የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w93 2/1 ገጽ 25-29
  • አምላክን በማገልገል እርካታ አግኝቻለሁ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አምላክን በማገልገል እርካታ አግኝቻለሁ
  • መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሃይማኖታዊ አስተዳደጌ
  • የሕይወት ለውጥ
  • ቤተሰቤና ሌሎችም ጥሩ ምላሽ ሰጡ
  • አዲስ ሥራ
  • በሊሶቶና በቦትስዋና ማገልገል
  • ማስተማርና መተርጎም
  • “የደወልሽው ቁጥር የተሳሳተ ነው”
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ከይሖዋ ድርጅት ጋር ማደግ
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ሳታቋርጡ ዝሩ ይሖዋ እንዲበቅል ያደርገዋል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1991
መጠበቂያ ግንብ—1993
w93 2/1 ገጽ 25-29

አምላክን በማገልገል እርካታ አግኝቻለሁ

ጆሹዋ ቶንግዋና እንደተናገረው

በ1942 በጣም ግራ ተጋብቼ ነበር። በሰባተኛው ቀን አክባሪ አድቬንቲስቶች የሚዘጋጁና በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚዘጋጁ ጽሑፎችን እከታተል ነበር። እንደ ጥንቶቹ እሥራኤላውያን “በሁለት አሳብ እያነከስኩ ነበር።” — 1 ነገሥት 18:​21

የሰባተኛው ቀን አክባሪ አድቬንቲስቶች “የትንቢት ድምፅ” በሚል ርዕስ የሚታተሙ ትምህርታዊ ንግግሮችን ይልኩልኝ ነበር። ጥያቄዎቻቸውን መመለስ ደስ ይለኝ ነበርና በፈተናዎቹ በሙሉ ካለፍኩ ጥሩ የምስክር ወረቀት እንደሚሰጡኝ ቃል ገብተውልኝ ነበር። “የትንቢት ድምፅ” እና የመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ሁለቱም የሚላኩልኝ ከደቡብ አፍሪካው የኬፕ ከተማ መሆኑን ተገነዘብኩ። ‘እነዚህ ድርጅቶች እርስ በርሳቸው ይተዋወቁ ይሆን? ትምህርቶቻቸውስ እርስ በርሳቸው ይስማሙ ይሆን? የማይስማሙ ከሆነ ደግሞ ትክክለኛው ማንኛው ነው?’ በማለት ራሴን እጠይቅ ነበር።

ለጉዳዩ እልባት ለማግኘት ስል ለሁለቱም ድርጅቶች ተመሳሳይ ደብዳቤዎችን ጻፍኩላቸው። ለምሳሌ ያህል ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር “‘የትንቢት ድምፅ’ የሚባለውን ትምህርት የሚያዘጋጁትን ሰዎች ታውቋቸዋላችሁን? ካወቃችኋቸው ደግሞ ስለሚያስተምሩት ነገር ምን ትላላችሁ?” በማለት ጻፍኩ። ከጊዜ በኋላ ከሁለቱም ቡድኖች መልስ አገኘሁ። ከመጠበቂያ ግንብ የመጣልኝ መልስ “የትንቢት[ን] ድምፅ” እንደሚያውቁትና ሥላሴ እና ክርስቶስ ወደ ምድር የሚመለሰው በሥጋው ነው የሚለውን የመሳሰሉት ትምህርቶቹ ቅዱስ ጽሑፋዊ እንዳልሆኑ ገለጹልኝ። ደብዳቤያቸውም እነዚህ መሠረተ ትምህርቶች ሐሰት መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ጥቅሶችን የያዘ ነበር።  — ዮሐንስ 14:​19, 28

“የትንቢት ድምፅ” አዘጋጆች የላኩልኝ መልስ “የመጠበቂያ ግንብ ሰዎችን” እንደሚያውቋቸውና በሚያስተምሩት ነገር እንደማይስማሙ የሚገልጽ ነበር። ለምን እንደማይስማሙ ግን ምክንያት አልሰጡም። ስለዚህ የይሖዋ ምስክሮች የሚጠቀሙበት ሕጋዊ ድርጅት የሆነውን መጠበቂያ ግንብ ማኅበርን ለመደገፍ ወሰንኩ። በአሁኑ ጊዜ ከምስክሮቹ ጋር ከተባበርኩ ከ50 ዓመት በኋላ ያንን ትክክልኛ ውሳኔ በማድረጌ ምንኛ ደስተኛ ነኝ!

ሃይማኖታዊ አስተዳደጌ

የደቡብ አፍሪካ ከተማ ከሆነችው ከፔተርዝበርግ በስተምሥራቅ በምትገኘው ማካኜ በምትባል ገጠርማ አካባቢ በ1912 ተወለድኩ። ማካኜ በዚያን ጊዜ በእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር ሥር ስለነበረች እኔም የዚህ ቤተ ክርስቲያን አባል ሆንኩ። ዕድሜዬ አሥር ዓመት ሲሆን ቤተሰቤ የሉተራን በርሊን ሚሲዮን ቤተ ክርስቲያን ወደሚያይልበት አካባቢ ተዛወሩና ወላጆቼም የዚያ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ሆኑ። እኔም ብዙ ሳልቆይ በቁርባን ሥነ ሥርዓት ላይ ለመገኘት፣ እንዲሁም የዳቦ ቁራሽ ለመብላትና ከወይኑ ፉት ለማለት ብቃት አገኘሁ፤ ይሁን እንጂ መንፈሳዊ ፍላጎቴን አላረካል⁠ኝም።

የስምንት ዓመት ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ አባቴ ወደ ኪልነርተን ማሠልጠኛ ተቋም ላከኝና በ1935 የሦስተኛ ዓመት የአስተማሪነት የምስክር ወረቀት ተቀበልኩ። አብረውኝ ከሚሠሩት መምህራን አንዷ ካሮሊን የምትባል ወጣት ሴት ነበረች። ተጋባንና ቆየት ብሎም ካሮሊን ደማሪስ ብለን የጠራናትን ሴት ልጅ ወለደች። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሰህላሌ በሚባል የማማትሻ የገጠር ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሆንኩ። ትምህርት ቤቱ የሚካሄደው በዳች ተሐድሶ ቤተ ክርስቲያን ስለነበረ የዚህ ቤተ ክርስቲያን አባሎች ሆንንና በቅዳሴዎቹ አዘውትረን እንገኝ ነበር። ይህን ያደረግነው የወቅቱ ፋሽን ስለነበረ ነው እንጂ ምንም እርካታ አላመጣልኝም።

የሕይወት ለውጥ

በ1942 አንድ እሁድ ቀን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መዝሙር ስንለማመድ አንድ ነጭ ሰው ፍጥረት፣ ስሙን ማስከበር እና ዝግጅት የተሰኙ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የተዘጋጁ የእንግሊዝኛ መጻሕፍት ይዞ መጣ። መጻሕፍቱ የመጻሕፍት መደርደሪያዬን ያሳምሩልኛል ብዬ በማሰብ በሦስት ሺልንግ ገዛኋቸው። በኋላ ሰውየው ስሙ ቴኔ በሳደንሆት እንደሆነና እርሱም ከይሖዋ ምስከሮች አንዱ መሆኑን ተረዳሁ። በአካባቢያችን ያለው የይሖዋ ምስክር እርሱ ብቻ ነበር። ቴኔ በሚቀጥለው ጊዜ ሊጎበኘኝ ሲመጣ የሸክላ ማጫወቻ ይዞ መጣና በጃጅ ራዘርፎርድ የተሰጡ አንዳንድ ንግግሮችን አሰማኝ። “ወጥመድ እና ማጭበርበር” የተሰኘው ንግግር በጣም አስደሰተኝ፤ ካሮሊንና ጵርስቅላ የተባለችው ከእኛ ጋር የምትኖር እህቴ ግን አልተደሰቱበትም ነበር። ቴኔ ሦስተኛ ጊዜ ሊጠይቀን ሲመጣ ለጓደኞቼም እንዳሰማቸው ሸክላዎቹን ሰጥቶኝ ሄደ።

አንድ ቀን ፍጥረት የተሰኘውን መጽሐፍ ገጾቹን እያገላበጥኩ ስመለከት “ሙታን የት ናቸው?” የሚለውን ርዕስ አገኘሁ። ወደ ሰማይ የሄዱት የሞቱ ሰዎች ነፍሳት ስለሚያገኙት ደስታ ለማወቅ ተስፋ በማድረግ ማንበብ ጀመርኩ። ነገር ግን ከጠበቅሁት በተቃራኒ መጽሐፉ ሙታን በመቃብራቸው ውስጥ እንደሆኑና ምንም አንደማያውቁ የሚገልጽ ነበር። እንደ መክብብ 9:​5, 10 የመሳሰሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይህን ሐሳብ ለመደገፍ ተጠቅሰው ነበር። ሌላው ምዕራፍ “ሙታንን መቀስቀስ” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን ሙታን አንዳች እንደማያውቁና ትንሣኤን እንደሚጠባበቁ ለመግለጽ በማስረጃነት የተጠቀሰው ዮሐንስ 5:​28, 29 ነበር። ይህ የሚያሳምን ነገር ነበር። የሚያረካ ማብራሪያም ነበር።

ያኔ በ1942 “የትንቢት ድምፅ” ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋርጬ ከመጠበቂያ ግንብ ጽሑፎች ስለተማርኳቸው ነገሮች ለሌሎች መናገር ጀመርኩ። ጥሩ ምላሽ ለመስጠት የመጀመሪያ የነበረው በኪልነርተን ማሠልጠኛ ተቋም የክፍል ጓደኛዬ የነበረው ጁዳ ሌትስዋሎ ነበር።

ጁዳና እኔ በፔተርዝበርግ ለአፍሪካውያን ምስክሮች በተዘጋጀው ስብሰባ ለመገኘት 51 ኪሎ ሜትር በብስክሌት ሄድን። ከዚያ በኋላ መንፈሳዊ ወዳጆች ለጎረቤቶቼ የመንግሥቱን መልእክት ለማቅረብ እንድችል እኔን ለመርዳት ከፔተርዝበርግ እስከ ማማትሻ ድረስ አዘውትረው ይመጡ ነበር። በመጨረሻም በ1944 በፔተርስበርግ በተደረገ ሌላ ስብሰባ ላይ ሕይወቴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት ተጠመቅሁ።

ቤተሰቤና ሌሎችም ጥሩ ምላሽ ሰጡ

ካሮሊን፣ ጵርስቅላና ሴት ልጄ ደማሪስ ወደ ዳች ተሐድሶ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸውን ቀጥለው ነበር። ከዚያም አደጋ ደረሰብን። ካሮሊን ጤነኛ ይመስል የነበረውን ሳሙኤል የሚል ስም ያወጣንለትን ሁለተኛ ልጃችንን ወለደች። ነገር ግን በድንገት ታመመና ሞተ። የካሮሊን ቤተ ክርስቲያን ጓደኞች አምላክ ልጁን የወሰደው ከእርሱ ጋር በሰማይ እንዲሆን ፈልጎት ነው ብለው በመናገር ምንም የሚያጽናና ሐሳብ መስጠት የማይችሉ ሆኑ። ካሮሊን በመጨነቅ “አምላክ ልጃችንን ለምን ይወስዳል?” እያለች መጠየቋን ቀጠለች።

የደረሰብን አደጋ ወሬው በፔተርዝበርግ ለነበሩት ምስክሮች ሲደርሳቸው መጡና በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እውነተኛ ማጽናኛ ሰጡን። ካሮሊን “መጽሐፍ ቅዱስ ሰው ስለሚሞትበት ምክንያት፣ ስለ ሙታን ሁኔታና ስለ ትንሣኤ ተስፋ የሚናገረው አሳማኝ ነው፣ እኔንም በጣም አጽናንቶኛል። በአዲሱ ዓለም ለመገኘትና ልጄን ከመቃብር ለመቀበል ፍላጎት አድሮብኛል” በማለት የተሰማትን በሌላ ጊዜ ገልጻለች።

ካሮሊን ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዷን አቆመችና በ1946 እርሷ፣ ጵርስቅላና ጁዳ ሦስቱም ተጠመቁ። ጁዳ ወዲያው እንደተጠመቀ ማማህሎላ በሚባል ገጠርማ ቦታ የስብከት ሥራውን ለመጀመር ሄዶ፤ እስከአሁንም ድረስ በሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋይነት በማገልገል ቀጥሏል።

ጁዳ ሲሄድ ቦይኔ በመባል የተጠራውን ጉባኤያችንን ለማካሄድ የቀረሁት ወንድ እኔ ብቻ ነበርኩ። በኋላም ግራስሊ ማትላቲዬ የሚባል ወንድም ወደ ክልላችን ተዛውሮ መጣና ከጊዜ በኋላ እህቴን ጵርስቅላን አገባ። በየሳምንቱ ግራስሊና እኔ የአካባቢው የአፍሪካ ቋንቋ በሆነው በሴፔዲ የሕዝብ ንግግር በየተራ እንሰጥ ነበር። ለሰዎቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማቅረብ ማኅበሩ ጽሑፎችን ወደ ሴፔዲ ቋንቋ እንድተረጉም ጠየቀኝ። ሰዎች ከዚህ ጽሑፍ ጥቅም ሲያገኙ ማየቴ ታላቅ እርካታ አመጣልኝ።

የሕዝባዊ ስብሰባ ዘመቻችንን ለማፋፋም በክልሉ በሙሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግሮችን ለማሰማት ትልቅ የድምፅ ማጉሊያ ያለው መሣሪያ ገዛን። ይህን ከባድ ዕቃ ከቦታ ወደ ቦታ ለማጓጓዝ በአህያ የሚጎተት ጋሪ ተዋስን። በዚህም ምክንያት ጎረቤቶቻችን “የአህያው ቤተ ክርስቲያን ሰዎች” የሚል ቅጽል ስም አወጡልን።

ትንሹ ጉባኤያችን ማደጉን ቀጠለ። ከጊዜ በኋላ ሁለቱ ታላቅ እህቶቼና ባሎቻቸው ምስክሮች ሆኑና እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ታማኞች ሆነው ኖሩ። በተጨማሪም አሁን ምፖኮዴበ በመባል ከተሰየመው የቦይኔ ጉባኤ ብዙዎቹ የሙሉ ጊዜ የወንጌላዊነት አገልግሎትን ጀመሩና የሚበዙቱ እስካሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በዚህ የተበታተኑ የገጠር መንደሮች ባሉበት ሠፊ አካባቢ ሁለት ጉባኤዎች ያሉ ሲሆን በድምሩ ከ70 በላይ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ በንቃት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

አዲስ ሥራ

በ1949 በትምህርት ቤት ማስተማሬን ተውኩና የዘወትር አቅኚ አገልጋይ ሆንኩ። የመጀመሪያው ምድቤ በትራንስቫል በሚገኘው በቫልዎተር አካባቢ የነጮች ይዞታ በሆኑ እርሻዎች ላይ ተቀጥረው ለሚሠሩ ጥቁሮች መመስከር ነበር። አንዳንዶቹ ነጭ ባለመሬቶች በዚያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለውን አዲስ የአፓርቴይድ ፖሊሲ ስለተቀበሉ ጥቁሮች ከነጮች የበታች መሆናቸውን አምነው መቀበልና ለነጮች ማገልገል አለባቸው የሚለውን እምነት አጥብቀው ለመደገፍ ቆርጠው ተነሱ። ስለዚህ ለጥቁር የቀን ሠራተኞች ስሰብክላቸው አንዳንድ ነጮች ጥቁሮቹ ለነጮች እንዳይታዘዙ የምሰብክ መስሎአቸው ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ኮሚኒስት ነህ ብለው በመወንጀል እንገድልሃለን ብለው ዛቱ⁠ብኝ።

ሁኔታውን ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቢሮ ሪፖርት አደረግሁና ወዲያውኑ ዳወልስክሉፍ ወደሚባል ሌላ ገጠርማ ቦታ ተዛወርኩ። በዚሁ ጊዜ አካባቢ ሚስቴም የማስተማር ሥራዋን ተወችና ከእኔ ጋር በአቅኚነት ሥራ መካፈል ጀመረች። በ1950 አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ከአገልግሎት ስንመለስ ከማኅበሩ የተላከ አንድ ትልቅ ኤንቬሎፕ አገኘን። ደብዳቤው እኔ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ለመሆን ሥልጠና እንድቀበል የተጋበዝኩበት መሆኑ በጣም አስገረመን። በደቡብ አፍሪካ ለሦስት ዓመት ጉባኤዎችን ከጎበኘን በኋላ በ1953 ከውቅያኖስ አካባቢ ርቆ በመሬት በታጠረ የደቡብ አፍሪካ ማዕከላዊ ምድር በሊሶቶ እንድናገለግል ተመደብን።

በሊሶቶና በቦትስዋና ማገልገል

በሊሶቶ ማገልገል ስንጀምር ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓትን ለመፈጸም ሲባል ለመገደል ዒላማ የሚሆኑት እንግዶች ናቸው የሚል ብዙ ወሬ ነበር። ጉዳዩም ሚስቴንና እኔን አሳሰበን፤ ነገር ግን የሶቶ ወንድሞቻችን ፍቅርና እንግዳ ተቀባይነት እንዲህ ዓይነቱን ፍርሃት ወዲያውኑ እንድንረሳ ረድቶናል።

በሊሶቶ ማሉቴ ተራራዎች የሚገኙ ጉባኤዎችን በማገለግልበት ጊዜ እስክመለስ ድረስ ሚስቴ በቆላው ምድር የአቅኚነት አገልግሎቷን እያከናወነች እንድትጠብቀኝ እየተውኩአት በአይሮፕላን እሄድ ነበር። በተራራዎቹ ላይ ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው ስሄድ መንገድ እንዳይጠፋኝ ወንድሞች በደግነት ይረዱኝ ነበር።

አንድ ጊዜ ወደሚቀጥለው ጉባኤ ለመድረስ የኦሬንጅን ወንዝ በፈረስ መሻገር እንዳለብን ተነገረኝ። የተቀመጥኩበት ፈረስ ገራም እንደሆነ ቢያረጋግጡልኝም ፈረሶች የወንዝ ወኃ ሲያይልባቸው ሸክማቸውን ለማራገፍ እንደሚሞክሩ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶኝ ነበር። ፈረስ የመጋለብም ሆነ የመዋኘት ጥሩ ችሎታ ስለሌለኝ ፈራሁ። ወዲያውም ወደ ወንዙ ደረስንና ውኃው ደግሞ ሞልቶ እስከኮርቻው ደረሰ። በጣም ከመፍራቴ የተነሳ ልጓሙን ለቅቄ የፈረሱን ጋማ ጨምድጄ ያዝኩኝ። በሰላም ተሻግረን ወዲያው ማዶ ስንደርስ ምን ያህል እፎይ አልን!

በዚያ ዕለት ማታ በፈረስ በመሄዴ ምክንያት ሰውነቴ በጣም ቆስሎ ስለነበር እንቅልፍ ሊወስደኝ አልቻለም። ቢሆንም ወዳጆቻችን ለጉብኝታችን ታላቅ አድናቆት ስላሳዩ ጉዞው ሊደረግ ይገባው ነበር። በሊሶቶ የጉብኝቱን ሥራ ስጀምር ከፍተኛው የአስፋፊዎች ቁጥር 113 ነበር። በአሁኑ ጊዜ ያ ቁጥር ወደ 1,649 ከፍ ብሏል።

በ1956 የስብከት ምድባችን አሁን ቦትስዋና በመባል ወደምትጠራውና ድሮ ግን ቤቹዋናላንድ ፕሮቴክቶሬት ትባል ወደነበረችው ሥፍራ ተለወጠ። ቦትስዋና በጣም ትልቅ አገር ስለሆነች ሁሉም አስፋፊዎች ወዳሉበት ቦታ ሁሉ ለመድረስ ረዥም ርቀት መሸፈን ያስፈልግ ነበር። የምንጓዘው በባቡር ወይም ደግሞ በክፍት የጭነት መኪናዎች ነበር። መቀመጫ ስላልነበረ ከጓዛችን ጋር በወለሉ ላይ ለመቀመጥ እንገደድ ነበር። ብዙውን ጊዜ ወደፈለግንበት ቦታ የምንደርሰው አቧራ ለብሰንና ደክመን ነበር። ክርስቲያን ወንድሞቻችን ምን ጊዜም አቀባበል ያደርጉልንና ደስተኛ ፊታቸው ያነቃቃን ነበር።

በዚያን ጊዜ የማኅበሩ ጽሑፎች በቦትስዋና ታግደው ነበርና ከቤት ወደቤት የምናደርገው ስብከት የሚደረገው በጥንቃቄና የማኅበሩን ጽሑፍ ሳንጠቀም ነበር። አንድ ጊዜ በማፓሻላላ መንደር አጠገብ ስንሠራ ተያዝንና ታሠርን። ለራሳችን መከላከያ ለማቅረብ መጽሐፍ ቅዱስን ገልጠን በማቴዎስ 28:​19, 20 ላይ የተመዘገበውን አነበብንላቸው። አንዳንዶቹ አማካሪዎች በገለጻችን ቢደነቁም አለቃቸው ግን የአካባቢው ምስክሮች እንዲገረፉ አዘዘ። ከዚያ በኋላ በጣም ያስደነቀን ነገር አለቃው እንዲላላና እንዲምረን ቄሱ ስለእኛ መማጸናቸው ነበር። አለቃውም ተስማማ፤ እኛም ተለቀቅን።

ብዙ ስደትና በጽሑፎቻችንም ላይ እገዳ ቢኖርም የመንግሥቱ ሥራ ማደጉን ቀጠለ። ቦትስዋና ስደርስ የነበሩት አስፋፊዎች ከፍተኛ ቁጥር 154 ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ ይህ ቁጥር ወደ 192 ከፍ አለ። በአሁኑ ጊዜ በዚያ ምድር ላይ የሚሰብኩ 777 የይሖዋ ምስክሮች አሉ።

ማስተማርና መተርጎም

ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን ሽማግሌዎች በሚሰለጥኑበት የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት በማስተማር አገለግል ነበር። በኋላም በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት አስተማሪ የመሆን መብት አግኝቻለሁ። ሚስቴና እኔ አልፎ አልፎ በደቡብ አፍሪካው ቅርንጫፍም አገልግለናል። በቅርኝጫፉ በምናገለግልባቸው ወቅቶች እኔ በትርጉም ሥራ ስረዳ ካሮሊን ደግሞ በወጥ ቤት ትሠራ ነበር።

አንድ ቀን በ1969 የቅርንጨፉ የበላይ ተመልካች ፍራንስ ሙለር ወደእኔ መጥቶ “ወንድም ቶንግዋና፣ አንተንና ሚስትህን ቢሮዬ መጥታችሁ ላነጋግራችሁ እፈልጋለሁ” አለኝ። ስንሄድም በ1969 በሎንዶን በተደረገው “ሠላም በምድር ላይ” ዓለም አቀፍ ስብሰባ እንዲገኙ ከተመረጡት ተሰብሳቢዎች መካከል እንድንሆን መመረጣችንን ነገረን። በኢንግላንድና በስኮትላንድ የነበሩ ወንድሞቻችን ባደረጉልን መስተንግዶ ተደሰትን፤ ለዓለም አቀፉ ወንድማማችነት ያለንን አድናቆትም በእጅጉ ጨመረልን።

ላለፉት አራት አሥርተ ዓመታት ካሮሊን በወንጌላዊነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ታማኝ ጓደኛዬ ሆናለች። አንድ ላይ ሆነን ብዙ ደስታዎችንና አንዳንድ ኀዘኖችን አሳልፈናል። ሁለት ልጆቻችንን በሞት ብናጣም ሴት ልጃችን ደማሪስ አድጋ ጥሩ ምስክር ሆናለች። በደቡብ አፍሪካው ቅርንጫፍ በትርጉም ሥራ አገልግላ ነበር።

አሁን በተጓዥነት ሥራውን ለመቀጠል ጤንነታችን አይፈቅድልንም። ስለዚህ ላለፉት ጥቂት ዓመታት በፔተርዝበርግ አቅራቢያ በምትገኝ ሴሸኮ የምትባል የአፍሪካውያን ከተማ ባለው ጉባኤ ውስጥ ልዩ አቅኚዎች ሆነን በማገልገል ላይ ነን። በመሪ የበላይ ተመልካችነት እያገለገልኩ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “በእርካታ መሞላት ከ[ይሖዋ] ፊት ጋር” መሆኑን ይናገራል። እኔም በእርግጥ በደቡባዊ አፍሪካ አምላክን በማገልገል ደስታና እርካታ አግኝቻለሁ።  — መዝሙር 16:​11 አዓት

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በደቡብ አፍሪካ በሴሸኮ ከተማ ሲመሰክሩ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ