የይሖዋን በጎች እንዲጠብቁ የተሾሙ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’
“ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን [“ወንዶችን ስጦታ አድርጎ፣” NW] ሰጠ።”—ኤፌሶን 4:8
1. አንዲት እህት በጉባኤዋ ስላሉ ሽማግሌዎች ምን ብላ ተናገረች?
“ስለ እኛ በጣም ስለምታስቡና ስለምትጨነቁ እናመሰግናችኋለን። ፈገግታችሁ፣ ፍቅራችሁና አሳቢነታችሁ ከልብ የመነጨ ነው። እኛን ለማዳመጥና መንፈሳችንን የሚያነቃቁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላት ወርወር ለማድረግ ሁልጊዜ ዝግጁዎች ናችሁ። ለእናንተ ያለኝ ከፍ ያለ ግምት እንዳይቀንስ ዘወትር እጸልያለሁ።” አንዲት ክርስቲያን እህት በጉባኤዋ ለሚገኙት ሽማግሌዎች የጻፈችው ደብዳቤ ይህን የሚመስል ነበር። አሳቢ የሆኑ ክርስቲያን እረኞች በሚያሳዩት ፍቅር ልቧ በጣም እንደተነካ ግልጽ ነው።—1 ጴጥሮስ 5:2, 3
2, 3. (ሀ) በኢሳይያስ 32:1, 2 መሠረት ሩኅሩኅ ሽማግሌዎች የይሖዋን በጎች የሚጠብቁት እንዴት ነው? (ለ) አንድ ሽማግሌ እንደ ስጦታ ተደርጎ ሊታይ የሚችለው በምን ወቅት ነው?
2 ሽማግሌዎች ይሖዋ በጎቹን ለመጠበቅ ያደረገው ዝግጅት ናቸው። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐንስ 10:16) ይሖዋ በጎቹን በጣም ይወድዳቸዋል፤ ለእነርሱ ካለው ፍቅር የተነሳም ውድ በሆነው የኢየሱስ ደም ገዝቷቸዋል። ስለዚህ ሽማግሌዎች በጎቹን በርኅራኄ ሲጠብቁ ይሖዋ የሚደሰት መሆኑ ምንም አያጠራጥርም። (ሥራ 20:28, 29) እነዚህን ሽማግሌዎች ወይም ‘መሳፍንት’ በተመለከተ የተነገረውን ትንቢታዊ መግለጫ ልብ በሉ:- “ሰውም ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ፣ በጥም ቦታም እንደ ወንዝ ፈሳሽ፣ በበረሀም አገር እንደ ትልቅ ድንጋይ ጥላ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 32:1, 2) አዎን፣ የይሖዋን በጎች ይጠብቃሉ፣ ያነቃቃሉ እንዲሁም ያጽናናሉ። ስለዚህም መንጋውን በርኅራኄ የሚጠብቁ እረኞች አምላክ የሚጠብቅባቸውን ነገር ለማድረግ የተቻላቸውን ያህል ይጥራሉ።
3 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ተብለው የተጠቀሱት እንዲህ ያሉት ሽማግሌዎች ናቸው። (ኤፌሶን 4:8 NW) ስጦታ ሲባል ወደ አእምሮህ የሚመጣው ስጦታ ተቀባዩ በጣም የሚያስፈልገውን ወይም የሚያስደስተውን ነገር ማግኘቱ ነው። አንድ ሽማግሌ አስፈላጊውን እርዳታ ለመስጠትና መንጋው ደስታ እንዲያገኝ አስተዋጽኦ ለማበርከት ችሎታውን ሲጠቀምበት እንደ ስጦታ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ይህንን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ለበጎቹ ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት ጎላ አድርገው የሚገልጹት ኤፌሶን 4:7-16 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የጳውሎስ ቃላት መልሱን ይሰጡናል።
‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ የሰጠው ማን ነው?
4. በመዝሙር 68:18 ፍጻሜ መሠረት ይሖዋ ‘ወደ ላይ የወጣው’ በምን መንገድ ነው? ‘ስጦታ ሆነው የተሰጡት ወንዶችስ’ እነማን ነበሩ?
4 ጳውሎስ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ብሎ ሲናገር “ወደ ላይ ዓረግህ፣ ምርኮን ማረክህ፣ ስጦታንም [“ወንዶችንም ስጦታ አድርገህ፣” NW] ለሰዎች ሰጠህ” በማለት ንጉሥ ዳዊት ስለ ይሖዋ የተናገራቸውን ቃላት መጥቀሱ ነበር። (መዝሙር 68:18) እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከገቡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ ወደ ጽዮን ተራራ ‘ዓረገና’ ዳዊትን ንጉሥ አድርጎ በመሾም ኢየሩሳሌምን የእስራኤል መንግሥት ዋና ከተማ አደረገ። ይሁን እንጂ እዚህ ላይ የተጠቀሱት ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ እነማን ነበሩ? የተስፋይቱ ምድር ድል በተደረገች ጊዜ በምርኮ የተያዙት ወንዶች ናቸው። ከእነዚህ ምርኮኞች መካከል ጥቂቶቹ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በሚከናወነው ሥራ እንዲረዱ ለሌዋውያን ተሰጥተው ነበር።—ዕዝራ 8:20
5. (ሀ) ጳውሎስ መዝሙር 68:18 በክርስቲያን ጉባኤ ላይ ፍጻሜ እንዳለው ያመለከተው እንዴት ነው? (ለ) ኢየሱስ ‘ወደ ሰማይ የወጣው’ በምን ዓይነት መንገድ ነው?
5 ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ መዝሙራዊው የተናገራቸው ቃላት በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የላቀ ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው አመልክቷል። ጳውሎስ የመዝሙር 68:18ን ሐሳብ በመጥቀስ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን። ስለዚህ:- ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም [“ወንዶችን ስጦታ አድርጎ፣” NW] ሰጠ ይላል።” (ኤፌሶን 4:7, 8) ጳውሎስ ይህን መዝሙር የአምላክ ወኪል በሆነው በኢየሱስ ላይ እንደሚሠራ አድርጎ ገልጾታል። ኢየሱስ በታማኝነት በመመላለስ ‘ዓለምን አሸንፏል።’ (ዮሐንስ 16:33) በተጨማሪም አምላክ ከሞት ስላስነሳው በሞትና በሰይጣን ላይ ድል ተቀዳጅቷል። (ሥራ 2:24፤ ዕብራውያን 2:14) በ33 እዘአ ትንሣኤ ያገኘው ኢየሱስ “ከሰማያት ሁሉ በላይ” ማለትም ከሰማያዊ ፍጥረታት ሁሉ በላይ ወጥቷል። (ኤፌሶን 4:9, 10፤ ፊልጵስዩስ 2:9-11) ኢየሱስ እንደ አንድ ድል አድራጊ ከጠላቶቹ “ምርኮን” ማርኳል። እንዴት?
6. ወደ ላይ የወጣው ኢየሱስ በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ የሰይጣንን ቤት መበዝበዝ የጀመረው እንዴት ነው? “ምርኮኞቹንስ” ምን አደረጋቸው?
6 ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት በአጋንንት ተይዘው የነበሩትን ሰዎች በማዳን በሰይጣን ላይ ያለውን ኃይል አስመስክሯል። ኢየሱስ ይህን ሲያደርግ የሰይጣንን ቤት የወረረ፣ እርሱን ያሰረና ንብረቱን የወረሰ ያክል ነበር። (ማቴዎስ 12:22-29) ከሙታን የተነሳውና ‘በሰማይና በምድር ሥልጣን የተሰጠው’ ኢየሱስ ምን ያክል ሊበዘብዝ እንደሚችል አስቡ! (ማቴዎስ 28:18) ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ የአምላክ ወኪል በመሆን በ33 እዘአ ከዋለው ከጴንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ ለረዥም ጊዜያት በኃጢአትና በሞት ባርነት እንዲሁም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር የነበሩትን ወንዶች ‘ማርኮ በመውሰድ’ የሰይጣንን ቤት መበዝበዝ ጀመረ። እነዚህ ‘ምርኮኞች’ በፈቃደኝነት ‘የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሙሉ ነፍስ የሚያከናውኑ የክርስቶስ ባሪያዎች’ ሆነዋል። (ኤፌሶን 6:6) ኢየሱስ ከሰይጣን ቁጥጥር ሥር መንጥቆ በማውጣት እንደ ይሖዋ ፍላጎት ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ አድርጎ ለጉባኤ የሰጣቸው ያክል ነበር። ሰይጣን ንብረቶቹ ከጉያው ውስጥ ተነጥቀው ሲወሰዱበት ምን ያክል እንደሚቆጣ ልትገምቱ ትችላላችሁ!
7. (ሀ) ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ በጉባኤ ውስጥ በምን ኃላፊነት ይሠራሉ? (ለ) ይሖዋ ሽማግሌ ሆኖ ለሚያገለግል ለእያንዳንዱ ወንድ ምን አጋጣሚ ሰጥቷል?
7 እነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ በዛሬው ጊዜ ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ እናገኛቸዋለን? አዎን፣ እናገኛቸዋለን! በዓለም ዙሪያ ከ87,000 በሚበልጡ በአምላክ ሕዝብ ጉባኤዎች ውስጥ ‘በወንጌላዊነት፣ በእረኝነትና በአስተማሪነት’ ጠንክረው በመሥራት በሽማግሌነት ሲያገለግሉ እናገኛቸዋለን። (ኤፌሶን 4:11) ሽማግሌዎቹ መንጋውን በጭከና የሚገዙ ቢሆኑ ኖሮ ሰይጣን በጣም ይደሰት ነበር። ሆኖም አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ለጉባኤው የሰጣቸው እንዲህ እንዲያደርጉ አይደለም። ይሖዋ እነዚህን ወንዶች የሰጠው የጉባኤውን ደህንነት እንዲጠብቁ ሲሆን እነርሱም በአደራ ለተሰጧቸው በጎች በእርሱ ፊት በኃላፊነት ተጠያቂዎች ናቸው። (ዕብራውያን 13:17) ሽማግሌ ሆነህ የምታገለግል ከሆነ ለወንድሞችህ የተሰጠህ ስጦታ ወይም በረከት መሆንህን ማረጋገጥ እንድትችል ይሖዋ ግሩም የሆነ አጋጣሚ ሰጥቶሃል። ይህንንም አራት አስፈላጊ የሆኑ ኃላፊነቶችን በመፈጸም ማሳየት ትችላለህ።
“ማስተካከል” አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ
8. ሁላችንም አልፎ አልፎ በምን በምን መንገዶች ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገናል?
8 አንደኛ፣ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ የተሰጡት “ቅዱሳንን ለማስተካከል” እንደሆነ ጳውሎስ ተናግሯል። (ኤፌሶን 4:12 NW) “ማስተካከል” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው ስም አንድን ነገር “ወደ ተገቢው ቦታ መመለስን” ያመለክታል። ሁላችንም ፍጽምና የሌለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን አስተሳሰባችን፣ ዝንባሌያችን ወይም ጠባያችን ከአምላክ አስተሳሰብና ፈቃድ ጋር እንዲስማማ በየጊዜው መስተካከልና “ወደ ተገቢው ቦታ መመለስ” ይኖርብናል። ይሖዋ በፍቅሩ ተገፋፍቶ አስፈላጊውን ማስተካከያ እንድናደርግ የሚረዱንን ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ሰጥቶናል። ይህን የሚያከናውኑት እንዴት ነው?
9. አንድ ሽማግሌ አንድን ስህተት የፈጸመ በግ እንዲስተካከል ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው?
9 አንድ ሽማግሌ በደል የፈጸመን ምናልባትም ‘ሳያውቀው የተሳሳተ እርምጃ የወሰደን’ አንድ በግ እንዲረዳ ሊጠየቅ ይችላል። እርዳታውን ሊሰጥ የሚችለው እንዴት ነው? ገላትያ 6:1 “እንደዚህ ያለውን ሰው በየውሃት መንፈስ አቅኑት” ይላል። አንድ ሽማግሌ ምክር በሚሰጥበት ጊዜ ሻካራ ቃላት በመጠቀም ስህተት የፈጸመውን ግለሰብ አይቆጣውም። ምክሩ፣ ምክር ተቀባዩን የሚያበረታታ እንጂ ‘የሚያስፈራራ’ መሆን የለበትም። (2 ቆሮንቶስ 10:9 የ1980 ትርጉም፤ ከኢዮብ 33:7 ጋር አወዳድር።) ግለሰቡ ራሱ በሠራው ድርጊት አፍሮ ሊሆን ስለሚችል አንድ አፍቃሪ እረኛ የግለሰቡን መንፈስ ሊሰብሩ የሚችሉ ቃላትን ከመሰንዘር ይቆጠባል። ምክር፣ ሌላው ቀርቶ ጠንካራ ተግሳጽ እንኳ በፍቅር አነሳሽነት የተሰጠና በፍቅራዊ መንገድ የቀረበ መሆኑ በግልጽ የሚታይ ከሆነ የተሳሳተውን ሰው አመለካከት ወይም አካሄድ ለማቃናት እንዲሁም ወደ ቀድሞ ሁኔታው ለመመለስ እንደሚረዳ እሙን ነው።—2 ጢሞቴዎስ 4:2
10. ሌሎችን ማስተካከል ምንን ይጨምራል?
10 ይሖዋ የሚያስተካክሉንን ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ የሰጠን ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የሚያነቃቁና ለሕዝቡ ምሳሌ ይሆናሉ በሚል ነው። (1 ቆሮንቶስ 16:17, 18፤ ፊልጵስዩስ 3:17) ሌሎችን ማስተካከል ማለት የተሳሳተ አካሄድ የሚከተሉትን ማረም ብቻ ሳይሆን ታማኝ የሆኑትም ከትክክለኛው ጎዳና እንዳይወጡ መርዳትንም የሚያካትት ነው።a የምንኖረው ተስፋ የሚያስቆርጡ በርካታ ችግሮች በሞሉበት ጊዜ እንደመሆኑ ብዙዎች ጸንተው እንዲቀጥሉ ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶች አስተሳሰባቸው ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር እንዲስማማ ጥንቃቄ የተሞላበት እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ታማኝ ክርስቲያኖች ጥልቅ ከሆነ የዋጋቢስነት ወይም የከንቱነት ስሜት ጋር ይታገላሉ። እነዚህ “የተጨነቁ ነፍሳት” ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይወዳቸውና ከልብ ተጨንቀው የሚያቀርቡትን አገልግሎት እንኳ እንደማይቀበል ሆኖ ሊሰማቸው ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 5:14 NW) ሆኖም ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ አምላክ ለአገልጋዮቹ ካለው ስሜት ፈጽሞ የራቀ ነው።
11. ሽማግሌዎች ከከንቱነት ስሜት ጋር የሚታገሉትን ለመርዳት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
11 ሽማግሌዎች እንደነዚህ ያሉትን ለመርዳት ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? ይሖዋ ለእያንዳንዱ አገልጋይ እንደሚያስብ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን አንብቡላቸው። እንዲሁም እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በእነርሱም ላይ እንደሚሠሩ አረጋግጡላቸው። (ሉቃስ 12:6, 7, 24) ይሖዋ እንዲያገለግሉት ወደ እርሱ እንደሳባቸውና ይህ ደግሞ ጥሩ ባሕርይ እንዳየባቸው የሚያሳይ መሆኑን እንዲገነዘቡ እርዷቸው። (ዮሐንስ 6:44) እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች በርካታ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችም ተመሳሳይ የሆነ ስሜት እንደሚሰማቸው አረጋግጡላቸው። ነቢዩ ኤልያስ በአንድ ወቅት በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ከመደቆሱ የተነሳ ሞትን ተመኝቶ ነበር። (1 ነገሥት 19:1-4) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የተቀቡ ክርስቲያኖች ልባቸው ‘ይፈርድባቸው’ ነበር። (1 ዮሐንስ 3:20) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት ታማኞች ‘የእኛው ዓይነት ስሜት’ እንደነበራቸው ማወቁ የሚያጽናና ነው። (ያዕቆብ 5:17 NW) ከዚህም በተጨማሪ በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ የወጡ የሚያበረታቱ ርዕሶችን ለእነዚህ ተስፋ ለቆረጡ ሰዎች ልትከልሱላቸው ትችላላችሁ። እነዚህ ሰዎች አጥተውት የነበረውን በራስ የመተማመን መንፈስ መልሰው እንዲያገኙ የምታደርጉትን ከፍቅር የመነጨ ጥረት ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ አድርጎ በሰጣችሁ አምላክ ዘንድ ፈጽሞ የሚረሳ አይደለም።—ዕብራውያን 6:10
መንጋውን “መገንባት”
12. “የክርስቶስን አካል እንዲገነቡ” የሚለው አባባል ምንን ያመለክታል? መንጋውን ለመገንባት የሚያስችለው ቁልፍ ምንድን ነው?
12 ሁለተኛ፣ “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” የተሰጡት “የክርስቶስን አካል እንዲገነቡ” ነው። (ኤፌሶን 4:12) እዚህ ላይ ጳውሎስ አንድ ምሳሌያዊ አገላለጽ ተጠቅሟል። “መገንባት” የሕንፃ ሥራን የሚያመለክት ሲሆን “የክርስቶስ አካል” ደግሞ የቅቡዓን የክርስቲያን ጉባኤ አባላት የሆኑ ሰዎችን ያመለክታል። (1 ቆሮንቶስ 12:27፤ ኤፌሶን 5:23, 29, 30) ሽማግሌዎች ወንድሞቻቸው በመንፈሳዊ ጠንካሮች እንዲሆኑ መርዳት ይኖርባቸዋል። ግባቸው መንጋውን ‘ማፍረስ ሳይሆን ማነጽ ነው።’ (2 ቆሮንቶስ 10:8) ‘ፍቅር የሚያንጽ’ በመሆኑ መንጋውን ለመገንባት የሚረዳው ዋነኛ ቁልፍ ፍቅር ነው።—1 ቆሮንቶስ 8:1
13. ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ማለት ምን ማለት ነው? ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌሎች ቦታ ማስቀመጣቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
13 ሽማግሌዎች መንጋውን ለመገንባት የሚረዳቸው አንደኛው የፍቅር ገጽታ ራስን በሌሎች ቦታ የማስቀመጥ ባሕርይ ማዳበራቸው ነው። ራስን በሌሎች ቦታ ማስቀመጥ ማለት ለሌሎች ከልብ ማዘን ሲሆን ይህም ያለባቸውን የአቅም ገደብ ግምት ውስጥ በማስገባት አስተሳሰባቸውንና ስሜታቸውን ለይቶ ማወቅ ማለት ነው። (1 ጴጥሮስ 3:8) ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌሎች ቦታ ማስቀመጣቸው በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ዋናው ምክንያት ‘ወንዶችን ስጦታ’ አድርጎ የሰጠው ይሖዋ ስለ ሌሎች ከልቡ የሚያስብ በመሆኑ ነው። አገልጋዮቹ ሲሰቃዩ ሥቃያቸው ይሰማዋል። (ዘጸአት 3:7፤ ኢሳይያስ 63:9) የአቅማቸውን ውስንነት ግምት ውስጥ ያስገባል። (መዝሙር 103:14) ታዲያ ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌላው ቦታ የሚያስቀምጡ መሆናቸውን ሊያሳዩ የሚችሉት እንዴት ነው?
14. ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌሎች ቦታ የሚያስቀምጡ መሆናቸውን ሊያሳዩ የሚችሉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?
14 አንድ ተስፋ የቆረጠ ሰው ሊያነጋግራቸው ሲመጣ በጥሞና በማዳመጥ ስሜቱን ለመረዳት ይሞክራሉ። የወንድሞቻቸውን አስተዳደግ፣ ባሕርይና ያሉበትን ሁኔታ ለመረዳት ይጥራሉ። ከዚያም ሽማግሌዎች ገንቢ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ እርዳታ በሚሰጧቸው ጊዜ በጎቹ ችግሮቻቸውን ከሚረዱላቸውና ከሚያስቡላቸው እረኞች የመጣ በመሆኑ እርዳታቸውን ያለ ችግር ይቀበላሉ። (ምሳሌ 16:23) በተጨማሪም ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌላው ቦታ ማስቀመጣቸው የሌሎችን የአቅም ገደቦችና በዚህም ሳቢያ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ስሜቶች ግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ይገፋፋቸዋል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ትጉህ ክርስቲያኖች በእድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል ምክንያት ሊሆን ይችላል በአምላክ አገልግሎት የሚፈልጉትን ያክል ከፍተኛ ድርሻ ማበርከት ባለመቻላቸው የተነሳ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸው ይሆናል። ሌሎች ደግሞ አገልግሎታቸውን ለማሻሻል ማበረታቻ ማግኘት ያስፈልጋቸው ይሆናል። (ዕብራውያን 5:12፤ 6:1) ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌላው ቦታ ማስቀመጣቸው ገንቢ የሆኑ ‘ያማሩ ቃላትን’ እንዲናገሩ ይገፋፋቸዋል። (መክብብ 12:10) የይሖዋ በጎች የሚያንጻቸውና ከልባቸው የሚያነሳሳቸው ነገር ካገኙ እርሱን ለማገልገል የቻሉትን ሁሉ ያደርጋሉ!
አንድነትን የሚያሰፍኑ ወንዶች
15. ‘በእምነት አንድ መሆን’ የሚለው አባባል ምን ነገርን ያመለክታል?
15 ሦስተኛ፣ “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማወቅና በማመን ወደሚገኝ አንድነት” መድረስ እንችል ዘንድ “ስጦታ የሆኑ ወንዶች” ተሰጥተውናል። (ኤፌሶን 4:13) ‘በእምነት አንድ መሆን’ የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው በእምነት መመሳሰልን ብቻ ሳይሆን በአማኞች መካከል ሊኖር የሚገባውን አንድነት ጭምር ነው። አምላክም ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ የሰጠበት ሌላኛው ምክንያት በሕዝቦቹ መካከል አንድነት እንዲሰፍን ለማድረግ ነው። ሽማግሌዎች ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?
16. ሽማግሌዎች በመካከላቸው አንድነት እንዲኖር ማድረጋቸው አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
16 በመጀመሪያ ደረጃ ራሳቸው ሽማግሌዎቹ በመካከላቸው አንድነት ሊኖር ይገባል። በእረኞቹ መካከል መከፋፈል ካለ በጎቹ ችላ ሊባሉ ይችላሉ። መንጋውን በእረኝነት ለመጠበቅ ሊውል የሚችለው ውድ ጊዜ በተንዛዙ ስብሰባዎችና እርባና በሌላቸው ጉዳዮች ላይ በመጨቃጨቅ ሊባክን ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 2:8) ሽማግሌዎች በጣም የተለያዩ የየራሳቸው ባሕርያት ያላቸው በመሆናቸው ውይይት በሚያደርጉበት በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በቅጽበት ስምምነት ላይ ላይደርሱ ይችላሉ። አንድነት ሽማግሌዎች የተለያየ ዓይነት አመለካከት እንዳይኖራቸው ወይም ነፃ መድረክ ፈጥረው ስሜታቸውን በነፃነት እንዳይገልጡ አያግዳቸውም። ሽማግሌዎች ተቻኩለው ወደ መደምደሚያ ከመድረሳቸው በፊት አንዳቸው ሌላውን በአክብሮት በማዳመጥ አንድነታቸውን ይጠብቃሉ። እንዲሁም አንድም የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ እያንዳንዱ ሽማግሌ የሽማግሌዎች አካል ያሳለፈውን ውሳኔ ለመቀበልና ለመደገፍ ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል። ሽማግሌዎች ሐሳበ ግትር ከመሆን በመራቅ ‘ሰላማዊና ምክንያታዊ’ በሆነችው ‘በላይኛይቱ ጥበብ’ የሚመሩ መሆናቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ።—ያዕቆብ 3:17, 18 NW
17. ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን ሊረዱ የሚችሉት እንዴት ነው?
17 በተጨማሪም ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን ለማድረግ ንቁዎች ናቸው። እንደ ጎጂ ሐሜት፣ የሌሎችን ሐሳብ በመጥፎ የመተርጎም ወይም የተከራካሪነት መንፈስ የመሰሉ የሚከፋፍሉ ተጽዕኖዎች የጉባኤውን ሰላም አደጋ ላይ በሚጥሉበት ጊዜ ሽማግሌዎች ሳይዘገዩ ጠቃሚ ምክሮችን ይለግሳሉ። (ፊልጵስዩስ 2:2, 3) ለምሳሌ ያህል ሽማግሌዎች ከመጠን በላይ ስህተት የሚለቃቅሙ ወይም በሌሎች ጉዳይ ጥልቅ የሚሉ ግለሰቦች ያጋጥሟቸው ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 5:13፤ 1 ጴጥሮስ 4:15) ይህ አካሄዳቸው አምላክ ካስተማረን መንገድ ፈጽሞ የሚቃረን እንደሆነና እያንዳንዱ ግለሰብ “የገዛ ራሱን ሸክም” የመሸከም ኃላፊነት እንዳለበት እንዲገነዘቡ በማድረግ ሽማግሌዎች እነዚህን ሰዎች ሊረዷቸው ይሞክራሉ። (ገላትያ 6:5, 7፤ 1 ተሰሎንቄ 4:9-12) ቅዱሳን ጽሑፎችን በመጠቀም ይሖዋ በርካታ ነገሮችን ለእያንዳንዳችን ሕሊና እንደተወና በእነዚህ ጉዳዮች በሌሎች ላይ ፈጽሞ መፍረድ እንደማይኖርብን ሽማግሌዎች ያብራሩላቸዋል። (ማቴዎስ 7:1, 2፤ ያዕቆብ 4:10-12) በአንድነት አብሮ ለማገልገል በጉባኤ ውስጥ እርስ በርስ የመተማመንና የመከባበር መንፈስ ሊሰፍን ይገባል። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በመለገስ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ሰላማችንንና አንድነታችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዱናል።—ሮሜ 14:19
መንጋውን መጠበቅ
18, 19. (ሀ) ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ ከእነማን ይጠብቁናል? (ለ) በጎቹ ከሌላ ከምን አደጋ ጥበቃ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል? ሽማግሌዎች በጎቹን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
18 አራተኛ፣ ይሖዋ “እንደ ስሕተት ሽንገላ ባለ ተንኮል በሰዎችም ማታለል ምክንያት በትምህርት ነፋስ ሁሉ” ተሸንፈን እንዳንወድቅ “ወንዶችን ስጦታ አድርጎ” ሰጥቶናል። (ኤፌሶን 4:14) “ማታለል” የሚለው የመጀመሪያው ግሪከኛ ቃል “በኩብ ማጭበርበር” ወይም “በኩብ ጨዋታ የተካነ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ይህ አባባል ብልጣ ብልጥ የሆኑ ከሃዲዎች ሥራቸውን እንዴት አድርገው እንደሚያከናውኑ አያስታውሰንም? በአፈ ጮሌነት እውነተኛ ክርስቲያኖችን አባብለው ከእውነት እንዲወጡ ለማድረግ ቅዱሳን ጽሑፎችን አጣምመው ያቀርባሉ። ሽማግሌዎች እንደነዚህ ያሉ ‘ጨካኝ ተኩላዎችን’ በንቃት መከታተል አለባቸው!—ሥራ 20:29, 30
19 ከዚህም በተጨማሪ የይሖዋ በጎች ከሌላ አቅጣጫ ከሚሰነዘሩ ጥቃቶችም ጥበቃ ማግኘት ይኖርባቸዋል። የጥንቱ እረኛ ዳዊት በድፍረት የአባቱን መንጎች ከነጣቂ አራዊት ጠብቋል። (1 ሳሙኤል 17:34-36) በተመሳሳይም ዛሬ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክርስቲያን እረኞች የይሖዋን በጎች በተለይ ደግሞ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ደካሞችን ለማንገላታት ወይም ለመጨቆን የሚሞክሩ ሰዎችን በድፍረት መጠበቅ የሚያስፈልጓቸው ወቅቶች አልፎ አልፎ ሊነሱ ይችላሉ። ሽማግሌዎች በማታለል፣ በማጭበርበርና በተንኮል ክፋትን በመፈጸም በፈቃዳቸው ኃጢአት የሚሠሩ ሰዎችን ቶሎ ብለው ከጉባኤ ያስወግዳሉ።b—1 ቆሮንቶስ 5:9-13፤ ከመዝሙር 101:7 ጋር አወዳድር።
20. ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ በሚያደርጉልን ጥበቃ የደህንነት ስሜት ሊሰማን የሚችለው ለምንድን ነው?
20 ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶችን’ በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በሚያደርጉልን ፍቅራዊ እንክብካቤ ደህንነት ሊሰማን ይችላል። በርኅራኄ ያስተካክሉናል፣ በፍቅር ይገነቡናል፣ አንድነታችን እንዲጠበቅ ያደርጋሉ እንዲሁም በድፍረት ከአደጋ ይጠብቁናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ በጉባኤ ውስጥ የተሰጣቸውን የኃላፊነት ቦታ እንዴት መመልከት ይኖርባቸዋል? እኛስ ለእነርሱ ያለንን አድናቆት እንዴት ልናሳይ እንችላለን? በሚቀጥለው ርዕስ እነዚህ ጥያቄዎች ይብራራሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ማስተካከል” ተብሎ የተተረጎመው ይኸው ቃል በግሪኩ የሴፕቱጀንት ትርጉም በመዝሙር 17[16]:5 ላይ የተሠራበት ሲሆን እዚያ ላይም ታማኙ ዳዊት አረማመዱ ከይሖዋ ጎዳና ሳይወጣ ጸንቶ እንዲቆም ጸልዮአል።
b ለምሳሌ ያህል ኅዳር 15, 1979 መጠበቂያ ግንብ (የእንግሊዝኛ) እትም ገጽ 31-2 ላይ የወጣውን “የአንባብያን ጥያቄዎች” እና ጥር 1, 1997 እትም ገጽ 26-9 ላይ “ክፉ የሆነውን እንጸየፍ” የሚለውን ተመልከት።
ታስታውሳለህን?
◻ ‘ስጦታ የሆኑ ወንዶች’ እነማን ናቸው? አምላክ በክርስቶስ በኩል ለጉባኤ የሰጣቸውስ ለምንድን ነው?
◻ ሽማግሌዎች መንጋውን እንዲያስተካክሉ የተሰጣቸውን ኃላፊነት የሚወጡት እንዴት ነው?
◻ ሽማግሌዎች የእምነት ባልደረቦቻቸውን ለመገንባት ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
◻ ሽማግሌዎች የጉባኤውን አንድነት መጠበቅ የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች ራሳቸውን በሌሎች ቦታ ማስቀመጣቸው በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተደቆሱትን ለማበረታታት ይረዳቸዋል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሽማግሌዎች መካከል አንድነት መኖሩ በጉባኤው ውስጥም አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋል