ናክማንዲዝ—የክርስትናን እምነት ውድቅ አድርጓልን?
መካከለኛው ዘመን። ይህ ዘመን ሲነሳ ምን ነገር ትዝ ይላችኋል? የመስቀል ጦርነት? ኢንኩዊዚሽን? ሥቃይ? ምንም እንኳ ነፃ የሆነ ሃይማኖታዊ ውይይት የተደረገበት ወቅት ባይሆንም በዚያን ዘመን ማለትም በ1263 በአውሮፓ ታሪክ በዓይነቱ ልዩ የሆነ በአይሁድና በክርስትና መካከል አንድ ክርክር ተደርጎ ነበር። በክርክሩ ተካፋይ የሆኑት እነማን ነበሩ? ምን አከራካሪ ጉዳዮች ተነስተው ነበር? ክርክሩ ዛሬ እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተን ለማወቅ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
ክርክሩን ያስነሳው ምንድን ነው?
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በመካከለኛው ዘመን በሙሉ ራሷን እንደ እውነተኛ ሃይማኖት አድርጋ ስታቀርብ ቆይታ ነበር። ሆኖም አይሁዶች የአምላክ ምርጥ ሕዝቦች ነን ከሚለው አቋማቸው ፍንክች አላሉም። ቤተ ክርስቲያን አይሁዶች ሃይማኖታቸውን እንዲለውጡ ማሳመን አለመቻሏ ብስጭት ያስከተለባት ከመሆኑም በላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት የኃይል እርምጃ እንድትወስድና ሰዎችን እንድታሳድድ አድርጓታል። በመስቀል ጦርነት ወቅት ከጥምቀት ወይም ከሞት አንዱን እንዲመርጡ ከተጠየቁ በኋላ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አይሁዶች ተጨፍጭፈዋል ወይም በእንጨት ላይ ተሰቅለው ተቃጥለዋል። ቤተ ክርስቲያን በምታደርገው ቅስቀሳ የተነሳ በብዙ አገሮች ፀረ አይሁድ እንቅስቃሴ በጣም ተስፋፍቶ ነበር።
ይሁን እንጂ በ12ኛው እና በ13ኛው መቶ ዘመን በስፔይን ካቶሊኮች ዘንድ ለየት ያለ አመለካከት ነበር። አይሁዶች የክርስትናን እምነት እስካልነኩ ድረስ የሃይማኖት ነፃነት የተፈቀደላቸው ሲሆን ሌላው ቀርቶ በንጉሡ ቤተ መንግሥት ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸው ነበር። ሆኖም እንዲህ ዓይነት መብት ካገኙ ከአንድ መቶ ዓመት ገደማ በኋላ የዶሚኒካን ቄሶች አይሁዶች በኅብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተደማጭነት ለመቀነስና ወደ ካቶሊክ እምነት እንዲለወጡ ለማድረግ አንዳንድ እርምጃዎችን ወሰዱ። ዶሚኒካኖች የአርጎን ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ጀምስ በይፋ ክርክር የሚደረግበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ገፋፉት፤ ዓላማቸው የአይሁድ ሃይማኖት ውድቅ መሆኑንና ሁሉም አይሁዶች ሃይማኖታቸውን መለወጥ እንደሚያስፈልጋቸው ማረጋገጥ ነበር።
በአይሁዶችና በክርስቲያኖች መካከል ክርክር ሲደረግ ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አልነበረም። በ1240 በፈረንሳይ ፓሪስ ውስጥ አንድ ይፋዊ ክርክር ተደርጎ ነበር። ክርክሩ አይሁዶች እንደ ቅዱስ አድርገው የሚመለከቱትን የታልሙድ መጽሐፍ ለማጣጣል የታለመ ነበር። ሆኖም በክርክሩ የተሳተፉት አይሁዳውያን እንደልብ ሐሳባቸውን የመግለጽ ነፃነት አልተሰጣቸውም። ቤተ ክርስቲያን በክርክሩ መርታቷን ከገለጸች በኋላ በጣም ብዙ የታልሙድ መጽሐፍ ቅጂ በአደባባይ ተቃጠለ።
የተለያዩ አመለካከቶችን እምብዛም የማይቃወመው የአርጎኑ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ጀምስ እንዲህ ዓይነቱን የፌዝ ክርክር የሚቀበል ሰው አልነበረም። ዶሚኒካኖች ይህን ስለተገነዘቡ ሌላ መንገድ ቀየሱ። “ዶሚኒካኖች እንደ ፓሪሱ በፌዝ ሳይሆን በአክብሮትና በማግባባት መልክ” አይሁዶችን ለክርክር እንደ ጋበዙ ኪያም ማኮቢ ጁዳይዝም ኦን ትራያል በተባለው መጽሐፋቸው ላይ አስፍረዋል። ዶሚኒካኖች ወደ ካቶሊክ ሃይማኖት ተለውጦ የዶሚኒካን ቄስ የሆነውን አይሁዳዊ ፓብሎ ክርስቲያኒን ዋና ወኪላቸው አድርገው አቀረቡ። ፓብሎ ክርስቲያኒ ስለ ታልሙድና ረቢዎች ስለጻፏቸው ጽሑፎች ባለው እውቀት ተጠቅመው በክርክሩ መርታት እንደሚችሉ እርግጠኞች ነበሩ።
ናክማንዲዝ ለምን ተመረጠ?
በስፔይን ውስጥ ለአይሁዶች ሊከራከር የሚችል መንፈሳዊ ብቃት ያለው የታወቀ ሰው ሞሰስ ቤን ናክማን ወይም ናክማንዲዝ ብቻ ነበር።a በ1194 ገደማ በሄሮና ከተማ የተወለደው ናክማንዲዝ ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለ ራሱን የመጽሐፍ ቅዱስና የታልሙድ ምሁር አድርጎ አሳወቀ። በ30 ዓመቱ አብዛኛውን የታልሙድ መጽሐፍ አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ የጻፈ ሲሆን ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ በአይሁድ ኅብረተሰብ መካከል የመከፋፈል አዝማሚያ እንዲፈጠር አድርገው በነበሩት የማይሞኒደስ ጽሑፎች ላይ የተነሳውን ውዝግብ ለማብረድ የግንባር ቀደምትነት ሚና የተጫወተው እሱ ነበር።b ናክማንዲዝ በዘመኑ ከነበሩት ሁሉ ታላቅ አይሁዳዊ የመጽሐፍ ቅዱስና የታልሙድ ምሁር እንደነበረ ይገመታል፤ በዚያ ወቅት በአይሁድ እምነት ውስጥ ከማይሞኒደስ ቀጥሎ ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው ሰው ሳይሆን አይቀርም።
ናክማንዲዝ በካታሉኒያ በሚገኘው የአይሁድ ኅብረተሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው ሰው ነበር፤ ሌላው ቀርቶ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ጀምስ እንኳ በርካታ መንግሥታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ አማክሮታል። ከፍተኛ የማሰብ ችሎታው በአይሁድም ሆነ በአሕዛብ ዘንድ አክብሮትን አትርፎለታል። ዶሚኒካኖች አይሁዶችን በሚገባ ለማዋረድ የታወቀው የአይሁዶች ረቢ ለክርክሩ መቅረብ እንዳለበት ተሰምቷቸው ነበር።
ዶሚኒካኖች የአድሎአዊነት ዝንባሌ እንደሚኖራቸው ስለተረዳ ናክማንዲዝ ክርክሩ እንዲደረግ ስምምነት ላይ ለመድረስ አመንትቶ ነበር። ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች መልስ መስጠት እንጂ ምንም ዓይነት ጥያቄ መጠየቅ አይችልም ነበር። ሆኖም ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች መልስ በሚሰጥበት ጊዜ እንደልቡ መናገር እንዲፈቀድለት በመጠየቅ ንጉሡ ያቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ። ንጉሥ ጄምስ ቀዳማዊ በዚህ ተስማማ። በመካከለኛው ዘመን በጠቅላላ እንዲህ ዓይነቱ አንጻራዊ የመናገር ነፃነት ከዚያ ቀደም ያልነበረ ከዚያም በኋላ ያልተደገመ መሆኑ ንጉሡ ለናክማንዲዝ የነበረውን ከፍተኛ ግምት የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው። ያም ሆኖ ግን ናክማንዲዝ ስጋት ነበረበት። በክርክሩ ላይ የከረረ ጥላቻ እንዳንጸባረቀ ተደርጎ ከታየ ለእሱም ሆነ ለአይሁድ ማኅበረሰብ አደገኛ መዘዝ ያስከትላል። በማንኛውም ጊዜ ዓመፅ ሊፈነዳ ይችላል።
የናክማንዲዝ እና የፓብሎ ክርስቲያኒ ክርክር
ክርክሩ የተካሄደው ባርሴሎና በሚገኘው የንጉሡ ቤተ መንግሥት ውስጥ ነበር። ክርክሩ አራት መድረክ የፈጀ ሲሆን ይኸውም ሐምሌ 20, 23, 26 እና 27, 1263 ተካሂዶ ነበር። እያንዳንዱን የክርክር መድረክ በሊቀ መንበርነት የመራው ራሱ ንጉሡ ከመሆኑም በተጨማሪ የተለያዩ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ባለሥልጣናት እንዲሁም በዚያ የሚኖሩ የአይሁድ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተው ነበር።
ቤተ ክርስቲያን የክርክሩ ውጤት ምን እንደሚሆን አልተጠራጠረችም ነበር። ዶሚኒካኖች ባወጡት ይፋዊ መግለጫ ላይ የክርክሩ ዓላማ ‘እምነታቸው አንድ አጠራጣሪ ነገር ኖሮት በዚያ ጉዳይ ላይ ለመከራከር ሳይሆን የአይሁዶችን ስሕተት ለማስወገድና ብዙ አይሁዶች በእምነታቸው ላይ ያላቸውን ትምክህት እንዲያጡ ለማድረግ’ እንደሆነ ገልጸው ነበር።
ናክማንዲዝ ዕድሜው 70 ዓመት ገደማ ቢሆንም ክርክሩ መሠረታዊ በሆኑት ጉዳዮች ላይ ብቻ እንዲያተኩር ለማድረግ በመጣሩ የማሰብ ችሎታው ምን ያህል ንቁ እንደነበረ አሳይቷል። እንዲህ ሲል ጀመረ:- “[ቀደም ሲል] በአሕዛብና በአይሁዶች መካከል የተደረጉት ክርክሮች መሠረታዊ የእምነት መመሪያን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን የሃይማኖታዊ በዓሎችን የተለያየ ገጽታ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበሩ። ሆኖም እኔ በዚህ የንጉሡ ችሎት ፊት መከራከር የምፈልገው የሙግቱ ዋነኛ መንስኤ በሆነው ነገር ላይ ብቻ ነው።” ከዚያም ክርክሩ መሲሑ መጥቷል ወይስ አልመጣም፣ አምላክ ነው ወይስ ሰው እና እውነተኛውን ሕግ የያዙት አይሁዶች ናቸው ወይስ ክርስቲያኖች በሚሉት ነጥቦች ላይ ብቻ እንዲያተኩር ስምምነት ላይ ተደረሰ።
ፓብሎ ክርስቲያኒ ክርክሩን ሲጀምር መሲሑ እንደመጣ ከታልሙድ መጽሐፍ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚችል ተናገረ። ናክማንዲዝ ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ ታልሙድን የተቀበሉት ረቢዎች ለምን ኢየሱስን አልተቀበሉትም? ሲል በንዴት መለሰ። ክርስቲያኒ ግልጽ የሆኑ አሳማኝ ቅዱስ ጽሑፋዊ ነጥቦችን ከመጥቀስ ይልቅ ድፍንፍን ካለው የረቢዎች ጽሑፍ በተደጋጋሚ ይጠቅስ ነበር። ናክማንዲዝ የተጠቀሱት ሐሳቦች ከነጥቡ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው በማስረዳት አንድ በአንድ ውድቅ አደረጋቸው። ናክማንዲዝ እነዚህን ጽሑፎች ዕድሜ ልኩን ስላጠናቸው በክርክሩ በችሎታው ልቆ መታየቱ አያስገርምም። ክርስቲያኒ ከቅዱሳን ጽሑፎች በሚጠቅስበትም ጊዜ እንኳ የሚያቀርባቸው የመከራከሪያ ነጥቦች በቀላሉ የሚፈርሱ ነበሩ።
ናክማንዲዝ ለሚቀርብለት ጥያቄ መልስ ከመስጠት በስተቀር ሌላ እንዳይናገር የተከለከለ ቢሆንም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እምነት በአይሁዶችም ሆነ በሌሎች አስተዋይ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያጣበትን ምክንያት የሚያሳይ ጠንካራ የሆነ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ችሏል። የሥላሴን ትምህርት በተመለከተ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የሰማይና የምድር ፈጣሪ . . . ከአንዲት አይሁዳዊት ሴት ተወልዶ . . . በጠላቶቹ እጅ አልፎ ከተሰጠ በኋላ . . . ተገደለ ብሎ ለማመን ማንኛውም አይሁዳዊ ወይም ሌላ ሰው አእምሮው አይፈቅድለትም።” ናክማንዲዝ “ይህን እናንተ የምታምኑት፣ የእምነታችሁ ዋና መሠረት የሆነው ነገር [ትክክለኛ] የሆነ አስተሳሰብ ያለው ሰው አይቀበለውም” በማለት ቁልጭ ባለ አነጋገር ገልጿል።
ናክማንዲዝ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይቀር አይሁዳውያን ኢየሱስ መሲሑ ይሆንን የሚል ጥርጣሬ እንኳ እንዳያድርባቸው ያደረገውን ምክንያት ሲጠቅስ ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለተዘፈቀችበት የደም አፍሳሽነት ወንጀል ጎላ አድርጎ ተናግሯል። እንዲህ አለ:- “ነቢዩ በመሲሑ ዘመን . . . ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም በማለት ገልጿል። ከናዝራዊው ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መላው ዓለም በዓመፅና በዝርፊያ ተሞልቷል። [እንዲያውም] ክርስቲያኖች ከሌላው ሕዝብ የበለጠ ደም ያፈሳሉ፤ በተጨማሪም አኗኗራቸው ጨርሶ ከሥነ ምግባር ውጭ ነው። ጌታዬ ንጉሥ ሆይ ከእንግዲ ወዲህ ጦርነት የማይማሩ ከሆነ . . . ለእርስዎም ሆነ ለእነዚህ ሹማምንቶችዎ ምንኛ አስቸጋሪ ይሆናል!”— ኢሳይያስ 2:4
ከአራተኛው የክርክር መድረክ በኋላ ንጉሡ ክርክሩ እንዲያበቃ አደረገ። ለናክማንዲዝ እንዲህ አለው:- “የተሳሳተ አቋም ይዞ እንደ አንተ ጥሩ አድርጎ የተከራከረ ሰው በፍጹም አይቼ አላውቅም።” የአርጎን ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ጀምስ ናክማንዲዝ የመናገር ነፃነት እንደሚኖረውና ለደህንነቱም ጥበቃ እንደሚደረግለት በገባለት ቃል መሠረት 300 ዲናር ስጦታ ሰጥቶ ወደ ቤቱ በሰላም አሰናበተው። በሄሮና ጳጳስ ጥያቄ መሠረት ናክማንዲዝ ክርክሩን በጽሑፍ አሰፈረው።
ዶሚኒካኖች ወሳኝ ድል እንደሚቀዳጁ ሲናገሩ ስለነበረ እንደተናደዱ ግልጽ ነው። ራሱ በጽሑፍ ያሰፈረውን እንደማስረጃ በመጥቀስ ቤተ ክርስቲያንን ተሳድቧል በማለት በናክማንዲዝ ላይ ክስ መሠረቱበት። ንጉሡ ለናክማንዲዝ ጥሩ አመለካከት ማሳየቱ ቅር ስላሰኛቸው ዶሚኒካኖች ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ክሌመንት አራተኛ ይግባኝ አሉ። ናክማንዲዝ ዕድሜው ከ70 ዓመት በላይ የነበረ ቢሆንም ከስፔይን ተባረረ።c
እውነት የሚገኘው የት ነው?
ሁለቱ ወገኖች ያደረጉት ክርክር እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ለማወቅ ረድቷልን? ሁለቱም ወገኖች ቢሆኑ አንዱ የሌላውን ስሕተት ከማጉላት በስተቀር ግልጽ የሆነ የእውነት መልእክት አልተናገሩም። ናክማንዲዝ ውድቅ ያደረገው እውነተኛውን ክርስትና ሳይሆን ከኢየሱስ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት ሕዝበ ክርስትና የፈለሰፈቻቸውን እንደ ሥላሴ ያሉትን ሰው ሠራሽ ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ነው። ናክማንዲዝ ጎላ አድርጎ የገለጸው የሕዝበ ክርስትና የረከሰ ባሕርይና ከፍተኛ የደም ማፍሰስ ተግባር ታሪክም መዝግቦ ያስቀመጠው ሐቅ ነው።
ከዚህ አኳያ ሲታይ ናክማንዲዝም ሆነ ሌሎች አይሁዶች ሕዝበ ክርስትናን በመደገፍ በቀረቡት የመከራከሪያ ነጥቦች ሳይረቱ የቀሩት ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። ከዚህ በተጨማሪ ፓብሎ ክርስቲያኒ ያቀርባቸው የነበሩት የመከራከሪያ ነጥቦች በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሚገኙ ግልጽ በሆኑ አሳማኝ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረቱ ሳይሆኑ አለቦታቸው በሚጠቀሱ የረቢ ጽሑፎች ላይ ነበር።
ናክማንዲዝ እውነተኛውን ክርስትና በፍጹም ውድቅ አላደረገም። በእሱ ዘመን የኢየሱስ ትምህርት እውነተኛ ብርሃንና የመሲሕነቱ ማስረጃዎች በሐሰት ክርስቲያኖች ተጋርዶ ነበር። እንደዚህ ዓይነት የክህደት ትምህርት እንደሚመጣ ኢየሱስና ሐዋርያቱ ትንቢት ተናግረው ነበር።— ማቴዎስ 7:21-23፤ 13:24-30, 37-43፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1-3፤ 2 ጴጥሮስ 2:1, 2
ሆኖም ዛሬ እውነተኛው ሃይማኖት በግል ተለይቶ ሊታወቅ ይችላል። እውነተኛ ተከታዮቹን በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። . . . እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፣ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል።” (ማቴዎስ 7:16, 17) በዚህ መሠረት ትክክለኛውን ሃይማኖት ለይታችሁ ለማወቅ ጥረት እንድታደርጉ ግብዣ እናቀርብላችኋለን። በዚህ ረገድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃዎችን በትክክል ለመመርመር የይሖዋ ምሥክሮች እንዲረዱህ አድርግ። እንዲህ ካደረግህ ከመሲሑና ከአገዛዙ ጋር በተያያዘ አምላክ የሰጣቸውን ተስፋዎች ትክክለኛ ትርጉም ትማራለህ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ብዙ አይሁዶች ናክማንዲዝን “ራባይ ሞሰስ ቤን ናክማን” ከሚሉት የዕብራይስጥ ቃላት የመጀመሪያዎቹን ፊደላት በመውሰድና በማገጣጠም “ራምባን” ብለው ይጠሩታል።
b መጋቢት 1, 1995 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 20-3 “ማይሞኒደስ፣ የአይሁድን እምነት መልሶ ያዋቀረው ሰው” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c በ1267 ናክማንዲዝ አሁን እስራኤል ተብላ ወደ ምትጠራው አገር ሄደ። በሕይወቱ የመጨረሻ ዓመታት ብዙ ነገሮችን አከናውኗል። አይሁዶችን እንደገና ከማቋቋሙም በላይ በኢየሩሳሌም አንድ የጥናት ማዕከል መሥርቷል። የመጀመሪያዎቹን አምስት የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍት ማለትም ቶራህን የሚያብራራ ጽሑፍ ከማዘጋጀቱም በተጨማሪ ሰሜናዊ የጠረፍ ከተማ በሆነች በኤክሬ የአይሁድ ማኅበረሰብ መንፈሳዊ መሪ ሆኖ አገልግሏል፤ በ1270 በዚህች ከተማ ሞተ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ናክማንዴዝ ክርክሩን ያቀረበው በባርሴሎና ነበር
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከገጽ 19-20 ላይ የሚገኙት ሥዕላዊ መግለጫዎች:- Illustrirte Pracht - Bibel/Heilige Schrift des Alten und Neuen Testaments, nach der deutschen Uebersetzung D. Martin Luther’s