ይቅር ባይ ነህን?
ቢልና የ16 ዓመት ሴት ልጁ ሊዛ አይስማሙም ነበር። በመካከላቸው የሚፈጠሩት ከቁጥር የማይገቡ አለመግባባቶች ብዙውን ጊዜ እየከረሩ ይሄዱና መጯጯህን ያስከትላሉ። በመጨረሻ ውጥረቱ እያየለ ሄደና ሊዛ ከቤት እስከ መባረር ደረሰች።a
ከጊዜ በኋላ ሊዛ ስሕተተኛዋ እሷ መሆኗን ተገንዝባ አባቷ ይቅርታ እንዲያደርግላት ለመነችው። በጣም ተማርሮ የነበረው አባቷ ሊዛ ቀደም ሲል የፈጸመቻቸውን ስሕተቶች እንደማለፍ ሰላምን ለመፍጠር ያደረገችውን ጥረት አልቀበልም አለ። እስቲ አስበው! ለገዛ ልጁ ምሕረት ለማድረግ አሻፈረኝ አለ!
ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት አንድ ምንም ጥፋት ያልሠራ ሰው ባልፈጸመው ወንጀል ተከሶ ሞት ተፈረደበት። ምሥክሮች በሐሰት መሠከሩበት። የፖለቲካ ባለ ሥልጣኖች ፊታቸውን አዞሩበት፤ ፍትሕን ላለማየት ዓይናቸውን ጨፈኑ። ያ ምንም ወንጀል ያልሠራ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሊሞት ሲያጣጥር “አባት ሆይ፣ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” በማለት አምላክን በጸሎት ተማጽኗል።—ሉቃስ 23:34
ኢየሱስ ከልቡ በነፃ ይቅር ብሎአቸዋል፤ ተከታዮቹም በዚህ ረገድ እርሱን እንዲመስሉ ተመክረዋል። (ኤፌሶን 4:32) ይሁን እንጂ ልክ እንደ ቢል ብዙ ሰዎች ልባቸውን አደንድነው ይቅር ለማለት አሻፈረኝ ይላሉ። በዚህ ረገድ ያለህ አቋም እንዴት ነው? ሌሎች ሲበድሉህ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነህን? ከባድ በደሎችንስ? እነርሱንም ይቅር ማለት ይገባልን?
ይቅር ማለት ፈተና ነው
ይቅር ማለት ሁልጊዜ ቀላል አይሆንም። በእነዚህ አስጨናቂ ጊዜያት ደግሞ የሰዎች ግንኙነት ከምን ጊዜውም በበለጠ አስቸጋሪና የተወሳሰበ ሆኗል። በተለይም የቤተሰብ ኑሮ ብዙውን ጊዜ በተለያዩ ውጥረቶችና ግፊቶች የተሞላ ነው። ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ “በመጨረሻው ቀን” ይህን የመሰሉ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ ከብዙ ዓመታት በፊት ገልጾ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች [እኔ ያልኩት ይሁን ባዮች አዓት]፣ በትዕቢት የተነፉ . . . ይሆናሉ።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1–4
እንግዲያው ሁላችንም ሌሎችን ይቅር ለማለት ያለንን ችሎታ የሚፈትኑ ውጫዊ ግፊቶች እንደሚገጥሙን አሌ አይባልም። ከዚህም በተጨማሪ ከውስጣዊ ግፊቶችም ጋር እንታገላለን። ጳውሎስ የተሰማውን ሐዘን እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፣ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ።” (ሮሜ 7:19, 20) በዚህ ምክንያት ብዙዎቻችን የምኞታችንን ያህል ይቅር ባዮች አይደለንም። እንዲያውም ከዘር የወረስነው አለፍጽምናና ኃጢአት በሁላችንም ላይ ከባድ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል፤ አንዳንድ ጊዜም እኛን መሰል ለሆኑ የሰው ልጆች ያለንን አዘኔታ ያሳጡናል።
አንዲት ሴት ቀላል በደል የበደላትን ሰው ይቅር እንድትል ማበረታቻ ሲሰጣት “ራስን አስገድዶና አስጨንቆ ይቅርታ ሊደረግለት የሚገባው ማንም ሰው የለም” ስትል መልሳለች። እንዲህ ያለው አስተያየት ላይ ላዩን ሲታይ ለሌላው ደንታ ቢስ መሆን፣ በሰዎች ላይ መጨከን አልፎ ተርፎም ተጠራጣሪነት ሊመስል ይችላል። ጠለቅ ብለን ስንመለከተው ግን ብዙ ሰዎች ራስ ወዳድ፣ ስለ ሌላው ግድ የሌለውና ሌሎችን በጥላቻ ዓይን የሚመለከት አድርገው ለሚያስቡት ዓለም የሚሰማቸውን ብስጭት የሚገልጽ አስተያየት ሆኖ እናገኘዋለን። አንድ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች ይቅር ስትሏቸው ሊጫወቱባችሁ ይፈልጋሉ። ልክ እንደ ጅላጅል ይቆጥሯችኋል።”
እንግዲያው በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች የይቅር ባይነትን ጠባይ ማዳበር አስቸጋሪ መሆኑ አያስደንቅም። ያም ሆኖ ግን መጽሐፍ ቅዱስ በደግነት ይቅር እንድንል ያበረታታናል። (ከ2 ቆሮንቶስ 2:7 ጋር አወዳድር።) ይቅር ባዮች መሆን የሚኖርብን ለምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ስሞቹ ተለውጠዋል።