የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w05 12/1 ገጽ 13-17
  • ፈጣሪዬን ማገልገሌን ለመቀጠል ቆርጫለሁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ፈጣሪዬን ማገልገሌን ለመቀጠል ቆርጫለሁ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበልን
  • የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን
  • በተመደብንበት ቦታ መኖር ጀመርን
  • በሚስዮናዊነት ያገኘናቸው ተሞክሮዎች
  • ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም
  • ሌላ አሳዛኝ ክስተት
  • አገልግሎቴን ቀጠልኩ
  • ዓይኔንና ልቤን በሽልማቱ ላይ እንዲያተኩር አድርጌ ነበር
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • መጽሐፍ ቅዱስን በማስተማሩ ዓለም አቀፍ ሥራ ላይ በመካፈሌ ደስተኛ ነኝ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • በይሖዋ አገልግሎት ያሳለፍኩት በበረከት የተሞላ ሕይወት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • እጅግ ውድ የሆነ ሀብት ለሌሎች ማካፈል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
w05 12/1 ገጽ 13-17

የሕይወት ታሪክ

ፈጣሪዬን ማገልገሌን ለመቀጠል ቆርጫለሁ

ኮንስታንስ ቤናንቲ እንደተናገረችው

ሁሉ ነገር የሆነው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር! የዓመት ከአሥር ወር ልጃችን ካሚል ከባድ ትኩሳት ያዛትና በስድስት ቀን ውስጥ ሞተች። ከመጠን ባለፈ ሐዘን ተውጬ ነበር። እኔ ራሴ ሞትን ተመኘሁ። አምላክ እንዲህ ዓይነቱን ነገር የሚፈቅደው ለምንድን ነው? ግራ ገብቶኝ ነበር።

ወላጆቼ የጣሊያን ስደተኞች ናቸው። ሲሲሊ ውስጥ ከምትገኘው ከካስቴላማሬ ዴል ጎልፎ ወደ ኒው ዮርክ ከተማ ከመጡ በኋላ ታኅሣሥ 8, 1908 እኔ ተወለድኩ። ቤተሰባችን እናትና አባቴን ጨምሮ አምስት ወንዶችና ሦስት ሴቶች ልጆችን ያቀፈ ነበር።a

በ1927 አባቴ ሳንቶ ካታንዛሮ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ። ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት (ቤቴል ይባላል) ያገለግል የነበረው ጣሊያናዊ ወንድም ጆቫኒ ዴቼካ እኛ በምንኖርበት በኒው ጀርሲ አካባቢ ስብሰባ ይመራ ነበር። አባቴ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መስበክ የጀመረ ሲሆን በሞት እስካንቀላፋበት እስከ 1953 ድረስ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈሉን አላቋረጠም።

እናቴ በወጣትነቷ መነኩሴ የመሆን ምኞት የነበራት ቢሆንም እንኳ ወላጆቿ አልፈቀዱላትም። መጀመሪያ ላይ የእናቴን ምክር ስለሰማሁ አባቴ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያጠና አብሬው መገኘት አልፈልግም ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ አባቴ ላይ አንዳንድ ለውጦችን ማስተዋል ጀመርኩ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጀመረ በኋላ ይበልጥ የተረጋጋና የዋህ እየሆነ ከመምጣቱም በላይ በቤተሰቡ ውስጥ ሰላም ሰፍኖ ነበር። ይህ ደግሞ አስደሰተኝ።

በዚህ ወቅት ብሩክሊን ውስጥ ከተወለደና በእኔ ዕድሜ ላይ ከሚገኝ ቻርልስ ከተባለ ሰው ጋር ተዋወቅሁ። የእርሱም ቤተሰቦች ልክ እንደ እኔ ቤተሰቦች ከሲሲሊ የመጡ ነበሩ። ብዙም ሳንቆይ ተጫጨንና አባቴ በ1931 በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተካፍሎ ሲመለስ ተጋባን። በአንድ ዓመት ውስጥ ልጃችን ካሚል ተወለደች። ስትሞት ግን ልቤ በሐዘን ተሰበረ። አንድ ቀን ቻርልስ እያለቀሰ “ካሚል የአንቺ ልጅ እንደሆነች ሁሉ የእኔም ልጅ ናት። ለምን እርስ በርሳችን እየተጽናናን ሕይወታችንን አንመራም?” አለኝ።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበልን

አባቴ በካሚል የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ንግግር ሲሰጥ ስለ ትንሣኤ ተስፋ ተናግሮ እንደነበር ቻርልስ አስታወሰኝ። እኔም “በእርግጥ በትንሣኤ ታምናለህ?” ብዬ ጠየቅኩት።

“አዎን፣ አምናለሁ! መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ይበልጥ ለማወቅ ለምን አንመረምርም?” ብሎ መለሰልኝ።

ያን ሌሊት እንቅልፍ አልወሰደኝም። አባቴ ለሥራ ሳይወጣ ከጠዋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ ሄጄ እኔና ቻርልስ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንደምንፈልግ ነገርኩት። በጣም ከመደሰቱ የተነሳ አቀፈኝ። እናቴ አልጋ ላይ ሆና እኔና አባቴ የምናወራውን ትሰማ ነበር። ምን ተፈጠረ ብላ ጠየቀችኝ። እኔም “ምንም አይደለም፣ እኔና ቻርልስ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ፈልገን ነው” በማለት መለስኩላት።

“ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት አለብን” አለችኝ። ስለዚህ ወንድሞቼንና እህቶቼን ጨምሮ አሥራ አንዳችንም በቤተሰብ ሆነን ማጥናት ጀመርን።

መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ እንድጽናና የረዳኝ ከመሆኑም በላይ የነበረኝ የግራ መጋባት ስሜትና ሐዘን ቀስ በቀስ በተስፋ ተተካ። ከዓመት በኋላ ማለትም በ1935 እኔና ቻርልስ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሰዎች መስበክ ጀመርን። በየካቲት 1937 ብሩክሊን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስ የውኃ ጥምቀት አስፈላጊ መሆኑን እንደሚናገር የሚገልጽ ንግግር ከሰማን በኋላ በአቅራቢያችን ወደሚገኝ አንድ ሆቴል ሄደን ከሌሎች ጋር ተጠመቅን። ይህን እርምጃ የወሰድኩት ልጄን አንድ ቀን እንደገና አገኛታለሁ በሚል ተስፋ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ እያወቅኩትና እየወደድኩት የመጣሁትን ፈጣሪያችንን የማገልገል ፍላጎት ስላደረብኝ ነው።

የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርን

በዚያን ጊዜ የነበሩ ብዙ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ጥሩ ምላሽ ከመስጠት አልፈው በስብከቱ ሥራ አብረውን ስለሚካፈሉ፣ ስለተማርኩት ነገር ለሌሎች መንገር አስደሳችና የሚክስ ነበር። (ማቴዎስ 9:37) በ1941 እኔና ቻርልስ አቅኚዎች (የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮቻቸውን የሚጠሩበት ስም ነው) ሆንን። ብዙም ሳይቆይ ተንቀሳቃሽ ቤት ገዛን፤ ከዚያ በኋላ ቻርልስ የሱሪ ፋብሪካችንን ለታናሽ ወንድሜ ለፍራንክ አስረከበው። ከጊዜ በኋላ በልዩ አቅኚነት እንደተመደብን የሚያበስር ደብዳቤ ሲደርሰን በጣም ተደሰትን። መጀመሪያ ላይ እናገለግል የነበረው በኒው ጀርሲ ነበር፤ ከዚያም ወደ ኒው ዮርክ ከተማ ተላክን።

በ1946 በቦልቲሞር፣ ሜሪላንድ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ እያለን በቦታው የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች ተወካዮች ቀርበን እንድናነጋግራቸው ተነገረን። እዚያም ናታን ኖርንና ሚልተን ሄንሼልን አገኘናቸው። ስለ ሚስዮናዊ አገልግሎት በተለይ ደግሞ በጣሊያን ስለሚደረገው የስብከት ሥራ አነጋገሩን። ከዚያም በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር አጋጣሚ መኖሩን ከገለጹልን በኋላ እንድናስብበት ሐሳብ አቀረቡልን።

“በደንብ አስቡበትና መልሱን ንገሩን” አሉን። ከቢሮው እንደወጣን እኔና ቻርልስ እርስ በርስ ተያየንና ወዲያውኑ ወደ ቢሮው ተመልሰን “አስበንበታል፤ በጊልያድ ለመካፈል ዝግጁዎች ነን” አልናቸው። ከአሥር ቀን በኋላ በጊልያድ ትምህርት ቤት ሰባተኛውን ክፍል መካፈል ጀመርን።

በሥልጠና ያሳለፍናቸው ወራት ፈጽሞ የማይረሱ ናቸው። ከሁሉም በላይ ያስደነቀን ደግሞ አስተማሪዎቹ በውጪ አገር የሚገጥሙንን ችግሮች ለመጋፈጥ ዝግጁ እንድንሆን እኛን ለማሠልጠን ያሳዩት ትዕግሥትና ፍቅር ነበር። ሐምሌ 1946 ከተመረቅን በኋላ ብዙ ጣሊያናውያን በሚኖሩበት በኒው ዮርክ ከተማ በጊዜያዊነት እንድናገለግል ተመደብን። ከዚያ በኋላ አስደሳቹ ቀን ደረሰ! ሰኔ 25, 1947 በሚስዮናዊነት ወደተመደብንበት ወደ ጣሊያን ጉዞ ጀመርን።

በተመደብንበት ቦታ መኖር ጀመርን

ከዚያ ቀደም ለውትድርና አገልግሎት ይውል በነበረ አንድ መርከብ ጉዟችንን ጀመርን። ለ14 ቀናት ያህል በባሕር ላይ ከተጓዝን በኋላ የጣሊያን ወደብ ወደሆነችው ጀኖአ ገባን። ከተማዋ ከሁለት ዓመት በፊት ያቆመው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካደረሰባት ጉዳት አላገገመችም ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የባቡር ጣቢያው በቦምብ በመደብደቡ ምክንያት የመስኮቶቹ መስታወት ረግፎ ነበር። ከጀኖአ በዕቃ ማመላለሻ ባቡር ተሳፍረን ቅርንጫፍ ቢሮውና የሚስዮናውያን መኖሪያ ቤት ወደሚገኝበት ወደ ሚላን ተጓዝን።

ከጦርነቱ በኋላ በጣሊያን የኑሮው ሁኔታ በጣም አሽቆልቁሎ ነበር። መልሶ የመገንባት ጥረቶች የተጀመሩ ቢሆንም እንኳ ድህነት ተስፋፍቶ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ከባድ የጤና ችግር አጋጠመኝ። አንድ ዶክተር የልቤ ሁኔታ መጥፎ ደረጃ ላይ ስለደረሰ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ብመለስ የተሻለ እንደሆነ አስቦ ነበር። ያለው ነገር ትክክል አለመሆኑን በማወቄ ደስተኛ ነኝ። ይኸው ከ58 ዓመት በኋላም በተመደብኩበት ቦታ በጣሊያን እገኛለሁ።

ወደ ጣሊያን ከሄድን ከጥቂት ዓመታት በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙት ወንድሞቼ መኪና ሊልኩልን እንደሚፈልጉ ነገሩን። ይሁን እንጂ ቻርልስ ሐሳባቸውን ሳይቀበል ቀረ፤ እኔም በውሳኔው ተደስቻለሁ። እኛ እስከምናውቀው ድረስ በዚያን ጊዜ ጣሊያን ውስጥ አንድም ወንድም መኪና አልነበረውም፤ ስለዚህ ቻርልስ ከክርስቲያን ወንድሞቻችን ጋር ተመሳስለን ብንኖር የተሻለ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። በ1961 አነስተኛ መኪና እስከያዝንበት ጊዜ ድረስ ምንም መኪና አልነበረንም።

በሚላን የአፈር ወለል የነበረው የመጀመሪያው የመንግሥት አዳራሻችን የሚገኘው ምድር ቤት ውስጥ ነበር። መንግሥት አዳራሹ መጸዳጃ ቤት ያልነበረው ከመሆኑም ሌላ ቧንቧ ስላልነበረ ውኃ የሚባል ነገር ቤቱ ውስጥ የምናየው ዝናብ ዘንቦ ሲያጥለቀልቀን ብቻ ነው። ከወዲያ ወዲህ ውር ውር የምትል አንዲት ትንሽ አይጥም ነበረች። በአዳራሻችን የነበሩት ሁለት አምፑሎች ብቻ ነበሩ። እነዚህ ችግሮች ቢኖሩም እንኳ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በስብሰባዎቻችን ላይ ሲገኙና እድገት አድርገው አብረውን ሲያገለግሉ ማየት በጣም ያጽናናን ነበር።

በሚስዮናዊነት ያገኘናቸው ተሞክሮዎች

አንድ ቀን ፒስ—ካን ኢት ላስት? የሚለውን ቡክሌት ለአንድ ሰው አበርክተንለት ከቤቱ እየወጣን ሳለ ሳንቲና የምትባለው ባለቤቱ ከግሮሰሪ የገዛችውን ዕቃ ተሸክማ ስትገባ አገኘናት። ትንሽ በስጨት በማለት ስምንት ሴቶች ልጆችን ስለምታሳድግ ጊዜ እንዳልተረፋት ተናገረች። በሌላ ቀን ወደ ቤታቸው ተመልሼ ስሄድ ባለቤትዋ አልነበረም፤ እርሷን ግን ሹራብ ስትሠራ አገኘኋት። “ቁጭ ብዬ አንቺን የማዳምጥበት ጊዜ የለኝም፤ በዚያ ላይ ደግሞ ማንበብ አልችልም” አለችኝ።

በልቤ ወደ ይሖዋ ከጸለይኩ በኋላ ለባለቤቴ ሹራብ ሠርታ እንድትሸጥልኝ ጠየቅኳት። ከሁለት ሳምንት በኋላ ተመልሼ በመሄድ ሹራቡን የወሰድኩ ሲሆን ሳንቲናም “ዘ ትሩዝ ሻል ሜክ ዩ ፍሪ” በተባለው መጽሐፍ አማካኝነት ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች። ሳንቲና ማንበብ የተማረች ከመሆኑም ባሻገር ባለቤቷ ቢቃወማትም እንኳ እድገት አድርጋ ለመጠመቅ ችላለች። አምስት ልጆቿ የይሖዋ ምሥክሮች የሆኑላት ሲሆን እርሷም ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲቀበሉ ረድታለች።

በመጋቢት 1951 ከሁለት ሚስዮናውያን ማለትም ከሩት ካኖንb እና ከጊዜ በኋላ ወንድም ቢል ወንገርትን ካገባችው ከሎይስ ካልሃን ጋር ምንም የይሖዋ ምሥክር ወደሌለበት ወደ ብሬሻ ተዛወርን። የተሟላ የቤት ዕቃ ያለው አፓርታማ አግኝተን ነበር፤ ሆኖም ከሁለት ወር በኋላ ባለቤቱ ቤቱን በ24 ሰዓት ውስጥ ለቀን እንድንወጣ ጠየቀን። በቦታው ምንም የይሖዋ ምሥክር ባለመኖሩ ሆቴል ውስጥ መኖር ግድ ሆነብን፤ በዚያም ለሁለት ወራት ያህል ተቀመጥን።

የምንበላው ምግብ የተወሰነ ዓይነት ነበር። ቁርሳችንን ቡና በወተት ከክሮሰንት ጋር እንበላለን፤ ምሳችንንና እራታችንን ደግሞ ግሪሲኒ በቺዝ (ፎርማጆ) ከፍራፍሬ ጋር እንመገባለን። እነዚህ ችግሮች ቢኖሩብንም ደስታና የአምላክ በረከት አልተለየንም። በኋላ ላይ አነስተኛ አፓርታማ ያገኘን ሲሆን በ1952 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ እንደ መንግሥት አዳራሽ በተጠቀምንባት ትንሽ ክፍል ውስጥ 35 ሰዎች ተገኝተው ነበር።

ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም

በዚያን ጊዜም ቢሆን ቀሳውስቱ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በብሬሻ ስናገለግል አንዳንድ ልጆች በቄሶቻቸው ገፋፊነት ድንጋይ ይወረውሩብን ነበር። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ 16 ሰዎች ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረው በአጭር ጊዜ ውስጥ የይሖዋ ምሥክር ሆኑ። የሚገርመው ከእነዚህ ሰዎች መካከል ድንጋይ እንደሚወረውሩ ከሚዝቱብን ልጆች አንዱ ይገኝበታል! በአሁኑ ሰዓት በብሬሻ በሚገኝ አንድ ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። በ1955 ከብሬሻ ስንወጣ 40 የመንግሥቱ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ ይካፈሉ ነበር።

ከዚያ በኋላ ወደ ሌግሆርን (ሊቮርኖ) ተዛውረን ለሦስት ዓመት አገለገልን። በዚህ ጉባኤ ውስጥ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ሴቶች ነበሩ። በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ ለወንዶች የሚሠጡትን የጉባኤ ኃላፊነቶች የምናከናውነው እኛ ሴቶች ነበርን። በኋላም ከ11 ዓመት በፊት አገልግሎታችንን ወደጀመርንባት ወደ ጀኖአ ተዛወርን። በዚህ ጊዜ አንድ ጉባኤ ተቋቁሞ ነበር። የመንግሥት አዳራሹ ደግሞ እኛ በነበርንበት አፓርታማ የመጀመሪያው ፎቅ ላይ ነበር።

ጀኖአ እንደደረስን አንዲት ሴት ማስጠናት ጀመርኩ፤ የዚህች ሴት ባለቤት ቀደም ሲል ቦክሰኛ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ደግሞ የቦክስ ጅምናዚየም ኃላፊ ነበር። ሴትየዋ ፈጣን መንፈሳዊ እድገት አድርጋ ብዙም ሳትቆይ ክርስቲያን እህታችን ሆነች። ይሁን እንጂ ባለቤቷ ለረጅም ዓመታት ተቃውሟት ነበር። በኋላ ላይ ግን ከባለቤቱ ጋር ወደ ስብሰባዎች መምጣት ጀመረ። ይሁንና ወደ አዳራሹ ከመግባት ይልቅ ውጪ ተቀምጦ ያዳምጥ ነበር። ጀኖአን ለቀን ከሄድን በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀመርለት መጠየቁን ሰማን። ከጊዜ በኋላ ተጠምቆ አፍቃሪ ክርስቲያን የበላይ ተመልካች ሆኗል። እስከ ዕለተ ሞቱም ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል።

በተጨማሪም ፖሊስ እጮኛ ያላትን አንዲት ሴት መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናት ነበር። ይህ ሰው መጀመሪያ ላይ የተወሰነ ፍላጎት አሳይቶ ነበር፤ ከተጋቡ በኋላ ግን ባሕርይው ተለወጠ። በጣም ስለተቃወማት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቷን አቋረጠች። የተወሰነ ጊዜ ቆይታ ማጥናቷን ስትቀጥል ከዚህ በኋላ ስናጠና ቢያገኘን ሁለታችንንም በሽጉጥ እንደሚገድለን በመናገር ያስፈራራት ጀመር። ይሁን እንጂ መንፈሳዊ እድገት አድርጋ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በቅታለች። ያም ሆኖ እንደዛተብን ፈጽሞ አልተኮሰም። እንዲያውም ከዓመታት በኋላ ጀኖአ ሄጄ የአውራጃ ስብሰባ ስካፈል ከኋላዬ አንድ ሰው መጥቶ ዓይኔን ሸፈነኝና ማን መሆኑን እንድገምት ጠየቀኝ። የዚያች ሴት ባለቤት መሆኑን ስመለከት እንባዬን መቆጣጠር አቃተኝ። አቅፎ ሰላም ካለኝ በኋላ ራሱን ለይሖዋ ወስኖ በዚያን ዕለት እንደተጠመቀ ነገረኝ!

ቻርልስ ከ1964 እስከ 1972 ባሉት ዓመታት ጉባኤዎችን በመንፈሳዊ ለማበርታት ጉብኝት ሲያደርግ እኔም አብሬው የማገልገል መብት አግኝቼ ነበር። በፒድሞንት፣ በሎምባርዲየም እና በሊግዮሪያ በጥቅሉ በመላው ሰሜን ጣሊያን አገልግለናል ማለት ይቻላል። ከዚያም በፍሎረንስ አካባቢ ቀጥሎም በቬርሼሊ አቅኚ ሆነን አገልግለናል። በቬርሼሊ በ1977 የነበረው ጉባኤ አንድ ብቻ ቢሆንም በ1999 ከዚያ ስንለቅ የነበረው የጉባኤዎች ቁጥር ሦስት ደርሶ ነበር። በዚያን ወቅት 91 ዓመት ሞልቶኝ ነበር፤ ከዚያም ወደ ሮም ሄደን በአንጻራዊ ሁኔታ ሰላም በሰፈነበት አካባቢ በሚያምር የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ እንድንኖር ተነገረን።

ሌላ አሳዛኝ ክስተት

መጋቢት 2002 ላይ ለወትሮው ጥሩ ጤንነት የነበረው ቻርልስ በድንገት ታመመ። ጤንነቱ እያሽቆለቆለ ሄዶ ግንቦት 11, 2002 ሕይወቱ አለፈች። በ71 ዓመት የትዳር ዘመናችን ክፉውንም ደጉንም አብረን አሳልፈናል። የእርሱ መሞት ጥልቅ የሆነ ሐዘን አስከትሎብኛል።

ቻርልስ ሙሉ ልብስ ለብሶና በ1930ዎቹ ዓመታት ይዘወተር የነበረውን ኮፍያ አድርጎ በዓይነ ሕሊናዬ ይታየኛል። ፈገግታው ፊቴ ላይ ድቅን ይልብኛል፤ ወይም ያን የተለመደ ሳቁን የሰማሁ ይመስለኛል። በይሖዋ እርዳታ እንዲሁም ውድ ክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ባሳዩኝ ፍቅር በመበረታታት ይህን ክፉ ጊዜ መቋቋም ችያለሁ። ቻርልስን እንደገና የማይበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ።

አገልግሎቴን ቀጠልኩ

በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የያዘው ፈጣሪዬን ማገልገል ነው። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ‘ይሖዋ ቸር መሆኑን ቀምሼ አይቻለሁ።’ (መዝሙር 34:8) ፍቅሩን የቀመስኩ ሲሆን እንክብካቤውን ተመልክቻለሁ። ልጄን በሞት ባጣትም እንኳ ይሖዋ ለእኔም ሆነ ለእርሱ ደስታ የሚያመጡ በመላው ጣሊያን የሚገኙ ብዙ መንፈሳዊ ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ሰጥቶኛል።

በጣም የሚያስደስተኝ ነገር ቢኖር ስለ ፈጣሪዬ ለሰዎች መናገር ነው። መስበኬንም ሆነ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናቴን የቀጠልኩት ለዚህ ነው። ጤና በማጣቴ ብዙ መሥራት ስለማልችል የማዝንበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ ይሖዋ የአቅም ገደቤን እንደሚያውቅልኝ፣ የቻልኩትን ያህል በማድረጌ እንደሚደሰትብኝና እንደሚወደኝ ይገባኛል። (ማርቆስ 12:42) “በምኖርበት ዘመን ሁሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ በሕይወትም እስካለሁ ለአምላኬ እዘምራለሁ” ከሚሉት በመዝሙር 146:2 ላይ ከሚገኙት ቃላት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር እጥራለሁ።c

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የወንድሜ የአንጄሎ ካታንዛሮ ተሞክሮ በሚያዝያ 1, 1975 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 205-207 ላይ ይገኛል።

b የሕይወት ተሞክሮዋ በግንቦት 1, 1971 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 277-280 ላይ ይገኛል።

c ይህ ጽሑፍ በመዘጋጀት ላይ እያለ እህት ቤናንቲ ሐምሌ 16, 2005 በ96 ዓመታቸው በሞት አንቀላፍተዋል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካሚል

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1931 በሠርጋችን ዕለት

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጀመሪያ ላይ ፍላጎት ያልነበራት እናታችን ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት እንዳለብን ተስማማች

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1946 በጊልያድ ምርቃት ላይ ከወንድም ኖር ጋር

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከቻርልስ ጋር፣ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ