በሕይወቴ መሥራት የምችለው ከሁሉ የተሻለ ነገር
ቦብ አንደርሰን እንደተናገረው
የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ ጥቂት ጓደኞቼ እንዲህ ሲሉ ጠየቁኝ፦“ቦብ፣ እስካሁን በአቅኚነት የቀጠልከው ለምንድን ነው?” ፈገግ አልኩና “ከአቅኚነት የተሻለ ሥራ አለ ብላችሁ ታስባላችሁ?” አልኳቸው።
በ1931 ወደ አቅኚነት አገልግሎት ስገባ 23 ዓመቴ ነበር። አሁን 87ኛ ዓመቴ ሲሆን እስካሁን አቅኚነትን ተያይዤዋለሁ። በሕይወቴ ከዚህ የተሻለ ምንም ነገር ልሠራበት እንደማልችል አውቃለሁ።
ለምን እንደዚህ እንዳልኩ ግልጽ ላድርግላችሁ። በ1914 አንድ ትራክት ቤታችን አገኘን። ትራክቱ በጊዜው ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው በሚጠሩት የይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ነበረ። ምሥክሩ በተመለሰ ጊዜ እናቴ ስለ ሲኦል እሳት አጥብቃ ጠየቀችው። አጥባቂ ዌስሊያን ሜቶዲስት ሆና ብታድግም ይህንን የዘላለም ሥቃይ መሠረተ ትምህርት ከአፍቃሪው አምላክ ጋር ፈጽሞ ልታስማማው አልቻለችም። ስለ ጉዳዩ እውነቱን ስታውቅ “በሕይወቴ ውስጥ ሁሉ ከተሰማኝ የላቀ ደስታ ይሰማኛል!” አለች።
እናቴ በሜቶዲስት የሰንበት ትምህርት ቤት ማስተማሯን ወዲያውኑ አቆመችና አነስተኛ ቁጥር ካላቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር መተባበር ጀመረች። ከመርዚ ወንዝ ባሻገር ከሊቨርፑል ወደብ ፊት ለፊት ባለው በርከንሄድ በሚባለው የመኖሪያ ከተማችን የስብከት ሥራዋን ጀመረች፤ እንዲሁም በዛ ወዳሉ አጎራባች ከተሞች ሳታሰልስ በብስክሌት ትጓዝ ነበር። ለልጆችዋ ግሩም ምሳሌ በመተው በተቀረው የሕይወቷ ክፍል በዚህ ሰፊ ክልል መሥክራለች፤ እንዲሁም በአካባቢው በደንብ የታወቀች ሆናለች። እስከ መጨረሻው ትጉ ምሥክር በመሆን የ97 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ሆና በ1971 አረፈች።
እኔና ካትሊን እናታችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ባላት ስብሰባ አብረናት እንድንገኝ ከሜቶዲስት የሰንበት ትምህርት ቤት ለቀቅን። ኋላም አባቴ ሳይታሰብ ከእኛ ጋር ሲቀላቀል ወላጆቼ የአምላክ በገና በተባለው የእንግሊዝኛ መጽሐፍ አማካኝነት መደበኛ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምናደርግበትን ፕሮግራም አመቻቹ። በእነዚያ ጊዜያት እንዲህ የመሰሉ ጥናቶች አዲስ ቢሆኑም ዓመታት ከተቆጠሩ በኋላ ሁለታችንም ወደ አቅኚነት አገልግሎት መግባታችን ይህ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ እውነቶች ላይ ገና ከመጀመሪያ የተሰጠ ሥልጠና ዳጎስ ያለ ሽልማት ማስገኘቱን ያሳያል።
በ1920 በሊቨርፑል “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ፊልም መመልከታችን ለእኛ ለልጆችዋ መንፈሳዊ ለውጥ ያመጣ ጊዜ እንደ ነበር አጥብቃ ትገልጻለች፤ እውነቷንም ነበር። በዚያን ጊዜ ታዳጊ ወጣት እንደመሆኔ መጠን ያ ትዕይንት በአእምሮዬ ላይ የማይፋቅ ምስል ትቶ አልፏል። የኢየሱስን ሕይወት በተመለከተ በተለይም ለመሞት ሲሄድ የሚያሳየው ክፍል ቁልጭ ብሎ ይታወሰኛል። የተመለከትኩት ሁሉ በሕይወት ውስጥ እጅግ አንገብጋቢ በሆነው የስብከቱ ሥራ ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል!
በ1920ዎቹ መባቻ ላይ እሁድ እሁድ ከሰዓት በኋላ ከእናቴ ጋር ትራክቶች ማሰራጨት ጀመርኩ። በመጀመሪያ ትራክቶቹን በየቤቱ ትተን እንድንሄድ ተመክረን ነበር፤ በኋላ ግን ለየቤቱ ባለቤቶች በእጃቸው እንድንሰጣቸውና ከዚያም ፍላጎት ያሳዩትን ተመልሰን እንድንጠይቃቸው ተነገረን። ይህም ዛሬ እንዲህ ፍሬያማ ለሆኑት ተመላልሶ መጠይቅና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንቅስቃሴዎቻችን ቅድመ መሠረት እንደሆነ ሁልጊዜ አስባለሁ።
ወደ አቅኚነት አገልግሎት መግባት!
እኔና ካትሊን በ1927 ተጠመቅን። በ1931 የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ስም እንድንጠራ የተላለፈውን ውሳኔ የሰማሁት በሊቨርፑል አናሊቲካል ኬሚስት ሆኜ በምሠራበት ጊዜ ነበር። በሊቨርፑል የንግድ ክልሎች ውስጥ የሚሠሩ የማኅበሩን ኮልፖልተሮች (አሁን አቅኚ ይባላሉ) ሁል ጊዜ እመለከት ስለነበር ምሳሌነታቸው እጅጉን አነቃቅቶኛል። ሕይወቴን በይሖዋ አገልግሎት ማሳለፍ እንድችል ከዓለማዊ ውሎ ለመላቀቅ እንዴት እናፍቅ ነበር!
በዚያው ዓመት የበጋ ወቅት ጌሪ ጌራርድ የተባለው ጓደኛዬ ወደ ህንድ ሄዶ እንዲሰብክ ከሁለተኛው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዘዳንት ከጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ የአገልግሎት ምድብ እንደተቀበለ ነገረኝ። መርከብ ከመሳፈሩ ትንሽ ቀደም ብሎ ሊጠይቀኝና ስለ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መብት ሊነግረኝ ብቅ አለ። በሚሰናበተኝ ጊዜ “ቦብ፣ በቅርቡ አቅኚ እንደምትሆን እርግጠኛ ነኝ” በማለት ይበልጥ አበረታታኝ። የተፈጸመውም ይኸው ነበር። በዛው ዓመት በጥቅምት ወር ተመዘገብኩ። በአገሪቱ ጠባብ መንገዶች በብስክሌት እየተጓዙ በገለልተኛ አካባቢዎች ለሚገኙ ሰዎች መስበክ እንዴት ያለ ደስታ፣ እንዴት ያለ ነፃነት ነው! መቼም ቢሆን ልሠራው ከምችለው የላቀ አንገብጋቢ ሥራ እንደተያያዝኩ ከዚህ በኋላ አወቅሁ።
የመጀመሪያው የአቅኚነት ምድቤ ከሲርል ስቴንቲፈርድ ጋር የተገናኘሁበት ደቡብ ዌልዝ ነበረ። ሲርል በኋላ ካትሊንን አገባና ለብዙ ዓመታት አብረው በአቅኚነት አገለገሉ። የኋላ ኋላም ሴት ልጃቸው ሩት ወደ አቅኚነት አገልግሎት ገባች። በ1937 የኤሪክ ኩክስ የአገልግሎት ባልደረባ ሆኜ በፍሊትውድ ላንክሻየር ነበርኩ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ አቅኚዎች የሚሠሩት ከጉባኤ የአገልግሎት ክልል ውጪ በሆኑ የእንግሊዝ ገጠራማ ሥፍራዎች ብቻ ነበር። ነገር ግን በጊዜው ለንደን በሚገኘው የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ላለው ሥራ ኃለፊ የነበረው አልበርት ዲ ሽሮደር ሁለታችንም ወደ ብራድፈርድ ዮርክሻየር እንድንቀሳቀስ ወሰነ። በእንግሊዝ የሚገኙ አቅኚዎች አንድን ጉባኤ እንዲረዱ ሲመደቡ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር።
በ1946 ኤሪክ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ገባና አሁን ዚምቧቡዌ ተብላ በምትጠራው ደቡብ ሮዴዢያ ተመደበ፤ እሱና ባለቤቱ እስካሁን በደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ሚስዮናውያን ሆነው በታማኝነት እያገለገሉ ነው።
በ1938 ሌላ የአገልግሎት ምድብ ነበረኝ ይኸውም በሰሜናዊ ምዕራብ ላንክሻየርና ውብ በሆነው ዲስትሪክት ሃይቅ አካባቢዎች የዞን አገልጋይ (አሁን የወረዳ የበላይ ተመልካች ይባላል) ሆንኩ። እዚያም ከኦሊቭ ዳኬት ጋር ተገናኘሁ፤ ከዚያም ከተጋባን በኋላ ወዲያውኑ የወረዳ ሥራ ባልደረባዬ ሆነች።
አየርላንድ በጦርነቱ ዓመታት ወቅት
እንግሊዝ በጀርመን ላይ ጦርነት ካወጀችበት መስከረም 1939 ሳይውል ሳያድር የአገልግሎት ምድቤ ወደ አየርላንድ ተለወጠ። በእንግሊዝ የጦር ሠራዊት ምልመላ የተጀመረ ቢሆንም ጦርነቱ በቆየባቸው ዓመታት ገለልተኛ አገር ሆና በዘለቀችው ደቡባዊ አየርላንድ ሪፑብሊክ ግን ይህ አልነበረም። የአየርላንድ ሪፑብሊክና ሰሜናዊ አየርላንድ አንድ ወረዳ ቢደረጉም ማዕቀቡ ሥራ ላይ ውሎ ስለ ነበር ከእንግሊዝ ወደ የትኛውም የአየርላንድ ክፍል ለመሄድ የይለፍ ፈቃድ ማግኘት ያስፈልግ ነበር። ባለሥልጣኖች መሄድ እንደምችል ግን በእኔ ዕድሜ ያለው ተመልማይ ቡድን ሲጠራ ወዲያውኑ ወደ እንግሊዝ ለመመለስ እንድስማማ ነገሩኝ። በአፌ ብስማማም የይለፍ ፈቃዴ ሲዘጋጅ አብሮት የተያያዘ ምንም ዓይነት ግዴታ አለመኖሩ ያልጠበቅሁት ነገር ነበር!
በዚያን ጊዜ በመላው አየርላንድ የነበሩት ምሥክሮች ከ100 ጥቂት የሚልቁ ነበሩ። 1939 ዱብሊን በደረስን ጊዜ በአቅኚነት ብዙ ዓመታት ያሳለፈው ጃክ ኮር አገኘን። ባቅራቢያው ባለ ከተማ ሌሎች ሁለት አቅኚዎችና በጠቅላላው ወደ 20 የሚጠጉ ጥቂት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ዱብሊን እንዳሉ ነገረን። ጃክ በዱብሊን ለስብሰባ የሚሆን አንድ ክፍል ተከራይቶ ነበር፤ በዚያም ምን ጊዜም እሁድ እሁድ ለመሰብሰብ ተስማምተው ነበር። ይህ ዝግጅት በ1940 ጉባኤ እስከተመሠረተበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎ ነበር።
ሰሜናዊቷ አየርላንድ የዩናይትድ ኪንግደም ክፍል ስለነበረች ከጀርመን ጋር ጦርነት በመግጠሟ ምክንያት ከሰሜን ወደ ቤልፋስት ተዛወርን። እዚያም ምግብ የምንቀበልበት ኩፖን ነበረን፤ እንዲሁም ከአውሮፕላን ድብደባ ለማምለጥ ማታ ማታ መብራቶችን ሁሉ እናጠፋፋ ነበር። ምንም እንኳ የናዚ አውሮፕላኖች ቤልፋስትን ለመደብደብና አውሮፓ ወዳለው ማዕከላቸው ለመመለስ ከ1600 ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ርቀት መብረር የነበረባቸው ቢሆንም ከተማዋን በተሳካ ሁኔታ ለመደብደብ ችለዋል። በመጀመሪያው ጥቃት የመንግሥት አዳራሻችን ተጎዳ፤ እንዲሁም የመኖሪያ ሕንፃችን ተደመሰሰ፤ በጊዜው በከተማው ሌላኛ ክፍል የሚገኙትን ወንድሞች ልንጠይቅ ሄደን ስለነበር በአስደናቂ ሁኔታ አመለጥን። በዚያው ምሽት አንድ የምሥክሮች ቤተሰብ በአካባቢው ወደሚገኝ ወደ አንድ የቦንብ መጠለያ ሮጦ ይሄዳል። እዚያም እንደደረሱ ሞልቶ ስላገኙት ወደ ቤታቸው ተመለሱ። መጠለያው በቀጥታ ተመታና በውስጡ ያሉት ሁሉ ሲገደሉ ወንድሞቻችን ግን አነስተኛ መቆረጥና መቁሰል ደርሶባቸው በሕይወት ተረፉ። በእነዚህ አስቸጋሪ የጦርነት ዓመታት ወቅት ከወንድሞቻችን በአንዱም ላይ ጫን ያለ ጉዳት አልደረሰም ነበር፤ ለዚህም ይሖዋን አመሰገንን።
የመንፈሳዊ ምግብ አቅርቦት
ጦርነቱ እየተፋፋመ ሲመጣ እገዳዎች ይበልጥ እየጠበቁ መጡ፤ በመጨረሻም መልእክቶች ሳንሱር እንዲደረጉ ተወሰነ። ይህም መጠበቂያ ግንብ ወደ አገሪቱ እንዳይገባ ታገደ ማለት ነው። ምን ማድረግ እንደምንችል ግራ ቢገባንም ይሖዋ ግን እጁ አጭር አልነበረም። አንድ ቀን ጠዋት ስለ ቤተሰብ ጉዳዩች ደብዳቤ ይጽፍልኝ ከነበረ በካናዳ ከሚኖር “ዘመድ” አንድ ደብዳቤ ደረሰኝ። ማን እንደሆነ አላወቅሁም ነበር፤ ይሁን እንጂ የማነበው “አንድ አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ” እንደላከልኝ በቁራጭ ማስታወሻ ላይ ገልጾልኝ ነበረ። የላከው የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ ቢሆንም ሽፋኑ እንደ መደበኛው ቅጂ ስላልሆነ በፈታሾቹ አልተያዘም።
“በፎቶ ድራማ” ሥራ ተካፍላ የነበረችውን ማጂ ኩፐርን ጨምሮ በአካባቢው በሚኖሩ ምሥክሮች እርዳታ እኔና ባለቤቴ ጽሑፎችን ማባዛት ጀመርን። በካናዳ፣ በአውስትራሊያና በዩናይትድ ስቴትስ ከሚኖሩ ብዙ አዳዲስ ጓደኞቻችን ልሙጥ ሽፋን ያላቸው መጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ያለማቋረጥ ስለሚደርሱን ወዲያውኑ 120 ቅጂዎችን በአገር ውስጥ ለማሰራጨት ዝግጅት አደረግን። በእነርሱ ትጋትና ደግነት በመታገዝ በጦርነቱ ጊዜ ሁሉ አንድም ቅጂ አምልጦን አያውቅም።
ትልልቅ ስብሰባዎችንም ለማድረግ ችለን ነበር። ልጆች የተባለው አዲስ የእንግሊዝኛ ጽሑፍ የወጣበት የ1941 የአውራጃ ስብሰባ በጣም ግሩም ነበር። ሳንሱር የሚያደርገው ሰው ይህ መጽሐፍ ስለ ልጆች የሚናገር ነው ብሎ ስላሰበ ይመስላል መጽሐፉን አልተቃወመም፤ ስለዚህ የሚያስፈልገንን ይህል ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ቻልን! በሌላ ጊዜም ሰላም ዘላቂ ሊሆን ይችላልን? የተባለውን የእንግሊዝኛ ቡክሌት ቅጂዎች ከለንደን ማስገባት ስላልተቻለ አገር ውስጥ ታትሟል። እነዚህ ሁሉ እገዳዎች ቢጣሉብንም እንኳ መንፈሳዊ ጉዳት አልደረሰብንም።
ተቃውሞን ማሸነፍ
አንድ የይሖዋ ምሥክር በሚያንቀሳቅሰው ቤልፋስት በሚገኝ የአቅመ ደካሞች መንከባከቢያ የሚኖር አንድ ቄስ እንግሊዝ ለምትገኘው ሚስቱ ሪችስ የተባለውን መጽሐፍ ቅጂ ላከላት። እውነትን ትቃወም ስለ ነበር መልስ ስትልክ ይህንን ነጥብ ግልጽ አደረገች። በተጨማሪም “የአገር ፍቅር ስሜት የሌለው ድርጅት” እንደሆንን ገለጸች። ደብዳቤ ፈታሹ ይህችን ደብዳቤ ነጥሎ አወጣትና ጉዳዩን ለወንጀል ምርመራ ክፍል ሪፖርት አደረገ። በውጤቱም ቃል እንድሰጥ ወደ ፖሊስ ሰፈሩ ተጠራሁና ሪችስ የተባለውን መጽሐፍ አንድ ቅጂ እንዳመጣ ተጠየቅሁ። የሚያስደስተው በመጨረሻ መጽሐፉ ሲመለስ የተሰመረበት ሁሉ ስለ ሮማ ካቶሊክ ቤተ ክረስቲያን የሚናገረው መሆኑን አስተዋልኩ። ፖሊሱ አይ አር ኤ (አይሪሽ ሪፑብሊካን አርሚ) የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በዓይነ ቁራኛ የሚከታተል እንደበረ ስለማውቅ ይህ ነገር ትርጉም እንዳለው ተሰማኝ።
ፖሊሱ አቋማችንን ለመረዳት አስቻጋሪ ሆኖ ስላገኘው በጦርነት ጊዜያት ስለምናሳየው ገለልተኝነት አንድ በአንድ ጠየቀኝ። ይሁን እንጂ ባለሥልጣኖቹ በእኛ ላይ ምንም ዓይነት እርምጃ አልወሰዱም። በሌላ ጊዜ ስብሰባ ለማድረግ ፈቃድ ስጠይቅ ፖሊሱ ሁለት የፖሊስ ዜና ዘጋቢዎችን ልላክላችሁ ብሎ ጠየቀ። “በደስታ እንቀበላቸዋለን!” አልኩኝ። ወደ ስብሰባው በመምጣት የከሰዓት በኋላውን ስብሰባ አጫጭር ማስታወሻ እየጻፉ ተካፈሉ። በስብሰባው መጨረሻ ላይ “ስብሰባው በጣም የሚያስደስት ነው፤ ወደዚህ የተላክነው ለምንድን ነው?” ብለው ጠየቁ። በማግሥቱ ዳግመኛ መጡና ሰላም ዘላቂ ሊሆን ይችላልን? የተባለው የእንግሊዝኛ ቡክሌታችንን አንድ ቅጂ በነፃ ስንሰጣቸው በደስታ ተቀበሉ። የተቀረው ስብሰባ ምንም ችግር ሳያጋጥመን ተጠናቀቀ።
ጦርነቱ አክትሞ የጉዞ ማዕቀቦች ልል በነበሩበት ወቅት ፕሪስ ሁዝ ከለንደኑ ቤቴል ወደ ቤልፋስት መጣ። የመጣው በኋላ ሚስዮናዊ ሆኖ ቻይና ከተመደበው ሃሮልድ ኪንግ ጋር ነበር። ከለንደኑ ቅርንጫፍ ቢሮ ተለይተን ስድስት ዓመታት ካሳለፍን በኋላ እነዚህ ወንድሞች በሰጡን ንግግሮች ሁላችንም እጅግ ተበረታታን። ጥቂት ጊዜ እንዳለፈ በቤልፋስት ያለውን የመንግሥቱን ሥራ ለማጠናከር ሃሮልድ ዳዩርደን የተባለ ሌላ ታማኝ አቅኚ ከእንግሊዝ ተላከ።
ወደ እንግሊዝ መመለስ
ለአይሪሽ ወንድሞች ያለን ፍቅር በጣም አድጎ ስለነበር ወደ እንግሊዝ መመለስ አስቸጋሪ ነበረ። ነገር ግን እኔና ባለቤቴ ተመልሰን ማንችስተር ተመደብን፤ በኋላም የምሥራቹ አገልጋይ ይበልጥ ወደሚያስፈልግበት የላንክሻየር ሌላኛ ከተማ ወደሆነው ወደ ኒውተን ለ ዊሎውዝ ተዛወርን። ሴት ልጃችን ሎኧስ በ1953 ተወደች፤ በ16 ዓመቷ ወደ አቅኚነት አገልግሎት ስትገባ መመልከቱ ልብን በደስታ ሞቅ የሚያደርግ ነበር። አቅኚውን ዴቪድ ፓርኪንሰን ካገባች በኋላ በብዙ መንገድ የእኔንና የኦሊቭን ኮቴ በመከተል በሰሜናዊ አየርላንድ የሙሉ ጊዜ አገልግሎታቸውን ቀጠሉ። አሁን ከልጆቻቸው ጋር ወደ እንግሊዝ ተመልሰው ሁላችንም በአንድ ጉባኤ እናገለግላለን።
በሁኔታዎቻችን ላይ ለውጦች ቢኖሩም አቅኚነትን መቼም ቢሆን አላቆምኩም፣ እኔም ሆንኩ ኦሊቭ ይህንን ማድረግ አንፈልግም። ያስመዘገብኩት የአቅኚነት አገልግሎት በራሴ ጥረት ብቻ የተገኘ ሳይሆን የሚስቴ እገዛ እንዳለበት ሁልጊዜ ይሰማኛል፤ ምክንያቱም ያለ እርሷ የማያቋርጥ ፍቅራዊ እርዳታ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ፈጽሞ መቀጠል አልችልም ነበር። በእርግጥ አሁን ሁለታችንም ቶሎ ይደክመናል ቢሆንም መመሥከር፣ በተለይም አንድ ላይ ሆነን ለጎረቤቶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት እስካሁን ያስደስተናል። ባለፉት ዓመታት አንድ መቶ የሚያክሉ ግለሰቦች ራሳቸውን ወስነው የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ የመርዳት መብት አግኝተናል። ይህ እንዴት የሚያስደስት ነው! እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ እየሰፉ የሄዱት ቤተሰቦችም ምሥክሮች እየሆኑ ስለመጡ አሁን ይህ ቁጥር ብዙ እጥፍ መሆን አለበት ብዬ እገምታለሁ።
እኔና ኦሊቭ ባሳለፍናቸው ዓመታት ስላገኘናቸው አያሌ መብቶችና ተሞክሮዎች ሁልጊዜ እንነጋገራለን። እንዴት ያሉ አስደሳችና ከመቅጽበት ሮጠው ያለፉ ዓመታት ነበሩ! በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አምላኬን ይሖዋን አቅኚ ሆኖ ከማገልገል የተሻለ በሕይወቴ ምንም ዓይነት ነገር መሥራት እንደማልችል አውቃለሁ። አሁን ያለፈውን ጊዜ በአመስጋኝነት ስመለከትም ሆነ የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ ስጠባበቅ “ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና። ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ . . . ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ” የሚሉት የኤርምያስ ቃላት ላቅ ያለ ትርጉም እንዳዘሉ ተገንዝቤአለሁ።—ሰቆቃወ ኤርምያስ 3:22–24
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቦብና ኦሊቭ አንደርሰን