ማይሞኒደስ የአይሁድን አምነት መልሶ ያዋቀረው ሰው
“ከሙሴ እስከ ሙሴ ድረስ ሙሴን የሚያተካከል ሰው አልተነሳም።” ብዙ አይሁዶች ይህ እንቆቅልሽ የሆነ አነጋገር በ12ኛው መቶ ዘመን ለነበረው አይሁዳዊ ፈላስፋ፣ አቀናባሪና የታልሙድና የቅዱሳን ጽሑፎች ተንታኝ ለነበረው ለሞሰስ ቤን ማይሞን የተነገረ የአድናቆት መግለጫ እንደሆነ ያውቃሉ፤ ይህ ሰው ማይሞኒደስ እና ራምባም ተብሎም ይጠራል።a በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ማይሞኒደስን አያውቁትም፤ ሆኖም መጣጥፎቹ በአይሁዶች፣ በእስላሞችና በእሱ ዘመን በነበረው የቤተ ክርስቲያን አስተሳሰብ ላይ ትልቅ ተጽእኖ አሳድረዋል። መሠረታዊ ይዘቱን ሳይለቅ የአይሁድን እምነት መልሶ አዋቀረው። ማይሞኒደስ ማን ነው? ብዙ አይሁዶች “ዳግማዊው ሙሴ” እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱትስ ለምንድን ነው?
ማይሞኒደስ ማን ነው?
ማይሞኒደስ በ1135 በኮርዶባ ስፔይን ውስጥ ተወለደ። ገና በልጅነቱ አብዛኛውን ሃይማኖታዊ ሥልጠና የሰጠው አባቱ ማይሞን ከታወቀ የረቢዎች ቤተሰብ የተወለደ የታወቀ ምሁር ነበር። ኮርዶባ በ1148 በአልሞሃዶች እጅ ስትወድቅ አይሁዶች ወይ እምነታቸውን ለውጠው እስላም መሆን አለዚያም መሸሽ ነበረባቸው። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የማይሞኒደስ ቤተሰብ ለረጅም ጊዜያት ሲቅበዘበዝ ቆይቷል። በ1160 ማይሞኒደስ የሕክምና ትምህርቱን በተከታተለበት በፌዝ ሞሮኮ ውስጥ መኖር ጀመሩ። በ1165 ቤተሰቡ ወደ ፍልስጤም መሸሽ ነበረበት።
ይሁን እንጂ በእስራኤል የነበረው ሁኔታ የተረጋጋ አልነበረም። አነስተኛ የሆነው የአይሁድ ማኅበረሰብ ከሕዝበ ክርስትና የመስቀል ጦርነት ተዋጊዎችና ከእስላም ኃይሎች አደጋ ተደቅኖበት ነበር። ማይሞኒደስና ቤተሰቡ “በቅድስቲቷ አገር” ከስድስት ወራት ለሚያንስ ጊዜ ከተቀመጡ በኋላ ቀደም ሲል ፉስታት ተብላ ትጠራ በነበረችው በካይሮ ግብፅ ውስጥ ጥገኝነት አገኙ። የማይሞኒደስ ተሰጥኦዎች ሙሉ በሙሉ የታወቁት በዚህ ቦታ ነበር። በ1177 የአይሁድ ማኅበረሰብ አለቃ ሆነ፤ በ1185 ደግሞ የዝነኛው የእስላሞች መሪ የሳላዲን ቤተሰብ ሐኪም ሆኖ ተሾመ። ማይሞኒደስ በ1204 እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ እነዚህን ሁለት ሹመቶች እንደያዘ ቆይቷል። ልዩ የሕክምና ችሎታው በስፋት በመናኘቱ አንበሳው ሪቻርድ ይባሉ የነበሩት የእንግሊዙ ንጉሥ እንኳ ማይሞኒደስ የግል ሐኪማቸው እንዲሆን ለማድረግ ሙከራ አድርገው እንደነበር ይነገራል።
የጻፈው ምን ነበር?
ማይሞኒደስ ብዙ ጽሑፎችን ለንባብ ያበቃ ጸሐፊ ነው። ኮሜንታሪ ኦን ዘ ሚሽና የተባለውን የመጀመሪያውን ዋነኛ የሥነ ጽሑፍ ሥራውን በአብዛኛው ያጠናቀረው ከእስላሞች ይሰነዘርበት ከነበረው ስደት ይሸሽ በነበረበት ወቅት ነው።b በአረብኛ የተጻፈው ይህ ጽሑፍ አብዛኛዎቹን የሚሽና ጽንሰ ሐሳቦችና ሐረጎች ያብራራል፤ አንዳንድ ጊዜም የያዘውን ርዕስ ለቀቅ በማድረግ ማይሞኒደስ በአይሁድ እምነት ላይ ስላለው ፍልስፍና ይገልጻል። ስለ ሳንሄድሪን በሚገልጸው ሰፊ ክፍል ላይ ማይሞኒደስ መሠረታዊ የሆኑ 13 የአይሁድ እምነት ሥርዓቶችን አስፍሯል። የአይሁድ እምነት በይፋ የሚታወቁ መሠረታዊ ሥርዓቶች አልነበሩትም። ማይሞኒደስ ያወጣቸው 13 የእምነት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከዚያ በኋላ በተከታታይ ለወጡት የአይሁድ እምነት ደንቦች የመጀመሪያ ሞዴል ሆነዋል።—ገጽ 23 ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።
ማይሞኒደስ ማንኛውንም ነገር ቁሳዊውንም ሆነ መንፈሳዊውን ነገር ሁሉ ምክንያታዊ በሆነ ቅደም ተከተል ለማብራራት ሞክሯል። ጭፍን እምነትን አጣጥሏል፤ ለማንኛውም ነገር ምክንያታዊ የሆኑ ማስረጃዎችና ጭብጦች ናቸው ብሎ በሚያምንባቸው ነገሮች ላይ የተመሠረቱ ማብራሪያዎችን ይፈልግ ነበር። ይህ የተፈጥሮ ዝንባሌው ታላቅ እመርታ ያሳየበትን የሥነ ጽሑፍ ሥራ ማለትም ሚሽነህ ቶራህ የተባለውን ጽሑፍ እንዲጽፍ አድርጎታል።c
በማይሞኒደስ ዘመን አይሁዶች “ቶራህ” ወይም “ሕግ” የሚለው ቃል ሙሴ በጽሑፍ ያሰፈረውን ቃል ብቻ ሳይሆን ረቢዎች ለዘመናት ለሕጉ የሰጧቸውን ፍቺዎች ሁሉ የሚያጠቃልል ነው ብለው ያስቡ ነበር። እነዚህ ሐሳቦች በታልሙድና ረቢዎች ባሳለፏቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ብያኔዎች ላይ እንዲሁም ስለ ታልሙድ በጻፏቸው ጽሑፎች ላይ ተገልጸዋል። ማይሞኒደስ እነዚህ ሁሉ ሐሳቦች ያላቸው ስፋትና የተዛባ አቀማመጥ ተራው አይሁዳዊ የዕለት ተዕለት ኑሮውን የሚነኩ ውሳኔዎች ማድረግ እንዳይችል እንዳደረጉት ተገንዝቦ ነበር። ብዙዎቹ ጽሑፎች ከባድ በሆነ የአረማይክ ቋንቋ የተጻፉ ስለነበሩ አብዛኛዎቹ አይሁዶች በሕይወት ዘመናቸው በሙሉ፣ ረቢዎች የጻፏቸውን ጽሑፎች ሁሉ ማጥናት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አልነበሩም። ማይሞኒደስ ያቀረበው መፍትሔ ተግባራዊ የሆኑትን ውሳኔዎች ጎላ ጎላ አድርጎ በማስቀመጥ ይህን ሐሳብ አስተካክሎ ማሳተምና በየርዕሰ ጉዳዩ በመከፋፈል 14 መጽሐፎች አድርጎ ቅደም ተከተሉን በጠበቀ ሁኔታ ማደራጀት ነበር። በጣም ግልጽ በሆነና ምንም በማይዝ የዕብራይስጥ ቋንቋ ጻፈው።
ሚሽነህ ቶራህ እጅግ ተግባራዊ የሆነ መመሪያ በመሆኑ አንዳንድ የአይሁድ መሪዎች ሙሉ በሙሉ ታልሙድን ይተካዋል ብለው ሰግተው ነበር። ያም ሆኖ ግን የተቃወሙት እንኳ ይህ ሥነ ጽሑፍ እጅግ አስደናቂ የሆነ ምሁራዊ ሥራ እንደሆነ አምነው ተቀብለዋል። ይህ በሚገባ የተደራጀ መሠረታዊ ሥርዓት ታላቅ ለውጥ ያመጣ ክንውን ነው። ተራው ሰው ሊገነዘበው ወይም ሊረዳው የማይችለው በነበረው የአይሁድ እምነት ሥርዓት ላይ ነፍስ ዘርቶበታል።
ከዚያም ማይሞኒደስ ዘ ጋይድ ፎር ዘ ፐርፕሌክስድ የተባለ ሌላ ትልቅ ሥነ ጽሑፍ ማዘጋጀት ጀመረ። የግሪክ ሥነ ጽሑፎች ወደ አረብኛ በመተርጎማቸው ብዙ አይሁዶች አርስቶትልንና ሌሎች ፈላስፎችን በደንብ ማወቅ ጀምረው ነበር። አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን ቃላት ቀጥተኛ ትርጉም ከፍልስፍና ጋር ለማስታረቅ በመቸገር ግራ ተጋብተው ነበር። አርስቶትልን በእጅጉ ያደነቀው ማይሞኒደስ ዘ ጋይድ ፎር ዘ ፐርፕሌክስድ በተባለው መጽሐፍ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስንና የአይሁድ እምነትን መሠረታዊ ሐሳብ ከፍልስፍና አስተሳሰብና ጭብጥ ጋር በሚስማማ መንገድ ለማብራራት ሞክሯል።—ከ1 ቆሮንቶስ 2:1–5, 11–16 ጋር አወዳድር።
ማይሞኒደስ ከእነዚህ ታላላቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹና ከሌሎች ሃይማኖታዊ መጣጥፎቹ ሌላ በሕክምናና በሥነ ፈለክ መስክም ጥልቀት ባለው መንገድ ጽፏል። ይህም ቸል ሊባል የማይገባው ሌላው ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራው ገጽታ ነው። ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ የሚከተለውን ሐሳብ ይሰጣል፦ “የማይሞኒደስ ደብዳቤዎች በደብዳቤ አጻጻፍ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፍተዋል። ደብዳቤዎቹ ለረጅም ጊዜ ተጠብቀው የቆዩ የመጀመሪያው አይሁዳዊ ደብዳቤ ጸሐፊ እሱ ነው። . . . ደብዳቤዎቹ የሚጽፍላቸውን ሰዎች አእምሮና ልብ የሚማርኩ ነበሩ፤ የደብዳቤ አጻጻፉን ለሚጽፍላቸው ሰዎች በሚስማማ መንገድ ይለዋውጠው ነበር።”
ማይሞኒደስ ምን አስተምሯል?
ማይሞኒደስ በ13ቱ የእምነት መሠረታዊ ሥርዓቶቹ አማካኝነት ግልጽ የሆኑ የእምነት መግለጫዎችን አቅርቧል፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በቅዱስ ጽሑፉ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ይሁን እንጂ ሰባተኛውና ዘጠነኛው መሠረታዊ ሥርዓቶች በቅዱስ ጽሑፉ ላይ የተመሠረተውን ኢየሱስ መሲሕ ነው የሚለውን እምነት ይቃረናሉ።d እንደ ሥላሴ የመሰሉ የሕዝበ ክርስትናን የክህደት ትምህርቶች እንዲሁም የመስቀል ተዋጊዎች በፈጸሙት የግፍ ጭፍጨፋ ላይ እንደታየው ያለ ገሃድ የወጣ ግብዝነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ማይሞኒደስ ኢየሱስ መሲሕ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጥያቄ ጠለቅ ብሎ አለመመርመሩ አያስደንቅም።—ማቴዎስ 7:21–23፤ 2 ጴጥሮስ 2:1, 2
ማይሞኒደስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ከ[ክርስትና] የበለጠ እንቅፋት የሆነ ነገር ሊኖር ይችላልን? ሁሉም ነቢያት መሲሑ እስራኤልን የሚቤዥና የእስራኤል አዳኝ እንደሆነ ተናግረዋል . . . [በአንጻሩ ግን ክርስትና] አይሁዶች በሰይፍ እንዲገደሉ፣ ቀሪዎቹም እንዲበታተኑና እንዲዋረዱ፣ ቶራህ እንዲለወጥ እንዲሁም አብዛኛው የዓለም ሕዝብ እንዲሳሳትና ከጌታ ይልቅ ሌላ አምላክን እንዲያመልክ አድርጓል።”—ሚሽነህ ቶራህ፣ “ዘ ሎውስ ኦቭ ኪንግስ ኤንድ ዜር ዋርስ” ምዕራፍ 11
ማይሞኒደስ ከፍተኛ ከበሬታ ቢሰጠውም እንኳ ብዙ አይሁዶች ፊት ለፊት በተናገረባቸው አንዳንድ ጉዳዮች ረገድ እሱን ወደ ኋላ ገሸሽ ማድረግን ይመርጣሉ። ከአምላክ ጋር ምሥጢራዊ ግንኙነት ይደረግባቸዋል ተብሎ የሚታመንባቸው ልማዶች የሚፈጸሙበት የአይሁድ እምነት (ካባላህ) እየጎለበተ ሲመጣ በአይሁዶች ዘንድ ኮከብ ቆጠራ ይበልጥ ታዋቂነትን እያገኘ ሄደ። ማይሞኒደስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በኮከብ ቆጠራ ድርጊት የሚካፈልና ሥራውንም ሆነ ጉዞውን ኮከብ ቆጣሪዎች ባወጡት የጊዜ ሰሌዳ ላይ በማስመርኮዝ የሚያቅድ ሰው ከቅጣት አያመልጥም . . . እነዚህ ነገሮች በሙሉ ውሸትና ማታለያ ናቸው . . . በእነዚህ ነገሮች የሚያምን ሁሉ . . . ሞኝና አእሞሮ የጎደለው ነው።”—ሚሽነህ ቶራህ፣ “ሎውስ ኦቭ አይዶላትሪ” ምዕራፍ 11፤ ከዘሌዋውያን 19:26ና ከዘዳግም 18:9–13 ጋር አወዳድር።
ማይሞኒደስ ሌላ ልማድንም እንደዚሁ አጥብቆ ኮንኗል፦ “[ረቢዎች] ከግለሰቦችና ከማኅበረሰቦች የሚቀበሉትን ገንዘብ ደንግገዋል፤ እንዲሁም ሰዎች ይህ ነገር ግዴታና ተገቢ እንደሆነ እንዲያምኑ በማድረግ ያሞኟቸዋል . . . ይህ ሁሉ ስህተት ነው። በቶራህ ውስጥም ሆነ [በታልሙድ ላይ በሚገኘው] ዐዋቂዎች በተናገሩት ነገር ላይ ይህን እምነት የሚደግፍ አንድም ቃል የለም።” (ኮሜንታሪ ኦን ዘ ሚሽና፣ አቮት 4:5) ከእነዚህ ረቢዎች በተቃራኒው ማይሞኒደስ ራሱን ለመደጎም ሐኪም ሆኖ በርትቶ ይሠራ ነበር፤ ለሚያከናውናቸው ሃይማኖታዊ አገልግሎቶች ክፍያ አይቀበልም ነበር።—ከ2 ቆሮንቶስ 2:17ና ከ1 ተሰሎንቄ 2:9 ጋር አወዳድር።
የአይሁድ እምነትና ሌሎች እምነቶች የተነኩት እንዴት ነው?
ኢየሩሳሌም ውስጥ በሚገኘው የዕብራይስጥ ቋንቋ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ያሻይሁ ሊቦቪትስ “ማይሞኒደስ ከዕብራውያን አባቶችና ነቢያት ዘመን አንስቶ እስከ አሁኑ ዘመን ድረስ ባለው የአይሁድ እምነት ታሪክ ውስጥ ታላቅ ተጽእኖ ያሳደረ ዕውቅ ሰው ነው” ሲሉ ገልጸዋል። ኢንሳይክሎፔድያ ጁዳይካ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቷል፦ “ማይሞኒደስ በወደፊቱ የአይሁድ እምነት እድገት ላይ ያሳደረው በጎ ተጽእኖ ይህ ነው የሚባል አይደለም። . . . እንዲያውም ሲ ቺርኖቪትስ . . . ማይሞኒደስ ባይኖር ኖሮ የአይሁድ እምነት ተከፋፍሎ የተለያዩ የእምነት ክፍሎች ይፈጠሩ ነበር . . . የተለያዩ አዝማሚያዎችን አንድ በማድረግ ታላቅ ሥራ ሠርቷል ሲሉ ገልጸዋል።”
ማይሞኒደስ ማንኛውም ነገር ሥርዓቱን የጠበቀና ጭብጥ ያለው መሆን አለበት ከሚለው የራሱ ሐሳብ ጋር በሚስማማ መንገድ የአይሁዶችን አስተሳሰብ እንደገና በማደራጀት የአይሁድን እምነት መልሶ አዋቀረ። ምሁራኑም ሆኑ ብዙሃኑ ሕዝብ ይህ አዲስ ማብራሪያ ተግባራዊና ማራኪ ሆኖ አግኝተውታል። ተቃዋሚዎቹ እንኳ በመጨረሻ አብዛኛውን የማይሞኒደስ አመለካከት ተቀብለውታል። ምንም እንኳ የመጣጥፎቹ ዓላማ አይሁዳውያን ትኩረታቸውን ማብቂያ ከሌላቸው ሐተታዎች ዞር እንዲያደርጉ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ስለ እሱ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ረጃጅም ሐተታዎች ተጽፈዋል።
ኢንሳይክሎፔዲያ ጁዳይካ የሚከተለውን አስተያየት ይሰጣል፦ “ማይሞኒደስ . . . በመካከለኛው ዘመን ከሁሉ በላቀ ሁኔታ በሰዎች ላይ በጎ ተጽእኖ ያሳደረ አይሁዳዊ ፈላስፋ ነበር፤ ጋይድ ኦቭ ዘ ፐርፕሌክስድ የተባለው መጽሐፉም በአንድ አይሁዳዊ የተዘጋጀ ከሁሉ የላቀ ጠቀሜታ ያለው የፍልስፍና ሥራ ነው።” ዘ ጋይድ ፎር ዘ ፐርፕሌክስድ የተባለው መጽሐፍ ምንም እንኳ የተጻፈው በአረብኛ ቢሆንም ማይሞኒደስ በሕይወት እያለ ወደ ዕብራይስጥ ቋንቋ ተተርጉሟል። ከዚያም ብዙ ሳይቆይ በላቲን ቋንቋ ተተርጉሟል፤ ይህም መጽሐፉ በመላው አውሮፓ ለንባብ እንዲበቃ አስችሎታል። በዚህም ምክንያት ማይሞኒደስ የአርስቶትልን ፍልስፍና ከአይሁድ ትምህርት ጋር በማዋሃድ የፈጠረው በዓይነቱ ለየት ያለ የሐሳብ ቅንብር ወዲያውኑ በብዙ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ካለው የሕዝበ ክርስትና አስተሳሰብ ጋር ተቀላቀለ። አልበርተስ ማግነስንና ቶማስ አኩዊናስን የመሰሉ በዚያ ዘመን የነበሩት የሕዝበ ክርስትና ምሁራን ብዙውን ጊዜ የማይሞኒደስን አመለካከቶች ይጠቅሱ ነበር። የእስልምና ምሁራንም የማይሞኒደስ ትምህርት ተጽእኖ አሳድሮባቸዋል። የማይሞኒደስ ፍልስፍናዊ አመለካከት ከእሱ በኋላ የነበሩት እንደ ባሩክ ስፒኖዛ የመሰሉ የአይሁድ ፈላስፎች የጥንቱን ወግና ልማድ ከሚከተለው የአይሁድ እምነት ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን እንዲያገሉ አድርጓቸዋል።
ማይሞኒደስ የሥልጣኔ ዘመን ከመጀመሩ በፊት የኖረ ታላቅ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቅ ሥራ ያከናወነ ብርቱ መንፈስ የነበረው ሰው ተደርጎ ሊታይ ይችላል። እምነት መሠረት ያለው መሆን አለበት የሚለው አባባሉ አሁንም ተገቢ የሆነ መሠረታዊ ሥርዓት ነው። ይህ መሠረታዊ ሥርዓት ሃይማኖታዊ የሆኑ መናፍስታዊ እምነቶችን በመቃወም በኃይለ ቃል እንዲናገር አድርጎታል። ሆኖም የሕዝበ ክርስትና መጥፎ ምሳሌና የአርስቶትል ፍልስፍና ያሳደረበት ተጽእኖ ብዙውን ጊዜ ሙሉ በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር የሚስማሙ መደምደሚያዎች ላይ እንዳይደርስ አድርገውታል። ምንም እንኳ በማይሞኒደስ መካነ መቃብር ላይ ተቀርጾ በሚገኘው “ከሙሴ እስከ ሙሴ ድረስ ሙሴን የሚተካከል አልተነሳም” በሚለው መግለጫ ሁሉም ሰው የሚስማማ ባይሆንም የአይሁድን እምነት አቅጣጫና ይዘት መልሶ እንዳዋቀረው መታመን አለበት።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a “ራምባም” የዕብራይስጥ ምህጻረ ቃል ሲሆን “ራባይ ሞሰስ ቤን ማይሞን” ከሚሉት ቃላት የተወሰደ ስም ነው።
b ሚሽና አይሁዶች የቃል ሕግ በሚሉት ላይ የተመሠረተ የረቢዎች ሰፊ ሐተታ ጥንቅር ነው። በጽሑፍ የሠፈረው በሁለተኛው መቶ ዘመን ማብቂያና በሦስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ እዘአ ላይ ነው። ይህ የታልሙድ የመጀመሪያ ክፍል ሆነ። ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣ ይሆን? የተባለውን የእንግሊዝኛ ብሮሹር ገጽ 10 ተመልከት።
c ሚሽነህ ቶራህ የተባለው ስም ከዘዳግም 17:18 የተወሰደ የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን የሕጉ ቅጂ ወይም ድጋሚ ማለት ነው።
d ኢየሱስ ይመጣል ተብሎ ቃል የተገባለት መሲሕ መሆኑን የሚያሳዩ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ጦርነት የማይኖርበት ዓለም ይመጣ ይሆን? የሚለውን የእንግሊዝኛ ብሮሹር ገጽ 24–30 ተመልከት።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማይሞኒደስ ያወጣቸው 13 የእምነት መሠረታዊ ሥርዓቶችe
1. አምላክ የሁሉም ነገሮች ፈጣሪና ገዥ ነው። ሁሉንም ነገሮች የሠራው፣ እየሠራ ያለውና የሚሠራው እርሱ ብቻ ነው።
2. አምላክ አንድ ነው። እንደ እርሱ ያለ አንድነት ያለው ሌላ የለም።
3. አምላክ አካል የለውም። በሰብዓዊ አስተሳሰብ እርሱን መግለጽ አይቻልም።
4. አምላክ መጀመሪያም መጨረሻም ነው።
5. ለአምላክ ብቻ መጸለይ ተገቢ ነው። አንድ ሰው ለሌላ ለማንም ወይም ለምንም ነገር መጸለይ አይችልም።
6. ነቢያት የተናገሩት ቃል ሁሉ እውነት ነው።
7. ሙሴ የተናገረው ትንቢት ሙሉ በሙሉ እውነት ነው። ከእሱ በፊትም ሆነ በኋላ ከነበሩት ነቢያት ሁሉ የበላይ እርሱ ነው።
8. አሁን በእጃችን ያለው ቶራህ በሙሉ ለሙሴ ተሰጥቶት የነበረው ነው።
9. ቶራህ አይለወጥም፤ አምላክም ሌላ ሕግ አይሰጥም።
10. አምላክ የሰውን ሥራና አሳብ ሁሉ ያውቃል።
11. አምላክ ትእዛዛቱን የሚጠብቁትን ሰዎች ወሮታ ይከፍላቸዋል፤ ትእዛዛቱን የሚጥሱትን ደግሞ ይቀጣቸዋል።
12. መሲሑ ይመጣል።
13. ሙታን እንደገና ሕያው ይሆናሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
e ማይሞኒደስ እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ኮሜንታሪ ኦን ዘ ሚሽና (ሳንሄድሪን 10:1) ላይ አብራርቷቸዋል። ከጊዜ በኋላ የአይሁድ እምነት እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተቀባይነት ያገኙ ደንቦች አድርጎ ወስዷቸዋል። ከላይ ያለው ሐሳብ ከአይሁድ የጸሎት መጽሐፍ ላይ አጠር ተደርጎ የተወሰደ ነው።
[ምንጭ]
Jewish Division / The New York Public Library / Astor, Lenox, and Tilden Foundations