ለይሖዋ የሚገባውን መስጠት
ቲሞሊዮን ቫሲሊዮ እንደተናገረው
በአይቶኖሆሪ መንደር መጽሐፍ ቅዱስ በማስተማሬ ምክንያት ታስሬ ነበር። ፖሊሶቹ ጫማዬን አውልቀው ውስጥ እግሬን በዱላ ይደበድቡኝ ጀመር። ድብደባው እየቀጠለ ሲሄድ እግሬ ከመደንዘዙ የተነሳ የሚሰማኝ የሕመም ስሜት ጠፋ። በወቅቱ ግሪክ ውስጥ የተለመደ ነገር ለነበረው ለዚህ ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ያበቃኝን ሁኔታ ከመናገሬ በፊት እንዴት የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ እንደሆንኩ ልንገራችሁ።
በ1921 ከተወለድኩ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ቤተሰባችን በሰሜናዊ ግሪክ ወደምትገኘው የሮዶሊቮስ ከተማ ተዛወረ። በወጣትነቴ ዘመን ጋጠ ወጥ የሆነ አኗኗር እመራ ነበር። ገና የ11 ዓመት ልጅ ሳለሁ ሲጋራ ማጨስ ጀመርኩ። ከጊዜ በኋላ ከባድ ጠጪና ቁማርተኛ ሆንኩ፤ እንዲሁም በእያንዳንዱ ምሽት ማለት ይቻላል መረን ወደለቀቁ ጭፈራ ቤቶች እሄድ ነበር። የሙዚቃ ተሰጥዎ ስለነበረኝ በከተማው የነበረ የአንድ ባንድ አባል ሆንኩ። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ አብዛኞቹን የባንዱን የሙዚቃ መሣሪያዎች መጫወት ቻልኩ። የዚያኑ ያህል ደግሞ አንባቢና ፍትሕ ወዳድ ነበርኩ።
በ1940 መጀመሪያ ላይ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተፋፍሞ በነበረበት ወቅት የእኛ ባንድ በአንዲት ልጅ የቀብር ሥርዓት ላይ የሐዘን ማርሽ እንዲያሰማ ተጠራ። ዘመዶቿና ጓደኞችዋ ከልክ በላይ በሐዘን ተውጠው መቃብሩ አጠገብ ያለቅሱ ነበር። ይታይባቸው የነበረው ከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት በጣም ነካኝ። ‘የምንሞተው ለምንድን ነው? ከዚህ አጭር ከሆነው ሕልውናችን ሌላ ሕይወት ይኖራል? መልሶቹን ማግኘት የምችለው የት ነው?’ ስል ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ።
ከጥቂት ቀናት በኋላ በመጽሐፍ መደርደሪያዬ ላይ አንድ የአዲስ ኪዳን ቅጂ አየሁና አንስቼ ማንበብ ጀመርኩ። ማቴዎስ 24:7 ላይ የተገለጸው መጠነ ሰፊ ጦርነት የእርሱ መገኘት ምልክት ክፍል እንደሆነ የሚገልጸውን የኢየሱስን ቃል ሳነብ በጊዜያችን መፈጸም ያለበት ነገር እንደሆነ ተገነዘብኩ። በቀጣዮቹ ሳምንታት ይህን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂ ደጋግሜ አነበብኩት።
ከዚያም በታኅሣሥ 1940 በአቅራቢያዬ የነበረውን የአንዲት መበለት ቤተሰብ ለመጠየቅ ሄድኩ። ይህች መበለት አምስት ልጆች ነበሯት። በቤታቸው የላይኛው ክፍል ውስጥ ብዙ ቡክሌቶች ያገኘሁ ሲሆን ከመካከላቸውም አንዱ ኤ ዲዛይረብል ገቨርንመንት የሚል ርዕስ ያለውና በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ ነበር። ከዚያ ሳልወርድ ቡክሌቱን አንብቤ ጨረስኩ። ያነበብኩት ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻው ቀን’ በሚለው ጊዜ ውስጥ እንደምንኖርና ይሖዋ አምላክ በቅርቡ ይህን የነገሮች ሥርዓት ወደ ፍጻሜው አምጥቶ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም እንደሚተካው ሙሉ በሙሉ አምኜ እንድቀበል አደረገኝ።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
ከሁሉ በላይ ያስገረመኝ ነገር ታማኝ የሆኑ ሰዎች በምድራዊ ገነት ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩና በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በሚኖረው በዚያ አዲስ ዓለም ውስጥ ስቃይና ሞት እንደሚያከትም የሚናገረው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ ነበር። (መዝሙር 37:9-11, 29፤ ራእይ 21:3, 4) ገና አንብቤ ሳልጨርስ ለእነዚህ ነገሮች አምላክን በጸሎት ያመሰገንኩት ሲሆን እርሱ ያወጣቸውን ብቃቶችም እንዲያሳውቀኝ ጠየቅሁት። ይሖዋ በሙሉ ነፍስ ላመልከው የሚገባው አምላክ እንደሆነ ግልጽ ሆነልኝ።—ማቴዎስ 22:37
የተማርኩትን ነገር በሥራ ማዋል
ከዚያ ጊዜ አንስቶ ሲጋራ ማጨስ፣ መስከርና ቁማር መጫወት አቆምኩ። የመበለቲቱን አምስት ልጆች እንዲሁም ሦስት ታናናሽ ወንድሞችና እህቶቼን አንድ ላይ ሰብስቤ ከቡክሌቱ ያገኘሁትን ነገር ነገርኳቸው። ብዙም ሳንቆይ ሁላችንም ያወቅናትን ጥቂት ነገር ለሌሎች መንገር ጀመርን። አንድም የይሖዋ ምሥክር አግኝተን የማናውቅ ቢሆንም በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች አድርገው ይቆጥሩን ነበር። ከመጀመሪያው አንስቶ የተማርኳቸውን አስደናቂ ነገሮች ለሌሎች ለመንገር በየወሩ ከአንድ መቶ ሰዓት በላይ አሳልፍ ነበር።
በአካባቢው ከነበሩት የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄሶች አንዱ ስለእኛ ስሞታ ለማቅረብ ከንቲባው ፊት ቀረቡ። ሆኖም እኛ አልሰማንም እንጂ ከተወሰኑ ቀናት በፊት አንድ ወጣት የይሖዋ ምሥክር የጠፋ ፈረስ አግኝቶ ለባለቤቱ መልሶ ነበር። ይህ ወጣት እንዲህ ዓይነት የሐቀኝነት ተግባር በመፈጸሙ ምክንያት ከንቲባው ለይሖዋ ምሥክሮች አክብሮት ስላደረባቸው፣ ቄሱ የሚናገሩትን ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀሩ።
አንድ ቀን በጥቅምት 1941 ገደማ ገበያ ውስጥ እየመሰከርኩ ሳለ አንድ ሰው በአቅራቢያው በምትገኝ ከተማ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንደሚኖር ነገረኝ። ምሥክሩ ክሪስቶስ ትሪአንታፊሎ የሚባል የቀድሞ ፖሊስ ነበር። እርሱን ለማግኘት ስሄድ ከ1932 አንስቶ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ነገረኝ። በርከት ያሉ የቆዩ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ሲሰጠኝ በጣም ተደሰትኩ! እነዚህ ጽሑፎች መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ ረድተውኛል።
በ1943 በውኃ ጥምቀት ራሴን ለአምላክ መወሰኔን አሳየሁ። በዚያን ጊዜ ድራቪስኮስ፣ ፓሊዮኮሚና ማቭሮሎፎስ በሚባሉ ሦስት አጎራባች መንደሮች ውስጥ የአምላክ በገና (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ በመጠቀም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እመራ ነበር። ውሎ አድሮ በዚህ አካባቢ አራት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ሲቋቋሙ የማየት መብት አግኝቻለሁ።
ችግሮች ቢኖሩም በስብከቱ ሥራ መቀጠል
ግሪክ በ1944 ከጀርመን አገዛዝ ነፃ ከወጣች ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በአቴንስ ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር ግንኙነት መመሥረት ተቻለ። ቅርንጫፍ ቢሮው አንድም ሰው የመንግሥቱን መልእክት ባልሰማበት ክልል ውስጥ ምሥራቹን በማዳረስ እንድካፈል ጥሪ አቀረበልኝ። ወደዚያ ከሄድኩ በኋላ ለሦስት ወር ያህል በግብርና ሥራ የተሰማራሁ ሲሆን ቀሪውን የዓመቱን ጊዜ ደግሞ በአገልግሎት አሳለፍኩ።
በዚያ ዓመት እናቴ እንዲሁም የመጨረሻ ልጅዋን ማርያንቲን ሳይጨምር መበለቲቱና የቀሩት ልጆችዋ ሲጠመቁ በማየት ተባርኬአለሁ። ማርያንቲ የተጠመቀችው በ1943 ሲሆን በዚያው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ውድ ባለቤቴ ሆነች። ከሠላሳ ዓመት በኋላ ደግሞ በ1974 አባቴ የተጠመቀ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።
በ1945 መጀመሪያ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በስቴንስል የተባዛ የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ ከቅርንጫፍ ቢሮው ተላከልን። የመጽሔቱ ዋና ርዕስ “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚል ነበር። (ማቴዎስ 28:19 ዚ ኢምፋቲክ ዲያግሎት) ወዲያውኑ እኔና ማሪያንቲ ከስትሪሞን ወንዝ በስተ ምሥራቅ ርቀው የሚገኙትን ክልሎች ለመሸፈን ቤታችንን ለቅቀን ሄድን። ከጊዜ በኋላ አብረውን የሚያገለግሉ ሌሎች ምሥክሮችም መጡ።
አብዛኛውን ጊዜ ወደ አንድ መንደር ለመድረስ በባዶ እግራችን ገደላ ገደሎችንና ተራራዎችን አቋርጠን ብዙ ኪሎ ሜትሮች እንጓዝ ነበር። እንዲህ የምናደርገው ቅያሪ ጫማዎች ስላልነበሩን ጫማዎቻችን እንዳያረጁ ለመቆጠብ ብለን ነበር። ከ1946 እስከ 1949 በነበሩት ዓመታት ግሪክ ውስጥ የርስ በርስ ጦርነት ተፋፍሞ ስለነበር ከቦታ ቦታ መጓዝ በጣም አደገኛ ነበር። በአደባባይ የወደቁ አስከሬኖችን ማየት እንግዳ ነገር አልነበረም።
በነበሩት ችግሮች ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ በቅንዓት ማገልገላችንን ቀጠልን። ብዙ ጊዜ መዝሙራዊው እንዲህ ሲል የጻፈው ዓይነት ስሜት ነበረኝ:- “በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም፤ በትርህና ምርኩዝህ እነርሱ ያጽናኑኛል።” (መዝሙር 23:4) በእነዚህ ጊዜያት አብዛኛውን ጊዜ ለሳምንታት ከቤት ርቀን እንሄድ የነበረ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ በአገልግሎት በወር እስከ 250 ሰዓት አሳልፍ ነበር።
በአይቶኖሆሪ ያከናወንነው አገልግሎት
በ1946 ካገለገልንባቸው መንደሮች አንዱ ተራራ አናት ላይ የነበረው የአይቶኖሆሪ መንደር ይገኝበታል። እዚያ ያገኘነው ሰው መንደሩ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መስማት የሚፈልጉ ሁለት ሰዎች መኖራቸውን ነገረን። ይሁን እንጂ ሰውዬው ጎረቤቶቹን ስለፈራ እነዚህ ሰዎች ጋር ሊወስደን ፈቃደኛ አልሆነም። ያም ሆነ ይህ ቤታቸውን ፈልገን ስናገኘው ጥሩ አቀባበል አደረጉልን። እንዲያውም በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ሳሎናቸው በሰዎች ተሞላ! አንዳንዶቹ ዘመዶቻቸው ሌሎቹ ደግሞ የቅርብ ወዳጆቻቸው ነበሩ። ቁጭ ብለው በከፍተኛ ትኩረት ሲያዳምጡን በማየቴ በጣም ተገረምኩ። ብዙም ሳይቆይ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘት በጉጉት ይጠባበቁ እንደነበረና በጀርመን የግዛት ዘመን ግን በአካባቢው አንድም ምሥክር እንዳልነበረ ተረዳን። ፍላጎታቸውን የቀሰቀሰው ምንድን ነበር?
ሁለቱ የቤተሰብ ራሶች በአካባቢው በነበረው የኮሚኒስት ፓርቲ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የነበራቸው ሲሆን ለሕዝቡ የኮሚኒስት ጽንሰ ሐሳቦችን ያስተዋወቁትም እነርሱ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ግን በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጀውን ገቨርንመንት የተባለ መጽሐፍ አግኝተው በማንበባቸው ፍጹምና ጽድቅ የሰፈነበት መንግሥት የሚያስገኘው ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ አመኑ።
እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ እነዚህን ሰዎችና ጓደኞቻቸውን ቁጭ ብለን አስተማርናቸው። ለነበሯቸው ጥያቄዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ መልሶች ስንሰጣቸው በጣም ረኩ። ይሁን እንጂ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ መንደሩ ውስጥ የነበሩት ኮሚኒስቶች የቀድሞ መሪዎቻቸውን እምነት ያስቀየርኩት እኔ እንደሆንኩ ስላሰቡ ሊገድሉኝ አሴሩ። እንደ አጋጣሚ ሆኖ የመጀመሪያው ምሽት ላይ ከተገኙት መካከል መንደሩ ውስጥ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን የነገረኝ ሰው አንዱ ነበር። ውሎ አድሮ በመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እድገት አድርጎ በመጠመቅ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኗል።
ጭካኔ የተሞላበት ስደት
ከእነዚህ የቀድሞ ኮሚኒስቶች ጋር ከተገናኘን በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሁለት ፖሊሶች ስብሰባ እያካሄድን ወደነበረበት ቤት በኃይል ገቡ። አራታችን ላይ ጠመንጃ ደግነው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን። እዚያ ስንደርስ ከግሪክ ኦርቶዶክስ ቀሳውስት ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበረው መቶ አለቃ ሲዘልፈን ከቆየ በኋላ “ታዲያ ለእናንተ የሚገባው ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ።
ከኋላችን ቆመው የነበሩት ሌሎች ፖሊሶች “ደህና አድርገን እንቀጥቅጣቸው!” ሲሉ በአንድ ድምፅ ተስማሙ።
ይህ የሆነው ምሽት ላይ ነበር። ፖሊሶቹ ምድር ቤት ውስጥ ቆለፉብንና ቀጥሎ ወዳለው ቡና ቤት ሄዱ። ሞቅ ካላቸው በኋላ ተመልሰው መጥተው እኔን ወደ ላይኛው ክፍል ወሰዱኝ።
በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ስመለከት በማንኛውም ጊዜ ሊገድሉኝ እንደሚችሉ ተገነዘብኩ። ስለዚህ ማንኛውም ዓይነት ስቃይ ቢደርስብኝ መጽናት የሚያስችለኝን ጥንካሬ እንዲሰጠኝ ወደ አምላክ ጸለይኩ። የእንጨት ዱላ ይዘው መግቢያው ላይ እንደጠቀስኩት ውስጥ እግሬን ይደበድቡኝ ጀመር። ከዚያም እያገላበጡ ከደበደቡኝ በኋላ መልሰው ምድር ቤቱ ውስጥ ጣሉኝ። ቀጥሎ ሌላውን ወሰዱና ይደበድቡት ጀመር።
ይህን አጋጣሚ ሌሎቹ ሁለት ወጣት ምሥክሮች የሚጠብቃቸውን ፈተና እንዲቋቋሙ ለማዘጋጀት ተጠቀምኩበት። ፖሊሶቹ ግን በድጋሚ እኔን ወደ ላይኛው ክፍል ወሰዱኝ። ልብሶቼን አወላለቁና አምስቱም ጭንቅላቴን በቡትስ ጫማቸው እየረጋገጡ ለአንድ ሰዓት ያህል ደበደቡኝ። ከዚያም ከደረጃው ላይ ጣሉኝና ለ12 ሰዓታት ያህል ራሴን ስቼ ወደቅሁ።
መጨረሻ ላይ ስንለቀቅ መንደሩ ውስጥ የሚኖር የአንድ ቤተሰብ አባላት ሌሊቱን አሳደሩን፤ እንክብካቤም አደረጉልን። በሚቀጥለው ቀን ወደ ቤት ለመመለስ ጉዞ ጀመርን። ከድብደባው የተነሳ ሰውነታችን ዝሎና እጅግ ደክመን ስለነበር ለወትሮው ሁለት ሰዓት ብቻ የሚወስድብን የእግር ጉዞ ስምንት ሰዓት ፈጀብን። በድብደባው ሳቢያ ሰውነቴ በጣም አባብጦ ስለነበር ማሪያንቲ ልታውቀኝ አልቻለችም።
ተቃውሞ ቢኖርም እድገት ማድረግ
በ1949 የርስ በርስ ጦርነቱ ገና እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ወደ ተሰሎንቄ ተዛወርን። ከተማው ውስጥ ከነበሩት ከአራቱ ጉባኤዎች በአንዱ ረዳት አገልጋይ ሆኜ ተመደብኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ ጉባኤው ከፍተኛ ጭማሪ ስላሳየ ሌላ ጉባኤ ተቋቋመና የጉባኤው አገልጋይ ወይም ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆኜ ተሾምኩ። ከአንድ ዓመት በኋላ አዲሱ ጉባኤ በእጥፍ ገደማ ስላደገ አሁንም እንደገና ሌላ ጉባኤ ተመሠረተ!
በተሰሎንቄ የነበረው የይሖዋ ምሥክሮች እድገት ተቃዋሚዎችን አላስደሰታቸውም ነበር። አንድ ቀን በ1952 ከሥራ ወደ ቤት ስመለስ ቤታችን ሙሉ በሙሉ በእሳት ወድሞ አገኘሁት። ማሪያንቲ ለጥቂት ነበር ከሞት የተረፈችው። የዚያን ዕለት ምሽት ስብሰባ ላይ ቆሻሻ ልብስ ለብሰን የሄድንበትን ምክንያት ማስረዳት ነበረብን። ንብረታችን በሙሉ ወድሞ ነበር። ክርስቲያን ወንድሞቻችን ከፍተኛ ርኅራኄ ያሳዩን ሲሆን እርዳታም አድርገውልናል።
በ1961 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ፤ ይህም ወንድሞችን በመንፈሳዊ ለማጠናከር በየሳምንቱ አንድ ጉባኤ መጎብኘት ማለት ነበር። ከዚያ በኋላ በነበሩት 27 ዓመታት እኔና ማሪያንቲ በመቄዶንያ፣ ትሬስና ቴሳሊ የሚገኙትን ወረዳዎችና አውራጃዎች ጎብኝተናል። ምንም እንኳ ውዷ ባለቤቴ ማሪያንቲ ከ1948 አንስቶ ማየት እየተሳናት ቢሄድም በርካታ የእምነት ፈተናዎችን በጽናት በማሳለፍ አብራኝ በድፍረት አገልግላለች። እርሷም ብትሆን ብዙ ጊዜ ተይዛ ለምርመራ ቀርባለች እንዲሁም ታስራለች። ከዚያም ጤንነቷ እየተዳከመ ሄደና ለረጅም ጊዜ በካንሰር ከተሰቃየች በኋላ በ1988 ሞተች።
በዚያው ዓመት በተሰሎንቄ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። ይሖዋን በማገልገል ከ56 ዓመታት በላይ ካሳለፍኩ በኋላም አሁን በሁሉም የአገልግሎቱ ገጽታዎች በትጋት መሥራትና መሳተፍ እችላለሁ። አንዳንድ ጊዜ፣ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች በእያንዳንዱ ሳምንት እስከ 20 የሚደርሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መርቻለሁ።
ይሖዋ በሚያቋቁመው አዲስ ዓለም ውስጥ ለአንድ ሺህ ዓመት የሚዘልቅ ታላቅ የማስተማር መርሐ ግብር በጀመረበት ጊዜ ላይ እንደምንገኝ መገንዘብ ችያለሁ። ሆኖም ይህ ወደ ኋላ የምንልበት፣ የምናመነታበት ወይም የሥጋ ፍላጎቶቻችንን በማርካት የምንጠመድበት ወቅት እንዳልሆነ ይሰማኛል። በእርግጥም ይሖዋ በሙሉ ነፍስ ልናመልከውና ልናገለግለው የሚገባው አምላክ በመሆኑ ገና ከጅምሩ የገባሁትን ቃል እንድጠብቅ ስለረዳኝ አመሰግነዋለሁ።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የስብከት ሥራችን ታግዶ በነበረበት ወቅት ንግግር ስሰጥ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከማሪያንቲ ጋር