የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w94 12/1 ገጽ 2-5
  • አምላክ የለም ባይነት እንዴት እንደ መጣ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክ የለም ባይነት እንዴት እንደ መጣ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አመጣጡን መርምሮ መረዳት
  • ዘሮቹ ተዘሩ
  • የጥርጣሬ መንፈስ አቆጠቆጠ
  • አምላክ የለም ባይነት ከፍተኛ ተቀባይነት አገኘ
  • በ20ኛው መቶ ዘመን በአምላክ ላይ የተፈጸመ ክህደት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
  • ክፍል 19:- ከ17ኛው እስከ 19ኛው መቶ ዘመን—​ሕዝበ ክርስትና በዓለም ላይ ከተከሰቱት ለውጦች ጋር ያደረገችው ትንቅንቅ
    ንቁ!—1997
  • በዓለም ላይ ሃይማኖት ባይኖር ይሻል ይሆን?
    ንቁ!—2010
  • ፈጣሪ ስለመኖሩ እምነት ማዳበር ይቻላል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
w94 12/1 ገጽ 2-5

አምላክ የለም ባይነት እንዴት እንደ መጣ

የምንኖረው አለመረጋጋት በተንሠራፋባት ፕላኔት ላይ ነው። በጋዜጣ ላይ የሠፈሩ ጎላ ብለው የሚታዩ ርዕሶችን አየት አየት ብናደርግ በየዕለቱ ይህን ሐቅ የሚያረጋግጡ ሆነው እናገኛቸዋለን። ተስፋ አስቆራጭ የሆነው የዓለማችን ሁኔታ ብዙዎች የአምላክን መኖር እንዲጠራጠሩ አድርጓቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች እስከ ጭራሹ የአምላክን ሕልውና በመካድ አምላክ የለሾች ሆነዋል። የእርስዎም አመለካከት እንደዚህ ነውን?

በአምላክ ማመንዎም ሆነ አለማመንዎ በወደፊቱ ጊዜ ላይ ያለዎትን አመለካከት በእጅጉ ሊነካው ይችላል። አምላክ ከሌለ የሰው ዘር ከእልቂት የመትረፉ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ በሰው ጫንቃ ላይ የወደቀ ይሆናል። የሰው ልጅ ካለው የማውደም አቅም አንጻር ሲታይ ደግሞ ይህ ሊሆን የማይችል ሐሳብ ነው። አምላክ አለ ብለው የሚያምኑ ከሆነ በዚህች ፕላኔት ላይ ያለው ሕይወት በመጨረሻ ፍጻሜውን የሚያገኝ ዓላማ እንዳለው መቀበልዎ አይቀርም።

በታሪክ ዘመናት ሁሉ የአምላክን መኖር የመካድ ሁኔታ አልፎ አልፎ ይንጸባረቅ የነበረ ቢሆንም አምላክ የለም ባይነት በሰዎች ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየጨመረ የመጣው ከቅርብ መቶ ዘመናት ወዲህ ነው። ይህ የሆነው ለምን እንደሆነ ያውቃሉ?

አመጣጡን መርምሮ መረዳት

አንድ ረጅም ዛፍ ማራኪ እይታ አለው። ሆኖም ዓይን ሊመለከት የሚችለው ቅጠሎቹን፣ ቅርንጫፎቹንና ግንዱን ብቻ ነው። የዛፉ የሕይወት ምንጭ የሆኑት ሥሮቹ የሚገኙት ግን መሬት ውስጥ ተደብቀው ነው።

አምላክ የለም ባይነትም ከዚህ የተለየ አይደለም። ልክ እንደ አንድ ግዙፍ ዛፍ አምላክ የለም የሚለው ሐሳብ በ19ኛው መቶ ዘመንና ከዚያ በፊት በነበረው ጊዜ በጣም የሚማርክ ቅርጽ እስኪይዝ ድረስ እያደገ ሄደ። የሁሉም ነገር መገኛ የሆነ አንድ መንፈሳዊ አካል ሳይኖር ሕይወትም ሆነ አጽናፈ ዓለም ወደ መኖር ሊመጡ ይችላሉን? እንዲህ ዓይነት ፈጣሪ ማምለክ ጊዜን በከንቱ ማጥፋት ነውን? በዘመኑ የነበሩት ዋና ዋና ፈላስፎች የሰጡአቸው መልሶች ጠንከር ያሉና የማያሻሙ ናቸው። “ከእንግዲህ ወዲያ የሥነ ምግባር ሕጎች እንደማያስፈልጉን ሁሉ ሃይማኖትም አያስፈልገንም” በማለት ፍሬድሪክ ኒትሸ ተናግሯል። “ሃይማኖት የሰው ልጅ አእምሮ የሚያልመው ሕልም ነው” ሲል ሉትቪክ ፎየርባህም ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል። ከእሱ ዘመን በኋላ በነበሩት ብዙ አሥርተ ዓመታት ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ መጣጥፎችን ያዘጋጀው ካርል ማርክስ ደግሞ “የሰዎች አእምሮ ከሃይማኖት ማነቆ ይበልጥ እንዲላቀቅ ለማድረግ እፈልጋለሁ” ሲል በድፍረት ተናግሯል።

ብዙ ሰዎች በዚህ ተደስተው ነበር። ይሁን እንጂ የተመለከቱት የአምላክ የለሽነትን ቅጠሎች፣ ቅርንጫፎችና ግንድ ብቻ ነው። ሥሮቹ የበቀሉትና ያደጉት 19ኛው መቶ ዘመን ከመጀመሩ ከብዙ ጊዜ በፊት ነበር። የሚገርመው ነገር ደግሞ ዘመናዊውን የአምላክ የለሽነት እድገት የሚያራምዱት የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች መሆናቸው ነው! ይህ የሆነው እንዴት ነው? እነዚህ ሃይማኖታዊ ተቋሞች በብልሹ ምግባራቸው የተነሣ ሰዎች የጠበቁት ሳይሆን በመቅረቱ ከፍተኛ ቅሬታና ተቃውሞ እንዲያድርባቸው አድርገዋል።

ዘሮቹ ተዘሩ

በመካከለኛው መቶ ዘመን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተከታዮቿን አፍና ይዛ ነበር። “የቤተ ክርስቲያኒቱ ባለ ሥልጣናት ሕዝቡ የሚያስፈልገውን መንፈሳዊ ነገር ማሟላት ተስኗቸዋል” ሲል ዘ ኢንሳይክሎፔድያ አሜሪካና ይገልጻል። “ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉት ቀሳውስት በተለይም ጳጳሳቱ ከመኳንንት መካከል የተመለመሉ ሲሆኑ የያዙትንም ቦታ እንደ ክብርና ሥልጣን ማግኛ አድርገው ይመለከቱታል።”

እንደ ጆን ካልቪን እና ማርቲን ሉተር የመሳሰሉ አንዳንዶች ቤተ ክርስቲያኗን እንደገና ለማዋቀር ሞክረዋል። ይሁን እንጂ የተጠቀሙባቸው ዘዴዎች ሁልጊዜ የክርስቶስን መንገድ የተከተሉ ስላልነበሩ የተሃድሶ እንቅስቃሴያቸው ባለመቻቻልና በደም መፋሰስ የታወቀ ነው። (ከማቴዎስ 26:52 ጋር አወዳድር።) አንዳንዶቹ ጥቃቶች ከፍተኛ ጭካኔ የተሞላባቸው ስለነበሩ ከሦስት መቶ ዘመናት በኋላ ሦስተኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት የነበሩት ቶማስ ጀፈርሰን እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በካልቪን መጥፎ ጠባዮች የአምላክን ስም ከማጉደፍ ይልቅ ጭራሽ አምላክ የለም ብሎ ማመን ይበልጥ ይቅርታ ያስገኛል።”a

ተሃድሶው ንጹሕ አምልኮን መልሶ እንዳላመጣ ግልጽ ነው። ሆኖም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ኃይል አዳክሞታል። ቫቲካን በሃይማኖታዊ እምነት ላይ ያለ ተቀናቃኝ ይዛው የነበረውን የበላይነት አጥታለች። ብዙዎች አዲስ ወደ ተቋቋሙት የፕሮቴስታንት እምነት ክፍሎች ገብተዋል። ሌሎች ደግሞ ሃይማኖትን እንደጠበቁት ሆኖ ስላላገኙት የአምልኮ አቅጣጫቸውን በሰው ልጅ አእምሮ ላይ አሳርፈዋል። በዚህም ሳቢያ ማንኛውንም ሐሳብ የማይቃረን አመለካከት ተከሰተ። ይህም ስለ አምላክ የተለያዩ አመለካከቶች ብቅ ብቅ እንዲሉ በር ከፍቷል።

የጥርጣሬ መንፈስ አቆጠቆጠ

በ18ኛው መቶ ዘመን ምክንያታዊ አስተሳሰብ ለዓለም ችግሮች ፍቱን መድኃኒት ነው ተብሎ በሰፊው ይለፈፍ ነበር። ኢማኑኤል ካንት የተባለ አንድ ጀርመናዊ ፈላስፋ የሰው ልጅ እድገት የተጓተተው መመሪያን ለማግኘት በፖለቲካና በሃይማኖት ላይ በመደገፉ ነው ሲል ጠበቅ አድርጎ ተናግሯል። “ለማወቅ በቂ ድፍረት ይኑራችሁ! የራሳችሁን የማሰብ ችሎታ ለመጠቀም ድፍረት ይኑራችሁ!” ሲል አሳስቦ ነበር።

ይህ አመለካከት የ18ኛው መቶ ዘመን የፍልስፍና ንቅናቄ አንዱ ዓቢይ ገጽታ ነው፤ ይህ ምክንያታዊ እምነት የተንጸባረቀበት ዘመን ተብሎም ይጠራል። እስከ 18ኛው መቶ ዘመን ድረስ የዘለቀው ይህ ዘመን እውቀትን ለማግኘት ያለማቋረጥ ከፍተኛ ፍለጋ የተካሄደበት ዘመን ነበር። “በጭፍን እምነት ቦታ የጥርጣሬ መንፈስ ተተካ” በማለት ማይልስቶንስ ኦቭ ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። “የጥንቶቹ ባሕላዊ እምነቶችና ልማዶች አጠያያቂ ሁኔታ ውስጥ ገቡ።”

ከፍተኛ ጥናት የተካሄደበት አንዱ ‘የጥንት ባሕላዊ እምነት’ ሃይማኖት ነው። “ሰዎች በሃይማኖት ላይ የነበራቸውን አመለካከት ለወጡ” ሲል ዘ ዩኒቨርሳል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ወርልድ የተባለው መጽሐፍ ይናገራል። “በሰማይ ስለሚገኘው ሽልማት በሚናገረው ተስፋ የመርካታቸው ጉዳይ አከተመለት። በምድር ላይ የተሻለ ሕይወት ማግኘት የሚፈልጉ ሆኑ። ኃያል በሆነ መንፈሳዊ አካል ላይ የነበራቸው እምነት መክሰም ጀመረ።” በእርግጥም አብዛኛዎቹ የ18ኛውን መቶ ዘመን የፍልስፍና ንቅናቄ ያራምዱ የነበሩት ፈላስፎች ሃይማኖትን አቃልለው ተመልክተውታል። በተለይ ደግሞ የሥልጣን ጥመኛ የሆኑት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሰዎች ከድንቁርና እንዳይላቀቁ አድርገዋል በማለት ነቅፈዋል።

ከእነዚህ ፈላስፎች መካከል ብዙዎቹ በሃይማኖት ባለመርካታቸው ዴይስቶች (ፈጣሪ በአጽናፈ ዓለም ሕግጋት ውስጥ እጁ እንዳለበት የማይቀበሉ የተፈጥሮ ሃይማኖት አቀንቃኞች) ሆኑ። በአምላክ ያምናሉ፤ ነገር ግን አምላክ ስለ ሰው ምንም ደንታ የለውም ይላሉ።b ጥቂቶቹ የለየላቸው አምላክ የለም ባዮች ሆኑ። ከእነዚህም መካከል ሃይማኖት “የመከፋፈል፣ የመጃጃልና የወንጀሎች ምንጭ ነው” ሲሉ የተናገሩት ፈላስፋው ፖል ኤንሪ ቲሪ ኦልባክ አንዱ ናቸው። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ብዙዎች ሕዝበ ክርስትናን መታገስ ባለመቻላቸው ከኦልባክ አባባል ጋር ተስማምተዋል።

ሕዝበ ክርስትና አምላክ የለም ባይነት እያደገ እንዲሄድ ማድረጓ ፈጽሞ ከእሷ የማይጠበቅ ተግባር ነው! “አምላክ የለም ባይነት ሥር ሰዶ ያደገው በአብያተ ክርስቲያናት ነው” በማለት የቲኦሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ሚካኤል ጄ በክሌይ ጽፈዋል። “የምዕራባውያን ሕሊና በሃይማኖት ድርጅቶች በእጅጉ ተጎድቷል፤ እንዲሁም በእነርሱ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ አድሮበታል። አብያተ ክርስቲያናቱና የእምነት ክፍሎቹ አውሮፓን አፈራርሰዋታል፣ ብዙ ሰው በጭካኔ የተፈጀባቸውን ሴራዎች አቀናብረዋል፣ ሃይማኖታዊ ተቃውሞን ወይም አብዮትን አነሳስተዋል፣ ገዥዎችን ከሃይማኖታቸው ለማግለል ወይም ከሥልጣናቸው ለማውረድ ሞክረዋል።”

አምላክ የለም ባይነት ከፍተኛ ተቀባይነት አገኘ

በ19ኛው መቶ ዘመን አምላክ የለም የሚለው እምነት በይፋ ይነገርና ይስፋፋ ነበር። ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች አመለካከታቸውን በድፍረት ለማወጅ ምንም አልወላወሉም። አንድ የለየለት አምላክ የለም ባይ “ጠላታችን አምላክ ነው” በማለት ተናግሯል፤ እንዲሁም “የጥበብ መጀመሪያ አምላክን መጥላት ነው። የሰው ዘር እውነተኛ እድገት እንዲያደርግ ከተፈለገ የግድ አምላክ የለም በሚለው እምነት ላይ መመርኮዝ አለበት” ብሏል።

ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን ረቂቅ ለውጥ ተደረገ። አምላክ የለም የሚለው እምነት የነበረው ኃይል ደከም አለ። አንድ ለየት ያለ አምላክ የለም የሚል እምነት መስፋፋት ጀመረ፤ ይህም በአምላክ እናምናለን የሚሉትንም ሳይቀር ነክቷቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በተሃድሶው ሳቢያ የተከሰቱት የፕሮቴስታንት እምነት ክፍሎች ብዙ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ መሠረተ ትምህርቶችን እንደያዙ ቀጥለዋል። የነሐሴ 22, 1989 ገጽ 16–20 እና የመስከረም 8, 1989 ገጽ 23–7 የእንግሊዝኛ ንቁ! መጽሔት እትሞችን ተመልከት።

b ዴይስቶች አምላክ ልክ እንደ አንድ ሰዓት ሠሪ ፍጥረቱ መሥራት እንዲጀምር ካደረገ በኋላ ሙሉ በሙሉ ጀርባውን ሰጥቶታል፤ ለፍጥረቱ ምንም ደንታ የሌለው ሆኗል ይላሉ። ዘ ሞደርን ሄሪቴጅ የተባለው መጽሐፍ እንደሚለው ከሆነ ዴይስቶች “አምላክ የለም ባይነት የመጣው ሰዎች ተስፋ በመቁረጣቸው ሳቢያ የተፈጸመ ስህተት ነው ብለው ያምናሉ፤ የሰዎችን አስተሳሰብና ድርጊት የመቆጣጠር ባሕርይ ያለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መዋቅርና ውልፍት የማያደርጉትና አንዳችም ዓይነት ሐሳብ የማያስተናግዱት መሠረተ ትምህርቶቻቸው ግን ይበልጥ የከፉ ናቸው።”

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካርል ማርክስ

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሉትቪክ ፎየርባህ

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ፍሬድሪክ ኒትሸ

[በገጽ 2 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ሽፋን፦ Earth: By permission of the British Library; Nietzsche: Copyright British Museum (see also page 3); Calvin: Musée Historique de la Réformation, Genève (Photo F. Martin); Marx: U.S. National Archives photo (see also page 3); Planets, instruments, crusaders, locomotive: The Complete Encyclopedia of Illustration/​J. G. Heck; Feuerbach: The Bettmann Archive (see also page 3)

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ