ጠንካራ ጎናችሁ ለድክመት ምክንያት እንዲሆን አትፍቀዱ
አሥራ ስድስት የውኃ ማገጃ ክፍሎች የነበሯትና ምቾትና ቅንጦት እንዲኖራት ተደርጋ የተሠራችው ታይታኒክ የተባለችው ግዙፍ የመንገደኞች መርከብ ፈጽሞ እንደማትሰጥም ይታሰብ ነበር። በ1912 የመጀመሪያ ጉዞዋን ስታደርግ በውስጧ የነበሩት የመጠባበቂያ ጀልባዎች ብዛት መያዝ ከነበረባት ግማሽ የሚያህሉት ብቻ ነበሩ። መርከቧ ከበረዶ ዓለት ጋር ተላትማ በመስጠሟ ከ1,500 የሚበልጡ ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።
ፈሪሃ አምላክ የነበረው የጥንቷ ኢየሩሳሌም ንጉሥ ዖዝያን አስተዋይ የጦር መሪ ነበር። በይሖዋ እርዳታ ጠላቶቹን አንድ በአንድ አሸንፏል። “እስኪበረታም ድረስ እግዚአብሔር በድንቅ ረድቶታልና [የዖዝያን ዝና] እስከ ሩቅ ድረስ ተሰማ።” ከጊዜ በኋላ ግን “ልቡ ታበየ፣ አምላኩንም እግዚአብሔርን በደለ።” ዖዝያን በመታበዩ ምክንያት በለምጽ ተመታ።—2 ዜና መዋዕል 26:15-21፤ ምሳሌ 16:18
ጠንካራ ጎናችን በጥበብ፣ በልከኝነትና በትሕትና ካልተገራ በቀላሉ ደካማ ጎን ሊሆን ወይም ችግር ሊፈጥርብን እንደሚችል ከእነዚህ ሁለት ታሪኮች እንማራለን። ሁላችንም በሆነ መልኩ አንድ ዓይነት ጠንካራ ጎን ወይም ተሰጥኦ ስላለንና ይህም ለራሳችንም ሆነ ለሌሎች በተለይ ደግሞ ፈጣሪያችንን የሚያስደስትና እሴት እንዲሆን ስለምንፈልግ ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በእርግጥም አምላክ የሰጠንን ማንኛውንም ዓይነት ስጦታ በተሟላ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል አለብን። ሆኖም ስጦታው ጠቃሚ በረከት ሆኖ እንዲቀጥል በአግባቡ ልንቆጣጠረው ይገባል።
ለምሳሌ ያህል ሥራውን የሚያፈቅር አንድ ሰው የሥራ ሱሰኛ በመሆን ይህ ስጦታው በቀላሉ ደካማ ጎን እንዲሆንበት ሊያደርግ ይችላል። ጠንቃቃ የሆነ ሰው ደግሞ በቀላሉ ላይሞኝ ወይም ላይታለል ይችላል። ሆኖም ከጠንቃቃነቱ የተነሳ ምንም ዓይነት ውሳኔ ለማድረግ ይቸገር ይሆናል። ቅልጥፍናም ቢሆን መልካም ባሕርይ ነው፤ ይሁን እንጂ ሰዎች ሰብዓዊ ድክመት እንዳለባቸው ረስቶ ወደሌላኛው ጽንፍ መሄድ ደስታ የሚያሳጣ አሳቢነት የጎደለውና ድርቅ ያለ ሁኔታ እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ ባሉህ ጠንካራ ጎኖች ላይ ለማሰላሰል ጊዜ መድብ። ያሉህን ጠንካራ ጎኖች የምትጠቀምባቸው በአግባቡ ነው? ለሌሎች በረከት ናቸውን? ከሁሉ በላይ፣ “[የ]በጎ ስጦታ ሁሉ” ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ለማክበር ትጠቀምባቸዋለህ? (ያዕቆብ 1:17) ይህን ማድረግ ትችል ዘንድ ቁጥጥር ካልተደረገባቸው ደካማ ጎን አልፎ ተርፎም ጉዳት ሊሆኑ የሚችሉ ጠንካራ ጎኖችን በተመለከተ ተጨማሪ ምሳሌዎችን በዝርዝር እንመልከት።
የአእምሮ ችሎታችሁን በጥበብ ተጠቀሙበት
ጥሩ አእምሮ ግሩም ስጦታ እንደሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ሌሎች ከልክ በላይ የሚያሞግሱን ወይም የሚሸነግሉን ከሆነና ይህም ከልክ በላይ በራሳችን እንድንመካ ወይም ስለ ራሳችን የተጋነነ ግምት እንዲኖረን ካደረገን እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። ወይም የአምላክን ቃልና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የጥናት ጽሑፎችን የምንመለከታቸው እውቀት ለማካበት ብቻ የሚጠቅሙ እንደሆኑ አድርገን ይሆናል።
ከልክ በላይ በራስ መታመን በተለያዩ መንገዶች ሊገለጥ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ጥሩ የአእምሮ ችሎታ ያለው አንድ ሰው በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ክፍል ሲሰጠው ምናልባትም የሕዝብ ንግግር ወይም የቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ክፍል ሊሆን ይችላል ዝግጅቱን መጨረሻ ደቂቃ ላይ አደርገዋለሁ ብሎ ሊተወው አልፎ ተርፎም የይሖዋን በረከት ለማግኘት ሳይጸልይ ሊቀር ይችላል። ከዚህ ይልቅ ባለው የእውቀት ክምችትና ሐሳብ አፍልቆ የመናገር ችሎታው ላይ ይታመናል። ለጊዜው በተፈጥሮ ችሎታው ተጠቅሞ ቸልተኝነቱን ሊሸፍን ቢችልም የይሖዋን በረከት በተሟላ መልኩ እስካላገኘ ድረስ መንፈሳዊ እድገቱ መጓተቱ ይባስ ብሎም ማቆሙ የማይቀር ነው። ይህ መልካም የሆነ ስጦታውን ማባከን ነው!—ምሳሌ 3:5, 6፤ ያዕቆብ 3:1
በተጨማሪም እውቀት በመቅሰም ረገድ ፈጣን አእምሮ ያለው ሰው መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እውቀት ለመሰብሰብ የሚያገለግሉ ነገሮች ብቻ አድርጎ ይመለከታቸው ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ዓይነቱ እውቀት ‘ከማስታበይ’ ወይም ለራሳችን ያለን ግምት እንደ ፊኛ እንዲነፋ ከማድረግ በቀር ፍቅራዊ የሆነ ክርስቲያናዊ ወዳጅነት ‘ለመገንባት’ አይረዳም። (1 ቆሮንቶስ 8:1 NW፤ ገላትያ 5:26) በአንጻሩ ደግሞ መንፈሳዊው ሰው ምንም ዓይነት የአእምሮ ችሎታ ቢኖረው ሁልጊዜ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት ይጸልያል እንዲሁም በአምላክ መንፈስ ይታመናል። በፍቅር፣ በትሕትና፣ በእውቀትና በጥበብ በተመጣጠነ መልኩ እያደገ ሲሄድ ጠንካራ ጎኑ ከበፊቱ በበለጠ እሴት ይሆናል።—ቆላስይስ 1:9, 10
እንዲሁም ባለን ችሎታ ምክንያት ስለ ራሳችን የተጋነነ አመለካከት በማዳበር አቅምና ቦታችንን ከሳትን ችሎታችን እንቅፋት ይሆንብናል። የ1974 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ በጀርመን በሚገኝ አንድ ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ስለነበረ ልዩ የማስታወስ ተሰጥኦ ስላለው አንድ ወንድም ያወሳል። “መጀመሪያ ላይ የተማራቸውን ነገሮች የማስታወስና ለሌሎች የማካፈል ችሎታው ለወንድሞች የማበረታቻ ምንጭ ሆኖላቸው ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ‘የቡከንቫልድ ትንግርት’ በመባል እንደ ጣዖት መታየት የጀመረ ሲሆን የግል አመለካከቱን ጨምሮ የሚናገራቸው ነገሮች ሁሉ ትክክል እንደሆኑ ይታይ ጀመር።” ከዚያም ከእርሱ ሐሳብ ጋር ያልተስማሙ ወንድሞች እስር ቤት የገቡት ለይሖዋ ባላቸው ታማኝነት መሆኑ ተረስቶ እንደ ጠላት ይቆጠሩ ጀመር!
ይህ ጥሩ ተሰጥኦ ያለው ሰውም ሆነ እርሱን ከመጠን በላይ የካቡት ሰዎች ማንኛውም ዓይነት ችሎታ ቢኖራቸውም ይሖዋ “በልባቸውም ጠቢባን የሆኑትን ሁሉ አይመለከትም” የሚለውን ቃል ዘንግተው እንደነበር ግልጽ ነው። (ኢዮብ 37:24) የአምላክ ቃል “በትሑታን ዘንድ . . . ጥበብ ትገኛለች” ይላል። (ምሳሌ 11:2) ሐዋርያው ጳውሎስ አስተዋይና ከፍተኛ ትምህርት የቀሰመ ሰው ቢሆንም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን እንዲህ ብሏቸዋል:- “እኔም፣ ወንድሞች ሆይ፣ ወደ እናንተ በመጣሁ ጊዜ በቃልና በጥበብ ብልጫ . . . አልመጣሁም። . . . በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥም በእናንተ ዘንድ ነበርሁ፤ እምነታችሁም በእግዚአብሔር ኃይል እንጂ በሰው ጥበብ እንዳይሆን፣ ቃሌም ስብከቴም መንፈስንና ኃይልን በመግለጥ ነበረ እንጂ፣ በሚያባብል በጥበብ ቃል አልነበረም።”—1 ቆሮንቶስ 2:1-5
እውነተኛ ጥበብ ያለው ሰው ዓለም ለከፍተኛ እውቀት በሚኖረው አመለካከትም ሆነ ለስኬታማነት በሚሰጠው መመዘኛ አይዘናጋም። ስለዚህ ባሉት ተሰጥኦዎች ተጠቅሞ በሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ከመጋደል ወይም ዓለማዊ ሀብት ከማካበት ይልቅ ሕይወትና ችሎታን ለለገሰው አካል ምርጡን ይሰጣል። (1 ዮሐንስ 2:15-17) ይህንንም ማድረግ ይችል ዘንድ በሕይወቱ ውስጥ የመንግሥቱን ፍላጎቶች በአንደኛ ደረጃ በማስቀመጥ “በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች” የምታፈራ ዛፍ ይሆናል። በራሱ የተፈጥሮ ተሰጥኦዎች ሳይሆን ከይሖዋ በሚያገኘው በረከት የተነሳ “የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል።”—መዝሙር 1:1-3፤ ማቴዎስ 6:33
ክርስትና ጠንካራ ጎናችሁን የሚያጎለብት ይሁን
በመሠረቱ የክርስትና እምነት ብዙ ጠንካራ ጎኖች ስላሉት ዓለማዊ ፍልስፍናዎች ከክርስትና እምነት ጋር ሲነጻጸሩ ደካማ ሆነው ይታያሉ። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያናዊ ሕይወት ሐቀኛ፣ ሰው አክባሪ፣ ሰላማዊና ታታሪ የሆንን ሰዎችና የተሻልን ባል፣ የተሻልን ሚስት፣ የተሻልን ጎረቤት እንዲሁም ሠራተኞች እንድንሆን ይረዳናል። (ቆላስይስ 3:18-23) በተጨማሪም ንግግር በመስጠትና በማስተማር ረገድ የምናገኘው ክርስቲያናዊ ስልጠና ሐሳብ ለሐሳብ የመለዋወጥ ጥሩ ችሎታ እንድናዳብር ያስችለናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:13-15) በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ ክርስቲያኖች ለተጨማሪ ኃላፊነትና እድገት በአሠሪዎቻቸው ዘንድ የሚፈለጉ መሆናቸው የሚያስደንቅ አይደለም። ሆኖም ይህ ዓይነቱ ጠንካራ ጎን በጥንቃቄ ካልተያዘ አላግባብ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። የሥራ እድገት ወይም የሚያጓጓ የሥራ ዕድል መቀበል ሙሉ በሙሉ ለድርጅቱ ያደሩ በመሆን ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መቅረትን ማዘውተር ወይም አንድ ሰው ከቤተሰቡ ጋር የሚያሳልፈውን ውድ ጊዜ መሥዋዕት ማድረግ ሊጠይቅበት ይችላል።
በአውስትራሊያ የሚኖር የቤተሰብ ራስ የሆነ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ በንግዱ ዓለም እጅግ የተዋጣለት የነበረ ሲሆን እንደ ሰዎች አባባል “ሁሉ በእጁ” ነበር። ሆኖም በዚህ ሥርዓት ስኬታማ እንዲሆን በቀረበለት የሚያጓጓ ሁኔታ ለመጠቀም ፈቃደኛ አልሆነም። “ከቤተሰቤ ጋር እንዲሁም በክርስቲያናዊ አገልግሎት ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፍ ፈለግሁ” ሲል ተናግሯል። “ስለዚህ እኔና ባለቤቴ በዓለማዊ ሥራ ላይ የማውለውን ጊዜ ቀስ በቀስ መቀነስ እንደሚኖርብኝ ተስማማን። የግድ አስፈላጊ ካልሆነ በሳምንት አምስት ቀን የምሠራበት ምን ምክንያት አለ?” በማለት አክሎ ተናግሯል። ይህ ሽማግሌ በሕይወቱ ውስጥ በአግባቡ የታሰበባቸው ማስተካከያዎች በማድረግ በሳምንት ሦስት ወይም አራት ቀን እየሠራ ቤተሰቡን መርዳት እንደሚችል ተገነዘበ። ከጊዜ በኋላ በአካባቢው ባለው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታ ኮሚቴና የአውራጃ ስብሰባ አስተዳደር በመሳሰሉ ሌሎች የአገልግሎት መብቶች እንዲካፈል ግብዣ ቀረበለት። ጠንካራ ጎኖቹን በጥበብ ስለተጠቀመበት ለእርሱም ሆነ ለቤተሰቡ ደስታና እርካታ አስገኝቶለታል።
ለምናገኛቸው መብቶች ሊኖረን የሚገባ ሚዛናዊ አመለካከት
ክርስቲያን ወንዶች በጉባኤ ውስጥ ለአንዳንድ የአገልግሎት መብቶች ብቁ ለመሆን እንዲጣጣሩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን [“የበላይ ተመልካችነትን፣” NW] [ወይም የጉባኤ አገልጋይነትን] ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል።” (1 ጢሞቴዎስ 3:1) ቀደም ሲል እንደተጠቀሱት ጠንካራ ጎኖች ሁሉ የተለያዩ ኃላፊነቶችን ለመቀበል የምናሳየው ፈቃደኝነትም ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የታከለበት ሊሆን ይገባል። ማንኛውም ሰው በይሖዋ አገልግሎት የሚያገኘውን ደስታ እስኪያጣ ድረስ ብዙ ኃላፊነቶች መቀበል የለበትም። እርግጥ፣ ይሖዋ ኃላፊነት ከመቀበል በሚሸሽ ሰው ስለማይደሰት የፈቃደኝነት መንፈስ ማሳየት የሚያስመሰግን ብቻ ሳይሆን አስፈላጊም ነው። ይሁን እንጂ የፈቃደኝነት መንፈስ ልከኝነትና “ጤናማ አስተሳሰብ” የተንጸባረቀበት ሊሆን ይገባል።—ቲቶ 2:12 NW፤ ራእይ 3:15, 16
ኢየሱስ ያሳየው ገርነት፣ ማስተዋልና አሳቢነት በጣም ዝቅተኛ ደረጃ የነበራቸው ሰዎች እንኳ ከእርሱ ጋር ሲሆኑ ዘና እንዲሉ አድርጓቸዋል። ዛሬም ሰዎች የሌሎችን ችግር በመረዳትና አሳቢነት በማሳየት ረገድ ጠንካራ ጎን ካላቸው ሰዎች ጋር ሲሆኑ ዘና ይላሉ። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሞቅ ያለ መንፈስ ያላቸውና ሊቀረቡ የሚችሉ ሽማግሌዎች በእርግጥ እንደ ውድ ነገር አድርገን ልንመለከታቸው የሚገቡ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ናቸው። ሽማግሌዎች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ” ናቸው።—ኤፌሶን 4:8፤ ኢሳይያስ 32:2
ሆኖም ሽማግሌዎች ሌሎችን በመርዳት የሚያሳልፉትን ጊዜ ለግል ጥናት፣ ለማሰላሰል፣ ለጸሎትና ለሕዝብ በሚሰጠው ምሥክርነት ለመካፈል ከሚያስፈልጋቸው ጊዜ ጋር ሚዛናዊ ማድረግ አለባቸው። ያገቡ ሽማግሌዎች ደግሞ ለቤተሰቦቻቸው ጊዜ መመደብ እንደሚያስፈልጋቸው የታወቀ ነው። በተለይ በቤተሰቦቻቸው ዘንድ በቀላሉ የሚቀረቡ ሆነው መገኘት አለባቸው።
ግሩም በረከት የሆኑ ልባም ሴቶች
ተሰጥኦ እንዳላቸው ሽማግሌዎች ሁሉ መንፈሳዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሴቶችም ለይሖዋ ድርጅት ትልቅ እሴት ናቸው። በጥቅሉ ሲታይ ሴቶች ለሌሎች ሰዎች ትኩረት የመስጠት ተሰጥኦ አላቸው። ደግሞም ይሖዋ ይህን ባሕርይ ከፍ አድርጎ ከመመልከቱም በላይ ይህ ባሕርይ እንዲኖረን ያበረታታናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:4) ሆኖም ማንኛውም ክርስቲያን ‘በሌሎች ጉዳይ መግባት’ ስለማይፈልግና ሐሜተኛ መሆንም ስለሌለበት ‘ለባልንጀራው የሚሰጠው የግል ትኩረት’ ገደብ ሊኖረው ይገባል።—1 ጴጥሮስ 4:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:13
ሴቶች ሌሎች በርካታ ተሰጥኦዎችም አሏቸው። ለምሳሌ ያህል አንዲት ክርስቲያን ሚስት ከባልዋ የበለጠ የአእምሮ ችሎታ ይኖራት ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋን የምትፈራ “ልባም ሴት” እንደመሆንዋ መጠን ባልዋን በማክበር ያላትን ተሰጥኦ ተጠቅማ የሚጎድለውን ታሟላለታለች እንጂ ከእርሱ ጋር አትፎካከርም። እንዲሁም ጥበበኛና ትሑት የሆነ ባል በእርስዋ ከመቅናት ወይም ከመናደድ ይልቅ የሚስቱን ጠንካራ ጎኖች ከፍ አድርጎ ይመለከታል፤ በዚያም ይደሰታል። ቤተሰቧን ለማነጽና እርሷ እንደምታደርገው ሁሉ ልጆቿም ‘ይሖዋን እንዲፈሩ’ ለመርዳት ያላትን ተሰጥኦ በተሟላ መልኩ እንድትጠቀምበት ያበረታታታል። (ምሳሌ 31:10, 28-30፤ ዘፍጥረት 2:18 NW) እንዲህ ዓይነቶቹ አቅማቸውንና ቦታቸውን የሚያውቁ ትሑት ባልና ሚስቶች በእርግጥ ይሖዋን የሚያስከብር ትዳር በመመሥረት ረገድ ይሳካላቸዋል።
የኃይለኝነት ባሕርያችንን ማለዘብ
በጽድቅና የይሖዋን ፈቃድ በሙሉ ነፍስ በመፈጸም ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ባሕርይ ልከኝነትና ትሕትና ከታከለበት ትልቅ እሴት ሊሆን ይችላል። ሆኖም አንድ ሰው ይህን ባሕርይውን ተጠቅሞ ሌሎችን የሚጫን ወይም የሚያስፈራራ ከሆነ ደካማ ጎን ሊሆንበት ይችላል። በተለይ ይህ ነገር በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ትርጉም ይኖረዋል። ክርስቲያኖች አንዳቸው ከሌላው ጋር ሲሆኑም ሆነ የጉባኤ ሽማግሌዎች ባሉበት ነፃነት ሊሰማቸው ይገባል።—ማቴዎስ 20:25-27
ሽማግሌዎችም ጭምር አንዳቸው ከሌላው ጋር ሲሆኑ ነፃነት ሊሰማቸው ይገባል። በመሆኑም አንድ ላይ ተሰብስበው የሚያደርጉት ውሳኔ የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ እንጂ በአንድ ሰው ባሕርይ መሆን የለበትም። በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ በዕድሜ አነስተኛውንም ሆነ ዝምተኛ የሆነውን ሽማግሌ ጨምሮ የሽማግሌዎች አካል አባል የሆነን ማንኛውንም ሽማግሌ ሊመራ ይችላል። ስለዚህ ጠንካራ ባሕርይ ያላቸው ሽማግሌዎች ትክክል እንደሆኑ በሚሰማቸው ጊዜም እንኳ ለመሰል ሽማግሌዎች ‘አክብሮት በማሳየት’ የሌሎችን ሀሳብ መቀበልን በመማር ጠንካራ ጎናቸውን በአግባቡ መያዝ አለባቸው። (ሮሜ 12:10) መክብብ 7:16 በደግነት እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል:- “እጅግ ጻድቅ አትሁን፣ እጅግ ጠቢብም አትሁን፣ እንዳትጠፋ።”
“[የ]በጎ ስጦታ ሁሉ” ምንጭ የሆነው ይሖዋ ያሉትን ይህ ነው የማይባሉ ጠንካራ ጎኖች እጅግ ፍጹም በሆነ መንገድ ይጠቀምባቸዋል። (ያዕቆብ 1:17፤ ዘዳግም 32:4) እርሱ ደግሞ አስተማሪያችን ነው! ስለዚህ የተፈጥሮ ተሰጥኦዋችንን ወይም ጠንካራ ጎናችንን በማጎልበትም ሆነ እነዚህን ጠንካራ ጎኖች በጥበብ፣ በልከኝነትና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በመያዝ ረገድ ከእርሱ ለመማርና የተማርነውን በተግባር ለማዋል ጥረት እናድርግ። እንዲህ ስናደርግ ለሌሎች ምንኛ በረከት እንሆናለን!
[በገጽ 27 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
መንፈሳዊ እድገታችን ከልብ በምናደርገው ጥናትና በይሖዋ በመታመናችን ላይ የተመካ ነው
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቦታችንን ሳንስት ለሌሎች የምንሰጠው ትኩረት በረከት ሆኖ ይገኛል
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of The Mariners’ Museum, Newport News, VA