የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 5/15 ገጽ 28-31
  • ታልሙድ ምንድን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ታልሙድ ምንድን ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የታልሙድ አወቃቀር
  • የሁለት ታልሙዶች አወቃቀር
  • ታልሙድ ምን ነገር አከናውኗል?
  • ሚሽና እና ለሙሴ የተሰጠው የአምላክ ሕግ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • የቃል ሕግ በጽሑፍ የሰፈረው ለምን ነበር?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ረቢ ተብሎ ሊጠራ የሚገባው ማን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
  • ቀረዓታውያንና እውነትን ለማግኘት ያደረጉት ፍለጋ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 5/15 ገጽ 28-31

ታልሙድ ምንድን ነው?

“ታልሙድ በየትኛውም የታሪክ ዘመን ከተሠሩት ሁሉ የሚበልጥ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ መሆኑ ምንም አያጠያይቅም።”​—⁠ዘ ዩኒቨርሳል ጁዊሽ ኢንሳይክሎፔድያ

“[ታልሙድ] የሰው ልጅ ካፈራቸው ታላላቅ የምሁራን ሥራዎች አንዱ ነው፤ እጅግ ውስብስብ፣ ጥልቅ ትርጉም ያዘለና ረቂቅ ከመሆኑ የተነሣ ከፍተኛ ማስተዋል ያላቸውን ሰዎች አእምሮ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ ለሚበልጡ ዓመታት በሥራ ያስጠመደ ነው።”​—⁠ጄኮብ ኖይስነር፣ አይሁዳዊ ምሁርና ደራሲ

“ታልሙድ የአይሁዳውያንን ሕይወት መንፈሳዊና ምሁራዊ መዋቅር ደግፎ ያቆመ [የአይሁድ እምነት] ምሰሶ ነው።”​—⁠ኤዲን ስታይንሳልትስ፣ የታልሙድ ምሁርና ረቢ

ታልሙድ ለብዙ መቶ ዘመናት በአይሁዳውያን ሕይወት ላይ ይህ ነው የማይባል ተጽእኖ አሳድሮ እንደኖረ ምንም አያጠያይቅም። ከላይ የተገለጹትን ዓይነት ውዳሴዎች ይጉረፉለት እንጂ በአንጻሩ ደግሞ “የጨለማና የግራ መጋባት ባሕር” ተብሎ ተነቅፏል። የተናቀ የዲያብሎስ ሥራ ተብሎም ተወግዟል። በሊቀ ጳጳሳት ትእዛዝ በተደጋጋሚ ጊዜ ሳንሱር እንዲደረግ፣ እንዲወረስ አልፎ ተርፎም በአውሮፓ የሕዝብ አደባባዮች ተቆልሎ በእሳት እንዲቃጠል ተደርጓል።

ይህን ያህል ውዝግብ ያስነሣው ይህ ሥራ በእርግጥ ምንድን ነው? ታልሙድን ከሌሎች የአይሁዳውያን ጽሑፎች ልዩ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? የተጻፈው ለምን ነበር? በአይሁድ እምነት ላይ ይህን ያህል ተጽዕኖ ለማሳደር የበቃውስ እንዴት ነው? ከአይሁዳውያኑ ውጭ ላለው ዓለም ትርጉም አለውን?

በኢየሩሳሌም የነበረው ቤተ መቅደስ በ70 እዘአ ከጠፋ በኋላ በነበሩት 150 ዓመታት በመላዋ እስራ​ኤል የሚገኙት የረቢ ጠቢ​ባን የትምህርት ተቋማት የአይሁዳውያኑ ልማድ ተጠብቆ እንዲቆይ የሚያስችል አንድ አዲስ መሠረት ለመጣል በመጣደፍ ላይ ነበሩ። በቃል ሕጋቸው ውስጥ በተካተቱት የተለያዩ ወጎች ላይ ክርክር በማድረግ አንድ ላይ አሰባስበዋቸዋል። ይህን መሠረት አድርገው በመነሣት ለአይሁድ እምነት አዳዲስ ገደቦችንና የብቃት መለኪያዎችን ያወጡ ሲሆን እነዚህም ቤተ መቅደስ ሳይኖር በዕለት ተዕለት ሕይወት ቅዱስ ሆኖ ለመኖር የሚያስችሉ መመሪያዎች ሆነው አገልግለዋል። ይህ አዲስ መንፈሳዊ መዋቅር በሦስተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጀመሪያ ላይ በጁዳ ሃ-ናሲ በተጠናቀረው የሚሽና መጽሐፍ ውስጥ ተዘርዝሮ ይገኛል።a

ሚሽና መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ ማስረጃ ሳይፈልግ ራሱን ችሎ የቆመ መጽሐፍ ነው። ማብራሪያ የሚሰጥበት መንገድና የዕብራይስጥ ቋንቋው ዘይቤ ሳይቀር ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የተለየ ነው። በሚሽና ውስጥ ተጠቅሰው የሚገኙት ረቢዎቹ የደረሱባቸው ውሳኔዎች በየትኛውም ቦታ የሚኖሩትን አይሁዳውያን ሕይወት የሚነኩ ናቸው። በመሆኑም ጄኮብ ኖይስነር እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ሚሽና የእስራኤልን ሕገ መንግሥት አስገኝቷል። . . . ከሕጎቹ ጋር ተስማምቶ መኖርን የሚጠይቅ ነበር።”

ይሁን እንጂ በሚሽና ውስጥ ተጠቅሶ የሚገኘው የጠቢባኑ ሐሳብ ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር የሚተካከል ነውን የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ቢኖሩስ? በሚሽና ውስጥ የሚገኘው የታናይሞች (የቃሉ ሕግ አስተማሪዎች) ትምህርት ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ፍጹም ስምምነት እንዳለው ማስረዳት ይጠበቅባቸው ነበር። ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት ያስፈልግ ነበር። ሚሽናን በማብራራትና ትክክል ነው የሚያሰኙ ማስረጃዎችን በማቅረብ ሙሴ በሲና ተራራ ከተቀበለው ሕግ የመነጨ እንደሆነ ማረጋገጥ እንደሚጠበቅባቸው ተሰምቷቸው ነበር። ረቢዎች የቃሉ ሕግም ሆነ በጽሑፍ የሠፈረው ሕግ ዓላማቸውና መንፈሳቸው አንድ እንደሆነ የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለባቸው ተሰምቷቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ሚሽና ጭራሽ በአይሁድ እምነት እንደ መጨረሻ ባለ ሥልጣን ሆኖ መጠቀሱ ቀረና ለሃይማኖታዊ ውይይቶችና ክርክሮች አዲስ መሠረት ሆነ።

የታልሙድ አወቃቀር

ይህን ተፈታታኝ ሥራ የተጋፈጡት ረቢዎች አሞሬይም በመባል የሚታወቁ ሲሆን የሚሽና “ተርጓሚዎች” ወይም “ተንታኞች” ማለት ነው። እያንዳንዱ የትምህርት ተቋም አንድ እውቅ ረቢ ይኖረዋል። ጥቂት ምሁራንና ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ ውይይት ያካሂዳሉ። ይሁን እንጂ ከሁሉ የላቀ ግምት የሚሰጣቸው ውይይቶች የሚካሄዱት በዓመት ሁለት ጊዜ ይኸውም የእርሻ ሥራ በሚቀንስባቸው የአዳርና የኤሉል ወራት ሲሆን በዚህ ጊዜ በመቶ ብሎም በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሊገኙ ይችላሉ።

ኤዲን ስታይንሳልትስ እንዲህ ሲሉ አስረድተዋል:- “የተቋሙ አለቃ ወንበር ላይ ወይም ልዩ በሆነ ምንጣፍ ላይ ተቀምጦ ይመራል። ከእርሱ ፊት ለፊት በመጀመሪያው መደዳ ላይ ደግሞ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ምሁራን፣ የሥራ ባልደረቦቹ ወይም ጎበዝ ተማሪዎች ይቀመጡና ከእነርሱ በኋላ የተቀሩት ምሁራን ይቀመጣሉ። . . . የአቀማመጡ ሥርዓት እንደየደረጃቸው [እያንዳንዳቸው እንደሚሰጣቸው ግምት] በጥንቃቄ የሚደረግ ነው።” አንድ የሚሽና ክፍል ይጠቀሳል። ከዚያም ይህ ሐሳብ ታናይሞች ካሰባሰቡት ነገር ግን ሚሽና ውስጥ ካልገባ ተመሳሳይ ወይም ተጨማሪ ሐሳብ ጋር ይነጻጸራል። የግምገማው ሂደት ይጀመራል። በትምህርቶቹ መካከል ያለውን ውስጣዊ ስምምነት ለማግኘት ጥያቄዎች ይሰነዘራሉ፣ ቅራኔዎች ይገመገማሉ። የረቢዎቹን ትምህርት የሚደግፉ ጥቅሶች ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ለማግኘት ጥረት ይደረጋል።

እነዚህ ውይይቶች በሥርዓት የተደራጁ ቢሆኑም እንኳ አንዳንድ ጊዜ የተጋጋሉና ጫጫታ የሞላባቸው ይሆናሉ። በታልሙድ ውስጥ የተጠቀሱ አንድ ጠቢብ ስለሁኔታው ሲገልጹ በክርክሩ ወቅት ረቢዎቹ ከአፋቸው ‘እሳትን እንደሚተፉ’ አድርገው ተናግረዋል። (ሃሊን 137ለ፣ የባቢሎናውያን ታልሙድ) ስታይንሳልትስ ሂደቱን በሚመለከት እንዲህ ብለዋል:- “የተቋሙ አለቃ ወይም ንግግሩን የሚሰጠው ረቢ ችግሮቹን አስመልክቶ የራሱን ትርጓሜ ይናገራል። ብዙውን ጊዜ ከአድማጮች መካከል የሚኖሩት ምሁራን በሌሎች ጽሑፎች፣ በሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ሐሳብ በመመርኮዝ ወይም ራሳቸው ከደረሱበት ምክንያታዊ መደምደሚያ በመነሳት በጥያቄ ያዋክቡታል። አንዳንድ ጊዜ ክርክሩ፣ ለተነሳው ጥያቄ የማያሻማና ቅልብጭ ያለ መልስ የሚሰጥ እጥር ምጥን ያለ ይሆናል። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ሌሎች ምሁራን አማራጭ መፍትሔዎችን ያቀርቡና መጠነ ሰፊ ክርክር ይካሄዳል።” በዚያ የተገኙ ሁሉ በውይይቱ የመካፈል ነጻነት ነበራቸው። በዚያ ውይይት ወቅት ግልጽ የተደረጉት ጉዳዮች በሌሎች ምሁራን እንዲገመገሙ ወደ ሌሎች ተቋማት ይላካሉ።

ይሁን እንጂ እነዚህ ውይይቶች እንዲሁ ማብቂያ የሌላቸው ሕግ ነክ ክርክሮች ብቻ አልነበሩም። ከአይሁዳውያን መንፈሳዊ ሕይወት ጋር ግንኙነት ያላቸው ሕጋዊ ደንቦችና ሥርዓቶች ሃላካህ በመባል ይታወቃሉ። ይህ መጠሪያ የተገኘው “መንገድ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል ሲሆን ‘አንድ ሰው ሊመላለስበት የሚገባውን የሕይወት ጎዳና’ የሚያመለክት ትርጉም አለው። ከዚህ ውጭ ያሉት ጉዳዮች በሙሉ ማለትም ስለ ረቢዎችና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች፣ ብልህ አባባሎች እንዲሁም የእምነትና የፍልስፍና ጽንሰ ሐሳቦች ሃጋዳህ ተብለው ይጠራሉ፤ ይህም “መተረክ” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። ረቢዎች ክርክር በሚያካሂዱበት ወቅት ከሃላካህም ከሃጋዳህም እየጠቀሱ ይወያዩ ነበር።

ዘ ወርልድ ኦቭ ዘ ታልሙድ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ ሞሪስ አድለር እንዲህ ብለዋል:- “አንድ ብልህ የሆነ አስተማሪ በጣም የተንዛዛና አስቸጋሪ የሆነውን ሕግ ነክ ክርክር ቀለል ወዳለና ይበልጥ ገንቢ ወደሆነ ውይይት ይለውጠዋል። . . . በመሆኑም አፈታሪክና እውነተኛ ታሪክ፣ የዘመኑ ሳይንስና ትውፊት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያዎችና የሰዎች ታሪኮች፣ ድርሳናትና ሃይማኖታዊ ፍልስፍናዎች አንድ ላይ ተጣምረው እናገኛለን። ለተቋማቱ አሠራር እንግዳ ለሆነ ሰው፣ ይህ ምንም ቅንጅት የሌለው የመረጃ ጥርቅም መስሎ ሊታየው ይችላል።” በተቋማቱ ውስጥ ያሉት ምሁራን ከአንድ ርዕስ ወደሌላው የመዝለሉን ጉዳይ በዓላማ የተደረገ እንደሆነና ከሚወያዩበት ነጥብ ጋር ተዛምዶ እንዳለው አድርገው ይረዱታል። ሃላካህና ሃጋዳህ በረቢዎች የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሚገነባው አዲስ መዋቅር የግንባታ መሣሪያዎች ነበሩ።

የሁለት ታልሙዶች አወቃቀር

በመጨረሻ በፍልስጤም ምድር የነበረው የረቢዎች ዋነኛ ማዕከል ወደ ጥብርያዶስ ተዛወረ። ሌሎች ጉልህ ሥፍራ ያላቸው ተቋማት በሴፎረስ፣ በቂሳርያና በሊዳ ይገኙ ነበር። ይሁን እንጂ እያሽቆለቆለ የሄደው ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ ፋታ የለሹ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዲሁም በመጨረሻ ከሃዲዋ ክርስትና ያሳደረችው ተጽእኖና የቆሰቆሰችው ተቃውሞ በምሥራቅ ወደምትገኘውና የአይሁድ ሕዝብ መናኸሪያ ወደ ሆነችው ወደ ባቢሎን በሰፊው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።

ተማሪዎች በተቋማቱ ውስጥ ከታላላቆቹ ረቢዎች ለመማር ሲሉ ከባቢሎን ወደ ፍልስጤም ለብዙ መቶ ዘመናት ሲጎርፉ ኖረዋል። ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል አንዱ አባ ቤን ኢቦ ነበር። አባ አሪካ ማለትም ረጅሙ አባ በመባልም ይታወቅ የነበረ ሲሆን የኋላ ኋላ ራብ ብቻ ተብሎ መጠራት ጀመረ። በጁዳ ሃ-ናሲ ሥር ሆኖ ጥናቱን ካካሄደ በኋላ በ219 እዘአ ወደ ባቢሎን ተመለሰ። ይህም በባቢሎን ለነበረው የአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ጉልህ መንፈሳዊ ጠቀሜታ ነበረው። ራብ፣ ሱራ በምትባልና ብዙ አይሁዳውያን በሚገኙባት ቦታ አንድ ተቋም ከፈተ፤ ይሁን እንጂ በዚህ አካባቢ የነበሩት ምሁራን በጣም ጥቂት ነበሩ። ስሙ እየገነነ በመሄዱ 1,200 የሚያክሉ መደበኛ ተማሪዎችን እንዲሁም በአይሁዳውያኑ የአዳርና የኤሉል ወራት የሚሰበሰቡ በሺህ የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎችን መሳብ ችሏል። በራብ ዘመን የነበረው ሌላው እውቅ ሰው ሳሙኤል ደግሞ በኔሃርዲያ ሌላ ተቋም ከፈተ። ሌሎችም የጎላ ግምት የሚሰጣቸው ተቋማት በፓምቤዲና ሜሆዛ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረው ነበር።

በባቢሎን ከሚገኙት ታላላቅ ምሁራን መማር የሚቻልበት አጋጣሚ ተከፍቶ ስለነበር ከዚህ በኋላ ወደ ፍልስጤም መጓዙ አስፈላጊ አልነበረም። ሚሽና ራሱን የቻለ ጽሑፍ ሆኖ መዘጋጀቱ በባቢሎን የሚገኙት ተቋማት ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ መንገድ ጠርጓል። ከዚህ በኋላ በፍልስጤምና በባቢሎን ያለው የአጠናን ዘዴ የተለያየ ቢሆንም በየጊዜው የሚደረገው ግንኙነትና የአስተማሪዎች ልውውጥ የተቋማቱ አንድነት እንዲጠበቅ አስችሏል።

ወደ አራተኛው መቶ ዘመን እዘአ መገባደጃና ወደ አምስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ሁኔታው በተለይ በፍልስጤም ምድር ለነበሩት አይሁዳውያን አስቸጋሪ ሆኖባቸው ነበር። በወቅቱ ብቅ ባለው የከሃዲዋ ክርስትና ሥልጣን አማካኝነት የተጣሉት እገዳዎችና የተነሣው የስደት ማዕበል ሳንሄድሪንም ሆነ የናሲ (የፓትሪያርኩ) ሥልጣን በ425 እዘአ ከነጭራሹ እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል። በመሆኑም በፍልስጤም የነበሩት አሞሬይሞች በተቋማቱ ውስጥ የተደረጉትን ክርክሮች ከጥፋት ለመጠበቅ ሲሉ የእነዚህን ክርክሮች ማጠቃልያ አንድ ወጥ በሆነ መንገድ ማጠናቀር ጀመሩ። በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጨረሻ ላይ በችኮላ የተሠራው ይህ የጽሑፍ ሥራ የፍልስጤም ታልሙድ በመባል ይታወቃል።b

በፍልስጤም የነበሩት ተቋማት እያሽቆለቆሉ ሲሄዱ በባቢሎን የነበሩት አሞሬይሞች ግን እጅግ መጥቀው ነበር። አባዬ እና ራባ የክርክሩን ይዘት እጅግ ውስብስብና ረቂቅ መልክ እንዲይዝ አድርገውታል። ይህም ከጊዜ በኋላ በታልሙድ ላይ ለሚደረገው ግምገማ እንደ ናሙና ሆኖ አገልግሏል። ከዚያም ቀጥሎ በሱራ የነበረው ተቋም (371-427 እዘአ) መሪ የነበረው አሺ የክርክሮቹን ማጠቃለያ ሐሳቦች እያጠናቀረ ማዘጋጀት ጀመረ። ስታይንሳልት እንዳሉት ከሆነ ይህን ያደረገው “በቃል ብቻ የተደረገው እጅግ ሰፊ ይዘት ያለው ውይይት ጭራሽ ደብዛው ይጠፋል የሚል ፍርሃት” ስላደረበት ነበር።

ይህ እጅግ ከፍተኛ መጠን ያለው ሐሳብ አንድ ሰው ወይም አንድ ትውልድ ሊያዘጋጀው የሚችለው ነገር አልነበረም። የአሞሬይሞች ዘመን በባቢሎን ያበቃው በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ቢሆንም የባቢሎናውያኑን ታልሙድ የማዘጋጀቱ የመጨረሻ ሥራ ሳቦሬይም በሚባለው ቡድን አማካኝነት እስከ ስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ ዘልቆ ነበር። ሳቦሬይሞች የሚለው ቃል “ተንታኞች” ወይም “ሐሳብ ሰጪዎች” የሚል ትርጉም ካለው የአረማይስጥ ቃል የተገኝ ነው። እነዚህ የመጨረሻ አሳታሚዎች፣ ሳይቋጩ የቀሩትን በሺህ የሚቆጠሩ ሐሳቦችን እንዲሁም ለዘመናት ረቢዎች ያደረጓቸውን ክርክሮች በማቀናበር የባቢሎናውያን ታልሙድ ከዚያ ቀደም ብለው ከተዘጋጁት የአይሁዳውያን ጽሑፎች ሁሉ የተለየ እንዲሆን ያስቻለውን መልክ ሰጥተውታል።

ታልሙድ ምን ነገር አከናውኗል?

የታልሙድ ረቢዎች የሚሽና እና የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ምንጭ አንድ ነው የሚለውን ሐሳብ ለማረጋገጥ ቆርጠው ተነሱ። ግን ለምን? ጄኮብ ኖይስነር እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል:- “ጥያቄው በሚሽና አቋም ላይ ያተኮረ ነበር። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ አንገብጋቢው ጉዳይ የጠቢቡ ተዓማኒነት ሆኖ ተገኝቷል።” የጠቢቡን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ደግሞ እያንዳንዱ የሚሽና መስመር አንዳንድ ጊዜም እያንዳንዱ ቃል ይመረመራል፣ ይፈተናል፣ ይብራራል እንዲሁም በሆነ መንገድ ስምም ሆኖ እንዲቀመጥ ይደረጋል። ኖይስነር እንዳሉት በዚህ መንገድ ረቢዎቹ “የሚሽናን አቅጣጫ ከአንዱ ወደሌላ እንዲቀያየር አድርገዋል።” ሚሽና በራሱ ምሉዕ የሆነ ሥራ ሆኖ የተዘጋጀ ቢሆንም ከዚህ በኋላ ተነጣጠለ። በዚህ ሂደት ወቅት እንደገና ተሠርቷል፣ ማለትም እንደ አዲስ ተብራርቷል።

ይህ አዲስ ሥራ ማለትም ታልሙድ የረቢዎችን ዓላማ ለማሳካት አገልግሏል። የግምገማ ሕጎችን ማውጣታቸው ሕዝቡ እንደ ረቢዎች እንዲያስብ አድርጓል። ረቢዎቹ የእኛ የአጠናንና የግምገማ ዘዴ የአምላክን አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ነው ብለው ያምናሉ። የአምላክን ምሳሌ በመከተል አእምሮን መጠቀም ነው የተባለለት በታልሙድ ላይ የሚደረገው ጥናት እንደ አምልኮ ያለ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነገር ሆኗል። ታልሙድ በቀጣዮቹ ትውልድ ዘንድ ሁሉ በዚሁ ዘዴ መገምገም ነበረበት። ውጤቱስ ምን ሆነ? ታሪክ ጸሐፊው ሴሲል ሮዝ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ታልሙድ . . . [አይሁዳውያንን] ከሌሎች የተለዩ ሆነው እንዲታዩ የሚያደርጋቸውን ባሕርይ እንዲሁም አስገራሚ ጥንካሬ ኅብረት አላብሷቸዋል። ምሁራዊ ማብራሪያው ማስተዋላቸውን ያሰፋላቸው ከመሆኑም ሌላ . . . የአእምሮ ብስለት . . . አስገኝቶላቸዋል። ታልሙድ በመካከለኛው ዘመን ለነበረው ስደት የደረሰበት አይሁዳዊ የሚሸሽበት ሌላ ዓለም . . . አገሩ ስትጠፋ የሚያርፍበት ሌላ አባት አገር ሆኖለታል።”

ታልሙድ የረቢዎችን አሳብ ለሌሎች በማስተማር ረገድ ታላቅ ተጽዕኖ እንደነበረው ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ አይሁዳዊ ለሆኑም ሆነ ላልሆኑ ሰዎች የሚቀርበው ጥያቄ በእርግጥ ታልሙድ የአምላክን አስተሳሰብ ያንጸባርቃልን? የሚል ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​11-16

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስለ ሚሽና ዕድገትና ስለ ይዘቱ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት በኅዳር 15, 1997 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ሚሽና እና ለሙሴ የተሰጠው የአምላክ ሕግ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

b የፍልስጤም ታልሙድ የኢየሩሳሌም ታልሙድ በመባልም በሰፊው ይታወቃል። ይሁን እንጂ በአብዛኛው የአሞሬይሞች ዘመን አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይገቡ ይታገዱ ስለነበር ይህ ትክክለኛ ስያሜ አይደለም።

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሁለቱ ታልሙዶች​—የሚነጻጸሩት እንዴት ነው?

“ታልሙድ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ማጥናት” ወይም “መማር” ማለት ነው። በፍልስጤም ምድርና በባቢሎን የነበሩት አሞሬይሞች ሚሽናን ለማጥናት ወይም ለመገምገም ተነሥተው ነበር። ሁለቱም ታልሙዶች (የፍልስጤሙም ሆነ የባቢሎኑ) ሥራቸው ይኸው ነበር፤ ይሁን እንጂ የሚነጻጸሩት እንዴት ነው? ጄኮብ ኖይስነር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የመጀመሪያው ታልሙድ ማስረጃዎችን ሲገመግም ሁለተኛው ደግሞ ካሁን ቀደም የቀረቡትን ሐሳቦች ይመረምራል፤ የመጀመሪያው በጉዳዩ ላይ ብቻ የተወሰነ ሲሆን ሁለተኛው ግን ከዚያ አልፎ ይሄዳል።”

የባቢሎናውያን ታልሙድ መጠነ ሰፊ ጥናት የተካሄደበትና ዝርዝር ጉዳዮችን የያዘ መሆኑ ይበልጥ ሰፊ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን ጥልቀት ያለውና የሐሳብ አደራደሩም ሆነ የግምገማው ይዘት ወደ ልብ ዘልቆ የሚገባ እንዲሆን አስችሎታል። ብዙውን ጊዜ “ታልሙድ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የባቢሎናውያኑን ታልሙድ ነው። ባለፉት መቶ ዘመናት በሰፊው የተጠናውና አስተያየት የተሰነዘረበት ታልሙድ ይህኛው ነው። እንደ ኖይስነር አባባል የፍልስጤሙ ታልሙድ “ረቂቅ የስነ ጽሑፍ ሥራ” ሲሆን የባቢሎናውያኑ ታልሙድ ግን “የምሁራን ሥራ” ነው።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ