የአምላክን ነቢያት እንደ ምሳሌ አድርጋችሁ ተመልከቱ
“ወንድሞች ሆይ፣ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ።”—ያዕቆብ 5:10
1. የይሖዋ አገልጋዮች ስደት በሚደርስባቸውም ጊዜ እንኳ ደስተኞች እንዲሆኑ የሚረዳቸው ነገር ምንድን ነው?
በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች በዓለም ዙሪያ የኀዘንና የትካዜ መንፈስ ቢንሰራፋም እንኳ የይሖዋ አገልጋዮች ደስታ ይንጸባረቅባቸዋል። ይህ ሊሆን የቻለው አምላክን እያስደሰቱ እንዳሉ ስለሚያውቁ ነው። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች መከራን እየተቀበሉ ያሉት ለጽድቅ ብለው እንደሆነ ስለሚያውቁ ለሕዝብ በሚሰጡት ምሥክርነት ላይ የሚነሣውን ስደትና ተቃውሞ ጸንተው ይቋቋሙታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “ሲነቅፉአችሁና ሲያሳድዱአችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በውሸት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ። ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ፣ ሐሴትም አድርጉ፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና።” (ማቴዎስ 5:10–12) በእርግጥም የአምላክ አገልጋዮች እምነታቸውን የሚፈትኑ ነገሮች ባጋጠሟቸው ጊዜ ሁሉ ፈተናዎቹን እንደ ደስታ ይቆጥሯቸዋል።—ያዕቆብ 1:2, 3
2. በያዕቆብ 5:10 መሠረት ትዕግሥትን እንድናሳይ ምን ሊረዳን ይችላል?
2 ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ወንድሞች ሆይ፣ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ” ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 5:10) ደብሊው ኤፍ አርንትና ኤፍ ደብሊው ጊንግሪች እዚህ ላይ “ምሳሌ” ተብሎ የተተረጎመውን የግሪክኛ ቃል (ሃይፖ ዴግማ) “ምሳሌ፣ ሞዴል፣ አብነት” ብለው ተርጉመውታል። “ይኸውም አንድን ነገር እንድንመስለው የሚስበን ጥሩ ባሕርይ ነው።” በዮሐንስ 13:15 ላይ እንደተገለጸው “ይህ ምሳሌ ማለት ብቻ አይደለም። ልንይዘው የሚገባን ትክክለኛው ቅርጽ ማለት ነው።” (ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት) እንግዲያው በዘመናችን ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች ‘መከራን በመቀበል’ እና ‘በትዕግሥት’ ረገድ የይሖዋን ነቢያት እንደ ምሳሌ አድርገው መመልከት ይችላሉ። እነርሱ ያሳለፉትን ሕይወት ስናጠና ምን ሌላ ነገር መረዳት እንችላለን? ይህስ በስብከቱ ሥራችን ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
ከፍተኛ መከራ ደርሶባቸዋል
3, 4. ነቢዩ አሞጽ ከአሜስያስ ለተነሣበት ተቃውሞ ምን ምላሽ ሰጠ?
3 የይሖዋ ነቢያት ብዙ ጊዜ ከፍተኛ መከራ ደርሶባቸዋል ወይም ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። ለምሳሌ ያህል በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የጥጃ አምልኮ ካህን የነበረው አሜስያስ ነቢዩ አሞጽን ክፉኛ ተቃወመው። አሜስያስ አሞጽ ንጉሡ በሰይፍ ይሞታል፤ እስራኤላውያንም ይማረካሉ ብሎ ትንቢት በመናገር በዳግማዊ ኢዮርብዓም ላይ አሢሯል በማለት በውሸት ተናገረ። አሜስያስ አሞጽን በንቀት እንዲህ አለው፦ “ባለ ራእዩ ሆይ፣ ሂድ ወደ ይሁዳም ምድር ሽሽ፣ በዚያም እንጀራን ብላ፣ በዚያም ትንቢትን ተናገር፤ ነገር ግን ቤቴል የንጉሥ መቅደስና የመንግሥት ቤት ናትና ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ደግሞ ትንቢት አትናገር።” አሞጽ በዚህ ውረፋ ተደናግጦ ወደ ኋላ አላለም። እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ ላም ጠባቂና ወርካ ለቃሚ ነኝ እንጂ ነቢይ ወይም የነቢይ ልጅ አይደለሁም፤ እግዚአብሔርም በጎቹን ከመከተል ወሰደኝ፣ እግዚአብሔርም፦ ሂድ፣ ለሕዝቤም ለእስራኤል ትንቢት ተናገር አለኝ።”—አሞጽ 7:10–15
4 የይሖዋ መንፈስ አሞጽ በድፍረት ትንቢት እንዲናገር ብርታት ሰጠው። አሞጽ እንዲህ ብሎ በተናገረ ጊዜ አሜስያስ ምን እንደተሰማው ልትገምቱ ትችላላችሁ፦ “የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ አንተ፦ በእስራኤል ላይ ትንቢት አትናገር፣ በይስሐቅም ቤት ላይ አትስበክ ብለሃል፤ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ሚስትህ በከተማይቱ ውስጥ ጋለሞታ ትሆናለች፣ ወንዶችና ሴቶች ልጆችህም በሰይፍ ይወድቃሉ፣ ምድርህም በገመድ ትከፈላለች፤ አንተም በረከሰች ምድር ትሞታለህ፣ እስራኤልም ከምድሩ ተማርኮ ይሄዳል።” ትንቢቱ ተፈጽሟል። (አሞጽ 7:16, 17) ከሐዲው አሜስያስ ምንኛ ደንግጦ ይሆን!
5. ዘመናዊ የይሖዋ አገልጋዮች ያሉበትን ሁኔታና ነቢዩ አሞጽ የነበረበትን ሁኔታ እንዴት ማመሳሰል ይቻላል?
5 ይህ በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች ካሉበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። የአምላክን መልእክቶች በመናገራችን እኛም ከፍተኛ መከራ ይደርስብናል፤ ብዙ ሰዎችም ስለ ስብከቱ ሥራችን አንቋሽሸው ይናገራሉ። እውነት ነው፣ የመስበክ ሥልጣን ያገኘነው ከሃይማኖታዊ ኮሌጅ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ የመንግሥቱን የምሥራች እንድናውጅ ይገፋፋናል። የአምላክን መልእክት ለውጠን ወይም በርዘን አንናገርም። ከዚህ ይልቅ ልክ እንደ አሞጽ ሰሚዎቻችን ምንም ዓይነት ምላሽ ቢያሳዩ መልእክቱን በታዛዥነት እናውጃለን። —2 ቆሮንቶስ 2:15–17
ታግሠዋል
6, 7. (ሀ) የኢሳይያስ ትንቢት ጎላ ብሎ የተንጸባረቀበት ነገር ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ዘመን ያሉት የይሖዋ አገልጋዮች እንደ ኢሳይያስ የሚያደርጉት እንዴት ነው?
6 የአምላክ ነቢያት ትዕግሥት ነበራቸው። ለምሳሌ ያህል በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የይሖዋ ነቢይ ሆኖ ያገለገለው ኢሳይያስ ትዕግሥትን አሳይቶ ነበር። አምላክ እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ሂድ፣ ይህን ሕዝብ፦ መስማትን ትሰማላችሁ አታስተውሉምም፤ ማየትንም ታያላችሁ አትመለከቱምም በላቸው። በዓይናቸው እንዳያዩ፣ በጆሮአቸውም እንዳይሰሙ፣ በልባቸውም እንዳያስተውሉ፣ ተመልሰውም እንዳይፈወሱ፣ የዚህን ሕዝብ ልብ አደንድን፣ ጆሮአቸውንም አደንቁር፣ ዓይናቸውንም ጨፍን።” (ኢሳይያስ 6:9, 10) በእርግጥም ሕዝቡ የሰጡት ምላሽ ይኸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ሁኔታ ኢሳይያስ መናገሩን እንዲያቆም አደረገውን? አላደረገውም፤ ከዚህ ይልቅ በትዕግሥትና በቅንዓት የይሖዋን የማስጠንቀቂያ መልእክቶች አስታውቋል። ከላይ የተጠቀሱት የአምላክ ቃላት በዕብራይስጡ ቋንቋ ያላቸው አቀማመጥ ነቢያት ሕዝቡ “በተደጋጋሚ” [አዓት] የሰማውን መልእክት “ያለማቋረጥ ለረጅም ጊዜ” አውጀዋል የሚለውን ሐሳብ የሚደግፍ ነው።—ጄዝኒዩስ ሂብሪው ግራመር።
7 ዛሬ ብዙዎች ለምሥራቹ የሚሰጡት ምላሽ በኢሳይያስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ይሖዋ በኢሳይያስ በኩል ላስተላለፈው ቃል የሰጡትን ዓይነት ምላሽ ነው። ይሁን እንጂ ልክ እንደዚያ ታማኝ ነቢይ እኛም የመንግሥቱን መልእክት “በተደጋጋሚ” [አዓት] እንናገራለን። ይህ የይሖዋ ፈቃድ ስለሆነ በቅንዓትና በትዕግሥት እንዲህ ማድረጋችንን እንቀጥላለን።
‘እንዲሁ አደረጉ’
8, 9. የይሖዋ ነቢይ የነበረው ሙሴ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በምን በምን መንገዶች ነው?
8 ነቢዩ ሙሴ በትዕግሥትና በታዛዥነት ረገድ ምሳሌ የሚሆን ነው። በባርነት ሥር ከነበሩት እስራኤላውያን ጎን መቆምን መርጧል፤ ሆኖም ነፃ እስከሚወጡበት ጊዜ ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ነበረበት። አምላክ የእስራኤልን ሕዝብ ከባርነት ቀንበር አላቆ በእርሱ መሪነት ከግብጽ እንዲያወጣ እስከተጠቀመበት ጊዜ ድረስ በምድያም ምድር ለ40 ዓመታት ኖሯል። ሙሴና አሮን በግብጽ ገዥ ፊት በቀረቡ ጊዜ አምላክ ያዘዛቸውን በታዛዥነት ተናግረዋል፤ እንዲሁም አድርገዋል። እንዲያውም አምላክ እንዳዘዛቸው ‘እንዲሁ አደረጉ።’—ዘጸአት 7:1–6፤ ዕብራውያን 11:24–29
9 ሙሴ እስራኤል በምድረ በዳ ያሳለፋቸውን በውጣ ውረድ የተሞሉ 40 ዓመታት በትዕግሥት ችሎ አሳልፏል። በተጨማሪም የእስራኤልን የመገናኛ ድንኳን አሠራር በተመለከተና በይሖዋ አምልኮ ውስጥ የተሠራባቸውን ሌሎች ነገሮችንም በተመለከተ የተሰጡትን መለኮታዊ መመሪያዎች በታዛዥነት ተከትሏል። ነቢዩ የአምላክን መመሪያዎች በደንብ በመከተሉ እንዲህ የሚል እናነባለን፦ “ሙሴም እንዲሁ አደረገ፤ እግዚአብሔር እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።” (ዘጸአት 40:16) ከይሖዋ ድርጅት ጋር በመተባበር አገልግሎታችንን ስንፈጽም የሙሴን ታዛዥነት እናስታውስ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ለዋኖቻችን እንድንታዘዝ’ የሰጠውንም ምክር በሥራ ላይ እናውል።—ዕብራውያን 13:17
ይሆናል የሚል አመለካከት ነበራቸው
10, 11. (ሀ) ነቢዩ ሆሴዕ ይሆናል የሚል አመለካከት እንደነበረው የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) በአገልግሎት ክልሎቻችን ውስጥ ሰዎችን ቀርበን ስናነጋግር ሁልጊዜ ይሆናል የሚል አመለካከት ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?
10 ነቢያት የፍርድ መልእክቶችን ሲያስተላልፉና በእስራኤል ውስጥ በየቦታው ተሰበጣጥረው ለሚገኙት ታማኝ ሰዎች አምላክ ያለውን ፍቅራዊ አሳቢነት የሚያንጸባርቁ ትንቢቶችን ሲተነብዩ ይሆናል የሚል አመለካከት መያዝ አስፈልጓቸው ነበር። ይህ ሁኔታ ከ59 ለማያንሱ ዓመታት ነቢይ በነበረው በሆሴዕ ላይ ታይቷል። ይሆናል የሚል አመለካከት በመያዝ የይሖዋን መልእክት ያለማቋረጥ ተናግሯል፤ ትንቢታዊ መጽሐፉንም በሚከተሉት ቃላት ደምድሟል፦ “ይህን ነገር የሚያስተውል ጠቢብ፣ የሚያውቃትም አስተዋይ ማን ነው? የእግዚአብሔር መንገድ ቅን ነው፣ ጻድቃንም ይሄዱበታል፤ ተላላፊዎች ግን ይወድቁበታል።” (ሆሴዕ 14:9) ይሖዋ ምሥክርነት እንድንሰጥ እስከፈቀደልን ድረስ ይሆናል የሚል አመለካከት ይዘን ይገባናል የማንለውን የአምላክን ደግነት ለመቀበል የሚያበቃ አስተዋይነት ያላቸውን ሰዎች መፈለጋችንን እንቀጥል።
11 ‘የሚገባቸውን ሰዎች ፈልገን ለማግኘት’ ያለመታከት መሥራትና ነገሮችን አዎንታዊ በሆነ መንገድ መመልከት ይገባናል። (ማቴዎስ 10:11) ለምሳሌ ያህል የመኪና ወይም የቤት ቁልፍ ብንጥል በመጣንበት ተመልሰን ቀደም ሲል በነበርንባቸው የተለያዩ ቦታዎች ቁልፉን ለማግኘት እንዳክራለን። ምናልባት ልናገኘው የምንችለው ደጋግመን እንዲህ ካደረግን ብቻ ሊሆን ይችላል። ልክ እንደዚሁም በግ መሰል ሰዎችን ያለመታከት እንፈልግ። ብዙ ጊዜ በተሠራበት የአገልግሎት ክልል ውስጥ ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ በጎች ሲገኙ እንዴት ደስ ይለን ይሆን! ከዚህም ሌላ ለሕዝብ በምንሰጠው ምሥክርነት ላይ ቀደም ባሉት ጊዜያት እገዳ ተጥሎባቸው በነበሩባቸው አገሮች አምላክ ሥራችንን እየባረከው መሆኑ ምንኛ የሚያስደስት ነው!—ገላትያ 6:10
የማበረታቻ ምንጮች
12. በ20ኛው መቶ ዘመን የተፈጸመው የኢዮኤል ትንቢት የትኛው ነው? እንዴትስ?
12 የይሖዋ ነቢያት የተናገሯቸው ቃላት በአገልግሎታችን ትልቅ ማበረታቻ ሊሆኑን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ኢዮኤል የተናገረውን ትንቢት ተመልከት። ትንቢቱ በዘጠነኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ለነበሩት ከሃዲ እስራኤላውያንና ለሌሎች የተነገሩ የፍርድ መልእክቶችን ይዟል። ሆኖም ኢዮኤል በመንፈስ አነሣሽነት የሚከተለውንም ትንቢት ተናግሯል፦ “እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፣ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልምን ያልማሉ፣ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፤ ደግሞም በዚያ ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎች ላይ መንፈሴን አፈስሳለሁ።” (ኢዮኤል 2:28, 29) ይህ ትንቢት በ33 እዘአ ከዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ጀምሮ በኢየሱስ ተከታዮች ላይ ተፈጽሟል። በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን ደግሞ ይህ ትንቢት በስፋት ሲፈጸም እያየን ነው! በዛሬው ጊዜ ‘የሚተነብዩ’ ወይም የይሖዋን መልዕክት የሚያውጁ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉን። ከእነዚህም መካከል ከ600,000 በላይ የሚሆኑት በሙሉ ጊዜ የአቅኚነት አገልግሎት የተሰማሩ ናቸው።
13, 14. ወጣት ክርስቲያኖች በመስክ አገልግሎት ደስታን ማግኘት እንዲችሉ ምን ሊረዳቸው ይችላል?
13 የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ የሆኑ ወጣቶች ብዙ ናቸው። በዕድሜ የሚበልጧቸውን ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ማነጋገር ሁልጊዜ ቀላል አይሆንላቸውም። አንዳንድ ጊዜ ወጣት የይሖዋ አገልጋዮችን ‘ጊዜያችሁን በስብከት በከንቱ እያጠፋችሁት ነው፤ ሌላ ነገር ብትሠሩ ይሻላል’ ብለው የሚናገሯቸው ሰዎች አሉ። ወጣት የይሖዋ ምሥክሮቹ በዘዴ ያ ሰው እንዲህ ዓይነት ስሜት ሊሰማው በመቻሉ ማዘናቸውን በሚገልጽ መንገድ ሊመልሱለት ይችላሉ። አንድ ወጣት የምሥራቹ ሰባኪ “እርስዎን ከመሰሉ በዕድሜ የሚበልጡኝ ሰዎች ጋር በመነጋገሬ እንደምጠቀም ይሰማኛል፤ ደግሞም እደሰትበታለሁ” ብሎ ማከልን ጠቃሚ ሆኖ አግኝቶታል። ምሥራቹን መስበክ ማለት ጊዜን በከንቱ ማጥፋት ማለት አለመሆኑ ጥያቄ ውስጥም የሚገባ ነገር አይደለም። የብዙ ሰው ሕይወት በቋፍ ላይ የሚገኝበት ጊዜ ነው። አምላክ በኢዮኤል በኩል “እንዲህም ይሆናል፤ የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” በማለት ጨምሮ ተናግሯል።—ኢዮኤል 2:32
14 በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ከወላጆቻቸው ጋር የሚሰማሩ ልጆች የግል ግቦችን በማውጣት ረገድ የወላጆችን እርዳታ በደስታ ይቀበላሉ። እንዲህ ያሉ ወጣቶች ደረጃ በደረጃ ጥቅስ ከማንበብ ተነሥተው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ተስፋቸውን አብራርቶ እስከ መግለጽና ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ለሁኔታቸው ተስማሚ የሆነ ጽሑፍ እስከ ማበርከት ይደርሳሉ። ወጣት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ራሳቸው የሚያደርጉትን እድገትና የይሖዋን በረከት ሲመለከቱ ምሥራቹን በመስበክ ታላቅ ደስታ ያገኛሉ።—መዝሙር 110:3 አዓት፤ 148:12, 13
ቅንዓትና በትዕግሥት የመጠባበቅ ዝንባሌ
15. የሕዝቅኤል ምሳሌ ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ ያለንን ቅንዓት ለማቀጣጠል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
15 የአምላክ ነቢያት በዛሬው ጊዜ በአገልግሎታችን የሚያስፈልጉንን ጠባዮች ማለትም ቅንዓትንና በትዕግሥት የመጠባበቅን ዝንባሌ በማሳየት ረገድም ምሳሌ የሚሆኑ ናቸው። በመጀመሪያ እውነትን ከአምላክ ቃል ስንማር በድፍረት እንድንናገር የሚገፋፋ ኃይለኛ ቅንዓት አድሮብን ነበር። ሆኖም ከዚያ በኋላ ብዙ ዓመታት አልፈው ሊሆን ይችላል፤ ምሥክርነት የምንሰጥበትንም ክልል ብዙ ጊዜ ሸፍነነው ሊሆን ይችላል። በአሁኑ ጊዜ የመንግሥቱን መልእክት የሚቀበሉት ከስንት አንድ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ ቅንዓታችንን አቀዝቅዞታልን? እንደዚያ ከሆነ ስሙ “አምላክ ያጠነክራል” የሚል ትርጉም ያለውን ሕዝቅኤልን እንመልከት። ምንም እንኳ ሕዝቅኤል በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ልበ ደንዳና ሰዎች ቢያጋጥሙትም አምላክ አጠንክሮታል፤ እንዲሁም ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ግንባሩን ከአለት በበለጠ አጠጥሮት ነበር። በመሆኑም ሕዝቅኤል ሰዎቹ ሰሙም አልሰሙ አገልግሎቱን ለብዙ ዓመታት ማከናወን ችሏል። የእርሱ ምሳሌ እኛም እንዲሁ ማድረግ እንደምንችል ያሳያል፤ እንዲሁም ለስብከቱ ሥራ ያለንን ቅንዓት ለማቀጣጠል ሊረዳን ይችላል።—ሕዝቅኤል 3:8, 9፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:5
16. የትኛውን የሚክያስ ዝንባሌ ማዳበር ይገባናል?
16 በስምንተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ ትንቢት ይናገር የነበረው ሚክያስ በታጋሽነቱ የታወቀ ነበር። ሚክያስ “እኔ ግን ወደ እግዚአብሔር እመለከታለሁ፣ የመድኃኒቴንም አምላክ ተስፋ አደርጋለሁ፤ አምላኬም ይሰማኛል” ሲል ጽፏል። (ሚክያስ 7:7) የሚክያስ ትምክህት በጠንካራ እምነት ላይ የተመሠረተ ነበር። ልክ እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ሁሉ ሚክያስም ይሖዋ የወጠነውን ያለጥርጥር እንደሚፈጽመው ያውቅ ነበር። እኛም ይህን እናውቃለን። (ኢሳይያስ 55:11) እንግዲያው አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች ፍጻሜ በትዕግሥት የመጠባበቅን ዝንባሌ እናዳብር። ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት እምብዛም ፍላጎት በማያሳዩባቸው አካባቢዎች ጭምር ምሥራቹን በቅንዓት እንስበክ።—ቲቶ 2:14፤ ያዕቆብ 5:7–10
በዛሬው ጊዜ ትዕግሥትን ማሳየት
17, 18. ትዕግሥትን እንድናሳይ የትኞቹ ጥንታዊና ዘመናዊ ምሳሌዎች ሊረዱን ይችላሉ?
17 አንዳንዶቹ የይሖዋ ነቢያት ለብዙ ዓመታት ሥራቸውን ያለመታከት በትዕግሥት ያከናወኑ ቢሆንም የትንቢቶቻቸውን ፍጻሜ በዓይናቸው አላዩም። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ በደል እየተፈጸመባቸው በትዕግሥት ጸንተው ሥራቸውን ማከናወናቸው እኛም አገልግሎታችንን መፈጸም እንደምንችል ያስገነዝበናል። በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በነበሩት አሥርተ ዓመታት ታማኝ ቅቡዓን ካሳዩት ምሳሌም ትምህርት መቅሰም እንችላለን። ሰማያዊ ተስፋቸውን እነርሱ እንደጠበቁት ወዲያውኑ ባያገኙም ተስፋቸው የዘገየ መስሎ በመታየቱ ቅሬታ አድሮባቸው አምላክ ለእነርሱ የገለጸውን ፈቃዱን ለማድረግ ያላቸውን ቅንዓት እንዲያጠፋባቸው አልፈቀዱለትም።
18 ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል ብዙዎቹ መጠበቂያ ግንብንና የዚህ መጽሔት ተጓዳኝ የሆነውን የንቁ! መጽሔት (ቀደም ሲል ወርቃማው ዘመን ይባል ነበር፤ በኋላም ማጽናኛ ተብሎ ነበር) ለብዙ ዓመታት አሰራጭተዋል። በዛሬው ጊዜ ለመጽሔት ደንበኞቻችን እየሄድን መጽሔት እንደምናበረክትላቸው ሁሉ እነርሱም እነዚህን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸውን መጽሔቶች ሰዎች በመንገዶች ላይና በቤታቸው እንዲያገኙአቸው በማድረግ በቅንዓት ይሠሩ ነበር። አንዲት ምድራዊ ሕይወቷን የፈጸመች አረጋዊት እህት በመንገድ ላይ ምሥክርነት ስትሰጥ ሁልጊዜ ያዩአት የነበሩ በዚያ የሚያልፉ ሰዎች የት ጠፋች ብለው ጠይቀዋል። በሕዝብ ፊት ታከናውነው የነበረውን አገልግሎት ያስተዋሉ ሰዎች በሰጡአቸው የአድናቆት አስተያየቶች ላይ እንደታየው በታማኝነት እያገለገለች ባሳለፈቻቸው ብዙ ዓመታት ታላቅ ምሥክርነት ሰጥታለች! የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ እንደመሆንህ መጠን ዘወትር መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች በአገልግሎት በምታገኛቸው ሰዎች እጅ ውስጥ እንዲገቡ እያደረግህ ነውን?
19. ዕብራውያን 6:10–12 ምን ማበረታቻ ይሰጠናል?
19 የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላት ሆነው የሚያገለግሉት ወንድሞች በትዕግሥትና በታማኝነት ያከናወኑትን አገልግሎትም አስብ። ከእነርሱም መካከል በርከት ያሉት በአሁኑ ጊዜ በሰማኒያዎቹና በዘጠናዎቹ ዓመታት ዕድሜያቸው ላይ የሚገኙ ናቸው። ሆኖም እስከ አሁንም ድረስ ምድብ ሥራቸውን በቅንዓት እያከናወኑ ያሉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ናቸው። (ዕብራውያን 13:7) ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ሌሎች አረጋውያንና አልፎ ተርፎም የ“ሌሎች በጎች” ክፍል የሆኑ በዕድሜ የገፉ ሰዎችስ? (ዮሐንስ 10:16) አምላክ ሥራቸውንና ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ እንዳልሆነ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ። በዕድሜ የገፉ የይሖዋ ምሥክሮች ከእነርሱ ያነሰ ዕድሜ ካላቸው መሰል አማኞች ጋር በአምላክ አገልግሎት እምነትንና ትዕግሥትን በማሳየት የተቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ወደፊት ይግፉ። (ዕብራውያን 6:10–12) ከዚያም በጥንት ዘመን እንደነበሩት ነቢያት በትንሣኤ አለዚያም መጪውን “ታላቅ መከራ” በሕይወት አልፈው የዘላለም ሕይወትን ውድ ዋጋ ያገኛሉ።—ማቴዎስ 24:21
20. (ሀ) ነቢያት ከተዉት “ምሳሌ” ምን ትምህርት አግኝተሃል? (ለ) ነቢያት ያሳዩት ዓይነት ትዕግሥት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
20 የአምላክ ነቢያት እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትተውልናል! መከራን ችለው በመቋቋማቸው፣ ትዕግሥትን በማሳየታቸውና ሌሎችን አምላካዊ ባሕርያት በማንጸባረቃቸው በይሖዋ ስም የመናገር መብት አግኝተዋል። ዘመናዊ የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን እንደ እነርሱ እንሁን፤ እንዲሁም “በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ። በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ የሚናገረኝንም [አምላክ በእኔ በኩል የሚናገረውን አዓት] . . . አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ” በማለት እንደተናገረው እንደ ነቢዩ ዕንባቆም ዓይነት የጸና አቋም ይኑረን። (ዕንባቆም 2:1) ትዕግሥት ስናሳይና የታላቁን ፈጣሪያችንን የይሖዋን እጅግ ገናና የሆነ ስም በደስታ በሕዝብ ፊት ማሳወቃችንን ስንቀጥል ይህን የመሰለ ቆራጥ አቋም ይኑረን!—ነህምያ 8:10፤ ሮሜ 10:10
እነዚህን ነጥቦች ጨብጠሃልን?
◻ ነቢዩ አሞጽ ምን የድፍረት ምሳሌ ትቷል?
◻ ነቢዩ ሙሴ ምሳሌ የሚሆነው በምን በምን መንገዶች ነው?
◻ ዘመናዊ የይሖዋ አገልጋዮች እንደ አሞጽና እንደ ኢሳይያስ መሆን የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ክርስቲያን አገልጋዮች ሆሴዕና ኢዮኤል ካሳዩት ጠባይ ምን መማር ይችላሉ?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አሜስያስ የከረረ ተቃውሞ ቢያሳይም አሞጽ በድፍረት ትንቢት እንዲናገር የይሖዋ መንፈስ ብርታት ሰጥቶታል
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታማኝ የሆኑ ቅቡዓን በይሖዋ አገልግሎት ትዕግሥትን በማሳየት ጥሩ ምሳሌ ትተዋል
ሕዝቅኤልና ሚክያስ ካሳዩአቸው ምሳሌዎች መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?