ጭንቀትህን ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣል
“በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።”—1 ጴጥሮስ 5:6, 7
1. ጭንቀት ሊነካን የሚችለው እንዴት ነው? ይህን በምሳሌ ማስረዳት የሚቻለውስ እንዴት ነው?
ጭንቀት ሕይወታችንን በእጅጉ ሊነካው ይችላል። በሬዲዮ የሚተላለፍን ጥሩ ጣዕም ያለው ሙዚቃ አንዳንድ ጊዜ ከሚያስተጓጉለው የሚንጫጫ ድምፅ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። በሬዲዮው ሞገድ ላይ ጣልቃ እየገባ የሚረብሽ ድምፅ ከሌለ ጣዕመ ዜማ ያላቸው ሙዚቃዎች ሊያረኩና ለአድማጩ የተረጋጋ መንፈስ ሊያስገኙለት ይችላሉ። ይሁን እንጂ በሬዲዮው ውስጥ የሚንጫጫው ለመስማት የሚሰቀጥጥ ድምፅ ሌላው ቀርቶ ማራኪውን ዜማ ሊለውጠውና እኛንም ሊያናድደንና ሊያበሳጨን ይችላል። ጭንቀትም ባለን የመረጋጋት መንፈስ ላይ ተመሳሳይ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። በጣም አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መሳተፍ እስኪያቅተን ድረስ በከባድ ጭንቀት ውስጥ እንድንዘፈቅ ሊያደርገን ይችላል። እውነትም “ሰውን የልቡ ኀዘን ያዋርደዋል።”—ምሳሌ 12:25
2. ኢየሱስ ክርስቶስ ‘ስለ ኑሮ ጭንቀቶች’ ምን ብሎ ነበር?
2 ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጠን በላይ በመጨነቅ አሳባችን መከፋፈሉ ስለሚያመጣው አደጋ ተናግሯል። ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት በተናገረው ትንቢት ላይ እንዲህ ሲል አሳስቧል፦ “ልባችሁ በመጠጥ ብዛትና በስካር ስለ ትዳርም በማሰብ [በመጨነቅ የ1980 ትርጉም] እንዳይከብድ፣ ያ ቀንም በድንገት እንዳይመጣባችሁ ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ በምድር ሁሉ ላይ በሚቀመጡ ሁሉ እንደ ወጥመድ ይደርስባቸዋልና። እንግዲህ ሊመጣ ካለው ከዚህ ሁሉ ለማምለጥ፣ በሰው ልጅም ፊት ለመቆም እንድትችሉ ስትጸልዩ ሁል ጊዜ ትጉ።” (ሉቃስ 21:34–36) ቁንጣን እስኪይዘን መብላትና መጠጣት አእምሮአችንን ሊያሰንፈው እንደሚችል ሁሉ ‘በኑሮ ጭንቀት’ መደቆስም የማሰብ ችሎታችንን ደብዛውን አጥፍቶ አሳዛኝ ውጤት ላይ ሊጥለን ይችላል።
የጭንቀት ምንነት
3. ጭንቀት ተብሎ የተተረጎመው “አንዛይቲ” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ምን ፍቺ ተሰጥቶታል? ከመንስኤዎቹ መካከል አንዳንዶቹስ ምንድን ናቸው?
3 ጭንቀት ተብሎ የተተረጎመው “አንዛይቲ” የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል “ብዙውን ጊዜ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚከሰት ወይም ይከሰታል ተብሎ በሚጠበቅ መጥፎ አጋጣሚ ሳቢያ የሚመጣ ስጋት ወይም የሚያስፈራ ሐሳብ ነው” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። “ጭንቅ ጥብብ የሚያደርግ አሳብ ወይም ስሜት” ነው። እንዲሁም “ብዙውን ጊዜ (በላብ መጠመቅን፣ ውጥረትንና የልብ ትርታ መጨመርን በመሰሉ) አካላዊ ምልክቶችና የተፈጠረው ስጋት እውነት ይከሰት ይሆን፤ የሚከሰተውስ በዚህ መልኩ ይሆን በሚል ጥርጣሬ እንዲሁም ችግሩን የመቋቋም አቅም ይኖረኝ ይሆን በማለት በራሳችን ላይ በምናሳድረው ጥርጣሬ ተለይቶ የሚታወቅ ተፈጥሮአዊ ያልሆነና የምንይዘውንና የምንጨብጠው እስኪጠፋን ድረስ ግራ የሚያጋባ የስጋትና የፍርሃት ስሜት ነው።” (ዌብስተርስ ናይንዝ ኒው ኮሊጂየት ዲክሽነሪ) ስለዚህ ጭንቀት የተወሳሰበ ችግር ሊሆን ይችላል። ከብዙዎቹ መንስኤዎቹ መካከል በሽታ፣ እርጅና፣ ወንጀልን መፍራት፣ የሥራ ማጣትና ስለ ቤተሰብ ደህንነት ማሰብ አንዳንዶቹ ናቸው።
4. (ሀ) ስለ ሰዎችና ስለሚያስጨንቋቸው ነገሮች ምን ማስታወሳችን ጥሩ ነው? (ለ) ጭንቀት ካጋጠመን ምን ማድረግ ይቻላል?
4 ጭንቀት መንስኤዎቹ የተለያዩ ሁኔታዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ሁሉ ደረጃዎቹም የተለያዩ ናቸው። ለአንድ ሁኔታ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት ስሜት አያሳይም። በመሆኑም አንድ የሆነ ነገር ለእኛ ችግር ባይፈጥርብንም እንኳ እንደ እኛው የይሖዋ አምላኪዎች ለሆኑ ለአንዳንዶች የከባድ ጭንቀት መንስኤ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ይገባናል። ጭንቀት ሰላምን በሚያስገኘውና አስደሳች በሆነው የአምላክ ቃል እውነት ላይ ማተኮር እስኪሳነን ድረስ ከከበደን ምን ማድረግ ይቻላል? በይሖዋ ሉዓላዊነትና በክርስቲያን የአቋም ጽናት ረገድ ስለተነሡት አከራካሪ ጉዳዮች በትኩረት ማሰባችንን መቀጠል አዳጋች እስኪሆንብን ድረስ በጭንቀት ብንደቆስ ሊደረግ የሚችለው ነገር ምንድን ነው? ሁኔታዎቻችንን መለወጥ አንችል ይሆናል። ከዚህ ይልቅ እጅግ በተወሳሰቡ የኑሮ ችግሮች ሳቢያ የተከሰተን ከልክ ያለፈ ጭንቀት ለመቋቋም የሚረዱንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦች መፈለግ ይገባናል።
እርዳታ አለልን
5. ከመዝሙር 55:22 ጋር የሚስማማ ነገር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
5 ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜና በጭንቀት በሚወጠሩበት ጊዜ ከአምላክ ቃል ማጽናኛ ማግኘት ይችላሉ። እምነት የሚጣልበት መመሪያ እናገኝበታለን፤ እንዲሁም ይሖዋን በታማኝነት ከጎኑ ቆመን የምናገለግል አገልጋዮቹ እንደመሆናችን መጠን ብቻችንን እንዳልሆንን የሚያሳዩ ብዙ ማረጋገጫዎችን ይሰጠናል። ለምሳሌ ያህል መዝሙራዊው ዳዊት እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።” (መዝሙር 55:22) ከእነዚህ ቃላት ጋር የሚስማማ ነገር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የሚያስጨንቁንንና ስጋት የሚፈጥሩብንን ነገሮች እንዲሁም ያሰብነው ሳይሆንልን ቀርቶ የሚሰማንን ቅሬታ በሙሉ በአፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን ላይ በመጣል ነው። ይህም የደህንነት ስሜትና የልብ መረጋጋት እንድናገኝ ይረዳናል።
6. ፊልጵስዩስ 4:6, 7 በሚለው መሠረት ጸሎት ምን ሊያደርግልን ይችላል?
6 ጭንቀታችንን ሁሉ ጨምሮ ሸክማችንን በይሖዋ ላይ እንድንጥል ከተፈለገ ዘወትር ልባዊ ጸሎት ማቅረብ የግድ አስፈላጊ ነው። ይህም ውስጣዊ ሰላም ያስገኝልናል። ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ። አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) ተወዳዳሪ የሌለው “የእግዚአብሔር ሰላም” ራሳቸውን ለወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች ሌላው ቀርቶ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎች በሚያጋጥሟቸው ጊዜም እንኳ ያልተለመደ የመረጋጋት መንፈስ ይሰጣቸዋል። ይህ የሚገኘው ከአምላክ ጋር ባለን የቀረበ የግል ዝምድና ነው። መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ስንጸልይና መንፈስ ቅዱስ እንዲያነሳሳን ስናደርግ ከኑሮ ችግሮች በጠቅላላ አይገላግለንም። ከዚህ ይልቅ የመንፈስ ፍሬ የሆነውን ሰላምን እናገኛለን። (ሉቃስ 11:13፤ ገላትያ 5:22, 23) ይሖዋ ታማኝ ሕዝቡን በሙሉ ‘በሰላም እንዲኖሩ’ እንደሚያደርግና ዘላቂ ጉዳት የሚያመጣ ነገር እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ ስለምናውቅ ለጭንቀት እጃችንን አንሰጥም።—መዝሙር 4:8
7. ጭንቀትንን እንድንቋቋም በመርዳት ረገድ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ምን ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ?
7 ሆኖም በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ እያሰላሰልንና በጸሎት እየተጋንም እንኳ ጭንቀታችን እንዳለ ቢቀጥል ምን ማድረግ እንችላለን? (ሮሜ 12:12) በጉባኤ ውስጥ ያሉት የተሾሙ ሽማግሌዎችም ይሖዋ እኛን በመንፈሳዊ ለመርዳት ያዘጋጃቸው ናቸው። የአምላክን ቃል በመጠቀም፣ ከእኛ ጋር በመጸለይና ለእኛ በመጸለይ ሊያጽናኑንና ሊረዱን ይችላሉ። (ያዕቆብ 5:13–16) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደ እሱ ሽማግሌ የሆኑት የአምላክን መንጋ በፈቃደኝነት፣ ከልብ ተነሳስተውና ምሳሌ እየሆኑ እንዲጠብቁ አሳስቧቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:1–4) እነዚህ ሰዎች ስለ ደህንነታችን ከልብ ያስባሉ፤ እኛን ለመርዳትም ይፈልጋሉ። እርግጥ ከሽማግሌዎች እርዳታ ሙሉ ጥቅም ለማግኘትና በጉባኤ ውስጥ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ይዞ ለመመላለስ ሁላችንም የሚከተለውን የጴጥሮስ ምክር ልንሠራበት ይገባል፦ “ጎበዞች ሆይ፣ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም እርስ በእርሳችሁ እየተዋረዳችሁ ትሕትናን እንደ ልብስ ታጠቁ፣ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማልና፣ ለትሑታን ግን ጸጋን [ይገባናል የማንለውን ደግነት አዓት] ይሰጣል።”—1 ጴጥሮስ 5:5
8, 9. ከ1 ጴጥሮስ 5:6–11 ምን ማጽናኛ ማግኘት ይቻላል?
8 ጴጥሮስ እንዲህ ሲል አክሎ ተናግሯል፦ “እንግዲህ በጊዜው ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፤ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት። በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዘላለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ራሱ ፍጹማን ያደርጋችኋል ያጸናችሁማል ያበረታችሁማል። ለእርሱ ክብርና ኃይል እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።”—1 ጴጥሮስ 5:6–11
9 ‘አምላክ ስለ እኛ ስለሚያስብ የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል’ እንደምንችል መገንዘባችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! ከጭንቀታችን መካከል አንዳንዱ ዲያብሎስ ስደትና የተለያዩ መከራዎችን በማምጣት እኛን ከይሖዋ ጋር ለማቆራረጥ ከሚያደርገው ሙከራ የመነጩ ከሆኑ አቋማቸውን ሳያበላሹ ከይሖዋ ጋር ተጣብቀው የሚኖሩ በመጨረሻው ሁሉም ነገር ወደ ጥሩ ሁኔታ እንደሚለወጥላቸው ማወቁ ግሩም አይደለምን? አዎን፣ ለጥቂት ጊዜ ከተሠቃየን በኋላ ይገባናል የማንለውን ደግነት የሚያሳየን አምላክ ሥልጠናችንን ይጨርስና ጸንተንና በርትተን እንድንቆም ያደርገናል።
10. አንደኛ ጴጥሮስ 5:6, 7 ጭንቀትን ለማቃለል የሚረዱ ምን ሦስት ባሕርያትን ይጠቁማል?
10 አንደኛ ጴጥሮስ 5:6, 7 ጭንቀትን እንድንቋቋም የሚረዱ ሦስት ባሕርያትን ይጠቁመናል። አንደኛው ትሕትና ወይም ‘ራስን ዝቅ ማድረግ’ ነው። ቁጥር 6 ላይ ያለው “በጊዜው” የሚለው መግለጫ ትዕግሥት እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል። ቁጥር 7 አምላክ ‘ስለ እኛ ስለሚያስብ’ በእምነት ጭንቀታችንን ሁሉ በእርሱ ላይ መጣል እንደምንችል ያሳያል። እንዲሁም እነዚህ ቃላት በይሖዋ ላይ ሙሉ እምነት እንዲያድርብን ያበረታታሉ። እንግዲያው ትሕትና፣ ትዕግሥትና በአምላክ ላይ ሙሉ እምነት መጣል ጭንቀትን ለማቃለል እንዴት ሊረዱን እንደሚችሉ እንመልከት።
ትሕትና እንዴት ሊረዳ እንደሚችል
11. ትሕትና ጭንቀትን መቋቋም እንድንችል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
11 ትሑቶች ከሆንን የአምላክ አሳብ ከእኛ አሳብ በእጅጉ የላቀ መሆኑን አምነን እንቀበላለን። (ኢሳይያስ 55:8, 9) ትሕትና የማሰብ ችሎታችን ሁሉን ነገር መረዳት ከሚችለው ከይሖዋ የማሰብ ችሎታ ጋር ሲወዳደር በጣም ውስን መሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል። በጻድቁ ሰው በኢዮብ ላይ እንደታየው እኛ የማንረዳቸውን ነገሮች እርሱ ይመለከታል። (ኢዮብ 1:7–12፤ 2:1–6) “ከኃይለኛው ከእግዚአብሔር እጅ በታች” ራሳችንን ዝቅ በማድረግ ከታላቁ ሉዓላዊ ገዥ ጋር ሲነጻጸር ያለንን ዝቅተኛ ቦታ አምነን እንቀበላለን። ይህም እሱ እንዲደርሱብን የፈቀዳቸውን ሁኔታዎች እንድንቋቋም ይረዳናል። ልባችን ቶሎ እፎይታን ለማግኘት በጣም ሊጓጓ ይችላል፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ ባሕርያቱ ፍጹም ሚዛናቸውን የጠበቁ በመሆናቸው ለእኛ ሲል እርምጃ የሚወስድበትን ትክክለኛ ጊዜ ለይቶ ያውቃል። እንግዲያው እንደ ሕፃናት በመሆን ይሖዋ ጭንቀታችንን እንድንቋቋም እንደሚረዳን ተማምነን በትሕትና የይሖዋን ኃያል እጅ ሙጥኝ ብለን እንያዝ።—ኢሳይያስ 41:8–13
12. የዕብራውያን 13:5ን ቃላት በትሕትና በሥራ ላይ ካዋልን ስለ ቁሳዊ ነገሮች የመጨነቁ ጉዳይ ሊነካ የሚችለው እንዴት ነው?
12 ትሕትና ብዙውን ጊዜ ጭንቀታችንን ሊያቃልል የሚችለውን የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ምክር በሥራ ለማዋል ፈቃደኛ መሆንንም ይጨምራል። ለምሳሌ ያህል ጭንቀታችን የተከሰተው ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ በጣም በመጠመዳችን ሳቢያ ከሆነ የሚከተለውን የጳውሎስ ምክር ልብ ማለታችን ጥሩ ሊሆን ይችላል፦ “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፣ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ፦ አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና።” (ዕብራውያን 13:5) እንዲህ ያለውን ምክር በትሕትና በሥራ ላይ በማዋል ብዙዎች ለቁሳዊ ደህንነት በእጅጉ ከመጨነቅ ተገላግለዋል። የገንዘብ ችግራቸው ሊሻሻል ባይችልም እንኳ መንፈሳዊነታቸው እስኪጎዳ ድረስ አሳባቸውን አልተቆጣጠረውም።
ትዕግሥት የሚጫወተው ሚና
13, 14. (ሀ) በትዕግሥት መጽናትን በተመለከተ ኢዮብ ምን ምሳሌ ትቷል? (ለ) ይሖዋን በትዕግሥት መጠባበቃችን ምን ሊያደርግልን ይችላል?
13 በ1 ጴጥሮስ 5:6 ላይ ያለው “በጊዜው” የሚለው አገላለጽ በትዕግሥት የመጽናትን አስፈላጊነት ይጠቁማል። አንዳንድ ጊዜ አንድ ችግር ለረጅም ጊዜ ሊዘልቅ ይችላል። ይህም ጭንቀቱን ሊያባብሰው ይችላል። ነገሮችን ለይሖዋ መተው የሚያስፈልገን በተለይ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሲያጋጥም ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን [ደስተኞች አዓት] እንላቸዋለን፤ ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል፤ ጌታ እጅግ የሚምር የሚራራም ነውና።” (ያዕቆብ 5:11) ኢዮብ የኢኮኖሚ ክስረት ደርሶበታል፣ አሥር ልጆቹን በሞት ተነጥቋል፣ በሚዘገንን በሽታ ቁም ስቅሉን አይቷል፣ እንዲሁም ከሐሰተኛ አጽናኞች የተሳሳተ ነቀፋ ደርሶበታል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ቢያንስ ቢያንስ የተወሰነ ደረጃ ድረስ መጨነቁ ያለ ነገር ነው።
14 ያም ሆነ ይህ ኢዮብ በትዕግሥት የመጽናት ምሳሌ ነው። ከባድ የእምነት ፈተና ቢደርስብን ልክ እሱ እንዳደረገው እፎይታን ለማግኘት መታገሥ ሊኖርብን ይችላል። ይሁን እንጂ አምላክ ለእሱ ሲል እርምጃ ወስዷል፤ በመጨረሻ ኢዮብን ከሥቃዩ በመገላገል የተትረፈረፈ ወሮታ ከፍሎታል። (ኢዮብ 42:10–17) በትዕግሥት ይሖዋን መጠባበቅ ጽናታችንን ያጎለብተዋል፤ እንዲሁም ለእርሱ ምን ያህል እንዳደርን ያሳያል።—ያዕቆብ 1:2–4
በይሖዋ ታመኑ
15. በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን ያለብን ለምንድን ነው?
15 ጴጥሮስ እንደሱዉ አማኝ የሆኑትን አምላክ “ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” ሲል አሳስቧቸዋል። (1 ጴጥሮስ 5:7) ስለዚህ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን እንችላለን፤ መታመንም ይኖርብናል። ምሳሌ 3:5, 6 “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህም ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል” ይላል። በጭንቀት የተያዙ አንዳንዶች ከዚህ ቀደም ባጋጠሟቸው ሁኔታዎች የተነሣ ሌሎች ሰዎችን ለማመን ይቸገራሉ። ሆኖም የሕይወታችን ምንጭና ተንከባካቢ የሆነውን ፈጣሪያችን የምናምንበት በቂ ምክንያት አለን። አንድ የተወሰነ ነገር ቢደርስብን ራሳችን የምናሳየውን ምላሽ ልንታመንበት ባንችልም ከደረሰብን መከራ እንዲያላቅቀን ሁልጊዜ በይሖዋ ላይ መደገፍ እንችላለን።—መዝሙር 34:18, 19፤ 36:9፤ 56:3, 4
16. ኢየሱስ ክርስቶስ ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅን አስመልክቶ ምን ብሏል?
16 በአምላክ መታመን ከአባቱ የተማረውን ነገር ያስተማረውን ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስ መታዘዝን ይጨምራል። (ዮሐንስ 7:16) ኢየሱስ ይሖዋን በማገልገል ‘በሰማይ መዝገብ እንዲሰበስቡ’ ደቀ መዛሙርቱን አሳስቧቸዋል። ይሁን እንጂ ምግብን፣ ልብስንና መጠለያን ስለሚመለከቱ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮችስ ምን ሊባል ይቻላል? ኢየሱስ “አትጨነቁ” ሲል መክሯል። አምላክ ወፎችን እንደሚመግብ ጠቅሷል። አበቦችን ውብ በሆነ መንገድ ያለብሳቸዋል። የአምላክ ሰብዓዊ አገልጋዮች ከእነዚህ አይበልጡምን? እንዴታ፣ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ ሲል አሳስቧል፦ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፣ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል።” ኢየሱስ በመቀጠል “የነገው ጭንቀት ለነገው ይበቃል፤ ስለዚህ ለነገ አትጨነቁ [የ1980 ትርጉም]” ብሏል። (ማቴዎስ 6:20, 25–34) አዎን፣ ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስና መጠለያ ያስፈልገናል፤ ይሁን እንጂ በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ስለ እነዚህ ነገሮች ከልክ በላይ አንጨነቅም።
17. አስቀድሞ መንግሥቱን የመፈለግን አስፈላጊነት እንዴት በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል?
17 መንግሥቱን ቅድሚያ ሰጥተን ለመፈለግ በአምላክ መታመንና የምናስቀድማቸውን ነገሮች ትክክለኛውን ቅደም ተከተል ማስያዝ አለብን። የመተንፈሻ መሣሪያ ሳይዝ በውኃ ውስጥ ለውስጥ የሚዋኝ ዋናተኛ በውስጡ ዕንቁ የያዘ ዛጎል ፍለጋ ወደ ባሕሩ ወለል ሊጠልቅ ይችላል። ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው በዚህ መንገድ ነው። በእርግጥም ከፍተኛ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው! ይሁን እንጂ ከዚህ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ምንድን ነው? አየር ነው! ሳንባዎቹን በአየር ለመሙላት አዘውትሮ ወደ ላይ ብቅ ማለት አለበት። አየር ይበልጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነው። ልክ እንደዚሁም ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማግኘት በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ በተወሰነ ደረጃ አንዳንድ ሥራ ለመሥራት እንገደድ ይሆናል። ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፤ ምክንያቱም የቤተሰቡ ሕይወት የተመካው በእነዚህ ነገሮች ላይ ነው። አስፈላጊ ስለሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ከልክ በላይ እንዳንጨነቅ በአምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን አለብን። ከዚህም በላይ ‘የጌታ ሥራ ሲበዛልን’ “የይሖዋ ደስታ መሸሸጊያችን” ስለሚሆን ጭንቀታችን ይቀንስልናል።—1 ቆሮንቶስ 15:58፤ ነህምያ 8:10 አዓት
ጭንቀታችሁን በይሖዋ ላይ መጣላችሁን ቀጥሉ
18. ጭንቀታችንን ሁሉ በይሖዋ ላይ መጣላችን በእርግጥ ሊረዳን እንደሚችል የሚያሳይ ምን ማስረጃ አለ?
18 ሁልጊዜ በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ማተኮር እንድንችል ጭንቀታችንን ሁሉ በይሖዋ ላይ መጣላችንን መቀጠል አለብን። ለአገልጋዮቹ እንደሚያስብ ሁልጊዜ አስታውሱ። ይህን በምሳሌ ማስረዳት ይቻላል፦ አንዲት ክርስቲያን ሴት ባሏ ለእርሷ ታማኝ ሆኖ ባለመገኘቱ እንቅልፍ በዓይኗ አልዞር እስኪል ድረስ ተጨነቀች። (ከመዝሙር 119:28 አዓት ጋር አወዳድር።) ይሁን እንጂ ስትተኛ ጭንቀቷን ሁሉ በይሖዋ ላይ ትጥል ነበር። እሷና ሁለት ትንንሽ ሴት ልጆቿ እየተሠቃዩ መሆናቸውን በመንገር የልቧን ሁሉ ለአምላክ ታፈስለት ነበር። ይሖዋ እሷንና ልጆቿን እንደሚንከባከባቸው ታምን ስለነበር እፎይታን ለማግኘት እየጮኸች ከልቧ ከጸለየች በኋላ ሁልጊዜ እንቅልፍ ይወስዳት ነበር። ቅዱስ ጹሑፋዊ በሆነ መንገድ የተፋታችው ይህች ሴት በአሁኑ ጊዜ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ አግብታ በደስታ ትኖራለች።
19, 20. (ሀ) ጭንቀትን ልንቋቋም የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? (ለ) ጭንቀታችንን በሙሉ ምን ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል?
19 የይሖዋ ሕዝብ እንደመሆናችን መጠን ጭንቀትን መቋቋም የምንችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። በተለይ የአምላክን ቃል በሥራ ላይ ማዋል ጠቃሚ ነው። በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! ላይ እየታተሙ የሚወጡ ጠቃሚና ገንቢ የሆኑ ርዕሶችን ጨምሮ አምላክ “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል የሚያዘጋጀው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አለን። (ማቴዎስ 24:45–47) የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እርዳታ እናገኛለን። ቋሚና ልባዊ የሆነ ጸሎት በእጅጉ ይጠቅመናል። የተሾሙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች መንፈሳዊ እርዳታና ማጽናኛ ለመስጠት ዝግጁና ፈቃደኞች ናቸው።
20 የራሳችን ትሕትናና ትዕግሥት በጣም የከበደንን ጭንቀት መቋቋም እንድንችል በጣም ይጠቅሙናል። በተለይ ደግሞ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመናችን በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም እምነታችን የሚጎለብተው የእሱን እርዳታና መመሪያ ስናገኝ ነው። አምላክን ማመናችን ደግሞ ከልክ በላይ እንዳንረበሽ ሊያደርገን ይችላል። (ዮሐንስ 14:1) እምነት አስቀድመን መንግሥቱን እንድንፈልግና ጭንቀትን እንድንቋቋም ሊረዳን በሚችለው አስደሳች የጌታ ሥራ እንድንጠመድ ያነሳሳናል። ይህን የመሰለው እንቅስቃሴ የአምላክን የውዳሴ መዝሙር ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚዘምሩት መካከል እንደምንገኝ አስተማማኝ ሁኔታ እንዲሰማን ያደርጋል። (መዝሙር 104:33) እንግዲያው ጭንቀታችንን ሁሉ በይሖዋ ላይ መጣላችንን እንቀጥል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ጭንቀት ምን የሚል ፍቺ ሊሰጠው ይችላል?
◻ ጭንቀትን ልንቋቋም የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
◻ ትሕትናና ትዕግሥት ጭንቀትን ለማቃለል ሊረዱን የሚችሉት እንዴት ነው?
◻ ጭንቀትን በመቋቋም ረገድ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መታመን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
◻ ጭንቀታችንን ሁሉ በይሖዋ ላይ መጣላችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ “አትጨነቁ” ያለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህን?