“ብሉይ ኪዳን” ወይስ “የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች”?
በአሁኑ ወቅት በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በዕብራይስጥ/አረማይክ እና በግሪክኛ ቋንቋ የተጻፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች “ብሉይ ኪዳን” እና “አዲስ ኪዳን” እያሉ መጥራት የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ በእነዚህ ስሞች ለመጠቀም የሚያስችል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለን? የይሖዋ ምሥክሮች በጽሑፎቻቸው ውስጥ በእነዚህ ስሞች የማይጠቀሙትስ ለምንድን ነው?
እርግጥ ኪንግ ጀምስ ቨርሽንም ሆነ የማርቲን ሉተር የመጀመሪያ ትርጉም እንደሆነው እንደ ጀርመኑ ሴፕተምበርቴስታመንት (1522) ያሉ የቆዩ ትርጉሞች በ2 ቆሮንቶስ 3:14 ላይ ይህን ልማድ የሚደግፉ ይመስላል። ይህ ጥቅስ በኪንግ ጀምስ ቨርሽን እንዲህ ይነበባል፦ “አእምሯቸው ታውሮ ነበር፤ ማለትም ብሉይ ኪዳን ሲነበብ ያ መጋረጃ ሳይወሰድ እስከ ዛሬ ድረስ ይኖራልና፤ በክርስቶስ ብቻ የተሻረ ነውና።”
ይሁን እንጂ ሐዋርያው እዚህ ላይ እየተናገረ ያለው በተለምዶ “ብሉይ ኪዳን” ተብለው ስለሚጠሩት 39 መጻሕፍት ነውን? እዚህ ላይ “ኪዳን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ዲያቴኬ ነው። በስፋት የሚታወቀው ቲኦሎጂሽ ሪአልኤንዚክሎፓዲ የተባለው የጀርመን ሃይማኖታዊ ኢንሳይክሎፔድያ በ2 ቆሮንቶስ 3:14 ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ በዚህ ጥቅስ ላይ የተገለጹት ‘ብሉይ ዲያቴኬ ሲነበብ’ የሚሉት ቃላት በሚቀጥለው ቁጥር ላይ ከተጠቀሱት ‘የሙሴ መጻሕፍት ሲነበቡ’ ከሚሉት ቃላት ጋር ይመሳሰላሉ። ስለዚህ ይህ ጥቅስ ‘ብሉይ ዲያቴኬ’ የሙሴን ሕግ በተለይም አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት እንደሚያመለክት ይናገራል። ከክርስትና በፊት የተጻፈውን ጠቅላላውን የቅዱሳን ጽሑፎች ስብስብ እንደማያመለክት የተረጋገጠ ነው።
ሐዋርያው የጠቀሰው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን አንድ ክፍል ብቻ ማለትም ሙሴ በአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት ላይ የመዘገበውን አሮጌውን የሕግ ቃል ኪዳን ነው፤ የዕብራይስጥንና የአረማይክ ቅዱሳን ጽሑፎችን በሙሉ አልጠቀሰም። ከዚህም በላይ “አዲስ ኪዳን” የሚለው ቃል በመጀመሪያው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በየትም ቦታ ስለማይገኝ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፉትን የክርስቲያን ጽሑፎች “አዲስ ኪዳን” ናቸው ማለቱ አልነበረም።
በተጨማሪም እዚህ ላይ ጳውሎስ የተጠቀመበት ዲያቴኬ የተባለው የግሪክኛ ቃል ትክክለኛ ትርጉም “ቃል ኪዳን” የሚል መሆኑ ሊስተዋል የሚገባው ነው። (ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በ1984 በኒው ዮርክ መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ባለማጣቀሻውን የአዲሲቱ ዓለም የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ገጽ 1585 ተጨማሪ መግለጫ [Appendix] 7E ተመልከት።) ስለዚህ ብዙ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች “ብሉይ ኪዳን” ከመባል ይልቅ “አሮጌ ቃል ኪዳን” ተብለው በትክክል ተተርጉመዋል።
ከዚህ ጋር የሚያያዘው ሦስተኛው ምክንያት “ናሽናል ካቶሊክ ሪፖርተር” “‘ብሉይ ኪዳን’ የሚለው ቃል ዝቅ የሚያደርግና ጊዜው ያለፈበት ነው የሚል ስሜት የሚያሳድር መሆኑ አይቀርም” ሲል የገለጸው ነው። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አንዱም ክፍል ጊዜው ያላለፈበት ወይም “ያላረጀ” አንድ የሥራ ውጤት ነው። መልእክቱ ከመጀመሪያው የዕብራይስጥ ክፍል መጽሐፍ አንስቶ እስከ መጨረሻው የግሪክኛ ክፍል መጽሐፍ ድረስ አንድ ነው። (ሮሜ 15:4፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ስለዚህ በተዛቡ ግምቶች ላይ የተመሠረቱትን እነዚህን ስሞች የማንጠቀምባቸው ተገቢ ምክንያቶች አሉን፤ ይበልጥ ትክክለኛ የሆኑትን “የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች” እና “የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች” የሚሉትን ስያሜዎች ለመጠቀም እንመርጣለን።