የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w05 4/1 ገጽ 20-24
  • ቸል የተባለው የሙት ልጅ አፍቃሪ አባት አገኘ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ቸል የተባለው የሙት ልጅ አፍቃሪ አባት አገኘ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ስደተኛ፣ ከዚያም ወላጅ አልባ ሆንኩ
  • ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ አገኘሁ
  • የሚደግፈኝ ቤተሰብ አገኘሁ
  • ተቃውሞው ያልተጠበቀ ውጤት አስገኘ
  • በአሥር ዓመት ውስጥ ስምንት እስር ቤቶች አየሁ
  • በክርስቲያን ወንድሞች እርዳታ መንፈሳዊ እድገት አደረግሁ
  • ከ50 ለሚበልጡ ዓመታት ወደ ተለያዩ ቦታዎች ‘መሻገር’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ዋናው ዓላማዬ ይሖዋን ማስደሰት ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • በይሖዋ ፍቅራዊ ጥበቃ ሥር ሆኖ ማገልገል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ለይሖዋ የሚገባውን መስጠት ቲሞሊዮን ቫሲሊዮ እንደተናገረው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
w05 4/1 ገጽ 20-24

የሕይወት ታሪክ

ቸል የተባለው የሙት ልጅ አፍቃሪ አባት አገኘ

ዲሚትሪስ ሲዲሮፖሎስ እንደተናገረው

መኮንኑ ጠመንጃውን ወደፊቴ ገፋ አድርጎ “ይህንን መሣሪያ አንሳና ተኩስ” ሲል አንባረቀብኝ። እኔም በትሕትና ፈቃደኛ አለመሆኔን ገለጽኩ። በዚህን ጊዜ ሌሎቹ ወታደሮች እስኪደናገጡ ድረስ መኮንኑ በጆሮ ግንዴ ላይ የተኩስ እሩምታ ይለቅብኝ ጀመር። በወቅቱ መሞቴ የማይቀር መስሎ ተሰምቶኝ የነበረ ቢሆንም በሕይወት ለመትረፍ በቃሁ። ሆኖም ሕይወቴ አደጋ ላይ ሲወድቅ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም።

ወላጆቼ ቀጰዶቅያ፣ ቱርክ ከምትገኘው ካይዘሪ አቅራቢያ የሚኖሩ የአናሳ ጎሳ አባላት ነበሩ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በዚህ አካባቢ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ወደ ክርስትና ተለውጠው እንደነበር ይገመታል። (የሐዋርያት ሥራ 2:9) ይሁን እንጂ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሁኔታዎች በድንገት ተለወጡ።

ስደተኛ፣ ከዚያም ወላጅ አልባ ሆንኩ

ከተወለድኩ ከጥቂት ወራት በኋላ ማለትም በ1922 ተቀስቅሶ በነበረው የጎሳ ግጭት ምክንያት ወላጆቼ ወደ ግሪክ ተሰደዱ። በሁኔታው በመደናገጣቸው የወራት ዕድሜ ከነበረኝ ከእኔ በቀር የያዙት አንዳች ነገር አልነበረም። ከብዙ መከራና ስቃይ በኋላ ጉስቁልቁል ብለው በሰሜናዊ ግሪክ ባለችው ድራማ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው ካሪ የተባለች መንደር ደረሱ።

ትንሹ ወንድሜ ከተወለደ በኋላ ማለትም የአራት ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ሞተ። በዚያ ወቅት ገና የ27 ዓመት ሰው የነበረ ቢሆንም ያሳለፋቸው የስቃይና የመከራ ጊዜያት በቁም ጨርሰውት ነበር። በእጦት የተንገላታችው እናቴም ብትሆን ብዙም ሳትቆይ ሞተች። እኔና ወንድሜ በሕይወት ለመቆየት የሚያስፈልጉ ነገሮች አልነበሩንም። በመሆኑም ከአንዱ ጓለማውታ ወደ ሌላው እየተቀየርን የተወሰነ ጊዜ አሳለፍን፤ በመጨረሻም በ12 ዓመቴ በተሰሎንቄ ይገኝ ወደነበረው ጓለማውታ የተዛወርኩ ሲሆን በዚያም የመካኒክነት ሙያ ሥልጠና ጀመርኩ።

ያደግኩት የቤተሰብ ፍቅርና መተሳሰብ ባልነበረባቸው የሕፃናት ማሳደጊያዎች ውስጥ በመሆኑ ‘አንዳንድ ሰዎች ይህን ያህል ስቃይና ግፍ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር። በተጨማሪም ‘አምላክ ይህን የመሰለ አሳዛኝ ሁኔታ ሲደርስ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምን ይሆን?’ በማለት ራሴን እጠይቅ ነበር። ክፍል ውስጥ በሚሰጡን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ላይ አምላክ ሁሉን ቻይ እንደሆነ ቢነገረንም መከራ የመጣውና ይህን ያህል የተንሰራፋው ለምን እንደሆነ በቅጡ የሚያስረዳን አልነበረም። ሰዎች እውነተኛዋ ሃይማኖት የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ብቻ እንደሆነች በተደጋጋሚ ሲናገሩ እሰማ ነበር። ይሁን እንጂ “ኦርቶዶክስ እውነተኛ ሃይማኖት ከሆነ ለምን ሁሉም ሰው ኦርቶዶክስ አልሆነም?” ለሚለው ጥያቄዬ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት አልቻልኩም።

ያም ሆኖ መምህራችን ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ አክብሮት የነበረው ሲሆን ቅዱስ መጽሐፍ እንደሆነም አጥብቆ ይነግረን ነበር። የጓለማውታው ኃላፊም ተመሳሳይ አመለካከት ነበረው፤ ሆኖም ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይታወቅም በሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ አይካፈልም ነበር። ምክንያቱን ስጠይቅ በአንድ ወቅት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠና እንደነበር ሰማሁ፤ እኔ ግን ስለዚህ ሃይማኖት ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም።

አሥራ ሰባት ዓመት ሲሆነኝ በተሰሎንቄ በሚገኘው ጓለማውታ ጀምሬው የነበረውን ትምህርት አጠናቀቅሁ። በወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በመጀመሩ ግሪክ በናዚዎች ቁጥጥር ሥር ወደቀች። በረሃብ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ሬሳ በየመንገዱ ወድቆ ይታይ ነበር። እኔም ሕይወቴን ለማትረፍ ስል በጣም አነስተኛ በሆነ ክፍያ የቀን ሠራተኛ ሆኜ ለመቀጠር ወደ ገጠር ሄድኩ።

ከመጽሐፍ ቅዱስ መልስ አገኘሁ

በሚያዝያ 1945 ወደ ተሰሎንቄ እንደተመለስኩ በተለያዩ ጓለማውታዎች ውስጥ አብሮኝ ይኖር የነበረ የአንድ የልጅነት ጓደኛዬ እህት ልትጠይቀኝ መጣች። ፓስካሊያ የምትባለው ይህች ልጅ ወንድሟ መጥፋቱን ከነገረችኝ በኋላ ያለበትን ቦታ አውቅ እንደሆን ጠየቀችኝ። በጭውውታችን መሃል የይሖዋ ምሥክር እንደሆነችና አምላክ ለሰው ልጆች እንደሚያስብ ነገረችኝ።

እኔ ግን በምሬት ‘ከልጅነቴ ጀምሮ በችግር አለንጋ የተገረፍኩት ለምንድን ነው? ለምን ወላጅ አልባ ሆንኩ? አምላክ እንደዚያ ስንቸገር ለምን አልደረሰልንም?’ እያልኩ ብዙ ጥያቄዎችን በማንሳት ተቃወምኳት። እሷም “ለነዚህ ነገሮች ሁሉ ሊወቀስ የሚገባው አምላክ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነህ?” ስትል መልሳ ጠየቀችኝ። ከዚያም አምላክ ሰዎችን ለስቃይ እንደማይዳርግ ከመጽሐፍ ቅዱሷ ላይ አሳየችኝ። ይህም ፈጣሪ ለሰው ልጆች ፍቅር እንዳለው እንዲሁም በቅርቡ ሁኔታዎች የተሻሉ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ እንድገነዘብ ረዳኝ። እንደ ኢሳይያስ 35:5-7 እና ራእይ 21:3, 4 የመሳሰሉትን ጥቅሶች በመጠቀም ጦርነት፣ ስቃይ፣ ሕመም እንዲሁም ሞት በቅርቡ ተወግደው ታማኝ የሆኑ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ አስረዳችኝ።

የሚደግፈኝ ቤተሰብ አገኘሁ

የኋላ ኋላ የፓስካሊያ ወንድም በደፈጣ ተዋጊዎች መካከል በተደረገ ቀላል ግጭት መሞቱን ሰማሁ። ስለዚህ ቤተሰቦቿን ለማጽናናት በማሰብ ልጠይቃቸው ሄድኩ። ሆኖም ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነና እነሱ መንፈሳዊ ማጽናኛዎችን ለገሱኝ። ሌላም ጊዜ እንዲሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጨማሪ ማበረታቻ ለማግኘት ወደ ቤታቸው ሄድኩ፤ ብዙም ሳይቆይ ለጥናትና ለአምልኮ በምስጢር ይሰበሰቡ ከነበሩት ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተቀላቀልኩ። የይሖዋ ምሥክሮች በኅብረተሰቡ የተገለሉና በእገዳ ሥር የነበሩ ቢሆንም እንኳ ከእነርሱ ጋር ያለኝን ግንኙነት ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ።

በዚህ ትሑት ክርስቲያኖች ባሉበት ቡድን ውስጥ፣ አጥቼው የነበረውን ሞቅ ያለ ቤተሰባዊ ፍቅር አገኘሁ። እነዚህ ክርስቲያኖች በጣም ያስፈልገኝ የነበረውን መንፈሳዊ ድጋፍና እርዳታ ሰጥተውኛል። እኔን ለመርዳትና ለማጽናናት ምንጊዜም ዝግጁ የሆኑ ራስ ወዳድነት የሌለባቸው አሳቢ ወዳጆችን አፈራሁ። (2 ቆሮንቶስ 7:5-7) ከዚህም በላይ እነዚህ ወዳጆቼ አፍቃሪ ሰማያዊ አባት ወደ ሆነልኝ ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድቀርብ ረዱኝ። እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄና አሳቢነት ያሉት የይሖዋ ባሕርያት በጣም ማረኩኝ። (መዝሙር 23:1-6) በመጨረሻ ላይ መንፈሳዊ ቤተሰብና አፍቃሪ አባት አገኘሁ! ልቤ በዚህ በጣም ስለተነካ ብዙም ሳይቆይ ራሴን ለይሖዋ ከወሰንኩ በኋላ በ1945 መስከረም ወር ላይ ተጠመቅሁ።

በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘቴ እውቀቴ እንዲጨምር ብቻ ሳይሆን ያለኝ እምነት ይበልጥ እየጎለበተ እንዲሄድ ረድቶኛል። ምንም ዓይነት መጓጓዣ ስላልነበረ ብዙዎቻችን ከመንደራችን አንስቶ እስከ ጉባኤው ድረስ ያለውን 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን መንገድ የማይረሱ መንፈሳዊ ጭውውቶችን እያደረግን በእግራችን እንጓዝ ነበር። በ1945 መጨረሻ ላይ በሙሉ ጊዜ ወንጌላዊነት ማገልገል እንደምችል ስገነዘብ አቅኚ ሆንኩ። ብዙም ሳይቆይ ያለኝ እምነትና የአቋም ጽናት በእጅጉ ሊፈተን ስለነበር ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረቴ ጠቅሞኛል።

ተቃውሞው ያልተጠበቀ ውጤት አስገኘ

ፖሊሶች እንደሚገድሉን በመዛት በተደጋጋሚ የመሰብሰቢያ ቦታችንን ይፈትሹ ነበር። የእርስ በርስ ጦርነት በመባባሱ አገሪቱ በወታደራዊ ሕግ ትተዳደር ጀመር። ከዚያም ተቃዋሚ ቡድኖች ያለ ርኅራኄ እርስ በርሳቸው ይጨፋጨፉ ጀመር። ቀሳውስትም ሁኔታውን በመጠቀም ባለ ሥልጣናቱን የይሖዋ ምሥክሮች ኮሚኒስት ናቸው ብለው በማሳመን እጅግ የከፋ ስደት እንዲደርስብን አደረጉ።

በሁለት ዓመታት ውስጥ እኔና ሌሎች ሁለት ወንድሞች ለብዙ ጊዜያት የታሰርን ሲሆን ለስድስት ጊዜ ያህል ደግሞ እስከ አራት ወር የሚደርስ እስራት ተፈርዶብናል። ሆኖም እስር ቤቶቹ በፖለቲካ እስረኞች የተጨናነቁ ስለነበሩ በነፃ ለመለቀቅ ቻልን። እንዲህ ዓይነቱን ያልተጠበቀ ነፃነት ተጠቅመን ስብከታችንን ብንቀጥልም ብዙም ሳይቆይ እንደገና ታሰርን፤ በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ይህ ሁኔታ ሦስት ጊዜ ተከሰተ። ሌሎች ብዙ ወንድሞቻችን ምድረ በዳ ወደሆኑት ደሴቶች በግዞት መወሰዳቸውን ሰማን። እንዲህ ዓይነቱን ፈተና ለመጋፈጥ የሚያስችል ጠንካራ እምነት ይኖረኝ ይሆን?

በየዕለቱ ፖሊስ ጣቢያ ሄጄ ሪፖርት እንዳደርግ ሲወሰን ሁኔታዎች ይበልጥ እየከበዱ መጡ። ባለ ሥልጣናቱ እኔን በቅርብ ለመቆጣጠር እንዲያመቻቸው ፖሊስ ጣቢያ ወዳለበትና ለተሰሎንቄ ቅርብ ወደሆነችው ኢቮስሞስ መንደር እንድዛወር አደረጉ። እዚያም ከጣቢያው አቅራቢያ ቤት የተከራየሁ ሲሆን መተዳደሪያ ለማግኘት በየመንደሩ በመዘዋወር ከመዳብ የተሠሩ ማሰሮዎችንና መጥበሻዎችን አጸዳ ነበር። ይህ ሥራ በአካባቢው በሚገኙ መንደሮች ውስጥ በአቅኚነት በማገለግልበት ወቅት ፖሊሶቹ ሳያውቁብኝ በቀላሉ በየቤቱ እንድሄድ ይበልጥ አመቺ ሁኔታ ፈጠረልኝ። በዚህም የተነሳ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን በመስማት በጎ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ከአሥር የሚበልጡት ተጠምቀው የይሖዋ አምላኪዎች ሆነዋል።

በአሥር ዓመት ውስጥ ስምንት እስር ቤቶች አየሁ

ፖሊስ በዓይነ ቁራኛ እየተከታተለኝ እስከ 1949 መጨረሻ ድረስ ከቆየሁ በኋላ ወደ ተሰሎንቄ በተመለስኩ ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን ለመቀጠል ጓጉቼ ነበር። በ1950 ከችግሮች እፎይ አልኩ ባልኩበት ጊዜ በድንገት የጦር ሠራዊቱን እንድቀላቀል ታዘዝኩ። እኔ ግን በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሜ ምክንያት ‘ጦርነትን ላለመማር’ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። (ኢሳይያስ 2:4) ግሪክ ውስጥ በአስከፊነታቸው በሚታወቁት አንዳንድ እስር ቤቶች ያሳለፍኩት በስቃይ የተሞላ ረጅም ሕይወት የጀመረው በዚህ ሁኔታ ነበር።

መጀመሪያ የታሰርኩት ድራማ በምትባለው ከተማ ነበር። እዚያ በታሰርኩበት በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት አዲስ ምልምል ወታደሮች የዒላማ ተኩስ ልምምድ ያደርጉ ነበር። አንድ ቀን ወደ ልምምዱ ቦታ ወሰዱኝና አንደኛው መኮንን ጠመንጃውን ወደፊቴ ገፋ አድርጎ እንድተኩስ አዘዘኝ። ፈቃደኛ አለመሆኔን ሲመለከት ወደ እኔ መተኮስ ጀመረ። አቋሜን እንደማለውጥ የገባቸው ሌሎች መኮንኖች በጭካኔ ይደበድቡኝ ጀመር። ከዚህም በላይ ሲጋራ እየለኮሱ በእጆቼ መዳፎች ላይ እየተረኮሱ ያጠፉ ነበር። በመጨረሻም ለሦስት ቀናት በአንድ ገለልተኛ ክፍል ውስጥ ታሰርኩ። የእጄ ቃጠሎ በጣም ያሰቃየኝ የነበረ ከመሆኑም በላይ ጠባሳው ለብዙ ዓመታት አልጠፋም ነበር።

በጦር ፍርድ ቤት ከመቅረቤ በፊት ኢራክሊዮን፣ ቀርጤስ ወደሚገኝ የወታደሮች ካምፕ ተዛወርኩ። በዚያም አቋሜን ለማስለወጥ በማሰብ ክፉኛ ደበደቡኝ። አቋሜን እንዳላጎድፍ በመፍራት የሰማዩ አባቴ እንዲያጠነክረኝ ከልብ የመነጨ ጸሎት አቀረብኩ። በዚህ ወቅት “‘ይዋጉሃል፤ ዳሩ ግን አድንህ ዘንድ እኔ ከአ[ን]ተ ጋር ነኝና አያሸንፉህም’ ይላል እግዚአብሔር” የሚሉት በኤርምያስ 1:19 ላይ የሚገኙት ቃላት ወደ አእምሮዬ ይመጡ ነበር። ‘የአምላክ ሰላም’ መረጋጋትና እፎይታ ያስገኘልኝ ከመሆኑም በላይ በፍጹም ልብ በይሖዋ መታመን ጥበብ ያለበት እርምጃ መሆኑን አስተውያለሁ።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7፤ ምሳሌ 3:5

በኋላም ፍርድ ቤት ቀርቤ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደብኝ። በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች አደገኛ “የመንግሥት ጠላቶች” እንደሆኑ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። የዕድሜ ልክ እስራቴን የጀመርኩት ከካኒያ ወጣ ብሎ በሚገኘው ኢትሲድን በሚባል የወንጀለኞች እስር ቤት ሲሆን የታሰርኩት ለብቻዬ ነበር። ኢትሲድን ያረጀ ግንብ ቤት ሲሆን የታሰርኩበት ክፍል በአይጦች የተሞላ ነበር። በዚህም ምክንያት አይጦቹ ሰውነቴን እንዳይነኩ ለመከላከል ከእግር እስከ ራሴ ድረስ በአሮጌ ብርድ ልብስ መጠቅለል ነበረብኝ። በኋላም በሳምባ ምች በሽታ ተያዝኩ። ሐኪሙም የፀሐይ ብርሃን እንደሚያስፈልገኝ በመናገሩ በእስር ቤቱ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች እስረኞች ጋር የመወያየት አጋጣሚ አገኘሁ። ሆኖም ሁኔታዬ ይበልጥ እየተባባሰ በመሄዱና ሳንባዬ በጣም መድማት በመጀመሩ ኢራክሊዮን ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወሰድኩ።

መንፈሳዊ ቤተሰብ የሆኑልኝ የእምነት ባልደረቦቼ እርዳታ በሚያስፈልገኝ በዚህ ጊዜም እንኳ ከጎኔ አልተለዩኝም። (ቆላስይስ 4:11) በኢራክሊዮን የሚኖሩት ወንድሞች በየጊዜው እየመጡ በመጠየቅ ያጽናኑኝና ያበረታቱኝ ነበር። ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች ለመመሥከር እንዲያመቸኝ ጽሑፎች እንደምፈልግ በነገርኳቸው ጊዜ፣ ጽሑፎቹን ለመደበቅ የሚያስችል ከሥሩ የምስጢር ኪስ ያለው ሻንጣ ይዘውልኝ መጡ። በእነዚያ እስር ቤቶች ውስጥ በቆየሁባቸው ዓመታት አብረውኝ ታስረው ከነበሩት ውስጥ ቢያንስ ስድስቱ እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ለመርዳት በመቻሌ በጣም ደስ ብሎኛል!

በዚህ መሃል የእርስ በርስ ጦርነቱ ስላቆመ የእስር ዘመኔ ወደ አሥር ዓመት ተቀነሰ። የቀሩትን ዓመታት በሬዚምኖ፣ በጄንቲ ኩሌና በካሳንድራ እስር ቤቶች አሳለፍኩ። በስምንት እስር ቤቶች ውስጥ ለአሥር ዓመት ያህል ከቆየሁ በኋላ ተፈትቼ ወደ ተሰሎንቄ በተመለስኩ ጊዜ የተወደዱ ክርስቲያን ወንድሞቼ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ።

በክርስቲያን ወንድሞች እርዳታ መንፈሳዊ እድገት አደረግሁ

ከእስር በተፈታሁበት ወቅት በግሪክ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በአንጻራዊ ሁኔታ የአምልኮ ነፃነት አግኝተው ስለነበር አጋጣሚውን በመጠቀም ወዲያውኑ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቴን ቀጠልኩ። ብዙም ሳይቆይ ካቲና ከተባለች ይሖዋን የምትወድና በስብከቱ ሥራ በቅንዓት የምትካፈል ታማኝ ክርስቲያን እህት ጋር በመተዋወቄ ተጨማሪ በረከት አገኘሁ። ከዚያም በጥቅምት 1959 ተጋባን። ሴት ልጃችን አጋፔ መወለዷና የራሴ የሆነ ክርስቲያን ቤተሰብ ማግኘቴ የሙት ልጅ በመሆኔ ከደረሰብኝ ጉዳት ይበልጥ ለመፈወስ ረድቶኛል። ከሁሉም በላይ ቤተሰባችን አፍቃሪ ሰማያዊ አባት በሆነው በይሖዋ ጥበቃ ሥር የማገልገል መብት በማግኘቱ በጣም ተደስቻለሁ።—መዝሙር 5:11

ከአቅም በላይ በሆኑ ችግሮች ምክንያት አቅኚነቴን ለማቆም ብገደድም ባለቤቴ በሙሉ ጊዜ አገልግሎቷ መቀጠል እንድትችል ድጋፍ አደርግላት ነበር። በ1969 በኑረምበርግ፣ ጀርመን ብሔራት አቀፍ ስብሰባ በተደረገበት ወቅት በክርስቲያናዊ ሕይወቴ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነ ነገር ተከሰተ። እዚያ ለመሄድ በምዘጋጅበት ጊዜ ፓስፖርት እንዲሰጠኝ አመለከትኩ። ፓስፖርት ሳላገኝ ሁለት ወራት አለፉ፤ ባለቤቴ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማጣራት ወደ ቦታው ስትሄድ ኃላፊው ዳጐስ ያለ ሰነድ ከመሳቢያው ውስጥ አወጣና “ለዚህ ሰው ፓስፖርት የምትጠይቂው ጀርመን ሄዶ የሌሎችን ሃይማኖት እንዲያስለውጥ ነው? በፍጹም አይደረግም! ሰውየው አደገኛ ነው” በማለት ተናገረ።

በይሖዋ እርዳታና በአንዳንድ ወንድሞች እገዛ በቡድን ፓስፖርት ውስጥ በመካተቴ ግሩም በነበረው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ቻልኩ። ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከ150,000 በላይ የደረሰ ሲሆን ይሖዋ በመንፈሱ ይህን ዓለም አቀፍ መንፈሳዊ ቤተሰብ እየመራው እንዳለና አንድ እንዳደረገው በግልጽ ለማየት ችያለሁ። በኋለኛው የሕይወት ዘመኔም ክርስቲያናዊ የወንድማማችነት ኅብረት ያለውን ዋጋማነት በአድናቆት እንድመለከት አስችሎኛል።

በ1977 ታማኝ አጋሬ የሆነችው ውዷ ባለቤቴ ሞተች። ልጄን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማሳደግ የቻልኩትን ያህል ጥረት አድርጌያለሁ። ይሁንና ብቻዬን አልነበርኩም። መንፈሳዊ ቤተሰቦቼ በዚያን ወቅትም ቢሆን ከጎኔ አልተለዩም ነበር። በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት ሁሉ ድጋፋቸው ላልተለየኝ ወንድሞች ምንጊዜም አመስጋኝ ነኝ። እንዲያውም አንዳንዶቹ ለተወሰነ ጊዜ ቤታችን በመኖር ልጄን ተንከባክበውልኛል። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ያሳዩኝን ፍቅር መቼም አልረሳውም።—ዮሐንስ 13:34, 35

አጋፔም ካደገች በኋላ ኤልያስ የተባለ ታማኝ ወንድም አገባች። አሁን አራት ወንዶች ልጆች ያሏት ሲሆን ሁሉም በእውነት ውስጥ ይገኛሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተደጋጋሚ በአንጎሌ ውስጥ የደም መፍሰስ ችግር ስላጋጠመኝና ብዙም ጤና ስለሌለኝ ሴት ልጄና ቤተሰቧ ጥሩ እንክብካቤ እያደረጉልኝ ነው። የጤና ችግር ቢኖርብኝም እንኳ የምደሰትባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። በመላው ተሰሎንቄ በግለሰቦች ቤት በድብቅ የሚሰበሰቡ አንድ መቶ የሚያህሉ ወንድሞች ብቻ የነበሩበትን ጊዜ አስታውሳለሁ። አሁን ግን በዚህ አካባቢ ወደ አምስት ሺህ የሚጠጉ ወንድሞች ይገኛሉ። (ኢሳይያስ 60:22) የአውራጃ ስብሰባዎች በምናደርግበት ጊዜ አንዳንድ ወጣቶች ወደ እኔ ቀረብ ብለው “መጽሔቶች ቤታችን ይዘው ይመጡ እንደነበር ያስታውሳሉ?” ሲሉ ይጠይቁኛል። ወላጆቻቸው እነዚያን መጽሔቶች የማያነብቧቸው የነበረ ቢሆንም እንኳ ልጆቻቸው አንብበው መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ በቅተዋል!

የይሖዋ ድርጅት ያደረገውን እድገት ስመለከት እነዚያ አስቸጋሪ ፈተናዎች ለምን ደረሱብኝ እያልኩ መቆጨት እንደማይኖርብኝ ይሰማኛል። ለልጅ ልጆቼም ሆነ ለሌሎች ወጣቶች የሰማዩን አባት በወጣትነታቸው ካሰቡት መቼም እንደማይጥላቸው ሁልጊዜ እነግራቸዋለሁ። (መክብብ 12:1) ይሖዋ በእርግጥ “አባት ለሌላቸው ልጆች አባት” እንደሚሆን የተናገረው ቃል በእኔ ላይ ተፈጽሟል። (መዝሙር 68:5 የ1980 ትርጉም) ገና በልጅነቴ ቸል የተባልኩ የሙት ልጅ ብሆንም የኋላ ኋላ ተንከባካቢ አባት አገኘሁ!

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በድራማ እስር ቤት የወጥ ቤት ሠራተኛ ነበርኩ

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1959 በሠርጋችን ዕለት ከካቲና ጋር

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1960ዎቹ መገባደጃ ላይ በተሰሎንቄ አቅራቢያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ያደረግነው ስብሰባ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1967 ከልጃችን ጋር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ