ሳይንስ፣ ሃይማኖትና እውነትን ለማግኘት የተደረገው ፍለጋ
“ብዙ የሐሰት ሃይማኖቶች መሰራጨታቸው . . . በመጠኑ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል።”—ቻርልስ ዳርዊን
በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሳይንስና ሃይማኖት ተስማምተው ጎን ለጎን ይጓዙ ነበር። “ሌላው ቀርቶ በሳይንሳዊ መጣጥፎች ላይ እንኳ” ይላል ዳርዊን፦ ቢፎር ኤንድ አፍተር የተባለው መጽሐፍ “ጸሐፊዎች ትክክለኛና እውነት እንደሆነ አድርገው በማሰብ ስለ አምላክ ለመናገር ምንም አያቅማሙም ነበር።”
ኦሪጅንስ ኦቭ ስፒሽስ የተባለው የዳርዊን መጽሐፍ ይህ ሁኔታ እንዲለወጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል። ሳይንስና ዝግመተ ለውጥ ሃይማኖትንና አምላክን ገሸሽ ያደረገ ቁርኝት ፈጠሩ። “በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ውስጥ” አሉ ሰር ጁሊያን ሃክስሌይ “የመለኮታዊ ኃይል መኖር አስፈላጊ አይደለም ወይም ቦታ የለውም።”
በዛሬው ጊዜ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ የሳይንስ የማዕዘን ድንጋይ ነው ይባልለታል። በመካከላቸው ላለው ዝምድና ቁልፍ የሆነውን ምክንያት የፊዚክስ ምሁር የሆኑት ፍሬድ ሆይል ለይተው ጠቅሰውታል፦ “ነባሩን አስተሳሰብ የሙጥኝ ብለው የያዙ ሳይንቲስቶች እውነትን ከመፈለግ ይልቅ ይበልጥ ያሳሰባቸው ነገር ቀደም ሲል የነበሩት የተጋነኑ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ተመልሰው እንዳይመጡ የመከላከሉ ጉዳይ ነው።” ሳይንስ ሃይማኖትን እንዲጠላ ያደረጉት ምን ዓይነት የተጋነኑ አመለካከቶች ናቸው?
ሃይማኖት የፍጥረት ዘገባ መጥፎ ስም እንዲሰጠው አድርጓል
መጽሐፍ ቅዱስን ለመደገፍ ተብሎ የፍጥረት አማኞቹ በተለይም ከአክራሪ ፕሮቴስታንቶች ጋር የተቆራኙት ምድርና አጽናፈ ዓለም ያላቸው ዕድሜ ከ10,000 ዓመታት ያነሰ ነው በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ። ይህ የተጋነነ አመለካከት የከርሰ ምድር ጥናት ተመራማሪዎች፣ የጠፈር ተመራማሪዎችና የፊዚክስ ምሁራን ከደረሱባቸው ግኝቶች ጋር ስለሚጋጭ መዘባበቻ ሆኗል።
መጽሐፍ ቅዱስ የሚለው ግን ምንድን ነው? “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።” (ዘፍጥረት 1:1) ምን ያህል ጊዜ እንደወሰደ የተገለጸ ነገር የለም። እንዲያውም የፍጥረት ‘የመጀመሪያ ቀን’ እስከ ዘፍጥረት 1:3–5 ድረስ እንኳ ገና አልተጠቀሰም። ይህ መጀመሪያ “ቀን” ከመጀመሩ በፊት “ሰማይና ምድር” ነበሩ። እንግዲያው ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ሰማያትና ምድር በቢልዮን የሚቆጠሩ ዓመታት ዕድሜ ሊኖራቸው ይችላልን? ሊኖራቸው ይችላል። ሰማይና ምድር ምን ያህል ጊዜ እንዳለፋቸው መጽሐፍ ቅዱስ አይገልጽም።
ሌላው የተጋነነ የሃይማኖት አመለካከት አንዳንዶች ስድስቱን የፍጥረት ‘ቀናት’ የሚተረጉሙበት መንገድ ነው። አንዳንድ አክራሪ አማኞች በምድር ላይ የተከናወነው የፍጥረት ሥራ ቃል በቃል 144 ሰዓታትን ብቻ የፈጀ ነው ብለው ይከራከራሉ። ሳይንቲስቶች ይህ አባባል ጉልህ ከሆኑ ሳይንሳዊ ሐቆች ጋር እንደሚጋጭ ስለሚሰማቸው አይዋጥላቸውም።
ይሁን እንጂ ይህ ከሳይንስ ጋር ያልተጣጣመው የመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር ሳይሆን የአክራሪ አማኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ የፍጥረት “ቀን” የ24 ሰዓታት የጊዜ ርዝመት አለው አይልም። እንደ እውነቱ ከሆነ “እግዚአብሔር አምላክ ሰማይንና ምድርን” የፈጠረበት ቀን እነዚህን ሁሉ ‘ቀናት’ ያካተተ ነበር። ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱት ‘ቀናት’ ሁሉ ባለ 24 ሰዓታት ‘ቀናት’ ናቸው ማለት እንዳልሆነ ያሳያል። (ዘፍጥረት 2:4) አንዳንዶቹ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት ርዝማኔ ሊኖራቸው ይችላል።a
በመሆኑም ሕያዋን ነገሮች የተገኙት በፍጥረት ነው የሚለው ሐሳብ በአክራሪ አማኞች የተነሣ መጥፎ ስም ተሰጥቶታል። ስለ አጽናፈ ዓለም ዕድሜና ስለ ፍጥረት ‘ቀናት’ የሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ምክንያታዊ ከሆነ ሳይንስም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይስማሙም። ይሁን እንጂ ሳይንቲስቶች ሃይማኖትን እንዲጠሉ ያደረጓቸው ሌሎች የተጋነኑ አመለካከቶችም አሉ።
ሥልጣንን ዋቢ በማድረግ የተፈጸመ በደል
በታሪክ ዘመናት ሁሉ ለደረሰው ይህ ነው የማይባል የፍትሕ መጓደል ሃይማኖት ተጠያቂ ነው። ለምሳሌ ያህል በመካከለኛው መቶ ዘመን የፍጥረት መሠረተ ትምህርት ቤተ ክርስቲያን ለአውሮፓ ንጉሣዊ አገዛዝ የምትሰጠው ድጋፍ ትክክል ነው ለማለት በሚያስችል መልኩ በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሞ ነበር። በተዘዋዋሪ ይህ ማለት ሰዎች ሀብታምም ይሁኑ ድሆች በኅብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን የኑሮ ደረጃ እንዲይዙ የተደረገው በመለኮታዊ ውሳኔ ነው ማለት ነው። ዘ ኢንተለጀንት ዩኒቨርስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ሲል ይገልጻል፦ “ታናናሽ የሆኑ የሀብታም ልጆች ከቤተሰቡ ንብረት ላይ በጣም አነስተኛው ብቻ እንዲሰጣቸው ወይም ምንም እንዳይደርሳቸው የሚያደርገው ‘የአምላክ አሠራር’ እንደሆነ ይነገራቸው ነበር። የሠራተኛው መደብ ‘አምላክ በሰጠው ቦታ’ ረክቶ እንዲኖር ዘወትር ምክር ይሰጠው ነበር።”
እንግዲያው ብዙዎች “ቀደም ሲል የነበረው የተጋነነ ሃይማኖታዊ አመለካከት” ተመልሶ እንዳይመጣ መፍራታቸው አያስደንቅም። ሃይማኖት ብዙውን ጊዜ የሰውን መንፈሳዊ ፍላጎት ከማሟላት ይልቅ የሰውን መንፈሳዊ ፍላጎት የመበዝበዣ መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞበታል። (ሕዝቅኤል 34:2) ኢንዲያ ቱደይ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፦ “ሃይማኖት ባለፉት ዘመናት ሁሉ ካስመዘገበው ታሪክ አንፃር ሲታይ እስከ ዛሬ ድረስ ተቀባይነት ያለው መሆኑ የሚያስገርም ነው። . . . በታላቁ ፈጣሪ ስም . . . የሰው ልጆች በወንድሞቻቸው ላይ ዘግናኝ ጭካኔ ፈጽመውባቸዋል።”
የሐሰት ሃይማኖት ያስመዘገበው እጅግ የሚሰቀጥጥ ታሪክ በዳርዊን አስተሳሰብ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ዳርዊን “ክርስትና ከአምላክ የመጣ ነው የሚለው እምነቴ ቀስ በቀስ እየጠፋ ሄደ” ሲል ጽፏል። “ብዙ የሐሰት ሃይማኖቶች እንደ ሰደድ እሳት ምድርን ማጥለቅለቃቸው በመጠኑ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል።”
የእውነተኛው ሃይማኖት ድል አድራጊነት
ሃይማኖታዊ ግብዝነት ለዚህ ዓለም አዲስ ነገር አይደለም። ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩት የሥልጣን ጥመኛ ሃይማኖታዊ መሪዎች እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ላዩን ሲያዩአችሁ ጥሩ ሰዎች መስላችሁ ትታያላችሁ፤ ውስጣችሁ ግን በአስመሳይነትና በክፋት የተሞላ ነው።”—ማቴዎስ 23:28 [የፊሊፕስ ትርጉም]
እውነተኛ ክርስትና ግን ‘የዓለም ክፍል አይደለም።’ (ዮሐንስ 17:16) ተከታዮቹ ብልሹ በሆነ ሃይማኖትና ፖለቲካ አይሳተፉም። የፈጣሪን መኖር በሚክዱ ፍልስፍናዎችም አይታለሉም። “የዚች ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ፊት ሞኝነት ነውና” ሲል ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፏል።—1 ቆሮንቶስ 3:19
ሆኖም ይህ ማለት እውነተኛ ክርስቲያኖች ለሳይንሳዊ እውቀት ባይተዋር ናቸው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የእውነተኛ ሃይማኖት ተከታዮች ስለ ሳይንሳዊ ነገሮች የማወቅ ከፍተኛ ጉጉትና ስሜት አላቸው። በጥንት ዘመን የነበረው ነቢዩ ኢሳይያስ ‘ዓይንህን ወደ ላይ አንሥተህ ተመልከት፤ እነዚህን የፈጠረ ማን ነው?’ ተብሎ ነበር። (ኢሳይያስ 40:26) ኢዮብም እንደዚሁ ስለ ፈጣሪ የበለጠ ማወቅ እንዲችል የተፈጥሮን ድንቅ ነገሮችና አጽናፈ ዓለምን በደንብ እንዲያጤን ተነግሮት ነበር።—ኢዮብ ከምዕራፍ 38–41
አዎን፣ በፈጣሪ የሚያምኑ ሁሉ የፍጥረትን ዘገባ በአክብሮታዊ ፍርሃት ይመለከቱታል። (መዝሙር 139:14) ከዚህም በላይ ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተናገረውን አስደናቂ ተስፋ ያምናሉ። (ራእይ 21:1–4) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሰው ልጅ አመጣጥም ሆነ የወደፊት ዕጣው በጭፍን ዕድል ላይ የተመካ እንዳልሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ እየተማሩ ነው። ይሖዋ ሰውን የሠራበት ዓላማ አለው፤ ይህ ዓላማ ደግሞ ታዛዥ የሰው ልጆች በሙሉ በረከት በበረከት ይሆኑ ዘንድ ፍጻሜውን ያገኛል። ይህ ነገር ምን እንደሆነ ራስዎ መርምረው እንዲያገኙት እንጋብዝዎታለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የኅዳር 8, 1982 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት ገጽ 6–9 እና ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 545 ይመልከቱ። ስለ ፍጥረት ንድፈ ሐሳብና ይህ ንድፈ ሐሳብ ከሳይንስና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስለሚጋጭባቸው ነገሮች ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት መጋቢት 8, 1983 ገጽ 12–15 እና መጋቢት 22, 1983 ገጽ 12–15 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔቶችን ይመልከቱ።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማስረጃውን የማያውቁ ናቸውን?
“የይሖዋ ምሥክሮች እንኳ የማይናቅ የሥነ ሕይወት እውቀት ቀስመዋል” ሲሉ የሕግ አዋቂ የሆኑት ኖርማን ማክቤዝ በ1971 አሳትመው ባወጡት ዳርዊን ሪትራይድ—አን አፒል ቱ ሪዝን በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ጽፈዋል። ማክቤዝ ስለ ዝግመተ ለውጥ የሚናገር አንድ የንቁ! መጽሔት ርዕስ ካነበቡ በኋላ “የዳርዊንን ንድፈ ሐሳብ በጥልቀት የሚተቹ አንዳንድ ሐሳቦችን የያዘ መሆኑ በጣም አስደንቆኛል” በማለት ያስተዋሉትን ተናግረዋል። የተደረገውን ጥልቅ ምርምርና በጉዳዩ ላይ ሚዛናዊ አስተያየቶችን የሰጡ ጠበብት ያሉትን በመጥቀስ የቀረበውን ሐሳብ በመመልከት ደራሲው የሚከተለውን መደምደሚያ ሰጥተዋል፦ “ ከእንግዲህ በኋላ ሲምፕሰን ‘ . . . በ[ዝግመተ ለውጥ] የማያምኑ ሰዎች ሁሉ ሳይንሳዊ ማስረጃውን የማያውቁ ናቸው ማለት ይቻላል’ ቢሉ ተሳስተዋል።”
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሰው ዘር የወደፊት ዕጣ ለጭፍን ዕድል አልተተወም