ትምክህት ሊጣልበት የሚገባውን አምላክ ማገልገል
ኪሞን ፕሮጋኪስ እንደተናገረው
ጊዜው 1955 ነው፤ የምሽቱ ብርድ ያቆራምዳል። የ18 ዓመቱ ልጃችን ዮርጎስ ከሚሠራበት ሱቅ ሳይመለስ በመቅረቱ ባለቤቴ ያኑላ እና እኔ መጨነቅ ጀመርን። ድንገት አንድ ፖሊስ በራችንን አንኳኳ። “ልጃችሁ በብስክሌት ወደቤቱ ሲመጣ መኪና ገጭቶት ሞቷል” አለን። ከዚያም ራሱን ወደፊት በማድረግ በሹክሹክታ “በድንገተኛ አደጋ ተገደለ ብለው ይነግሯችኋል፤ ግን እመኑኝ ሆነ ብለው ነው የገደሉት” አለን። እርሱን ለመግደል ያሴሩት የአካባቢው ቀሳውስትና አንዳንድ የሚሊሻ መሪዎች ነበሩ።
ግሪክ ከብጥብጥና ከሰቆቃ እያገገመች ባለችባቸው በእነዚያ ዓመታት የይሖዋ ምሥክር መሆን በጣም አደገኛ ነበር። ከ15 ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ውስጣቸው ስለነበርኩ የግሪክ ኦርቶዶክስም ሆነ ሚሊሻዎቹ ያላቸውን ሥልጣን አሳምሬ አውቅ ነበር። ከ40 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በቤተሰባችን ላይ ለተፈጸመው ለዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መንስኤ የሆኑት ነገሮች ምን እንደሆኑ ልንገራችሁ።
ያደግሁት በግሪክ ነው
1902 በግሪክ ውስጥ ከምትገኘው የካልኪስ ከተማ አቅራቢያ ባለች አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ከሚኖር ሀብታም ቤተሰብ ተወለድሁ። አባቴ የአካባቢውን ፖለቲካ የሚያራምድ ሰው ሲሆን መላው ቤተሰባችን የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከታይ ነበር። አብዛኞቹ የአገሬ ሰዎች መሃይማን በነበሩበት በዚያ ወቅት ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን እየተከታተልኩ በጉጉት ማንበብ ጀመርኩ።
በ20ኛው መቶ ዘመን መግቢያ ላይ በእጅጉ ተንሰራፍተው የነበሩት ድህነትና የፍትሕ መጓደል የተሻለ ሁኔታ ያለው ዓለም የሚመጣበትን ጊዜ እንድናፍቅ አደረጉኝ። ሃይማኖት በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን የአገሬን ሰዎች ሁኔታ ሊያሻሽል ይገባዋል ብዬ አሰብኩ። የመንደሩ እውቅ ሰዎች የነበረኝን ሃይማኖታዊ ዝንባሌ በማየት የአካባቢው ማኅበረሰብ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄስ እንድሆን አጩኝ። ይሁን እንጂ ብዙ ገዳማትን ሄጄ የጎበኘሁና ቀደም ብዬም ከጳጳሳት እንዲሁም ከገዳማት ኃላፊዎች ጋር ብዙ የተነጋገርኩ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ያለውን ኃላፊነት ለመቀበል ዝግጁ ወይም ፈቃደኛ አልነበርኩም።
በእርስ በርስ ጦርነቱ መሃል
ብዙ ዓመታት ካለፉ በኋላ በ1941 ሚያዝያ ወር ግሪክ በናዚ ቁጥጥር ሥር ወደቀች። በዚህ ጊዜ ግድያ፣ ረሃብ፣ የመብት ገፈፋና ይህ ነው የማይባል የሰው ልጅ ሰቆቃ የሚታይበት የታሪክ ምዕራፍ ጀመረ። ጠንካራ የነፃነት ንቅናቄ ቡድኖች ብቅ ብቅ ማለት ጀመሩ፤ እኔም ከናዚ ወራሪዎች ጋር ፍልሚያ ከገጠሙት የሽምቅ ተዋጊ ቡድኖች ወደ አንዱ ተቀላቀልሁ። በዚህም ምክንያት በተደጋጋሚ ጊዜ ቤቴ በእሳት ተቃጥሎብኛል፣ በጥይት ተመትቻለሁ እንዲሁም አዝመራዬ እንዲወድም ተደርጓል። በ1943 መጀመሪያ ላይ እኔና ቤተሰቤ ወጣ ገባ ወደሆኑት ተራሮች ከመሸሽ ሌላ አማራጭ አልነበረንም። በጥቅምት 1944 የጀርመን ወረራ እስኪያበቃ ድረስ እዚያው ቆየን።
ጀርመኖች ለቀው ከሄዱ በኋላ የውስጥ ፖለቲካዊ አለመጣጣምና የእርስ በርስ ግጭት ፈነዳ። እኔ የነበርኩበት የሽምቅ ተዋጊ ቡድን በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከብርቱዎቹ ተዋጊ ኃይሎች አንዱ ሆኖ ነበር። ስለ ፍትሕ፣ እኩልነትና አንድነት የሚናገሩት ኮሙኒስታዊ መርሖዎች ይስቡኝ የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ግን እውነታውን ሳየው ጨርሶ ግራ የሚያጋባ ሆነብኝ። በቡድኑ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ስለነበረኝ ሥልጣን ሰዎችን እንደሚያበላሽ በቅርብ ማየት ችያለሁ። በጣም ጥሩ የሚመስሉ መርሖዎችና ደንቦች ቢኖሩም እንኳ ራስ ወዳድነትና አለፍጽምና ቀና የሆኑትን የፖለቲካ ዕቅዶች ሳይቀር ያበላሻሉ።
በተለይ በጣም ያስደነገጠኝ ነገር የኦርቶዶክስ ቀሳውስት በግጭቱ ውስጥ የተለያዩ ወገኖችን ደግፈው የራሳቸውን የሃይማኖት አባላት ለመግደል የጦር መሣሪያ ማንሳታቸው ነበር! ‘እነዚህ ቀሳውስት “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ሲል ያስጠነቀቀውን ኢየሱስ ክርስቶስን እንወክላለን ብለው እንዴት ሊናገሩ ይችላሉ?’ ብዬ አሰብኩ።—ማቴዎስ 26:52
የእርስ በርስ ጦርነቱ በሚካሄድበት በ1946 በማዕከላዊ ግሪክ በምትገኘው የላሚያ ከተማ ውስጥ ተደብቄ ነበር። ልብሴ እላዬ ላይ አልቆ ስለነበር ማንነቴን በመሰወር በከተማው ውስጥ ወደ ሚገኝ አንድ ልብስ ሰፊ ዘንድ በመሄድ አዲስ ልብስ እንዲሰፋልኝ ለማድረግ ወሰንኩ። እዚያም እንደደረስኩ ሞቅ ያለ ክርክር ይዘው ስለነበር እኔም ገባሁበት፤ ውይይቱ ስለ ፖለቲካ ሳይሆን ቀደም ሲል እጓጓለት ስለ ነበረው ስለ ሃይማኖት ነበር። ሁኔታውን ይታዘቡ የነበሩት ሰዎች በጉዳዩ ላይ ያለኝን እውቀት ሲመለከቱ ከአንድ ‘የሃይማኖታዊ ትምህርት ፕሮፌሰር’ ጋር እንድነጋገር ሐሳብ አመጡ። ወዲያውም ሊጠሩት ሄዱ።
እውነተኛ ተስፋ ማግኘት
ከ“ፕሮፌሰሩ” ጋር ስንወያይ የእምነቴ መሠረት ምን እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም “ቅዱሳን አባቶችና ታላቁ ሲኖዶስ” ናቸው ብዬ መለስኩለት። ሐሳቤን ከመቃወም ይልቅ ትንሿን መጽሐፍ ቅዱሱን ገለጠና ማቴዎስ 23:9, 10 ላይ ያሉትን የኢየሱስ ቃላት እንዳነብ ጠየቀኝ፦ “አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም፦ አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና፦ ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ።”
በዚህ ጊዜ ዓይኔ ተገለጠ! ይህ ሰው የሚናገረው እውነት እንደሆነ ገባኝ። ከይሖዋ ምሥክሮች አንዱ መሆኑን ሲገልጽልኝ የማነባቸው ጽሑፎች እንዲሰጠኝ ጠየቅሁት። ስለ መጽሐፍ ቅዱሱ የራእይ መጽሐፍ የሚያብራራውን ብርሃን (የእንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ አመጣልኝና መጽሐፉን ይዤ ወደ ተሸሸግሁበት ስፍራ ተመለስኩ። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው አውሬ ለረጅም ዘመናት ምስጢር ሆኖብኝ ነበር፤ ይህን መጽሐፍ ሳነብ ግን በ20ኛው መቶ ዘመን የሚገኙ ፖለቲካዊ ድርጅቶችን እንደሚያመለክት ተገነዘብኩ። መጽሐፍ ቅዱስ ለጊዜያችንም ተግባራዊ ጥቅም እንዳለው እንዲሁም እኔም ላጠናውና ሕይወቴን በውስጡ ካለው እውነት ጋር ላስማማ እንደሚገባኝ እየተገነዘብኩ መጣሁ።
ተይዤ ወደ ወኅኒ ወረድሁ
ብዙም ሳይቆይ ወታደሮች ተደብቄበት ወደነበረው ሥፍራ ድንገት መጥተው ያዙኝ። ከዚያም በአንዲት ጨለማ ክፍል ውስጥ ተጣልኩ። እንደ ሽፍታ ስታደን ስለቆየሁ እገደላለሁ ብዬ ሰግቼ ነበር። በዚያች ትንሽ ክፍል ውስጥ እያለሁ በመጀመሪያ ያነጋገረኝ የይሖዋ ምሥክር እየመጣ ይጠይቀኝ ነበር። ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ላይ እንድታመን ያበረታታኝ ነበር፤ እኔም ያደረግሁት ይህንኑ ነው። ከዚያም የስድስት ወር እስር ተፈርዶብኝ በኢካሪያ ወደምትገኘው የአጂያን ደሴት ተላክሁ።
እዚያም እንደደረስሁ ኮሙኒስት ነኝ ብዬ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክር ነኝ ብዬ ራሴን አስተዋወቅሁ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተማሩ ሌሎች ሰዎችም ታስረው ስለነበር ፈልጌ አገኘኋቸውና መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን አንድ ላይ ማጥናት ጀመርን። ከቅዱሳን ጽሑፎች ብዙ እውቀት እንዳገኝና ትምክህት ሊጣልበት የሚገባውን አምላካችንን ይሖዋን ይበልጥ እንዳውቀው ረዱኝ።
በ1947 የእስራት ዘመኔ ሲያበቃ ወደ አቃቤ ሕጉ ቢሮ ተጠራሁ። በጠባዬ በጣም እንደተነካ ከገለጸልኝ በኋላ ከእንግዲህ እንደገና ከታሰርኩ ለእርሱ እንዳስታውቀው አድራሻውን ሰጠኝ። እኔ እስር ቤት ሳለሁ ቤተሰቦቼ ወደ አቴንስ ሄደው ስለነበር አቴንስ ስደርስ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መሰብሰብ ጀመርኩ፤ ወዲያውም ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት ተጠመቅሁ።
እምነት በማስለወጥ ወንጀል ተከሰስሁ
ግሪክ በ1938 እና 1939 በወጣው የሌሎችን እምነት ማስለወጥን በሚከለክለው ድንጋጌ መሠረት ለብዙ አሥርተ ዓመታት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ስደት ስታደርስ ቆይታለች። በዚህም ምክንያት ከ1938 እስከ 1992 ድረስ በግሪክ ውስጥ ምሥክሮቹ 19,147 ጊዜ የታሰሩ ሲሆን ፍርድ ቤቶቹም በድምሩ የ753 ዓመታት እስር በይነውባቸዋል፤ ከዚህም መካከል 593 ዓመታቱን በእስር ቤት አሳልፈዋል። እኔ ራሴ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኬ ምክንያት ከ40 ጊዜ በላይ የታሰርሁ ሲሆን በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ 27 ወራት አሳልፌአለሁ።
አንድ ጊዜ የታሰርሁት በቻልሲስ ለሚገኙ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቄስ በጻፍኩት ደብዳቤ ምክንያት ነው። በ1955 የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ክርስትያንደም ኦር ክርስትያኒቲ ዊች ዋን ኢዝ “ዘ ላይት ኦቭ ዘ ዎርልድ”? (የዓለም ብርሃን ሕዝበ ክርስትና ነች ወይስ ክርስትና?) የሚለውን ቡክሌት ለቀሳውስት እንዲያሰራጩ ማበረታቻ ተሰጥቶ ነበር። ደብዳቤ ከጻፍኩላቸው ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ቀሳውስት መካከል አንዱ እምነት በማስለወጥ ወንጀል ከሰሱኝ። ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ አንድ የይሖዋ ምሥክር የሆነ ነገረ ፈጅና የአካባቢው ጠበቃ እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ አምላክ መንግሥት የመስበክ ግዴታ እንዳለባቸው በመግለጽ ግሩም የመከላከያ ሐሳብ አቀረቡ።—ማቴዎስ 24:14
የፍርድ ቤቱ የመሐል ዳኛ አርኪማንድራይቱን (ከጳጳሱ ቀጥሎ ያለ የቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ማዕረግ ነው) እንዲህ ብለው ጠየቋቸው፦ “ደብዳቤውንና ቡክሌቱን አንብበውታል?”
“ፈጽሞ” ሲሉ በቁጣ መለሱ። “ገና ፖስታውን ከፍቼ ሳየው ነው ቀዳድጄ የጣልኩት!”
ከዚያም የመሐል ዳኛው “ታዲያ ይህ ሰው እምነቴን ሊያስለውጠኝ ነበር ሊሉ የቻሉት እንዴት ነው?” በማለት ጠየቃቸው።
ከዚያም ጠበቃችን ለሕዝብ ቤተ መጻሕፍት እንዲያገለግል በጣም ብዙ መጻሕፍት በእርዳታ የሰጡ ፕሮፌሰሮችንና ሌሎች ሰዎችን ምሳሌ ጠቀሰ። “እነዚህ ሰዎች የሌሎች ሰዎችን እምነት ለማስለወጥ ሞክረዋል ይላሉን?” ሲል ጠየቃቸው።
ይህ የሰውን እምነት ማስለወጥ ነው እንደማይባል ግልጽ ነው። “ከክስ ነጻ ሆኗል” የሚለውን ውሳኔ ስሰማ ይሖዋን አመሰገንሁ።
የልጄ ሞት
በአብዛኛው የኦርቶዶክስ ቀሳውስት በሚያደርጉት ቁስቆሳ ምክንያት ልጄ ዮርጎስም መግቢያ መውጫ አጥቶ ነበር። የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማወጅ በነበረው የወጣትነት ቅንዓት ምክንያት እርሱም ጭምር በርካታ ጊዜያት ታስሯል። በመጨረሻም ተቃዋሚዎቹ እርሱን ለመግደል ወሰኑ፤ የቀረነው የቤተሰቡ አባላትም መስበካችንን እንድናቆም የሚያስጠነቅቅ መልእክት ደረሰን።
ዮርጎስ መሞቱን ሊያረዳን ወደቤታችን የመጣው ፖሊስ ልጃችንን ለመግደል ያሴሩት የአካባቢው የግሪክ ኦርቶዶክስ ቀሳውስትና አንዳንድ የሚሊሻ መሪዎች መሆናቸውን ነገረን። በእነዚያ ቀውጢ ቀናት እንዲህ የመሰሉት “አደጋዎች” የተለመዱ ነበሩ። የልጃችን ሞት በእጅጉ ቢያሳዝነንም በስብከቱ ሥራ በትጋት መካፈላችንን ለመቀጠልና በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመታመን ያለንን ቁርጠኝነት ይበልጥ አጠናክሮልናል።
ሌሎች በይሖዋ እንዲታመኑ መርዳት
በ1960ዎቹ አጋማሽ ላይ ባለቤቴና ልጆቼ የክረምቱን ወራት የሚያሳልፉት ከአቴንስ 50 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው የስካላ ኦሮፖስ መንደር ዳርቻ ነበር። በወቅቱ በዚያ አካባቢ የሚኖር አንድም ምሥክር ስላልነበረ ለጎረቤቶቻችን መደበኛ ባልሆነ መንገድ መመሥከሩን ተያያዝነው። አንዳንዶቹ የአካባቢው ገበሬዎች ጥሩ ምላሽ ሰጡ። ሰዎቹ ቀን ቀን በእርሻቸው ውስጥ ሲሠሩ ስለሚውሉ የምናስጠናቸው ማታ ከመሸ በኋላ ነበር፤ ከእነርሱ መካከል በርካታዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
ላለፉት 15 ዓመታት ያደረግነውን ጥረት ይሖዋ እንዴት እንደባረከልን በመመልከት ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ በየሳምንቱ መጨረሻ ወደዚያ እንሄድ ነበር። እናስጠናቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል 30 የሚያክሉት ለጥምቀት በቅተዋል። በመጀመሪያ አንድ የጥናት ቡድን ተቋቋመና እኔ ስብሰባውን እንድመራ ተመደብኩ። ቆየት ብሎም ቡድኑ ጉባኤ ከመሆኑም በላይ ዛሬ በዚያ አካባቢ በሚገኘው የማላካሳ ጉባኤ ውስጥ ከአንድ መቶ የሚበልጡ ምሥክሮች ይገኛሉ። እኛ ከረዳናቸው ሰዎች መካከል አራቱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ገብተው ማየታችን አስደስቶናል።
ውድ የሆነ ቅርስ
እኔ ራሴን ለይሖዋ ከወሰንኩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ባለቤቴ በመንፈሳዊ እድገት በማድረግ ተጠመቀች። ስደት በነበረባቸው አስቸጋሪ ጊዜያት ጠንካራ እምነቷን ጠብቃና ፍጹም አቋሟን ሳታላላ ጸንታ ኖራለች። እኔ በተደጋጋሚ እስር ቤት በመግባቴ ምክንያት ስለደረሱባት ብዙ ውጣውረዶች አጉረምርማ አታውቅም።
ላለፉት በርካታ ዓመታት አንድ ላይ ሆነን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ስንመራ ቀላል በሆነውና የግለት ስሜት በሚንጸባረቅበት አቀራረቧ ብዙ ሰዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ረድታለች። በአሁኑ ጊዜም የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔት በየጊዜው የምታደርስላቸው በጣም ብዙ የመጽሔት ደንበኞች አሏት።
በሕይወት ያሉት ሦስቱ ልጆቻችንና ቤተሰቦቻቸው ማለትም ስድስት የልጅ ልጆችና አራት የልጅ ልጅ ልጆች በይሖዋ አገልግሎት እንዲቀጥሉ የውዷ የትዳር ጓደኛዬ ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። እነርሱም ባለቤቴና እኔ የተጋፈጥናቸው ዓይነት ስደትና መራራ ተቃውሞ ባይገጥማቸውም እንኳ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ በመታመን በመንገዱ መመላለሳቸውን ቀጥለዋል። ከውዱ ዮርጎስ ጋር እንደገና በትንሣኤ ስንገናኝ ለሁላችንም እንዴት ያለ ደስታ ይሆን!
በይሖዋ ለመታመን ቆርጫለሁ
በእነዚህ ሁሉ ዘመናት የይሖዋ መንፈስ በሕዝቦቹ ላይ ሲሠራ ተመልክቻለሁ። በመንፈስ የሚመራው ድርጅቱ በሰዎች ጥረት ላይ መታመን እንደማንችል እንድገነዘብ ረድቶኛል። ወደፊት የተሻለ ነገር ይመጣል የሚለው ተስፋቸው ሁሉ ከትልቅ ውሸት ፈቅ የማይል ከንቱ ወሬ ነው።—መዝሙር 146:3, 4
ዕድሜዬ ቢገፋና ከባድ የጤና ችግር ቢኖርብኝም እንኳ ዓይኖቼ እውን በሆነው የመንግሥቱ ተስፋ ላይ እንዳተኮሩ ናቸው። የሐሰት ሃይማኖት ተገዢ ሆኜና በፖለቲካዊ መንገድ የተሻለ ነገር ለማምጣት ስጣጣር ያሳለፍኳቸው ዓመታት ይቆጩኛል። ያሳለፍኩትን ሕይወት እንደገና መጀመር የምችል ብሆን ኖሮ ውሳኔዬ ትምክህት ሊጣልበት የሚገባውን አምላክ ይሖዋን ማገልገል እንደሚሆን አንዳችም አልጠራጠርም።
(ኪሞን ፕሮጋኪስ በቅርቡ በሞት አንቀላፍቷል። ምድራዊ ተስፋ የነበረው ወንድም ነው።)
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኪሞን ከባለቤቱ ያኑላ ጋር በቅርቡ የተነሣው ፎቶ