በዓለም አቀፉ እውነተኛ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያገኘሁት ደስታ
ዊሊ ዴቪስ እንደተናገረው
በ1934 ታላቅ የኢኮኖሚ ድቀት ዓለምን አንቆ ይዞ ነበር። ዩናይትድ ስቴትስም በተጧጧፈው የኢኮኖሚ ትግል ውስጥ ትንቅንቅ ላይ ነበረች። በክሌቭላንድ ኦሃዮ ከነበረው ፕሮስፔክት ሪሊፍ ስቴሽን በተባለ የእርዳታ መስጫ ጣቢያ ከውጭ በኩል በአንድ ፖሊስና በአንድ አክራሪ ኮምኒስት መካከል ጥል ተነሥቶ ነበር። ፖሊሱ ኮምኒስቱንና ሁኔታውን ትመለከት የነበረችውን ቪኒ ዊሊያምስ የተባለችውን አያቴን በጥይት ገደላቸው።
አያቴ ጥቁር ፖሊሱ ደግሞ ነጭ ስለነበር ኮምኒስቶቹ በአጋጣሚው ተጠቅመው ግድያው የተፈጸመው በዘር ጥላቻ ምክንያት ነው ለማለት ሞክረው ነበር። በጋዜጦች ላይም “ዘረኛው የክሌቭላንድ ፖሊስ” እንዲሁም “የሟቾቹን ደም እንበቀላለን” የሚሉ ርዕሶች ያሏቸውን ዜናዎች አሰራጩ። የአያቴን የቀብር ሥነ ሥርዓት ያዘጋጁትና ያከናወኑት ኮምኒስቶቹ ነበሩ። የሬሳ ሣጥኑን የተሸከሙት ሰዎች ፎቶ ግራፍ አለኝ። ሁሉም ነጮችና የኮምኒስት ፓርቲው አባሎች ነበሩ። ቆይቶ የጥቁር አሜሪካውያን ንቅናቄ አርማ ሆኖ በታወቀው ዓይነት ሁሉም እጃቸውን ወደ ላይ አንሥተውና ጨብጠው ነበር።
አያቴ ስትሞት እኔ በልጅዋ ማህፀን ውስጥ ነበርኩ፤ ከአራት ወር በኋላም ተወለድኩ። አጣርቶ የመናገር እክል ነበረብኝ። ሳልንተባተብ መናገር አልችልም ነበር። በዚህ ምክንያት በልጅነቴ ያገኘሁት ትምህርት የንግግር ሕክምናን የሚጨመር ሆነ።
ወላጆቼ የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ተለያዩ። እኔና ታላቅ እኅቴ ከእናታችን ጋር አደግን። አሥር ዓመት ሲሞላኝ ቤተሰባችንን በገንዘብ ለመርዳት ስል ከትምህርት በኋላ ባሉት ጊዜያት በሸቀጣሸቀጥ መደብሮች መላላክ ጀመርኩ። ከሁለት ዓመት በኋላ ከትምህርት በፊትም ሆነ ከትምህርት በኋላ ባሉት ጊዜያት መሥራት ጀመርኩ። በዚህ መንገድ የቤተሰቡ ዋና የገቢ ምንጭ ሆንኩ። በኋላም እናቴ ሆስፒታል ገባችና ተከታታይ የቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈለጋት፤ ስለዚህ ትምህርቴን አቁሜ ሙሉ ቀን መሥራት ጀመርኩ።
ከአንድ የወንድማማች ማኅበር ጋር መተዋወቅ
በ1944 አንድ የይሖዋ ምሥክር “ነፃ የሚያወጣው እውነት” የተባለውን የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ለአጎቴ ልጅ ሚስት ሰጥቷት ነበር። እኔም ለእሷ በተጀመረው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ መገኘት ጀመርኩ። በዚያው ዓመት ላይ በስተ ምሥራቅ በኩል በሚገኘው ጉባኤ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መገኘት ጀመርኩ። የትምህርት ቤቱ መሪ የነበረው አልበርት ክራደክ እኔ ያለኝ ዓይነት የንግግር ችግር ነበረበት። ሆኖም ችግሩን እንዴት ማሸነፍ እንደሚችል ተምሮ ነበር። ወንድም ክራደክ እንዴት ያበረታታኝ ነበር!
በሰፈራችን የሚኖሩት ሰዎች በአብዛኛው ጣሊያኖች፣ ፖላንዳውያን፣ ሃንጋሪያውያንና አይሁዶች ስለነበሩ ጉባኤው ከእነዚህና ከሌሎች ጎሣዎች የመጡ ሰዎች ያሉበት ነበር። ነጮች ብቻ በሚገኙበት ከዚህ ጉባኤ ጋር ከተባበሩት የመጀመሪያዎቹ ጥቁር አሜሪካውያን መካከል እኔና የአጎቴ ልጅ ሚስት ነበርን። ቢሆንም ምሥክሮቹ ፈጽሞ የዘር ጥላቻ አላሳዩንም። እንዲያውም አዘውትረው በቤታቸው በመጋበዝ ያስተናግዱኝ ነበር።
አገልጋዮች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ስል በ1956 ወደ ደቡባዊ የዩናይትድ ስቴትስ ክፍለ ሀገር ሄድኩ። በበጋ ወራት በሚደረገው የወረዳ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ተመልሼ ወደ ሰሜን ስመጣ በክሌቭላንድ ከሚኖሩት ወንድሞች ብዙዎቹ ፈልገው አገኙኝና ስለ አገልግሎት እንቅስቃሴዬ ለመስማት ሞቅ ያለ ስሜት አሳዩኝ። እነርሱ ለእኔ ያሳዩት አሳቢነት “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፣ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” የሚለውን አስፈላጊ ትምህርት ሁልጊዜ ማስታወስ ያለብኝ መሆኑን አስተምሮኛል።—ፊልጵስዩስ 2:4
እየሰፋ የሄደ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
ለሦስት ዓመት ያህል አቅኚ ሆኜ በስብከቱ ሥራ በሙሉ ጊዜ ካገለገልኩ በኋላ በኅዳር ወር 1959 በይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት በብሩክሊን ቤቴል እንዳገለግል ተጠራሁ። በጽሑፍ መላኪያ ክፍል ተመደብኩ። በምሠራበት ክፍል የበላይ ተመልካች የነበረው ክላውስ ጀንሰንና በአንድ ክፍል ውስጥ አብሮኝ ይኖር የነበረው ዊሊያም ሃነን (ሁለቱም ነጮች ናቸው) መንፈሳዊ አባቶች ሆኑኝ። እኔ ስገባ እያንዳንዳቸው ወደ 40 ለሚጠጉ ዓመታት በቤቴል አገልግለው ነበር።
በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ወደ 600 የሚጠጉ ሲሆን ወደ 20 የሚሆኑት ጥቁር አሜሪካውያን ነበሩ። በዚህ ጊዜ ዩናይትድ ስቴትስ በዘር ልዩነት ትታመስ ስለነበር የተለያየ ቀለምና ዘር ባላቸው ሰዎች መካከል የነበረው ግንኙነት ሻክሮ ነበር። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክ ለሰው ፊት እንደማያደላ’ ያስተምረናል። ስለዚህ እኛም የምናዳላ መሆን አይገባንም። (ሥራ 10:34, 35) በቤቴል በየቀኑ በቁርስ ሰዓት ላይ የምናደርጋቸው መንፈሳዊ ውይይቶች አምላክ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ለመቀበል ያደረግነውን ውሳኔ አጠናክረውልናል።—መዝሙር 19:7
በብሩክሊን ቤቴል በማገልገል ላይ ሳለሁ ከቨርጂኒያ ክፍለ ሀገር ከሪችሞንድ ከተማ የመጣች ሎኧስ ረፈን ከተባለች አንዲት አቅኚ ጋር ተዋወቅሁ። በ1964 ተጋባን። ውሳኔያችን በሙሉ ጊዜ አገልግሎቱ ላይ ለመቆየት ነበር። ስለዚህ ከሠርጋችን በኋላ ወደ ደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። በመጀመሪያ ልዩ አቅኚዎች ሆነን አገለገልን። ከዚያም በ1965 በክልል ሥራ እንድሰማራ ጥሪ ቀረበልኝ። በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት በኬንታኪ፣ በቴክሳስ፣ በሉዊዚያና፣ በአላባማ፣ በጆርጂያ፣ በሰሜን ካሮሊና እና በሚሲሲፒ ክፍለ ሀገራት ያሉትን ጉባኤዎች ጎብኝተናል።
ወንድማማችነታችንን የሚፈትን ነገር
እነዚያ ዓመታት ትልቅ ለውጥ የታየባቸው ዓመታት ነበሩ። ወደ ደቡብ ክፍለ ሀገር ከመዛወራችን በፊት ነጮችና ጥቁሮች ተለያይተው እንዲኖሩ ተደርጎ ነበር። ጥቁሮች ነጮች በሚማሩበት ትምህርት ቤት እንዳይማሩ፣ ነጮች በሚመገቡባቸው ምግብ ቤቶች እንዳይገቡ፣ ነጮች በሚተኙባቸው ሆቴሎች እንዳይተኙ፣ ነጮች በሚገበዩባቸው የሸቀጣሸቀጥ መደብሮች እንዳይገበዩ፣ ሌላው ቀርቶ ነጮች የመጠጥ ውኃ ከሚያገኙበት የውኃ ማጠራቀሚያ እንዳይጠቀሙ ጭምር በሕግ የተከለከለ ነበር። ሆኖም የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት በ1964 የዜጎችን መብት አስመልክቶ የሕዝብ መጓጓዣን ጨምሮ በሕዝብ መገልገያ ቦታዎች ላይ የቀለምም ሆነ የዘር ልዩነት እንዳይደረግ ደነገገ። በዚህ ምክንያት ከዚያ በኋላ የዘርና የቀለም ልዩነት ለመፍጠር የሚያስችል አንዳችም ሕጋዊ መሠረት አልነበረም።
ስለዚህ ጥቁሮች ወይም ነጮች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ብቻ ይገኙ የነበሩባቸው ጉባኤዎች በአንድ ላይ ተዋህደው እርስ በእርሳቸው ፍቅርና መተሳሰብ ያሳዩ ይሆን? ወይስ ከአካባቢው በሚመጣው ተጽዕኖና ከዚህ ቀደም በነበሩት ሥር የሰደዱ ቅራኔዎች የተነሣ በአንድ ላይ መዋሃድ ያዳግታቸው ይሆን? የሚል ጥያቄ ተነሥቶ ነበር። በዚያን ጊዜ “በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትእዛዝ መከተል ቀላል አልነበረም።—ሮሜ 12:10
ሁሉም የአካባቢው ሕዝብ እንደሚያስታውሰው በተለይ በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ ጥቁሮችን ዝቅ አድርጎ መመልከት አይሎ ይታይ ነበር። እንዲህ ያለው አመለካከት በሕዝቡ አእምሮ ውስጥ ሰረጾ ሥር በመስደዱ በሁሉም የሕብረተሰቡ ክፍሎች በአብያተ ክርስቲያናት እንኳ ሳይቀር የሚታይ ነበር። ስለዚህ ለአንዳንድ ነጮች ጥቁሮችን ከነጮች ጋር እኩል አድርገው ለመመልከት ቀላል አልሆነላቸውም። በእርግጥ ያ ወቅት ለጥቁሮችም ሆነ ለነጮች ወንድማማችነታችን የሚፈተንበት ነበር።
በአጠቃላይ ሲታይ ግን ጉባኤዎቻችን ባንድ ላይ እንዲዋሃዱ ለቀረበው ሐሳብ ግሩም ምላሽ መሰጠቱ የሚያስደስት ነበር። ለብዙ መቶ ዘመናት የኖረውን ሆን ተብሎ አንዱን ዘር ከሌላው አስበልጦ የመመልከትን ልማድ በቀላሉ ፍቆ ማውጣት አልተቻለም ነበር። ሆኖም በአንድ ላይ መሰብሰብ ሲጀመር አብዛኞቹ ወንድሞቻችን ሁኔታውን በጥሩ መንገድ ተቀብለውትና ባንድ ላይ መሰብሰብ በመቻሉ ተደስተው ነበር።
እንዲያውም ባይገርማችሁ ምሥክር ያልነበሩ ሰዎች ጭምር ጉባኤዎቻችን ባንድ ላይ በመቀላቀላቸው መስማማታቸውን ብዙ ጊዜ ይገልጹ ነበር። ለምሳሌ ላኔት በተባለች የአላባማ ከተማ በመንግሥት አዳራሹ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች ጥቁሮች ለስብሰባ በመምጣታቸው ቅር ይላቸው እንደሆነ ተጠይቀው ነበር። አንዲት ነጭ አዛውንት የአንዱን ጥቁር ወንድም እጅ በመጨበጥ “እባካችሁ ወደ ሰፈራችን ኑና አምላካችሁን በምትፈልጉት መንገድ አምልኩ!” ሲሉ ተናገሩ።
ታማኝ ኢትዮጵያውያን ወንድሞች
በ1974 በኒው ዮርክ ከተማ በመጠበቂያ ግንብ የጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ለአምስት ወር ተኩል የሚስዮናዊነት ሥልጠና በማግኘታችን ተደሰትን። ከዚያም ኢትዮጵያ በምትባል አንዲት አፍሪካዊት አገር ተመደብን። ያኔ የአገሪቱ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከዙፋናቸው ወርደው በግዞት ቤት ይጠበቁ ነበር። የስበከት ሥራችን ታግዶ ስለነበረ ሞቅ ባለው ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ተደስተን እንኖር ነበር።
እውነተኛውን አምልኮ አጥብቀው በመያዛቸው የተነሣ ከጊዜ በኋላ ወደ ወኅኒ ከወረዱት ብዙ ታማኝ ወንድሞች ጋር አብረን ኖረንና አገልግለን ነበር። እንዲያውም ከውድ ወንድሞቻችን መካከል አንዳንዶቹ ተገድለዋል። አደራ ተሾመ በኢትዮጵያ ዋና ከተማ በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ አብሮኝ ያገለግል ነበር።a ለሦስት ዓመት ከታሰረ በኋላ ተገደለ። ባለቤቱም ጥልቅ ኀዘን ተሰምቷት ነበር። ዓመታት ካለፉ በኋላ ግን አቅኚ ሆና በደስታ ስታገለግል ማየቴ ምንኛ አስደሰተኝ!
ወርቁ አበበ የተባለ ሌላው ታማኝ ወንድም ስምንት ጊዜ ሞት ተፈርዶበት ነበር።b ሆኖም በፍጹም አልተበገረላቸውም። አንድ ጊዜ ተገናኝተን ስንጫወት በእስር ቤቱ ዘበኞች በሰደፍ የተመቱትን ጆሮዎቹን አሳየኝ። በየቀኑ ቢያንስ የሰደፍ ቁርስ፣ ምሳና እራት እንደሚሰጠው እንደ ቀልድ አድርጎ ነገረኝ። ወንድም ወርቁ ከጊዜ በኋላ ቢሞትም እስካሁን ድረስ ወንድሞች በፍቅር ያስታውሱታል።
ሌላው ትዝ ሲለኝ የፍቅር ስሜት የሚቀሰቅስብኝ ወንድም ደግሞ ኃይሉ የምሩ ነው።c ለባለቤቱ ፍቅር በማሳየት እንደ ምሳሌ ተደርጎ የሚጠቀስ ነው። ባለቤቱ ታሰረችበት። ነፍሰ ጡር ስለነበረች የመውለጃዋ ወራት ተቃርቦ ነበር። ኃይሉም በእርሷ ፋንታ መታሰር ይችል እንደሆነ የእስር ቤቱን ባለ ሥልጣኖች ጠየቀ። ከዚያም ታሰረና ጥቂት ቆይቶ እምነቱን ባለመካዱ ተገደለ።—ዮሐንስ 15:12, 13፤ ኤፌሶን 5:28
በኢትዮጵያ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ እየተባባሰ በመምጣቱ በ1976 ወደ ኬንያ ሄድን። በብዙዎቹ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ኬንያን ጨምሮ በኢትዮጵያ፣ በሱዳን፣ በሲሼልስ፣ በኡጋንዳና በታንዛኒያ የሚገኙ ወንድሞችን በመጎብኘት ለሰባት ዓመታት በተጓዥነት ሥራ አገልግለናል። በተጨማሪም ሥራችን በቡሩንዲና በሩዋንዳ ሕጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ባለ ሥልጣኖችን እንዲያነጋግሩ ከተላኩት ልዑካን አንዱ በመሆን ብዙ ጊዜ ወደ እነዚህ አገሮች ተጉዣለሁ።
በሥራችን ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ከተነሣ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የወረዳ ስብሰባ ለመገኘት በ1992 ጥር ወር ላይ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰን መሄዳችን በጣም አስደስቶናል። ቀደም ባሉት ጊዜያት ወንድሞች በትንንሽ ቡድኖች ብቻ ይሰበሰቡ ስለነበር በወረዳ ስብሰባው ላይ የተገኙት ከ7,000 በላይ ከሚሆኑት ሰዎች አብዛኞቹ እርስ በርስ አይተዋወቁም ነበር። በእያንዳንዱ የወረዳ ስብሰባ ቀን አብዛኞቹ ወንድሞች ፕሮግራሙ ከመጀመሩ ሁለት ሰዓት ቀደም ብለው በመምጣትና ካለቀም በኋላ እስኪመሽ ድረስ በመቆየት በፍቅራዊ ወንድማማችነታችን መደሰት ችለው ነበር።
የጎሣ ልዩነት ድል ተመታ
በአፍሪካ ለብዙ መቶ ዘመናት የጎሣ ልዩነት ተስፋፍቶ ቆይቷል። ለምሳሌ በቡሩንዲና በሩዋንዳ የሚገኙ ሁቱ እና ቱትሲ የሚባሉት ዋናዎቹ ጎሣዎች ለረጅም ጊዜ እርስ በርስ ሲጠላሉ ኖረዋል። እነዚህ አገሮች በ1962 ከቤልጅየም ቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላ ሁለቱ ጎሣዎች እርስ በእርስ በመጨፋጨፍ በየጊዜው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት አጥፍተዋል። የእነዚህ ጎሣዎች አባላት የሆኑ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ሆነው አንድ ላይ በሰላም ሲሠሩ ማየት ምንኛ አስደሳች ነው! እርስ በእርስ ያሳዩት እውነተኛ ፍቅር ሌሎች ብዙ ሰዎችም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲሰሙ አበረታቷቸዋል።
በተመሳሳይም በኬንያ ያሉ የተለያዩ ጎሣዎች ብዙ ጊዜ አምባጓሮ ሲፈጥሩ ይታያሉ። በኬንያ በሚገኙት የይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለው ክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ግን ምን ያህል ከዚህ የተለየ ነው! የተለያዩ ጎሣዎች በመንግሥት አዳራሹ ተሰብስበው በአንድነት ሲያመልኩ ማየት ትችላላችሁ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ የነበራቸውን የጎሣ ጥላቻ አውልቀው በመጣል የሌላው ጎሣ አባል የሆኑ ወንድሞቻቸውንና እኅቶቻቸውን ከልብ ሲወዱ ማየቴ በጣም አስደስቶኛል።
በወንድማማች ማኅበራችን ደስተኛ ነኝ
ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ከአምላክ ድርጅት ጋር ያሳለፍኩትን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ስመለከተው ልቤ በይሖዋ እና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይሞላል። በእውነትም ይሖዋ እና ኢየሱስ በምድር ላይ በጣም አስገራሚ የሆነ ነገር ፈጥረዋል! በአምላክ ሕዝቦች መካከል የነበሩት ሁኔታዎች ሁልጊዜ ፍጹም አልነበሩም፤ ዛሬም አይደሉም። ደግሞም ለብዙ መቶ ዓመታት ሰዎችን በዘርና በቀለም የሚከፋፍሉ የሰይጣን ዓለም ትምህርቶች ባንድ ጀምበር ተፍቀው እንደሚጠፉ መጠበቅ አይቻልም። ከዚያም በላይ አሁንም ገና ፍጽምና ይጎድለናል።—መዝሙር 51:5
የይሖዋን ድርጅት ከዓለም ጋር ሳወዳድር ዓለም አቀፍ ስለሆነው እውነተኛ የወንድማማች ማኅበራችን ልቤ በአድናቆት ይሞላል። በመንፈሳዊ እየመገቡ ያሳደጉኝን በክሌቭላንድ የነበሩ ነጭ ወንድሞችን አሁንም በፍቅር አስታውሳቸዋለሁ። እንዲሁም በደቡባዊው ዩናይትድ ስቴትስ የነበሩ ነጭም ሆኑ ጥቁር ወንድሞች መሠረተ ቢስ የሆነ የጥላቻ ስሜቶቻቸውን አስወግደው በምትኩ ከልብ የመነጨ የወንድማማች ፍቅር ሲያሳዩ በማየቴ ልቤ በደስታ ተሞልቷል። ከዚያም ወደ አፍሪካ ሄጄ የይሖዋ ቃል የጎሣ ጥላቻዎችን ፍቆ ሊያጠፋ እንደሚችል ማየቴ ዓለም አቀፋዊውን ወንድማማችነታችንን ይበልጥ እንዳደንቅ አድርጎኛል።
የጥንቱ ንጉሥ ዳዊት “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም፣ ያማረ ነው” በማለት ሁኔታውን በትክክል ገልጾታል።—መዝሙር 133:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የአደራ ተሾመ እና የኃይሉ የምሩ ፎቶ ግራፎች በ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ በገጽ 177 ላይ ይገኛሉ። የወርቁ አበበ ተሞክሮም በገጽ 178–81 ላይ ወጥቷል።
b የአደራ ተሾመ እና የኃይሉ የምሩ ፎቶ ግራፎች በ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ በገጽ 177 ላይ ይገኛሉ። የወርቁ አበበ ተሞክሮም በገጽ 178–81 ላይ ወጥቷል።
c የአደራ ተሾመ እና የኃይሉ የምሩ ፎቶ ግራፎች በ1992 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ በገጽ 177 ላይ ይገኛሉ። የወርቁ አበበ ተሞክሮም በገጽ 178–81 ላይ ወጥቷል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአያቴ የቀብር ሥነ ሥርዓት
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቱትሲ እና ሁቱ ምሥክሮች በሰላም አንድ ላይ ሲሠሩ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከሎኧስ ጋር