የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 10/1 ገጽ 3-4
  • መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሙ በትክክል ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሙ በትክክል ምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ ለማስተማር ይጠቅማል
    የመንግሥት አገልግሎታችን—1995
  • መጽሐፍ ቅዱስ​—አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው መጽሐፍ
    ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው?
  • አምላክን የሚያስደስቱ እውነተኛ ትምህርቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • መጽሐፍ ቅዱስ—ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ
    መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል?
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 10/1 ገጽ 3-4

መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሙ በትክክል ምንድን ነው?

“መጽሐፍ ቅዱስ ምሥጢር ነው፤ አንብበው እንዲረዱት ተብሎ የተጻፈ መጽሐፍ አይደለም” በማለት አንድ ሰው ተናግረዋል። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሚ መጽሐፍ መሆኑን አውቃለሁ፤ ሆኖም ስለ መጽሐፉ እምብዛም አላውቅም። ሐሳቡን መረዳት በጣም አስቸጋሪ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

“ብዙዎቹ ክርስቲያኖች . . . ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያውቃሉ ማለት አይቻልም” በማለት ዘ ቶሮንቶ ስታር አትቷል። አንዲት የካቶሊክ ሴት “መጽሐፍ ቅዱስ ስላለኝ ጥሩ ስሜት ይሰማኛል። ውስጣዊ ሰላም ይሰጠኛል” ብለዋል። “መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው በዓውሎ ነፋስና በማዕበል የተሞላን የሕይወት ባሕር አቋርጦ ከአደጋ ነጻ ወደሆነ ክልል የሚመራው ኮምፓስ (አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ) ነው” በማለት አንድ ዓሣ አጥማጅ ተናግሯል። ቀደም ሲል ሂንዱ የነበሩ አንድ ሰው “መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው፤ ለሰው ዘር የተሰጠ ገጸ በረከት ነው። መንፈሳዊ ሥቃይን የሚፈውስ መድኃኒት ነው” ሲሉ ገልጸውታል።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ትክክለኛ ጠቀሜታ አስመልክቶ የሚሰነዘሩት ሐሳቦች ብዙ ከመሆናቸውም በላይ የተለያዩ ናቸው። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሙ በትክክል ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዛሬ ከተጻፉት መጻሕፍት ሁሉ የላቀ ጠቀሜታ ያለውና በስፋት የተሰራጨ መጽሐፍ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች የሰው ልጅ የሚያደርገውና የሚጨብጠው እስኪጠፋው ድረስ እጅግ ያስጨነቁትና ወደፊትም የሚገጥሙት ችግሮች ምን መፍትሔ እንዳላቸው ይናገራሉ። የሚሰጠው ምክር መሬት ጠብ የማይል በመሆኑም የሚወዳደረው የለም። የሚያቀርባቸው የሥነ ምግባር ደረጃዎችም አቻ የማይገኝላቸው ናቸው። መልእክቱ ሰውን የመለወጥ ኃይል ያለውና ጠቃሚ ነው። አቻ የማይገኝለት ጠቀሜታ የሚሰጠውን ይህን መጽሐፍ ከመደርደሪያችን ላይ አንሥተን ሐሳቦቹን አንድ በአንድ ማጤንና በጥልቀት መመርመር ይገባናል።

መጽሐፍ ቅዱስ መቶ በመቶ ትክክለኛ እንደሆነ፣ እምነት የሚጣልበትና እውነተኛ ታሪክ የያዘ መሆኑን ሙሉ በሙሉ ተማምነንበት ልንገልጠው እንችላለን። በውስጡ የተዘገቡት ታሪካዊ ክስተቶች በዓለማዊ ታሪክ የተረጋገጡ ናቸው። በአርኪዮሎጂ ጥናት የተደረሰባቸው ግኝቶች በተደጋጋሚ መጽሐፍ ቅዱስ ሐቀኛና እውነተኛ መሆኑን መሥክረዋል። መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት 40 የሚያህሉ ሰዎች አንድም ነገር ሳይሸሽጉ በግልጽ መጻፋቸው ምንም የማይዋሹና አቋማቸውን የማያጎድፉ ሰዎች መሆናቸውን ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ በውስጡ የያዘው ሐሳብ እርስ በእርሱ የሚስማማ መሆኑ የሰው ልጆች ያፈለቁት አለመሆኑን ይጠቁማል። በውስጡ የተዘገቡት ክስተቶች በእርግጥ የተከናወኑ ነገሮች ናቸው። የሚጠቅሳቸው ሰዎች የፈጠራ ሰዎች አይደሉም። የሚጠቅሳቸው ቦታዎችና ሥፍራዎች በገሃዱ ዓለም የሌሉ አይደሉም። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት ያለ ጥርጥር ይሖዋ መሆኑን ለይተው የሚያሳውቁ ጉልህ የሆኑ ትንቢቶችን መጽሐፍ ቅዱስ ይዟል።—2 ጴጥሮስ 1:21

ታላቁ አስተማሪያችን ፈቃዱንና ዓላማዎቹን ማወቅ የሚፈልጉ ሁሉ ይህን እውቀት ማግኘት የሚችሉበት ዝግጅት መኖሩን አረጋግጧል። እንዲያውም ይሖዋ ሁሉም የሰው ልጆች ቃሉን እንዲያጠኑና “ትክክለኛ የእውነት እውቀት እንዲያገኙ” እንደሚፈልግ በማያሻማ አነጋገር ገልጾልናል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4 አዓት ፤ ምሳሌ 1:5, 20–33) ይህ በሕይወት ዘመናችን ልናከናውናቸው ከምንችላቸው እጅግ አስፈላጊ ነገሮች አንዱ ነው። ይህ ሁኔታ የግድ ልንወጣው የሚገባ ፈተና ነው። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይህን ተረድተው ነበር። ከእነርሱ መካከል አንዱ እንዲህ ብሎ ለመጻፍ ተገፋፍቶ ነበር፦ “የሚሻለውን ነገር ፈትናችሁ ትወዱ ዘንድ፣ ፍቅራችሁ በእውቀትና [በትክክለኛ እውቀትና አዓት] በማስተዋል ሁሉ ከፊት ይልቅ እያደገ እንዲበዛ ይህን እጸልያለሁ።”—ፊልጵስዩስ 1:9, 10፤ ቆላስይስ 1:9, 10

ፈጣሪ ፈቃዱንና ዓላማዎቹን ለሰብአዊው ቤተሰብ ለመግለጽ የተጠቀመበት ዋነኛ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እንዲሁም እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ እንዴት በዚያ ዓላማ ውስጥ እንደተካተትን ይገልጻል። በውስጡ ቀደም ሲል የተፈጸሙ ነገሮችን ዘግቦ ይዟል፤ የወደፊቱን ጊዜ ሥዕላዊ በሆነ መንገድ በአእምሮአችን ውስጥ ቁልጭ አድርጎ ይቀርጽብናል። መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ መሠረተ ትምህርቶችን ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ይገልጻል፤ ምን ማመን እንደሚኖርብን ወይም እንደማይኖርብን በመግለጽ ትክክለኛውን አቅጣጫ ያስይዘናል። (ሥራ 17:11፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) የሰው ልጅ ሊከተላቸው የሚገቡ የጠባይ መመሪያዎችን ይሰጣል፤ እንዲሁም ሰዎችን የተሳካ ውጤት በሚያስገኝና አስደሳች በሆነ ጎዳና ይመራቸዋል። (ማቴዎስ ከምዕራፍ 5 እስከ 7) የአምላክ መንግሥት ለሰው ዘር በሙሉ ብቸኛ ተስፋ መሆኗን ጎላ አድርጎ ይገልጻል፤ እንዲሁም መንግሥቱ ስሙን ለማስቀደስና ሉዓላዊነቱን ለማስከበር እንዴት መሣሪያ ሆና እንደምታገለግልም ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ከሕይወት ሰጪያችን ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ፍቅራዊ ግንኙነት እንዲኖረን ምን ዓይነት ጎዳና መከተል እንደሚገባን ይገልጻል።

ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ የሰው ዘር ከሚያገኘው ሽልማት ሁሉ እጅግ የላቀውን ማለትም ፍጹም ሰው ሆኖ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖርን ሽልማት እንዲያገኙ የሚያስችልዎት ብቸኛ መጽሐፍ ነው። (ሮሜ 6:23) የይሖዋ አንድያ ልጅ እንዲህ በማለት ይነግረናል፦ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3) እውነትም እንዲህ ያለ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው መጽሐፍ የዘላለም ሕይወት ሽልማትን ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ለመማር ሊያነሳሳን ይገባል። የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚገልጸው መጽሐፍ ቅዱስ አንብበን እንድንረዳው ተብሎ የተጻፈ መጽሐፍ ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ