የይሖዋ ምሥክሮች አዘውትረው ከቤት ወደ ቤት የሚሄዱት ለምንድን ነው?
‘ዛሬም እንደገና መጡ! ከጥቂት ሳምንታት በፊት እኮ መጥተው ነበር!’ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ወደ ቤትዎ ሲመጣ የሚሰማዎት እንዲህ ነውን? በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ቤታቸው ሄደው ያነጋግራሉ። አብዛኞቹ ሰዎች የራሳቸው ሃይማኖት ያላቸው መሆኑን ወይም ለመስማት ፍላጎት እንደሌላቸው እያወቁ ከቤት ወደ ቤት ከመሄድ ወደኋላ ያላሉት ለምንድን ነው? ብለው ይጠይቁ ይሆናል። ይህ መልስ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው።
በአምላክ ፊት ተጠያቂ ናቸው
የይሖዋ ምሥክሮች የአሁኑን ዓለም የነገሮች ሥርዓት መደምደሚያና መላዋን ምድር የሚገዛውን መጪውን የአምላክ ንጉሣዊ አገዛዝ አስመልክቶ የተነገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አንደኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረበት ከ1914 አንስቶ ሲፈጸሙ የቆዩ መሆናቸውን ከቅዱሳን ጽሑፎች ተረድተዋል። ለአንድ መቶ ዘመን ያህል ከተፈጸመው ዓመፅ፣ ደም መፋሰስና ጥላቻ አንፃር ሲታይ የሰው ልጆች ለችግሮቻቸው ፖለቲካዊ መፍትሔ የማግኘታቸው ዕድል ፈጽሞ የጨለመ ይመስላል። አሁንም የሰውን ልጅ እያጠቁ ያሉት ጦርነቶችና በየጊዜው የሚታዩት የሽብር ፈጠራ ድርጊቶች የሰው አገዛዝ የሰዎችን ልብ፣ አስተሳሰብና ዝንባሌ መለወጥ ያልቻለ መሆኑን ይመሠክራሉ። ባለፉት የታሪክ ዘመናት በተፈጸሙ በደሎች ሳቢያ ሰዎች ያደረባቸው ኃይለኛ ቁጭት የልዩ ልዩ ጎሣዎችን፣ ዘሮችንና የተለያዩ ሃይማኖት ተከታዮችን የሚያበጣብጥ መርዝ ሆኗል። ይህ እንደ ህንድ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ሰሜን አየር ላንድ፣ አፍጋኒስታን፣ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያና ደቡብ አፍሪካ ባሉት የተራራቁ አካባቢዎች አሁንም ያለ ችግር ነው። ታዲያ ለዚህ ብቸኛና ዘላቂ መፍትሔው ምን ይሆን?
ምሥክሮቹን የሚያነሣሣቸው ምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች ሊሠራ የሚችለው ብቸኛው መፍትሔ አምላክ የሚያመጣው መፍትሔ ማለትም በክርስቶስ ኢየሱስ የሚመራው ንጉሣዊ አገዛዝ መሆኑን ተገንዝበዋል። ኢየሱስ ባስተማረው ዝነኛ የሞዴል ጸሎት ላይም “እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ፦ በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በማለት ይህ አገዛዝ እንዲመጣ መለመን ያለብን መሆኑን አሳይቷል። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ጸሎት ማቅረብ ማለት አምላክ በሰው ልጆች ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅ ማለት መሆኑን ያምናሉ።—ማቴዎስ 6:9, 10
ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች አዘውትረው ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ይህን መልእክት ለሰዎች ለማድረስ መጣር እንዳለባቸው የሚሰማቸው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ጎላ አድርጎ በገለጻቸው በሚከተሉት ሁለት ትእዛዞች ምክንያት ነው፦ “ጌታ [ይሖዋ አዓት] አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፣ እርስዋም፦ ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።”—ማቴዎስ 22:37–39
ምሥክሮቹ የአምላክን በረከት ለማግኘት ይፈልጋሉ። ሰውን ሁሉ ስለሚወዱ ሌሎች ሰዎችም ጭምር የአምላክን በረከት እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ሰዎችን ቤታቸው ድረስ በመሄድ እንዲያነጋግሯቸው ራስ ወዳድነት የሌለው ፍቅር ግድ ይላቸዋል። ቢያንስ ቢያንስ “ደስተኛው አምላክ” ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች በጸዳች ምድር ላይ ለማምጣት ስለገባው የተስፋ ቃል ጎረቤቶቻቸው የማወቅ አጋጣሚ እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ።—1 ጢሞቴዎስ 1:11 አዓት፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
ክርስቲያኑ ሚስዮናዊ ጳውሎስ አምላክ በሰጠው ተስፋ ያምን ስለነበር እንዲህ ብሎ ጻፈ፦ “የእግዚአብሔር ባሪያና የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ፣ ለተመረጡት እምነት እንዲሆንላቸው በዘላለምም ሕይወት ተስፋ እንደ አምልኮት ያለውን እውነት እንዲያውቁ የተላከ፤ ስለዚህም ሕይወት የማይዋሽ እግዚአብሔር ከዘላለም ዘመናት በፊት ተስፋ ሰጠ።” አዎን፣ ‘የማይዋሸው’ አምላክ እርሱን ለማወቅና ለማገልገል ለሚፈልጉ ትሑት ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ ‘ተስፋ ሰጥቷል።’—ቲቶ 1:1, 2፤ ሶፎንያስ 2:3
የይሖዋ ምሥክሮች ገንዘብ ይከፈላቸዋል?
አልፎ አልፎ አንዳንድ ሰዎች ምሥክሮቹ ለሚያከናውኑት አገልግሎት ገንዘብ ይከፈላቸዋል ይላሉ። ይህ ፈጽሞ ከእውነት የራቀ አባባል ነው! የይሖዋ ምሥክሮች ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለሚገኘው ጉባኤ በላከው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ሲል የጻፋቸውን ቃላት አክብደው ይመለከታሉ፦ “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።”—2 ቆሮንቶስ 2:17
አንዳንድ የሃይማኖት መሪዎች ገንዘብ እየተከፈላቸው ይሰብካሉ። ለሚሰጡት ሃይማኖታዊ አገልግሎትም ይሁን በቴሌቪዥን የስብከት ፕሮግራም ላይ የንግድ ድርጅቶችን የሚያራምድ አገልግሎት ስለመስጠታቸው ገንዘብ ይከፈላቸዋል። ያብዛኞቹ ሃይማኖቶች ቀሳውስት ደሞዝ የሚከፈላቸው ናቸው።በአንጻሩ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ደሞዝ የሚከፈላቸው ቄሶች የሏቸውም። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት እንዲረዱ ታስቦ የተዘጋጁት ጽሑፎቻቸውንም እውነትን በቅንነት ለሚፈልጉ ሰዎች ብዙውን ጊዜ በነፃ ያበረክታሉ። ከእነዚህም ብዙዎቹ በፈቃደኝነት መዋጮ ለማድረግ ከልባቸው ይገፋፋሉ። በፈቃዳቸው አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ከእነዚህ ሰዎች የሚዋጣው ገንዘብ በምድር ዙሪያ የሚደረገውን የስብከት ሥራ ለማካሄድ የሚወጣውን ወጭ ይችላል። ምሥክሮቹ “በነፃ የተቀበላችሁትን በነፃ ስጡ” ከሚለው የኢየሱስ ምክር ጋር በመስማማት ጊዜያቸውና ጉልበታቸውን ጨምሮ ያላቸውን ሀብት በየዓመቱ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዓታት አምላክን ለማገልገል ይጠቀሙበታል። ስለዚህ ከቤት ወደ ቤት በመሄድና የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በመምራት ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ያስተምራሉ።—ማቴዎስ 10:8 የ1980 ትርጉም፤ 28:19, 20፤ ሥራ 20:19, 20
እውነታው እንደሚያረጋግጠው የይሖዋ ምሥክሮች ለግላቸው፣ ለጉባኤያቸው ወይም ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ገንዘብ የመሰብሰብ ዓላማ የላቸውም። ማንም የይሖዋ ምሥክር ከቤት ወደ ቤት እየሄደ በመመሥከሩ ገንዘብ አይከፈለውም። ታዲያ ሥራው የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው እንዴት ነው? በዓለም ዙሪያ ያሉ አድናቂ ሰዎች በፈቃዳቸው በሚያደርጉት መዋጮ ነው። ሙዳዬ ምጽዋት በማዞር የእርዳታ ገንዘብ አይሰበሰብም።
ምሥክርነታቸው በሰዎች አእምሮ ውስጥ ተተክሏል
ምሥክሮቹ ከቤት ወደ ቤት የሚያደርጉት አገልግሎትና መደበኛ ያልሆነ ስብከት በሰዎች አእምሮ ውስጥ የተተከለ ሆኗልን? በመገናኛ ብዙኃን የሚስተጋባው ነገር አዎን፣ በማለት ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል። በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በፊልሞች ላይ በር የሚያንኳኳ ሰው ከታየ የይሖዋ ምሥክሮች ይጠቀሳሉ። የካርቱን ሥዕሎችም ምሥክሮቹን ይጠቅሳሉ። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ሥራ በዓለም ዙሪያ የካርቱን ሥዕል አዘጋጂዎች የይሖዋ ምሥክሮችን እስኪጠቅሱ ድረስ በጣም የታወቀ ሆኗል። በካርቱን ሥዕሎች ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የቀረቡት በቀልድ መልክ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ምሥክሮቹ ከቤት ወደ ቤት በሚያደርጉት ስብከት መጽናታቸውን በሚያሳይ አዎንታዊ በሆነ መሠረታዊ ሐቅ ላይ የተመሠረቱ ናቸው።—ሥራ 20:20
በቅረቡ በወጣ መጽሔት ላይ በቀረበ የካርቱን ሥዕል ውስጥ አንድ ሰው በተራራ የሚኖር አንድን “ጉሩ” ለመጠየቅ ወደ ተራራ ይወጣል።a ሰውዬው ጉሩውን “ወደፊት ስለሚሆኑ ግሩም ነገሮች ንገረኝ!” ይለዋል። “ጉሩው” ምን መልስ ሰጠው? “እሺ . . . ረሃብ፣ ቸነፈርና የምድር መናወጥ በልዩ ልዩ ስፍራ ይሆናል። ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።” ሊጠይቅ የሄደው ሰውዬም “ታዲያ ይሄ ምሥራች የሆነው እንዴት ነው?” ይለዋል። “ጉሩውም” ቀበል አድርጎ “አምላክ እንባዎችን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል። . . . ሞትም ወይም ኀዘን ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም!” ይለዋል። ሊጠይቅ የሄደው ሰው “ስለ እነዚህ ነገሮች እንዴት ልታውቅ ቻልክ?” ብሎ ይጠይቀዋል። የሰጠው መልስ “ከይሖዋ ምሥክሮች የሚያመልጥ ማን አለ?” የሚል ነበር። የካርቱን ሥዕል አዘጋጂው ራሱ የይሖዋ ምሥክሮች አግኝተው አነጋግረውት መሆን አለበት!
ይህ የካርቱን ቀልድና ሌሎችም የሚገልጹት ዋናው ቁም ነገር የይሖዋ ምሥክሮች ሳያሰልሱ ከቤት ወደ ቤት የሚሄዱ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን መልእክታቸው አንድ ዓይነት መሆኑንም ጭምር ነው። የካርቱን ቀልድ አዘጋጂው የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት የሚያደርጉትን ምሥክርነትና ከሚጠቅሷቸው ጥቅሶች ቁልፍ የሆኑትን እጥር ምጥን ባሉ ቃላት ጠቅሷል።—ከማቴዎስ 24:7, 29ና ከራእይ 21:3, 4 ጋር አወዳድር።
አብዛኞቹ ሰዎች መልእክቱን አለመቀበላቸው ምሥክሮቹን ተስፋ አያስቆርጣቸውም፤ ወይም ቅንዓታቸውን አይቀንስባቸውም። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፦ “በመጨረሻው ዘመን እንደ ራሳቸው ምኞት የሚመላለሱ ዘባቾች በመዘበት እንዲመጡ ይህን በፊት እወቁ፤ እነርሱም፦ የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ፣ ከፍጥረት መጀመሪያ ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራልና ይላሉ።” ምሥክሮቹ ይህ ዓይነቱ መዘባበት ቢደርስባቸውም በፍቅር ተገፋፍተው አምላክ የዚህን ብልሹ ዓለም ፍጻሜ እስኪያመጣ ድረስ ቤታቸው ድረስ እየሄዱ ለጎረቤቶቻቸው መስበካቸውን ይቀጥላሉ።—2 ጴጥሮስ 3:3, 4
ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን አስቀድሞ ምሥራቹ ይሰበክ ዘንድ ይገባል ብሏል። ምሥራቹ መሰበክ ያለበት ለምን እንደሆነና እንዴት እንደሚሰበክ ተጨማሪ ምርምር ለማድረግ ቀጥሎ የሚቀርቡትን ሁለት ርዕሶች ይመልከቱ።—ማርቆስ 13:10
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “ጉሩ” በሂንዱ ሃይማኖት እንደ ሃይማኖታዊ መሪና አስተማሪ ተደርጎ የሚታይ ሰው ነው።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ደሞዝ የሚከፈላቸው ቄሶች የሏቸውም—ሁሉም በፈቃዳቸው በነፃ የሚያገለግሉ ናቸው