በፍጹሙ የፍቅር ማሰሪያ ተሳሰሩ
“እርስ በእርስ ስምም ሆናችሁ በፍቅር ተሳሰሩ።”—ቆላስይስ 2:2 አዓት
1, 2. በተለይ በዛሬው ጊዜ ምን የሚከፋፍል ተጽዕኖ አለ?
አድምጡ! አንድ ኃይለኛ ድምፅ በሰማይ ውስጥ ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዲህ ሲል እያስተጋባ ነው፦ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቁጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።” (ራእይ 12:12) እያንዳንዱ ዓመት ባለፈ ቁጥር ይህ መልእክት ለምድር ነዋሪዎች ይበልጥ አስፈሪ እየሆነ መጥቷል።
2 የይሖዋ ቀንደኛ ባላጋራ፣ ተቃዋሚ (ሰይጣን) እና ስም አጥፊ (ዲያብሎስ) ተብሎ መጠራት ከጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል። ይሁን እንጂ ይህ አታላይ በአሁኑ ጊዜ ሌላ ተንኮል መሸረብ ጀምሯል፤ ቁጡ አምላክ ሆኗል! ለምን? በ1914 በሰማይ በጀመረው ጦርነት ሚካኤልና መላእክቱ ከሰማይ ስላባረሩት ነው። (ራእይ 12:7–9) ዲያብሎስ ሰዎች ሁሉ አምላክን ከማምለክ ገሸሽ እንዲሉ ማድረግ እችላለሁ በማለት ያስነሳውን ግድድር ለማስመስከር የቀረው ጊዜ አጭር እንደሆነ ያውቃል። (ኢዮብ 1:11፤ 2:4, 5) ሰይጣንና አጋንንቱ ማምለጫ ቀዳዳ ስለሌላቸው ልክ ቀፎው እንደተነካ የንብ መንጋ ቁጣቸውን እረፍት የለሽ በሆነው የሰው ዘር ላይ እየተወጡ ነው።—ኢሳይያስ 57:20
3. ሰይጣን ውርደት መከናነቡ በጊዜያችን ምን ውጤት አስከትሏል?
3 የሰው ልጅ ዓይኖች የማያዩአቸው እነዚህ ክንውኖች በአሁኑ ጊዜ በሰው ልጆች ላይ አጠቃላይ የሆነ የሥነ ምግባር ውድቀት ለምን ሊኖር እንደቻለ ግልጽ ያደርጉልናል። በተጨማሪም ተስማምተው መኖር ስላልቻሉ ብቻ እየተገነጣጠሉ ያሉትን አገሮች ለማዋሃድ ሰዎች የሚያደርጓቸውን መፍጨርጨሮች ይገልጻሉ። የጎሳና የዘር ቡድኖች አንዳቸው በሌላው ላይ የሚፈጽሙት አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት አልባ እንዲሆኑና ከቀዬዎቻቸው እንዲፈናቀሉ እያደረገ ነው። ሕገ ወጥነት ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን እያደገ መምጣቱ ምንም አያስደንቅም! ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ‘የብዙ ሰዎች ፍቅር እየቀዘቀዘ ነው።’ በየትም ቦታ የምታየው ጸብና ጥላቻ በዛሬው ጊዜ ያለውን ዕረፍት የለሽ የሰው ዘር ለይቶ የሚያመለክት ነው።—ማቴዎስ 24:12
4. የአምላክ ሕዝብ ለየት ባለ አደጋ ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው?
4 ከዓለም ሁኔታ አንጻር ሲታይ ኢየሱስ ለተከታዮቹ የጸለየው ጸሎት ይበልጥ ጥልቀት ያለው ትርጉም ይኖረዋል፦ “ከክፉ [ከክፉው የ1980 ትርጉም] እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም። እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።” (ዮሐንስ 17:15, 16) በዛሬው ጊዜ “ክፉው” ቁጣውን የሚወጣው በተለይ ‘የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በሚጠብቁትና የኢየሱስም ምሥክር ባላቸው’ ላይ ነው። (ራእይ 12:17) ይሖዋ በንቃትና ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ባይጠብቃቸው ኖሮ የታመኑ ምሥክሮቹ ከምድር ገጽ በጠፉ ነበር። ሕይወታችን የተመካው አምላክ ለመንፈሳዊ ደህንነታችንና ለመንፈሳዊ ጤንነታችን ባዘጋጃቸው ዝግጅቶች በሙሉ በሚገባ በመጠቀማችን ላይ ነው። ይህም ሐዋርያው በቆላስይስ 1:29 ላይ እንዳሳሰበው በክርስቶስ በኩል ከሚሠራው መንፈሱ አሠራር ጋር በሚስማማ መንገድ ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረግን ይጨምራል።
5, 6. የቆላስይስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ ምን ተሰምቶት ነበር? የ1995 መሪ ጥቅስስ ተስማሚ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ምንም እንኳ ጳውሎስ በአካል አግኝቷቸው ባያውቅም በቆላስይስ ይኖሩ የነበሩ ወንድሞቹን ይወዳቸው ነበር። “ስለ እናንተ ምን ያህል እንደማስብ መረዳት እንድትችሉ እመኛለሁ” ሲል ነግሯቸዋል። (ቆላስይስ 2:1 ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ኢንግሊሽ፣ በጄ ቢ ፊሊፕስ) የኢየሱስ ተከታዮች የዚህ ዓለም ክፍል ስላልሆኑ “ክፉው” በመካከላቸው የዓለምን መንፈስ በመዝራት የወንድሞችን አንድነት ለማናጋት የሚያደርገውን ሙከራ ይገፋበታል። ኤጳፍራ ከቆላስይስ ይዞት የመጣው ዜና ይህ ሁኔታ በተወሰነ ደረጃ ተከስቶ እንደነበረ ይጠቁማል።
6 ጳውሎስ ክርስቲያን ወንድሞቹን በተመለከተ ያሳስቡት ከነበሩት ነገሮች አንዱና ዋንኛው በሚከተሉት ጥቂት ቃላት ቁልጭ ብሎ ተገልጿል፦ “እርስ በእርስ ስምም ሆናችሁ በፍቅር ተሳሰሩ።” በመከፋፈልና በጥላቻ በተሞላው በዛሬው ዓለም ውስጥ ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላት ልዩ ትርጉም አላቸው። የጳውሎስን ምክር ከልብ ከተከተልን የይሖዋን ጥበቃ እናገኛለን። በተጨማሪም የመንፈሱ ኃይል የዓለምን ግፊቶች እንድንከላከል በመርዳት በሕይወታችን ውስጥ ሲሠራ እንመለከታለን። ይህ ምንኛ ጥበብ ያለበት ምክር ነው! በመሆኑም ቆላስይስ 2:2 የ1995 መሪ ጥቅሳችን ይሆናል።
7. በእውነተኛ ክርስቲያኖች መካከል ምን ዓይነት ስምምነት መኖር አለበት?
7 ሐዋርያው ቀደም ሲል ለቆሮንቶስ በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሰውን አካል እንደ ምሳሌ ተጠቅሞበታል። “እርስ በእርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ” በቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ውስጥ “መለያየት እንዳይሆን” ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 12:12, 24, 25) እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው! ብልቶቻችን አንዳቸው በሌላው ላይ የተመኩ ናቸው፤ እያንዳንዱ ብልት ከተቀረው አካላችን ጋር የተያያዘ ነው። በቅቡዓንና በገነት ምድር ላይ ለመኖር ተስፋ በሚያደርጉ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ለተገነባው ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበርም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። በራሳችን እየተመራን ለመኖር ስንል ከመሰል ክርስቲያኖች አካል ራሳችንን ማግለል የለብንም! በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የሚሠራው የአምላክ መንፈስ ከወንድሞቻችን ጋር ባለን ኅብረት አማካኝነት በከፍተኛ መጠን ይፈስልናል።
እርስ በእርስ ስምም መሆን ከእውቀት ጋር የተያያዘ ነው
8, 9. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ስምምነት እንዲሰፍን ለምናደርገው አስተዋጽኦ መሠረታዊው ነገር ምንድን ነው? (ለ) ስለ ክርስቶስ እውቀት ያገኘኸው እንዴት ነው?
8 ከጳውሎስ ቁልፍ ነጥቦች አንዱ ክርስቲያናዊ ስምምነት ከእውቀት ጋር በተለይ ስለ ክርስቶስ ከሚናገረው እውቀት ጋር የተያያዘ ነው የሚል ነው። ጳውሎስ ክርስቲያኖች “በፍቅር ተሳስረው ፍጹም ማስተዋል የሚያስገኘውን የሙሉ መተማመንን ባለጸግነት በማትረፍ የእግዚአብሔር ምስጢር [የአምላክ ቅዱስ ምሥጢር ትክክለኛ እውቀት አዓት] የሆነውን ክርስቶስን እንዲያውቁ” ጽፏል። (ቆላስይስ 2:2 የ 1980 ትርጉም) የአምላክን ቃል ማጥናት ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ እውቀትን፣ ይኸውም የተለያዩ እውነታዎችን ቀስመናል። ከእነዚህ እውነታዎች መካከል ብዙዎቹ ከአምላክ ዓላማ ጋር እንዴት እንደሚጣጣሙ ስንረዳ ኢየሱስ የሚጫወተውን ወሳኝ ሚና እንረዳለን። “የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በእርሱ ነውና።”—ቆላስይስ 2:3
9 ስለ ኢየሱስና እርሱ በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስላለው ድርሻ የሚሰማህ እንደዚህ ነውን? በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙዎች ኢየሱስን ተቀብዬዋለሁ አንዲሁም ድኜያለሁ ብለው ለመናገር ፈጣኖች ናቸው። ይሁን እንጂ በእርግጥ ኢየሱስን ያውቁታል? በፍጹም፤ ምክንያቱም አብዛኞቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነው በሥላሴ መሠረተ ትምህርት ያምናሉ። ይህን በተመለከተ እውነቱ ምን እንደሆነ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ ስለተናገረውና ስላደረገው ነገርም ሰፋ ያለ እውቀት እንደሚኖርህ የታወቀ ነው። በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው በተባለው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ ጠቃሚ መረጃ የሚሰጥ ጥናት በማካሄድ ይህን እውቀት መቅሰም የሚችሉበትን ርዳታ አግኝተዋል። ሆኖም ስለ ኢየሱስና ስለ መንገዶቹ ያለን እውቀት ይበልጥ ጥልቀት እያገኘ መሄዱን እንዲቀጥል እንፈልጋለን።
10. የተሰወረን እውቀት በቀላሉ ልናገኝ የምንችለው በምን መንገድ ነው?
10 “የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ” በኢየሱስ “የተሰወረ” ነው የሚለው አነጋገር እንዲህ ዓይነቱ እውቀት ከእኛ የመረዳት አቅም በላይ ነው ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንደ ተቆፈረ የማዕድን ማውጫ ጉድጓድ ነው። ከየት መቆፈር እንደምንጀምር ግራ በመጋባት በአንድ ሰፊ ቦታ ላይ በፍለጋ መባዘን አያስፈልገንም። እውነተኛ እውቀት የሚጀምረው መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚገልጸው ነገር መሆኑን አውቀናል። ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ የሚጫወተውን ሚና ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ስንረዳ የእውነተኛ ጥበብና የትክክለኛ እውቀት መዝገብ እናገኛለን። ስለዚህ ይበልጥ በጥልቀት መቆፈራችንን በመቀጠል አስቀድመን በቆፈርነው በዚሁ ምንጭ የሚገኙትን ተጨማሪ የከበሩ ወይም ውድ ነገሮች ማውጣት ያስፈልገናል።—ምሳሌ 2:1–5
11. ስለ ኢየሱስ በማሰላሰል እውቀታችንንና ጥበባችንን እንዴት ልናሳድገው እንችላለን? (ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን እግር እንዳጠበ የሚናገረውን ምሳሌ ጠቅሰህ ወይም ሌሎች ምሳሌዎችን በመጠቀም አስረዳ።)
11 ለምሳሌ ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር እንዳጠበ እናውቅ ይሆናል። (ዮሐንስ 13:1–20) ይሁን እንጂ ባስተማረው ትምህርትና ባሳየው አመለካከት ላይ አሰላስለናልን? እንዲህ በማድረግ ባሕርይው(ዋ) ለረጅም ጊዜ ሲያበሳጨን የኖረን አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት የምንይዝበትን መንገድ እንድናስተካከል የሚያስችለንን አዎን፣ እንዲህ ለማድረግ የሚገፋፋንን የጥበብ መዝገብ ማውጣት እንችላለን። ወይም ደግሞ ፈጽሞ የማንወደው ሥራ ሲሰጠን ዮሐንስ 13:14, 15 የያዘውን ቁም ነገር ሙሉ በሙሉ ከተረዳን በኋላ የምናሳየው ምላሽ ለየት ያለ ሊሆን ይችላል። እውቀትና ጥበብ የሚነካን በዚህ መንገድ ነው። ስለ ክርስቶስ ካገኘነው ተጨማሪ እውቀት ጋር በሚስማማ መንገድ የክርስቶስን ምሳሌ ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ስንኮርጅ በሌሎች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል? ምናልባት መንጋው ‘ይበልጥ እርስ በእርስ ስምም ሆኖ በፍቅር ይተሳሰር’ ይሆናል።a
ሐሳብን የሚከፋፍሉ ነገሮች ስምምነትን ሊያጠፉ ይችላሉ
12. ንቁዎች ሆነን መከላከል ያለብን የትኛውን እውቀት ነው?
12 ትክክለኛ እውቀት ‘እርስ በርስ ስምም ሆነን በፍቅር እንድንተሳሰር’ የሚያደርገን ከሆነ “በውሸት እውቀት” የተባለው ነገር ደግሞ ምን ነገርን ያስከትላል? ተቃራኒውን ማለትም ክርክርን፣ ጥልንና ከእምነት መንገድ መውጣትን ያስከትላል። ስለዚህ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን እንዳስጠነቀቀው ራሳችንን ከእንዲህ ዓይነቱ የውሸት እውቀት መጠበቅ አለብን። (1 ጢሞቴዎስ 6:20, 21) በተጨማሪም ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ማንም በሚያባብል ቃል እንዳያስታችሁ ይህን እላለሁ። እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን፣ እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ።”—ቆላስይስ 2:4, 8
13, 14. (ሀ) የቆላስይስ ወንድሞች በእውቀት ረገድ አደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኙ የነበረው ለምን ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ አንዳንዶች በእንዲህ ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ላይ እንደማይገኙ ሆኖ የሚሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል?
13 የቆላስይስ ክርስቲያኖች በውሸት እውቀት በሆነው አታላይ ተጽዕኖ ተከበው ነበር። በቆላስይስና በአካባቢዋ ይገኙ የነበሩ ብዙ ሰዎች ለግሪክ ፍልስፍናዎች ከፍተኛ ቦታ ይሰጡ ነበር። በተጨማሪም ክርስቲያኖች የበዓላት ቀናትንና ምግብን በተመለከተ የሚፈለጉትን ብቃቶች የመሰሉ የሙሴ ሕግ ያቀፋቸውን ነገሮች እንዲጠብቁ የሚፈልጉ የአይሁድን እምነት የሚያስፋፉ ሰዎች ነበሩ። (ቆላስይስ 2:11, 16, 17) ጳውሎስ ወንድሞቹ እውነተኛ እውቀት ማግኘታቸውን አልተቃወመም፤ ነገር ግን ማንም ሰው የሚያባብሉ የመከራከሪያ ነጥቦች በመጠቀም ሰው ለሕይወትና ለተለያዩ ተግባራት ያለው ተራ የሆነ አመለካከት እውነት ነው ብለው እንዲያምኑ በማድረግ እንዳያጠምዳቸው መጠንቀቅ ነበረባቸው። በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች አስተሳሰባቸውና የሚያደርጓቸው ውሳኔዎች ስለ ሕይወት በሚሰጡት በእንዲህ ዓይነት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ጽንሰ ሐሳቦችና አመለካከቶች እንዲመሩ ከፈቀዱ በጉባኤ አባላት መካከል ስምምነትንና ፍቅርን የሚያደፈርስ ነገር እንደሚፈጥር መረዳት ትችላለህ።
14 ‘አዎን፣ የቆላስይስ ክርስቲያኖች አደጋ ተደቅኖባቸው እንደነበረ አውቃለሁ፤ እኔ ግን ነፍስ አትሞትም ወይም አምላክ ሥላሴ ነው የሚሉትን ለመሰሉ የግሪክ ጽንሰ ሐሳቦች ተጽዕኖ የተጋለጥኩ አይደለሁም፤ ትቼው ወደወጣሁት የሐሰት ሃይማኖት አረማዊ በዓላት እንድሳብ የሚያደርግ አደጋ ያለ መስሎም አይታየኝም’ ብለህ ታስብ ይሆናል። መልካም ነው። በኢየሱስ በኩል የተገለጠውና በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የሚገኘው መሠረታዊ እውነት የላቀ መሆኑን በጽኑ ማመኑ ጥሩ ነው። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ተስፋፍተው የሚገኙት ሌሎች ፍልስፍናዎች ወይም ሰብዓዊ አመለካከቶች ለሚያሳድሩት ተጽዕኖ ተጋልጠን ይሆን?
15, 16. የአንድን ክርስቲያን አስተሳሰብ ሊነካው የሚችለው ምን ዓይነት አመለካከት ነው?
15 ከእንዲህ ዓይነቶቹ አመለካከቶች አንዱ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ነው፦ “የመምጣቱ የተስፋ ቃል ወዴት ነው? አባቶች ከሞቱባት ጊዜ . . . ይዞ ሁሉ እንዳለ ይኖራል።” (2 ጴጥሮስ 3:4) ይህ ሐሳብ በሌሎች ቃላት ሊገለጽ ይችላል፤ አመለካከቱ ግን ያው ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ‘በርከት ካሉ አሥርተ ዓመታት በፊት በመጀመሪያ እውነትን ሳውቅ መጨረሻው “ደፉ ላይ ደርሶ” ነበር። ነገር ግን አሁንም አልመጣም፤ ወደፊትስ መቼ እንደሚመጣ ማን ያውቃል?’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። እውነት ነው፣ መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ የሚያውቅ ሰው የለም። ሆኖም ኢየሱስ ምን ዓይነት አመለካከት እንድንይዝ እንዳሳሰበ ልብ በል፦ “ጊዜው መቼ እንዲሆን አታውቁምና ተጠንቀቁ ትጉ።”—ማርቆስ 13:32, 33
16 መጨረሻው መቼ እንደሚመጣ ስለማናውቅ የተሟላና “የተዝናና” የሚባለውን ዓይነት ኑሮ ለመኖር እቅድ ማውጣት ይኖርብናል የሚል አስተሳሰብ መያዙ ምንኛ አደገኛ ነው! ይህ አቋም ‘ለእኔ (ወይም ለልጆቼ) ጥሩ ገቢ የሚያስገኝና የተደላደለ ኑሮ መኖር የሚያስችለኝ ከፍ ያለ ሥራ ማግኘት የሚያስችሉ እርምጃዎችን ብወስድ ጥሩ ይሆናል። እርግጥ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እገኛለሁ፤ እንዲሁም በስብከቱ ሥራ በተወሰነ ደረጃ እካፈላለሁ፤ ከዚህ በተረፈ ግን ከፍተኛ ተጋድሎ የማደርግበት ወይም ትልቅ መሥዋዕቶችን የምከፍልበት ምንም ምክንያት የለም’ በሚለው አስተሳሰብ ሊንጸባረቅ ይችላል።—ማቴዎስ 24:38–42
17, 18. ኢየሱስና ሐዋርያቱ ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን አጥብቀው አሳስበውናል?
17 ይሁን እንጂ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ምሥራቹን በመስበክ፣ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረግና መሥዋዕቶችን ለመክፈል ፈቃደኛ በመሆን ረገድ በጥድፊያ ስሜት እንድንኖር ምክራቸውን እንደለገሱ አሌ ሊባል አይችልም። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወንድሞች ሆይ፣ ይህን እናገራለሁ፤ ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሚስቶች ያሉአቸው እንደሌላቸው ይሁኑ፣ . . . የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፣ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።”—1 ቆሮንቶስ 7:29–31፤ ሉቃስ 13:23, 24፤ ፊልጵስዩስ 3:13–15፤ ቆላስይስ 1:29፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:10፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:4፤ ራእይ 22:20
18 ጳውሎስ የተደላደለ ኑሮን ግብ እንድናደርግ ከማበረታታት እጅግ በተለየ መልኩ በመንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን እርሱ ይበቃናል። . . . መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፣ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ።”—1 ጢሞቴዎስ 6:7–12
19. በአንድ ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሰዎች ኢየሱስ ያበረታታውን የሕይወት አመለካከት ሲቀበሉ ጉባኤው እንዴት ይነካል?
19 አንድ ጉባኤ ‘በሕዝብ ፊት ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት’ በጣም የሚጥሩ ቀናተኛ ክርስቲያኖችን ያቀፈ በሚሆንበት ጊዜ ስምምነት መኖሩ ያለ ነገር ነው። “ነፍሴ፣ ለብዙ ዘመን የሚቀር ብዙ በረከት አለሽ፤ ዕረፊ፣ ብዪ፣ ጠጪ፣ ደስ ይበልሽ” ለሚለው አስተሳሰብ እጃቸውን አይሰጡም። (ሉቃስ 12:19) ከዚህ ይልቅ ሁለተኛ በማይደገመው በዚህ ሥራ የተቻላቸውን ያህል ሙሉ በሙሉ ለመካፈል እንዲችሉ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ በመሆን በአንድ ዓይነት ጥረት የተሳሰሩ ናቸው።—ከፊልጵስዩስ 1:27, 28 ጋር አወዳድር።
ከሚያባብሉ ክርክሮች እንጠንቀቅ
20. ክርስቲያኖች ሊታለሉ የሚችሉበት ሌላው መስክ ምንድን ነው?
20 እርግጥ ነው፣ ክርስቲያኖች ‘በሚያባብሉ ቃላት ሊታለሉ’ የሚችሉባቸው ሌሎች መንገዶች ወይም ‘እርስ በእርስ ስምም ሆነው በፍቅር እንዳይተሳሰሩ’ የሚያደርጉ ከንቱ ማታለያዎች አሉ። በጀርመን የሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮ “አንድ ጉዳይ በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ ሰፊ ውዝግብ አስነስቶ ነበር፤ አስፋፊዎች አልፎ ተርፎም ሽማግሌዎች አንድ ወንድም በሚጠቀምባቸው የሕክምና ዓይነቶች ላይ በተነሳው ክርክር የተለያየ አቋም ይዘው ነበር” ሲል ጽፏል። አክለውም “የሕክምና ዘዴዎቹ በጣም ብዙ መሆናቸውና የታካሚዎቹ ቁጥር በርካታ መሆኑ አወዛጋቢ የሆነ ነገር ሊነሳ የሚችልበት አጋጣሚ ፈጥሯል፤ እንዲሁም የሕክምና ዘዴዎች መናፍስታዊ ጠባይ ካላቸው አደገኛ ሁኔታ ሊጋብዙ ይችላሉ።”—ኤፌሶን 6:12
21. በዛሬው ጊዜ አንድ ክርስቲያን ሊያተኩርበት የሚገባውን ትክክለኛ ነገር ሊያጣ የሚችለው እንዴት ነው?
21 ክርስቲያኖች አምላክን ማምለክ እንዲችሉ በሕይወት መቀጠልና ጤናማ ሆነው መኖር ይፈልጋሉ። ሆኖም በዚህ ሥርዓት ውስጥ የአለፍጽምና ውጤት ለሆኑት ለእርጅናና ለበሽታ ተገዢዎች ነን። ስለ ጤና ጉዳዮች አጥብቆ ከማሰብ ይልቅ ለእኛም ሆነ ለሌሎች እውነተኛ መፍትሔ በሆነው ነገር ላይ ማተኮር ይኖርብናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:16) ጳውሎስ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች የሰጠው ምክር ያተኮረው በክርስቶስ ላይ እንደነበረ ሁሉ ይህ መፍትሔም ያተኮረው በክርስቶስ ላይ ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስ አንዳንዶች “በሚያባብል ቃል” ትኩረታችንን ከክርስቶስ በማራቅ ምናልባትም ሕመምን ለይቶ ማወቅ ወደሚቻልባቸው ዘዴዎች፣ ወደ ሕክምናዎች ወይም ጤናን ለማሻሻል ይረዳሉ ወደሚባሉ የአመጋገብ ሥርዓቶች ዘወር ሊያደርጉን እንደሚችሉ እንዳመለከተ አስታውስ።—ቆላስይስ 2:2–4
22. በሽታን ለይቶ ማወቅና ሕክምና መስጠት ስለሚቻልባቸው መንገዶች የሚነገሩትን ቁጥር ሥፍር የሌላቸው አባባሎች በተመለከተ ምን ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
22 በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ስለ ሁሉም ዓይነት ሕክምናዎችና በሽታን ለይቶ ማወቅ ስለሚቻልባቸው ዘዴዎች የሚገልጹ ማስታወቂያዎችና በሕክምናዎቹ የተገኙትን ጥቅሞች የሚዘረዝሩ የምሥክርነት ቃሎች እየጎረፉባቸው ነው። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በስፋት ጥቅም ላይ የዋሉና ዕውቅና ያገኙ ናቸው፤ ሌሎቹ ደግሞ በስፋት የተተቹ ወይም አጠራጣሪ የሆኑ ናቸው።b እያንዳንዱ ሰው ጤንነቱን በተመለከተ ምን እንደሚያደርግ መወሰን የራሱ ኃላፊነት ነው። ይሁን እንጂ በቆላስይስ 2:4, 8 ላይ የሚገኘውን የጳውሎስ ምክር የሚቀበሉ ሰዎች፣ የመንግሥቱ ተስፋ የሌላቸውና እፎይታን ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውን ብዙ ሰዎች እንዲስቱ ካደረጓቸው ‘የሚያባብሉ ቃሎች’ እና ‘ከንቱ ማታለያዎች ይጠበቃሉ።’ አንድ ክርስቲያን ምንም እንኳ አንድ የሕክምና ዓይነት ለራሱ ጥሩ እንደሆነ ቢያምንበትም ሰፊ የመወያያና የውዝግብ ርዕስ ሊሆን ስለሚችል በክርስቲያን ወንድማማች ማኅበር መካከል ይህን ማስፋፋት አይኖርበትም። በዚህ መንገድ በጉባኤ ውስጥ ስምምነት የመኖሩን አስፈላጊነት በጣም ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ሊያሳይ ይችላል።
23. በተለይ እኛ ለደስታ የሚሆን ምክንያት ያለን ለምንድን ነው?
23 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያናዊ ስምምነት ለእውነተኛ ደስታ መሠረት መሆኑን ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። በእሱ ዘመን የነበሩት ጉባኤዎች ቁጥር በዛሬው ጊዜ ካሉት ያነሰ እንደነበረ አያጠያይቅም። ሆኖም ለቆላስይስ ሰዎች እንዲህ በማለት ሊጽፍላቸው ችሎ ነበር፦ “በሥጋ ምንም እንኳ ብርቅ፣ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና፣ ሥርዓታችሁንም በክርስቶስም ያለውን የእምነታችሁን ጽናት እያየሁ ደስ ይለኛል።” (ቆላስይስ 2:5፤ በተጨማሪም ቆላስይስ 3:14ን ተመልከት።) እኛ የምንደሰትበት ምክንያት ከዚህ ምንኛ የላቀ ነው! በምድር ዙሪያ የሚገኙትን የአምላክ ሕዝቦች አጠቃላይ ሁኔታ የሚያንጸባርቀውን የስምምነት፣ የመልካም ሥርዓትና የእምነት ጽናት እውነተኛ ማስረጃ በራሳችን ጉባኤ ውስጥ መመልከት እንችላለን። ስለዚህ ያለንበት ሥርዓት በቀረው አጭር ጊዜ ውስጥ እያንዳንዳችን ‘እርስ በእርስ ስምም በመሆን በፍቅር ለመተሳሰር’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ምንም እንኳ ትምህርት ልንቀስም የምንችልባቸው ማለቂያ የሌላቸው ዘገባዎች ቢኖሩም በጉባኤህ ውስጥ ስምምነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ሊያበረክት የሚችል ምን ነገር በግልህ ስለ ኢየሱስ መማር እንደምትችል ከሚከተሉት ምሳሌዎች ተመልከት፦ ማቴዎስ 12:1–8፤ ሉቃስ 2:51, 52፤ 9:51–55፤ 10:20፤ ዕብራውያን 10:5–9።
b የሰኔ 15, 1982 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 22–9 ተመልከት።
ልብ ብለኸዋልን?
◻ የ1995 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት ጥቅስ ምንድን ነው?
◻ የቆላስይስ ክርስቲያኖች እርስ በእርስ ስምም በመሆን በፍቅር መተሳሰር ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? በዛሬው ጊዜስ እንደዚህ የምናደርገው ለምንድን ነው?
◻ በዛሬው ጊዜ በተለይ ክርስቲያኖች ነቅተው ሊጠብቁት የሚገባ አታላይ የሆነ የሕይወት አመለካከት ምንድን ነው?
◻ ክርስቲያኖች ስለ ጤናና በሽታን ማወቅ ስለሚቻልባቸው መንገዶች በሚነገሩት የሚያባብሉ ቃላት እንዳይታለሉ ንቁዎች መሆን የሚኖርባቸው ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለወደፊቱ ጊዜ ያወጣሃቸው ዕቅዶች በኢየሱስ መገኘት ላይ ያተኮሩ ናቸውን?