የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 6/1 ገጽ 14-19
  • ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ ማድነቅ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ ማድነቅ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ‘ከእናንተ ጋር አብረን የምንሠራ ነን’
  • በደስታ እንዲያገለግሉ ሁሉንም መርዳት
  • ‘ታዛዦችና ተገዥዎች ሁኑ’
  • “ከመጠን ይልቅ አክብሯቸው”
  • የይሖዋን በጎች እንዲጠብቁ የተሾሙ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ‘በመካከላችሁ በትጋት እየሠሩ ያሉትን አክብሯቸው’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ‘ለደስታችን ከእኛ ጋር አብረው የሚሠሩት’ ክርስቲያን ሽማግሌዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • ሽማግሌዎች—የሐዋርያው ጳውሎስን አርዓያ መከተላችሁን ቀጥሉ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 6/1 ገጽ 14-19

‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ ማድነቅ

“በመካከላችሁ የሚደክሙትን . . . ስለ ሥራቸውም በፍቅር ከመጠን ይልቅ [አክብሯቸው።]”​—⁠1 ተሰሎንቄ 5:​12, 13

1. በሐዋርያት ሥራ 20:​35 መሠረት መስጠት ምን ኃይል አለው? አብራራ።

“ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ [“ደስተኛ፣” NW] ነው።” (ሥራ 20:​35) እነዚህ የኢየሱስ ቃላት እውነት መሆናቸውን የሚያረጋግጥ በቅርቡ ያደረግከው የምታስታውሰው ነገር አለ? ምናልባት ከልብ ለምትወደው ሰው ስጦታ ሰጥተህ ይሆናል። ይህ ሰው ስጦታህን ከፍ አድርጎ እንዲመለከተው ስለፈለግህ ስጦታውን በጥንቃቄ መርጠሃል። ስጦታውን የሰጠኸው ሰው ፊቱ በደስታ ሲፈካ ስትመለከት የአንተም ልብ ምንኛ በደስታ ይሞላል! በጥሩ ውስጣዊ ስሜት ተገፋፍቶ የሚደረግ ስጦታ የፍቅር መግለጫ ሲሆን ፍቅር ደግሞ ደስታ የማስገኘት ኃይል አለው።

2, 3. (ሀ) ከይሖዋ የሚበልጥ ደስተኛ የለም ለማለት የሚቻለው ለምንድን ነው? ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ መስጠቱስ ልቡን ደስ የሚያሰኘው እንዴት ነው? (ለ) አምላክ የሰጠንን ስጦታ ምን ማድረግ አንፈልግም?

2 ታዲያ ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ’ ምንጭ ከሆነው ከይሖዋ ይበልጥ ደስተኛ ሊኖር ይችላልን? (ያዕቆብ 1:​17፤ 1 ጢሞቴዎስ 1:​11) እርሱ ማንኛውንም ስጦታ የሚሰጠው በፍቅር ተገፋፍቶ ነው። (1 ዮሐንስ 4:​8) ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችም’ አምላክ በፍቅሩ ተገፋፍቶ በክርስቶስ በኩል ለጉባኤ የሰጣቸው ስጦታዎች ናቸው። (ኤፌሶን 4:​8) አምላክ መንጋውን የሚጠብቁ ሽማግሌዎች እንዲኖሩ ማድረጉ ለሕዝቦቹ ያለውን የጠለቀ ፍቅር የሚያሳይ ነው። እነዚህ ወንዶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን የግድ ማሟላት ስለሚገባቸው በጥንቃቄ የተመረጡ ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:​1-7፤ ቲቶ 1:​5-9) ‘መንጋውን በርኅራኄ መጠበቅ’ እንዳለባቸው ያውቃሉ። በዚህም የተነሳ በጎቹ እንደዚህ ያሉ አፍቃሪ እረኞች በማግኘታቸው የአመስጋኝነት ስሜት ያድርባቸዋል። (ሥራ 20:​29፤ መዝሙር 100:​3) ይሖዋ የበጎቹ ልብ እንዲህ ባለ የአመስጋኝነት ስሜት ሲሞላ ሲመለከት የእርሱም ልብ በደስታ እንደሚሞላ የተረጋገጠ ነው!​—⁠ምሳሌ 27:​11

3 አምላክ አንድን ነገር በስጦታ መልክ ሲሰጠን ስጦታውን አቃልለን እንደማንመለከተው ወይም ምስጋናቢሶች እንደማንሆን እሙን ነው። አሁን የሚከተሉት ሁለት ጥያቄዎች ይነሳሉ:- ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ድርሻ እንዴት መመልከት ይኖርባቸዋል? የተቀሩት የመንጋው አባላትስ ‘ስጦታ ለሆኑ ወንዶች’ ያላቸውን አድናቆት እንዴት ሊያሳዩ ይችላሉ?

‘ከእናንተ ጋር አብረን የምንሠራ ነን’

4, 5. (ሀ) ጳውሎስ ጉባኤን ከምን ጋር አመሳስሎታል? ይህስ ተስማሚ ምሳሌ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የጳውሎስ ምሳሌ እርስ በርስ ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ምን ያመለክታል?

4 ይሖዋ ‘ስጦታ ለሆኑት ወንዶች’ በጉባኤ ውስጥ የተወሰነ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። እርግጥ ነው ሽማግሌዎች ሥልጣናቸውን አለ አግባብ ሊጠቀሙበት አይፈልጉም። ሆኖም ፍጽምና የሌላቸው ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን በዚህ ረገድ በቀላሉ ሊሳሳቱ እንደሚችሉ ያውቃሉ። ታዲያ ከመንጋው ጋር ባላቸው ግንኙነት ራሳቸውን እንዴት መመልከት ይኖርባቸዋል? ሐዋርያው ጳውሎስ የተጠቀመበትን ምሳሌ ልብ በሉ። ጳውሎስ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ የተሰጡበትን ምክንያት ካብራራ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ነገር ግን እውነትን በፍቅር እየያዝን በነገር ሁሉ ወደ እርሱ ራስ ወደሚሆን ወደ ክርስቶስ እንደግ፤ ከእርሱም የተነሣ አካል ሁሉ እያንዳንዱ ክፍል በልክ እንደሚሠራ፣ በተሰጠለት በጅማት ሁሉ እየተጋጠመና እየተያያዘ፣ ራሱን በፍቅር ለማነጽ አካሉን ያሳድጋል።” (ኤፌሶን 4:​15, 16) ጳውሎስ ሽማግሌዎችንና ሌሎች አባላትን ጨምሮ ጠቅላላውን ጉባኤ ከሰው አካል ጋር አመሳስሎ ገልጿል። ይህ ተስማሚ ምሳሌ የሆነው ለምንድን ነው?

5 የሰው አካል የተለያዩ ብልቶች ያሉት ቢሆንም ያለው ራስ ግን አንድ ብቻ ነው። ሆኖም ጡንቻ ይሁን ነርቭ ወይም ደግሞ የደም ሥር ጥቅም የማይሰጥ አንድም የአካል ክፍል የለም። እያንዳንዱ የሰውነት ብልት ጠቃሚ ሲሆን ለመላው አካል ጤንነትና ውበት የሚያበረክተው ድርሻ አለው። በተመሳሳይም ጉባኤ የተለያዩ በርካታ ብልቶች ያሉት ሲሆን እያንዳንዱ ብልት ወጣትም ሆነ በዕድሜ የገፋ፣ ጠንካራም ሆነ አቅመ ደካማ ለመላው ጉባኤ መንፈሳዊ ጤንነትና ውበት አንድ ዓይነት ድርሻ ማበርከት የሚችል ነው። (1 ቆሮንቶስ 12:​14-26) ማንም ሰው ምንም አንደማይጠቅም አድርጎ ስለራሱ ማሰብ አይኖርበትም። በሌላ በኩል ደግሞ ሁላችንም ማለትም እረኞችም ሆንን በጎች ክርስቶስ ራስ የሆነለት አካል ክፍል እንደመሆናችን መጠን አንዳችን ከሌላው እንደምንልቅ ሆኖ ሊሰማን አይገባም። በዚህም የተነሳ ጳውሎስ እርስ በርስ ሊኖረን የሚገባውን ፍቅር፣ አሳቢነትና አክብሮት ግልጽ በሆነ መንገድ አስቀምጦታል። ሽማግሌዎች ይህን መገንዘባቸው በጉባኤው ውስጥ ስላላቸው ቦታ የትሕትናና ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲይዙ ይረዳቸዋል።

6. ጳውሎስ ሐዋርያዊ ሥልጣን ቢኖረውም እንኳ የትሕትና መንፈስ ያሳየው እንዴት ነበር?

6 እነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ የአምልኮ ባልደረቦቻቸውን ሕይወት ወይም እምነት ለመቆጣጠር አይፈልጉም። ጳውሎስ የሐዋርያነት ሥልጣን የነበረው ቢሆንም ራሱን ዝቅ በማድረግ “ለደስታችሁ ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን እንጂ፣ በእምነታችሁ በእናንተ ላይ የምንገዛ አይደለንም” በማለት ለክርስቲያኖች ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 1:​24) ጳውሎስ የወንድሞቹን እምነትና ሕይወት የመቆጣጠር ምኞት አልነበረውም። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚፈልጉ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የታቀፉ የታመኑ ወንዶችና ሴቶች መሆናቸውን አስቀድሞ በትምክህት ተናግሮ ስለነበር እንደዚያ የማድረጉ አስፈላጊነት ፈጽሞ አልታየውም። ስለዚህም ስለ ራሱና የጉዞ ባልደረባው ስለነበረው ስለ ጢሞቴዎስ ‘አምላክን በደስታ ለማገልገል ከእናንተ ጋር የምንሠራ ነን’ ብሎ ለመናገር ችሏል። (2 ቆሮንቶስ 1:​1) እንዴት ያለ የትሕትና መንፈስ ነው!

7. ትሑት የሆኑ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ስላላቸው ቦታ ምን ነገር ይገነዘባሉ? በሥራ ባልደረቦቻቸው ላይስ ምን ዓይነት ትምክህት አላቸው?

7 በዛሬ ጊዜ ያሉ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችም’ ተመሳሳይ የሆነ ነገር እንዲያደርጉ ይጠበቅባቸዋል። ‘ለደስታችን ከእኛ ጋር አብረው የሚሠሩ’ ናቸው። ትሑት የሆኑ ሽማግሌዎች ሌሎች በአምላክ አገልግሎት ምን ያክል መሥራት እንዳለባቸው የመወሰን መብት እንዳልተሰጣቸው ይገነዘባሉ። አገልግሎታቸውን እንዲያሰፉ ወይም እንዲያሻሽሉ ማበረታቻ የሚሰጡ ቢሆኑም ለአምላክ የሚ​ቀርብ አገልግሎት ፈቃደኛ ከሆነ ልብ ተፈ​ንቅሎ መውጣት እንዳለበት ያውቃሉ። (ከ2 ቆሮንቶስ 9:​7 ጋር አወዳድር።) የሥራ ባልደረቦቻቸው ደስተኞች ከሆኑ አቅማቸው የፈቀደላቸውን ያክል እንደሚሠሩ ሙሉ እምነት አላቸው። ስለዚህ የእነሱ ልባዊ ምኞት ወንድሞቻቸው ‘አምላክን በደስታ እንዲያገለግሉ’ መርዳት ነው።​—⁠መዝሙር 100:​2 የ1980 ትርጉም

በደስታ እንዲያገለግሉ ሁሉንም መርዳት

8. ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸው ይሖዋን በደስታ እንዲያገለግሉ የሚረዱባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?

8 እናንት ሽማግሌዎች፣ ወንድሞቻችሁ በደስታ እንዲያገለግሉ እንዴት ልትረዷቸው ትችላላችሁ? ምሳሌ በመሆን ማበረታቻ ልትሰጡ ትችላላችሁ። (1 ጴጥሮስ 5:​3) ለአገልግሎቱ ያላችሁ ቅንዓትና ደስታ ግልጽ ሆኖ የሚታይ ይሁን፤ በዚህም የተነሳ ሌሎች የእናንተን ምሳሌ ለመከተል ሊነሳሱ ይችላሉ። በሙሉ ነፍስ ለሚያደርጉት ጥረት አመስግኗቸው። (ኤፌሶን 4:​29) ሞቅ ያለና ከልብ የመነጨ ምስጋና ሌሎች ጠቃሚና ተፈላጊ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ይረዳል። በጎቹ አምላክን ለማገልገል የተቻላቸውን ሁሉ የማድረግ ፍላጎት እንዲያዳብሩ ያበረታታቸዋል። አሉታዊ በሆነ መንገድ አታወዳድሩ። (ገላትያ 6:​4) አንዱን ከሌላው ማወዳደሩ ሌሎች እንዲሻሻሉ ከማድረግ ይልቅ ተስፋ እንዲቆርጡ ያደርጋቸዋል። ከዚህም በላይ የይሖዋ በጎች የተለያየ ዓይነት ሁኔታና ችሎታ ያላቸው ግለሰቦች ናቸው። ልክ እንደ ጳውሎስ ወንድሞቻችሁን እንደምትተማመኑባቸው ግለጹላቸው። ፍቅር ‘ሁሉን ስለሚያምን’ ወንድሞቻችን አምላክን እንደሚወዱና እርሱን የማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ጠንካራ እምነት አለን። (1 ቆሮንቶስ 13:​7) ‘አክብሮት ስታሳዩአቸው’ አቅማቸው የሚፈቅደውን ሁሉ ለማድረግ ይነሳሳሉ። (ሮሜ 12:​10) በጎቹ ማበረታቻና ማነቃቂያ ከተሰጣቸው ብዙዎቹ በአምላክ አገልገሎት የቻሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉና ከአገልግሎቱም ደስታ እንደሚያገኙ እርግጠኞች ሁኑ።​—⁠ማቴዎስ 11:​28-30

9. እያንዳንዱ ሽማግሌ በደስታ ማገልገል እንዲችል ሁሉም ሽማግሌዎች የትኛውን አመለካከት መያዛቸው ይጠቅማቸዋል?

9 ‘የሥራ ባልደረቦች’ እንደሆናችሁ አድርጋችሁ ራሳችሁን በትሕትና መመልከታችሁ በደስታ እንድታገለግሉና ሌሎች ሽማግሌዎች ያላቸውን ልዩ ስጦታ እንድታደንቁ ይረዳችኋል። እያንዳንዱ ሽማግሌ ጉባኤውን ለመጥቀም ሊሠራበት የሚችል የራሱ የሆነ ተሰጥኦና ችሎታ አለው። (1 ጴጥሮስ 4:​10) አንዱ የማስተማር ተሰጥኦ ይኖረው ይሆናል። ሌላው ደግሞ ጥሩ አደራጅ ሊሆን ይችላል። ሌላው ደግሞ በሚያሳየው ሞቅ ያለ መንፈስና ርኅራኄ በቀላሉ የሚቀረብ ዓይነት ሰው ሊሆን ይችላል። ሁሉንም ዓይነት ተሰጥኦ በእኩል ደረጃ የያዘ ሽማግሌ የለም። ታዲያ አንድ ሽማግሌ አንድ ተሰጥዖ እንበል የማስተማር ተሰጥዖ ቢኖረው ከሌሎች ልቆ እንዲታይ ያደርገዋልን? በጭራሽ! (1 ቆሮንቶስ 4:​7) በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሽማግሌ ባለው ልዩ ተሰጥኦ መመቅኘት ወይም በችሎታው ምክንያት ሌሎች ሲያደንቁት እኛ ምንም እንደማንጠቅም ሆኖ ሊሰማን አይገባም። ይሖዋ የሚያየው አንድ ዓይነት ተሰጥኦ እንዳላችሁ አትዘንጉ። ይሖዋም እነዚህን ልዩ ተሰጥዖዎች እንድታዳብሩና ወንድሞቻችሁን ለመርዳት እንድትጠቀሙበት ሊረዳችሁ ይችላል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​13

‘ታዛዦችና ተገዥዎች ሁኑ’

10. ‘ስጦታ ለሆኑ ወንዶች’ ያለንን አድናቆት መግለጹ ተገቢ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

10 አንድ ስጦታ ስናገኝ አድናቆታችንን መግለጻችን የሚጠበቅ ነገር ነው። ቆላስይስ 3:​15 “የምታመሰግኑም ሁኑ” ይላል። ታዲያ ይሖዋ ለሰጠን ውድ ስጦታ ማለትም ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ በተመለከተስ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? እርግጥ ነው በአንደኛ ደረጃ የምናመሰግነው ደግ ሰጭ የሆነውን ይሖዋን ነው። ይሁን እንጂ ‘ስጦታ ለሆኑት ወንዶችስ?’ እንደምናደንቃቸው ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው?

11. (ሀ) ‘ስጦታ ለሆኑ ወንዶች’ ያለንን አድናቆት እንዴት መግለጽ እንችላለን? (ለ) “ታዘዙ” እና “ተገዙ” የሚሉት አባባሎች ምን ትርጉም አላቸው?

11 ሽማግሌዎች የሚሰጡንን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ምክሮች ለመቀበልና የሚያደርጓቸውን ውሳኔዎች ለማክበር ፈጣኖች በመሆን ‘ስጦታ ለሆኑ ወንዶች’ ያለንን አድናቆት ልናሳይ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ይመክረናል:- “ለዋኖቻችሁ [“ግንባር ቀደም ሆነው ለሚያገለግሏችሁ፣” NW] ታዘዙና ተገዙ፤ እነርሱ ስሌትን እንደሚሰጡ አድርገው፣ ይህንኑ በደስታ እንጂ በኃዘን እንዳያደርጉት፣ ይህ የማይጠቅማችሁ ነበርና፣ ስለ ነፍሳችሁ ይተጋሉ።” (ዕብራውያን 13:​17) ግንባር ቀደም ሆነው ለሚያገለግሉት ‘መታዘዝ’ ብቻ ሳይሆን ‘መገዛትም’ እንዳለብን ልብ በሉ። “መገዛት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል፣ ቃል በቃል ሲተረጎም “በ . . . ሥር ሆኖ በእሽታ መታዘዝ” ማለት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት አር ሲ ኤች ሌንስኪ “ታዘዙ” እና “ተገዙ” በሚሉት ቃላት ላይ ሐሳብ ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ሰው እንዲያደርግ በተነገረው ነገር ሲስማማ እንዲሁም የነገሩን ትክክለኛነትና የሚያስገኘውን ጥቅም ሲያምንበት ይታዘዛል፤ . . . የተለየ አመለካከት ቢኖረውም እንኳ በእሽታ ይታዘዛል።” ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች የሰጡን መመሪያ ግልጽ ሆኖ ከገባንና ከተስማማንበት ያለ አንዳች ማንገራገር እንታዘዝ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከውሳኔው በስተጀርባ ያለው ምክንያት ባይገባንስ?

12. አንድ ውሳኔ የተላለፈበት ምክንያት ሙሉ በሙሉ ባይገባን እንኳ ተገዥ ወይም እሺ ባይ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

12 ታዛዦች ወይም እሺ ባዮች መሆን ያለብን በዚህ ወቅት ነው። ለምን? ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት ብቃት ያላቸው እነዚህ መንፈሳዊ ወንዶች ከልባቸው ስለሚጨነቁልን እንደሆነ ማመን ይኖርብናል። ደግሞም እንዲጠብቋቸው ስለተሰጧቸው በጎች ለይሖዋ መልስ እንደሚሰጡ ጠንቅቀው ያውቃሉ። (ያዕቆብ 3:​1) ከዚህም በተጨማሪ ወደ እዚህ ውሳኔ እንዲደርሱ ያደረጓቸው እኛ የማናውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማስታወስ ይኖርብናል።​—⁠ምሳሌ 18:​13

13. ሽማግሌዎች ለሚያስተላልፉት የፍርድ ውሳኔ ተገዥ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

13 ለፍርድ ውሳኔዎች ተገዥ መሆንን በተመለከተስ? በተለይም ውሳኔው የምንወደውን ሰው ማለትም ዘመዳችንን ወይም የቅርብ ጓደኛችንን ማስወገድ ከሆነ ውሳኔውን መቀበል ልንቸገር እንችላለን። አሁንም ቢሆን ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ያሳለፉትን ውሳኔ እሺ ብሎ መቀበሉ ከሁሉ የተሻለ ነው። እነሱ ከእኛ ይልቅ ሐቁን የማወቅም ሆነ ጉዳዩን ይበልጥ የማገናዘብ አጋጣሚ አላቸው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ወንድሞች እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ብዙ ይጨነቃሉ፤ ‘ይሖዋን ወክሎ ፍርድ መስጠት’ ከባድ ኃላፊነት ነው። (2 ዜና መዋዕል 19:​6) አምላክ ‘ይቅር ባይ’ መሆኑን ስለሚያውቁ ምሕረት ለማሳየት የሚያስችሉ መንገዶችን ሁሉ ይፈልጋሉ። (መዝሙር 86:​5) ሆኖም ጉባኤውን ንጹሕ አድርገው መጠበቅ ስለሚኖርባቸው ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞችን እንዲያስወግዱም መጽሐፍ ቅዱስ ያዝዛቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 5:​11-13) ብዙውን ጊዜ ኃጢአተኛው ራሱ ውሳኔውን ይቀበላል። ወደ አእምሮው እንዲመለስ የሚያደርገው ብቸኛ መንገድ እንዲህ ያለው ቅጣት ሊሆን ይችላል። በምንወደው ግለሰብ ላይ የተላለፈውን ውሳኔ ተቀብለን ለውሳኔው ራሳችንን የምናስገዛ ከሆነ ግለሰቡ ከተሰጠው ተግሳጽ ተጠቃሚ እንዲሆን እየረዳነው ነው ማለት ነው።​—⁠ዕብራውያን 12:​11

“ከመጠን ይልቅ አክብሯቸው”

14, 15. (ሀ) በ1 ተሰሎንቄ 5:​12, 13 መሠረት ለሽማግሌዎች አሳቢነት ልናሳያቸው የሚገባን ለምንድን ነው? (ለ) ሽማግሌዎች ‘በመካከላችን ይደክማሉ’ ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?

14 ‘ስጦታ ለሆኑ ወንዶች’ አሳቢ በመሆን ለእነርሱ ያለንን አድናቆት ልናሳይ እንችላለን። ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚገኘው ጉባኤ ሲጽፍ የጉባኤውን አባላት እንዲህ በማለት መክሯል:- “በመካከላችሁ የሚደክሙትን በጌታም የሚገዙአችሁን የሚገሥጹአችሁንም . . . በፍቅር ከመጠን ይልቅ [አክብሯቸው።]” (1 ተሰሎንቄ 5:​12, 13) “የሚደክሙትን” የሚለው አገላለጽ ራሳቸውን ምንም ሳይቆጥቡ ለእኛ የሰጡትን ሽማግሌዎች ጥሩ አድርጎ የሚገልጽ አይደለምን? እነዚህ የተወደዱ ወንድሞች የተሸከሙትን ከባድ ሸክም እስቲ ለአንድ አፍታ እንመልከት።

15 ብዙውን ጊዜ ሽማግሌዎች ቤተሰብ ያላቸው በመሆናቸው የቤተሰባቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሰብዓዊ ሥራ መሥራት አለባቸው። (1 ጢሞቴዎስ 5:​8) ሽማግሌው ልጆች ካሉት ደግሞ ልጆቹ የአባታቸውን ጊዜና ትኩረት ይሻሉ። በትምህርት ቤት ሥራቸው ሊያግዛቸው እንዲሁም የወጣትነት ጉልበታቸው ጤናማ በሆነ መዝናኛ እንዲታደስ ለማድረግ ጊዜ መድቦ ልጆቹን ማዝናናት ይኖርበታል። (መክብብ 3:​1, 4) ከሁሉም በላይ ደግሞ ለቤተሰቡ ዘወትር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት፣ አብሯቸው በመስክ አገልግሎት በመሥራትና ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ይዟቸው በመሄድ የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት መንከባከብ ይኖርበታል። (ዘዳግም 6:​4-7፤ ኤፌሶን 6:​4) ሽማግሌዎች ብዙዎቻችን ካሉብን ከእነዚህ የተለመዱ ኃላፊነቶች በተጨማሪ ሌሎች ኃላፊነቶች እንዳሉባቸው መዘንጋት የለብንም። በስብሰባ ላይ ለሚቀርቡ ክፍሎች ይዘጋጃሉ፤ የእረኝነት ጉብኝት ያደርጋሉ፤ የጉባኤውን መንፈሳዊ ደህንነት ይጠብቃሉ እንዲሁም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ፍርድ ነክ ጉዳዮችን ይመለከታሉ። አንዳንዶች ደግሞ ከወረዳ ስብሰባዎች፣ ከአውራጃ ስብሰባዎች፣ ከመንግሥት አዳራሽ ግንባታና ከሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ጋር የተያያዙ ተጨማሪ ኃላፊነቶች አሉባቸው። በእርግጥም እነዚህ ወንድሞች ‘ብዙ ይደክማሉ!’

16. ለሽማግሌዎች ያለንን አሳቢነት ልናሳይ የምንችልባቸውን መንገዶች ግለጽ።

16 አሳቢነታችንን ልናሳይ የምንችለው እንዴት ነው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ቃልም በጊዜው ምንኛ መልካም ነው!” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 15:​23፤ 25:​11) ከልብ በመነጨ ስሜት የምንገልጽላቸው የአድናቆትና የማበረታቻ ቃላት የሚያከናውኑትን ትጋት የተሞላበት ሥራ እንዲሁ በቀላሉ እንደማንመለከተው ሊያሳይ ይችላል። በተጨማሪም ከእነርሱ በምንጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ መሆን ይገባል። እርግጥ ከእነርሱ እርዳታ ለማግኘት ያለ ምንም ፍርሃት በነፃነት ልንቀርባቸው ይገባናል። ‘ልባችን የሚናወጥበትና’ የአምላክን ቃል ‘በማስተማር በኩል ብቃቱ ካላቸው’ ወንድሞች ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ፣ መመሪያ ወይም ምክር ማግኘት የሚያስፈልገን ወቅት ሊኖር ይችላል። (መዝሙር 55:​4፤ 1 ጢሞቴዎስ 3:​2) በአንጻሩ ደግሞ አንድ ሽማግሌ ቤተሰቡም ሆነ ጉባኤው የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ችላ ብሎ ማለፍ ስለማይችል ለእኛ ሊኖረው የሚችለው ጊዜ በጣም ውስን እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ብዙ ለሚደክሙት ለእነዚህ ወንድሞች ያዳበርነው ‘የወንድማማች ፍቅር’ ከመጠን በላይ እንዳንጠብቅባቸው ያደርገናል። (1 ጴጥሮስ 3:​8) ከዚያ ይልቅ ምክንያታዊ ሆነው የሚሰጡን ጊዜም ሆነ ትኩረት ምንም ያክል ይሁን ምን አድናቂዎች እንሁን።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​5

17, 18. ሽማግሌ ባል ያላቸው ሚስቶች ምን ዓይነት መሥዋዕቶችን ይከፍላሉ? እነዚህ ታማኝ እህቶች የሚከፍሉትን መሥዋዕት አንደቀላል እንደማንቆጥረው እንዴት ልናሳይ እንችላለን?

17 ስለ ሽማግሌ ሚስቶችስ ምን ለማለት ይቻላል? ለእነርሱስ ቢሆን አሳቢነት ልናሳያቸው አያስፈልግምን? ጉባኤው ባሎቻቸውን ይጋራባቸዋል። ይህም የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት እንዲያደርጉ ይጠይቅባቸዋል። አልፎ አልፎ ሽማግሌዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሊያሳልፉት የሚችሉትን ምሽት ለጉባኤ ጉዳዮች እንዲያውሉ የሚገደዱበት ጊዜ አለ። በብዙ ጉባኤዎች የሚገኙ የታመኑ ክርስቲያን ሴቶች እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች በመሆናቸው ምክንያት ባሎቻቸው የይሖዋን በጎች እንዲንከባከቡ አስችሏቸዋል።​—⁠ከ2 ቆሮንቶስ 12:​15 ጋር አወዳድር።

18 እነዚህ ታማኝ ክርስቲያን እህቶች የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ እንደ ቀላል እንደማንመለከተው እንዴት ልናሳይ እንችላለን? በትንሹም በትልቁም ባሎቻቸውን ባለማስቸገር እንደሚሆን ግልጽ ነው። ጥቂት የአድናቆት ቃላት መሰንዘሩም ያለውን ኃይል አቅልለን መመልከት አይኖርብንም። ምሳሌ 16:​24 እንዲህ ይላል:- “ያማረ ቃል የማር ወለላ ነው፤ ለነፍስ ጣፋጭ ለአጥንትም ጤና ነው።” አንድ ምሳሌ ተመልከቱ። ከአንድ ክርስቲያናዊ ስብሰባ በኋላ አንድ ባልና ሚስት ወደ አንድ ሽማግሌ ቀርበው በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ስለሚገኝ ልጃቸው ሊያነጋግሩት እንደሚፈልጉ ይነግሩታል። ሽማግሌው ከባልና ሚስቱ ጋር እየተነጋገረ ሳለ ባለቤቱ ፈንጠር ብላ ትጠብቀው ነበር። ውይይቱ እንዳበቃ እናትየው ወደ ሽማግሌው ሚስት ቀርባ “ባለቤትሽ ቤተሰቤን ለመርዳት ሲል ለወሰደው ሰዓት ላመሰግንሽ እፈልጋለሁ” አለቻት። እነዚህ ቀላልና አስደሳች የአድናቆት ቃላት የሽማግሌውን ሚስት ልብ በእጅጉ ነክተዋል።

19. (ሀ) ሽማግሌዎች በቡድን ደረጃ የትኞቹን ሥራዎች በመፈጸም ላይ ናቸው? (ለ) ሁላችንም ምን ለማድረግ መቁረጥ ይኖርብናል?

19 ከይሖዋ ‘መልካም ስጦታዎች’ መካከል አንዱ በጎችን እንዲጠብቁ የተደረገው የሽማግሌዎች ዝግጅት ነው። (ያዕቆብ 1:​17) እነዚህ ወንዶች ፍጹማን አለመሆናቸው የታወቀ ነው። እኛ ሁላችን እንደምንሳሳት ሁሉ እነሱም ይሳሳታሉ። (1 ነገሥት 8:​46) ሆኖም በዓለም ዙሪያ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች በቡድን ደረጃ መንጋውን በማስተካከል፣ በመገንባት፣ አንድ በማድረግና በመጠበቅ ይሖዋ የሚፈልግባቸውን ሥራ በታማኝነት በመፈጸም ላይ ናቸው። እያንዳንዱ ሽማግሌ የይሖዋን በግ በርኅራኄ ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ለወንድሞች የተሰጠ ገጸ በረከት መሆኑን ያረጋግጥ። እንዲሁም የተቀረነው ሁላችንም ለሽማግሌዎች ታዛዥና ተገዥ በመሆንና ለሚያከናውኑት ትጋት የተሞላበት ሥራ ያለንን አሳቢነት በማሳየት ‘ስጦታ ለሆኑት ወንዶች’ ያለንን አድናቆት ለመግለጽ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ይሖዋ በፍቅሩ ተገፋፍቶ ‘ከእናንተ ጋር በደስታ አብረን የምንሠራ ነን’ ብለው ለበጎቹ ሊናገሩ የሚችሉ ወንዶችን በመስጠቱ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

◻ ጉባኤ ከአካል ጋር በትክክል ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው?

◻ ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸው ይሖዋን በደስታ እንዲያገለግሉ እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ?

◻ ግንባር ቀደም ሆነው ለሚያገለግሉት መታዘዝ ብቻ ሳይሆን መገዛትም ያለብን ለምንድን ነው?

◻ ለሽማግሌዎች ያለንን አድናቆት በምን በምን መንገድ ልናሳይ እንችላለን?

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች፣ ሌሎች በሙሉ ነፍስ ለሚያደርጉት ጥረት አመስግኗቸው

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎች በአገልግሎት በሚያሳዩት ቅንዓት የተሞላበት ምሳሌ የቤተሰብ አባሎችም ሆኑ ሌሎች በደስታ እንዲያገለግሉ ሊረዱ ይችላሉ

[በገጽ 18 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

በመካከላችን የሚደክሙትን ሽማግሌዎች እናደንቃቸዋለን!

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ