የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 10/15 ገጽ 4-7
  • ሙታን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሙታን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሞት ለሰው ዘር የታሰበ ነገር አልነበረም
  • ምን ዓይነት ተስፋ?
  • ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር የተደረጉ ግንኙነቶች
  • የእውነትና የፍቅር አምላክ የሆነው ይሖዋ
  • በሞት የተለዩን የምንወዳቸው ሰዎች ምን ይሆናሉ?
    ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት
  • ሙታንን ልትፈራ ይገባሃል?
    ንቁ!—2009
  • ከሞት በኋላ ሕይወት— እንዴት፣ የትና ደግሞስ መቼ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • የማይሞት መንፈስ አለህን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 10/15 ገጽ 4-7

ሙታን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?

ሙታንን መፍራት የመጣው የሞተው ሰው ከሞት በኋላ የምትኖር ነፍስ ወይም መንፈስ አለችው በሚለው ግምታዊ ሐሳብ የተነሣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ጽንሰ ሐሳብ ውሸት መሆኑን በግልጽ የሚያስተምር ከሆነ ሙታን ሊጎዱህ ይችላሉ ወይስ አይችሉም? የሚለው ጥያቄ እዚሁ ላይ ያከትምለታል ማለት ነው። እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሙታን ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ የአምላክ ቃል እንዲህ ይላል፦ “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፣ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።”—መክብብ 9:5, 6

ከዚህ አንጻር ስንመለከተው ሙታን ሊረዱአችሁ አለዚያም ሊጎዱአችሁ ይችላሉን? ቅዱሳን ጽሑፎች አይችሉም የሚል መልስ ይሰጣሉ። ሙታን አይሰሙም አይለሙም። በሕይወት ካሉት ሰዎች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ አይችሉም፤ ወይም ፍቅርም ሆነ ጥላቻ ማንኛውንም ዓይነት ስሜት መግለጽ አይችሉም። ወይም ደግሞ ምንም ዓይነት እርምጃ መውሰድ አይችሉም። በምንም ዓይነት ልትፈሯቸው አይገባም።

‘አዎን፣ እየተናገራችሁ ያላችሁት ስለ ሥጋዊ አካል ሞት ከሆነ ትክክል ልትሆኑ ትችላላችሁ’ በማለት አንዳንዶች ይናገሩ ይሆናል። ‘ይሁን እንጂ ሥጋዊ ሞት የሕይወት ማክተሚያ አይደለም። የሚያደርገው ነገር ቢኖር መንፈስንና ሥጋን መለያየት ብቻ ነው። ያ መንፈስ በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሊረዳ አለዚያም ሊጎዳ ይችላል።’ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት አላቸው።

ለምሳሌ ያህል በማዳጋስካር ውስጥ ሕይወት መሸጋገሪያ ብቻ ነው የሚል እምነት አለ። ስለዚህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ወይም የአንድን ሰው አስከሬን ከመቃብር ማውጣት ከሠርግ የበለጠ ከፍ ተደርጎ ይታያል። ሰውዬው የመጣው ከቀድሞ አባቶቹ ዘንድ ነው፤ ሲሞት ደግሞ ተመልሶ ወደነሱ ይሄዳል የሚል አመለካከት አላቸው። በዚህም ምክንያት በሕይወት ያሉ ሰዎች የሚኖሩባቸው ቤቶች የሚሠሩት ከጊዜ ብዛት በሚፈራርሱ እንደ እንጨትና ጡብ ከመሳሰሉ ነገሮች ነው። የሙታን “መኖሪያ” የሆኑት መቃብሮች የሚሠሩት ግን በጥቅሉ ይበልጥ በረቀቀ መንገድና ለረጅም ጊዜ መቆየት እንዲችሉ ተደርጎ ነው። የአንድን ሰው አስከሬን ከመቃብር በሚያወጡበት ጊዜ ቤተሰቡና ጓደኞቹ እንደሚባረኩ ሆኖ ይሰማቸዋል። በተጨማሪም ሴቶች የሞተውን ዘመዳችንን አጥንቶች ከነካን ወላድ እንሆናለን ብለው ያምናሉ። ይሁን እንጂ አሁንም የአምላክ ቃል ምን ይላል?

ሞት ለሰው ዘር የታሰበ ነገር አልነበረም

ይሖዋ አምላክ ሰውን የፈጠረው በሕይወት እንዲኖር መሆኑንና ሞትንም የጠቀሰው አለመታዘዝ የሚያመጣው ጣጣ መሆኑን ለመግለጽ ብቻ እንደሆነ ማወቁ የሚያስደስት ነው። (ዘፍጥረት 2:17) የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት ግን ኃጢአት መሥራታቸውና በዚህም ሳቢያ ኃጢአት ሞት የሚያስከትል ውርሻ ሆኖ ለሁሉም የሰው ዘር መዳረሱ የሚያሳዝን ነው። (ሮሜ 5:12) ስለዚህ ሞት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ካመፁበት ጊዜ ጀምሮ የሕይወት እውነታ ሆኖ ቆይቷል ብሎ መናገር ይቻላል። አዎን፣ መራራ የሕይወት እውነታ ሆኖ ቆይቷል። የተፈጠርነው በሕይወት እንድንኖር ነው። ይህም ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ሞትን የሕይወት ፍጻሜ አድርገው በማየት በጸጋ መቀበል ያቃታቸው ለምን እንደሆነ በከፊል ይጠቁመናል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ በሚለው መሠረት አምላክ አለመታዘዝ ሞት ያስከትላል በማለት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ በመቃወም ሰይጣን የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ስለ ሞት የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው ለማድረግ ሞክሯል። (ዘፍጥረት 3:4) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ግን አምላክ እንዳለው ሰዎች እንደሚሞቱ ገሃድ እየሆነ መጣ። በዚህም ምክንያት ሰይጣን ላለፉት ብዙ ዘመናት ‘ከሚሞተው የሰው አካል ላይ በሕይወት የሚተርፍ መንፈሳዊ አካል አለ’ የሚል ሌላ ውሸት በመናገር ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል። እንዲህ ያለ ማታለያ ኢየሱስ ‘የሐሰት አባት’ ብሎ ከገለጸው ከሰይጣን ዲያብሎስ ሁኔታ ጋር የሚሄድ ነገር ነው። (ዮሐንስ 8:44) በአንጻሩ አምላክ ለሞት የሰጠው ምላሽ የሚያበረታታ ተስፋ ነው።

ምን ዓይነት ተስፋ?

ይህ ለብዙዎች የሚሆን የትንሣኤ ተስፋ ነው። “ትንሣኤ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል አናስታሲስ ነው። ቃል በቃል ሲተረጎም “እንደገና መነሣት” ማለት ነው። ይህ ቃል ከሞት መነሣትን ያመለክታል። አዎን፣ ሰው በሞት ያንቀላፋል፤ ይሁን እንጂ አምላክ በኃይሉ ተጠቅሞ አንድን ሰው እንደገና ሊያስነሣው ይችላል። ሰው ሕይወትን ያጣል፤ ይሁን እንጂ አምላክ መልሶ ሕይወትን ሊሰጠው ይችላል። የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን ሰምተው የሚነሡበት ሰዓት ይመጣል” ብሏል። (ዮሐንስ 5:28, 29 አዓት) ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ይነሡ ዘንድ እንዳላቸው ተስፋ በእግዚአብሔር ዘንድ አለኝ” ሲል ገልጿል። (ሥራ 24:15) ከክርስትና ዘመን በፊት ይኖር የነበረው ታማኙ የአምላክ አገልጋይ ኢዮብም በትንሣኤ ላይ ያለውን ተስፋ ተናግሯል፦ “በውኑ ሰው ከሞተ ተመልሶ ሕያው ይሆናልን? መለወጤ እስኪመጣ ድረስ፣ የሰልፌን ዘመን ሁሉ በትዕግሥት በተጠባበቅሁ ነበር። በጠራኸኝና በመለስሁልህ ነበር።”—ኢዮብ 14:14, 15

ሙታን መንፈሳዊ አካል ይዘው በሕይወት ይኖራሉ የሚለው ሐሳብ ውሸት መሆኑን ይህ ግልጽ የትንሣኤ ተስፋ አያረጋግጥምን? ሙታን ሕያዋን ከሆኑና በሰማይ ወይም በሌላ መንፈሳዊ ዓለም በመኖር እየተደሰቱ ከሆነ ትንሣኤ ምን ትርጉም ይኖረዋል? ዋጋቸውን ወይም ዕድላቸውን ተቀብለው የለምን? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሙታን ቃል በቃል የሞቱ፣ የማይሰሙ የማይለሙ እንደሆኑና አፍቃሪው አባታችን ይሖዋ ቃል በገባው አዲስ ዓለም በገነት ውስጥ በትንሣኤ እስከሚነቁበት እስከ ታላቁ የመባነኛ ጊዜ ድረስ እንደሚያንቀላፉ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ሞት ማለት የሥጋና የመንፈስ መለያየት ማለት ካልሆነና መንፈስ በሕይወት መኖሩን የማይቀጥል ከሆነ ከመንፈሳዊ ዓለም ጋር ይደረጋሉ ስለሚባሉት ግንኙነቶችስ ምን ሊባል ይቻላል?

ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር የተደረጉ ግንኙነቶች

ከመንፈሳዊው ዓለም የመጡ ናቸው ስለሚባሉት መልእክቶች ብዙ ሪፖርቶች ተዘግበዋል። እነዚህ መልእክቶች በትክክል የመነጩት ከየት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሰይጣን ራሱ የብርሃን መልአክ መስሎ ይቀርባል። ወኪሎቹም ጥሩ ነገር አምጪዎች መስለው መቅረብ አይሳናቸውም” ሲል ያስጠነቅቀናል። (2 ቆሮንቶስ 11:14, 15 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) አዎን፣ ሰዎችን ይበልጥ በቀላሉ ለማታለልና ለማሳሳት አጋንንት (ዓመፀኛ መላእክት) አንዳንድ ጊዜ ጠቃሚ ነገር የሚለግሱ መስለው በመቅረብ ሕያዋን ከሆኑ ሰዎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ አድርገዋል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የማታለል ዘመቻ አስመልክቶ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፦ “አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና . . . የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ።” (1 ጢሞቴዎስ 4:1) ስለዚህ ከሞተው ሰው የመጣ ነው የሚባለው ማንኛውም ምላሽ ራሳቸውን “ጥሩ ነገር አምጪዎች” አስመስለው ከሚያቀርቡትና ሃይማኖታዊ ውሸት ከሚያስፋፉት እንዲሁም ሰዎችን ከአምላክ ቃል እውነት እንዲርቁ ለሚያደርጓቸው አጉል እምነቶች ባሪያ ከሚያደርጓቸው ከአጋንንት የመጣ ምላሽ መሆን አለበት።

መዝሙር 146:3, 4 [የ1879 ትርጉም] ሙታን ምንም ነገር መናገርም ሆነ ማድረግ እንደማይችሉ ወይም ምንም ነገር ሊሰማቸው እንደማይችል ሲያረጋግጥልን እንዲህ ይላል፦ “ባለቆች ማዳን በማይችሉት በሰው አትታመኑ። መንፈሱ ትወጣለች ወደ መሬትም ይመለሳል። በዚያን ጊዜ ትምክህቱ ሁሉ ይጠፋል።” “ትወጣለች” የተባለችው የትኛዋ መንፈስ ናት? በመተንፈስ የምትንቀሳቀሰው የሰው የሕይወት ኃይል ናት። ስለዚህ የሞተው ሰው መተንፈስ ሲያቆም የስሜት ሕዋሳቱ መሥራታቸውን ያቆማሉ። ምንም የማይሰማና የማይለማ ይሆናል። ስለዚህ በሕይወት ያሉትን ሰዎች ፈጽሞ ሊቆጣጠር አይችልም።

መጽሐፍ ቅዱስ ሰውም ሆነ እንስሳ ሲሞቱ ምንም ነገር የማይሰሙ በድን እንደሚሆኑና ወደተሠሩበት አፈር እንደሚመለሱ በመግለጽ የሰውን ሞት ከእንስሳ ሞት ጋር የሚያነጻጽረው ለዚህ ነው። መክብብ 3:19, 20 እንዲህ ይላል፦ “የሰው ልጆችና የእንስሳ እድል ፈንታ አንድ ነው፤ ድርሻቸውም ትክክል ነው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ የሁሉም እስትንፋስ አንድ ነው፤ ሁሉም ከንቱ ነውና ሰው ከእንስሳ ብልጫ የለውም። ሁሉ ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ነው ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል።”

አጋንንት ሰዎች ከሞተው ሰው ጋር ግንኙነት ማድረግ እንችላለን፤ እንዲሁም የሞተው ሰው በእኛ ላይ የሆነ ተጽእኖ የሚያሳድር ነገር ያደርጋል የሚል አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ለማታለል እንደሚጥሩ ይሖዋ አምላክ ስለሚያውቅ በጥንት ዘመን የነበሩትን ሕዝቡን እስራኤላውያንን እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸው ነበር፦ “ምዋርተኛም፣ ሞራ ገላጭም፣ አስማተኛም፣ መተተኛም፣ በድግምት የሚጠነቁልም፣ መናፍስትንም የሚጠራ፣ ጠንቋይም፣ ሙታን ሳቢም በአንተ ዘንድ አይገኝ። ይህንም የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የተጠላ ነው።”—ዘዳግም 18:10–12

ሙታን ሊጎዱን ይችላሉ የሚለው ሐሳብ ከአምላክ የመጣ አለመሆኑ ግልጽ ነው። እርሱ የእውነት አምላክ ነው። (መዝሙር 31:5፤ ዮሐንስ 17:17) “በመንፈስና በእውነት” ለሚያመልኩት የእውነት አፍቃሪዎች ግሩም የወደፊት ሕይወት አዘጋጅቶላቸዋል።—ዮሐንስ 4:23, 24

የእውነትና የፍቅር አምላክ የሆነው ይሖዋ

‘ሊዋሽ የማይችለው’ አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን የሞቱና ወደ መቃብር የወረዱ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አግኝተው እንደሚነሡ ቃል ገብቷል! (ቲቶ 1:1, 2፤ ዮሐንስ 5:28) ይህ ፍቅራዊ የትንሣኤ ተስፋ ይሖዋ ለሰብዓዊ ፍጥረታቱ ደህንነት እጅግ እንደሚያስብና ሞትን፣ ኀዘንንና ሥቃይን ለማስወገድ ልባዊ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል። ስለዚህ ሙታንን መፍራት ወይም ስለ እነርሱና ስለ ተስፋዎቻቸው ከሚገባው በላይ ማሰብና መጨነቅ አይገባንም። (ኢሳይያስ 25:8, 9፤ ራእይ 21:3, 4) አፍቃሪውና ፍትሐዊ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ሞት ያስከተለውን ጉዳት በማስተካከል ሊያስነሣቸው ይችላል፤ ያስነሣቸውማል።

የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ቃል በተገባው ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ በምድር ላይ የሚኖሩት ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ የሚያስረዱ ብዙ መግለጫዎችን ይዟል። (መዝሙር 37:29፤ 2 ጴጥሮስ 3:13) ሁሉም ሰው በሰላምና በደስታ እንዲሁም በፍቅር የሚኖርበት ጊዜ ይሆናል። (መዝሙር 72:7፤ ኢሳይያስ 9:7፤ 11:6–9፤ ሚክያስ 4:3, 4) ሁሉም ሰው ያለ ስጋት የሚኖርበት ጥሩ ቤት እንዲሁም አስደሳች ሥራ ይኖረዋል። (ኢሳይያስ 65:21–23) ሁሉም ሰው ሊመገባቸው የሚችል ብዙ ጥሩ ጥሩ ነገሮች ይኖራሉ። (መዝሙር 67:6፤ 72:16) ሁሉ ሰው የተሟላ ጤንነት ይኖረዋል። (ኢሳይያስ 33:24፤ 35:5, 6) ሐዋርያትና ቁጥራቸው የተወሰነ ተጨማሪ ሰዎች በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የሚገዙ ቢሆንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ የሌሎች ሰዎች ነፍሳት በሰማይ የሚያገኟቸው በረከቶች አሉ ብሎ የሚጠቅሰው ምንም ነገር የለም። (ራእይ 5:9, 10፤ 20:6) በቢልዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎች ከሞት በኋላ ሕያው ሆነው ይቀጥላሉ የሚለው አባባል እንግዳ ነገር ነው።

ይሁን እንጂ ሙታን ሕያዋን ነፍሳት ሆነው መኖራቸውን እንዳቆሙ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያስተምር ስናውቅ እንግዳ ነገር አይሆንብንም። ሙታን ሊጎዱህ አይችሉም። በመታሰቢያ መቃብር ያሉት አንቀላፍተዋል፤ አምላክ በወሰነው ጊዜ እስከሚነሡ ድረስ ምንም ነገር የማይሰሙ በድን ናቸው። (መክብብ 9:10፤ ዮሐንስ 11:11–14, 38–44) እንግዲያው ተስፋችንና ምኞታችን በአምላክ ላይ የተመካ ነው። “በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሴትም እናደርጋለን።”—ኢሳይያስ 25:9

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ቃል በግልጽ እንደሚያሳየው ሙታን ትንሣኤያቸው እስከሚደርስ ድረስ ምንም ነገር ማድረግ አይችሉም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ