“በወርቅ ፈንታ አልማዝ አገኘሁ”
ሚካሊስ ካሚናሪስ እንደተናገረው
ወርቅ ፍለጋ በሄድኩበት በደቡብ አፍሪካ አምስት ዓመት ከተቀመጥኩ በኋላ ከወርቅ የበለጠ ውድ ነገር ይዤ ወደ አገሬ ተመለስኩ። ለሌሎች ላካፍለው ስለምፈልገው አሁን ስላለኝ ሀብት እስቲ ልንገራችሁ።
በአይኦኒያ ባሕር ሴፋሎኒያ በምትባል የግሪክ ደሴት በ1904 ተወለድኩ። ገና በልጅነቴ ሁለቱንም ወላጆቼን በሞት አጣሁ፤ ስለዚህ ያለ ወላጅ አደኩ። እርዳታ ስለሚያስፈልገኝ ብዙ ጊዜ ወደ አምላክ እጸልይ ነበር። ምንም እንኳ አዘውታሪ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚ የነበርኩ ብሆንም ለመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ መሃይም ነበርኩ። ምንም መጽናኛ አላገኘሁም።
በ1929 የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ወሰንኩ። ጠፍ የሆነችውን የተወለድኩባትን ደሴት ትቼ በመርከብ ተሳፍሬ በእንግሊዝ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ ጉዞ ቀጠልኩ። ከ17 ቀናት የባሕር ላይ ቆይታ በኋላ ደቡብ አፍሪካ ኬፕ ታውን ደረስኩ፤ እዚያም እንደደረስኩ አንድ የአገሬ ሰው ሥራ ቀጠረኝ። ይሁን እንጂ ቁሳዊ ሀብት መጽናናትን አልሰጠኝም።
የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር
በደቡብ አፍሪካ ለሁለት ዓመት ያክል እንደተቀመጥኩ አንድ የይሖዋ ምሥክር ከምሠራበት ቦታ መጥቶ ካነጋገረኝ በኋላ በግሪክኛ ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አበረከተልኝ። ከሰጠኝ ጽሑፎች መካከል ሙታን የት ናቸው? እና ጭቆና የሚያበቃው መቼ ነው? የተባሉት (የእንግሊዝኛ) ቡክሌቶች ይገኙበታል። እንዴት በጉጉት እንዳነበብኳቸው ትዝ ይለኛል፤ ሌላው ቀርቶ ጥቅሶቹን በሙሉ በቃሌ ይዤያቸው ነበር። አንድ ቀን ለአንድ የሥራ ባልደረባዬ እንዲህ አልኩት:- “ለብዙ ዓመታት ስፈልገው የነበረውን ነገር አገኘሁ። ወደ አፍሪካ የመጣሁት ወርቅ ፍለጋ ነበር፤ ነገር ግን በወርቅ ፈንታ አልማዝ አገኘሁ።”
አምላክ ይሖዋ የሚባል የግል ስም እንዳለው፣ መንግሥቱ በሰማይ እንደተቋቋመችና በዚህ የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንደምንኖር ሳውቅ በጣም ነው የተደሰትኩት። (መዝሙር 83:18 NW፤ ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:3-12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ራእይ 12:7-12) የይሖዋ መንግሥት ለሁሉም የሰው ዘሮች መጨረሻ የሌላቸው በረከቶች እንደምታመጣ ማወቅ እንዴት ያስደስታል! ውድ የሆነው እውነት በዓለም ዙሪያ የሚሰበክ መሆኑ ሌላው በጣም የማረከኝ ነገር ነበር።— ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 11:6-9፤ ማቴዎስ 24:14፤ ራእይ 21:3, 4
ወዲያው በኬፕ ታውን የሚገኘውን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ፈልጌ ካገኘሁ በኋላ ተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አገኘሁ። በተለይ ደግሞ የግሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ በማግኘቴ በጣም ተደሰትኩ። ያነበብኩት ነገር ለሌላ ሰው እንድመሰክር ገፋፋኝ። በተወለድኩባት ከተማ በሊክሱሪኦን ለሚገኙ ዘመዶቼ፣ ለጓደኞቼና ለማውቃቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በመላክ ስለ እምነቴ መመስከር ጀመርኩ። አንድ ሰው ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለገ ሕይወቱን ለአምላክ መወሰን እንዳለበት ቀስ በቀስ ከጥናቴ ተረዳሁ። ስለዚህ ወዲያው በጸሎት ራሴን ለአምላክ ወሰንኩ።
አንድ ቀን በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኘሁ፤ ሆኖም እንግሊዝኛ ቋንቋ ስለማላውቅ ምን እንደተባለ አንዲትም ቃል አልተረዳሁም። በፖርት ኤልዛቤት ብዙ ግሪኮች ይኖሩ እንደነበረ ስሰማ ጓዜን ጠቅልዬ ወደዚያ ተዛወርኩ፤ ሆኖም ግሪክኛ የሚናገር አንድም የይሖዋ ምሥክር አላገኘሁም። ስለዚህ የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ እንድሆን ወደ ግሪክ ለመመለስ ወሰንኩ። ‘የፈለገው ነገር ይምጣ እንጂ ወደ ግሪክ እመለሳለሁ’ እያልኩ ከራሴ ጋር ስነጋገር ትዝ ይለኛል።
በግሪክ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት
በ1934 የጸደይ ወር ዱሊኦ በምትባል የኢጣሊያ የንግድ መርከብ ተሳፍሬ ጉዞ ጀመርኩ። ፈረንሳይ ማርሴል ደርሼ በዚያ የአሥር ቀን ቆይታ ካደረግኩ በኋላ ፓትሪስ በምትባል የመንገደኞች መርከብ ተሳፍሬ ወደ ግሪክ ሄድኩ። ባሕር ላይ እንዳለን መርከቧ የቴክኒክ ችግር ገጠማት፤ ከዚያም ሌሊት ላይ ሕይወት አድን ጀልባዎች እንዲዘረጉ ትእዛዝ ተሰጠ። የፈለገው ነገር ይምጣ እንጂ ወደ ግሪክ እመለሳለሁ ያልኩት ትዝ አለኝ። የሆነ ሆኖ አንዲት የኢጣሊያ ጎታች ጀልባ ደረሰችና እየጎተተች ኔፕልስ ኢጣሊያ አደረሰችን። በመጨረሻም ፒሬቭስ ግሪክ ደረስን።
ከዚያ በቀጥታ ወደ አቴንስ አመራሁ፤ እዚያ እንደደረስኩም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ቅርንጫፍ ቢሮ ጎበኘሁ። የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች የሆነው አታናሲዮስ ካራናሲዮስ ሲያነጋግረኝ የሙሉ ጊዜ የስብከት ምድብ እንዲሰጠኝ ጠየቅኩ። በሚቀጥለው ቀን በደቡባዊ የግሪክ ክፍል ወደሚገኘው ወደ ፔሎፖኒሰስ ጉዞ ቀጠልኩ። ይህ አውራጃ እንዳለ የእኔ የአገልግሎት ክልል ሆኖ ተሰጠኝ!
ከከተማ ወደ ከተማ፣ ከመንደር ወደ መንደር፣ ከእርሻ ወደ እርሻ እና ከገጠር ወደ ገጠር በመሄድ በጋለ ስሜት የስብከቱን ሥራ ተያያዝኩት። ብዙም ሳይቆይ ማይክል ትሪያንዳፊሎፑሎስ የሚባል የአገልግሎት ጓደኛ አገኘሁ፤ በ1935 በጋ ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከጀመርኩ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ አጠመቀኝ! ምንም ዓይነት የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት ስለሌለ የትም ቦታ ስንሄድ የምንጓዘው በእግራችን ነበር። ትልቁ ችግራችን የቄሶች ተቃውሞ ነበር፤ እንዳንሰብክ ለመከልከል የማያደርጉት ነገር አልነበረም። ከዚህ የተነሳ ብዙ ሰዎች ከመሬት ተነስተው ይጠሉን ጀመር። እንቅፋቶች ቢኖሩም የምሥክርነቱ ሥራ ተከናውኗል፤ የይሖዋም ስም ከዳር እስከ ዳር ታውጅዋል።
ተቃውሞዎችን በጽናት መቋቋም
አንድ ቀን ጠዋት በተራራማው የአርካዲያ አውራጃ እየሰበኩ ሳለ ማጉሊያና ወደሚባል አንድ መንደር ደረስኩ። ለአንድ ሰዓት ያክል ከመሰከርኩ በኋላ የቤተ ክርስቲያን ደወል ሲደወል ሰማሁ። የደወሉት ለእኔ እንደሆነ ወዲያው ገባኝ! በአንድ የግሪክ ኦርቶዶክስ የደብር ኃላፊ ቄስ የሚመራ ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። ቶሎ ብዬ የአገልግሎት ቦርሳዬን ዘጋሁና በልቤ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። የደብሩ ኃላፊ ቄስ አንድ መንጋ ውሪ አስከትሎ በቀጥታ ወደ እኔ መጣ። “ይሄ ነው! ይሄ ነው!” እያለ ይጮኽ ጀመር።
ልጆቹ ዙሪያዬን ክብብ አደረጉኝ፤ ከዚያም ቄሱ ወደ እኔ ራመድ በማለት ‘ሊያረክሰኝ ስለሚችል’ በእጄ ልነካው አልፈልግም እያለ በቦርጩ ይገፋኝ ጀመር። “በሉት! በሉት!” ብሎ ጮኸ። ሆኖም በዚህ ጊዜ አንድ ፖሊስ ድንገት ደርሶ ሁላችንንም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዞን ሄደ። ቄሱ አድማ ቀስቅሰሃል ተብሎ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ 300 ድራክማ መቀጮ እና የፍርድ ቤቱን ወጪዎች እንዲከፍል ተወሰነበት። እኔ በነፃ ተለቀቅሁ።
አዲስ ወደሆነ አካባቢ ስንደርስ ተለቅ ያለውን ከተማ ማረፊያችን በማድረግ ከዚያ ተነስተን ወደ አራት ሰዓት የሚያክል በእግራችን በመጓዝ ሌሎች የአገልግሎት ክልሎችን በሙሉ ሸፍነን እንመለሳለን። ይህም ማለት ገና ጎህ ሳይቀድ እንወጣና አንድ ወይም ሁለት መንደር ሸፍነን ማታ ጨለማ ሲሆን ወደ ማረፊያችን እንመለሳለን። በአካባቢው ያሉትን መንደሮች ከሸፈንን በኋላ ባረፍንበት ከተማ እንመሰክራለን። ከዚያም ወደ ሌላ አካባቢ እንሄዳለን። ቄሶች ሕዝቡን በእኛ ላይ ይቀሰቅሱብን ስለነበረ ብዙ ጊዜ ተይዘን ታስረናል። በማዕከላዊ ግሪክ በሚገኘው በፓርናሱስ አካባቢ ለበርካታ ወራት በፖሊስ ስፈለግ ነበር። ሆኖም ሊይዙኝ አልቻሉም።
አንድ ቀን እኔና ወንድም ትሪያንዳፊሎፑሎስ በቦኢኦሺያ አውራጃ በሚገኘው በሙሪኪ መንደር እየሰበክን ነበርን። መንደሩን ለሁለት ከፈልነውና እኔ ወጣት ስለሆንኩ አቀበታማውን አካባቢ መሥራት ጀመርኩ። ከዚያም ከበታቼ ድንገት ጩኸት ሰማሁ። ወደታች እየሮጥኩ ‘ወንድም ትሪያንዳፊሎፑሎስን እየደበደቡት ነው’ ብዬ አሰብኩ። የመንደሩ ሰዎች በአካባቢው ባለ አንድ ቡና ቤት ተሰብስበዋል፤ ቄሱ ልክ እንደተቆጣ በሬ ወዲያና ወዲህ ይንጎራደዳል። “እነዚህ ሰዎች ‘የእባቡ ዘር’ እያሉ ይጠሩናል” ሲል ጮኸ።
ቄሱ ከዘራው እስኪሰበር ድረስ ወንድም ትሪያንዳፊሎፑሎስን እራሱ ላይ ስለፈነከተው ደሙ በፊቱ ላይ ይንዠቀዠቅ ነበር። ደሙን ከጠራረግኩለት በኋላ ከዚያ አካባቢ ሄድን። ቴቤዝ የምትባለው ከተማ እስክንደርስ ድረስ ሦስት ሰዓት በእግራችን ተጓዝን። እዚያም እንደደረስን አንድ ክሊኒክ ሄደን ቁስሉ ታሸገለት። ሁኔታውን ለፖሊስ ሪፖርት አደረግንና ክስ መሠረትን። ሆኖም ቄሱ ከፖሊሶቹ ጋር ግንኙነት ስለነበረው በመጨረሻ በነፃ ተለቀቀ።
ሉከስ በምትባለው ከተማ እያገለገልን ሳለን ከአካባቢው የፖለቲካ መሪዎች የአንዱ ተከታይ “በቁጥጥር ሥር” አውሎን በመንደሩ ውስጥ ወደሚገኘው ቡና ቤት ይዞን ሄደ፤ እዚያ ስንደርስ ሁሉም እየተነሳ ይሰድበን፣ ያላግጥብን ጀመር። የፖለቲካ መሪውና የእሱ ባለሥልጣኖች እየተንጎራደዱ ቡጢያቸውን እያሳዩ ያስፈራሩንና ይደነፉብን ጀመር። ሁሉም ሰክረው ነበር። ስድባቸውና ድንፋታቸው ከእኩለ ቀን ጀምሮ ጀምበር እስክትጠልቅ ድረስ ቀጠለ፤ እኛ ግን ምንም ሳንረበሽ ጥፋተኞች አለመሆናችንን በፈገግታ መግለጻችንን በመቀጠል በልባችን ይሖዋ አምላክ እንዲረዳን ጸለይን።
ምሽቱ ለዓይን ያዝ ሲያደርግ ሁለት ፖሊሶች ደረሱልን። ከዚያም ወደ ፖሊስ ጣቢያ ይዘውን ከሄዱ በኋላ በጥሩ ሁኔታ ተንከባከቡን። የፖለቲካ መሪውም አድራጎቱን ትክክለኛ ለማስመሰል በሚቀጥለው ቀን መጥቶ በግሪክ ንጉሥ ላይ ፕሮፓጋንዳ ይነዛሉ ሲል ከሰሰን። ስለዚህ ፖሊሱ በሁለት ሰዎች አሳጅቦ ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ላሚያ ከተማ ላከን። ከዚያም ለሰባት ቀን በማረፊያ ቤት ከቆየን በኋላ ለፍርድ እንድንቀርብ እጃችን በካቴና ታስሮ ወደ ላሪሳ ከተማ ተወሰድን።
በላሪሳ የሚገኙ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ቀደም ብሎ ተነግሮአቸው ስለነበረ መምጣታችንን ይጠባበቁ ነበር። ያሳዩን ፍቅር ለዘቦቹ ትልቅ ምስክርነት ነበር። ቀደም ሲል ሌተናል ኮለኔል የነበረውና አሁን የይሖዋ ምሥክር የሆነው የእኛ ጠበቃ በከተማው በጣም የታወቀ ሰው ነበር። በፍርድ ቤቱ ፊት ቀርቦ ስለ እኛ በመከራከር የተመሠረተብን ክስ ሐሰት መሆኑን አረጋገጠ፤ እኛም በነፃ ተለቀቅን።
የይሖዋ ምሥክሮች ስብከት በአጠቃላይ ሲታይ ስኬታማ መሆኑ ተቃውሞው ይበልጥ እንዲባባስ አደረገ። በ1938 እና 1939 የአንድን ሰው ሃይማኖት ማስቀየርን የሚከለክል ሕግ ወጣ፤ ከዚህም የተነሳ እኔና ማይክል ከዚህ ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበናል። ከዚያ በኋላ በሥራችን ላይ ብዙ ትኩረት እንዳንስብ ለየብቻ ሆነን እንድናገለግል ቅርንጫፍ ቢሮው ምክር ሰጠን። የአገልግሎት ጓደኛ ሳይኖረኝ ብቻዬን ማገልገል ከብዶኝ ነበር። የሆነ ሆኖ በይሖዋ በመታመን የአቲካን፣ የቦኤሺያን፣ የቲዮቲስን፣ የኢቦኦያን፣ የኤቶሊያን፣ የአካርናኒያ፣ የዩርታኒያን እና የፔሎፖኒሶስን አውራጃዎች በእግሬ እየተጓዝኩ ሸፈንኩ።
በዚህ ወቅት በጣም የረዱኝ መዝሙራዊው በይሖዋ ስለመታመን የተናገራቸው ምርጥ ቃላት ናቸው። “በአንተ ከጥፋት እድናለሁና፣ በአምላኬም ቅጥሩን እዘልላለሁ። ኃይልን የሚያስታጥቀኝ መንገዴንም የሚያቃና፣ እግሮቼን እንደ ብሖር እግሮች የሚያበረታ በኮረብቶችም የሚያቆመኝ እግዚአብሔር ነው።”— መዝሙር 18:29, 32, 33
በ1940 ኢጣሊያ በግሪክ ላይ ጦርነት አወጀች፤ ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የጀርመን ጦር አገሪቱን ወረረ። በአገሪቱ ወታደራዊ ሕግ ታወጀ፤ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር መጻሕፍት ታገዱ። እነዚያ ወቅቶች በግሪክ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች በጣም አስቸጋሪ ነበሩ፤ ሆኖም በሚያስደንቅ ሁኔታ ቁጥራቸው ጨምሮ በ1940 ቁጥራቸው 178 የነበሩት ምሥክሮች በ1945 በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ 1,770 ደርሷል!
በቤቴል ማገልገል
በ1945 አቴንስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተጠራሁ። ቤቴል “የአምላክ ቤት” ማለት ሲሆን በዚያን ወቅት ይገኝ የነበረው በሎምባርዱ ጎዳና በአንድ የኪራይ ቤት ውስጥ ነበር። አንደኛ ፎቅ ላይ ቢሮዎች የሚገኙ ሲሆን ምድር ቤት ደግሞ የኅትመት ሥራ ይከናወን ነበር። በኅትመት ክፍሉ አንዲት አነስተኛ የማተሚያ ማሽንና አንድ የወረቀት መቁረጫ ነበረ። የኅትመቱን ሥራ የሚያከናውኑት ሁለት ወንድሞች ብቻ ነበሩ፤ ሆኖም ወዲያው ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች ከቤታቸው እየተመላለሱ ሥራውን ማገዝ ጀመሩ።
ብሩክሊን ኒው ዮርክ ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ጋር ተቋርጦ የነበረው ግንኙነት በ1945 እንደገና ተጀመረ፤ በዚያው ዓመት እንደገና መጠበቂያ ግንብ በግሪክኛ ቋንቋ በቋሚነት ማተም ጀመርን። ከዚያም በ1947 ቅርንጫፍ ቢሮአችንን ወደ 16 ቴንዱ ጎዳና አዛወርነው፤ የኅትመት ሥራው ግን በዚያው በሎምባርዱ ጎዳና ቀጠለ። ከጊዜ በኋላ በሎምባርዱ ጎዳና ይገኝ የነበረው ማተሚያ አምስት ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው ንብረትነቱ የአንድ የይሖዋ ምሥክር ወደሆነ አንድ ፋብሪካ ተዛወረ። ለተወሰነ ጊዜ ሦስቱም ቦታ እየሄድን እንሠራ ነበር።
በቴንዱ ጎዳና ከሚገኘው መኖሪያችን ሌሊት ተነስተን ወደ ማተሚያ ቤቱ እንሄድ የነበረው ትዝ ይለኛል። እስከ ቀኑ 7 ሰዓት በዚያ ከሠራሁ በኋላ ያተምንባቸውን ወረቀቶች ለማድረስ ወደ ሎምባርዱ ጎዳና እሄዳለሁ። እነዚህ ወረቀቶች እዚያ ከተወሰዱ በኋላ በመጽሔት መልክ ታጥፈው ይሰፉና በእጅ ይከረከማሉ። ከዚያም ተዘጋጅተው ያለቁትን መጽሔቶች ፖስታ ቤት ካደረስን በኋላ ሦስተኛ ፎቅ ይዘን ወጥተን መጽሔቶቹን በዓይነት በዓይነታቸው በመለየትና በፖስታዎቹ ላይ ቴምብር በመለጠፍ የፖስታ ቤቱን ሠራተኞች እንረዳቸዋለን።
በ1954 በግሪክ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከ4,000 በላይ አድጎ ስለነበረ ለሥራው ሰፋ ያለ ሕንፃ አስፈልጎ ነበር። ስለዚህ በአቴንስ ካርታሊ ጎዳና ወደሚገኝ አንድ ባለ ሦስት ፎቅ አዲስ ቤቴል ተዛወርን። በ1958 በማድቤት ያለውን ሥራ በበላይነት እንድቆጣጠር ተጠየቅሁ፤ እስከ 1983 ድረስ በዚሁ ኃላፊነት አገልግያለሁ። ይህ በእንዲህ እንዳለ በይሖዋ አገልግሎት ታማኝ ረዳት የሆነችልኝን ኤሊፍቴሪያን በ1959 አገባሁ።
ተቃውሞን እንደገና በጽናት መቋቋም
በ1967 ወታደራዊ ጁንታ ሥልጣን ያዘ፤ በስብከት ሥራችን ላይ በድጋሚ እገዳ ተጣለ። ሆኖም በሥራችን ላይ የሚጣሉ እገዳዎችን በመወጣት ረገድ የቀድሞው ተሞክሮ ስላለን ወዲያው ነገሮችን አስተካከልንንና በተሳካ ሁኔታ በድብቅ መሥራታችንን ቀጠልን።
ስብሰባዎቻችንን በግል መኖሪያ ቤቶች የምናደርግ ሲሆን ከበር ወደ በር በምናገለግልበት ጊዜ በጣም እንጠነቀቅ ነበር። ያም ሆኖ ግን ወንድሞቻችን በየጊዜው ይያዙ ነበር፤ ከዚህም የተነሳ በርካታ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ነበሩ። ጠበቆቻችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ የፍርድ ጉዳዮችን ለመከታተል ሁልጊዜ ከላይ ታች እንደተሯሯጡ ነበር። ተቃውሞ ቢኖርም አብዛኞቹ ምሥክሮች በተለይም ቅዳሜና እሁድ በስብከቱ ሥራ መካፈላቸውን አላቋረጡም ነበር።
ቅዳሜ ወይም እሁድ የቀኑን አገልግሎታችንን ካጠናቀቅን በኋላ ሁልጊዜ ከመካከላችን የቀረ መኖር አለመኖሩን እናረጋግጥ ነበር። ብዙውን ጊዜ ሳይመለሱ የቀሩት በአካባቢው በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው ይገኛሉ። ስለዚህ ብርድ ልብስና ምግብ እንወስድላቸውና እናበረታታቸው ነበር። ከዚያም ለጠበቆቻችን ከነገርናቸው በኋላ ለታሰሩት ወንድሞች ለመሟገት ሰኞ ዕለት ወደ አቃቤ ሕጉ ዘንድ ይሄዳሉ። ይህን ሁሉ መከራ የምንቀበለው ለእውነት ስንል ስለነበረ ሁኔታውን በጸጋ ተቀብለነዋል!
በእገዳው ወቅት በቤቴል ይካሄድ የነበረው የኅትመት ሥራ ተዘግቶ ነበር። ስለዚህ ከአቴንስ ወጣ ብላ የምትገኘው እኔና ኤሊፍቴሪያ የምንኖርባት ቤት የኅትመት ሥራ የሚከናወንባት ቦታ ሆና ነበር። ኤሊፍቴሪያ ግዙፍ በሆነ አንድ የጽሕፈት መኪና የመጠበቂያ ግንብ ቅጂዎችን ታይፕ ታደርግ ነበር። ከሥር ካርቦን አድርጋ በአንድ ጊዜ አሥር ወረቀቶችን ካስገባች በኋላ ፊደሎቹ በወረቀቶቹ ላይ እንዲወጡ የጽሕፈት መኪናውን በኃይል ትመታ ነበር። እኔ ደግሞ የተለያዩትን ገጾች ከሰበሰብኩ በኋላ አንድ ላይ አድርጌ በወረቀት ማያያዣ ሽቦ እሰፋቸዋለሁ። ሁልጊዜ ማታ ማታ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ እንሠራ ነበር። ከእኛ በታች ባለው ፎቅ ውስጥ የሚኖር አንድ ፖሊስ ይኖር የነበረ ቢሆንም ለምን ፈጽሞ ጠርጥሮን እንደማያውቅ እስከ ዛሬ ድረስ ይገርመናል።
የማያቋርጥ እድገት በማየት መደሰት
በ1974 በግሪክ የዲሞክራሲ ሥርዓት ተመለሰ፤ የስብከት ሥራችንም በድጋሚ ይበልጥ በግልጽ መካሄድ ቀጠለ። ሆኖም በእነዚያ ሰባት የእገዳ ዓመታት ከ6,000 በላይ አዳዲስ ምሥክሮችን በማግኘት አስደናቂ ጭማሪ በማድረግ ጠቅላላው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከ17,000 በላይ ሆኗል።
በተጨማሪም የተለመደውን የኅትመት ሥራችንን በዚያው በቅርንጫፍ ቢሮው ግቢ ውስጥ ቀጠልን። ከዚህም የተነሳ በካርቴሊ መንገድ የሚገኘው የቤቴል ሕንፃ ለሥራው የማይመጥን ሆነ። ስለዚህ ከአቴንስ ትንሽ ወጣ ብሎ በሚገኘው በማሩሲ 1 ሄክታር መሬት ተገዛ። 27 መኝታ ክፍሎች፣ አንድ ፋብሪካ፣ ቢሮዎችንና ሌሎች ነገሮችን ያካተተ ቤቴል ተሠራ። ይህም በጥቅምት 1979 ተመረቀ።
ይህም ሆኖ ከዚህ የሰፋ ቦታ አስፈልጎናል። ስለዚህ ከአቴንስ በስተሰሜን 60 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ 22 ሄክታር መሬት ተገዛ። አካባቢው ኢሊዮና የሚባል ሲሆን ለዓይን የሚማርኩ ተራሮችና ለምለም ሸለቆዎች የሚታዩበት አንድ የኮረብታ ጥግ ነው። በዚህ ቦታ እያንዳንዳቸው ለስምንት ሰዎች የሚበቃ መኖሪያ ያላቸው 22 ቤቶችን ያቀፈ ከበፊቱ በጣም ትልቅ የሆነ ቤቴል ተሠርቶ ሚያዝያ 1991 ተመረቀ።
ከ60 ዓመታት በላይ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ካሳለፍኩ በኋላ አሁንም ጤንነቴ ጥሩ ነው። ‘በሽምግልናዬም እየለመለምኩ በመሆኔ’ ደስተኛ ነኝ። (መዝሙር 92:14) በተለይ የእውነተኛ አምላኪዎቹን ቁጥር ከፍተኛ ጭማሪ በሕይወት ቆይቼ በዓይኔ እንዳይ ስላደረገኝ ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ። ነቢዩ ኢሳይያስ “በሮችሽም ሁል ጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጥግና የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ያመጡ ዘንድ ሌሊትና ቀን አይዘጉም” በማለት እንዲህ ዓይነት ጭማሪ እንደሚኖር አስቀድሞ ተናግሯል።— ኢሳይያስ 60:11
ከሁሉም ብሔር በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ይሖዋ ድርጅት ሲጎርፉና ከታላቁ መከራ በሕይወት ተርፈው ወደ አዲሱ ዓለም እንዴት መግባት እንደሚችሉ ሲማሩ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው! (2 ጴጥሮስ 3:13) የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ይህ ዓለም ሊሰጥ ከሚችለው ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ውድ ሆኖ አግኝቼዋለህ ብዬ ከልቤ መናገር እችላለሁ። አዎን፣ ወርቅ ሳይሆን ሕይወቴን ከመጠን በላይ ያበለጸጉልኝን መንፈሳዊ አልማዞች አግኝቼአለሁ።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ሚካሊስ እና ኤሊፍቴሪያ ካሚናሪስ
(በስተቀኝ) በሎምባርዱ ጎዳና የሚገኘው ማተሚያ ቤት