የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ይሖዋ ከጠላቶቹ ይልቅ ኃያል ነው
ዲያብሎስና አጋንንቱ በሐሰት ሃይማኖትና በመናፍስትነት በመጠቀም የምሥራቹ ስብከት እንዲስተጓጎል ለረዥም ጊዜ ጥረዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በ2 ቆሮንቶስ 4:4 ላይ “የክርስቶስ የክብሩ ወንጌል ብርሃን እንዳያበራላቸው፣ የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን አሳብ አሳወረ” በማለት የሰይጣንን መሰሪ ዓላማ ይገልጻል።
ቢሆንም ይሖዋ አምላክ ከሰይጣን ይልቅ ኃያል ነው። የይሖዋ ባላንጣዎች ‘ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ያለውን መለኮታዊ ፈቃድ እንዳይፈጸም ለማገድ አንዳች ሊያደርጉ አይችሉም። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ከአውስትራሊያ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የተገኙ የሚከተሉት ሪፖርቶች ይህንን ያጎላሉ።
◻ አንዲት ሴት ለ20 ዓመት ከሃይማኖት ተለይታ ከቆየች በኋላ እንደገና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጀመረች። ለመጽሐፍ ቅዱስ ያላት ፍላጎት እንደገና መቀስቀሱ ብዙ ጥያቄዎች እንዲኖሯት ስላደረገ መልሶቻቸውን ለማግኘት ትችል ዘንድ ለርዳታ ወደ አምላክ ጸለየች። እውነቱን ለማግኘት ፍለጋ ለማድረግ ብትሻም ወደ ቀድሞ ሃይማኖቷ መመለሱ ችግሯን ሊፈታላት እንደማይችል አወቀች። በዚህ ፋንታ ወደ አንድ የአሮጌ መጽሐፍ መደብር ሄደችና ሃይማኖት ነክ የሆኑ ማንኛውም ዓይነት መጻሕፍት እንዳላቸው በመጠየቅ ፍለጋዋን ጀመረች።
የመደብሩ ባለቤት በመደብሩ ሳይሆን በመኖሪያ ቤቷ ሃይማኖታዊ መጽሐፍ እንዳላት አስታወሰች። መጽሐፉ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የሚል ርዕስ ያለውና በይሖዋ ምሥክሮች የታተመ ነበር። ሴትዮዋ መጽሐፉን በጉጉት አነበበችውና ለብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቿ መልስ አገኘች። በስልክ ማውጫ መጽሐፍ በመታገዝ የይሖዋ ምሥክሮችን ከፈለገች በኋላ በመጨረሻ አገኘቻቸው። ከዚያም ቋሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች።
◻ አንዲት ወጣት ሴት የክታብ ሽያጭ ለማስተዋወቅ ስትል በአካባቢው ለሚታተመው ጋዜጣ ገንዘብ ከፈለች። ማስተዋወቂያው ‘በጣም ኃያል የሆነ የመካከለኛው ዘመን ክታብ’ በማለት አቀረበው። አንዷ የይሖዋ ምሥክር ይህንን ማስታወቂያ ተመለከተች። በተሰጠው ስልክ ቁጥር ለመደወልና ክታቡ አለው የተባለውን ኃይል ከወዴት እንዳገኘው ልታነጋግራት ወሰነች። መጽሐፍ ቅዱስ በአጋንንታዊ ተግባራት ላይ ያለውን አመለካከት የተመረኮዘ ውይይት ተከተለ። ባለ ክታቧ ሴት ከአንድ ቀን በፊት አምላክ ያለባትን የአጋንንት ችግር ለመወጣት እንዲረዳት ጸልያ እንደነበረ ገለጸችላት። ምሥክሯ በስልክ ሌላ ውይይት ለማድረግ ዝግጅት አደረገች።
በደወለች ጊዜ ወጣቷ ሴት እቤት አልነበረችም። እናትየው ስልኩን አነሱና “ለልጄ የነገርሻት ምን እንደሆነ ባላውቅም የተፈጸመው ግን ተአምር ነው!” አሏት። መጀመሪያ ስልክ ከተደወለላት ጀምሮ ሴት ልጃቸው ሁሉንም ሰይጣናዊ ሥዕሎችና መጻሕፍት እርግፍ አድርጋ በማስወገድ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ እንደ ጀመረች አወሩላት።
ብዙም ሳይቆይ ወጣቷን ሴት በግል አግኝታ ለማነጋገር ዝግጅት አደረገች። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በቋሚነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማድረጉን ሳታንገራግር ተቀበለች። በዚህ ብቻ ሳትወሰን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻቸው በመገኘት ከምሥክሮቹ ጋር መቀራረብ ጀመረች። የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ እውቀት ፍንትው ብሎ እንዲበራ በማድረግ አሁንም ይሖዋ አጋንንትን ድል መታቸው።