ድርጅት ጋር ማገልገል
ሮበርት ሆትስፌልት እንደተናገረው
ዛሬ ብዙ ሰዎች ከርቀት መቆጣጠር በሚያስችል የኤሌክትሮኒክ መሣሪያ (ሪሞት ኮንትሮል) በመጠቀም ቴሌቪዥናቸውን ከፍተው ባለ ቀለም ፊልሞችን እየተመለከቱ የየምሽቱን ዜናዎች ሲያዳምጡ እንደ ልዩ ነገር አድርገው አይቆጥሩትም። ይሁን እንጂ የ12 ዓመት ልጅ ሳለሁ ፊልም በሚታይበት ትልቅ ሰሌዳ ላይ በጣም በመገረም አፍጥጬ የተመለከትኩበት ጊዜ የትናንት ያህል ቅርብ ሆኖ ይታወሰኛል። ከእውነተኛ ቁመቱ የበለጠ መጠን ያለውን የአንድ ሰው ምስል ሰሌዳው ላይ አየሁ፤ ደግሞም ይናገር ነበር!
ታዲያ ይህ ምን ያስደንቃል? ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ሆኖም ጥቁርና ነጭ ቀለም ብቻ ያለው ድምፅ አልባ ተንቀሳቃሽ ፊልም ይታይ በነበረበት በ1915 ይህ ለእኔ እንደ ተአምር የሚቆጠር ነበር። ግርማ ሞገስ ያለው አንድ ጢማም ሰውዬ በስክሪኑ ላይ ብቅ አለና “በዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የተዘጋጀው የፍጥረት ፎቶ ድራማ ቀጥሎ ይቀርባል” አለ። ለቀጣዮቹ ሁለት ሰዓታት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈረው ታሪክ አንድ በአንድ ቀረበ። የፊልሙ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልእክት ግልጽና የሚያነቃቃ ነበር። ይሁንና እኔን የሳበኝ ተንቀሳቃሹ ፊልምና በየጣልቃው የሚታየው ባለ ቀለም ስላይድ ፊልም፣ ከዚህም ጋር የተቀናጀው ንግግር ነበር።
ያኔ ይህን ያህል ልብ አላልኩትም ነበር፤ ይሁን እንጂ አዲስ ምዕራፍ ከፋች ለሆነው ለዚህ ቴክኖሎጂ የነበረኝ የወጣትነት ስሜት ሙሉውን ዕድሜዬን በግስግጋሴው ተወዳዳሪ ከሌለው ድርጅት ጋር ለመሥራት ላስቻለኝ ሙያ ዋዜማ ነበር።
የልጅነት ጊዜዬ
በ1891 አባቴ ዲሌንበርግ ከምትባል የጀርመን ከተማ ወደ አሜሪካ ተዛውሮ መጣና በፔንሲልቫንያ አልጌኒ በጀርመናውያን ሰፈር መኖር ጀመረ። እዚያም ትንሽ ቆይቶ ቤተሰቦቿ ጀርመናውያን የሆኑ አንዲት ልጃገረድ ተዋወቀና ተጋቡ። ሐምሌ 7, 1903 ተወለድኩ። ጀርመንኛና እንግሊዝኛ መናገር ችዬ አደግሁ። አንደኛው የዓለም ጦርነት በ1914 ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ በወቅቱ ወረርሽኝ በነበረው የሳንባ ነቀርሳ በሽታ ሁለቱንም ወላጆቼን ተነጠቅሁና ወላጅ አልባ ሆንሁ። በዚያው ወቅት አያቴ በአንጎሉ ውስጥ ደሙ ፈስሶ ሞተ።
የአባቴ ታናሽ እህት ሚና ቦመር እኔን ለማሳደግ በደግነት ወደ ቤቷ ወሰደችኝ። “አምስት ልጆች አሉኝ፤ አንድ ብጨምር ደግሞ አይጎዳኝም” አለች። ምንም እንኳ ወላጆቼን ማጣቴ ባጣም ቢሰማኝም አክስቴ ሚና በጥሩ ሁኔታ አሳደገችኝ።
አክስቴ ለብዙ ዓመታት በአልጌኒ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በዚያ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ይጠሩበት የነበረ ስም ነው) ጉባኤ አባል ነበረች። ከ1909 ቀደም ባሉት ጊዜያት በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት የነበረው ወንድም ሲ ቲ ራስልም የሚሰበሰበው እዚሁ ጉባኤ ነበር። አክስቴ ወደ ስብሰባዎች ትወስደኝ ነበር። ቤተሰባችን ከስብሰባ በኋላ ለማጥናት ወይም ለመስበክ ያደረገው የተቀናጀ ጥረት ባይኖርም በስብሰባ ላይ የሰማናቸውን ነገሮች ለምናውቃቸው ሰዎች መደበኛ ባልሆነ መንገድ እናካፍላቸው ነበር።
በዚህ ጊዜ ነበር “ፎቶ ድራማ” ስሜቴን የመሰጠው። መካኒክ የመሆን ዝንባሌ ስለነበረኝ የአዲሶቹ የፎቶ ግራፍ አነሳስ ዘዴዎች እንዲሁም የድምፅና የፎቶ ግራፎቹ ቅንብር በጣም ማረከኝ። በፊልሙ ውስጥ የአበባ እንቡጦች ደረጃ በደረጃ ሲፈኩ ማየት በጣም ይማርክ ነበር!
በ1916 በወንድም ራስል ሞት በጣም አዘንን። እዚያው አልጌኒ እንኖር ስለነበር በካርኔጂ አዳራሽ በተደረገው የቀብሩ ንግግር ላይ ተገኝተን ነበር። በ1903 ወንድም ራስል ከኢ ኤል ኢተን ጋር የተከራከረው እዚህ አዳራሽ ውስጥ ነበር። የሜቶዲስት ኤፒስኮፓል ቄስ የነበረው ይህ ሰው የወንድም ራስልን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራዊነት ከንቱ ለማድረግ በማሰብ ስድስት ቀን የፈጀ ሙግት የገጠመው በዚህ አዳራሽ እንደነበር ሰምቻለሁ። ውጤቱ ግን ከተጠበቀው ተቃራኒ ሆነና ራስል ‘በገሃነም ላይ ውኃ በማፍሰስ እሳቱን አጠፋው’ ተብሎ ተነገረ። በፔትስበርግ የነበረችው ታዋቂዋ ኮልፖልተር ሣራ ኬሊን ራስልንና ባለቤቱን በግል ታውቃቸው ነበር። ማሪያ ራስል “ለውዱ ባለቤቴ” የሚል ጽሑፍ ያለበት የአበባ ጉንጉን በመቃብሩ ላይ ስታስቀምጥ እኅት ሣራ አይታለች። ምንም እንኳ ማርያ አያሌ ዓመታት ቀደም ብላ ራሷ ብትለየውም ወንድም ራስልን አሁንም እንደ ባለቤቷ አድርጋ ትመለከተው ነበር።
ዓመታት እያለፉ በሄዱ መጠን ለወደፊቱ ሙያዬ ጠቃሚ የሆኑ ቴክኒካዊ ችሎታዎችን ለማዳበር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን አግኝቻለሁ። የሕግ ሞግዚቴ የነበረው አጎቴ የሕንፃ ሥራ ኮንትራክተር ነበር። ትምህርት ቤት ሲዘጋ በትልልቅ ቤቶች ውስጥ የነበሩትን የጋዝ መብራቶች ወደ ኤሌክትሪክ መብራቶች ሲለውጡ ከኤሌክትሪክ ሠራተኞቹ ጋር እንድሠራ ይፈቅድልኝ ነበር። በ1918 የትምህርት ቤታችን ልጆች በትርፍ ጊዜያቸው የሬድዮ ቴሌግራፍ መገናኛ መሣሪያ ሠሩ። ከኤሌክትሪክና ከማግኔት ጋር የተያያዙ ነገሮችን ለማጥናትና ልምምድ ለማድረግ በየምሽቶቹ እንገናኝ ነበር። በ1926 እኔ እና አንድ ጓደኛዬ መርከበኞች ሆነን ዓለምን ለመዞር አድሮብን የነበረውን ምኞት እውን ለማድረግ ወሰንን። በሬድዮ ቴሌግራፍ ኦፕሬተርነት ለመሠልጠን በአሜሪካ የሬድዮ ኮርፖሬሽን ትምህርት ቤት ተመዘገብን።
አዲስ ሕይወት በቤቴል
የሬድዮ ትምህርት ቤታችን የሚገኘው በኒው ዮርክ ከተማ ነበር። በብሩክሊን በተከራየነው የማሶኒክ ቤተ መቅደስ አዳራሽ ውስጥ ይደረግ በነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወንዝ ተሻግሬ መሄድ ነበረብኝ። በዚያ ጊዜ በመላው የኒው ዮርክ ከተማ የነበረው ጉባኤ አንድ ብቻ ነበር። ከቤቴል (የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞች መኖሪያ) የመጡ ወንድሞች ለሬድዮ ሠራተኛነት የሚያበቃ ፈቃድ ለማግኘት እንደማጠና ሲያውቁ “ለምን መርከበኛ ትሆናለህ? እኛ የሬድዮ ጣቢያ እዚህ ስላለን የሬድዮ ኦፕሬተር ያስፈልግናል” አሉ። ወደ ቢሮ ሄጄ እንዳነጋግራቸው ጠሩኝ። ስለ ቤቴል የማውቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዋና መሥሪያ ቤት መሆኑን ብቻ ነበር።
ወንድሞች አነጋገሩኝ። ትምህርቴን ከጨረስኩና የሬድዮ ሠራተኛነት ፈቃድ ካገኘሁ በኋላ ወደ ቤቴል እንድመጣ ሐሳብ አቀረቡልኝ። ከተመረቅሁ በኋላ በውቅያኖስ በመርከብ ላይ ለመኖር ከመወሰን ይልቅ ያሉኝን ጥቂት ልብሶች ያዝኩና በባቡር ተሳፍሬ ወደ ቤቴል ገሰገስኩ። ምንም እንኳ ራሴን ለይሖዋ የወሰንኩና ለብዙ ዓመታት በስብከቱ ሥራ ተሳትፎ ሳደርግ የቆየሁ ብሆንም እስከ ታኅሣሥ 1926 ድረስ አልተጠመቅሁም ነበር። ይህም ቤቴል ገብቼ ሁለት ሳምንት ካለፈኝ በኋላ ነበር። በዚያን ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ነገር ያልተለመደ አልነበረም።
በዚያን ጊዜ በቤቴል 150 የምንሆን ወንድሞች ጭንቅንቅ ባለ ሁኔታ እንኖር ነበር። በእያንዳንዱ ክፍል አራት ወንድሞች ባንድ ላይ እንኖር ነበር። ሁላችንም በአንድ ግቢ ውስጥ እንመገብ፣ እንሠራና እንተኛ ስለነበር እንዲሁም ሁላችንም የምንሰበሰበው በኒው ዮርክ ከተማ በሚገኘው ብቸኛ ጉባኤ ስለነበር አብዛኞቹን ወዲያው አወቅኳቸው። በ1927 በ124 ኮሎምቢያ ሃይትስ የአዲሱ የቤቴል መኖሪያ ቤት ሥራ ተጠናቀቀ። እዚያም በአንድ ክፍል ውስጥ ሁለት ወንድሞች ለመኖር ቻልን።
በተጨማሪም በ1927 በ117 አዳምስ ጎዳና የተሠራው አዲሱ ፋብሪካ ሥራ ጀመረ። በ55 ካንኮርድ ስትሪት ላይ ከነበረው አሮጌ ፋብሪካ ወደ አዲሱ መሣሪያዎችን በማጓጓዝ ረድቻለሁ። በፋብሪካው ውስጥ ከሬድዮ መሣሪያዎች ሌላ አሳንሰሮች፣ የማተሚያ መሣሪያዎች፣ የላውንድሪ ዕቃዎችና በጋዝ የሚሠሩ ማሞቂያዎች ነበሩ። የኤሌክትሪክ ሽቦ ያለውን ማሞቂያ ደግሞ ከነበረበት ነቅዬ በአዲሱ ቦታ እገጥመው ነበር።
ቤቴል ውስጥ ያለው ግን ፋብሪካ ብቻ አልነበረም። እያንዳንዱን መጽሐፍ፣ ትራክትና መጽሔት በማተም የሚሳተፉ ትሑትና ታታሪ ሠራተኞች የበዙበት ቦታ ነው። በዓለም ላይ ታዋቂነትን ለማትረፍ የተነሣሡ ሰዎች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ ዓላማቸው የጌታን ሥራ መሥራት ብቻ ነበር። ደግሞም ብዙ ሥራ ነበር!
ከወንድም ራዘርፎርድ ጋር የነበረኝ ቅርርብ
የማኅበሩ ሁለተኛ ፕሬዘዳንት ከነበረው ከጆሴፍ ራዘርፎርድ ጋር የመሥራት መብት ማግኘቴ በጣም ጠቅሞኛል። ወንድም ራዘርፎርድ ቁመቱ 1 ሜትር ከ83 ሴንቲ ሜትር ሲሆን ደልዳላና ጠንካራ ሰውነት ነበረው፤ ወፍራም ግን አልነበረም። በቤቴል ከነበሩት ወጣት ወንድሞች ብዙዎች እስኪለምዱት ድረስ ይፈሩት ነበር። ወንድም ራዘርፎርድ ሌት ተቀን የሚያጠናና ጽሑፎችን የሚያዘጋጅ ነበር።
ወንድም ራዘርፎርድ ቀልድ የሚያውቅ ሰው ነበር። ከወንድም ራስል ጊዜ ጀምሮ በቤቴል የነበሩ በዕድሜ የገፉ ሁለት እህቶች ነበሩ። እነዚህ እህቶች ኮስታራ ፊት ስለነበራቸው የሚያስቅ ነገር ቢኖርም እንኳ ጮክ ብሎ መሳቅ ተገቢ አይደለም ብለው ያምኑ ነበር። አንዳንድ ጊዜ በእራት ሰዓት ወንድም ራዘርፎርድ ሁሉንም የሚያስቅ አንድ ነገር ይናገር ነበር፤ ይህም እነዚህን እህቶች ያስቆጣቸዋል። ሆኖም ብዙ ጊዜ በምግብ ሰዓት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶች የሚያመሩ ሐሳቦች ጭምር ያመጣ ነበር።
ወንድም ራዘርፎርድ ምግብ በማዘጋጀት ጥሩ ችሎታ ነበረው። ለወንድሞች ምግብ ማዘጋጀት ያስደስተው ነበር። አንድ ጊዜ የቤቴል ወጥ ቤት ሠራተኞች ዶሮ ሲገነጣጥሉ ከአጥንቶቹ አንዳንዶቹ ተሰባበሩባቸው። ወደ ወጥ ቤቱ ድንገት ዘው አለና ትክክለኛውን አገነጣጠል አሳያቸው። በምግቡ ውስጥ የዶሮ አጥንት ስብርባሪዎችን ማየት አይወድም ነበር!
ከቢሮ ውጭ ብዙ ጊዜ ከወንድም ራዘርፎርድ ጋር ጥቂት ጊዜ ለማሳለፍ አጋጣሚዎችን አገኝ ነበር። በደብሊው ቢ ቢ አር የሬድዮ ጣቢያችን ወይም በስቴትን አይላንድ በሚገኘው በጥናት ክፍሉ ውስጥ የመገናኘት አጋጣሚ ነበረኝ። ወንድም ራዘርፎርድ በጣም ደግና የሚሰብከውን ነገር በተግባር የሚያውል ሰው ነበር። ራሱ የማያደርገውን ሌሎች እንዲያደርጉት አይጠብቅባቸውም ነበር። በብዙዎቹ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች ውስጥ ኃላፊነት ካለቸው ሰዎች ጋር ሲወዳደር ወንድም ራዘርፎርድ ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ ባሕርይ ነበረው። ለይሖዋ መንግሥት ያደረ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ነበር።
የገንዘብ ችግሮች የተከሰቱባቸው ቀውጢ ጊዜያት
ቤቴል ከገባሁ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዓለም ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ደረሰባት። የገቢ ምንጮች እየነጠፉ ሄዱ፤ የገንዘብ ዋጋም ጋሸበ። ሥራ ጠፋ። ያለው ገንዘብ ጥቂት ነበር። የቤቴል ሥራ የሚካሄደው በእርዳታ በሚገኘው ገንዘብ ሲሆን ይሖዋ ለሥራው የሚያስፈልገውን ገንዘብ እንድናገኝ ያደርግ ነበር። ሁሉም እንደሚፈልገው ባይሆንም ምግብ አጥተን በፍጹም አናውቅም። በተቻለ መጠን በቁጠባ እንኖር ነበር። ከቤቴል ውጭ ያሉ ወንድሞችም በሚችሉት ሁሉ ይረዱን ነበር።
በ1932 የፋብሪካችን የበላይ ተመልካች የነበረው ታማኙ ወንድም ሮበርት ማርቲን ሞተ። የሃያ ሰባት ዓመቱ ናታን ኖር የወንድም ማርቲንን ቦታ ተክቶ እንዲሠራ ተሾመ። ወንድም ኖር ጥሩ ችሎታ ያለው ወጣት ነበር። እርሱ የፋብሪካው የበላይ ተመልካች ሆኖ መሾሙን ለመቀበል ያዳገተው ማንንም ወንድም አላየሁም። ሌሎች ታማኝ ወንድሞችም አንዳንዶቹን ለመጥቀስ ያህል ጆን ከሪዘን፣ ጆርጅ ኬሊ፣ ዳግላስ ጋልብሬይዝ፣ ራልፍ ሌፍለር እና ኢድ ቤከር ባጠቃላይ አብረውኝ የሠሩት ውድ ወንድሞች ሁሉ ያላቸውን ጥበብና የፈጠራ ችሎታ በፈቃዳቸው ለመንግሥቱ አገልግሎት አውለዋል።—ከዘጸአት 35:34, 35 ጋር አወዳድር።
ሬዲዮ ጣቢያ ላይ መሥራት
ድርጅታችን በተገኘው መንገድ ሁሉ ምሥራቹን ለማሰራጨት የቆመ ነበር። መላው ዓለም ስለ መንግሥቱ ማወቅ ያስፈልገው ነበር። እኛ ግን በሺህ የምንቆጠር ብቻ ነበርን። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበሩት ዓመታት የሬድዮ ቴክኖሎጂ ገና ጨቅላ ነበር። ሆኖም አንዳንድ አስተዋይ ወንድሞች ይህን የመገናኛ ዘዴ ይሖዋ በወቅቱ እንዲጠቀሙበት የሰጣቸው እንደሆነ አድርገው ተመልክተውት ነበር። ስለዚህ በ1923 በኒው ዮርክ ክፍለ ሀገር ውስጥ የራሳቸው ምክር ቤት ካሏቸው አምስት ክፍላተ ከተሞች መካከል አንዷ በሆነችው በስቴትን አይላንድ የደብልዩ ቢ ቢ አርን የሬድዮ ጣቢያ ማቋቋም ጀመሩ።
አንዳንዴ የጣቢያችን ሠራተኛ እኔ ብቻ የምሆንባቸው ጊዜያት ነበሩ። እኖር የነበረው እዚያው በስቴትን አይላንድ ሲሆን የኤሌክትሪክ ብልሽት ሲያጋጥም ወይም የመሣሪያ ጥገና ማድረግ ሲያስፈልግ በብሩክሊን ወደሚገኘው ፋብሪካ ለመሄድ በጀልባና በመሬት ውስጥ ለውስጥ በሚሄድ ባቡር ለሦስት ሰዓት ያህል እጓዛለሁ። የሬድዮ ጣቢያችን ራሱን ችሎ የሚሠራ እንዲሆን በናፍታ የሚሠራ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ሞተር ገዛን። በስቴትን አይላንድ የራሳችን የውኃ ጉድጓዶች ስለነበሩን እዚያ ለሚገኙት ጥቂት ሠራተኞችና በብሩክሊን ላሉት የቤቴል ቤተሰብ አባላት ለምግብነት የሚያገለግል የጓሮ አትክልት እናበቅል ነበር።
በኋላ ተጨማሪ ረዳቶች አግኝቼ ሁኔታዬ እስከተሻሻለበት ጊዜ ድረስ በሬድዮ ሥራው በነበረኝ ኃላፊነት ምክንያት በስብሰባና በመስክ አገልግሎት የነበረኝ ተሳትፎ በጣም ውስን ነበር። በዓመት እረፍታችን ካልሆነ በስተቀር በማኅበራዊ ጉዳዮች ለመሳተፍም ሆነ ቅዳሜና እሁድ ከከተማ ወጣ ብሎ ለመዝናናት ጊዜ አልነበረንም። አንድ ወቅት ላይ አንድ ሰው “እንዲህ ያለው ጥብቅ ፕሮግራም ቤቴልን ትተህ እንድትሄድ አሳስቦህ አያውቅም?” ብሎ ጠየቀኝ። እውነቱን ለመናገር “እንዲህ ያለው ሐሳብ መጥቶብኝ አያውቅም” ብዬ መለስኩለት። ራሳቸውን ለአምላከ ከወሰኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሮ መኖርና መሥራት መብትና ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው። መሠራት ያለበት አዲስ የሥራ ውጥን ጠፍቶ አያውቅም።
የሚያነቃቁ የሬድዮ ድራማዎችን እናዘጋጅና በሬድዮ እናስተላልፍ ነበር። ቀደም ብለው የተቀረጹ የድምፅ ቅንብሮች ስላልነበሩን የራሳችንን ዘዴ መፍጠር ነበረብን። ለስለስ ያለ የነፋስ ሽውታ እና የነጎድጓድ ድምፅ አስመስሎ ማሰማት የሚችል መሣሪያ ሠራን። ለሁለት የተከፈሉ የኮኮነት ፍሬ ቅርፊቶችን ከእንጨት በተሠሩ ሣጥኖች ላይ መታ መታ ስናደርግ ድንጋይ በተነጠፈባቸው መንገዶች ላይ የሚራመዱ የፈረስ ኮቴዎች የሚያሰሙትን ዓይነት ድምፅ ያሰማሉ። የምናዘጋጀው እያንዳንዱ ድራማ አስደናቂ ክንውን ነበር። ሰዎችም በጥሞና ያዳምጡ ነበር። ጊዜያቸውን የሚሻሙ ነገሮች እምብዛም ባልነበረባቸው በእነዚያ ጊዜያት ሰዎች በሬድዮ የሚተላለፉትን ድራማዎች ቁጭ ብለው በጥሞና ያዳምጡ ነበር።
በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ ማኅበሩ አንድን ፕሮግራም በብዙ የሬድዮ ጣቢያዎችና ከቴሌፎን መሥመሮች ጋር በማያያዝ ወደተለያዩ ቦታዎች በማስተላለፍ በሬድዮ ታሪክ ውስጥ ሊረሳ የማይችል ክንውን አስመዝግቧል። በዚህ መንገድ የመንግሥቱ ዜና በምድር ዙሪያ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ተዳርሷል።
የሸክላ ማጫወቻ
በ1930ዎቹ አጋማሽና በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ ንግግሮችን በሬድዮ ለማሰራጨት የሚረዱ፣ የሸክላ ማጫወቻዎችንና ሌሎች የድምፅ መሣሪያዎችን ለእኛ እንደሚመቹ አድርግን ሠራን። ንግግሮችን እንደ መስተዋት ለስላሳ ሆነው በልዩ መንገድ ከሰም በተሠሩት ዲስኮች ቀዳን። ከዚያም እያንዳንዱ ኦሪጅናል ቅጂ ጉድለት ያለበት መሆኑና አለመሆኑ በማይክሮስኮፕ በጥንቃቄ መረመርን። ጉድለት ከተገኘበት በሌላ ሸክላ እንደገና መቀዳት ይኖርበት ነበር። ከዚያም ከሰም በተሠራው ዲስክ የተቀዳው ኦሪጅናል ቅጂ የሸክላ ማጫዎቻ ወደሚያዘጋጁ ኩባንያዎች እንልከዋለን።
በደንብ ከማስታውሳቸው ስሜት ቀስቃሽ ከሆኑት ነገሮች አንዱ በ1933 “ቅዱሱ ዓመት በሰላምና በብልጽግና ላይ ያመጣው ውጤት” በሚል ርዕስ በወንድም ራዘርፎርድ የተሰጠው ንግግር ነው። የሮማው ጳጳስ ያንን ዓመት “ቅዱስ ዓመት” ብለው ሰይመውት ነበር። እኛም ይህ ዘበት እንደሆነና ምንም የሚመጣ ሰላምና ብልጽግና እንደሌለ በሬድዮና በሸክላ ማጫወቻዎች በሚተላለፉ ንግግሮች አጋለጥን። በዚያው ዓመት ሂትለር በሥልጣን ኮርቻ ላይ ተቆናጠጠ። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንም ድጋፏን ሰጠችው። ስለዚህ ለሰላም የነበረው ተስፋ እልም ብሎ ጠፋ።
በዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምትፈልገውን ጉዳይ ለማስፈጸም የቆመ ካቶሊክ አክሽን የተባለ ድርጅት ተቋቋመ። ዋና ዋናዎቹን ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና መጽሐፎች አትመው በሚያወጡ ድርጅቶች ውስጥ የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን የኅትመት ቦርድ ኮሚቴ አባላት አድርገው አስቀመጧቸው። በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት ማንኛውም የሬድዮ ጣቢያ የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግሮቻችንን እንዳያስተላለፍ በማስፈራራት አሳደሙብን። በተለይ በኒው ጀርሲ አካባቢ ይኖሩ በነበሩ ብዙ ምሥክሮች ላይ የካቶሊክ አክሽን አባላት ሆ ብለው በመውጣት ጥቃት አደረሱባቸው። እነዚያ ጊዜያት ቀላል አልነበሩም።
በመስክ አገልግሎት ያከናወንኩት አስደሳች ሥራ
የ1950ዎቹ አጋማሽ ከመድረሱ በፊት ቁጥራቸው እያደገ የመጣው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቤታቸው ድረስ በመሄድ ብዙ ሰዎችን ማነጋገር ችለው ነበር። ይህም ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲገባቸው ለመርዳት ከሬድዮ የበለጠ ውጤታማ መንገድ ሆኖ ተገኘ። ስለዚህ በ1957 ደብልዩ ቢ ቢ አር የተባለውን የሬድዮ ጣቢያ ለመሸጥና ገንዘቡን በሌሎች አገሮች የሚካሄደውን የሚስዮናዊነትን ሥራ ለማስፋፋት እንዲውል ተወሰነ።
በ1955 በብሩክሊን በሚገኘው በቤድፎርድ ጉባኤ ተመደብኩ። እዚያም በቋሚነት የመጠበቂያ ግንብ ጥናት እመራ ነበር። በተጨማሪም ወደ ሰሜናዊ የኒው ዮርክ ክፍለ ሀገር፣ ፔንሲልቫንያ፣ ኮኔቲከት እንዲሁም ወደ ኒው ጀርሲ እየሄድኩ ንግግር እንድሰጥ በማኅበሩ እላክ ነበር። በቤድፎርድ ጉባኤ ስመደብ ‘አሁን 50 ዓመት ሆኖኛል። በመስክ አገልግሎት በምችለው ሁሉ አሁንኑ መሳተፍ አለብኝ። በኋላ የወገብ ሕምም ያጋጥመኝና ብዙ ላልሠራ እችላለሁ’ ብዬ አሰብኩ።
በእነዚያ ዓመታት ሁሉ የመንግሥቱ ዘር ቴክኒካዊ በሆነ መንገድ በሬድዮ በሚዘራበት ስፍራ ስሠራ ከቆየሁ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በቀጥታ በግለሰቦች ልብ ላይ መትከልና ማጠጣት በጣም ያስደስታል። ከጉባኤው ጋር ሆኖ ማገልገል በጣም አስደስቶኛል። የተለያዩ ወንድሞችና እኅቶች እንደ ቤተሰባቸው አባል አድርገው ስለሚያዩኝ ብቸኝነት እንዳይሰማኝ አድርገውኛል። በዚያ ጊዜ ትንንሽ ልጆች የነበሩት ዛሬ አድገው እያሉም አያታችን ይሉኛል። እግሬ ደረጃዎችን ለመውጣት ወይም ከመሬት በታች ወደተዘረጉ መንገዶች ለመውረድ ችግር እስከፈጠረብኝ ድረስ ለ30 ዓመታት ያህል በመስክ አገልግሎት ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል። በ1985 ወደ ብሩክሊን ሃይትስ ጉባኤ ተዛወርኩ። ይህ ጉባኤ ስብሰባ የሚያደርገው ቤቴል ውስጥ ነው።
የይሖዋ ድርጅት በብዙ መልኩ እየሰፋ ሲሄድ ራቅ ብለው በሚገኙ አገሮች በተደረጉት የይሖዋ ምሥክሮች ትልልቅ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት የይሖዋን በረከት በግል የማየት መብት አግኝቻለሁ። ዓለምን ለመዞር ችያለሁ! ከ1950ዎቹ ጀምሮ ቤቴላውያን ከሆንነው መካከል አንዳንዶቻችን በለንደን፣ በፓሪስ፣ በኑረምበርግ በኮፐንሃገን የሚካሄደውን ሥራ ለማየት ወደነዚህ አገሮች ሄደን ነበር። የተጓዝነውም በፊት ቦምብ ጣይ በነበሩ አሁን ግን የሕዝብ ማመላለሻ በሆኑ አውሮፕላኖች፣ በጀልባና በባቡር ነበር። ጉዞዎቹ አስደሳች እይታ ነበራቸው። ከሁሉ በላይ አስደሳች የነበረው እይታ ግን ሞቅ ባለ ስሜት እንኳን ደህና መጣችሁ የሚሉ ብዙ ወንድሞች ነበሩ። በኋለኞቹ አሥርተ ዓመታት ወደ ምሥራቅ፣ በድጋሚ ወደ ምዕራብ አውሮፓና አሁን በቅርብ ደግሞ ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ለመጓዝ ችለናል። በፖላንድ፣ በቺኮዝሎቫኪያና በጀርመን የተደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች እጅግ አስደሳች ነበሩ። እኔ አባል መሆን ስጀምር ከነበረው ይልቅ ቲኦክራሲያዊው ቤተሰባችን ምን ያህል አድጓል!
መለኮታዊ አመራር
ድርጅቱ የወሰዳቸው ትንንሽ የሚመስሉ እርምጃዎች የኋላ ኋላ በጣም ትልቅ እርምጃ ሆነው ተገኝተዋል። የምሥክርነቱን ሥራ ለመሥራት እንዲረዱን አዳዲስ እቅዶችን በምንወጥንበት ወይም አዲስ ብልሃት ለመፍጠር በምንሯሯጥበት ጊዜ ይህ ዓይነቱ ታላቅ እድገት ይገኛል ብሎ የገመተ ማን ነበር? ይሖዋ ለሚሰጠው አመራር አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት በእምነት ወደፊት ገፋን።
ዘወትር እያደገ የሚሄደው ይህ ድርጅት በምድር ዙርያ ላለው የአገልግሎት መስክ በወቅቱ ባለው አዲስ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ወይም የራሱን ቴክኖሎጂ ፈጥሮ ምሥራቹን ከማዳረስ ወደኋላ ያለበት ጊዜ የለም። መንግሥቱን ለማወጅ ይሠራባቸው ከነበሩት ዘዴዎች መካከል ከቤት ወደ ቤት መስበክ፣ በተለያዩ የሬድዮ ጣቢያዎች መልእክቱን ማስተላለፍ፣ በሸክላ ማጫዎቻ ተጠቅሞ ምሥክርነት መስጠት እንዲሁም በግል መኖሪያ ቤቶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምራት ይገኙበታል። ቀደም ባሉት ጊዜያት የራሳችንን ማተሚያዎች ማቋቋማችንና አሁን ደግሞ በኮምፒውተር ተጠቅሞ ለኅትመት የሚያገለግሉ ገጾችን ማዘጋጀት፤ እንዲሁም በኦፍሴት ማተሚያ መጠቀሙ በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት፣ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትና ዘወትር የሚደረጉት ብሔራት አቀፍ ስብስባዎች ሁሉም ለይሖዋ አምላክና ለልጁ ክብር በማምጣት በኩል ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ በአካል ተገኝቼ ለማየትና ተሳትፎ ለማድረግ መብት አግኝቻለሁ።
ይሖዋ በመንፈሱ የሚመራው ምድራዊ ድርጅት ምን መሠራት እንዳለበትና እንዴት አድርጎ ሊሠራ እንደሚገባ መመሪያ የሚያገኘው ከይሖዋ መሆኑ ግልጽ ሆኖልኛል። የሚታየውም ሆነ የማይታየው የይሖዋ አጽናፈ ዓለማዊ ድርጅት አንድነቱን ጠብቆ ይንቀሳቀሳል።
ወጣት እያለሁ መርከበኛ ለመሆን የነበረኝን እቅድ ስለተውኩ በፍጹም ጸጸት ተሰምቶኝ አያውቅም። በዓለም ላይ ከሚከናወኑት ነገሮች ሁሉ ይበልጥ አስደሳች የሆኑና ትርጉም ያላቸው ለውጦች የሚካሄዱት እዚሁ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ሆኖ ሳለ እንዴት ቁጭት ሊሰማኝ ይችላል! ስለዚህ ‘ወደ ላይኛው ጥሪ’ በሚወስደው መንገድ ያደረግሁት ጉዞ ጸጸትን ሳይሆን በጣም ብዙ ደስታና በረከትን አስገኝቶልኛል—ፊልጵስዩስ 3:13, 14
ወጣቶች 1914ን እንዲያስታውሱ ሁልጊዜ እነግራቸዋለሁ። መዝሙር 19:14ን ማለቴ ነው። ጥቅሱ “አቤቱ [ይሖዋ አዓት]፣ ረድኤቴ መድኃኒቴም፣ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” ይላል። በሁሉም ነገር ይሖዋን ማስደሰት እንፈልጋለን። ዳዊት እንዲህ ሲል እንዳቀረበው ዓይነት ጸሎት ለመጸለይ እንፈልጋለን፦ “አቤቱ [ይሖዋ አዓት]፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፣ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ።” (መዝሙር 25:4, 5) እነዚህ ቃላት ብዙ ቁም ነገሮችን ይዘዋል። እነዚህን ቃላት ማስታወሳችን ይሖዋ ከሚመራውና በሁሉም መስክ እያደገ ከሚሄደው ድርጅት ጋር አብረን እየተራመድን በትክክለኛው መንገድና በትክክለኛው አቅጣጫ መጓዛችንን እንድንቀጥል ይረዳናል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንድም ራዘርፎርድ ለወንድሞች ምግብ ማዘጋጀት ያስደስተው ነበር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሮበትር ሆትስፌልት በደብልዩ ቢ ቢ አር የሬድዮ ጣቢያ ላይ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወንድም ሆትስፌልት በቅርቡ የተነሣው ፎቶግራፍ