የሕይወት ታሪክ
በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኩት በበረከት የተሞላ ሕይወት
ራስል ከርዘን እንደተናገረው
የተወለድኩት መስከረም 22, 1907 ማለትም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ የከፈተው አንደኛው የዓለም ጦርነት ከመፈንዳቱ ሰባት ዓመት በፊት ሲሆን ቤተሰቤ ከሁሉ ነገር የላቀ ሀብት ነበረው። ታሪካችንን ትንሽ ከሰማችሁ በኋላ በዚህ አባባሌ እንደምትስማሙ እርግጠኛ ነኝ።
ሴት አያቴ ገና ከትንሽነቷ ጀምሮ ስለ አምላክ እውነቱን ለማወቅ ትጥር ነበር። ገና አሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳትገባ ስዊዘርላንድ ውስጥ በምትገኘውና ውብና ማራኪ በሆነችው ትውልድ ከተማዋ ስፒትዝ ያሉትን የተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖች ጎብኝታለች። አያቴ ትዳር ከያዘች ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ማለትም በ1887 ቤተሰባችን ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ዳርቻዎች ከፈለሱት ስደተኞች ጋር አብሮ ተሰደደ።
ቤተሰቡ ኦሃዮ መኖር ከጀመረ በኋላ ማለትም በ1900 ገደማ አያቴ ስትፈልገው የነበረውን ሃብት ቻርልስ ቴዝ ራስል ዘ ታይም ኢዝ አት ሃንድ በሚል ርዕስ ባዘጋጀውና ወደ ጀርመንኛ በተተረጎመው መጽሐፍ ገጾች ውስጥ አገኘች። ወዲያው መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደያዘ ተገነዘበች። አያቴ እንግሊዝኛ ብዙም ማንበብ ባትችልም የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ኮንትራት ገብታ ነበር። ይህም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ይበልጥ እንድትረዳ ያስቻላት ከመሆኑም በላይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታዋንም አሻሽሎላታል። ወንድ አያቴ የሴት አያቴን ያህል ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍላጎት አልነበረውም።
አያቴ ከወለደቻቸው 11 ልጆች መካከል እርስዋ ያገኘችውን ውድ መንፈሳዊ ሃብት ከፍ አድርገው የተመለከቱት ጆን እና አዶልፍ የተባሉት ወንዶች ልጆችዋ ብቻ ነበሩ። ጆን አባቴ ሲሆን በ1904 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) ሴንት ሉዊስ ሚዙሪ ውስጥ ባደረጉት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠምቋል። አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ገቢያቸው አነስተኛ ስለነበረ በወቅቱ ሴንት ሉዊስ ሚዙሪ ውስጥ ይደረግ የነበረውን ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት አስታክኮ በተደረገው አነስተኛ የባቡር ክፍያ ለመጠቀም ሲባል የስብሰባው ቀን የንግድ ትርኢቱ ከሚካሄድበት ጊዜ ጋር እንዲገጣጠም ተደርጓል። በኋላም በ1907 አጎቴ አዶልፍ ኒያጋራፎልስ ኒው ዮርክ ውስጥ በተደረገ አንድ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠመቀ። አባቴና አጎቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማሩትን በቅንዓት ይሰብኩ የነበረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ሁለቱም የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች (አሁን አቅኚ ይባላሉ) ሆኑ።
በመሆኑም በ1907 ስወለድ ቤተሰቤ በመንፈሳዊ ሃብታም ሆኖ ነበር። (ምሳሌ 10:22) ጆንና አይዳ የተባሉት ወላጆቼ በ1908 ፑት ኢን ቤይ ኦሃዮ ውስጥ ወደተደረገው “ወደ ድል መገስገስ” የተሰኘ የአውራጃ ስብሰባ ሲወስዱኝ ገና ሕፃን ነበርኩ። ስብሰባውን በሊቀ መንበርነት የመራው በወቅቱ ተጓዥ አገልጋይ የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ነው። ከስብሰባው ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ ዳልተን ኦሃዮ መጥቶ ቤታችንን የጎበኘ ሲሆን እዚያ ለሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ንግግር ሰጥቷል።
እርግጥ በዚያን ጊዜ የተከናወኑትን ነገሮች ማስታወስ ባልችልም በ1911 ማውንቴን ሌክ ፓርክ ሜሪላንድ ውስጥ ያደረግነውን የአውራጃ ስብሰባ ፈጽሞ አልረሳውም። በስብሰባው ላይ እኔና ታናሽ እህቴ ኤስተር ከቻርልስ ቴዝ ራስል ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ ያገኘን ሲሆን በወቅቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የሚያካሂዱትን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ በበላይነት ይቆጣጠር ነበር።
ሰኔ 28, 1914 የሳራዬቮው አርክዱክ ፈርዲናንድና ሚስቱ ተገድለው የአንደኛው የዓለም ጦርነት ሲፈነዳ እኔና ቤተሰቤ ኮሎምበስ ኦሃዮ ውስጥ እየተካሄደ በነበረው ሰላም የሰፈነበት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ነበርን። ከእነዚያ የቀድሞ ዓመታት ጀምሮ የይሖዋ ሕዝቦች በሚያደርጓቸው ብዙ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የመገኘት መብት አግኝቻለሁ። አንዳንዶቹ ስብሰባዎች 100 እና ከዚያ ብዙም የማይበልጡ ተሰብሳቢዎች ብቻ የነበሩዋቸው ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ከፍተኛ የተሰብሳቢ ቁጥር የነበራቸውና በአንዳንድ የዓለም ታላላቅ ስታዲየሞች ውስጥ የተካሄዱ ነበሩ።
ቁልፍ ቦታ ላይ የሚገኘው ቤታችን
ከ1908 እስከ 1918 ባለው ጊዜ ውስጥ ዳልተን የሚገኘውና ፒትስበርግ፣ ፔንስልቬንያንና ክሌቭላንድ፣ ኦሃዮን በሚያገናኝ አማካይ ስፍራ ላይ የቆመው ቤታችን በቁጥር አነስተኛ የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚያደርጓቸውን የጉባኤ ስብሰባዎች አስተናግዷል። ቤታችን የብዙ ተጓዥ ተናጋሪዎች ማረፊያም ሆኖ ነበር። ፈረሶቻቸውንና ጋሪዎቻቸውን ከጋጣው ጀርባ ካሰሩ በኋላ ቤታችን ውስጥ ለተሰበሰቡ ሰዎች አስደሳች ተሞክሮዎችንና መንፈሳዊ እንቁዎችን ያካፍሉ ነበር። እነኛ ጊዜያት ምንኛ አበረታች ነበሩ!
አባቴ መምህር ቢሆንም ልቡ ግን ከሁሉም ዓይነት የማስተማር ሥራ በላቀው በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላይ ነበር። ቤተሰቡን ሁልጊዜ ስለ ይሖዋ ያስተምር የነበረ ሲሆን በእያንዳንዱ ምሽት በቤተሰብ መልክ እንጸልይ ነበር። በ1919 የጸደይ ወቅት ላይ አባቴ ፈረሳችንና ጋሪያችንን በመሸጥ በምትኩ የስብከቱን ሥራ ለማስፋፋት የምትስማማ አንዲት በ1914 የተሠራች ፎርድ መኪና በ175 የአሜሪካን ዶላር ገዛ። በ1919 እና በ1922 ሴዳር ፓይንት ኦሃዮ ውስጥ ወደተደረጉት ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው የአውራጃ ስብሰባዎች የሄድነው በዚህች መኪና ነበር።
መላው ቤተሰባችን ማለትም እማማ፣ አባባ፣ ኤስተር፣ ታናሽ ወንድሜ ጆንና እኔ ለሕዝብ በሚሰጠው ምሥክርነት እንካፈል ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ የቤት ባለቤት ያቀረበልኝን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ አስታውሳለሁ። በወቅቱ የሰባት ዓመት ገደማ ልጅ ነበርኩ። “ማሙሽ፣ አርማጌዶን ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀኝ። በአባቴ እርዳታ በመታገዝ ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ መስጠት ችዬ ነበር።
የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መጀመር
ቤተሰባችን በ1931 ኮሎምበስ ኦሃዮ ውስጥ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተገኘ ሲሆን በዚህ ስብሰባ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን አዲስ ስም ስንቀበል በጣም ተደስተን ነበር። ጆን በጣም ከመደሰቱ የተነሳ እኔና እርሱ አቅኚ መሆን እንዳለብን ወሰነ።a እናቴ፣ አባቴና ኤስተርም አቅኚዎች ሆኑ። በቤተሰብ መልክ አስደሳች በሆነው የአምላክን መንግሥት በመስበኩ ሥራ መካፈል ምንኛ መታደል ነው! ይሖዋ በዚህ መልክ ስለባረከን ሳላመሰግነው የዋልኩበት ቀን የለም። በጣም ተደስተን የነበረ ቢሆንም ገና ተጨማሪ ደስታ ይጠብቀን ነበር።
የካቲት 1934 ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ (ቤቴል ይባላል) ማገልገል ጀመርኩ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ጆንም አብሮኝ በቤቴል ማገልገል ጀመረ። ጄሲ የምትባል ውድ ሚስቱን በ1953 እስካገባበት ጊዜ ድረስ አንድ ክፍል ውስጥ አብረን ኖረናል።
ጆንና እኔ ቤቴል ከገባን በኋላ ወላጆቻችን አቅኚዎች በመሆን በተለያዩ ቦታዎች ያገለገሉ ሲሆን ኤስተርና ባለቤቷ ጆርጅ ሪድም አብረዋቸው አገልግለዋል። ወላጆቻችን በ1963 ምድራዊ ሕይወታቸውን እስከጨረሱበት ጊዜ ድረስ አቅኚዎች ነበሩ። ኤስተርና ባለቤቷ ጥሩ ቤተሰብ ያፈሩ ሲሆን እጅግ የሚወደዱ የእህት ልጆች በማግኘት ተባርኬአለሁ።
የቤቴል ሥራና አብሬያቸው እሠራ የነበሩ ወንድሞች
ጆን የቴክኒክ ሙያውን በቤቴል የተጠቀመበት ሲሆን ከሌሎች ቤቴላውያን ጋር በመተባበር ከቦታ ቦታ ሊዘዋወሩ የሚችሉ የሸክላ ማጫወቻዎችን መሥራትን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮጄክቶች ተካፍሏል። በሺህዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን መሣሪያዎች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ ተጠቅመውባቸዋል። ጆን ኮንትራት ለገቡ ግለሰቦች የሚላኩ መጽሔቶች ለመጠቅለልና በሽፋኖቻቸው ላይ ስምና አድራሻ ለመለጠፍ የሚያስችል ማሽን በመንደፍና በመሥራትም የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
በቤቴል ማገልገል ስጀምር መጀመሪያ የተመደብኩት በመጽሐፍ መጠረዣ ክፍል ውስጥ ነበር። በጊዜው በፋብሪካው ውስጥ የሚሠሩ ሌሎች ወጣቶችም የነበሩ ሲሆን አንዳንዶቹ አሁንም ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ኬሪ ባርበርና ሮበርት ሆትስፌልት ይገኙበታል። አንዳንዶቹ በሞት ያንቀላፉ ሲሆን ከእነዚህ ተወዳጅ ወንድሞች መካከል ናታን ኖር፣ ካርል ክላይን፣ ላይመን ስዊንግል፣ ክላውስ ጄንሰን፣ ግራንት ሱተር፣ ጆርጅ ጋንጋስ፣ ኦሪን ሂባርድ፣ ጆን ሳዮራስ፣ ሮበርት ፔይን፣ ቻርልስ ፌከል፣ ቤኖ ቡርቺክ እና ጆን ፔሪ ይገኙበታል። እነዚህ ወንድሞች ከዓመት እስከ ዓመት በምድባቸው የጸኑ ሲሆን አማርረውም ሆነ “እድገት” ጠብቀው አያውቁም። ያም ሆኖ ግን ከእነዚህ ታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ድርጅቱ ሲያድግ ከፍተኛ ኃላፊነቶች ተቀብለዋል። እንዲያውም አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ እስከማገልገል ደርሰዋል።
እነዚህን ከመሳሰሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ከሚያደርጉ ወንድሞች ጋር መሥራቴ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቶኛል። ሰዎች ለሰብዓዊ ሥራቸው ደሞዝ ይከፈላቸዋል። ይህ ሽልማታቸው ነው። በቤቴል ማገልገል ብዙ መንፈሳዊ በረከቶች የሚያስገኝ ሲሆን እነዚህን በረከቶች የሚያደንቁት መንፈሳዊ ወንዶችና ሴቶች ብቻ ናቸው።—1 ቆሮንቶስ 2:6-16
ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለ ማለትም በ1923 ቤቴል የገባው ናታን ኖር በ1930ዎቹ ዓመታት ውስጥ የፋብሪካ የበላይ ተመልካች ሆኖ ነበር። በየቀኑ ፋብሪካው ውስጥ በመዘዋወር ለእያንዳንዱ ሠራተኛ ሰላምታ ይሰጥ ነበር። አዳዲሶቹ ቤቴላውያን እንዲህ ያለውን የግል አሳቢነት እናደንቅ ነበር። በ1936 ከጀርመን አንድ አዲስ የማተሚያ መሣሪያ ያገኘን ሲሆን አንዳንዶቹ ወጣት ወንድሞች መሣሪያውን ለመገጣጠም በጣም ተቸግረው ነበር። ስለዚህ ወንድም ኖር ራሱ ቱታ አጥልቆ ሥራው በደንብ እስኪዋሃዳቸው ድረስ ከአንድ ወር ለሚበልጥ ጊዜ አብሯቸው ሠርቷል።
ወንድም ኖር በጣም ጠንካራ ሠራተኛ ከመሆኑ የተነሣ ብዙዎቻችንን ያስንቅ ነበር። ይሁን እንጂ እንዴት መዝናናት እንደሚቻልም ያውቅ ነበር። ጥር 1942 የይሖዋ ምሥክሮችን ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ በበላይነት የመቆጣጠር ኃላፊነት ከተቀበለም በኋላ እንኳ ሳይቀር አልፎ አልፎ ሳውዝ ላንሲንግ ኒው ዮርክ አጠገብ በሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ ከቤቴላውያንና ከጊልያድ ተማሪዎች ጋር ቤዝቦል ይጫወት ነበር።
ሚያዝያ 1950 የቤቴል ቤተሰብ 124 ኮሎምቢያ ሃይትስ ብሩክሊን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው አዲስ ባለ አሥር ፎቅ የመኖሪያ ሕንጻ ተዛወረ። አዲሱ የመመገቢያ ክፍል ሁላችንም አንድ ላይ ተሰባስበን መመገብ የምንችልበት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል። ሕንጻው በግንባታ ላይ በነበረባቸው ሦስት ዓመታት ቤተሰባችን የጠዋት አምልኮ ፕሮግራም ማካሄድ አልቻለም ነበር። ይህ ፕሮግራም እንደገና ሲጀምር ምንኛ ተደስተን ነበር! ወንድም ኖር የአዳዲስ ቤቴላውያንን ስም ለማስታወስ እንድረዳው ከእርሱ ጋር በሊቀ መንበሩ ጠረጴዛ እንድቀመጥ መደበኝ። በዚህ ቦታ ላይ ለጠዋት አምልኮና ለቁርስ 50 ለሚያክሉ ዓመታት ተቀምጫለሁ። ከዚያም ነሐሴ 4, 2000 ይህ የመመገቢያ ክፍል በመዘጋቱ በቀድሞው ታወርስ ሆቴል ከሚገኙትና እደሳ ከተደረገላቸው የመመገቢያ ክፍሎች ውስጥ ወደ አንዱ ተዛወርኩ።
በ1950ዎቹ ዓመታት ለተወሰነ ጊዜ በፋብሪካ ውስጥ ሊኖታይፕ በሚባለው መሣሪያ ላይ ሠርቻለሁ። እዚያም ፊደላትን በመገጣጠም መስመሮችን ብሎም ገጾችን ካሟላሁ በኋላ የማተሚያ ፕሌቶች አዘጋጅ ነበር። ይህ ዓይነቱን ሥራ ባልወደውም ማሽኖቹን በበላይነት የሚቆጣጠረው ዊልያም ፒተርሰን ለእኔ የነበረው አሳቢነት እዚያ ያሳለፍኩትን ጊዜ በጥሩ ትዝታ እንዳስታውሰው አድርጎኛል። ከዚያም በ1960 107 ኮሎምቢያ ሃይትስ የሚገኘውን አዲስ የመኖሪያ ሕንጻ ቀለም የሚቀቡ ፈቃደኛ ሠራተኞች በማስፈለጋቸው እዚያ ሄጄ እያደገ ለመጣው የቤቴል ቤተሰባችን የተሠሩትን አዳዲስ ሕንጻዎች ቀለም ለመቀባት ፈቃደኝነቴን ገለጽኩ።
የ107 ኮሎምቢያ ሃይትስ ሕንጻ ቀለም ተቀብቶ እንዳለቀ ብዙም ሳይቆይ ወደ ቤቴል የሚመጡ ጎብኚዎችን ተቀብሎ የማስተናገድ ሥራ ሲሰጠኝ በጣም ተገረምኩ። እንግዳ ተቀባይ ሆኜ ያሳለፍኳቸው የመጨረሻዎቹ 40 ዓመታት በቤቴል እንዳሳለፍኳቸው እንደ ሌሎቹ ዓመታት ሁሉ በጣም አስደሳች ነበሩ። ወደ ቤቴል ለሚመጡ ጎብኚዎችም ሆነ ለአዳዲስ ቤቴላውያን ለመንግሥቱ ጭማሪ የምናደርገው የተባበረ ጥረት ስላስገኘው ውጤት መተረክ እጅግ ያስደስታል።
ትጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች
የቤቴል ቤተሰባችን በመንፈሳዊ በጣም ሃብታም ነው። ምክንያቱም አባላቱ ለመጽሐፍ ቅዱስ ከፍተኛ ፍቅር አላቸው። መጀመሪያ ቤቴል ስመጣ በማጣሪያ ንባብ (proofreading) ሥራ ታገለግል የነበረችውን ኤማ ሃሚልተንን መጽሐፍ ቅዱስን ምን ያህል ጊዜ እንዳነበበች ጠየቅኋት። “ሠላሳ አምስት ጊዜ” በማለት መለሰች። “ከዚያ በኋላ ግን መቁጠሬን አቆምኩ።” በዚሁ ጊዜ በቤቴል ያገለግል የነበረው መንፈሰ ጠንካራው አንቶን ኮርበር “መጽሐፍ ቅዱስን ከዓይናችሁ አታርቁት” ማለትን ያዘወትር ነበር።
ወንድም ራስል በ1916 ሲሞት ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ራስል ተሸክሞት የነበረውን ድርጅታዊ ኃላፊነት ተረከበ። ራዘርፎርድ ሃይለኛና የተዋጣለት የሕዝብ ተናጋሪ የነበረ ሲሆን በዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት የይሖዋ ምሥክሮችን ወክሎ በጠበቃነት ተሟግቷል። ራዘርፎርድ በ1942 ሲሞት ወንድም ኖር በቦታው ተተካ። ኖር የሕዝብ ተናጋሪነት ችሎታውን ለማሻሻል ጠንክሮ ሠርቷል። የመኝታ ክፍሌ ከእርሱ መኝታ ክፍል አጠገብ ስለነበር አብዛኛውን ጊዜ ንግግሮቹን ደጋግሞ ሲለማመድ እሰማው ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ ትጋት የተሞላበት ጥረት ጥሩ የሕዝብ ተናጋሪ እንዲሆን አስችሎታል።
ወንድም ኖር የካቲት 1942 ቤቴል ያለነው ወንድሞች የማስተማርና የንግግር ችሎታችንን እንድናሻሽል የሚረዳ ፕሮግራም እንዲወጣ አደረገ። ትምህርት ቤቱ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምርምር በማድረግና ሕዝብ ፊት ወጥቶ ንግግር በመስጠት ላይ ያተኮረ ሲሆን መጀመሪያ ላይ እያንዳንዳችን በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪክ ላይ ያተኮረ አጭር ንግግር እንድንሰጥ ተመደብን። የመጀመሪያው ንግግሬ በሙሴ ላይ ያተኮረ ነበር። በ1943 በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ተመሳሳይ ትምህርት ቤት የተቋቋመ ሲሆን እስከዛሬም ሥራውን ቀጥሏል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማካበትና ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴዎች ማዳበር በቤቴል አሁን ድረስ አጽንኦት የሚሰጠው ነገር ነው።
የካቲት 1943 የጊልያድ የሚስዮናውያን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ተከፈተ። በአሁኑ ጊዜ 111ኛው ክፍል ገና መመረቁ ነው! ተቋቁሞ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከ58 የሚበልጡ ዓመታት ያሳለፈው ይህ ትምህርት ቤት እስካሁን ድረስ ከ7, 000 የሚበልጡ ሚስዮናውያንን አሰልጥኖ ያስመረቀ ሲሆን እነዚህ ሚስዮናውያን በዓለም ዙሪያ በሚገኙ አገሮች ውስጥ በማገልገል ላይ ናቸው። የሚያስገርመው ትምህርት ቤቱ በ1943 ሥራውን ሲጀምር በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከ100, 000 ብዙም አይበልጥም ነበር። አሁን ግን የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ የሚካፈሉ ከ6, 000, 000 በላይ ምሥክሮች ይገኛሉ!
መንፈሳዊ ውርሻዬን ማድነቅ
ጊልያድ ከመቋቋሙ ጥቂት ቀደም ብሎ ከቤቴል የተውጣጣን ሦስት ወንድሞች ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙትን ጉባኤዎች እንድንጎበኝ ተመድበን ነበር። እነዚህን ጉባኤዎች በመንፈሳዊ ለማጠንከር ስንል አንድ ወይም ሁለት ቀን ብሎም ሳምንት ያህል እንቆይ ነበር። የወንድሞች አገልጋይ ተብለን እንጠራ የነበረ ሲሆን ይህ ስያሜ በኋላ የወረዳ አገልጋይ ወይም የወረዳ የበላይ ተመልካች በሚለው ተተክቷል። ይሁን እንጂ ጊልያድ ከተከፈተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ተመልሼ አንዳንድ ኮርሶች እንዳስተምር ተጠየቅሁ። ከ2 እስከ 5 ያሉትን ክፍሎች በቋሚነት ያስተማርኩ ሲሆን ከቋሚዎቹ አስተማሪዎች አንዱን በመተካት 14ኛውን ክፍልም አስተምሬአለሁ። በይሖዋ ድርጅት ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ከሚሰጣቸውና እኔ ራሴ ከነበርኩባቸው ክንውኖች መካከል አንዳንዶቹን ከተማሪዎቹ ጋር መከለሴ መንፈሳዊ ውርሻዬን ይበልጥ እንዳደንቅ አድርጎኛል።
ባለፉት ዓመታት ካገኘኋቸው አስደሳች መብቶች መካከል አንዱ የይሖዋ ሕዝቦች ባደረጓቸው ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው። በ1963 ከ500 ከሚበልጡ ልኡካን ጋር “የዘላለሙ ምሥራች” በተሰኙት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት በዓለም ዙሪያ የተጓዝኩ ሲሆን ከተገኘሁባቸው ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው ሌሎች የአውራጃ ስብሰባዎች መካከል በ1989 ዋርሶ ፖላንድ፣ በ1990 በርሊን ጀርመን እንዲሁም በ1993 ሞስኮ ሩሲያ ውስጥ የተደረጉት ይገኙበታል። በእያንዳንዱ ስብሰባ ላይ በናዚ ወይ በኮሙኒስት አሊያም በሁለቱም አገዛዝ ሥር ይደርስባቸው የነበረውን ስደት ለአሥርተ ዓመታት በጽናት ከተቋቋሙ ውድ ወንድሞችና እህቶች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ አግኝቼአለሁ። እነዚህ ተሞክሮዎች ምንኛ እምነቴን አጠንክረውልኛል!
በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኩት ሕይወት በእርግጥም በበረከት የተሞላ ነው! ያገኘኋቸውን መንፈሳዊ በረከቶች ዘርዝሬ መጨረስ አልችልም። በተጨማሪም ከቁሳዊ ሃብት በተለየ እነዚህን ውድ ነገሮች ለሌሎች ስናካፍል ሃብታችንም የዚያኑ ያህል ይጨምራል። አልፎ አልፎ አንዳንዶች ምነው እውነት ቤት ውስጥ ባላደግን ሲሉ እሰማለሁ። ከአምላክ ድርጅት ውጪ ቢያድጉ ኖሮ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ይበልጥ ያደንቁ እንደነበር ይሰማቸዋል።
ወጣቶች እንዲህ ሲሉ ስሰማ ቅር እሰኛለሁ። ምክንያቱም እንዲህ ሲሉ በሌላ አባባል በይሖዋ መንገድ ተኮትኩቶ ማደግ ጥሩ አይደለም ማለታቸው ነው። ሆኖም ሰዎች በኋለኛው የሕይወት ዘመናቸው እውነትን ሲያገኙ እርግፍ አድርገው መተው የሚኖርባቸውን መጥፎ ልማዶችና የተዛቡ አስተሳሰቦች እስቲ አስቡ። ወላጆቼ ሦስት ልጆቻቸውን በይሖዋ የጽድቅ መንገድ ኮትኩተው በማሳደጋቸው በጣም አመስጋኝ ነኝ። ጆን ሐምሌ 1980 እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። ኤስተር አሁንም ታማኝ ምሥክር ናት።
ከብዙ ታማኝ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜ መለስ ብዬ ስመለከት ልቤ በደስታ ይሞላል። በቤቴል ከ67 የሚበልጡ አስደሳች ዓመታት አሳልፌአለሁ። ያላገባሁ ቢሆንም ብዙ መንፈሳዊ ልጆችና የልጅ ልጆች አሉኝ። ገና ያልተዋወቅኳቸውን የዓለም አቀፉን መንፈሳዊ ቤተሰብ አዳዲስ አባላት ሳስብ ልዩ ደስታ ይሰማኛል። እያንዳንዱ የዚህ ቤተሰብ አባል ውድ ነው። “የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች” የሚሉት ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው!—ምሳሌ 10:22
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የተጠመቅሁት አቅኚ መሆን እንዳለብኝ ከተወሰነ በኋላ ማለትም መጋቢት 8, 1932 ነበር።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከግራ ወደ ቀኝ:- አባቴ ወንድሜን ጆንን ጭኑ ላይ አስቀምጦት፣ ኤስተር፣ እኔና እናቴ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1945 በአንድ የጊልያድ ክፍል ውስጥ ሳስተምር
ከላይ በስተ ቀኝ:- የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪዎች የሆኑት ኤድዋርዶ ኬለር፣ ፍሬድ ፍራንዝ፣ እኔና አልበርት ሽሮደር
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኩትን በበረከት የተሞላ ሕይወት መለስ ብዬ ሳስብ