የሰው ልጅ ሥቃይ የሚያከትምበት ጊዜ ይኖር ይሆን?
በሳራዬቮ በሕዝብ በተጨናነቀ አንድ የገበያ ቦታ የፈነዳ ቦምብ ያስከተለው አሠቃቂ ሁኔታ፤ በሩዋንዳ ያለው የእርስ በርስ ፍጅትና መተራረድ፤ በሶማሊያ የሚገኙ ምግብ ምግብ እያሉ የሚጮኹ የተራቡ ሕፃናት፤ በሎስ አንጀለስ የመሬት መንቀጥቀጥ ከደረሰ በኋላ የሞተባቸውን ሰው ብዛት የሚቆጥሩ በድንጋጤ ግራ የተጋቡ ቤተሰቦች፤ ጎርፍ ባጥለቀለቃት ባንግላዴሽ የሚገቡበት ጠፍቷቸው የጎርፉ ሰለባ የሆኑ ሰዎች፤ እነዚህን የመሳሰሉ አሳዛኝ የሰው ልጅ ሥቃይ ትዕይንቶች በየዕለቱ በቴሌቪዥን ወይም በመጽሔትና በጋዜጣ ይቀርቡልናል።
የሰው ልጅ ሥቃይ ያስከተለው አንዱ መጥፎ ውጤት ሰዎች በአምላክ ላይ እምነት እንዲያጡ ማድረጉ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የአይሁድ ማኅበረሰብ በታተመ ጽሑፍ ላይ የሰፈረ ሐሳብ “የክፋት መኖር ለእምነት ምን ጊዜም በጣም ከባድ እንቅፋት እንደ ፈጠረ ነው” ይላል። ደራሲዎቹ እንደ ኦሽቪትዝ ባሉ የናዚ ማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የተፈጸሙትን ጭፍጨፋዎችና በሂሮሽማ ላይ በፈነዳው ቦምብ የደረሱትን እልቂቶች ይጠቅሳሉ። ደራሲዎቹ በመቀጠል “ጻድቅና ኃያል የሆነ አምላክ የብዙ ንጹሐን ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ እንዴት ሊፈቅድ ይችላል የሚለው ጥያቄ አንድን የሃይማኖት ሰው ሕሊናውን ሊከነክነውና በጣም ግራ ሊያጋባው ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።
በጣም የሚያሳዝነው አሠቃቂ እልቂቶችን የሚገልጹ ዘገባዎች ያለማቋረጥ በመጉረፋቸው ሳቢያ የሰው ስሜት ሊደነዝዝ ይችላል። ብዙ ሰዎች ዘመዶቻቸውና የሚወዷቸው ሰዎች እስካልተነኩባቸው ድረስ በሌሎች ሰዎች ላይ የሚደርሰው ሥቃይ ምንም አይሰማቸውም።
ሆኖም ቢያንስ ለዘመዶቻችን ለማዘን መቻላችን ራሱ ስለ ፈጣሪያችን አንድ ነገር ሊያስገነዝበን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ‘በአምላክ መልክ’ እና ‘[በእሱ] ምሳሌ’ ተፈጥሯል ይላል። (ዘፍጥረት 1:26, 27) ይህ ማለት ግን ሰዎች በመልክ አምላክን ይመስላሉ ማለት አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ ‘አምላክ መንፈስ’ እንደሆነና ‘መንፈስ ደግሞ ሥጋና አጥንት’ እንደሌለው ስለገለጸ ይህ ሊሆን አይችልም። (ዮሐንስ 4:24፤ ሉቃስ 24:39) በአምላክ መልክ የተፈጠሩ መሆን የሚያመለክተው አምላካዊ የሆኑ ባሕርያትን ለማንጸባረቅ ያለንን ችሎታ ነው። ስለዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች እየተሠቃዩ ላሉ ሰዎች ስለሚያዝኑ የሰዎች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ በሥቃይ ላይ ለሚገኙት ሰብዓዊ ፍጥረቶቹ በጣም ይራራል፤ እንዲሁም ጥልቅ ሐዘን ይሰማዋል ብለን መደምደም አለብን።—ከሉቃስ 11:13 ጋር አወዳድር።
አምላክ አዛኝነቱን ያሳየበት አንዱ መንገድ የሥቃይ መንስዔ ምን እንደሆነ የሚገልጽ በጽሑፍ የሰፈረ ማብራሪያ ለሰው ዘር በመስጠት ነው። ይህንንም ያደረገው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። አምላክ ሰውን የፈጠረው እንዲሠቃይ ሳይሆን በሕይወቱ እንዲደሰት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያሳያል። (ዘፍጥረት 2:7–9) በተጨማሪም የመጀመሪያዎቹ ሰዎች የአምላክን የጽድቅ አገዛዝ አንቀበልም በማለታቸው በራሳቸው ላይ ሥቃይን እንዳመጡ ይገልጻል።—ዘዳግም 32:4, 5፤ ሮሜ 5:12
ያም ሆኖ ግን አምላክ እየተሠቃየ ላለው የሰው ልጅ ማዘኑን አልተወም። ይህም የሰውን ልጅ ሥቃይ ወደ ፍጻሜው ለማምጣት በገባው ተስፋ በግልጽ ታይቷል። “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4፤ በተጨማሪም ኢሳይያስ 25:8ን 65:17–25ና ሮሜ 8:19–21ን ተመልከት።
እነዚህ ግሩም ተስፋዎች አምላክ የሰው ልጅ ሥቃይ በጣም እንደሚሰማውና ይህን ሥቃይ ወደ ፍጻሜው ለማምጣት ቁርጥ ውሳኔ እንዳደረገ ያረጋግጣሉ። ከሁሉ በፊት ግን የሰው ልጆችን ሥቃይ ያስከተለው ምንድን ነው? አምላክስ ይህ ሥቃይ እስከ ዘመናችን እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው?
[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ሽፋንና በገጽ 32 ላይ: Alexandra Boulat/Sipa Press
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Kevin Frayer/Sipa Press