በ20ኛው መቶ ዘመን በአምላክ ላይ የተፈጸመ ክህደት
“የሚያስከትልባቸው ውጤት ጥሩም ይሁን መጥፎ ሰዎች አምላክ የለም የሚለውን አመለካከት አሜን ብለው በመቀበልና አምላክን ፈጽሞ ከአእምሮአቸው በማውጣት የራሳቸውን ሕይወት በራሳቸው እየመሩ ነው።”—ዋን ሃንድረድ ይርስ ኦቭ ዲቤት ኦቨር ጎድ—ዘ ሶርስስ ኦቭ ሞደርን ኤቲዝም
ረጅም ዛፍ ምንም እንኳ በመጀመሪያ ሲታይ የሚማርክ ቢሆንም እያደር ግን የትም ቦታ የሚገኝ ነገር ተደርጎ መታየት ይጀምራል። የዛፉ መኖር የተለመደ ነገር ይሆናል፤ ከዚያ በኋላ ቁመቱ የመጀመሪያውን ያህል አስገራሚ አይሆንም።
አምላክ የለም ባይነትም እንደዚሁ ነው። አምላክ የለም የሚለው አመለካከት በ19ኛው መቶ ዘመን ብዙ ክርክር አስነስቶ የነበረ ቢሆንም በዛሬው ጊዜ ግን የአምላክን መኖር መካድ የሚያስቆጣ ወይም የሚረብሽ ነገር አይደለም። ተቀባይነት ኖረውም አልኖረው ሰዎች የራሳቸውን እምነትና አመለካከት መከተል የሚችሉበት ይህ ዘመን አምላክ የለም ባይነት በአምላክ ከማመን ጋር በሰላም መኖር እንዲችል በር ከፍቶለታል።
ይህ ማለት ግን አብዛኛዎቹ ሰዎች በቀጥታ አምላክ የለም ይላሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በእስያ በሚገኙ 11 አገሮች በተወሰኑ ሰዎች ላይ የተካሄደ የአንድ ጥናት ውጤት እንደሚያሳየው አምላክ የለም ባዮች በአማካይ ከ2 በመቶ አይበልጡም። ያም ሆነ ይህ የአምላክ የለሽነት መንፈስ ሌላው ቀርቶ አምላክ አለ ብለው በሚያምኑ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተስፋፍቷል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?
የአምላክን ሥልጣን መካድ
“አንዳንድ ጊዜ አምላክ የለም ባይነት በተግባር አምላክን መካድን ወይም ቸል ማለትን ያመለክታል” ሲል ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና ገልጿል። በዚህም ምክንያት ዘ ኒው ሾርተር ኦክስፎርድ ኢንግሊሽ ዲክሽነሪ “ኤቲስት [አምላክ የለም ባይ]” ለተባለው የእንግሊዝኛ ቃል “በሥነ ምግባር አምላክን የሚክድ ሰው፤ አምላክ የሌለው ሰው” የሚል ሁለተኛ ፍቺ ሰጥቶታል።—ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
አዎን፣ አምላክ የለም ባይነት የአምላክን መኖር አለዚያም ሥልጣኑን መካድ ወይም ደግሞ ሁለቱንም ያካተተ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የአምላክ የለሽነት መንፈስ በቲቶ 1:16 ላይ “እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፣ ዳሩ ግን . . . በሥራቸው ይክዱታል” በማለት ይጠቅሰዋል።—ከመዝሙር 14:1 ጋር አወዳድር።
እንዲህ ዓይነቱ የአምላክን ሥልጣን ያለ መቀበል ሁኔታ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ባልና ሚስት ወደ ነበሩበት ጊዜ መለስ ብለን ልንመለከተው እንችላለን። ሔዋን የአምላክን መኖር አምና ተቀብላ ነበር፤ ሆኖም ‘እንደ አምላክ መልካሙንና ክፉውን የምታውቅ ለመሆን’ ፈለገች። ይህም ‘የራስዋ አለቃ ልትሆን’ እንደነበረና የራስዋን የሥነ ምግባር ሕግጋት ልታወጣ እንደነበረ ይጠቁማል። በኋላም አዳም በዚህ የአምላክን ሥልጣን የመካድ ተግባር ከሔዋን ጎን ቆመ።—ዘፍጥረት 3:5, 6
ይህ አመለካከት በጊዜያችን ተስፋፍቷልን? እንዴታ። ራስን ነጻ ለማውጣት በሚደረገው ከፍተኛ ጥረት አንድ ረቂቅ የሆነ አምላክ የለም ባይነት ተንጸባርቋል። “በዛሬው ጊዜ ሰዎች በአምላክ ቁጥጥር ሥር መኖር ሰልችቷቸዋል” በማለት ዋን ሃንድረድ ይርስ ኦቭ ዲቤት ኦቨር ጎድ—ዘ ሶርስስ ኦቭ ሞደርን ኤቲዝም የተባለው መጽሐፍ ተናግሯል። “ሰዎች . . . በነጻነት መኖር ይመርጣሉ።” የመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ሕግ ተግባራዊ ሊሆን የማይችልና ከእውነታ የራቀ ነው በሚል ወደ ጎን ገሸሽ ተደርጓል። የብዙዎቹ አስተሳሰብ “ቃሉን እሰማ ዘንድ . . . እግዚአብሔር ማን ነው? እግዚአብሔርን አላውቅም” በማለት በዕብሪት እንደተናገረው እንደ ግብፁ ፈርዖን ነው። ፈርዖን የይሖዋን ሥልጣን አልቀበልም ብሎ ነበር።—ዘጸአት 5:2
ሕዝበ ክርስትና በአምላክ ላይ የፈጸመችው ክህደት
በአምላክ ሥልጣን ላይ ከሁሉ የበለጠ አሳፋሪ ክህደት የፈጸሙት ንፁሕ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ሰው ሠራሽ በሆኑ ወጎች የተኩት የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ናቸው። (ከማቴዎስ 15:9 ጋር አወዳድር።) ከዚህም በተጨማሪ በ20ኛው መቶ ዘመን የተካሄዱትን ይህ ነው የማይባል ደም የፈሰሰባቸውን ጦርነቶች ደግፈዋል፤ በዚህም መንገድ እውነተኛ ፍቅር እንድናሳይ የሚያዘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ጎን ገሸሽ አድርገዋል።—ዮሐንስ 13:35
በተጨማሪም ቀሳውስት በአምላክ የሥነ ምግባር አቋም ደረጃዎች ላይ ጀርባቸውን በማዞር አምላክን ክደዋል። ለምሳሌ እንደ ማስረጃ መጥቀስ ቢያስፈልግ በልጆች ላይ የጾታ ብልግና የፈጸሙ ቄሶችን ጉዳይ ለመመልከት ምን ጊዜም የፍርድ ቤት ሙግት እንደተካሄደ ነው። ሕዝበ ክርስትና ያለችበት ሁኔታ የጥንቶቹ እስራኤልና ይሁዳ ከነበሩበት ሁኔታ ጋር ይመሳሰላል። “ምድሪቱም ደም፣ ከተማይቱም ዓመፅን ተሞልታለች፤ እነርሱም:– እግዚአብሔር ምድሪቱን ትቶአታል እግዚአብሔርም አያይም ብለዋል” ተብሎ ለነቢዩ ሕዝቅኤል ተነግሮት ነበር። (ሕዝቅኤል 9:9፤ ከኢሳይያስ 29:15 ጋር አወዳድር።) እንግዲያው ብዙዎች የሕዝበ ክርስትናን አብያተ ክርስቲያናት ከናካቴው እርግፍ አድርገው መተዋቸው አያስደንቅም! ይሁን እንጂ በአምላክ ማመናቸውን መተው አለባቸውን?
አምላክ የለም ለማለት አጥጋቢ ምክንያቶች ናቸውን?
የሃይማኖትን ግብዝነት አስተዋሉም አላስተዋሉ ብዙ አምላክ የለም ባዮች በአምላክ ማመንን በዓለም ላይ ካለው መከራ ጋር አንድ ላይ አጣምሮ መቀበል ያዳግታቸዋል። አንድ ጊዜ ሲሞን ደ በቭዋ የተባሉ ሴት “በዓለም ላይ ያለው እርስ በእርሱ የሚጋጭ ነገር ሁሉ የተቆለለበት ፈጣሪ አለ ብዬ ከማሰብ ይልቅ ፈጣሪ የለም ብዬ ማሰብ ይቀለኛል” ብለዋል።
በግብዝ ሃይማኖተኞች ቆስቋሽነት የሚፈጸመውን ጨምሮ በዓለም ያለው ግፍ አምላክ እንደሌለ የሚያረጋግጥ ነውን? እስቲ አስበው:– አንድ ቢላዋ ለማስፈራራት ፣ለማቁሰል ወይም ከዚያም አልፎ አንድን ንጹሕ ሰው ለመግደል ቢጠቀሙበት ይህ ድርጊት ቢላዋው ሠሪ እንደሌለው ያረጋግጣልን? ከዚህ ይልቅ ዕቃው በተሳሳተ መንገድ ጥቅም ላይ እንደዋለ አያሳይምን? ልክ እንደዚሁም በሰው ላይ የደረሰው አብዛኛው ሐዘን የሰው ልጆች አምላክ የሰጣቸውን ችሎታ እንዲሁም ምድርን ራሷን አላግባብ እየተጠቀሙባቸው እንዳለ የሚያሳይ ነው።
ይሁን እንጂ አንዳንዶች ልናየው እስካልቻልን ድረስ በአምላክ ማመን ምክንያታዊ አይደለም የሚል ስሜት ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ አየር፣ የድምፅ ሞገድና ሽታስ? እነዚህንም ነገሮች በጭራሽ ልናያቸው አንችልም፤ ሆኖም እነዚህ ነገሮች እንዳሉ እናውቃለን። ሳንባችን፣ ጆሮዎቻችንና አፍንጫችን ይህን ይነግሩናል። ማስረጃ ካለን ሊታይ በማይችለውም ነገር እንደምናምን የተረጋገጠ ነው።
የሳይንስ ጠበብት የሆኑት ኧርቪንግ ዊልያም ክኖብሎክ ኤሌክትሮኖችን፣ ፕሮቶኖችን፣ አተሞችን፣ አሚኖ አሲዶችንና የተወሳሰበውን እንጎላችንን ጨምሮ ሊታይ የሚችለውን ማስረጃ ከመረመሩ በኋላ “በአምላክ አምናለሁ፤ ምክንያቱም የተለያዩ ነገሮች ላሉበት ሁኔታ ምክንያታዊ ማብራሪያ የሚሆነኝ የእሱ መለኮታዊ ሕልውና ብቻ ነው” ለማለት ተገደዋል። (ከመዝሙር 104:24 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም ፊዚዮሎጂስት (ስለ ሕያው ፍጥረታት አካላዊ አሠራር የሚያጠኑት) ማርሊን ቡክስ ክሪዴር “እንደ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ሆኜም ሆነ ሕይወቱን ሙሉ በሙሉ ለሳይንሳዊ ጥናትና ምርምር እንዳዋለ ሰው ሆኜ ስመለከተው ስለ አምላክ መኖር ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ የለኝም” ሲሉ ገልጸዋል።
እንዲህ ዓይነት እምነት ያላቸው እነዚህ ሰዎች ብቻ አይደሉም። የፊዚክስ ፕሮፌሰር የሆኑት ሄንሪ ማርጌኖ እንዳሉት “እጅግ የመጠቁትን ሳይንቲስቶች ብትመለከቱ በመካከላቸው የምታገኟቸው አምላክ የለም ባዮች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው።” የሳይንስ እድገቶችም ሆኑ የሃይማኖት ውድቀት በፈጣሪ ማመናችንን እንድንተው ሊገፋፋን አይገባም። ለምን እንደሆነ እስቲ እንመርምር።
እውነተኛ ሃይማኖት ያለው ልዩነት
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት የነበሩት ቶማስ ጀፈርሰን በ1803 እንዲህ ብለው ጽፈው ነበር፦ “የክርስትናን ብልሹነት ያለጥርጥር አወግዛለሁ፤ የማወግዘው ግን እውነተኛዎቹን የራሱን የኢየሱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች አይደለም።” አዎን፣ በሕዝበ ክርስትናና በክርስትና መካከል ልዩነት አለ። ብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና መሠረታዊ ሥርዓቶች የተመሠረቱት በሰዎች ወጎች ላይ ነው። በአንጻሩ ደግሞ የእውነተኛው ክርስትና እምነቶች ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የቆላስይስ ሰዎች “ትክክለኛ እውቀትን”፣ “ጥበብን” እና “መንፈሳዊ ማስተዋልን” ማግኘት እንደሚኖርባቸው ጽፎላቸው ነበር።—ቆላስይስ 1:9, 10 አዓት
ይህ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ልንጠብቀው የሚገባ ነገር ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ተከታዮቹን “እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ብሎ አዟቸዋል።—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ፊደላቱን ጋደል አድርገን የጻፍናቸው እኛ ነን።
ዛሬ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ትእዛዝ በዓለም ዙሪያ በ231 አገሮች ውስጥ እያከናወኑ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በ12 ቋንቋዎች የተረጎሙ ሲሆን ከ74,000,000 ቅጂዎች በላይ አትመዋል። ከዚህም በላይ በቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራም አማካኝነት በአሁኑ ጊዜ ከ4,500,000 በላይ የሆኑ ሰዎችን ‘የኢየሱስን ትእዛዛት በሙሉ እንዲጠብቁ’ እየ ረዱ ነው።
ይህ የትምህርት ፕሮግራም ብዙ ውጤት አለው። የተመሠረተው በሰዎች አስተሳሰብ ላይ ሳይሆን በአምላክ ጥበብ ላይ በመሆኑ እውነተኛ የእውቀት ጮራ ይፈነጥቃል። (ምሳሌ 4:18) ከዚህም በተጨማሪ ከሁሉም ሕዝብና ዘር የተውጣጡ ሰዎች የሰው ልጅ ያካሄደው “የ18ኛው መቶ ዘመን የፍልስፍና ንቅናቄ” ፈጽሞ ሊያከናውነው ያልቻለውን ነገር ይኸውም አንዳቸው ለሌላው እውነተኛ ፍቅር እንዲኮተኩቱ የሚያስችላቸውን “አዲሱን ሰው” እንዲለብሱ እየረዳቸው ነው።—ቆላስይስ 3:9, 10
እኛ ባለንበት በዚህ በ20ኛው መቶ ዘመን እውነተኛ ሃይማኖት ድል እየተቀዳጀ ነው። የአምላክን መኖርም ሆነ ሥልጣኑን አይክድም። ወደ አንዱ የመንግሥት አዳራሻቸው ብቅ ብለው የይሖዋ ምሥክሮችን በመጎብኘት ይህን እንዲመለከቱ እንጋብዝዎታለን።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አምላክ የለም ባይነት የመጣበትን መሠረት ማጠናከር
በ18ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ይኖር የነበረው ፈላስፋ ደኒ ዲደሮ ባለ አንድ ጥራዝ ኢንሳይክሎፔድያ ከእንግሊዝኛ ወደ ፈረንሳይኛ የመተርጎም ሥራ ተሰጥቶት ነበር። ይሁን እንጂ የሠራው ሥራ አሠሪው ከጠበቀው በላይ ነበር። ዲደሮ እሱ በኖረበት ዘመን የነበረውን አመለካከት የሚያንጸባርቀውን 28 ጥራዞች ያሉትን ኦንሲክሎፔዲ ለንባብ ለማብቃት ወደ ሦስት አሥርተ ዓመታት ፈጅቶበታል።
ምንም እንኳ ኦንሲክሎፔዲው ብዙ ጠቃሚ ትምህርቶችን ያዘለ ቢሆንም በሰብዓዊ ጥበብ ላይ ያተኮረ ነው። ግሬት ኤጅስ ኦቭ ማን የሚል ርዕስ ያለው የመጻሕፍት ስብስብ እንደሚለው ከሆነ ኦንሲክሎፔዲው “ሰው የማሰብ ችሎታን እንደ መሠረታዊ መመሪያው አድርጎ በመጠቀም በእምነት ቦታ ቢተካው ሕይወቱን ማሻሻል ይችል ነበር የሚለውን [የፈላስፎችን] ጥራዝ ነጠቅ የሆነ እምነት ለመስበክ አላንገራገረም።” አምላክ አንድም ቦታ ላይ አልተጠቀሰም። “አዘጋጂዎቹ ሃይማኖት ሰዎች ሊያውቋቸው ከሚገቡ ነገሮች አንዱ አለመሆኑን በርዕስ አመራረጣቸው ግልጽ አድርገው አሳይተዋል” በማለት ዘ ሞደርን ሄሪቴጅ የተባለው መጽሐፍ ተናግሯል። እንግዲያው አብያተ ክርስቲያናት ኦንሲክሎፔዲውን ለማገድ መሞከራቸው አያስደንቅም። ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ፖለቲካን፣ ሥነ ምግባርንና ሃይማኖትን ለማጥፋት የተወጠነ ነው በማለት አውግዘውታል።
ጠላቶች ቢኖሩትም የዲደሮን ኦንሲክሎፔዲ ወደ 4,000 የሚጠጉ ሰዎች አዘዋል። በጣም ውድ ከሆነው የመጽሐፉ ዋጋ አንጻር ሲታይ ቁጥሩ እጅግ አስገራሚ ነው። የጊዜ ጉዳይ ሆኖ ነው እንጂ ይህ የአምላክ የለሽነት ውስጣዊ ስሜት ብዙም ሳይቆይ አምላክን ወደ መካድ እንደሚያመራ የታወቀ ነበር።