ጉረኛ እንዳትሆን ተጠንቀቅ
በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ጉረኝነትን እንደ ጥሩ ነገር አድርገው ይዘውታል። ጠንካራ ጎኔ፣ ችሎታዬና ያከናወንኩት ጥሩ ሥራ ይታይልኝ ማለት የተለመደ እየሆነ መጥቷል። አንዳንዶች አሸናፊ ለመሆን ጉራ መንዛት ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ። ጉረኝነት የአንድን ሰው ክብር ከፍ እንደሚያደርግ የሚሰማቸውም አልታጡም። ታይም መጽሔት “ትሕትና ጊዜ ያለፈበት እየሆነ መጥቷል” ሲል ጽፏል። ጁዲ ጌሊን የተባሉ ደራሲ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “የሚያሳዝነው ግን ያለምንም እፍረት ጉራ መንዛት . . . አዲስ ፋሽን ሆኗል። ከጓደኛ ወይም ከሚያውቁት ሰው ጋር በሚደረገው ጭውውት ውስጥ ጉራ መንፋት እንደ ቅመም ይጨመራል።”
ብዙዎች ተደናቂ የሆኑ ሰዎችን እንደ አርአያ አድርገው በመመልከት የሚያደርጉትን ሁሉ ይቀዳሉ። “በዚህ የታሪክ ወቅት ላይ የእኔ በዓለም ላይ ታላቅ ሰው መሆን እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ አይደለም” ሲል አንድ የቀድሞ የቦክስ ሻምፒዮና የተናገራቸውን ቃላት ሰምተህ ይሆናል። የቢትልስ የሙዚቃ ባንድ አባል የሆነ አንድ ሰው “በአሁኑ ጊዜ እኛ ከኢየሱስ ክርስቶስ የበለጠ ተወዳጅነት አለን” ሲል የተናገረው የታወቀ አባባልም አለ። አንዳንዶች እነዚህን አባባሎች ክፋት እንደሌለባቸው አድርገው ቢመለከቷቸውም ሌሎች ግን ራስን ከፍ ከፍ ማድርግ ተገቢ መሆኑን የሚያሳዩ ጥሩ ምሳሌዎች እንደሆኑ አድርገው በመመልከት እነዚህን ቃላት የተናገሩትን ሰዎች ይከተላሉ።
የጉረኝነት መብዛት የሚከተለውን ጥያቄ ያስነሣል፦ አንድ ሰው ስለ ንብረቱና ስለ ችሎታው ጉራውን ቢነዛ ትክክል ነውን? አንድ ሰው በሥራው ውጤት ኩራት ቢሰማውና ይህንንም ለቅርብ ጓደኞቹና ለዘመዶቹ ቢነግር ምንም ስሕተት የለበትም። ይሁን እንጂ “አንድ ዓይነት ሀብት ወይም ችሎታ ካለህ በሌሎች ዘንድ እንዲታይልህ አድርግ” በሚለው አባባል ስለሚስማሙት ሰዎች ምን ሊባል ይቻላል? በተጨማሪም በግልጽ ጉራቸውን ባይነዙም በተዘዋዋሪ ግን ስለችሎታቸውና ስላከናወኑት ሥራ ሌሎች እንዲያውቁላቸው ለማድረግ ስለሚጥሩትስ? አንዳንዶች እንደሚሉት እንዲህ ዓይነቱ ልታወቅ ልታወቅ ባይነት ትክክል ወይም አስፈላጊ ነውን?
ከሌሎች ጋር የሚኖርህን ግንኙነት ይነካል
ሰዎች ጉራ መንዛታቸው በአንተ ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ አስብ። ለምሳሌ ቀጥሎ ያሉትን አነጋገሮች እንዴት ትመለከታቸዋለህ?
“ሌሎች ሰዎች ከጻፏቸው መጽሐፎች ይልቅ እኔ ያልጻፍኳቸው መጽሐፎች ይበልጣሉ።”—አንድ የታወቁ ደራሲ።
“በፍጥረት ጊዜ ኖሬ ቢሆን ኖሮ አጽናፈ ዓለም የተሻለ አቀማመጥ እንዲኖረው ጠቃሚ ምክር እሰጥ ነበር።”—አንድ የመካከለኛው ዘመን ንጉሥ።
“አምላክ ሊኖር አይችልም፤ ምክንያቱም አምላክ ካለ ከኔ በቀር ሌላ ሊሆን አይችልም።”—አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን ፈላስፋ።
በዚህ አነጋገራቸው እነዚህ ሰዎች ይማርኩሃልን? አብረሃቸው ብትሆን የምትደሰት ይመስልሃልን? እንደማትደሰት የተረጋገጠ ነው። በቅንነትም ሆነ በቀልድ የሚነገር ጉራ ሌሎች እንዲጨነቁ፣ እንዲናደዱ፣ ምናልባትም ቅንዓት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። በመዝሙራዊው አሳፍ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ይህ ነበር። እሱም “የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመጸኞች ቀንቼ ነበርና” ሲል ሳይሸሽግ ተናግሯል። (መዝሙር 73:3) ማናችንም ብንሆን በወዳጆቻችንና አብረውን በሚውሉ ሰዎች ላይ መጥፎ ስሜት ማሳደር እንደማንፈልግ የተረጋገጠ ነው። አንደኛ ቆሮንቶስ 13:4 “ፍቅር . . . አይመካም” ይላል። አምላካዊ የሆነ ፍቅርና ለሌሎች ስሜት ያለን አሳቢነት ችሎታችንና ሀብታችን ይታይልን ከማለት እንድንቆጠብ ይገፋፋናል።
አንድ ሰው ራሱን የሚቆጣጠርና የማይመካ ከሆነ አጠገቡ ያሉት ሰዎች እንዲዝናኑና ስለራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው ያደርጋል። ይህ ደግሞ እጅግ ውድ የሆነ ችሎታ ነው። እንግሊዛዊ የፖለቲካ ሰው የነበሩት ሎርድ ቼስተርፊልድ “ከቻልክ ከሌሎች ሰዎች የበለጠ ጥበበኛ ሁን፤ ነገር ግን ከእነሱ የበለጠ ጥበበኛ መሆንህን አትንገራቸው” ሲሉ ልጃቸውን የመከሩት ምናልባት ይህን በአእምሮአቸው ይዘው ይሆናል።
የሰዎች ተሰጥዎ ይለያያል። ለአንዱ ቀላል የሆነው ለሌላው ከባድ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ፍቅር ካለው የእሱ ዓይነት ተሰጥዎ የሌላቸውን ሰዎች በርኅራኄ እንዲይዝ ይገፋፋዋል። ሌላው ሰው ደግሞ በሌላ መስክ የራሱ ተሰጥዎ ሊኖረው ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፣ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ” ሲል መክሮናል።—ሮሜ 12:3
ጉረኝነት ከደካማነት የሚመጣ ነው
አንዳንድ ሰዎች ከጉረኛ ሰዎች ጋር በሚሆኑበት ጊዜ የበታችነት ስለሚሰማቸው ከእነሱ ይርቃሉ። ሌሎች ደግሞ ከዚህ የተለየ ግምት ይወስዳሉ። ጉረኞች በራሳቸው የማይተማመኑ ሰዎች ናቸው ብለው ይደመድማሉ። ፍራንክ ትሪፔት የተባሉት ደራሲ ጉረኛ ሰው በሌሎች ዓይን ለምን ዝቅ ብሎ እንደሚታይ እንደሚከተለው በማለት ያብራራሉ፦ “ጉረኝነት ብዙውን ጊዜ አንዳንድ የግል ድክመቶችን እንደሚያሳይ ማንም ሰው በልቡ ያውቃል።” ብዙ ሰዎች የጉረኞች ውስጣዊ ሁኔታ በቀላሉ ስለሚገባቸው ጉራ ከመንዛት መቆጠብ ጥበብ አይደለምን?
“ግን እኮ ሊካድ አይችልም!”
አንዳንዶች ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ ተገቢ እንደሆነ ለማስመሰል የሚሰጡት ምክንያት ይህ ነው። በአንዳንድ ነገሮች በእርግጥ ተሰጥዎ እያላቸው እንደሌላቸው ሆኖ መታየት ግብዝነት እንደሆነ ይሰማቸዋል።
ይሁን እንጂ ጉራቸው እውነት ነውን? ለራስ የሚሰጠው ግምት ከአድልዎ የጸዳ አይሆንም። እኛ ለራሳችን እንደ ትልቅ ችሎታ አድርገን የምንገምተው ነገር በሌሎች ዘንድ ተራ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው ችሎታውን ማሳየት እንዳለበት በኃይል ከተሰማው ችሎታው ያን ያህል እንዳልሆነ፤ የማስታወቂያ ድጋፍ የሚያስፈልገው ደካማ ችሎታ መሆኑን ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” የሚል ማስጠንቀቂያ በመስጠት ራስን የማታለል ሰብዓዊ ዝንባሌ እንዳለ ይጠቁማል።—1 ቆሮንቶስ 10:12
አንድ ሰው በአንድ ዓይነት መስክ ልዩ ተሰጥዎ ቢኖረውም እንኳ ይህ ራሱ ጉራውን እንዲነዛ ሊያደርገው ይገባልን? አይገባም፤ ምክንያቱም ጉራ መንዛት ሰውን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ነገር ግን ያለን ማንኛውም ተሰጥዎ ከአምላክ የመጣ ነው። ክብር ሊቀበል የሚገባው እርሱ ነው። በተፈጥሮ ላገኘነው ነገር ለምን ክብር እንቀበላለን? (1 ቆሮንቶስ 4:7) ከዚህም በተጨማሪ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉን ሁሉ ድክመቶችም አሉን። ሐቀኝነት ስህተቶቻችንንና ድክመቶቻችንን እንድናውቅ ያስገድደናልን? እንዲህ ብለው የሚያስቡ ጉረኞች የሉም ማለት ይቻላል። ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ግሩም የንግግር ችሎታ ያለው ሰው ኖሮ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከትምክህተኝነት አለመራቁ መጥፎ አሟሟት አስከትሎበታል። በሄሮድስ ላይ የደረሰው ይህ አስቀያሚ ሁኔታ ትምክህተኝነት በብዙ ሰዎች ዘንድ የተጠላ እንደሆነ ሁሉ በአምላክ ዘንድም የቱን ያህል የተጠላ እንደሆነ ያሳያል።—ሥራ 12:21–23
ተሰጥዎቻችንና ጠንካራ ጎኖቻችን ምንም ማስታወቂያ ሳንናገር ራሳቸው መታወቃቸው አይቀርም። ሌሎች ሰዎች አንድ ሰው ያለውን ችሎታ ወይም ያከናወነውን ጥሩ ሥራ ተመልክተው ሲያመሰግኑት ምስጋናውን ለሚቀበለው ሰው የበለጠ ሞገስ ይሆንለታል። ምሳሌ 27:2 “ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም፤ ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይደለም” በማለት የጥበብ ምክር ይሰጣል።
ጉራ መንዛት አሸናፊ ለመሆን ይረዳልን?
አንዳንዶች ፉክክር ባለበት በዛሬው ኅብረተሰብ ውስጥ ተወዳዳሪን ለማሸነፍ በትምክህት ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ስለ ችሎታዎቻቸው በይፋ ካልተናገሩና እንታይ እንታይ ካላሉ ሳይደነቁና ማንም ሳያውቃቸው ተረስተው የሚቀሩ ስለሚመስላቸው ይጨነቃሉ። ቮግ ከተባለው መጽሔት የተወሰደው የሚከተለው አስተያየት የእነሱን ዓይነት ጭንቀት የሚያሳይ ነው፦ “ድሮ ትሕትና ጥሩ ሥነ ምግባር እንደሆነ እንማር ነበር፤ አሁን ግን ዝምተኝነት ጉድለት እንዳለብን ሊያስቆጥረን እንደሚችል እየተማርን ነው።”
የዚህን ዓለም መመዘኛ ተከትለው ለመሻሻል ለሚፈልጉ ሰዎች ይህ ዓይነቱ ጭንቀት ምናልባት ተገቢ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አንድ ክርስቲያን የሚኖረው አቋም ከዚህ የተለየ ነው። አንድ ክርስቲያን አምላክ ትዕቢተኛ ያልሆኑትን ትሑታን ሰዎች እንደሚፈልግና በችሎታቸውም እንደሚጠቀም ያውቃል። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን በራስ ወዳድነት ዘዴዎች መጠቀም የለበትም። እርግጥ ነው፣ ከመጠን በላይ በራሱ የሚመካ ግለሰብ ተከራክሮ ወይም አግባብቶ ጊዜያዊ ክብር ሊያገኝ ይችል ይሆናል። ውሎ አድሮ ግን ይጋለጣል፣ ትሑት መሆንን ይማራል ወይም ውርደት ይደርስባታል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፣ ራሱንም የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል” ሲል እንደተናገረው ነው።—ማቴዎስ 23:12፤ ምሳሌ 8:13፤ ሉቃስ 9:48
ራስን አለመካብ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን “የማገኘው ማንኛውም ሰው በሆነ መንገድ ይበልጠኛል፤ ምክንያቱም ከእርሱ የምማረው ነገር ይኖራል” ሲሉ ጽፈዋል። የእርሳቸው አነጋገር “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ ምክንያት አንድ እንኳን አታድርጉ፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ እንዲሻል በትሕትና ይቁጠር” ከሚለው ጳውሎስ በመለኮታዊ መንፈስ አነሣሽነት ለክርስቲያኖች ከጻፈው ምክር ጋር ይስማማል። (ፊልጵስዩስ 2:3) በዚህ ዓይነት አቅምንና ቦታን ማወቅ አንድን ሰው ከሌሎች እንዲማር ያደርገዋል።
ስለዚህ ጠንካራ ጎንህ ደካማ ጎንህን የሚያሳይ እንዳይሆን ተጠንቀቅ። ጉራ ችሎታህንና ያከናወንካቸውን መልካም ሥራዎች እንዲያቃልልብህ አትፍቀድ። ባሉህ ባሕርያት ላይ አቅምንና ቦታን የማወቅን ግሩም ባሕርይ አክልባቸው። አንድ ሰው በሌሎች ሰዎች ፊት ከፍ ብሎ እንዲታይ የሚያደርገው ይህ ነው። አቅምንና ቦታን ማወቅ አንድ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረው ይረዳዋል፤ እንዲሁም በይሖዋ አምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝለታል።—ሚክያስ 6:8፤ 2 ቆሮንቶስ 10:18