በይሖዋ ፍቅራዊ ጥበቃ ሥር ሆኖ ማገልገል
ላምፕሮስ ዙምፖስ እንደተናገረው
አንድ በጣም ወሳኝ ምርጫ ከፊቴ ተደቅኖ ነበር። ይህም ሀብታም አጎቴ በሰፊ የእርሻ ቦታው ሥራ አስኪያጅ እንድሆን ያቀረበልኝን ግብዣ በመቀበል የቤተሰቤን የገንዘብ ችግር መፍታት ወይም ይሖዋ አምላክን በሙሉ ጊዜ ማገልገል ነበር። ወደ መጨረሻ ውሳኔዬ እንድደርስ የገፋፉኝን ሁኔታዎች ልንገራችሁ።
ግሪክ ውስጥ በምትገኝ ቮሎስ በተባለች ከተማ በ1919 ተወለድኩ። አባቴ የወንድ ልብሶችን ይነግድ ስለነበር ጥሩ ኑሮ እንኖር ነበር። ሆኖም በ1920ዎቹ ማብቂያ ላይ በደረሰው የኢኮኖሚ ድቀት አባቴ ከሰረና ሱቁ ተዘጋ። በተስፋ መቁረጥ የተዋጠውን የአባቴን ፊት በተመለከትኩ ቁጥር አዝን ነበር።
ቤተሰቤ ለጥቂት ጊዜ በከባድ ድህነት ተቆራምዶ ነበር። በየቀኑ አንድ ሰዓት ቀደም ብዬ ከትምህርት ቤት እወጣና ለምግብ እደላ ሰልፍ እይዝ ነበር። ከድህነታችን በስተቀር ሰላም የሰፈነበት ቤተሰብ ነበረን። የሕክምና ዶክተር ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረኝም ቤተሰቤን በሕይወት ለማቆየት ስል በአሥራዎቹ ዕድሜዬ አጋማሽ ላይ ትምህርቴን አቋርጬ ሥራ ጀመርኩ።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጀርመኖችና ጣሊያኖች ግሪክን ከመያዛቸውም በተጨማሪ ከባድ ረሃብ ገብቶ ነበር። ብዙውን ጊዜ ጓደኞቼና የማውቃቸው ሰዎች በረሃብ የተነሳ መንገድ ላይ ሲያጣጥሩ እመለከት ነበር። ይህ መቼም ቢሆን የማልረሳው አሠቃቂ ትዕይንት ነው! አንድ ጊዜ ቤተሰባችን በግሪክ የዕለት ተዕለት ምግብ የሆነውን ዳቦ ሳይቀምስ 40 ቀናት አሳልፈዋል። እኔና ታላቅ ወንድሜ የቤተሰባችንን ሕይወት ለማትረፍ በአቅራቢያችን ወደሚገኙ መንደሮች ሄድንና ከጓደኞቻችንና ከዘመዶቻችን ዘንድ ድንች ይዘን መጣን።
መታመሜ በረከት አስገኘ
በ1944 መጀመሪያ ላይ ፕሉረሲ በተባለ የሳንባ በሽታ በጠና ታመምኩ። ሆስፒታል ውስጥ ሦስት ወር ባሳለፍኩበት ጊዜ አንድ የአጎቴ ልጅ ሁለት ቡክሌቶች አመጣልኝና “አንብባቸው፤ እንደምትወዳቸው እርግጠኛ ነኝ” አለኝ። አምላክ ማነው? እና ከለላ (በእንግሊዝኛ የሚገኙ) የተባሉ በመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተሙ ቡክሌቶች ነበሩ። ቡክሌቶቹን ካነበብኳቸው በኋላ ጽሑፎቹ የያዟቸውን ፍሬ ነገሮች አብረውኝ ለነበሩ በሽተኞች አካፈልኳቸው።
ከሆስፒታል እንደወጣሁ ቮሎስ ተብሎ በሚጠራ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መካፈል ጀመርኩ። ሆኖም ለአንድ ወር ያክል ተመላላሽ ታካሚ ስለነበርኩ ከቤት አልወጣም ነበር። ስለዚህ በቀን ከስድስት እስከ ስምንት ሰዓት ለሚያክል ጊዜ የድሮ መጠበቂያ ግንብ እትሞችንና በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጁ ሌሎች ጽሑፎችን አነብ ነበር። ይህም መንፈሳዊ እድገቴን በጣም አፋጠነው።
ለጥቂት ተረፍኩ
በ1944 አጋማሽ ላይ አንድ ቀን በቮሎስ ከተማ በአንድ መናፈሻ ውስጥ አግዳሚ ወንበር ላይ ተቀምጬ ነበር። የጀርመንን ወራሪ ጦር የሚደግፉ የግሪክ ወታደሮች ከየት መጡ ሳይባል ቦታውን ከበቡና እዚያ የነበርነውን በሙሉ ያዙን። የተያዝነው 24 የምናክል ሰዎች ስንሆን ታጅበን በአንድ የሲጋራ መጋዘን ውስጥ ወደሚገኝ የጌስታፖች ዋና ጽሕፈት ቤት ተወሰድን።
ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ አንድ ሰው የእኔንና መናፈሻው ውስጥ ሳነጋግረው የነበረውን ሰው ስም ሲጠራ ሰማሁ። አንድ ግሪካዊ የጦር አዛዥ አስጠሩንና ወታደሮቹ ይዘውን ሲሄዱ ዘመዴ የሆነ አንድ ሰው እንዳየንና የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን እንደነገራቸው ነገሩን። ባለ ሥልጣኑ ወደ ቤታችን መሄድ እንደምንችል ከነገሩን በኋላ ምናልባት እንደገና እንዳንያዝ ካርዳቸውን ሰጡን።
ተይዘው ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ወረራውን በሚቃወሙ የግሪክ ተዋጊዎች ለተገደሉ ሁለት የጀርመን ወታደሮች በቀል እንደተረሸኑ በማግስቱ ሰማን። ለጥቂት ከሞት ከመትረፌም በተጨማሪ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ለማየት ችያለሁ።
በ1944 ማብቂያ ላይ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን በውኃ ጥምቀት አሳየሁ። በሚቀጥለው በጋ ምሥክሮቹ በተራራ ላይ በሚገኝ ስክሊትሮ በሚባል ጉባኤ እንድካፈል ዝግጅት ያደረጉልኝ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ያገገምኩት እዚያ ነበር። የጀርመን ወረራ ካበቃ በኋላ የጀመረው የግሪክ የእርስ በርስ ጦርነት በዚህ ጊዜ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ነበር። የነበርኩበት መንደር ለሽምቅ ተዋጊዎች እንደ ማዕከል ሆኖ ያገለግል ነበር። የአካባቢው ቄስና አንድ ሌላ ተንኮለኛ ሰው ለመንግሥት ይሰልላል ብለው ከሰሱኝና እዚያው በተቋቋመ የሽምቅ ተዋጊዎች ወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀርቤ መስቀለኛ ጥያቄ ቀረበልኝ።
ጉዳያችን በሚታይበት በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይ የአካባቢው የሽምቅ ተዋጊዎች መሪ ተገኝቶ ነበር። እዚያ መንደር የተቀመጥኩበትን ምክንያትና ክርስቲያን እንደመሆኔ መጠን በእርስ በርስ ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ ገለልተኛ እንደሆንኩ ተናግሬ ስጨርስ መሪው “ይህንን ግለሰብ አንድ ሰው ጫፉን ቢነካው አልለቀውም!” በማለት ለሰዎቹ ነገሯቸው።
ከጊዜ በኋላ ከአካላዊ ይልቅ በመንፈሳዊ ጤንነቴ በርትቼ የትውልድ ከተማዬ ወደሆነችው ቮሎስ ተመለስኩ።
መንፈሳዊ እድገት
ወዲያውኑ በጉባኤ ውስጥ የሒሳብ አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። በቀሳውስት ገፋፊነት በሚቀርበው ሃይማኖት የማስቀየር ክስ የተነሳ ብዙ ጊዜ መያዝን ጨምሮ የእርስ በርሱ ጦርነት ያስከተላቸው ችግሮች ቢኖሩም በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈል ለእኔም ሆነ ለተቀሩት የጉባኤያችን አባላት ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶልናል።
በ1947 መግቢያ ላይ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ጎበኘን። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንዲህ ያለ ጉብኝት ሲደረግልን ይህ የመጀመሪያው ነበር። በዚህ ጊዜ ቮሎስ የሚገኘው ታዳጊው ጉባኤያችን ለሁለት የተከፈለ ሲሆን እኔ የአንደኛው ጉባኤ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች ሆንኩ። መንግሥታዊ ያልሆኑ ወታደሮችና ብሔርተኛ ድርጅቶች በሕዝቡ መካከል ፍርሃት ይነዙ ነበር። ቀሳውስት በአጋጣሚው ተጠቀሙበት። ኮሚኒስቶች ወይም የግራ ክንፍ ደጋፊ ናቸው የሚል የሐሰት ወሬ በማሰራጨት ባለሥልጣኖች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እንዲነሱ አድርገዋል።
የተያዝኩባቸውና የታሰርኩባቸው ጊዜያት
በ1947 አሥር ጊዜ ያክል የተያዝኩ ሲሆን ሦስት ጊዜ ለፍርድ ቀርቤአለሁ። በሦስቱም ጊዜያት በነፃ ተለቀቅሁ። በ1948 የፀደይ ወራት የሰው ሃይማኖት በማስቀየር ተከሰስኩና አራት ወር እንድታሰር ተፈረደብኝ። ቅጣቱን ቮሎስ እስር ቤት ውስጥ አሳለፍኩ። በዚሁ ጊዜ በጉባኤያችን ውስጥ የነበሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በእጥፍ የጨመሩ ሲሆን ወንድሞች ልባቸው በደስታ ተሞልቶ ነበር።
ጥቅምት 1948 ጉባኤያችን ውስጥ በኃላፊነት ከሚሠሩ ስድስት ወንድሞች ጋር ስብሰባ እያደረግን ሳለ አምስት ፖሊሶች በኃይል ተጠቅመው ወደ ቤት በመግባት መሣሪያ ደቅነውብን ይዘውን ሄዱ። የተያዝንበትን ምክንያት ሳይነግሩን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከወሰዱን በኋላ ገረፉን። ቀድሞ ቦክሰኛ የነበረ አንድ ፖሊስ ፊቴ ላይ በቡጢ መታኝ። ከዚያም በአንዲት ትንሽ የእስረኛ ክፍል ውስጥ ከተቱን።
በኋላም የእስር ቤቱ አዛዥ ወደ ቢሮው አስጠራኝ። በሩን ከፍቼ ስገባ የቀለም ብልቃጥ ወረወረብኝ፤ ብልቃጡ ስቶኝ ግድግዳው ላይ ተከሰከሰ። ይህንን ያደረገው እኔን ለማስፈራራት ነበር። ከዚያም ቁራጭ ወረቀትና ብዕር ሰጠኝና “ቮሎስ ውስጥ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች በጠቅላላ ስም ዝርዝራቸውን ጽፈሕ ነገ ጠዋት እንድታመጣልኝ። ይህን ባታደርግ ምን እንደሚከተልህ ታውቃለህ!” ብሎ አዘዘኝ።
ምንም መልስ አልሰጠሁም፤ ሆኖም ወደ እስር ቤት ክፍሉ ስመለስ ከወንድሞች ጋር ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። የራሴን ስም ብቻ ጻፍኩና እስከምጠራ ድረስ እጠባበቅ ጀመር። ነገር ግን የአዛዡ ድምፅ ጠፋ። ለካስ ሌሊቱን የጠላት ጦር መጥቶ ኖሮ አዛዡ ወታደሮቹን ይዞ ዘምቷል። በተፈጠረው ግጭት በከባድ ሁኔታ ስለቆሰለ አንድ እግሩ የግድ መቆረጥ ነበረበት። በመጨረሻም ጉዳያችን በፍርድ ቤት መታየት ጀመረና ሕጋዊ ያልሆነ ስብሰባ አድርገዋል የሚል ክስ ቀረበብን። ሰባታችንም አምስት ዓመት እንድንታሰር ተፈረደብን።
እስር ቤቱ ውስጥ በሚደረገው የእሑድ ቅዳሴ ላይ አልገኝም ስላልኩ ከሰው ወደተገለለ እስር ቤት ላኩኝ። በሦስተኛው ቀን ከእስር ቤቱ አዛዥ ጋር እንድነጋገር ጠየቅኩ። የእስር ቤቱን አዛዥ “ይቅርታ አድርግልኝና ለእምነቱ ሲል አምስት ዓመት በእስር ቤት ለማሳለፍ ፈቃደኛ የሆነን ሰው መቅጣት ሞኝነት ይመስላል” አልኩት። በነገሩ ላይ ከልብ ካሰበበት በኋላ፦ “ከነገ ጀምሮ እዚህ እኔ ቢሮ ውስጥ አጠገቤ ትሠራለህ” አለኝ።
በመጨረሻ እስር ቤቱ ውስጥ የአንድ ዶክተር ረዳት ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። በዚህ የተነሳ ስለ ጤና አጠባበቅ ብዙ ትምህርት የቀሰምኩ ሲሆን ይህም በኋለኞቹ ዓመታት በጣም ጠቅሞኛል። እስር ቤት ሳለሁ ለመመስከር የሚያስችሉ ብዙ አጋጣሚዎች የነበሩኝ ሲሆን ሦስት ሰዎች ቀና ምላሽ ሰጥተው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል።
አራት ለሚያክሉ ዓመታት እስር ቤት ውስጥ ካሳለፍኩ በኋላ በመጨረሻ በ1952 በአመክሮ ተፈታሁ። ከጊዜ በኋላ በገለልተኝነት አቋም የተነሳ ኮሪንዝ ውስጥ ፍርድ ቤት ቀረብኩ። (ኢሳይያስ 2:4) እዚያም በወታደራዊ እስር ቤት ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ከማሳለፌም በተጨማሪ በተደጋጋሚ ጊዜያት ተደብድቤአለሁ። አንዳንድ ወታደራዊ አዛዦች “ልብህን በጩቤ ቆራርጬ አወጣዋለሁ፣” ወይም “በአንድ አፍታ በጥይት እገደላለሁ ብለህ እንዳታስብ፤ ተሠቃይተህ እንድትሞት ነው የማደርገው” በማለት ማስፈራሪያዎችን ይፈጥሩ ነበር።
ለየት ያለ ፈተና
ብዙም ሳይቆይ ወደ ቤቴ ተመለስኩና ግማሽ ቀን እየሠራሁ ከቮሎስ ጉባኤ ጋር ማገልገል ጀመርኩ። አንድ ቀን አቴንስ ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ አንድ ደብዳቤ ደረሰኝ። ደብዳቤው ለሁለት ሳምንት ሥልጠና ወስጄ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ጉባኤዎችን መጎብኘት እንድጀምር የሚጠይቅ ነበር። በዚሁ ጊዜ ልጅ የሌለውና የሰፊ እርሻ ቦታ ባለቤት የሆነው አጎቴ ጠቅላላ ንብረቱን እንዳንቀሳቅስለት ጠየቀኝ። ቤተሰቤ አሁንም በድህነት ይማቅቁ ስለነበር ይህ ሥራ ያለባቸውን የኢኮኖሚ ችግር ይቀረፍላቸው ነበር።
ላቀረበልኝ ግብዣ ምስጋናዬን ሄጄ ገለጽኩለት፤ ሆኖም ልዩ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ለመቀጠል እንደወሰንኩ ነገርኩት። በዚህ ጊዜ ከመቀመጫው ተነስቶ ኮስተር ብሎ አየኝና ወዲያው ክፍሉን ትቶ ወጣ። ቤተሰቤን ለተወሰኑ ወራት ሊደግፍልኝ የሚችል ከፍተኛ የገንዘብ ስጦታ ይዞ መጣ። “ወስደህ እንደፈለግክ አድርገው” አለኝ። በዚያን ጊዜ የተሰማኝን ስሜት አሁንም እንኳ መግለጽ ያስቸግረኛል። ይሖዋ ‘ያደረግኸው ትክክለኛ ምርጫ ነው። እኔ ከአንተ ጋር ነኝ’ ብሎ ሲናገር የሰማሁት ያህል ነበር።
ቤተሰቦቼ በእቅዴ ከተስማሙ በኋላ ታኅሣሥ 1953 ወደ አቴንስ ሄድኩ። ምንም እንኳ የይሖዋ ምሥክር የሆነችው እናቴ ብቻ ብትሆንም ሌሎቹ የቤተሰቤ አባላትም ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዬን አይቃወሙም ነበር። አቴንስ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ስደርስ ሌላ አስደሳች ነገር ጠበቀኝ። አባቴ የጡረታ መብቱን ለማስከበር ያደረገው የሁለት ዓመት ጥረት ያን ዕለት እንደተሳካለት የሚገልጽ ከእህቴ የተላከ ቴሌግራም ነበር። ከዚህ የበለጠ ምን እፈልጋለሁ? በይሖዋ አገልግሎት ከፍ ብለው ለመብረር የተዘጋጁ ክንፎች እንዳሉኝ ሆኖ ተሰማኝ!
በጥንቃቄ መሥራት
በወረዳ ሥራ ባሳለፍኩት የመጀመሪያ ዓመት በጣም መጠንቀቅ ነበረብኝ። ምክንያቱም የይሖዋ ምሥክሮች ከሃይማኖታዊና ከፖለቲካዊ መሪዎች ከፍተኛ ስደት ይደርስባቸው ነበር። በተለይ በትንንሽ ከተማዎችና መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞችን ለመጎብኘት ጨለማን ሽፋን በማድረግ ብዙ ሰዓታት እጓዝ ነበር። ወንድሞች ሊያዙ እንደሚችሉ እያወቁ እቤት ውስጥ ተሰብስበው በትዕግሥት ይጠባበቁኝ ነበር። እነዚያ ጉብኝቶች ሁላችንንም ምንኛ እርስ በርስ እንድንበረታታ አድርገውናል!—ሮሜ 1:11, 12
አንዳንድ ጊዜ እንዳይነቃብኝ ለማድረግ ሌላ ሰው መስዬ እንቀሳቀስ ነበር። አንድ ጊዜ አንድ ኬላ አልፌ መንፈሳዊ እረኝነት በጣም የሚያስፈልጋቸው ወንድሞች ጋር ለመድረስ እንደ እረኛ ለብሼ ነበር። በ1955 እኔና አንድ ወንድም ከፖሊሶች ትኩረት ለማምለጥ የነጭ ሽንኩርት ነጋዴዎች ለመምሰል ሞክረን ነበር። ምድባችን አነስተኛ በሆነችው ኦርጎስ ኦሬስቲኮን ውስጥ የሚኖሩ አገልግሎት ያቆሙ ወንድሞችን ማግኘት ነበር።
ከተማዋ ውስጥ በሚገኘው የገበያ ቦታ ሽንኩርታችንን ዘረጋን። ሆኖም አካባቢውን የሚቆጣጠር አንድ ወጣት ፖሊስ ጥርጣሬ ስላደረበት በአጠገባችን ባለፈ ቁጥር ትኩር ብሎ ይመለከተን ነበር። በመጨረሻም “የነጭ ሽንኩርት ነጋዴ አትመስልም” አለኝ። በዚህ ጊዜ ሦስት ወጣት ሴቶች መጡና ነጭ ሽንኩርት መግዛት እንደሚፈልጉ ነገሩኝ። ወደ ነጭ ሽንኩርቱ በማመልከት “ይህ ወጣት ፖሊስ ነጭ ሽንኩርት ስለሚበላ ምን ያህል ጠንካራና መልከ ቀና እንደሆነ ተመልከቱ!” አልኳቸው። ሴቶቹ ፖሊሱን አይተው ሳቁ። እርሱም ሳቀና ከአጠገባችን ሄደ።
እርሱ ሲሄድ በአጋጣሚው ተጠቅሜ መንፈሳዊ ወንድሞቻችን ልብስ ወደሚሰፉበት ሱቅ ሄድኩ። አውቄ የገነጠልኩትን የጃኬት ቁልፍ እንዲሰፋልኝ ከመካከላቸው አንዱን ጠየቅኩት። እየሰፋ እያለ ወደ ጆሮው ጠጋ በማለት ድምፄን ዝቅ አድርጌ “ከቅርንጫፍ ቢሮ እናንተን ለማየት ነው የመጣሁት” አልኩት። ወንድሞች ለብዙ ዓመታት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት አድርገው ስለማያውቁ መጀመሪያ ላይ ፈርተው ነበር። የቻልኩትን ያክል ካበረታታኋቸው በኋላ በከተማው መካነ መቃብር ተገናኝተን ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ ያዝን። ጉብኝቱ የሚያበረታታ ስለነበር ወንድሞች በክርስቲያናዊ አገልግሎት እንደገና ቀናተኞች መሆናቸው ያስደስታል።
ታማኝ የትዳር ጓደኛ አገኘሁ
የተጓዥነት ሥራ ከጀመርኩ ከሦስት ዓመት በኋላ ማለትም በ1956 ለስብከቱ ሥራ ከፍተኛ ፍቅር ካላትና መላ ሕይወቷን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለማሳለፍ ከምትፈልግ ኒኪ ከተባለች አንዲት ወጣት ክርስቲያን ጋር ተገናኘሁ። ተዋደድንና ሰኔ 1957 ተጋባን። በግሪክ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ተስፋፍቶ በነበረበት በዚያ ወቅት የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለኒኪ ይከብዳት ይሆናል ብዬ ሰግቼ ነበር። በይሖዋ እርዳታ ሥራውን የተዋጣችው ከመሆኑም በላይ በግሪክ ውስጥ በወረዳ ሥራ ከባለቤቷ ጋር በመተባበር ረገድ የመጀመሪያዋ ሴት ሆናለች።
በተጓዥነት ሥራ ለአሥር ዓመታት አብረን ያገለገልን ሲሆን ግሪክ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹን ጉባኤዎች ጎብኝተናል። ብዙ ጊዜ አንድ ጉባኤ ለመድረስ ሌላ ሰው መስለንና ጓዛችንን ተሸክመን ጨለማን ተገን በማድረግ ለብዙ ሰዓታት እንጓዝ ነበር። ምንም እንኳ ብዙውን ጊዜ ከባድ ተቃውሞ ቢያጋጥመንም የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር የሚያሳየውን አስደናቂ እድገት ስንመለከት እንደሰት ነበር።
የቤቴል አገልግሎት
ጥር 1967 እኔና ኒኪ ቤቴል ተብሎ በሚጠራው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንድናገለግል ተጋበዝን። ግብዣው ዱብ ዕዳ ቢሆንብንም ይሖዋ ነገሮችን እንደሚያመቻች በመተማመን ግብዣውን ተቀበልን። በዚህ አገልግሎት ብዙ ጊዜያት ካሳለፍን በኋላ በዚህ የቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ ማዕከል ማገልገል ምንኛ ታላቅ መብት እንደሆነ ተገንዝበናል።
ቤቴል ከገባን ከሦስት ወር በኋላ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ስለጨበጠ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በድብቅ መከናወን ቀጠለ። በትንንሽ ቡድኖች መሰብሰብ፣ ትልልቅ ስብሰባዎችን በጫካ ውስጥ ማድረግ፣ በጥበብ መስበክ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በድብቅ ማተምና ማሰራጨት ቀጠልን። ከዓመታት በፊት በዚህ መልኩ ሥራችንን እናከናውን ስለነበረ እነዚህን ሁኔታዎች መላመዱ አስቸጋሪ አልነበረም። ምንም እንኳ የተለያዩ እገዳዎች ቢጣሉብንም በ1967 ከ11,000 በታች የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በ1974 ከ17,000 በላይ ሆነዋል።
እኔና ኒኪ 30 ከሚያክሉ ዓመታት የቤቴል አገልግሎት በኋላ የጤንነታችን ሁኔታና ዕድሜአችን አቅማችንን ውስን ቢያደርገውም እንኳ አሁንም መንፈሳዊ በረከቶች እያገኘን ነው። ከአሥር ለሚበልጡ ዓመታት የኖርነው አቴንስ ውስጥ ካርታሊ ጎዳና በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ነበር። በ1979 ከአቴንስ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኝ ማሩሲ ተብሎ በሚጠራ ቦታ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ተመረቀ። ሆኖም ከ1991 ጀምሮ ከአቴንስ በስተ ሰሜን 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ኤሊኦና በሚባል ቦታ በተሠራው ሰፊ በሆነ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ መኖር ጀመርን። እዚህም በቤቴል ክሊኒክ ውስጥ እያገለገልኩ ሲሆን የእስር ቤቱ ዶክተር ረዳት በመሆን ያገኘሁት ሥልጠና በጣም ጠቅሞኛል።
ከአራት አሥርተ ዓመታት በላይ ባሳለፍኩት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት “ከአንተ ጋር ይዋጋሉ፣ ነገር ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና ድል አይነሡህም፣ ይላል እግዚአብሔር” በማለት ይሖዋ የገባውን ቃል እውነተኝነት እንደ ኤርምያስ ተገንዝቤአለሁ። (ኤርምያስ 1:19) አዎን፣ እኔና ኒኪ በይሖዋ በረከት የተሞላ ጽዋ ጠጥተናል። ይሖዋ ዘወትር በሚያሳየን ፍቅራዊ አሳቢነትና ይገባናል በማንለው ደግነት ሁልጊዜ ደስ ይለናል።
በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግባቸው እንዲያደርጉ እመክራቸዋለሁ። በዚህ መንገድ ይሖዋ ‘የሰማይን መስኮት እከፍትላችኋለሁ፣ በረከት አትረፍርፌ አፈስላችኋለሁ’ በማለት የሰጠውን ተስፋ የሚፈጽም መሆኑንና አለመሆኑን ሊፈትኑት ይችላሉ። (ሚልክያስ 3:10) እናንተ ወጣቶች፣ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ከታመናችሁ ሁላችሁንም እንደሚባርካቸሁ ከራሴ ተሞክሮ አረጋግጥላችኋለሁ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ላምፕሮስ ዙምፖስ እና ሚስቱ ኒኪ