እጅግ ውድ የሆነ ሀብት ለሌሎች ማካፈል
ግሎሪያ ማላስፒና እንደተናገረችው
የሲሲሊ የባሕር ዳርቻ ከእይታችን ሲጠፋ እኔና ባለቤቴ ትኩረታችንን በመድረሻችን የሜዲትራኒያኑ ደሴት ማልታ ላይ ማነጣጠር ጀመርን። ምን ዓይነት አስደናቂ አጋጣሚ ነው! መርከቡ ባሕሩን ሲያቋርጥ በመጀመሪያ መቶ ዘመን ሐዋርያው ጳውሎስ በማልታ ያጋጠመውን ተሞክሮ አስታወስን።—ሥራ 28:1–10
ዓመቱ 1953 ሲሆን በጊዜው የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት ሥራ በማልታ ሕጋዊ ዕውቅና አላገኘም ነበር። ከዓመት በፊት ከመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ተመርቀን በኢጣሊያ ተመድበን ነበር። ለትንሽ ጊዜ ጣሊያንኛ ካጠናን በኋላ ማልታ ላይ ምን እንደሚጠብቀን ለማየት ጓጓን።
በዚያ የወጣትነት ጊዜዬ በውጭ አገር እንዴት ሚስዮናዊ ልሆን ቻልኩ? እስኪ ልንገራችሁ።
የእናቴ ቀስቃሽ ምሳሌነት
በ1926 ቤተሰባችን በፎርት ፍራንሴስ ኦንታሪዮ ካናዳ ሳለ እናቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በጊዜው የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁበት ስም ነው) አሁን ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞትን አያዩም የሚል ቡክሌት ተቀበለች። በከፍተኛ ስሜት አነበበችውና በዚያው ሳምንት በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት በሚደረገው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ተገኘች። እናቴ ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢ ነበረች። ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረውን እውነት ስትፈልገው እንደነበረ ሀብት አድርጋ ተቀበለችው። (ማቴዎስ 6:33፤ 13:44) ምንም እንኳ ከአባቴ ኃይል የታከለበት ተቃዎሞ ቢደርስባትና ሦስት የምታሳድጋቸው ሴቶች ልጆች ቢኖሩም በተማረችበት ጸንታለች።
በሚቀጥሉት 20 ዓመታት እናቴ ያሳየችው የማይወላውል እምነት እኔንና ሁለቱን እህቶቼን ቴልማንና ቪኦላን ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚገኘው የዘላለም ሕይወት ያወቅነውን ተስፋ አጥብቀን እንድንይዝ አድርጎናል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ብዙ አስቸጋሪ መከራ ቢደርስባትም የመረጠችውን አቅጣጫ ትክክለኛነት በፍጹም ተጠራጥረን አናውቅም።
በ1931 ገና የአሥር አመት ልጅ ሳለሁ በደቡባዊው ሚነሶታ ዩ ኤስ ኤ ወደሚገኘው እርሻ ቦታ ተዛወርን። ወደዚያ በመሄዳችን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበረን የዘወትር ግንኙነት ቢቋረጥም ከእናቴ የምናገኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ግን አልተቋረጠም። በኮልፖልተርነት ወይም በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት የምታከናውነው የሙሉ ልብ አገልግሎት እኔም በዚህ ሥራ ከእሷ ጎን እንድሰለፍ አድርጎኛል። በ1938 ሁለቱ እህቶቼና እኔ በዱሉዝ ሚነሶታ በተደረገው ስብሰባ ላይ በመጠመቅ ራሳችንን ለይሖዋ መወሰናችንን አሳየን።
በ1938 የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ አቅኚ (የኮልፖርተር አዲሱ ስም) ሆኜ ራሴን ለመቻል እንዲያስችለኝ የንግድ ሥራ ትምህርት እንድከታተል እናቴ አበረታታችኝ። አባታችን የራሳችሁ ጉዳይ ነው ብሎ ጥሎን ሲሄድ የእናቴ ምክር ጥሩ እንደነበረ ተረጋገጠ።
ውድ ሀብታችንን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለሌሎች ማካፈል
በመጨረሻ በ1947 ወደ ካሊፎርኒያ ተዛወርኩና የአቅኚነቱን ሥራ በሳን ፍራንሲስኮ ጀመርኩ። በሎስ አንጀለስ ለሚደረገው “በሁሉም ብሔራት መስፋፋት” ለተባለው ስብሰባ በቅድመ ዝግጅት ሥራ ተሳታፊ ሆኜ እያለ ከፍራንሲስ ማላስፒና ጋር ተገናኘሁ። ለሚስዮናዊነት ሥራ ያለን የጋራ ግብ የፍቅር ግንኙነት እንድንመሠርት አደረገ። በ1949 ተጋባን።
መስከረም 1951 ፍራንሲስና እኔ ወደ 18ኛው ክፍል የጊልያድ ትምህርት ቤት ተጋበዝን። ከአምስት ወራት ትጋት የተሞላበት ስልጠና በኋላ የካቲት 10, 1952 የምንላክበት አገር የት እንደሆነ በትምህርት ቤቱ ፕሬዘዳንት ናታን ኤች ኖር በፊደላት ቀደም ተከተል ተነበበ። “ኢጣሊያ፣ ወንድም ማላስፒና እና ባለቤቱ” ብሎ ሲናገር በአእምሮአችን ጉዟችንን ጀመርን!
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ወደ ጄኖዋ ኢጣሊያ ለምናደርገው አሥር ቀን የሚፈጅ ጉዞ ከኒው ዮርክ በመርከብ ተሳፈርን። በብሩክሊኑ ዋና መሥሪያ ቤት ሠራተኞች የሆኑት ጆቫኒ ዴቼካ እና ማክስ ላርሰን መሳፈሪያው ድረስ በመምጣት ተሰናበቱን። በጄኔዋ ወደ አገሪቱ ለመግባት ከሚያስፈልገው ውስብስብ ፎርማሊቲ ጋር የተላመዱ ሚስዮናውያን ተቀበሉን።
በአካባቢያችን ባለው ነገር ሁሉ በመደሰት ወደ ቦሎኛ ለመሄድ ባቡር ተሳፈርን። ስንደርስ የተመለከትነው በሁለተኛ የዓለም ጦርነት የቦንብ ድብደባ እስካሁን መልኳ የጠፋ ከተማ ነበር። ቢሆንም የጠዋቱን አየር እንደሚያውደው የሚያጓጓ ሽታ ያለው የሚቆላ ቡናና ቁጥር ስፍር ለሌለው የፓስታ ዓይነት የተዘጋጀ በቅመም የተከሸነ ስጎ የመሳሰሉ ብዙ አስደሳች ነገሮች ነበሩ።
እቅድን ግብ ማድረስ
በቃል የተሸመደደ መልእክት ይዘን ወደ አገልግሎት እንሄድና ወይ መልእክቱን እስኪቀበሉ አሊያም በሩን እስኪዘጉብን ድረስ እሱኑ እንናገር ነበር። ሐሳባችንን በደንብ ለመግለጽ ያለን ምኞት ቋንቋውን በትጋት እንድናጠና አነሳሳን። ከአራት ወራት በኋላ ኔፕልስ በሚገኝ አዲስ የሚስዮናውያን ቤት ተቀምጠን እንድንሠራ ተመደብን።
ይህች ትልቅ ከተማ በአስገራሚ እይታዎቿ የታወቀች ናት። እዚህ ባለው አገልግሎታችን ብንደሰትም ከአራት ወራት በኋላ ባለቤቴ በክልል ወይም በተጓዥነት ሥራ ከሮም እስከ ሲሲሊ ያሉትን ጉባኤዎች እንዲጎበኝ ተመደበ። በኋላም ወደ ማልታና በሰሜን አፍሪካ ወደ ምትገኘው ሊቢያ ድረስ እንሄድ ነበር።
ከኔፕልስ እስከ ሲሲሊ በዚያን ጊዜ የነበረው የባቡር ጉዞ አካላዊ ጥንካሬን የሚፈታተን ነበር። አንዳንዴ በታጨቀ ባቡር ውስጥ በተጨናነቁ መተላለፊያዎች ላይ ከስድስት እስከ ስምንት ለሚያክሉ ሰዓታት እንቆም ነበር። ቢሆንም በአካባቢያችን ያሉ ሰዎችን ለማወቅ ጥሩ አጋጣሚ ሰጥቶናል። እቤት የሚዘጋጅ ወይን የያዘ ትልቅ ደምበጃን ረዥሙ መንገድ ያስከተለበትን የውኃ ጥም ለማርካት ከያዘው ወይን አልፎ አልፎ ጎንጨት ለሚያደርግለት ባለቤት እንደ መቀመጫ ሆኖ ያገለግላል። የወዳጅነት መንፈስ ያላቸው መንገደኞች ሁሌ ዳቦአቸውንና ሳላሚያቸውን (ከአሳማ ወይም ከበሬ ሥጋ የሚሠራ የምግብ ዓይነት) በማካፈል የሚያደርጉልን ግብዣ እንግዳ ተቀባይነታቸውን የሚያ ሳይ የምናደንቀው ልብን ሞቅ የሚያደርግ ድርጊት ነው።
በሲሲሊ ሻንጣችንን ተሸክመው ተራራው ጫፍ ወዳለው ጉባኤ ለመድረስ ሦስት ሰዓት ተኩል ሳያርፉ አቀበቱን በሚወጡ ወንድሞቻችን አቀባበል ይደረግልን ነበር። የክርስቲያን ወንድሞቻችን ሞቅ ያለ አቀባበል ድካማችንን ያስረሳናል። አንዳንድ ጊዜ በማያዳልጣት በቅሎ ተቀምጠን እንጓዛለን ቢሆንም በቅሎዋ ትንሽ እንኳ ብትደናቀፍ ከበታቻችን የሚጠብቀንን እልም ያለ ገደል ፈጽሞ ወደታች አንመለከትም። ወንድሞቻችን ችግር ቢኖርባቸውም እንኳ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያላቸው ጽኑ አቋም አጠንክሮናል፤ አንዲሁም የተመለከትነውም ፍቅር ከእነሱ ጋር በመገናኘታችን አመስጋኞች እንድንሆን አድርጎናል።
ማልታና ሊቢያ
በሲሲሊ ወንድሞቻችን ትዝታ ተሞልተን ወደ ማልታ ለመጓዝ በመርከብ ተነሳን። ሐዋርያው ጳውሎስ እዚህ ደጋግ ሰዎችን አግኝቶ ነበር እኛም ያገኘነው ይህንኑ ነው። የሴንት ፓል ባሕረ ሰላጤ ማዕበል በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ጀልባዎች ይጋፈጡ የነበረውን አደጋ እንድንገነዘብ አድርጎናል። (ሥራ 27:39 እስከ 28:10) ገና ከፊታችን የሊቢያ ጉዞ ይጠብቀን ነበር። ሥራችን በታገደበት በዚህ የአፍሪካ አገር እንዴት መሥራት እንችል ይሆን?
አሁንም ሙሉ በሙሉ ልዩ የሆነ ባህል አጋጠመን። በተወሰነ ርቀት የተደረደሩ አምዶች ባሉባቸው የመሐል ከተማው አውራ ጎዳናዎች ቀስ እያልን ስንራመድ የትሪፖሊ ከተማ መልክና የሚሰማው ድምፅ ትኩረቴን ሳበው። ወንዶች ከቀኑ የሚያቃጥል የሳሃራ በረሃ ሙቀትና ከምሽቱ ቁር ራሳቸውን ለመከላከል ከግመል ጠጉር የተሠራ ልብስ ይለብሳሉ። ሰዎች ከሚኖሩበት አካባቢ የአየር ጠባይ ጋር ራሳቸውን የሚያስማሙበትን መንገድ መረዳትንና ማክበርን ተምረናል።
ጥንቃቄ የተሞላበት የወንድሞች ቅንዓት በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ስለመደገፍና እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ሥር በመስበክ በኩል ብዙ እውቀት ያካበቱት የሚሰጡትን መመሪያ መከተል እንደሚበጅ ይበልጥ አስተምሮናል። ክርስቲያን ወንድሞቻችን ከተለያዩ ብሔራት የተውጣጡ ቢሆኑም ለይሖዋ በሚያቀርቡት አገልግሎታቸው ተስማምተው ይሠራሉ።
አዲስ የሥራ ምድብ
በስብከት ሥራችን ላይ በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት ኢጣሊያን ለቀን ለመሄድ ተገደድን፤ ቢሆንም በ1957 ብራዚል ሄደን እንድንሰብክ አዲስ የሥራ ምድብ ሲሰጠን በደስታ ተቀበልን። ፍራንሲስና እኔ ከአገሩ ኑሮና ባሕል ጋር ከተለማመድን ከስምንት ወር በኋላ ፍራንሲስ የክልል ሥራ እንዲሠራ ተጋበዘ። በአውቶቡስ፣ በአውሮፕላንና በእግር ተጉዘናል። ይህ ሰፊና ውብ አገር ልክ በጂኦግራፊ ትምህርት ላይ እንደቀረበ ካርታ በፊታችን ተንጣሎ ይታይ ነበር።
የመጀመሪያው ክልላችን በሳኦ ፖሎ ያሉ አሥር ጉባኤዎችንና በሳኦ ፖሎ ግዛት ውስጥ እንዲሁም በየባሕሩ ዳር የሚገኙ አሥር ትንንሽ ከተሞችን ይይዛል። በጊዜው በእነዚያ ከተሞች አንድም ጉባኤ አልነበረም። በመጀመሪያ ማረፊያ ቦታ እንፈልግና ከተረጋጋን በኋላ የመንግሥቱን መልእክት ይዘን ከቤት ወደ ቤት እናንኳኳለን። በተጨማሪም ከመጠበቂያ ግንብ ትምህርት ሰጪ ፊልሞች አንዱን ለመመልከት እንዲመጡ የግብዣ ወረቀት እንተውላቸዋለን።
ፊልሞችን፣ የፊልም ማሳያ መሣሪያ፣ ትራንስፎርመር፣ ፋይሎች፣ ጽሑፍ፣ የግብዣ ወረቀቶችን እንዲሁም ለተጋባዦች ፊልሙ የሚታይበትን ቦታ የሚጠቁም ወረቀት በእጅ ለማተም የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን በአውቶቡስ ማጓጓዝ ቀላል ሥራ አልነበረም። ከዚህ ጋር ስትነጻጸር ትንሿ የልብስ ሻንጣችን ከባድ አልነበረችም። የፊልም ማሳያ መሣሪያችን በኮሮኮንች መንገድ ስንጓዝ ጉዳት እንዳይደርስባት በጭናችን ላይ በጥንቃቄ እናስቀምጠው ነበር።
ለፊልም ማሳያ የሚሆን ቦታ ፈልገን ካገኘን በኋላ ከቤት ወደ ቤት እንሄድና ለፊልሙ ትርኢት የግብዣ ወረቀት እንተውላቸዋለን። አንዳንድ ጊዜ በሆቴሎች ውስጥ ፊልሙን ለማሳየት ፈቃድ እናገኝ ነበር። በሌላ ጊዜ ደግሞ ባዶ ሜዳ ላይ ሁለት ምሰሶዎች ተክለን አንሶላ እንዘረጋ ነበር። ብዙዎቻቸው ተንቀሳቃሽ ምስል ፈጽሞ አይተው የማያውቁት አመስጋኝ አድማጮቻችን ፍራንሲስ ጽሑፉን ሲያነብ ቆመው ልብ ብለው ያዳምጡታል። በኋላም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እናድል ነበር።
ወደ መንደሮቹ ለመድረስ በአውቶቡስ እንጓዛለን። አንዳንዶቹ ወንዞች ማቋረጫ ድልድይ ስላልነበራቸው አውቶቡሱ ትልቅ መንሳፈፊያ ላይ ይደረግና ወደ ሌላኛው አቅጣጫ እንዲሻገር ይደረጋል። ከአውቶቡሱ እንድንወርድና አውቶቡሱ ወደ ወንዙ ሲያዘም ካየን ከአውቶቡሱ ጋር እንዳንሰጥም በመንሳፈፊያው ሌላኛ ጎን እንድንዘል ይነገረን ነበር። ደግነቱ አንድም ቀን አውቶቡሱ ወደ ወንዙ ገብቶብን አያውቅም። ይህ ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ወንዙ ሰው በል በሆኑ ትልልቅ ዓሦች የተሞላ ነበር።
በ1958 የኒው ዮርኩ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ከተገኘን በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ብራዚል ተመልሰን የተጓዥነት ሥራችንን ቀጠልን። የወረዳ ሥራችን በደቡብ የኡራጓይን ጠረፍ፣ በምዕራብ ፓራጓይን፣ በሰሜን የፔርናምቦን ግዛትና በምሥራቃዊው ብራዚል ክፍል ደግሞ የአትላንቲክን ውቅያኖስ ያጠቃልላል።
የሥጋ ደዌ በሽተኞች ገለልተኛ መንደር
በ1960ዎቹ አጋማሽ በአንድ የሥጋ ደዌ በሽተኞች ገለልተኛ መንደር ከማህበሩ ፊልሞች መካከል አንዱን እንድናሳይ ግብዣ ቀረበልን። ፍርሃት እንደነበረብኝ አልሸሽግም። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ካነበብነው በስተቀር ስለ ሥጋ ደዌ በሽታ ያለን እውቀት አናሳ ነበር። ነጭ ቀለም ወደ ተቀባው ግቢ ከገባን በኋላ ወደ አንድ ትልቅ አዳራሽ ወሰዱን። በአዳራሹ ውስጥ ለእኛና ለመሣሪያዎቻችን በገመድ የተከለለ ስፍራ ነበር።
ሲረዳን የነበረው የኤሌክትሪክ ሠራተኛ በገለልተኛ መንደሩ 40 ዓመት ኖሯል። የእጅ አንጓዎቹንና አንዳንድ የሰውነት ክፍሉን በማሳጣት በሽታው ክፉኛ ሰውነቱን አበላሽቶታል። መጀመሪያ ብደናገጥም ፍልቅልቅነቱና የአሠራሩ ጥበብ ዘና እንድል አደረገኝ። አስፈላጊዎቹን ዝግጅቶች እንዳጠናቀቅን ስለ ብዙ ነገሮች መወያየት ጀመርን። በተቋሙ ውስጥ ካሉት አንድ ሺህ ጉዳተኞች መካከል ከሁለት መቶ በላይ ተገኙ። በሽታው ብዙ የተለያየ ደረጃ እንዳለው ለመረዳት ቻልን። ይህ ለእኛ ምን ዓይነት ስሜትን የሚነካና የሚያሳዝን ነበር!
ኢየሱስ “ብትወድስ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ለለመነው ለምጻም ምን እንደተናገረው እናስታውሳለን። ኢየሱስ ሰውዬውን ዳሰሰውና “እወዳለሁ ንጻ” በማለት መዳኑን እንደሚፈልግ አረጋገጠለት። (ማቴዎስ 8:2, 3) ፕሮግራሙ ከተጠናቀቀ በኋላ ብዙዎቹ ወደ እኛ ቀርበው በመምጣታችን አመሰገኑን፤ የተጎዳ ሰውነታቸው የሰው ልጆች ታላቅ መከራ ጉልህ ምልክት ነው። በኋላም የአካባቢው ምሥክሮች ተጨማሪ ትምህርት የማግኘት ፍላጎት ያደረባቸውን ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን አስጠኑ።
ያሉብንን አንዳንድ ከባድ የጤና ችግሮች ለማስታመም እንችል ዘንድ በ1967 ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። እነዚህን የጤንነት ችግሮች ለማስወገድ እየተከታተልን እያለ እንደገና በክልል ሥራ የማገልገል መብት አገኘን። ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት ከፍራንሲስ ጋር በዩናይትድ ስቴት በተጓዥነት ሥራ ተካፍያለሁ። በዚህ ጊዜ እሱ በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ አስተማሪ ሆኖ አገልግሏል።
ማንኛውም ዓይነት የሥራ ምድብ ቢሰጠው እሺ ብሎ የሚቀበል አፍቃሪና ታማኝ የኑሮ ጓደኛ ማግኘቱ ለእኔ ምን ዓይነት የብርታት ምንጭ ነበር! የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሆነውን ሀብት በአራት አህጉራት አብረን የማካፈል መብት አግኝተናል።
ውዱ ሀብት በሚሰጠው ኃይል መጽናት
በ1950 እናቴ በ1924 የተጠመቀውን ታማኝ ወንድም ዴቪድ ኢስተርን አገባች። በሙሉ ጊዜ ሰባኪነት አብረው ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል። ነገር ግን በእናቴ የሕይወቷ መገባደጃ ዓመታት የነርቭ ሥርዓትን የሚያጠቃው አልዘሚር በሽታ ይታይባት ጀመር። በሽታው አእምሮዋን ስለነካባት ብዙ እንክብካቤ ትፈልግ ነበር። ደጋፊ የሆነችው እህቴና ዴቪድ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ውድ መብት እንድንተው ስለማይፈልጉ እሷን የመንከባከቡን ከባድ ኃላፊነት ተሸክመው ነበር። እናቴ እስከሞተችበት 1987 ድረስ ያሳየችው የታማኝነት ምሳሌ የሕይወታችንን አቅጣጫ እንድንቀይስ ያደረገን ሲሆን በምትካፈልበትም የሰማያዊ ተስፋ ሽልማት እንጽናናለን።
በ1989 ፍራንሲስ ብርታቱ እንደቀድሞው እንዳልሆነ አስተዋልኩ። ሳናውቀው በብዙ የዓለም ክፍሎች የታወቀው ቢልሃርዝያ የተባለው በሽታ እየጎዳው ነበር። በ1990 ይህ ምህረት የለሽ በሸታ አሸነፈውና በይሖዋ አገልግሎት 40 ዓመት አብሬው የተካፈልኩትን ተወዳጅ የኑሮ ጓደኛዬን አጣሁ።
ማስተካከያ ማድረግን የሚጠይቁ ለውጦች የሕይወት ክፍል ናቸው። አንዳንዶቹ ቀላል ጥቂቶቹ ደግሞ አስቸጋሪ ናቸው። ነገር ግን ውድ ሀብት የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚሰጠን ይሖዋ በድርጅቱ እንዲሁም በቤተሰቦቼ ፍቅርና ማበረታቻ በመስጠት አጽንቶኛል። መሬት ጠብ የማይሉትን የይሖዋ ተስፋዎች ፍጻሜ በጉጉት በመጠባበቅ አሁንም ርካታ እያገኘሁ ነው።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባለቤቴና እኔ በኢጣሊያ ሚስዮናዊ ሆነን ስናገለግል