‘ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል’
ጆርጅ ኮች እንደተናገረው
ጠዋት ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል ከቆየን በኋላ የአገልግሎት ጓደኛዬ ሁለት ሳንድዊቾች አወጣ። በልተን እንደጨረስን ሲጋራ ለማጨስ ከኪሴ አወጣሁ። “እውነትን ከሰማህ ምን ያህል ጊዜ ሆኖሃል?” ሲል ጠየቀኝ። “ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ላይ የተገኘሁት ትላንትና ማታ ነው” አልኩት።
የተወለድኩት መጋቢት 3, 1917 በዩ ኤስ ኤ፣ ፔንሲልቬንያ ከፒትስበርግ በስተ ምሥራቅ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ፣ በትንሿ የአቨንሞር ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ የእርሻ ቦታ ነው። ወላጆቼ እኔን፣ እህቴንና አራት ወንድሞቼን ያሳደጉን በዚህ ቦታ ነው።
ሃይማኖታዊ ትምህርት እምብዛም አላገኘንም። አንድ ወቅት ላይ ወላጆቼ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ የነበረ ቢሆንም መሄድ ያቆሙት ገና ትንንሽ ልጆች እያለን ነው። ይሁን እንጂ በፈጣሪ መኖር ከማመናችንም በላይ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንከተል ነበር።
ወላጆቼ ኃላፊነትን እንዴት መመልከት እንዳለብኝና እንዴት መወጣት እንደምችል እጅግ ጠቃሚ የሆነ ስልጠና ሰጥተውኛል። የግብርና ሕይወት ይህን ይመስል ነበር። ሆኖም ሕይወታችን በሥራ ብቻ የተያዘ አልነበረም። እንደ ቅርጫት ኳስ፣ ቤዝቦል፣ ፈረስ ግልቢያና ዋና በመሳሰሉ ጤናማ መዝናኛዎች እንዝናና ነበር። በዚያን ጊዜ ገንዘብ ማግኘት አስቸጋሪ ቢሆንም የግብርና ሕይወት ግን አስደሳች ነበር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርታችንን የተከታተልነው ባለ አንድ ክፍል ትምህርት ቤት ውስጥ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታችንን የተከታተልነው ደግሞ ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ነው።
አንድ ቀን ምሽት ከጓደኛዬ ጋር በከተማው ውስጥ እየተጓዝን ሳለ አንዲት ቆንጆ ልጃገረድ እሱን ሰላም ለማለት ከቤቷ ወጣች። በዚህ ጊዜ ጓደኛዬ ከልጅቷ ጋር ማለትም ከፈርን ፕሩ ጋር አስተዋወቀኝ። እንዳጋጣሚ ሆኖ የእሷ ቤት እና እኔ የምማርበት ትምህርት ቤት የሚገኘው በአንድ አካባቢ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ በቤቷ በኩል ሳልፍ ፈርን ውጪ ሆና ስትሠራ አያት ነበር። ታታሪ ሠራተኛ መሆንዋ በግልጽ የሚታይ ነበር፤ ይህ ደግሞ ስሜቴን ማረከው። በመካከላችን የጠበቀ ጓደኝነትና ፍቅር ዳብሮ ስለነበር ሚያዝያ 1936 ላይ ተጋባን።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማግኘት
እኔ ከመወለዴ በፊት በከተማው ውስጥ ያሉ ሰዎች በእምነታቸው ምክንያት የሚያንገላቷቸው አንዲት አረጋዊት ሴት ነበሩ። እማዬ ቅዳሜ ቅዳሜ ለገበያ ወደ ከተማ ስትወጣ ትጠይቃቸው የነበረ ከመሆኑም በላይ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ቤታቸውን ታጸዳላቸውና ትላላካቸው ነበር። እማዬ ቀደም ሲል በነበረው አጠራር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለነበሩት ለእኚህ የይሖዋ ምሥክር ደግነት በማሳየቷ ይሖዋ እንደባረካት እርግጠኛ ነኝ።
ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የአክስቴ ልጅ በድንገት ሞተች። አክስቴ ከቤተ ክርስቲያኑ እምብዛም ማጽናኛ ባታገኝም ጎረቤቷ የሆነች አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ግን አጽናንታታለች። ይህች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ምን እንደሚሆን አስረዳቻት። (ኢዮብ 14:13-15፤ መክብብ 9:5, 10) ይህን ስታውቅ በጣም ተጽናናች። አክስቴ ደግሞ በተራዋ ስለ ትንሣኤ ተስፋ ለእናቴ ነገረቻት። እናቴ ወላጆችዋ የሞቱት ልጅ በነበረችበት ጊዜ ስለሆነና አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ምን እንደሚሆን የማወቅ ጉጉት ስለነበራት የሰማችው ነገር ፍላጎትዋን ቀሰቀሰው። ይህ ተሞክሮ ምንጊዜም መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን የመጠቀምን አስፈላጊነት እንድገነዘብ አስችሎኛል።
እማዬ በ1930ዎቹ ዓመታት በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ እሁድ እሁድ ጠዋት ላይ በራዲዮ የሚያሰራጨውን ንግግር ታዳምጥ ጀመር። በእነዚያ ዓመታት ምሥክሮቹ እኛ በምንኖርበት አካባቢም ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ጀመሩ። ይዘውት የሚዘዋወሩትን የሸክላ ማጫወቻ ግቢያችን ውስጥ በሚገኝ በአንድ የዛፍ ጥላ ሥር ያስቀምጡና በሸክላ የተቀረጹትን የወንድም ራዘርፎርድ የስብከት ንግግሮች ያሰሙ ነበር። በእነዚህ ንግግሮች እንዲሁም መጠበቂያ ግንብ እና ወርቃማው ዘመን (አሁን ንቁ!) በሚባሉት መጽሔቶች ሳቢያ የእማዬ ፍላጎት ሕያው ሆኖ ሊቀጥል ችሏል።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1938 የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራት ያላቸው ሁሉ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ገደማ ላይ በሚገኝ አንድ የግል መኖሪያ ቤት ውስጥ በሚደረግ ልዩ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ የግብዣ ወረቀት ተላከላቸው። እናቴ ስብሰባው ላይ መገኘት ስለፈለገች እኔና ፈርን እንዲሁም ሁለት ወንድሞቼ አብረናት ሄድን። የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የሆኑት ጆን ቡዝ እና ቻርለስ ሄስለር ወደ 12 ለምንጠጋ ተሰብሳቢዎች ንግግር አደረጉልን። ስብሰባው እንዳለቀ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ወደ አገልግሎት የሚወጣ ቡድን ማደራጀት ሲጀምሩ ከእነሱ ጋር አገልግሎት ለመውጣት ፈቃደኛ የሚሆን ሰው ታጣ። በዚህ ጊዜ ወንድም ሄስለር “ለምን አብረኸን አትሄድም?” ሲል ጠየቀኝ። ምን እንደሚያደርጉ በትክክል የማውቀው ነገር ባይኖርም እንኳ አብሬአቸው የማልሄድበት ምንም ምክንያት አልነበረኝም።
እኩለ ቀን ድረስ ከቤት ወደ ቤት ካገለገልን በኋላ ወንድም ሄስለር ሁለት ሳንድዊች አወጣ። በአንድ ቤተ ክርስቲያን ደረጃ ላይ ተቀምጠን መብላት ጀመርን። ወንድም ሄስለር ስብሰባ ላይ ስገኝ የመጀመሪያዬ መሆኑን ያወቀው ከኪሴ ሲጋራ ካወጣሁ በኋላ ነበር። በዚያው ቀን ምሽት ከእኛ ጋር ራት እንደሚበላና ጎረቤቶቻችንን ለመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት እንድንጋብዝ ነገረን። ራት በልተን እንደጨረስን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመራልን ሲሆን ተጋብዘው ለመጡ ወደ አሥር ለሚጠጉ ጎረቤቶቻችን ደግሞ ንግግር አቀረበ። በየሳምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረግ እንዳለብን ነገረን። ምንም እንኳ ጎረቤቶቻችን በዚህ ሐሳብ ሳይስማሙ ቢቀሩም እኔና ፈርን ግን ሳምንታዊ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት አደረግን።
በእውነት ውስጥ እድገት ማድረግ
ከዚያ ብዙም ሳንቆይ እኔና ፈርን ወደ መስክ አገልግሎት ወጣን። በመኪናው ኋለኛ ወንበር ላይ ተቀምጠን ሲጋራችንን ስንለኩስ ታላቅ ወንድሜ ዞር ብሎ አየንና “የይሖዋ ምሥክሮች እኮ ሲጋራ አያጨሱም” ብሎ ነገረን። ፈርን ሲጋራውን ወዲያውኑ በመስኮት ወረወረችው፤ እኔ ግን አጭሼ ጨረስኩ። ምንም እንኳ ሲጋራ ማጨስ ያስደስተን የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን በጭራሽ ሲጋራ ነክተን አናውቅም።
በ1940 ከተጠመቅን በኋላ እኔና ፈርን አቅኚነት ተብሎ የሚጠራውን የሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራ የሚያበረታታ ርዕስ በአንድ ስብሰባ ላይ አጥንተን ነበር። ወደ ቤታችን ለመመለስ በጉዞ ላይ ሳለን አንድ ወንድም “አንተና ፈርን አቅኚ እንዳትሆኑ የሚከለክላችሁ ነገር ያለ አይመስለኝም” አለን። የሰጠንን ሐሳብ የማንቀበልበት ምንም ምክንያት ስላልነበረን ለዚህ አገልግሎት ራሳችንን አቀረብን። በ30 ቀናት ውስጥ ሥራ እንደማቆም በመግለጽ ለመሥሪያ ቤቴ የሥራ መልቀቂያ ማመልከቻ አስገባሁና አቅኚነት ለመጀመር ዝግጅት አደረግን።
የት ማገልገል እንዳለብን ለማወቅ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ካማከርን በኋላ በሜሪላንድ ባልቲሞር ለማገልገል ሄድን። እዚያ ለአቅኚዎች መኖሪያ ቤት ተዘጋጅቶ የነበረ ሲሆን ለመኝታና ምግብ ወርኃዊ ክፍያው 10 የአሜሪካ ዶላር ነበር። አርማጌዶን እስኪመጣ ድረስ ያለ ችግር ያሰነብተናል ብለን ያሰብነው ጥቂት ተቀማጭ ገንዘብ ነበረን። (ራእይ 16:14, 16) እንዲያውም አርማጌዶን በጣም ቅርብ እንደሆነ ይሰማን ነበር። ስለዚህ የአቅኚነት አገልግሎት ስንጀምር ቤታችንንም ሆነ ሌላ ሌላውን ነገር ሁሉ እርግፍ አድርገን ተውነው።
ከ1942 እስከ 1947 ድረስ በባልቲሞር በአቅኚነት አገለገልን። በእነዚያ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥመው ነበር። ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን ቤት ስንሄድ አንዳንድ ጊዜ የራሳችንን መኪና ከመጠቀም ይልቅ ሌላ ሰው እንዲያደርሰን እናደርግ ነበር። እንዲህ በማድረግ የመኪና ጎማዎቻችንን እንዳያፈነዱብን መከላከል ችለናል። ማንም ሰው እንዲህ የመሰለው ተቃውሞ እንዲደርስበት እንደማይፈልግ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሁልጊዜ በመስክ አገልግሎት እንደሰት ነበር ማለት እችላለሁ። እንዲያውም ትንሽም ቢሆን ደስታ የሚያስገኝልን የጌታን ሥራ መሥራታችን ነበር።
ብዙም ሳንቆይ ያጠራቀምነው ገንዘብ በሙሉ አለቀ። የመኪና ጎማዎቻችንም ሆኑ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችን አለቁ። ሁለቴ ይሁን ሦስቴ ለረጅም ጊዜያት ታመምን። በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ቀላል ባይሆንም ሥራውን የማቆም ሐሳብ ግን ፈጽሞ ወደ አእምሮአችን መጥቶ አያውቅም። ሌላው ቀርቶ በጉዳዩ ላይ እንኳ ተነጋግረን አናውቅም። በአቅኚነት ሥራ መቀጠል እንድንችል ኑሯችንን ቀላል አደረግን።
የሥራ ምድብ ለውጦች
በ1947 በካሊፎርንያ ሎስ አንጀለስ በሚደረግ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሄድን። እዚያ ሳለን እኔና ወንድሜ ዊልያም ጉባኤዎችን ለመጎብኘትና ለመርዳት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንድናገለግል መመደባችንን የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን። ምንም ዓይነት ልዩ ስልጠና ሳናገኝ አገልግሎቱን በእምነት ጀመርን። በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት እኔና ፈርን በኦሃዮ፣ በሚሺጋን፣ በኢንዲያና፣ በኢሊኖይስ እና በኒው ዮርክ አገለገልን። በ1954፣ ሚስዮናውያንን ለማሰልጠን በተቋቋመው ትምህርት ቤት ማለትም በጊልያድ 24ኛ ክፍል ላይ እንድንገኝ ተጋበዝን። እዚያ ሳለን ፈርን የፖሊዮ በሽታ ያዛት። ደግነቱ በሽታው ሙሉ በሙሉ ስለተዋት በኒው ዮርክና በከኔቲከት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንድናገለግል ተመደብን።
በከኔቲከት ስታምፎርድ እያገለገልን በነበረበት ጊዜ በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ናታን ኤች ኖር ቅዳሜና እሁድን ከእሱና ከባለቤቱ ከኦድሪ ጋር በቤቴል እንድናሳልፍ ጋበዘን። ሌሎች ምግቦችን ጨምሮ ጣፋጭ የሆነ የተጠበሰ ሥጋ አዘጋጅተው ጥሩ ራት ጋበዙን። ከዚህ ቀደም ከእነሱ ጋር ትውውቅ ስለነበረን አብረን ጊዜ ከማሳለፋችንና ራት ከመብላታችን በተጨማሪ ወንድም ኖር ሊነግረኝ የፈለገው ነገር እንዳለ በደንብ አውቄአለሁ። በዚያው ምሽት ትንሽ ቆየት ብሎ “ወደ ቤቴል ብትመጣ ምን ይመስልሃል?” ሲል ጠየቀኝ።
“ስለ ቤቴል ሕይወት ብዙም የማውቀው ነገር ስለሌለ እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም” ስል መለስኩለት።
ለበርካታ ሳምንታት በጉዳዩ ላይ ካሰብንበት በኋላ ለወንድም ኖር እንድንመጣ የሚፈልግ ከሆነ መምጣት እንደምንችል ነገርነው። በቀጣዩ ሳምንት፣ በ21ኛው የጋብቻ በዓላችን ዕለት ማለትም ሚያዝያ 27, 1957 ወደ ቤቴል እንድንመጣ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰን።
ወንድም ኖር ቤቴል በደረስን በመጀመሪያው ቀን ከእኔ የሚጠበቀው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ነገረኝ። እንዲህ አለኝ:- “ካሁን በኋላ የወረዳ አገልጋይ አይደለህም፤ ወደዚህ የመጣኸው በቤቴል እንድታገለግል ነው። ይህ ልታከናውነው የሚገባ በጣም አስፈላጊ ሥራ ነው፤ በመሆኑም ቤቴል ውስጥ የምታገኘውን ስልጠና በመጠቀም ጊዜህንና ጉልበትህን ሥራው ላይ እንድታውል እንፈልጋለን። እዚሁ እንድትሆን እንፈልጋለን።”
ቤቴል ውስጥ ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር
በመጀመሪያ የተመደብኩት በመጽሔት ኮንትራትና በጽሑፍ መላኪያ ክፍሎች ነበር። ከዚያም ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ ወንድም ኖር ወደ ቢሮው ጠራኝና ወደ ቤቴል የተጠራሁበት ዋናው ምክንያት የቤቴል ቤቶችን እንዳስተዳድር መሆኑን ነገረኝ። “እዚህ የመጣኸው የቤቴል ቤቶችን እንድታስተዳድር ነው” ሲል ግልጽ መመሪያ ሰጠኝ።
የቤቴል ቤቶችን የማስተዳደሩ ሥራ በልጅነቴ በግብርና ሕይወት ውስጥ ሳለሁ ወላጆቼ የሰጡኝን ስልጠናዎች እንዳስታውስ አድርጎኛል። የቤቴል ሕይወት ከተለመደው የቤተሰብ ኑሮ ጋር በጣም ይመሳሰላል። ልብስ ማጠብ፣ ምግብ ማብሰል፣ ዕቃ ማጠብ፣ አልጋ ማንጠፍና እነዚህን የመሳሰሉ ሌሎች ሥራዎችም ይከናወናሉ። የቤቴል ቤቶች ቢሮ አንድ ሰው በቤቱ እንዳለ እንዲሰማው ለማስቻል ቤቴልን ተስማሚ የመኖሪያ ቦታ ለማድረግ ይጥራል።
በቤቴል ውስጥ ሥራው እንዴት እንደሚከናወን በማየት ቤተሰቦች ብዙ ትምህርት ሊያገኙ የሚችሉ ይመስለኛል። ጠዋት በማለዳ እንነሳና በዕለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ውይይት በማድረግ ቀኑን በመንፈሳዊ ነገሮች እንጀምራለን። ትጉ ሠራተኞች እንድንሆን የሚጠበቅብን ከመሆኑም በላይ ሕይወታችን ሚዛናዊ ሆኖም በሥራ የተያዘ ነው። አንዳንዶች እንደሚመስላቸው ቤቴል ገዳም አይደለም። ሕይወታችን በፕሮግራም ስለሚመራ ብዙ ሥራ እናከናውናለን። ብዙዎች እዚህ ያገኙት ስልጠና ከጊዜ በኋላ በቤተሰባቸው ውስጥም ሆነ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ኃላፊነቶችን ለመቀበል እንደረዳቸው ተናግረዋል።
ወደ ቤቴል የሚመጡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች በጽዳት፣ በልብስ ንጽሕና ወይም ፋብሪካ ውስጥ እንዲሠሩ ሊመደቡ ይችላሉ። ያለንበት ዓለም ይህ ዓይነቱ የጉልበት ሥራ የሚያዋርድና ክብራችንን የሚነካ እንደሆነ አድርጎ ሊያሳምነን ይፈልጋል። ሆኖም በቤቴል ያሉ ወጣቶች የቤቴል ቤተሰብ በሥርዓትና በደስታ መሥራት እንዲችል እነዚህ ሥራዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ይገነዘባሉ።
ይህ ዓለም አንድ ሰው እውነተኛ ደስታ እንዲያገኝ ሥልጣንና ታዋቂነት ሊኖረው ይገባል የሚለውንም ሐሳብ ያራምዳል። ይህ ትክክለኛ አስተሳሰብ አይደለም። የተሰጠንን ሥራ ስናከናውን ‘ልናደርገው የሚገባንን ሥራ እየሠራን’ ከመሆናችንም በላይ የይሖዋንም በረከት ያስገኝልናል። (ሉቃስ 17:10) እውነተኛ እርካታና ደስታ ማግኘት የምንችለው የሥራችን ዓላማ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸምና የመንግሥቱን ጉዳዮች ማራመድ መሆኑን የምናስታውስ ከሆነ ነው። ይህን ካስታወስን ማንኛውም ሥራ አስደሳችና አርኪ ሊሆንልን ይችላል።
በመስፋፋቱ ሥራ ተሳትፎ የማድረግ መብት
ወደ ቤቴል ከመምጣታችን ከአሥር ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በ1942 በኦሃዮ ክሌቭላንድ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ወንድም ኖር “ሰላም—ዘላቂ ሊሆን ይችላልን?” የሚል ንግግር ሰጥቶ ነበር። በወቅቱ እየተካሄደ የነበረው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንደሚያቆምና የስብከቱን ሥራ በሰፊው ለመሥራት የሚያስችል ሰላማዊ ጊዜ እንደሚኖር በግልጽ አብራራ። በ1943 ሚስዮናውያንን ለማሰልጠን የጊልያድ ትምህርት ቤት እንዲሁም ወንድሞች በሕዝብ ፊት የመናገር ችሎታቸውን ማሻሻል እንዲችሉ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተቋቋመ። ትልልቅ የአውራጃ ስብሰባዎችም ተደርገዋል። በተለይ ደግሞ በ1950ዎቹ ውስጥ በኒው ዮርክ ያንኪ ስታድየም የተደረጉት ስብሰባዎች በዓይነታቸው ልዩ ነበሩ። በ1950 እና በ1953 በዚያ ከተደረጉት ስብሰባዎች ጋር በተያያዘ ለስምንት ቀን በተካሄዱት በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ የተገኙ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች የሚያርፉበትን በተንቀሳቃሽ ቤቶችና ድንኳኖች የተሠራ ትልቅ ጊዜያዊ ከተማ በማደራጀቱ ሥራ የመሳተፍ መብት አግኝቼ ነበር።
በ1958 የተደረገውን በትልቅነቱ አቻ ያልተገኘለትን የአውራጃ ስብሰባ ጨምሮ እነዚህ ስብሰባዎች ከተደረጉ በኋላ በመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ረገድ ከፍተኛ ጭማሪዎች ታይተዋል። ይህ ጭማሪ በቤቴል በምንሠራው ሥራ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ነበረው። በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተጨማሪ ሠራተኞችን ለመቀበል ቦታና ተጨማሪ ክፍሎች ማግኘት የግድ አስፈላጊ ሆኖ ነበር። እያደገ ላለው የቤቴል ቤተሰብ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማሟላት ተጨማሪ የመኝታ ክፍሎች፣ ወጥ ቤቶችና የመመገቢያ ክፍሎች ማግኘት ግድ ሆኖብን ነበር።
ወንድም ኖር እኔና የፋብሪካ የበላይ ተመልካች የሆነው ማክስ ላርሰን ተጨማሪ ሕንፃዎች ለመሥራት የሚያስችል አመቺ ቦታ እንድንፈልግ ነገረን። በ1957 ወደ ቤቴል ስመጣ ወደ 500 የሚጠጋው ቤተሰባችን በአንድ ትልቅ የመኖሪያ ሕንፃ ላይ ይኖር ነበር። ሆኖም ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ማኅበሩ በአቅራያቢው የነበሩትን የታወርስ፣ የስታንዲሽ እና የቦሰርት ሆቴሎች ገዝቶ ያደሰ ሲሆን ሌሎች በርካታ አነስተኛ የአፓርተማ ሕንፃዎችንም ገዝቷል። በ1986 ማኅበሩ የማርጋሬት ሆቴል የተገነባበትን መሬት ገዛና ቦታው ላይ የነበረውን አዲስ የሚያምር ሕንፃ ወደ 250 ለሚጠጉ ሰዎች መኖሪያ እንዲሆን አደረገ። ከዚያም በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተጨማሪ 1,000 ሠራተኞች መያዝ የሚችል ባለ 30 ፎቅ የመኖሪያ ሕንፃ ተገነባ። በአሁኑ ጊዜ ብሩክሊን ቤቴል ከ3,300 በላይ ለሚሆኑት የቤተሰባችን አባላት የመኖሪያና የምግብ አቅርቦትን ማሟላት ችሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ከብሩክሊን ቤቴል 160 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በኒው ዮርክ ዎልኪል የሚገኝ አንድ ቦታ ተገዛ። ከ1960ዎቹ ማብቂያ አንስቶ በነበሩት ዓመታት በዚህ ቦታ ላይ የመኖሪያ ሕንፃዎችና አንድ ትልቅ የማተሚያ ሕንፃ ተገንብቷል። በአሁኑ ጊዜ ወደ 1,200 የሚጠጉ የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሚኖሩትና የሚሠሩት እዚህ ቦታ ላይ ነው። በ1980 በኒው ዮርክ ከተማ አቅራቢያ ከአውራ ጎዳና ብዙም ያልራቀ ወደ 250 ሄክታር መሬት የሚጠጋ ቦታ ለማግኘት ፍለጋ ተጀመረ። የመሬት አሻሻጩ ወኪል ሳቀብንና “ለመሆኑ እንዲህ ዓይነት ቦታ የምታገኙ ይመስላችኋል? ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው” አለን። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ቀን ጠዋት ስልክ ደውሎ “የምትፈልጉትን ዓይነት ቦታ አግኝቻለሁ” አለን። በዛሬው ጊዜ በኒው ዮርክ ፓተርሰን የሚገኘው ይህ ቦታ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል በሚል ስያሜ ይታወቃል። በዚህ ቦታ ላይ የተለያዩ ትምህርቶች የሚሰጡ ሲሆን ከ1,300 የሚበልጡ አገልጋዮችን ያቀፈ ቤተሰብም አለ።
ያገኘኋቸው ትምህርቶች
አንድ ሰው የተዋጣለት የበላይ ተመልካች ሊሆን የሚችለው ከሌሎች ጠቃሚ ሐሳቦችን የሚቀበል ከሆነ ነው። የቤቴል ቤቶች የበላይ ተመልካች ሆኜ በማገልገል ባገኘሁት መብት በሥራ ላይ እንዲውሉ ያደረግኳቸው አብዛኞቹ ሐሳቦች ከሌሎች የመነጩ ነበሩ።
ወደ ቤቴል ስመጣ ብዙዎቹ በዕድሜ ገፍተው ነበር፤ ዛሬ አብዛኞቹ ሞተዋል። በአሁኑ ጊዜ እኔም ዕድሜዬ ገፍቷል። ዕድሜያቸው ገፍቶ የሚሞቱትን የሚተካቸው ማን ነው? አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ችሎታ ያላቸው አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ራሳቸውን አቅርበው ሥራውን በታማኝነት የሚያከናውኑት ናቸው።
መታወስ ያለበት ሌላው አስፈላጊ ነገር ልባም ሚስት ያላት ጠቀሜታ ነው። ውዷ ባለቤቴ ፈርን የምትሰጠኝ ድጋፍ ቲኦክራሲያዊ ሥራዎቼን በሚገባ ማከናወን እንድችል በእጅጉ ረድቶኛል። ባሎች፣ ሚስቶቻቸው በተሰጧቸው ምድብ ሥራዎች ይደሰቱ እንደሆነ የማረጋገጥ ኃላፊነት አለባቸው። እኔና ፈርን የምንደሰትበትን ነገር በማድረግ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እንድንችል አንድ ነገር አስቀድሜ ለማዘጋጀት ጥረት አደርጋለሁ። የግድ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ነገር መሆን የለበትም፤ ዘወትር ከምናደርገው ነገር ለየት ያለ መሆኑ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። አንድ ባል ሚስቱን ለማስደሰት አንዳንድ ነገሮች የማድረግ ኃላፊነት አለበት። ከእሷ ጋር የሚያሳልፈው ጊዜ ውድ ከመሆኑም በላይ በቶሎ ያልፋል። ይህም በመሆኑ ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልገዋል።
ኢየሱስ በተናገረለት በመጨረሻው ቀን ውስጥ በመኖሬ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል። ያለንበት ዘመን የሰው ልጅ ካሳለፋቸው የታሪክ ዘመናት ሁሉ ይበልጥ አስገራሚ የሆነ ጊዜ ነው። ጌታ ቃል ለተገባው አዲስ ዓለም ዋዜማ ዝግጅት ድርጅቱን እንዴት እያሳደገው እንዳለ በእምነት ዓይናችን ለማየት ችለናል። በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኩትን የሕይወት ዘመን መለስ ብዬ ስመለከት ድርጅቱን የሚመራው ይሖዋ እንጂ ሰው አለመሆኑን መገንዘብ ችያለሁ። እኛ የእሱ ተራ አገልጋዮች ስለሆንን ምንጊዜም አመራሩን ለማግኘት መጣር አለብን። ምን ማድረግ እንዳለብን ሲጠቁመን በፍጥነት መታዘዝና ተባብረን መሥራት ይኖርብናል።
ከድርጅቱ ጋር ሙሉ በሙሉ ከተባበራችሁ የተሟላና አስደሳች ሕይወት እንደምታገኙ ጥርጥር የለውም። አቅኚ፣ የወረዳ የበላይ ተመልካች፣ የጉባኤ አስፋፊ፣ የቤቴል አገልጋይም ሆናችሁ ሚስዮናዊ የሚሰጣችሁን መመሪያ ተከተሉ እንዲሁም ምድብ ሥራችሁን ከፍ አድርጋችሁ ተመልከቱት። በእያንዳንዱ ምድብ ሥራና በይሖዋ አገልግሎት በምታሳልፉት በእያንዳንዱ የሥራ ቀን ደስተኛ ለመሆን የተቻላችሁን አድርጉ። አንዳንድ ጊዜ ሊደክማችሁ ሥራ ሊበዛባችሁ ወይም ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊሰማችሁ ይችላል። ሕይወታችሁን ለይሖዋ የወሰናችሁበትን ዓላማ ማስታወስ የሚኖርባችሁ በዚህ ጊዜ ነው። ሕይወታችሁን የወሰናችሁት የእሱን እንጂ የራሳችሁን ፈቃድ ለማድረግ አይደለም።
ሥራ ላይ ውዬ ባከናወንኩት ሥራ እርካታ ያላገኘሁበት አንድም ቀን የለም። ለምን? ምክንያቱም በሙሉ ነፍሳችን ራሳችንን ለይሖዋ ስናቀርብ ‘ልናደርገው የሚገባንን እንዳደረግን’ በማወቃችን እርካታ እናገኛለን።
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1946 በባልቲሞር በአቅኚነት ሳገለግል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1950 በጊዜያዊው ከተማ ውስጥ ከፈርን ጋር ሆነን
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሔት ክፍል
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1950 የነበረው ጊዜያዊ ከተማ
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል ]
ከኦድሪ እና ከናታን ኖር ጋር ሆነን
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኒው ዮርክ ፓተርሰን የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሁኑ ጊዜ ከፈርን ጋር