ሳታቋርጡ ዝሩ ይሖዋ እንዲበቅል ያደርገዋል
በፍሬድ ሜትካልፍ እንደተነገረው
ገና በ1948 በከቤት ወደቤት አገልግሎቴ ወቅት በደቡብ አየርላንድ በኮርክ ከተማ ዳርቻ የሚገኝ አንድ አነስተኛ የእርሻ ቦታ ጐበኘሁ። ለገበሬው ማንነቴን ስገልጽለት ፊቱ ቀላ። በጣም ተቆጣና ኮሚኒስት ነህ ብሎ ከጮኸብኝ በኋላ መንሹን ሊያመጣ ሮጠ። ከዚያ ምንም ሳላመነታ ከእርሻው በርግጌ ወጣሁና ከመንገዱ ዳር የተውኩት ብስክሌቴ ላይ ዘልዬ ወጣሁ። እዚያ የነበረው ቁልቁለት በጣም ቀጥ ያለ ቢሆንም ገበሬው መንሹን እንደጦር የሚወረውርብኝ መስሎ ስለተሰማኝ ምንም ወደኋላዬ ሳልመለከት የቻልኩትን ያህል በፍጥነት ብስክሌቴን አበረርኳት።
በ1946 በልዩ አቅኚነት ከኢንግላንድ ወደ አየርላንድ ከመጣሁ ጀምሮ ከእንዲህ ዓይነቱ አጸፋ ምላሽ ጋር ተዋውቄያለሁ። አባል የሆንኩበት በቁጥር 24 የመንግሥት ሰባኪዎች የነበሩበት አነስተኛ ቡድን ቀደም ሲል የጥላቻና የስም ማጥፋት ሴራ አጋጥሞታል። ይሁን እንጂ የይሖዋ መንፈስ በመጨረሻው ውጤት እንደሚያስገኝ እርግጠኛ ነበርኩ።—ገላትያ 6:8, 9
ነገሮቹ እንዴት እንደተፈጠሩ ከማውሳቴ በፊት ስለ ሕፃንነት ሕይወቴና በእንደዚህ ዓይነት ፈታኝ ሁኔታዎች ሥር ብዙ ስለጠቀመኝ ማሠልጠኛ ትንሽ ልንገራችሁ።
ጥሩ የወላጅ ምሳሌነትና ማሠልጠኛ
አባቴ እውነትን ያገኘው ገና በ1914 ነበር። በሼፊልድ ኢንግላንድ ከእግር ኳስ ጨዋታ ወደ ቤት ሲመለስ ሳለ የሙታንን ሁኔታ የሚገልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ አነበበ። ከዚህ ቀደም ለጥያቄዎቹ መልስ ለመፈለግ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን ጐብኝቷል። ይሁን እንጂ ምንም ያህል አልተሳካለትም። በዚያ ጽሑፍ ውስጥ አሁን ያነበበው ነገር አስደሰተው። ይህ ጽሑፍ ወዳስተዋወቀው “እስተዲስ ኢን ዘ እስክሪፕቸርስ” የተሰኘ መጽሐፍ 6 ጥራዞች እንዲላኩለት ጠየቀ። በጉጉት አብዛኛውን ጊዜም እስከሚነጋጋ ድረስ ቁጭ ብሎ ያነባቸው ነበር። አባባ እውነቱን በፍጥነት ተገነዘበ።
ወዲያው በአካባቢው ከሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር መተባበር ጀመረ። ይህም አብዛኛውን ጊዜ መሪ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለገለበት ከ40 ዓመታት በላይ የቆየ ጉድኝነት ነበር። ከወንድሞቹ መካከል ሁለቱና ሦስቱም እህቶቹ እውነትን መቀበላቸው አባቴን አስደሰተው። ከወንድሞቹም አንዱ ለአንዲት ወጣት ረዳት (ሠራተኛ) መሠከረላትና እሷና እህቷ ሁለቱም ሕይወታቸውን ወስነው ተጠመቁ። ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ። አባቴና ወንድሙም እነዚህን ሁለት ወጣት ሴቶች አገቡ።
በቤተሰቤ ውስጥ “በጌታ ምክርና ተግሣጽ” ካደግነው አራት ወንዶች ልጆች አንዱ እኔ ነኝ። (ኤፌሶን 6:4) ወላጆቼ በውስጣችን እውነትን ለመትከል ያላደረጉት ጥረት ባለመኖሩ ደስ ይለኛል። በወቅቱ ወላጆች ለልጆች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሲያስተምሩ የሚረዱ በተለይ ለልጆች ማስተማሪያ የተዘጋጁ ጽሑፎች አልነበሩም። ይሁን እንጂ ዘ ሐርፕ ኦቭ ጐድ በተባለው መጽሐፍ በመገልገል በሳምንት ሁለት ጊዜ የዘወትር የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነበረን። እንደዚሁም የዕለቱን ጥቅስ አዘውትረን እንወያይበት ነበር።—ዘዳግም 6:6, 7፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15
እናቴና አባቴ ለስብሰባዎች ባላቸው አድናቆትና ለአገልግሎት ባላቸው ቅንዓት ጥሩ ምሳሌዎች ነበሩ። አባቴ ከመልካም መንፈሳዊ ብቃቶቹ ሌላ ጥሩ የጨዋታ ለዛ (ቀልድ) አዋቂ ነበርና ይህንንም ለኛ ለልጆቹ አስተላልፎት ነበር። የወላጆቼ ጥረት ጥሩ ውጤቶችን አምጥቷል። አሁን በ60ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ አራቱም ልጆቻቸው ይሖዋን በደስታ እያመለክን (እያገለገልን) ነው።
ወደ አቅኚነት አገልግሎት መግባት
ሚያዝያ 1939 በ16 ዓመት ዕድሜዬ ትምህርቴን ጨረስኩና የዘወትር አቅኚ ሆንኩ። አባቴም በአቅኚነት አገልግሎት ተካፋይ ሆነና የመጀመሪያ ደረጃ ሥልጠና ሰጠኝ። በብስክሌት እየተጓዝን ከቤታችን በሰባት ማይል ርቀት ያሉ ክልሎችን በሙሉ አንድ በአንድ ሸፈንን። በየቀኑ ሁለታችንም 50 ትናንሽ መጻሕፍቶችን ይዘን እንወጣና ሳናበረክታቸው አንመለስም ነበር።
ከሁለት ዓመታት በኋላ ከመጀመሪያዎቹ ልዩ አቅኚዎች መካከል ለመሆንና በብሪታኒያ ውስጥ ለመመደብ መብት አገኘሁ። ይህንን በረከት መቀበል ደስታ ነበር። ይሁን እንጂ አምላካዊ ደስተኛ ቤትን ትቶ መሄድ የሚያስደነግጥ ነበር። በጊዜ ብዛት ከይሖዋ እርዳታ ጋር ለመድኩት።
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በገለልተኝነት ጉዳይ ከሌሎች ወጣት ምሥክሮች ጋር በታሠርኩ ጊዜ የአቅኚነት አገልግሎቴ ተቋረጠ። በዱርሃም እሥር ቤት እንደ ወእ (ወጣት እሥረኛ) ተመደብኩ። ይህም ማለት በብርድ የአየር ጠባይ ወቅት ለየት ያለ ጉዳት የሚያስከትለውን አጭር ሱሪ (ቁምጣ) መልበስ ነበረብኝ ማለት ነው። አሁን በብሪታኒያ የቅርንጫፍ ቢሮ አስተባባሪ የሆነው ዊልፍ ጉች የብሪታንያ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል የሆነው ፒተር ኤሊስ፣ ፍሬድ አዳምስ እና እኔ (ሁላችንም የስድስት ጫማ እርዝማኔ ያለን) እንደተማሪዎች ቁምጣ ለብሰን በአንድ ላይ ቆመን እስቲ ይታያችሁ!
ምድብ—በአየርላንድ
ከእሥር ቤት ከተለቀቅሁ በኋላ ለሦስት ዓመታት ያህል በተለያዩ የኢንግላንድ ክፍሎች በአቅኚነት አገለገልኩ። ከዚያም በኋላ ፈታኝም አርኪም ሊሆን የበቃ በአየርላንድ ሪፑብሊክ ተደለደልኩ። ስለ አየርላንድ የማውቀው ነገር ቢኖር ሁሉም ሰው ለማለት የሚያስደፍር ያህል ማንኛውም ሰው የሮማ ካቶሊክ እምነት ተከታይ መሆኑን ነበር። ይሁን እንጂ በአንዳንዶች የተሰጠውን አስተያየት ችላ አልኩና ድልድሌን ከመቀበል አላመነታሁም። ወቅቱ የእውነተኛ አምልኰ መስፋፊያ ስለነበረ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንደሚረዳኝ እርግጠኛ ነበርኩ።
በአየርላንድ ሪፑብሊክ የሚኖሩ ምሥክሮች አንድ ወይም ሁለት ብቻ ተበታትነው ሲኖሩ አብዛኞቹ በዋና ከተማው በዱብሊን ይኖሩ ነበር። ስለዚህ አብዛኛው ሕዝብ አንድም የይሖዋ ምሥክር አይቶ አያውቅም ነበር። ከሌሎች ሦስት ልዩ አቅኚዎች ጋር በኮርክ ከተማ ሥራ ጀመርኩ። አድማጭ ጆሮ ማግኘት ቀላል አልነበረም። በቅዳሴያቸው ጊዜ ቀሳውስቱ እኛን “ኮሚኒስት ዲያብሎሶች” ብለው በመጥራት ያለማቋረጥ ሕዝቡን ያስጠነቅቁ ነበር። ጋዜጦችም ሥራችንን (እንቅስቃሴያችንን) በመቃወም (ሕዝቡን) ያስጠነቅቁ ነበር።
አንድ ቀን አንድ ፀጉር አስተካካይ በረዥም ምላጩ ፀጉሬን ይከረክም ነበር። በጨዋታ ላይ በኮርክ ምን እየሠራሁ እንዳለሁ ጠየቀኝ። ስነግረው በጣም ተናደደና ዘለፈኝ። እጁ በንዴት ይንቀጠቀጥ ነበርና ራሴን በክንዶቼ ሸጉጬ ከሱቁ መውጣት ብቻ ታየኝ! ከዚያ በአንዴ ውልቅ ብሎ መውጣት እንዴት እፎይታ ነበር!
የሕዝብ ረብሻ
አንዳንዴ ሕዝባዊ አመጽ ያጋጥመን ነበር። ለምሳሌ መጋቢት 1948 አንድ ቀን ባልንጀራዬ ፍሬድ ካፊን በረብሻ በተደበደበበት ወቅት ከቤት ወደ ቤት በማገልገል ላይ ነበርን። ሕዝቡ እያሳደደው ወደ አውቶብስ ተራ ሮጦ በመግባት የአውቶብሱን ሾፌርና ረዳቱን ዕርዳታ ጠየቀ። እነሱም በመርዳት ፋንታ በድብደባው ተባበሩበት። ፍሬድ ከዚያ ሮጠና ርቆ በሚገኝ የአንድ ቄስን ቤት በሚያዋስን አንድ ትልቅ አጥር አጠገብ ለመደበቅ ቻለ።
በዚያን ሰዓት እኔ ብስክሌቴን ላመጣ ሄጄ ነበር። ወደ ከተማው ማዕከል ለመድረስ በተገንጣይ መንገድ ሄድኩ። ወደ ዋናው መንገድ ስደርስ ለካስ ረብሸኞቹ ይጠብቁኝ ነበር። ሁለት ሰዎች ቦርሳዬን ነጠቁና በውስጡ የነበሩትን ነገሮች ወደ ሰማይ በተኗቸው። ከዚያም በቡጢና በእርግጫ ይመቱኝ ጀመር። አንድ ነጭ ለባሽ ፖሊስ ድንገት ደረሰና እኔንና አጥቂዎቼን ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ ከመማታት አቆማቸው።
ይህ ድብደባ (ጥቃት) “ወንጌልን መመከቻና መጽኛ ለማድረግ” (ለወንጌል ለመመከትና በሕግ ለማስከበር) መሠረት ለመጣል አስችሏል። (ፊልጵስዩስ 1:7) ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት በመጣ ጊዜ ራሱም የሮማ ካቶሊክ የሆነው ያ ፖሊስ መሠከረልኝና ስድስት ግለሰቦች ለድብደባ ወንጀላቸው ተፈረደባቸው። ይህ ጉዳይ እኛ ከቤት ወደ ቤት ለመሄድ መብት እንዳለን ከማሳየቱም ሌላ (በእኛ ላይ) ኃይል ሊጠቀሙ ለሚያስቡ ሁሉ እንደመከላከያ (ማስፈራሪያ) ሆኗል።
በመጀመሪያ ላይ እንደ ኮርክ ዓይነቶቹ ቦታዎች እህቶችን በአቅኚነት መላክ በጣም አደገኛ እንደሆነ ታስቦ ነበር። ይሁን እንጂ ፍላጎት ያሳዩ ሴቶችን እህቶች ቢጐበኟቸው የተሻለ እንደሚሆን ይታሰብ ነበር። በመሆኑም ከዚህ ጥቃት (ድብደባ) ትንሽ ቀደም ብሎ ማህበር ሁለት መልካም አቅኚ እህቶችን ወደ ኮርክ ልካ ነበር። አንደኛዋ በኋላ ሚስዮናዊት ሆና በቺሊ ግሩም ሥራ ያከናወነች ኢቪሊን ማክፈርሌን ናት። ሌላዋ በአየርላንድ አቅኚ ለመሆን ብላ በለንደን የነበራትን ቤት የሸጠችው ካሮሊን ፍራንሲስ ስትሆን (በኋላ) ሚስቴ ሆነች።
የእውነት ዘሮች በቀሉ
በእንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሥር የመንግሥቱን ዘሮች መዝራታችን ጊዜ ማባከን ነው ብሎ ማሰብ ቀላል በሆነ ነበር። እውነት እዚህና እዚያ ሲበቅል ማየቱ ግን ነገሮችን ለማብቀል ባለው የይሖዋ ኃይል የነበረንን ትምክህት ጠብቆልናል። ለምሳሌ ያህል አንድ ጊዜ ማህበር እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን የሚለውን መጽሐፍ ለመጠየቅ ደብዳቤ ጽፎላት የነበረውን ሰው ስምና አድራሻ ላከችልን። አድራሻው ከኮርክ ከተማ 22 ማይሎች ርቃ ከምትገኘው ፈርሞይ የምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ነበር። ስለዚህ ይህን ሰው ለመፈለግ አንድ እሁድ በቢስክሌቴ ወደዚያ ሄድኩ።
ፈርሞይ ስደርስ አንድ ሰው እንዲያመለክተኝ ጠየቅሁት “እሱማ ገና ዘጠኝ ማይል ከተጓዝክ በኋላ ነው ያለው” አለኝ። እዚያም ሄድኩና በመጨረሻ ትንሽ የገጠር መንገድ ወረድ ብሎ የሚገኝ እርሻ ጋ ደረስኩ። መጽሐፉ እንዲላክለት ጽፎ የነበረው ወጣት ሰው ከእርሻው በር ላይ ቆሞ ነበር። ራሴን ሳስተዋውቀው እንዲህ አለ፦ “ያ መጽሐፍ በክብደቱ ልክ ወርቅ ሊያወጣ የሚገባው ነው።” መልካም ውይይት አደረግን። ከዚያ 30 ማይል ወደቤቴ በብስክሌቴ ስመለስ ርቀቱን እምብዛም አላሰብኩትም። አሁንም እንኳን ከ40 ዓመታት በኋላ ያንን “ወጣት” ሰው ቻርለስ ሪንን በታላላቅ ስብሰባዎች በየዓመቱ ሳገኘው በጣም ደስ ይለኛል። ዛሬ በኮርክ አካባቢዎች አሥር ጉባኤዎች አሉ።
በ1950ዎቹ ካሮሊንና እኔ በአየርላንድ ማዕከላዊ ቦታዎች የእውነትን ዘሮች በተንን። በ1951 “ግራኒ” ሀሚልተንና ምራቷን የመሳሰሉ ቅን ሰዎች በፍጥነት ምላሽ በሰጡ ጊዜ ለመጽናት ማበረታቻ መጣልን፤ “ግራኒ” ሀሚልተን ሎንግ ፎርድ በተባለው ገጠር የመጀመሪያዋ የተጠመቀች አስፋፊ ሆነች።—1 ተሰሎንቄ 2:13
የማረፊያ ቦታዎች ችግር ነበረብን፤ በመሬት ከበርቴዎቹ ላይ ተጽዕኖ ሲደረግባቸው ወዲያውኑ እንድንለቅ ጠየቁን። ስለዚህ ሦስት ማረፊያ ቦታዎችን ወዲያው ወዲያው በተከታታይ ስላስለቀቁን የመሬት ንጣፍ ያለው ድንኳንና የመኝታ ከረጢት ገዛንና “Y” ሞዴል በሆነች ፎርድ መኪና ይዘን እንዞር ጀመር። የዕለቱን ምስክርነታችንን ባበቃንበት ማንኛውም ቦታ ድንኳናችንን እንተክል ነበር። በኋላ 13 ጫማ ርዝመት ያለው ተሳቢ አገኘን። ጥቂት ዘመናዊ ምቾቶች ያሉት ትንሽ ተሳቢ ነበር። የሚጠጣ ውሃ ለማግኘት ሩብ ማይል እንጓዝ ነበር። የሙቀት መከላከያም አልነበረንም። ይሁን እንጂ (ይህ ተሳቢ) ለእኛ የቅንጦት ዕቃ ነበር። አንድ ቀን አንድ ዝናብ የመታው የዛፍ ሥር አድጦኝ በጣም ጥልቅ ባይሆንም ረዥምና ጠባብ ጉድጓድ (የውሃ) ውስጥ ወደኋላዬ ስወድቅ ቀልደኛነቴ ፈተና ደርሶበት ነበር። እንደዚያም ሆኖ በዚያው ተሳቢ ውስጥ የክልል የበላይ ተመልካቹና ሚስቱ ሊጐበኙን በመጡ ጊዜ አስተናገድን።
አንዳንድ ጊዜ ደጋግ ሰዎች ያልተጠበቀ ደግነት ያሳዩ ነበር። ለምሳሌ በ1958 በምዕራብ አየርላንድ ወደምትገኘው ስሊጐ የምትባል ቦታ (ከተማ) ሌላ ባልና ሚስት አቅኚዎች ከተባረሩ ከስምንት ዓመታት በኋላ ሄድን። ተሳቢያችንን የምናቆምበት ቦታ እንድናገኝ ይሖዋ እንዲረዳን ጸለይን። ከብዙ ሰዓቶች ፍለጋ በኋላ አንድ ትልቅ ያልተሠራበት የድንጋይ መፍለጫ ቦታ አገኘን። ከእግር መንገዱ ወረድ ብሎ ከብት የሚጠብቅ ሰው የድንጋይ መፍጫ ቦታው ንብረትነት የሱ ቤተሰብ መሆኑን ነገረን። የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ወኪሎች መሆናችንን ነገርነውና “ልንጠቀምበት እንችላለንን?” ብለን ጠየቅነው። ልንጠቀምበት እንደምንችል ነገረን።
“የየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ወኪሎች ናችሁ?” ብሎ በጠየቀን ጊዜ ለአንዳፍታ ሰግተን ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆንን ነገርነው። ግን የወዳጅነት አቀራረቡን ስላለወጠብን ታላቅ እፎይታ አገኘን። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ለቦታው የዓመት ኪራይ ደረሰኝ ሰጠንና እንዲህ አለን፦ “ምንም ገንዘብ አንፈልግም ግን እናንተ ሰዎች (የይሖዋ ምሥክሮች) የሚያጋጥማችሁን ተቃውሞ ስለምናውቅ ማንም ሰው እዚህ ቦታ ለመሆን ያላችሁን መብት የሚጠይቅ ቢኖር ይህ ማስረጃ ይሁናችሁ።”
እስሊጐ በነበርንበት ጊዜ አንድ የታወቀ ባለሱቅና እግር ኳስ ተጫዋች የሆነ ሰው የበፊቶቹ አቅኚዎች በከተማው በነበሩበት ጊዜ ፍላጐት ያሳየ ሰው እንዳለ ሰማን። ለስምንት ዓመታት (ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር) የነበረው ግንኙነት በጣም ጥቂት ነበር። ታዲያ አሁንስ እንዴት ይሆን ብለን አሰብን። ራሴን ሳስተዋውቀው በማቲበርን (ሰውየው) ፊት ላይ የታየው የሚያበራ (አንጸባራቂ) ፈገግታ መልሱን ሰጠን። ከዓመታት በፊት የተዘሩት የእውነት ዘሮች አልደረቁም ነበር። አሁንም በስሊጐ የሚገኘው አነስተኛ ንቁ ጉባኤ አባል ነው።
የተለየ አመለካከት
ብዙዎች ለእኛ የነበራቸው ተቃራኒ አመለካከት አብነት የሆነችው አንዲት ቦታ የአትሎን ከተማ ነበረች። በ1950 በዚያ ቦታ የተጠናከረ ምሥክርነት በተጀመረ ጊዜ ቀሳውስት በአንዱ የከተማይቱ ክፍል ለሚኖሩ ሁሉ የይሖዋ ምስክሮችን እንደማይፈልጉ የሚናገር አቤቱታ ላይ እንዲፈርሙ አደረጉ። ይህንኑም (አቤቱታ) ወደ መንግሥት ላኩ። ያም ለጥቂት ዓመታት ሥራውን በአትሎን መካሄድ በጣም አስቸጋሪ አደረገው። አንድ ወቅት የወጣቶች ቡድን የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ሲገነዘቡ ድንጋይ ይወረውሩብኝ ጀመር። ወደ አንድ ሱቅ በመስኰት ተጠግቼ ስቆም ባለቤቱ እኔን ለማዳን ብሎ ሳይሆን ይበልጡን መስኰቱን ለማዳን ሲል ወደ ውስጥ አስገባኝና በኋላ በር አስወጥቶ ሰደደኝ።
ይሁን እንጂ በቅርቡ በነሐሴ 1989 በአንቶን ከተማ ለአንድ ታማኝ ወንድም ቀብር ሥነ ሥርዓት ንግግር ሳደርግ ይሖዋ ነገሮችን እንዴት እንዲያድጉ እንዳደረጋቸው በጣም ተገረምኩ። ከጉባኤው አባሎች በተጨማሪ 50 የሚሆኑ የአካባቢው ሕዝብ ወንድሞች በሠሩት መልካም የመንግሥት አዳራሽ የተሰጠውን የቀብር ሥነ ሥርዓት ንግግር ሲደረግ በአክብሮት አዳመጡ።
በጊልያድ ትምህርት ቤት ልዩ ሥልጠና
በ1961 በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ10 ወር ትምህርት እንድከታተል ተጋበዝኩ። ይህ ልዩ ትምህርት የተዘጋጀው ለወንድሞች ብቻ ስለነበር ካሮሊንና ይህን ግብዣ በጸሎት ልናስብበት አስፈለገን። ለ12 ዓመታት ተለያይተን አናውቅም። ከዚህም በላይ ሚስቴ ራሷም የጊልያድ ትምህርት ቤት ለመከታተልና ሚስዮናዊት ለመሆን ልባዊ ፍላጎት ነበራትና ባለመጋበዟ በጣም አዘነች። ይሁን እንጂ አእምሮ ሰፊ በመሆኗ የመንግሥቱን ፍላጐት በማስቀደም መሄድ እንዳለብኝ ተስማማች። ትምህርቱ አስደናቂ መብት ነበር። ሆኖም ወደቤት መመለሴና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ በአየርላንድ ይተክሉና ያጠጡ ለነበሩት 200 ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑ ምሥክሮችን ለማበረታታት በማህበሩ የቅርንጫፍ ቢሮ ሥራ መጠመዴ አስደሳች ነበር።
ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ1979 ለቅርንጫፍ ኰሚቴ አባሎች የተዘጋጀ ልዩ የጊልያድ ትምህርት (ሥልጠና) በተጋበዝኩ ጊዜ ካሮሊንም ወደ ኒውዮርክ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አብራኝ ሄደች። እሷም ከዚያ በኋላ ሁለት ዓመት ቆይታ ስለሞተች ያ ጊዜ የሕይወቷ መጨረሻ የደመቀ ክፍል ሆነ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አብረን ባገለገልንባቸው 32 ዓመታት በሙሉ ካሮሊና ለይሖዋ አገልግሎት የነበራትን ቅንዓት ወይም ነገሮችን እንዲያድጉ እንደሚያደርግ የነበራትን እምነት አጥታ አታውቅም።
በጣም ናፈቅኋት። ለመጽናናት የረዳኝ አንድ ነገር በወቅቱ በንቁ! መጽሔት ላይ (የካቲት 8, 1981) የወጣ “የምታፈቅሩትን ሰው ስታጡ ያለሱ(ሷ) መኖርን መማር” የሚል ርዕሰ ትምህርት ነበር። ያጣኋትን ጓደኛ ባሰብኩ ቁጥር እንባዬ ይመጣል። ይሁን እንጂ ያ ርዕሰ ትምህርት ያቀረበውን ሐሳብ በሥራ በማዋል በይሖዋ አገልግሎት ሥራ የሚበዛልኝ ሆኜ ቀጠልኩ።
የይሖዋ በረከት ቀጠለ
ከዚህ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ማለትም በ1980 የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ወንድም ሊማን ስዊንግል በደብላን አዲስ የቅርንጫፍ ሕንፃ መርቆ ሲከፍት ተገኝቼ ነበር። በዚያ ጊዜ ሰሜናዊውን አየርላንድ ጨምሮ በመስኩ 1,854 አቅኚዎች ማየት እንዴት ያስደስት ነበር! አሁን ደግሞ አሥር ዓመት ቆይቶ ለ1990 የዓመቱ መጽሐፍ ከፍተኛው የአስፋፊ ቁጥር 3,451 እንደደረሰ ይገልጻል።
በመሃሉ ተጨማሪ በረከትም አገኘሁ። በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት መምህርነት ሳገለግል ርዳታ ይበልጥ በሚያስፈልግበት በአየርላንድ ለማገልገል መጥታ የነበረች የምታምርና ቀናተኛ እህት የሆነችውን ኢቪሊን ሀልፎርድን አገኘሁ። ግንቦት 1986 ተጋባንና በአምላካዊ እንቅስቃሴዬ ሁሉ እውነተኛ ድጋፍ ሆነችኝ።
ትምህርት ከጨረስኩ ጀምሮ ካሳለፍኳቸው 51 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዓመታት ውስጥ 44ቱ ያለፉት በአየርላንድ ነው። እኔ የረዳኋቸውን ብዙዎቹን አሁንም ይሖዋን ሲያገለግሉ አንዳንዶችም ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ሆነው ማየት ልብን በደስታ የሚያሞቅ ነው። አንድ ሰው ሊኖረው ከሚችለው ደስታ ሁሉ የበለጠው ሌላውን ሰው በሕይወት መንገድ ላይ እንዲሄድ መርዳት ነው ብዬ ያለ ማመንታት መናገር እችላለሁ።
ከባድ ተቃውሞ ቢኖርም በአየርላንድ እውነተኛ አምልኰ በስፍራው ሁሉ ሲያብብ ማየት እምነትን የሚያጠነክር ነው። ዛሬ በአገሪቱ በሙሉ 3,500 የሚያህሉ አስፋፊዎች ከ90 በላይ ከሆኑ ጉባኤዎች ጋር ይተባበራሉ። እውነትም ይሖዋ ሊያደርገው ለሚችለው ነገር ወሰን የለውም። እኛ በትጋት ከተከልንና ካጠጣን እርሱ ነገሮችን ያሳድጋቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 3:6, 7) ይህ እውነት መሆኑን አውቃለሁ። በአየርላንድ ሲፈጸምም አይቻለሁ።