የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
የመንግሥቱ ምሥራች ይሰበካል
የአምላክ ቀንደኛ ጠላት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ላለፉት መቶ ዘመናት የእውነተኛውን ክርስትና ሥርጭት ለመግታት በፖለቲካ ባለ ሥልጣናትና በሐሰት ሃይማኖት በተንኮል ተጠቅሟል። ነገር ግን እነዚህ ዘዴዎች አይሳኩለትም። ኢየሱስ “ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል [“ይሰበክ ይሆናል” ወይም “ሊሰበክ ይችላል” አላለም]” ብሎ ተንብዮአል።—ማቴዎስ 24:14
የሰይጣን ዘዴዎች አለመሳካታቸው በግሪክ በግልጽ ታይቷል። በዚህ አገር የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምሥራች ከመስበክ እንዲታቀቡ ጥረት ያደርጋል። ቢሆንም የሚቀጥለው ተሞክሮ እንደሚያጎላው ምንም እንኳ ተቃውሞ ቢኖር ይዋል ይደር እንጂ ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይደርሳቸዋል።
የዛሬ 30 ዓመት ገደማ አንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄስ ምሥራቹን ተቀበሉ። በዚህም ብቻ ሳይወሰኑ ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ። ቢሆንም ቤተ ዘመዶቻቸው ርምጃቸውን በጽኑ በመቃወም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያቆሙ ተጽዕኖ አሳደሩባቸው። ቤተሰቦቻቸውን ደስ ለማሰኘት ብለው የቅስና ሥራቸውን ቢቀጥሉም የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን እንዲማሩ እንደረዷቸውና እሳቸው ግን በሐሰት ሃይማኖት ውስጥ ላላቸው ማዕረግ ብለው ከእነሱ ጋር መተባበራቸውን እንዳቆሙ ያውቁ ነበር።
ዳሩ ግን አንዳንድ ጊዜ አጋጣሚው ሲፈጠር የይሖዋ ምሥክሮችን ደግፈው ይናገራሉ። በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሚያገኟቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመማር ከፈለጉ ከምሥክሮቹ ጋር ማጥናት እንዳለባቸው አጥብቀው ያሳስቧቸው ነበር። ከዓመታት በኋላ አንዳንዶቹ ምክራቸውን ተከትለዋል።
በቅርቡ ቄሱ በጣም ታመሙና ብዙም ሳይቆዩ እንደሚሞቱ አወቁ። ሆስፒታል ተኝተው እያሉ ልጆቻቸውን አስጠሩ፣ ልጆቻቸውም በአልጋቸው ዙሪያ ተሰባሰቡ።a ከዚያም ከሞቱ እንደገና ሊያገኟቸው እንደሚችሉ ለልጆቻቸው ነገሯቸው። ሰዎች በምድር ላይ በገነት ለመኖር በትንሣኤ እንደሚነሱ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ነገሯቸው። ነገር ግን ይህ ሲፈጸም ለማየት ከፈለጉ እውነትን ከመጽሐፍ ቅዱስ መማርና ራሳቸውን ከሐሰት ሃይማኖት ማግለል እንዳለባቸው ነገሯቸው። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት እንዲፈጥሩና እንዴት እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆን እንደሚቻል ከእነሱ እንዲማሩ ለመኗቸው።
ብዙም ሳይቆይ ቄሱ ሞቱ። ቢሆንም ለልጆቻቸው የሰጡት የመለያያ ምክር ጥሩ ውጤት አፈራ። እንደሌሎቹ ዘመዶቻቸው ሁሉ ሴት ልጃቸው የይሖዋ ምሥክሮችንና ሥራቸውን አጥብቃ ትቃወም ነበር። ነገር ግን በሞት አፋፍ ላይ የነበሩት አባቷ ያቀረቡትን ከልብ የመነጨ ልመና ችላ ማለት ስላልቻለች ጊዜ ሳታባክን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘችና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። በቅርቡ ሕይወቷን ለይሖዋ አምላክ በመወሰንና ራሷን መወሰኗን በውኃ ጥምቀት በማሳየት ከምሥክሮቹ አንዷ ሆነች።
በግሪክም ሆነ በሌሎቹ 230 አገሮች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ባለው ኃይል ይመካሉ። “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፣ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” የሚለው የኢየሱስ ትንቢት ፍጻሜ በሆነው ሥራ የሚካፈሉት በመንፈስ ቅዱስ ሙሉ ድጋፍ አማካይነት ነው።—ሥራ 1:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የግሪኩ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስቱ እንዲያገቡ ይፈቅዳል።